ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለምን ጠላት አበዛብን?

ስሜነህ ደስታ

ዓባይ ወይም ናይል ወንዝ 6 ሺህ 700 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት የዓለም ረጅሙን ጉዞ ያደርጋል:: በዚህ ጉዞው ውስጥም በቀጥታ ወሰናቸውን አቋርጦ የሚያልፍባቸውም ሆኑ ወሰናቸውን ሣይነካ ግብር የሚከፍሉለት አነስተኛ ወንዞች ያላቸው 11 አገራት አሉት:: የሚገርመው ሁሉም አገራት ዝናውን እና ጉልበተኛነቱን ከመመሥከር ያለፈ ተጠቅመውበታል አይባልም:: በግዛቱ ውስጥ ከሚገኙት መካከል የግብጽን ያህል አቅሙን አሟጦ የተጠቀመበት አገር አይገኝም:: ከእሷ በመቀጠል ሱዳን በናይል ወንዝ ላይ የተሻለ ተጠቃሚ ናት:: ከዚያ ባለፈ 85 በመቶ የሚሆነውን የውሃ መጠን የሚመግበውን ዓባይን ከአብራኳ የምትወልደው ኢትዮጵያ በወንዙ ላይ ምንም አልተጠቀመችበትም:: ለታችኛው የተፋሰሱ አገራት ለእርሻ ሥራ የሚሆነው ለም አፈርም የሚሄደው በአብዛኛው ከዓባይ ወንዝ ነው:: ናይል እንዲያው ሥሙ ብቻ እንጂ በተለይ ለላይኛው የተፋሰሱ አባል አገራት ምንም ፋይዳ አልሠጠም:: በናይል ላይ የተገነቡት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ እንኳ ከአንድ እጅ ጣቶች ቁጥር አይበልጡም:: የላይኛው የተፋሰሱ አገራት አቅም ማነስ እና የታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት የላይኞቹን አንድም የልማት እንቅስቃሴ እንዳያከናውኑበት ተፅዕኖ ሲያደርጉ መቆየታቸው ከናይል ጋር የማይመጣጠን ተግባር እንዲያከናውኑ አድርጐ ቆይቷል::

ወደ ምድረ ግብጽ ቁልቁል ከሚፈሰው የናይል ወራጅ ውሃ 85 በመቶው ከኢትዮጵያ ነው። ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ ሽቅብ ከሚፈሱት ክፋቶች 85 በመቶው ከግብጽ ሳይሆኑ አይቀሩም። ብዙዎቹ ውጭ-ወለድ የኢትዮጵያ ችግሮች ምንጫቸው ቢጠና ግብጽ ከመሆን አይዘልም። ለምሳሌ የአፍሪካ ቀንድ ለብዙ ዘመናት እርጋታና ሰላም የራቀው ቀጣና ሆኖ መዝለቁ። የኢትዮጵያ በዓላትና የማይሰራባቸው ቀናት መብዛታቸው ራሱ የግብጽ ተንኮል ነው በማለት አስረጅ ጠቅሰው የሚከራከሩ ምሁራን አሉ። በግብጾችም ቢሆን አይፈረድም። እርግጥ ዘላቂ አገራዊ ጥቅም ዋስትና እሚያገኘው ከወዳጅነትና ከፍትህ ነው።‹ልክ ናቸው አይደሉም›ን ትተን ግን ኢትዮጵያን አቆርቁዞና ቀስፎ መያዝ ዋነኛ የህልውናቸው ዋስትና አድርገው ስለቆጠሩት በዚያ አቅጣጫ በሙሉ አቅማቸው ቢረባረቡ እሚገርም አይሆንም። የግብጽ ጥፍሮችን ከአንገታችን ማላቀቅ ደግሞ ለእኛ የህልውናና የሞት ሽረት ጉዳይ ይሆናል።

ኢትዮጵያ የራሴን የተፈጥሮ ሀብት፣ የአባይን ወንዝ ውሃ በመጠቀም የማልማት መሠረታዊ መብት አለኝ፤ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ከውሃው ማግኘት ያለባቸውን ድርሻ ያገኛሉ።የግድቡ መሰራት በውሃው መጠን ላይ የሚያደርሰው ችግር የለም፤ ግድቡ የአካባቢውንም፤ ሀገሮች ተጠቃሚ ያደርጋል የሚለውን አቋሟን በተደጋጋሚ ገልጻለች።

ኢትዮጵያ የዓባይን ውሃ ገድባ ፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ ለመጠቀም በምታደርገው እንቅስቃሴ ከውስጥም ከውጭም አካላት እንከኖችና ፈተናዎች ለምን ይበዙባታል? መፍትሔውስ ምን መሆን ይገባዋል? የሚሉትንና ተዛማጅ ጉዳዮች በመያዝ በአ.አ.ዩ. የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ ከሆኑት ከፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ፣ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ቅርስ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር ከሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ በከሬ እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት ዶክተር አረጋዊ በርሄ ጋር ቆይታ አድርገናል።

