በጁንታው መቃብር ላይ የሚገነባው ዴሞክራሲ

 ሀብታሙ ስጦታው

የትናንቱ ገመናችን

በአገራችን ኢትዮጵያ በርካታ መንግስታት ተፈራርቀዋል። ይሁን እንጂ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ረገድ ያልተሳካላት እንደሆነች አለም የሚያውቀው ሀቅ ነው። በእነዚህ መንግስታት በኩል የነበረው ልምድ እና ቅብብሎሽ የሚያመለክተው መገዳደል፣ ደም መፋሰስ እና አንዱ የመንግስት ስርዓት በሌላው ላይ ቂም እና ቁርሾ በመያዝ ለቀጣይ ትውልድ የሚተርፍ አጥፊና አገር አውዳሚ እርሾ ማቆየት ነው። በመሆኑም አዴስ የሚመሰረት መንግስትም ቢሆን በዚህ ባህል ጉዞውን ‹‹ሀ›› ይላል። ይህ አካሄድ ደግሞ መቆሚያ ሊበጅለት ካልቻለ ቀጣዩ ትውልድም ቂምና ቁርሾ እየወረሰ በተለመደው አዙሪት ውስጥ እንዴዳክር ያስገድደዋል።

አገሪቱ ረጅም ታሪክ ያላት ናት እየተባለ ሲነገር የመቆየቱን ያህል ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ለትውልድ የሚተርፍ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል በመገንባት ታሪኳ እጅጉን አልሆነላትም። ሁኔታው ከአለመታደል ባለፈ አሳዛኝ ያደርገዋል። አሁን ያለው ትውልድ ማንኛውንም ዋጋ ከፍሎ አዙሪቱን መቀየር አለበት የሚለው መሰረታዊ ሀሳብ ሁሉንም ያስማማ ጉዳይ ሆኗል። የዛሬው ትውልድ ‹‹ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ያስፈልጋታል፤ ለመጪው ትውልድ የሚተርፍ የሰለጠነ ፖለቲካ ስርዓት ይገባታል›› ብሎ በቁርጠኝነት የሚያደርገው ወቅታዊ ተጋድሎው ለስልጣን ሽሚያ ሳይሆን ለሰለጠነ የፖለቲካ ባህል እና ለዘላቂ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሊውል ይገባል፤ ያስፈልጋልም።

የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህልን በሚመለከት ያለፉት ዘመናት ታሪካችን የትውልድን ህይወት ከመንጠቅ በተጨማሪ የተደረገው ሽግግር ዴሞክራሲያዊነት የናፈቀው ከፊወዳል ወደ ከፋ አምባገነናዊ ስርዓት የዘለቀ ነበር። 1983ዓ.ም መንበረ ስልጣኑን የተቆጣጠረው ህወሓት መራሹ መንግስት የአገሪቱን ዴሞክራሲ በሕገመንግስት ቋጥሮ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ህዝቡ ዴሞክራሲ ቅንጦት እስኪመስለው ድረስ በግፍ መግደል እና የሴራ ጨዋታ መለያው ሆኖ ብዙ ዋጋ አስከፈለ።

ያለፉት 27 አመታት ብዙ መልኮች ቢኖሩትም ድምሩ ግን ዜሮ ነው። ይህ የዜሮ ድምር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዴሞክራሲያዊ እንደነበር ብዙ ቢነገርለትም መጨረሻው ሀገር ማፍረስ ሆኖ አገሪቱን ለሌላ የቤት ስራ ዳርጓት አለፈ። በእነዚህ ዓመታት የህወሓት/የጁንታው/ አመራሮች ስለዴሞክራሲ በመገናኛ ብዙሀን ‹‹በመልካም ግንባታ ላይ ነን›› ሲሉ ነግረውናል፤ በሕገ መንግስቱም አስፍረዋል፤ በመረጧቸው ‹ምሁራን› የተለያዩ ጥናት መሰል ወረቀቶችንም ከትበዋል። የተሰራው ውሸት ጠገብ ትርክት ዴሞክራሲን ከመገንባት ይልቅ ብሄር ብሔረሰቦችን ሆድና ጀርባ ለማድረግ አቅሙ የበረታ ነው። ይህም በጣም በሚያሳዝን መልኩ ለአገር ቀጣይነት ፈተና ሆኖ ቅርቃር ውስጥ ከቷታል። ይህ እውነት ከህዝቡ የተሰወረ አይደለም።

