ብርሃን

እግዜር ግን ለሴትነት አዳልቷል። እውነት አዳልቷል..። ካልሆነ በአጠገቧ ሳገድም ለምን ትገዝፍብኛለች?

በሴትነቷ ፈር ውስጥ የብርሃን ጎርፍ ይንፎለፎላል። በምሽት ጉያዋ ውስጥ ምስል አትማ እንደምትንፏቀቅ ጨረቃ የብርሃን ምንጭ ከቀይ ፊቷ ላይ ይፈልቃል። እንደአራስ ገላ ከሊጥ የተማሰለ የሚመስል፣ እንደመስተዋት ርቃን ብርሃን የሚያስተላልፍ ውብ ፊት እግዜርን የማማበት ተፈጥሮዋ ነው። በክረምት ጎሾ በዳመነ ሰማይ ደረት ላይ እንደሚብለጨለጭ የመብረቅ ብልጭታ ሲያዩዋት ነፍስ ታዘማለች። ትካዜዬ ወንዝ የሚሻገረው በእሷ ነው። በአየኋት ቅጽበት ቀን ሙሉ የምተክዘው ትካዜ አለኝ።

ብርሃናማ ናት..እንደጨረቃ። የውበት ጸዳል የሚንቦገቦግበት ፊት። ሰው ሆኖ ብርሃናማ መሆን ይቻላል? ሁሌ ከእጄ የማይጠፋው የአፈንጋጩ የኦሾ ፍልስፍና እንኳን የእሷን ውበት ያክል አላስለፈለፈኝም። ማማር ስትወድ። አንድም ቀን ከላመል ጉድፍ ጋር አላየኋትም። ደሞ ዘናጭ ናት..ከሰውነቷ ጋር ያበሩ፣ ውበቷን ያጎሉ ደመቅማቃ ልብሶች ታዘወትራለች። ጸጉሯ አጭር ነው..ፊትሽ ለአጭር ጸጉር የሚሆን ነው ተብላ ረጅም ጸጉሯን ያሳጨደችው ይመስለኛል። ብርሃናማ ፊት ከብርሃናማ ዐይኖች ጋር ፊት ለፊቴ ሲደነቀሩ አልደነባበርም፤ ለቀን ሙሉ የሚሆነኝን የሐሳብ ስንቅ ከውብ ፊቷ ላይ እቃርማለሁ። የሆነ ልማድ አላት..አንድን ሰው ለረጅም ጊዜ የማየት። በዛ ዐይንና ውበት ለረጅም ጊዜ መታየትን ዳዋውን አስቡት? በውበቷ በኩል ስርየት የሌላቸውን ትላልቅ ኃጢአቶችን ሠርቻለሁ። ካህን ፊት ቀርቤ ብናዘዛቸው መዳኛ የማላገኝባቸውን ኃጢአቶች። ጸንቼ ሰንብቼ መሰነካከያዬ የእሷ ፊት ነው።

ምኗን ከምን አወዳድሬ እንደማተልቅ ባላውቅም ዐይኖቿ በውበቷ ሰማይ ላይ ብርሃንን የሚረጩ የሴትነቷ ማሾ ይመስሉኛል። ከፀሐይ የተዛመደች ይመስል፣ ከተሲያት የተቆራኘች ይመስል በዐይኖቿ በኩል የሚፋጅ ተፈጥሮ አላት። እንደዛ ባያምሩ በዛ ልክ አትወደስም የሚል ሐሳብ ይመጣልኛል። ሰንብቶ ደግሞ ከተፈጥሮዋ ላይ ግማሹ ቢደበዝዝ በውበት ማንም አይበልጣትም፤ የሚል ሞጋች ሐሳብ ይፈጠርብኛል። ሰማይ ላይ ተንጠልጥላ ዓለምን እንዳወገገችው ጨረቃ ለልቤ ከተማ ፀሐዬ ናት።