የዓባይ ተፋሰስ የውሃ ገብነትና የበርሃማነት ሁለት ተቃራኒ ጫፎችን በአንድ የሚያስተሳስር ቢሆንም፣ ሁለቱን ጫፎች በአንድ የሚያዋህድና የኢኮኖሚ ጥቅም ተጋሪ ማድረግ አዳጋች ሆኖ ለዘመናት ቆይቷል።የተፈጥሮ ሀብቱ የጋራ ባለቤትነትን ባረጋገጠ መንገድ፣ በፍትሐዊነት ሊጋሩት የሚገባ የውሃ ሀብት መሆን ሲገባው የአንድ ወገን ተጠቃሚነት እንዲቀጥል የሚፈልጉ አካላት አሁንም አሉ።

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቱ አመንጪና ባለቤት ብትሆንም ይህንን ሀብቷን ሳትጠቀምበት ቆይታለች።የተለያዩ የኢትዮጵያ መንግሥታትና ነገሥታት ተፋሰሱን የማልማት ጽኑ ፍላጐታቸውን በሚገልጹበት ወቅት ዘንግተውት የማያውቁት ጽኑ የሆነው አቋም፣ በተፋሰሱ ተጋሪ ሀገር ሕዝቦች ላይ ጉዳት ያለማድረስ መርሆ እንደሆነ ታሪካዊ ማስረጃዎች ያመላክታሉ።

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ቅርስ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ በከሬ እንደሚሉት የዓባይ ወንዝ ታሪክ 30 ሚሊዮን ዓመታት ታሪክ ያለውና ግብጽ፣ አክሱም እና ኑቢያ ሥልጣኔ ያበረከቱበት ነው።እነዚህ ሥልጣኔዎች አንዱ ከአንዱ ጋር በንግድ ዕርስ በዕርስ በጥቅም የተሳሰሩና የትብብር መንፈስ ያለው ታሪክ አላቸው። ዘመናዊው ታሪክ ሲመጣ ግን ግጭቱ መጣ። የቅኝ አገዛዝ ታሪክ ተጀምሮ በዘመናዊ እርሻ ምርት በማምረት ወደ ውጭ መላክ ሲጀመር እንግሊዞች ግብጽን መቆጣጠር ማለት ዓባይን መቆጣጠር መሆኑን አምነው አስዋን ግድብን ገድበው የማያቋርጥ የመስኖ ልማት ለማልማት የሚያስችል ስትራቴጂ ነደፉ።ሱዳንም አብራ ተጠቃሚ ሆነች።ግብጽም እ.ኤ.አ. 1922 ነፃ ስትወጣ የእንግሊዝን ስትራቴጂ ተከተለች።ከዚያ በኋላ ግብጾች ‹‹የውሃው የመጀመሪያዎቹ ተጠቃሚዎች እኛ ነን፤ ማንም ሊነካ አይችልም፤ ታሪካዊ መብት አለን›› ማለት ጀመሩ።ሱዳንም የግብጽን ጥቅም በማይነካ መልኩ ተጠቃሚ ሆናለች፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በመጋቢት ወር 2003 ዓ.ም. የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ይፋ ባደረገበት ወቅት ለዘመናት ሲንፀባረቅ የቆየውን የኢትዮጵያ ጽኑ አቋም የሆነውን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን አልዘነጋም።በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ በ850 ኪሎ ሜትር በሚርቀው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ እውን እየሆነ ያለው የዓባይ ውሃ ልማት ፕሮጀክትን ለመገንባት ተወጥኖ የነበረው በ1956 ዓ.ም. ነበር።ከቀድሞው ዕቅድ እጅግ ብዙ እጥፍ ሆኖ ዛሬ ላይ የኢትዮጵያንና የተፋሰሱ ሀገራት ተጋሪነት ሊያረጋግጥ እየተቃረበ ይገኛል።የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይፋ ሆኖ ወደ ትግበራ መግባት በዘመናት የቆየውንና የአንድ ሀገር የብቻ ሀብት መስሎ የሚታየውን ፖለቲካዊ አስተሳሰብና እምነት በመቀየር ላይ ጉልህ ምልክት አለው።ግድቡ ሲጠናቀቅ የዘመናት የኢፍትሃዊነት ቀንበርን በመስበር ኢትዮጵያንም ሆነ ሌሎች የተፋሰሱ ተጋሪ ሀገሮችን ነፃ ከማውጣት ባሻገር ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ አለው።