ህወሓት /ጁንታው/ መሩ መንግስት ምን ያህል ኢ-ዴሞክራሲያዊ ነበር? የሚለው ጥያቄ መልክና ዓይነቱ ሲበዛ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ ይናገርለታል። ስርዓቱ በህይወት እያለ ዴሞክራሲያዊ ነው እየተባለ ብዙ የተወራለት ቢሆንም እውነተኛ መልኩ ግን አምባገነናዊ ሆኖ በመዝለቁ ህዝቡ አምርሮ ታግሎታል፤ ድልም ነስቷል። በተለይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹ ጫፍ የደረሱ በመሆናቸው አሁን ለተገኘው የለውጥ አየር ህዝቡ ያደረገው ተጋድሎ ትልቅ ዋጋ ከፍሎበታል።

ዛሬ ትግሉን ዳር በማድረስ የጁንታው ግብዓተ መሬት በተፈፀመ ማግስት ላይ በመሆናችን በቀጣይ የሚገነባው ዴሞክራሲ ምን መልክ ሊኖረው ይገባል? የሚለው አሁን ላለው ትውልድ የለመደውን አዙሪት  

 ለመቀልበስ መልካም እድል ፈጥሯል። አገሪቱን ከመንታ መንገድ ላይ ያወጣው የህዝብ ትግል አዴስ ለውጥ ጎዳና ላይ አድርሷታል። በመሆኑም አሁን ያለው ትውልድ ከመጠፋፋት ሴራ ወጥቶ፤ ከቂም በቀል ርቆ ዜጎች በሀሳብ የበላይነት ብቻ መንግስት የሚገነቡበት እንዴሆን በጁንታው መቃብር ላይ እውነተኛ ዴሞክራሲን የመገንባቱን የቤት ስራ ለማረጋገጥ ዜጎችን ማነጋገሩ ትክክል እንደሆነም ምሁራን ይመክራሉ።

የተዋጣለት ዴሞክራሲ

እንዴት ያለ ነው?

ዓለም በአንድ አገር ውስጥ ያለውን የዴሞክራሲ ስርዓት ደረጃ ለመለካት ያስቀመጠው የዴሞክራሲ ስርዓት /Index/ መለኪያ አለ። ይህ መለኪያ አንድ አገር የተዋጣለት ዴሞክራሲን ገንብታለች አልገነባችም? የሚለውን በሚገባ በመለካት ይታወቃል። በመሆኑም መለኪያውን በሚመለከት በተለያየ ወቅት የተለያዩ የዴሞክራሲ ስርዓት ነጥቦች ተቀምጠዋል፤ ጥቅም ላይም ውለዋል። ሆኖም ግን ዛሬ ያሉትን የተለያዩ ነጥቦችን በሶስት ሰፋፊ ክፍሎች እንዴጠቃለሉ መደረጉን የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂብእዜር ፈረደ የዴሞክራሲ መለኪያዎች በሶስት ይከፈላሉ የሚለውን ሀሳብ በመደገፍ ይናገራሉ። ዶክተሩ እንደሚያስረዱት ቀዳሚው ነጥብ በአገሪቱ ብዝሀነት/diversity/ እንዴት ተስተናግዷል/ ይስተናገዳል? የሚለው ነው። ሁለተኛው የሲቪል ዜጎች ነፃነት /civil liberty/ ያለበት ሁኔታ ምን መልክ ይዟል? ሶስተኛው የፖለቲካ ባህል /political culture/ መሆናቸውን ያስረዳሉ። እነዚህ ክፍሎች የየራሳቸው ሰፋፊ ዝርዝር ነጥቦች እንዳሏቸውም በመጠቆም።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ፍልስፍና ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አስምሬ በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ አንድ አገር የተዋጣለት ዴሞክራሲ ገንብታለች ሲባል መሰረታዊ ከሆኑ ጉዳዮች ውስጥ አገሪቱ ህዝቦቿን የስልጣን ባለቤት አድርጋለች ወይ? ብለህ ስትጠይቅ የምታገኘው መልስ ይናገራል ሲሉ ይሞግታሉ። በዚህም ህዝብ የመረጠውን ይሾማል፤ ያወርዳል የሚለውን መርህ ያስገነዝባል። ሁለተኛ ጉዳይ አገራቱ የህግ የበላይነት የተረጋገጠባቸው ሊሆኑ ግድ ነው ባይ ናቸው። ሁሉም ዜጋ፤ የመንግስት ባለስልጣንም ሆነ ተቋማት በህግ ፊት እኩል የሚጠየቁባቸው መኖሩ የአገራቱ መገለጫ ወይም መለያ ነው። በሶስተኛነት ፍትህ እና እኩልነት የተረጋገጠባቸው ሲሆኑ በተለይ ዜጎች በአገራቸው ፍትህ ማግኘት መቻላቸው ያለብሔር፣ ሃይማኖት እና አመለካከት ልዩነት ተግባራዊ መሆን አለበት።