ይሁን እንጂ ግድቡን በተመለከተ የተለያዩ እንከኖችና ሳንካዎች ሲያጋጥሙ ይስተዋላል።ኢትዮጵያ የዓባይን ውሃ ተጠቅማ ግድብ በመገንባት ፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ ለመጠቀም የምታደርገው እንቅስቃሴ ከሀገር ውስጥና ከውጭ አካላት ለምን ፈተናዎች እንደበዙባት በርካቶች ብዙ ብለዋል።እንደዶክተር አረጋዊ በርሄ ገለፃ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያንን ሕይወት በዋናነት የሚለውጥ ከመሆኑ በላይ ሉዓላዊነትን የሚያስከብር ነው።ከዚህ አልፎ የዚህ ግድብ መጠናቀቅ ለአካባቢውም አስተዋጽኦ አለው።በውጤቱም ይሁን በሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ለኢትዮጵያ መቀየርና መለወጥ ለአካባቢውም የሚያበረክተው ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።ይሄን ዕድገት የማይፈልጉ ወገኖች እንቅፋት ሆነው መቆየታቸውን ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉ ወገኖች እነማን እንደሆኑም ዶክተር አረጋዊ ይዘረዝራሉ።በተለይ የህወሓት አመራር ከፖለቲካው መገንጠል ጋር ተያይዞ የውጭ ኃይሎችም እንዲገቡ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ አንጻር ጥቅማቸው የሚጎድል እየመሰላቸው በህዳሴ ግድቡ ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር ሙከራዎች ሲያደርጉ ቆይተዋል።ይሄ ሙከራ ግን በፕሮፖጋንዳ ደረጃ እንጂ በተጨባጭ መሬት ላይ የዋለ ችግር አልፈጠረም።አንዳንድ ጽንፈኞች ከህወሓት አመራር ጋር በመተባበር ሕዝቡን እየከፋፈሉ፣ ተጽዕኖ ለመፍጠር ሞክረዋል፤ ሰላም እንዳያገኝ፣ ተረጋግቶ እንዳይቀጥል፣ ለህዳሴ ግድቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዳያደርግ መጠነኛ እንቅፋት ፈጥረዋል። እነዚህ ከህወሓት አመራር ጋር አብረው የሚጠፉ ኃይሎች ስለሆኑ እስከዚህ ድረስ ከባድ ናቸው ተብለው አይገመቱም።የውጭ ኃይሎች ተልዕኮ ይዘው የሚመጡም ሰዎች ይኖራሉ።ለግል ጥቅማቸው ብለው ወይም ሥልጣን ለመያዝ ብለው ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር የሚሠሩም አይጠፉም።እነዚህ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብን ጥቅም ለማቆም አይችሉም።ሕዝቡ አሁን ተባብሮ ተነስቷል፤ እዚህ ግባ የሚባል እንቅፋት ይፈጠራሉ ብለው እንደማይገምቱ ዶክተር አረጋዊ ያረጋግጣሉ።

ዶክተር አረጋዊ እንደሚሉት ከውጭ አካላት እንከን ፈጣሪዋ በዋናነት ግብጽ ነች።የግብጽን ዱካ እየተከተለች እንቅፋት የምትፈጥረው ደግሞ ሱዳን ነች።ሱዳን ከግብጽ እንዲሁም ከህወሓት አመራሮችና ርዝራዦች ጋር ባላቸው ቅርበት የተነሳ የሚፈጥሩት ይመስለኛል ይላሉ።እነዚህ ኃይሎች ቀኝ ገዢዎች ሲሠሩት የነበረው ሴራ በመከተል ከዓባይ ውሃ የሚገኘውን ጥቅም ለብቻቸው ለማድረግ ባላቸው ምኞት፣ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ችግር ለመፍጠር ይነሳሳሉ።የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለነቃ፣ የዓለም ሕዝብም የዓባይን ግድብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ስለሚገባው ልፋታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየመነመነ ነው ያለው።የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ ልብ ተነስቷል።ይሄን ግድብ ዳር ለማድረስ አሻራውን ለማኖር በአድዋ ጦርነት ጊዜ በአንድነት ተነሳስቶ የጣልያንን ወራሪ ኃይል እንዳሸነፈው ሁሉ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ትልቅ ትንሽ ሳይል ከምንጊዜውም በላይ ተነቃቅቶ ስለተነሳ ግድቡ ተጠናቆ እንደሚታይ እርግጠኛ መሆን እንደሚቻል ዶክተር አረጋዊ እምነታቸውን ያስቀምጣሉ።

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በያዘችው ዕቅድ የታላቁ ህዳሴ ግድብን አጠናቃ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ሆና ከፍተኛ ደረጃ እንዳትደርስ ከውስጥም ከውጭም ስለገጠሟት እንከኖች ፕሮፌሰር ያዕቆብም ይዘረዝራሉ።እንደእሳቸው ገለፃ በዋናነት የሚጠቀስ ፈተና ግድቡ በተጀመረበት ዕቅድ መሠረት በፍጥነትና ጥራት ባለው ሁኔታ በጥንቃቄ እንዳይሠራ በኃላፊነት የተመደበው የኢፌዴሪ ብረታብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/ የተባለው ድርጅት የፈጠረው ችግር አለ።ግድቡ በተያዘለት ዕቅድ ባለመጠናቀቁ የሕዝብም የመንግሥትም ወጪ ጨምሯል።በዚህም በሀብት ብክነት በኩል ጫና መፍጠሩ የሚታወቅ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ዋና ሳንካና እንቅፋት ግብጽ መሆኗ ሁሉንም ያስማማ ይመስላል።የአባይ ውሃ ባለሙሉ መብት እኔ ብቻ ነኝ የሚል አቋሟን በግልፅ አቅርባ ሞግታለች።ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ተጠቅማ ልማቶችን አካሂዳለሁ ብላ ስትነሳ በይፋ ተቃውማለች።የዲፕሎማሲ መድረኮችን ተጠቅማ በቅርቡም በሩቅም ላሉ ወገኖች አሳሳች መረጃዎችን ረጭታለች። በቅርቡ ደግሞ ሱዳን የግብጽን ፈለግ የምትከተል እንደምትመስል ፕሮፌሰር ያዕቆብ ይገልጻሉ፡፡