አገራት እነዚህን ጉዳዮች አሟልተው ሲገኙ የተዋጣ ዴሞክራሲን እየገነቡ ነው ብሎ በድፍረት መናገር ያስችላል። ከዚህ በተጨማሪ ፍትሃዊና ነፃ ምርጫ በተሟላ ሁኔታ እያካሄዱ የዘለቁና የቻሉ፣ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር፣ የሃሳብ፣ የአመለካከት ወይም የሃይማኖት ብዝሀነት ሰፍኖባቸው ሂደቱን በሚገባ አሟልተው የተገኙ አገራት የተሳካ ዴሞክራሲ ገንብተዋል ማለት ይቻላል ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰሩ ሃሳባቸውን ያቀርባሉ።

ዴሞክራሲያዊ ባህል ከዴሞክራ ሲያዊ ማህበረሰብ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ለዴሞክራሲ መሰረት ከሆኑ ነገሮች አንዱ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብን መመስረት ነው። ‹‹ዴሞክራሲ አለ ልንል የምንችለው ማህበረሰብ እንደ ማህበረሰብ ዴሞክራሲያዊ ሲሆን ነው፤›› በማህበረሰቡ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ባህል ሳይኖር ዴሞክራሲያዊ መንግስት ሊኖር አይችልም ይላሉ። በመሆኑም ተጨባጭ በሆኑ መለኪያዎች ስናያቸው ዴሞክራሲን እየገነቡ ነው የምንላቸው አገራት እነዚህን መርሆች አሟልተው የተገኙ ናቸው ሲሉ ይከራከራሉ።

«ሙት ዴሞክራሲያዊነት»

ከላይ ከተቀመጡት የተለያዩ መስፈርቶች አኳያ በኢትዮጵያ በተለይ ባለፉት 27 ዓመታት ዴሞክራሲያዊ መብቶች በአግባቡ ተይዘዋል? ወይስ ተረግጠዋል? ህዝቡስ የራሱን መንግስት መሰረተ ወይስ ተጭኖበት ነበር? መሰረታዊ የሚባሉ የህዝቡ ሀሳብን በነፃነት መግለፅ፣ የመደራጀት መብት ፣የህግ የበላይነት፣ የእምነት ነፃነት እና የመሳሰሉት ነገሮች በመለኪያዎቹ ልክ የአገሪቱን ዴሞክራሲ መመዘን ግድ ይላል።

ፕሮፌሰር ውሂብእዜር እንደሚገልፁት ኢት ዮጵያ በተለይ ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተጀምሮ ነበር ወይ ብሎ ለሚጠይቅ ምላሹ ዜሮ ለመሆኑ አሁን የደረስንበት ደረጃ ብቻውን አስረጂ ነው። ስርዓቱ በሶስት መሰረታዊ ምክንያቶች ከዴሞክራሲ ጋር ተጣልቶ ኖሯል፤ ሲሉ አስረጂ በማቅረብ ይሞግታሉ።