ከዚህም ባለፈ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ውጤት ለኢትዮጵያም ሆነ ለአካባቢው ሀገሮች የሚሰጠው ጥቅም በይፋ የሚታወቅ ቢሆንም አንዳንድ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ግድቡ እንዲስተጓጎል ሲሠሩ ይታያል። እንደ ዶክተር አረጋዊ አነጋገር እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች አርቀው የማያስቡ፣ ለሀገር እድገት ግድ የሌላቸው እንዲሁም ለግል ጥቅምና ሥልጣን የተስገበረቡ ወገኖች ናቸው። በኢትዮጵያ ታሪክ ባንዳዎች ነበሩ፤ እነዚህ ባንዳዎች በየትኛውም ክልል ከማንኛው ብሔረሰብ ይገኛሉ።ይሄ የነበረም፣ አሁንም ያለ ነገር ነው። እነዚህ ሰዎች የሀገራቸውን ጥቅም ቅድሚያ ስለማይሰጡ፣ ለራሳቸው ጥቅምና ሥልጣን ቅድሚያ ስለሚሰጡ አሳልፎ የመስጠት አዝማሚያ የሚያሳዩ ወገኖች አሉ። ይህ ተግባራቸው በሕዝቡ በተባበረ ትግል ሊገታ የሚችል ነገር ነው። እነዚህ ኃይላት የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም ለማሰናከል ያላቸው ችሎታ በጣም ትንሽ ነው። ሕዝቡ አሁን ተባብሮ ተነስቷል፤ መተባበሩ እስከቀጠለ ድረስ እዚህ ግባ የሚባል እንቅፋት ይፈጠራል ብለው አይገምቱም።

ቅጥረኝነት፣ ከሃዲነትና ጥቅም ፈላጊነት ቢኖርም ብዙ ጊዜ ታሪካችን የሚያሳየው አንድነታችንን የሚያጠናክር ነው የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ አብዛኛው ሕዝብ በህብረት ስር በመሆኑ እንከን ለመፍጠር የሚሞክሩትን ሰዎች ይቋቋማል። በመሆኑም ፋታ ባለመስጠት ሁልጊዜም በአንድነት በመቀጠል ግድቡ እንዲያልቅ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስ ፈልግ ያስገነዝባሉ።

ፕሮፌሰር ያዕቆብ በበኩላቸው ኢትዮጵያዊ ሆነው ግድቡ በተያዘው እቅድ እንዳይጠናቀቅ ለማስተጓጎል ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች በሁለት ምክንያት የተሳሳቱ ናቸው ይላሉ።አንደኛው ስህተት ነገረ ዓለሙ ሁሉ ጠፍቷቸዋል፤ ብሔራዊ ጥቅም ምን እንደሆነ አልተረዱም ማለት ነው። የሀገራቸው ኢትዮጵያ ልማት ነገ ለእነሱም ልጆች፣ የልጅ ልጆቻቸው የሚጠቅማቸው መሆኑን ያልተገነዘቡ ናቸው። ሁለተኛው የሀገራቸው የኢትዮጵያን ልማት እንዳያዩ በተለያዩ ምክንያቶች የተደለሉ ወይም ደግሞ ከግብጽ ጋር መተባበሩ እነሱ የሚፈልጉትን የፖለቲካ ጥቅም ያስገኝልኛል በሚል ራስ ወዳድ የሆነ የተሳሳተ አስተሳሰብ በመነሳት ይመስላል።ደግነቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀገር ወዳድ፣ ብሔራዊ ጥቅም የሚጠብቅና ዳር ድንበር የሚያስከብር ነው።በታሪክም በተለያዩ ጊዜያት የታየ በመሆኑ እነዚህ ኃይሎች በጊዜያዊነት አንዳንድ ችግር ሊፈጥሩ ቢችሉም እርባና ሊኖራቸው አይችልም:: ኢትዮጵያውያን በጋራ ጥቅማቸው ላይ ህብረት በመፍጠር ጥቅማቸውን ያለማስነካት ታሪክ ባለቤት እንደሆኑ ይገልጻሉ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የኃይል ፍላጐት ከማረጋገጡ በላይ ኢትዮጵያን በዓለም የኃይል አቅርቦት ገበያ ያስተዋውቃታል። ከህዳሴው ግድብ የሚመነጨው ኃይልን በሱዳን – ግብፅ – ሊቢያ – ሞሮኮና ስፔን ድረስ መሸጥ ይቻላል።በሌላ መስመር በሱዳን – ግብፅ – ጆርዳን – ሶሪያና ቱርክ ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ያስችላል። የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ምሕረት ደበበ፣ በአንድ ወቅት እንደተናገሩት በዓለም ገበያ ለኤሌክትሪክ ኃይል በኪሎ ዋት ሰዓት የሚሰጠው አማካኝ ዋጋ 20 የአሜሪካን ሳንቲም መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ የዋጋ ተመን መሠረት ከህዳሴው ግድብ የኃይል ሽያጭ 3.06 ቢሊዮን ዶላር በዓመት ማግኘት እንደሚቻል፤ ይኸውም በጂዲፒው ላይ የስድስት መቶኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።ይህ ከሆነ የህዳሴው ግድብን እውን ለማድረግ የሚጠይቀውን ወጪ በአጭር ጊዜ መመለስ ይቻላል። በመሆኑም በግድቡ የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ከማዋል በተጨማሪ ሌሎችም የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆነው ኢትዮጵያም በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንደምትሆን ያሳያል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚያጠራቅመው ውሃ ምንም ዓይነት ሰው ሠራሽ ጣልቃ ገብነት ሳይጨመርበት በዓመት 6,540 ቶን የዓሣ ምርት ማግኘት ይቻላል። በዚህ የህዳሴ ግድብ ውሃ ላይ በሰው ሠራሽ መንገድ የዓሣ ልማት ማካሄድ ከተቻለ ደግሞ በዓመት 30 ሺህ ቶን ዓሣ ማለትም በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሚመረተውን ዓሣ መጠን እጥፍ ሊያደርገው እንደሚችል፤ የሚለማውን የዓሣ ሀብትን ወደ ውጭ በመላክ እስከ 100 ሺህ ዶላር ዓመታዊ ገቢ ማግኘት እንደሚቻል በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የዓሣ ሀብት ልማት ላይ ተመራማሪ የሆኑት የዶ/ር ዮሴፍ ተክለ ጊዮርጊስን የጥናት ግኝትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በአካባቢው የሚከማቸው የውሃ መጠንና ተራራማው መልክዓ ምድር አዕዋፍን በመሳብ የቱሪስቶችን ቀልብ ሊገዛ እንደሚችል ይታወቃል። ጐብኚዎችን በግድቡና በኃይል ማመንጫ ቤቶች ውስጥ ለውስጥ በማስጐብኘት ገቢ ማግኘት ይቻላል።በምሽት ደግሞ በውሃው ላይ የተለያዩ ሰው ሠራሽ ተለዋዋጭ ብርሃናማ ቀለማት በመፍጠር፣ ከውሃው ፍሰት ጋር የሚቀናጅ ማጀቢያ ሙዚቃ በማከል የጐብኚዎች ቁጥር ጨምሮ የቱሪስት የመስህብ ቦታ ማድረግ ይቻላል።

ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ፣ ከዓሣ ሽያጭም ሆነ ከጎብኝዎች የሚገኘው ገቢ ለኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።የግድቡ መገንባት ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት። ለዚህ ነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ለኢትዮጵያውያን የህልውና ጉዳይ የሚሆነው።

ኢትዮጵያ የዓባይን ውሃ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ ተጠቅመን እንልማ የሚል ሀሳብ ይዛ ስትንቀሳቀስ ከሌሎቹ የተፋሰሱ ሀገራት በጎ ምላሽ አግኝታለች።ግብጽ በቅርቡ ደግሞ ሱዳን ለመቀበል ተቸግረዋል።ዶክተር አረጋዊ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፤ ግብጽም ሆነ ሱዳን ለመቀበል የተቸገሩትበት ምክንያት ጥቅሙን ለብቻቸው ለማድረግ ፈልገው ነው።የግድቡ ሥራ ተጠናቆ ተግባር ላይ ሲውል የውሃ መጠኑ ይቀንሳል የሚል ፍራቻ ስላላቸው ነው። ፍራቻቸው ግን ሀቁን ተንተርሶ የመነጨ አይደለም። ከኢትዮጵያ ጋር ቢተባበሩ ኖሮ የበለጠ ይጠቀሙ ነበር። በአንድ በኩል ፍራቻ ነው።በሌላ በኩል ደግሞ የገዢዎቻቸውን የኮሎኒያሊስቶችን አሠራር በመከተል ለብቻ ለመጠቀም ያለ ፍላጎት እየተጫናቸው ይመስላል ብለዋል።

በዘመናዊው ታሪክ ግብጽ በዓባይ ውሃ ጠፍጣፋ የሆነውን ለም መሬት ተጠቅማ ሰፋ ባለ ሁኔታ አልምታለች።ሱዳን በወንዙ ዳርቻ ያለው መሬቷ ይሄንን ያህል ሰፊ ስላልሆነ በመስኖ ተጠቅማ የምታለማው እንደ ግብጽ አይደለም። ሱዳን ውስጥ የተሠሩት ግድቦች የግብጽን ፍላጎት ሊነኩ በማይችሉ መልኩ የተሠሩ ናቸው። ዋናው ተጠቃሚና ውሃውን የምትቆጣጠረው ግብጽ ነች። ፕሮፌሰር አየለ ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ፍትሐዊ በሆነ ሁኔታ በጋራ ለመጠቀም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ለግብጽ በሽታ ነው ይላሉ። ምክንያታቸውን ሲገልጹ በዓባይ ውሃ የኤሌክትሪክ ኃይል ታመነጫለች፣ የመስኖ እርሻ ትጠቀማለች፣ ዓሣ ለማምረት ሆነ ለቱሪዝም ትጠቀማለች። ከዚህ በተጨማሪ ውሃውን ከግድቡ በማውጣት በረሃውን እያለማች ትገኛለች። ከዚህ በሚገኘው ጥቅም ከፍተኛ የሆነ የመከላከያ ኃይል ፈጥራለች። በዚህ የመከላከያ ኃይሏ በመመካት የዓባይን ውሃ ማንም መንካት አይችልም በማለት ለማስፈራራት እንደምትሞክርና ሱዳንም የጥቅም ተጋሪ ለመሆን ካላት ፍላጎት የተነሳ የምትተባበር መሆኑን ያስረዳሉ። ሰው ሠራሽ የሆነው የናስር ሀይቅ በረሃ ላይ የተገነባ ስለሆነ ውሃው በአብዛኛው ተኖ ነው የሚያልቀው።ኢትዮጵያ ዓባይን በመገደቧ ዓመቱን ሙሉ የተመጠነ ውሃ ለግብጽም ለሱዳንም ስለሚደርሳቸው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸው ባለፈው ዓመት ወደ መቶ ሺህ ሕዝብ በጎርፍ ምክንያት ሱዳን ውስጥ መፈናቀላቸውን እንደ ማሳያ ያቀርባሉ።