ዶክተሩ የጁንታው ቡድን ወደ ስልጣን የመጣበት መንገድ በምርጫ ሳይሆን በጦርነት በመሆኑ ዴሞክራሲ ላለመኖሩ ቀዳሚ አስረጂ አድርገው አቅርበዋል። ህወሓት ከላይ ከተጠቀሱት ሶስት ክፍሎች በተለይ ከሲቪል ነፃነቶች ጋር በቀጥታ የሚጣረሰው ባልተሟላ ሁኔታ የሚከተለው የማርክሲስት ሌሊኒስት ፍልስፍና በአገሪቱ ዴሞክራሲ አለመጀመሩ ሁለተኛው ገፊ ምክንያት ነው ሲሉ ያብራራሉ። ይህ ፍልስፍናው ሰብዓዊ መብትን ለማክበር አይፈቅድለትም፤ ይህ ደግሞ በቀጥታ ከሲቪል ነፃነቶች ጋር አጋጭቶት ዓመታትን ተሻግሯል። የሃይማኖት ነፃነትና የመደራጀት መብት ከወረቀት ላይ ወርዶ መሬት ያልነካ ለመሆኑ ብዙ እማኝ እና አስረጂ ማቅረብ እንደሚቻል አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ሶስተኛው ምክንያት ይህን ፍልስፍና ይመሩ የነበሩ ቡድኖች ይዘውት የመጡት ማህበራዊ ጉድለቶች ነው ይላሉ፤ ፕሮፌሰር ውሂብእግዜር። ቡድኑ የነበረው የስነልቦና ጉድለት ራሱን የበታች አድርጎ የሚወስድ በመሆኑ ‹‹እዋጣለሁ፤ ከስልጣን እገለላለሁ፤ አሁን ያለኝን ጥቅሞች አጣለሁ፤›› የሚል ነው፤ ይህ ደግሞ የዴሞክራሲ ስርዓት ባህሪም ባለመሆኑ በአገሪቱ ዴሞክራሲ ተጀምሮ ነበር ማለት አይቻልም ሲሉ ይከራከራሉ።

በኢትዮጵያ ትልቁ ጥያቄ የዴሞክራሲ ስርዓት ሲሆን ይህ ግን በተለያዩ ጉዳዮች እየተሸፈነ እና እየታፈነ መምጣቱ ችግሩን አክፍቶታል። ይህም በአገሪቱ ዴሞክራሲን የማዋለድ ጥያቄ አስቀርቶታል፤ አጨናግፎታልም። በዚህ ድምር ምክንያቶች ዜጎች ዴሞክራሲን የቅንጦት እስኪመስል ድረስ ምኞት ሆኖ ቀርቷል ሲሉ ያስገነዝባሉ።

ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ በበኩላቸው የጁንታው ቡድን ከዱር ጀምሮ የመጣበትን ስርዓት ስንመለከት ይከተለው የነበረው ፍልስፍና፣ በተግባር የሚናገሩትን ደምሮ ለሚያስተውለው ዴሞክራሲያዊ ስብዕና የላቸውም ሲሉ በዶክተር ውሂብእግዜር ሃሳብ ይስማማሉ። በግለሰብ ደረጃም ቢሆን አንዳቸውም የዴሞክራሲን ‹ሀሁ›› የሚያውቁ አይደሉም ባይ ናቸው። ዴሞክራሲን የማያውቅ ዴሞክራሲን ያመጣል ብሎ ማሰብ አይቻልም። መጀመሪያውኑ ፓርቲውንና ራሳቸው የሚመሩበትን ሞራል ስታይ የዴሞክራሲ መንፈስ የላቸውም። ከጅምሩ የዴሞክራሲ ፅንሰ ሀሳብ የሌላቸው በመሆኑ ዴሞክራሲን ያመጣሉ ብሎ የጠበቀ በጣም ውስን ሰው ነበር ሲሉ ያስታውሳሉ። አለመታደል ሆኖ እንጂ መሪዎች ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ቀናኢ መሆን ነበረባቸው። ቡድኑን በቁንጮነት ከመሰረቱትና ከመሩት ጀምሮ የዴሞክራሲ እሴት የሌላቸው እንደነበሩ አቋም ይዘው ይከራከራሉ።

የጁንታው ቡድን /ስርዓቱ/ ዴሞክራሲን ያመከነው ከሕገመንግስቱ ጀምሮ ነው። ሕገመንግስቱን የሚያመልኩ ቢኖሩም እንደ ሀገር ዴሞክራሲያዊ መብቶች የታሰሩት በዚሁ ሰነድ ነው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ፤ አንድ ሀገር ስርዓት የምትፈጥረው በሕገመንግስት ላይ ተመስርታ ነው። ፖሊሲም ሆነ ሕግ ብታወጣ መሰረቱ ሕገመንግስት ነው። በመሆኑም አገሪቱ ዴሞክራሲያዊ እንዳትሆን ተደርጎ የተቀረጸ ነው። በዚህ ሕገ መንግስት ሕዝቦች አብረው መኖርም አገር መገንባትም አልተቻለም፤ በመሆኑም የሚፈለገውን ዴሞክራሲ ማምጣት አይቻልም ብለዋል። የሀገሪቱ ትልቁ ነቀርሳ ሕገ መንግስቱ ነው። ከ20 እስከ 25 የሚደርሱ አንቀፆች አሉ ዴሞክራሲ በአገሪቱ እንዳይኖር ሆን ተብለው የተሰነቀሩ። ለዚህ ነው በርካታ ምሁራን በአገሪቱ ዴሞክራሲ ተጨናግፏል የሚሉት ይላሉ።

ተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂብእዜር እንዳመለከቱት፤ በአገሪቱ ያለው የፖለቲካ ባህል በሚገባ መታየት አለበት ባይ ናቸው። ‹‹ዴሞክራሲ ሳይኖር ዴሞክራሲ መገንባት አይቻልም፤ በማህበረሰቡ ውስጥ የዴሞክራሲ ባህል ከሌለ ዴሞክራሲን የመገንባቱ ሂደት አስቸጋሪ ነው›› ሲሉ ዶክተሩ የማህበረሰብ የፖለቲካ ባህል እሴት ለዴሞክራሲ

 ስርዓት ግንባታ ወሳኝነት አመልክተዋል። በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ‹ትዕግስት› ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ እሴት ነው ሲሉ በአብነት ያስቀምጣሉ። አንዳንድ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ትዕግስት የሚጠይቁ በመሆናቸው ዴሞክራሲን ለመገንባት ማህበረሰባዊ ትዕግስት ወሳኝ እሴት ነው። የሌሎች ሀሳብ ለእኛ በማይዋጥልን ወቅት የራሳችን አቋም ይኖረናል። በሌሎች ሀሳብ ባንስማማም ሀሳቡን በሀሳብ መልክ በቅንነት ተቀብሎ መቆየት ይገባል። ይህ በሀገራችን በጣም ኋላ የቀረ እሴት ነው። ይህ እሴት በማህበረሰቡ ውስጥ የነበረ ቢሆንም በጁንታው የሴራ ተግባር ሊጠፋ እንደቻለ ይናገራሉ። የአንድ ማህበረሰብ ወሳኝ የዴሞክራሲ እሴት ፍትህ እና ጤናማ የፖለቲካ ውድድር የማድረግ ባህል በመሆኑ ሊነሱ የሚገባቸው እሴቶች ናቸው።

ፍትህ በሁሉም ቦታዎች እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ይህ እሴት በእምነት ተቋማት ሳይቀር አስፈላጊ ነው። በእርግጥ ፍትህ በኢ-መደበኛ ጭምር በማህበረሰቡ ውስጥ የቆየ ቢሆንም በተሰራው ክፉ ስራ ሊመክን ችሏል። ከእነዚህ ጉዳዮች አንፃር በስርዓቱ ውስጥ የነበረው በፍትህ የአለመተማመን አባዜ ወደ ማህበረሰቡ ተጋብቶ ክፍተቱ ሰፍቶ ዛሬ ሌላ መልክ ይዟል። የነበረው ስርዓት ልዩነትን በእጅጉ የሚነዛ ስለነበር ከላይ ያነሳናቸው የዴሞክራሲ እሴቶች ከአገሪቱ ርቀው ዴሞክራሲ ለህዝቡ ከምኞት ሳያልፍ ዛሬ ላይ ደርሰናል።