ግድቡን በተመለከተ ሌሎች የተፋሰስ ሀገሮች  ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያ፣ ቡሩንዲ ከኢትዮጵያ ጋር በጣም በቅርብ እየተጋገዙ የሚሠሩ ሀገሮች ናቸው።ከአሁን በፊት ከግብጽና ከሱዳን አንገት ለአንገት ተያይዘው ድርድር አካሂደው የትብብር ማዕቀፍ ሁሉ ፈርመዋል። ስለዚህ እነዚህ የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገሮች በኢትዮጵያ ላይ እንቅፋት ሆነው አይታዩም፤ እንዲያውም አጋዥና ተባባሪ ናቸው በማለት ፕሮፌሰር ያዕቆብ የተፋሰሱ ሀገራት የትብብር ማዕቀፍ እንዴት እንደተፈራረሙ ያስታውሳሉ።

ሀሳባቸውን በመቀጠል፤ ግብጽ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሱዳን እንቅፋት የሚሆኑት ጥቅማችንን እናጣለን በሚል ነው።ውሃ አመንጪ የሆነችው ኢትዮጵያ በዓባይ ውሃ ለመጠቀም የምታደርገው እንቅስቃሴ ግብጽንም ሆነ ሱዳንን ለመጉዳት ታልሞ የሚተገበር ስላልሆነ የተፋሰሱ ሀገራት ፍትሃዊ በሆነ አጠቃቀም ልማትን እያካሄዱ ግብጽም ሆነ ሱዳን የውሃው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፍላጎት አላት። ግብጾች በዚህ ጉዳይ ስለማይተማመኑ፣ ከዚህ በፊት ውሃውን እንደፈለጋቸው ይጠቀሙ ስለነበረ ይህን የበላይነታቸውን ማስቀጠል ይፈልጋሉ። በጋራ ጥቅም ላይ ከመመስረት ይልቅ የሌሎች መጠቀም እኛን ይጎዳል ብሎ በማሰብ መልካም ያልሆነ መንገድ ተከትለው ነው የሚገኙት ብለዋል።

ሱዳን ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከምታገኘው ጥቅሟ ይልቅ ለግብጽ ፖለቲካዊ ጥምረት ትኩረት የሰጠችበትን ምክንያት ዶክተር አረጋዊ በርሄ ሲናገሩ፤ ሱዳኖች ከግብጽ ጋር የሚተባበሩት የፍራቻ ግንኙነት ነው።ኢትዮጵያ ዓባይን ገድባ ለራሷ ብቻ ተጠቃሚ ትሆናለች የሚል ፍራቻ ነው። ይሄ ፍራቻ ግን በውል ሲታይ፣ በዕውቀት ሲታይ ትርጉም የሌለው ፍራቻ ነው። ምክንያቱም ውሃውን በአግባቡ ከተጠቀምን፤ በተለይ ወደ ሰማይ በእንፋሎት መልክ የሚተነው መቀነስ ከተቻለ፤ ውሃ ወደ መሬት እንዲሰርግ ለማድረግ ከተቻለ፤ ጫካው እንዲለማና እንዲጠበቅ ማድረግ ከተቻለ፤ ይሄ ሁሉ ፍራቻቸው ትርጉም አይኖረውም ነበር።ፍራቻው ከመጠራጠርና ካለማወቅ የተነሳ ይመስላል በማለት ሱዳን ፍራቻዋ እያየለባት ከግብጽ ጋር ህብረት ለመፍጠር እንደተገደደች ይገልጻሉ፡፡

የዓባይን ውሃ አጠቃቀም በተመለከተ ግብጽ ይዛ የምትንገታገተው የቅኝ ገዥዋ እንግሊዝ የፈጠረችውን እንጂ ሀገራቱ በጋራ ስምምነት አድርገው አይደለም የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ ሱዳን የራሷን አቋም ይዛ ተንቀሳቅሳ እንደማታውቅና ግብጽ የምትላትን የምትከተል እንደሆነች ይገልጻሉ። በመሆኑም የሱዳን አቋም አይገርማቸውም።በመቀጠልም፤ ‹‹የዓባይን ውሃ አጠቃቀም ታሪክ ስገመግም አሁን ሱዳን ያደረገችው ወረራ፣ ሱዳን ሳትሆን ግብጽ ናት የወረረችን እላለሁ›› በማለት ግምገማቸውን ያስቀምጣሉ።