‹‹ለእኔ ከማህበረሰባዊ የዴሞክራሲ ባህል ደረጃ በዘለለ ስልጣን ላይ የነበረው ስርዓት በማህበረሰቡ ውስጥ በሴቷና በማህበረሰቡ መካከል የነበረውን ግጭት ወደ ታች /decentralized/ በማድረግ ማህበረሰቡ ውስጥ ከቶታል። በተለይ ከሶስት አመታት ወዴህ ግጭቶች ማህበረሰባዊ ሆነው አንድ ህዝብ በሌላው ህዝብ ላይ እንዴነሳ፤ እንዴጋጭ የተሰራበት ነበር። ይህ የሚያመለክተው ከዴሞክራሲ ጋር የተጣላው ሀይል፣ መንግስት/ቡድን/ በመሆኑ የነበረበትን የስነልቦና ጉድለት /የበታችነት/ ማህበረሰቡ ውስጥ ማስረፁን ነው። በዚህ ሳቢያ በአገሪቱ የሚከሰቱ ግጭቶች በአጠቃላይ መንግስትና ማህበረሰብን መለየት እስካለመቻል አድርሶታል›› ሲሉ ተባባሪ ፕሮፌሰር አፅንኦት ይሰጣሉ።

ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ ዴሞክራሲ አለት ላይ ተዘርቶ የሚበቅል አይደለም ሲሉ ሀሳባቸውን ይገልፃሉ። በአንድ አገር ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። ጠንካራ የፍትህ ተቋማት፣ ጠንካራ የመገናኛ ብዙሀን፣ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊና የተማረ ማህበረሰብ የዴሞክራሲ ስርዓትን በሚገባ ለመገንባት ስራዎች ናቸው። እነዚህ ጉዳዮች በሌሉበት ዴሞክራሲ አለ አሊያም ተጀምሯል ማለት አይቻልም። ሲሉም የዶክተር ውሂብእዜርን ሀሳብ ያጠናክራሉ። በአገሪቱ እነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ተሟልተው የተገኙበት ሁኔታ ባለመኖሩ ዴሞክራሲ ያለፉት 28 ዓመታት የውሸት ነበር ሲሉ ይገልፃሉ።

ኢትዮጵያ ከላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች አሟልታ ያልተጓዘች አገር በመሆኗ ስለ ዴሞክራሲ ማውራት በእጅጉ አስቸገሪ ነው ሲሉ ያስገነዝባሉ። በመሆኑም ባለፉት ስርዓቶች ስለ ዴሞክራሲ የምናወራበት ሁኔታዎች አልነበሩም። አለት ላይ መዝራት እንደማይቻለው ሁሉ በሌለ የዴሞክራሲ መሰረት ዴሞክራሲ ብሎ መነጋገር አይቻልም። የህግ የበላይነት፣እኩልነት፣ ህዝብ የስልጣን ባለቤት ሆኖ በመረጠው መተዳደር/የህዝብ የመሾም እና የማውረድ ተግባራዊ መብት/ የፍትህ ስርዓት አፈር ድሜ የገቡበት እንጂ ነፍስ ዘርተው አልታዩም። በሁሉም የዴሞክራሲ መስፈርቶች ስትመዝነው የአገሪቱ ዴሞክራሲ ‹‹ሙት ዴሞክራሲ›› ነበር ብሎ መሰየም ይቻላል ባይ ናቸው።

የዴሞክራሲ ተቋማትን በሚገባ ስንፈትሽ ጥንካሬያ ቸውም ሆነ ውድቀታቸው በቀጥታ ከማህበረሰብ ንቃተ ህሊን ጋር ይያያዛል። ጠንካራና ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ጠንካራ የዴሞክራሲ ስርዓት የመገንባት እድሉ ሰፊ ነው። ምክንያቱም ተቋማት የማህበረሰባዊ ንቃተ ህሊና መገለጫዎች ናቸው። የዜጎች የፖለቲካ ንቃተ ህሊና በማህበረሰብ እድገት ልክ የሚጓዝና የሚቀዳ ነው። ይህ ደግሞ ማህበረሰቡ ውስጥ ያለ የዴሞክራሲ ስርዓት እሴት ነው። የዜጎች ንቃተ ህሊና ባደገ ቁጥር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው ቀና ይሆናል። ይህ በትምህርት የሚገኝ ነው እንጂ አገር ዴሞክራሲያዊ ሆኖ አይፈጠርም። ጠንካራ ተቋማት የምንፈጥረው በትምህርት በመሆኑ የነቃ ማህበረሰብ በመፍጠር ረገድ አስፈላጊ ነው።