ሱዳን በግድቡ ዙሪያ የኢትዮጵያን ሀሳብ የምትቃወም ከሆነ የሱዳንን ብሔራዊ ጥቅም አጉልቶ የሚሠራ መንግሥትና አመራር ሱዳኖች የላቸውም ማለት ይቻላል የሚሉት ፕሮፌሰር ያዕቆብ ደግሞ ምክንያታቸውን ሲዘረዝሩ፤ ለሱዳን ውሃ ዓመቱን ሙሉ ስለሚሄድላት የጎርፍ ውሃ ይዞት የሚመጣውን ደለል በብዙ መጠን ይቀንስላታል።ዓመቱን ሙሉ ውሃ ማግኘቷ ውሃ አጠር በሆነውና በተንጣለለ ለም መሬት ላይ ለሚሠራ የእርሻ ሥራ እንዲሁም በመስኖ ለሚለማ የግብርና ሥራዎችም ተስፋ ይሆናታል።ይህ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ የሚቀርብላት የኤሌክትሪክ ኃይል በጣም ጥሩ በሆነ ዝቅ ባለ ዋጋ ዓመቱን ሙሉ የምታገኝበት ሁኔታም ነበር።ከኢትዮጵያ ጋር በሀገር ደረጃ ከሚደረጉ ትብብሮች ባሻገር በግድቡ ምክንያት በሕዝቦችና በባለሀብቶች መካከል ሌሎች የትብብር መስኮችም ሊበ ጁና ሊደራጁ የሚችሉባቸው ዕድሎች አሉ ይላሉ።ሱዳን ይህን ብሔራዊ ጥቅሟን በግብጽ ጫና ወይም በአመራር ላይ ያሉ ተታለው ወደ ግብጽ ማድላታቸው አስገራሚ እንደሆነባቸው ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ከውስጥም ሆነ ከውጭ አካላት አሁንም ሆነ ወደፊት በዓባይ ውሃ አጠቃቀሟ እንከኖችና ፈተናዎች እንዳይደርሱባት ምን ማድረግ እንደሚገባትና ሲድርስባት እንዴት ባለ ሁኔታ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባት ዶክተር አረጋዊ ቁልፉ መተባበር ነው ይላሉ።በሀገርና በጋራ ጥቅም ላይ አንድ ዓይነት ራዕይ፣ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ፣ አንድ ዓይነት ሥነልቦና ማሳደር ያስፈልጋል። ይሄ ካለ ማንም የውጭ ኃይል ጥቃት ሊያደርስብን አይችልም።ቁልፉ ነገር በሀገር ጉዳይ ወይም በሕዝብ ጥቅም እና በግል ጉዳይ ወይም በግል ጥቅም መካከል ያለው ልዩነት ጠንቅቆ አውቆ በጋራ ስትራቴጂ መንደፍ፤ ማስተባበርና መተግበር ነው።ተባብሮ መቆም ይገባል።ጣልያንን ያሸነፍነው ስለተባበርን ነው።ከጫፍ እስከ ጫፍ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተባብሮ ጣልያንን ስለገጠመው አሸነፈው፤ ባይተባበር ኖሮ አያሸንፍም ነበር።ጠበንጃ ወይም ጀብደኝነት ብቻ አይደለም የሚያሸንፈው። የሚያሸንፈው ህብረት ነው።ሕዝቡ ስለተባበረ ነው ጠላትን ማሸነፍ የተቻለው።ጣልያንም ባህር ተሻግሮ መጥቶ ሀገራችንን የቅኝ ግዛት ሀገር ለማድረግ ሕዝባችንን ባርነት ውስጥ ለመክተት፣ መሬቷን ለራሱ ሕዝብ የእርሻ ቦታ ለማድረግና በግብርና ለመጠቀም አቅዶ ነበር፤ ነገር ግን አልተሳካለትም።ያልተሳካለት ዋናው ምክንያትና ምስጢር ሕዝቡ ሀገር ወዳድ ስለሆነና በህብረት ተነሳስቶ ሀገሬን አሳልፌ አልሰጥም ስላለ ነው።ይሄ እንደ አንድ ታሪክ በሕዝቡ ውስጥ ፀርፆ ያለ ስለሆነ ወደ ፊትም እንደዚህ ያለ ትንኮሳ ወይም የወረራ ዕቅድ የማይሠራ መሆኑን በተለያየ አጋጣሚ አሳይቷል፤ ያሳያልም።ህብረት ካለ የዓባይን ውሃ ተጠቃሚነት ይሁን ሌላ የሀገር ፍላጎቶች ሊጠበቁ ይችላሉ።

ፕሮፌሰር ያዕቆብ የዶክተር አረጋዊን ሀሳብ በመደገፍ ዋናው ነገር ኢትዮጵያ የራሷ ጥቅምና ህልውና፣ ዳር ድንበሯን፣ ልማቷንና ዕድገቷን ለማስቀጠል ኃላፊነቱን የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ መያዝ አለበት ይላሉ።የኢትዮጵያን ጥቅም የማይፈልጉ ከቅርብም ሆነ ከሩቅ ዛሬም ነገም እንደ ኢትዮጵያ ተባብሮ በመሥራት ነቅቶ መጠበቅ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። ይህ ግድብ የሀገሪቱ የሰንደቅ አላማ ፕሮጀክት ተብሎ የተያዘ ስለሆነ በመላው ኅብረተሰብ ድጋፍ ሳንካዎቹንና ተግዳሮቶቹን በጣጥሶ መሄድ ይገባል።ግድቡን በፍጥነት ጨርሶ የታቀደውን የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ተጠቃሚ በመሆን በቀጣይ ዘመን ላይ ኢትዮጵያ የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገትና ብልጽግና እንድታገኝ ጥረት ማድረጉ መቀጠል ያስፈልጋል።የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉ ምንጊዜም ስለማይተኙላት ነቅቶ በመጠበቅ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