በመሆኑም ስለ ዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ሲነሳ ያማረ ህንፃ እና ጠንካራ አመራር ማስቀመጥ ብቻውን የሚያመጣው ውጤት አይኖርም። ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት በቀጥታ የሚገናኙት ከማህበረሰብ ንቃተ ህሊና ጋር ነው። ንቃተ ህሊናው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ማህበረሰብ ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት ይገነባል። በፖለቲካል ሳይንስ ውስጥ ያለው አንድ አነጋገር አለ፤ ‹‹The people get the goverment they deserve›› ይህ ማለት ‹‹ህዝብ በልኩ የሚገባውን መንግስት ያገኛል›› ማለት ነው። የአሜሪካ ህዝብ ያለው የዴሞክራሲ ደረጃ ማለት ህዝቡ ያለው ንቃተ ህሊና ልክ ማለት ነው። የሚመራን መንግስት፣ ሕዝቡ ያለው ንቃተ ህሊና እና ተቋማቱ ከዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው ጋር መሳ ለመሳ ሆነው ይገኛሉ። በመሆኑም ንቃተ ህሊናው የዳበረ ማህበረሰብ የዴሞክራሲ ተቋማትን ከመገንባት አስቀድሞ ሊኖረን የሚገባ ወሳኝ ጉዳይ ይሆናል። የፍትህም ሆነ የትምህርት ተቋማት ግንባታ እና ዘመናዊነት ከህብረተሰብ ንቃተ ህሊና ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው።

በጁንታው መቃብር ላይ…

አሁን ያለው ትውልድ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን በሚገባው ልክ መሰረት ለማስያዝ በእጁ ያለውን ወርቅ መጠቀም እንጂ በከንቱ ማስቀረት የለበትም። በመሆኑም ይህን ስርዓት መሰረቱን ለማቆም የሚጠበቁ መሰረታዊ ነገሮች ውስጥ የተወሰኑትን ነጥቦች የሚያነሱት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ ናቸው። ቀዳሚው የቤት ስራ ሕገመንግስቱን ማሻሻል ነው። ሕገመንግስቱ የጁንታው ቡድን ሰነድ እንጂ የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ብሎ መውሰድ አይቻልም። ይህ ሰነድ እንዳይኖሩ የሚያደርግ፤ አብሮ አገር መገንባት የማያስችል፤ ፀረ- ዴሞክራሲያዊ በመሆኑ እያንዳንዷ አንቀፅ ተለቅሞ መቀየር ያለበት እንዴቀየር፤ መጨመር ያለበት ደግሞ እንዴጨመር እድሉ መመቻቸት አለበት። ይህ ሳይሆን ዴሞክራሲን ለመጀመር ማሰብ በራሱ አዳጋች ነው።

ሁለተኛው ጉዳይ ስርዓቱ ወድቋል ተቀብሯል። ሆኖም ግን ስርዓቱ ምንድን ነው? ብሎ በትኩረት ማየት ለሚገነባው ዴሞክራሲ ትልቅ ጥቅም አለው። ስርአቱ ግለሰብም ተቋምም ነው። እነዚህ ሰዎች /የጁንታው ቁንጮዎች/ ስለተወገዱ ብቻ ነገሩ አብሮ ይሞታል ማለት አይደለም። የስርዓቱ ተከታዮች በስፋት በመኖራቸው የፖለቲካ አስተሳሰቡ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው እንቅፋት በመሆኑ እንዳይመለስ ተደርጎ መዘጋት አለበት በማለት ሁለቱም ምሁራን ተመሳሳይ ምክረ ሀሳብ ያቀርባሉ።