ፕሮፌሰር ያዕቆብ እንደሚገልፁት በጉልበት ለመምጣት ለሚፈልጉ አካላት በተቀናጀ መንገድ እንደ አመጣጣቸው መመከት ነው።የኢትዮጵያ ተጻራሪዎች እንዳይጠናከሩ ከውስጥ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር ከውጭም በጣም ተቀራርቦ መሥራት ያስፈልጋል።ትኩረት በመስጠት በጣም ከፍተኛ የሆነ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት ይገባል።ይሄ ወዳጆቿ አጠገቧ እንዲሆኑ ይጠቅማል። ወዳጅነት እንዲጠነክር በንግድም፣ በኢንቨስትመንትም በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማድረግ ይገባል። ጠላቶቿ እንዲያፍሩና እንዲሸማቀቁ ኢትዮጵያን ለመጫን ፍላጎትና አቅም እንዳይኖራቸው ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ይሄ በአንድ ጀንበር የሚደረግ ሳይሆን የሚገነባ፣ የሚያድግና ከዚያም አቅም የሚያገኝ የኢትዮጵያን ከፍታና ጉልበት በአካባቢውም ሆነ በዓለም ዙሪያ የሚያጎላ ስለሆነ ኢትዮጵያ በዚህ አቅጣጫ ራሷን ማስተካከልና መተግበር አለባት በማለት ኢትዮጵያውያን የጋራ ጥቅማቸው እንዳይነካ በህብረት መሥራታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በዲፕሎማሲ መድረክም በጣም መሥራት እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ ህብረትን ጠብቆ በአንድነት መሥራት ከሚለው ከሁለቱ ምሁራን ሀሳብ ጋር ይስማማሉ። ኢትዮጵያ ግድቡን ሙሉ በሙሉ በመጨረስ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ መሆን ስትጀምር የግብጽ ሞኖፖሊ ይሰበራል።ይህ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሦስት አራት ተጨባጭ የሆኑ በዓባይ ውሃ ላይ ማስቀመጥ ከተቻለ ያን ጊዜ ግብጽ ወደ ዴሞክራሲያዊ አሠራር እንዲሁም ፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ ለመጠቀም ትስማማለች። ዋናው ቁልፍ ጉዳይ ግድቡን ጨርሶ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንዲሁም ሌሎች ተጨባጭ የሆኑ ሥራዎችን ዓባይ ላይ መተግበር እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ይገልጻሉ።

ግብጾች ለዘመናት በኖረው ፕሮፓጋንዳቸው «ግብጽ ያለ ናይል መኖር አትችልም» የሚለው ስብከታቸው አሁን ጊዜው አልፎበታል። በተቃራኒው የናይል ወንዝ አመንጪ አገራት ያለ ወንዙ መኖር አይችሉም የሚባልበት ደረጃ ላይ እንደደረስን ማወቅና መረዳት አለባቸው። የግብጽ ኢኮኖሚ እርሷ እንደምትለው በግብርና ላይ የተንጠለጠለ አይደለም። ግብርና ያለው ድርሻ ከ13 በመቶ አይዘልም። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የተፋሰሱ አገራት ኢኮኖሚ ግን በግብርና ላይ ያለው ጥገኝነት እስከ 80 በመቶ የሚደርስ ነው። ስለሆነም የአባይ ወንዝ ከግብጽ ይልቅ ለኢትዮጵያ በጣም አስፈላጊ መሆኑን በዚህች ቁንጽል ማስረጃ ብቻ መመልከት ይቻላል። መሬት ላይ ያለው እውነታ ይሄም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ወንዙን ብቻዬን ልጠቀምበት አላለችም። ቢቻል በጋራ አልምተን በጋራ እንጠቀምበት፤ ካልተቻለ ግን የመጠቀም መብቴ ላይ ማንም ከፊቴ ሊቆም አይገባም ነው የምትለው። ግብጾች አብረው መዋኘት አይችሉም፤ መስመጥ እንጂ። ዘመኑ ደግሞ አብሮ መዋኘትና ሻምፒዮን የሚኮንበት ነው። ይህ ግን ለግብጽ አይሠራም። ዛሬም ድረስ የቅኝ ግዛት ውልን ይዘው አደባባይ ይወጣሉ፤ ለድርድርም ይቀርባሉ። ይሄ ለግብጽ ሕዝብ ውርደት ነው። የቅኝ ግዛት ውልን ይዞ መብቴ ይከበርልኝ ማለት አገሪቷን ከቅኝ ግዛት ነፃ ለማውጣት በአንድም በሌላም ዋጋ የከፈሉ የአገሪቷን ባለውለታዎች ሁሉ መክዳትና ውለታቸውን አፈር ላይ መጣልም ነው። ስለሆነም ግብጽና ግብጻውያን ቅኝ ግዛት ትክክል ነው ከሚለው አቋማቸው ሊወጡ ይገባል።

Recommended For You