መንግስትም ሆነ ህዝብ ይህን ስርዓት እስከመጨ ረሻው ተጨባጭ በሆነ ሁኔታ ማራገፍ አለበት። ይህ ስራ በሁሉም ክልሎች በአጠቃላይ ሊሰራ ይገባል ምክንያቱም የነበረው ስርዓት ፀረ- ዴሞክራሲያዊ ነው። በጁንታው መቃብር ላይ የሚገነባ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ በመሰረታዊነት ሊሰራው የሚገባ ቀዳሚ ስራ ፀረ- ዴሞክራሲያዊ የሆነውን አስተሳሰብ ታሪክ ከማድረግ ነው። አስተሳሰቡን ዳግም ህይወት ሊዘራ የሚያደርጉ ተቋማት ዳግም የማይመለሱበትን ሁኔታ ማስቀረት መቻል ትልቁ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው የቤት ስራ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

በሶስተኛነት የዴሞክራሲ ስርዓት ትልቁ አቅም እና መሰረት ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብን መገንባት መቻል ነው። ማህበረሰቡን ዴሞክራሲያዊ የማድረግ ጉዳይ በራሱ ውስጥ ካሉ መልካም እሴቶች ሊጀምር ይገባል። ባህላዊ የሆኑ ዴሞክራሲያዊ እሴቶቹን ማጎልበት። ከዚህ ባለፈ ማህበረሰቡን በመደበኛም ሆነ ኢ- መደበኛ በሆነ መንገድ ማስተማር እና ማሰልጠን ይቻላል። በተለይ ከእነዚህ መሰረታዊ የዴሞክራሲ ስርዓት ግብዓቶች ውስጥ የህዝብ ስልጣንን ማረጋገጥ፤ ህዝብ ይሾማል፤ ይሽራል የሚለውን ትክክለኛ አባባል ተግባራዊ ማድረግ ቀና የዴሞክራሲ መንገድን ይፈጥራል።

አንድ ማህበረሰብ ዴሞክራሲያዊ እንዴሆን በፍትህ እምነት ኖሮት ሕግ ፊት ሁሉም እኩል እንዴዳኙ መደረግ አለበት። ይህ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብን ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለመመስረት ያስችላል። የዴሞክራሲ ተቋማት ከዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ እሴቶች ስለሚቀዳ የስርዓቱን ግንባታ ምቹ እንደሚያደርገው የበርካታ አገራት ተሞክሮም ሆነ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች አመላክተዋል። በመሆኑም እንደ አንዳንድ አገራት ልምድ ማህበረሰብን ዴሞክራሲያዊ በማድረግ ረገድ የባህል አብዮት ሊያስፈልገን ይችላል። የዴሞክራሲ ስርዓቱን ስኬታማ በማድረግ ረገድ ደግሞ እንዳለፉት ዘመናት ጉዳዩን ሁሉ ለመንግስት እና ለፓርቲ መተው አይገባም። ዜጎች በሙሉ አቅማቸውና እውቀታቸው ተቀራራቢ አረዳድና ትግበራ ውስጥ ሊገቡ ይገባል ሲሉም ሃሳባቸውን አቅርበዋል።

ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት አንድ አገር እንደ አገር ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዴቀጥል የሚያስችሉ ጉዳዮች ናቸው ሲሉ ተመሳሳይ ሀሳብ የሚያቀርቡት ሁለቱ ምሁራን፤ አሜሪካን በእየ ምርጫ ዘመኗም ሆነ በአስተዳደር ጉዞዋ ዴሞክራሲያዊ ሆና እንድትቀጥል ያደረጋት ግለሰቦች አይደሉም፤ ዴሞክራሲያዊ ከሆነው ማህበረሰብ/ህዝብ የተቀዱት የዴሞክራሲ ተቋማቶቿ ናቸው ብለዋል።

እውነት ነው! አሜሪካ የማንክደው ዴሞክራሲያዊ የሆነ ማህበረሰብ አላት፤ ከዚህ ማህበረሰባዊ እሴቶች የሚቀዱ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትም መስርታለች። የትኛውም ስርዓት እና ግለሰብ ይምጣም ይሂድ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን የሚያስቀጥሉት ተቋማት እና ማህበረሰቡ አብረው ይጓዛሉ። በመሆኑም የህወሓት ጁንታ ቡድን ሄዶ የሚተካውን አዴስ ስርዓት የሚረከቡ እና በሕግ ደረጃ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ እና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት በዘላቂነት ሊኖሩን፣ሊገነቡ ግድ ይላል።

Recommended For You