ስትለብስ ዝርክርክ ናት ልበል? እንጃ እርግጠኛ አይደለሁም..። ከአለባበሷ ተርፎ አሊያም ተዛንፎ ወይ ባቷን ወይ እንብርቷን ወይ ገላጣ ጀርባዋን፣ ወይ ደረቷን፣ ወይ የወገቧን ዙሪያ ሳላየው ቀርቼ አላውቅም። በቋፍ ላለ ለእኔ ዓይነቱ ልክፍተኛ ያን ውብ ገላ ማየት ሌላ ፈተና ነበር። በአየሁት የሆነ ነገሯ ሁሉ ምራቄን እውጣለሁ። የሴት ገላ አይቼ ለጉሮሮዬ ዕዳ የሆንኩበት በእሷ ውበት ነው።

የከፋው ነገር እኔን አትወደኝም። አንድ ቢሮ ውስጥ ለዓሥር ስንሠራ የማታወራው ከእኔ ጋር ብቻ ነው። ዓለም ላይ የሰው ልጅ ሁሉ አልቆ እኔና እሷ ብቻ ብንቀር የምትጎራበተኝ አይመስለኝም። እኔ ፊትና ሌሎች ወንዶች ፊት ሁለት ዓይነት ናት። የምትደናበረውና የምትመናቀረው እኔን ስታይ ነው። አንድ ቀን ቀናኝ..ፊትለፊቴ ተረከዛማ ጫማዋ ተበጠሰ። በሁለት እጅዋ እንደእሷ መንገደኛውን የሚያስቀላውጡ መልከኛ ፔስታሎችን አንጠልጥላለች። (እገምታለሁ ልብስ ነው የያዘችው። በየሳምንቱ ዓርብ በሥራ በኩል ገበያ ወጥቶ የአማራትን የመሸመት አመል አላት) ተረከዛማ ጨማዋ ተበጠሰ። እኔን ርዳታ ከመጠየቅ ውጪ ምንም ምርጫ እንደሌላት በማሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ የምታወራበትን አጋጣሚ በኩፈሳ ስጠብቅ እግሯን እየጎተተች አልፋኝ ሄደች። እንደዚህ የጠላችኝ ምን በድያት ነው? ወደሚል የሐሳብ አዘቅት ተወረወርኩ።

ከብዙ ቀናት በኋላ አንድ ረፋድ ውስጤ የሚመላለስን ሐሳብ ተከትዬ ከቢሮዬ ወጣሁ። እንደነገሩ ነው የለበስኩት። የመሥሪያ ቤታችን እብድ መሳይ ሠራተኛ ነኝ። በዚህ ዝርክርክነቴ እዛች ጣኦት መሳይ ቆንጆ ሴት ፊት ስቀርብ ደፋርነቴ ነው የሚመጣብኝ። ከአእምሮ እንጂ ለአካል ግድ የለኝም።

ማሰብ እወዳለሁ። በሆነ ርእሰ ጉዳይ ላይ መወያየትና መከራከር የምዝናናበት ተፈጥሮዬ ነው። አንዳንዶች አለባበሴን አይተው በሩቁ የማይረባ ያደርጉኛል። የተረዱኝ ደግሞ በግድም ለወዳጅነት ይመርጡኛል። እንደእኔ ነፍሱን በሐሳብ ያከሳ ሰው አላውቅም። አእምሮ አፍ ቢኖረው በአግባቡ የተጠቀመብኝ ሰው ብሎ ይኩራራብኝ ነበር። እኔ ስወጣ ጀምበር ስትገባ ከመንገድ ተገናኘን። ፀሐያማው ቀዬ ጠይም ደመና ለበሰ። ወዲያው ማካፋት ጀመረ። የተረገመ ቀን አልኩ። እንደሐሳቤ ሳይሆን ሲቀር እንዲህ የምለው መርገምት አለ። ጥሩ ለአለበሰ፣ ሐሳባዊ ለሆነ ሰው ፀሐይ ሆነ ደመና ምን ሊበጀው? ከካፊያው ሽሽት ከመሥሪያ ቤታችን አቅራቢያ ወደሚገኝ ገብቼበት ወደማላውቅ ካፌ ሰተት አልኩ። ዝናቡን ከራሴ ላይ ላራግፍ አንገቴን እየወዘወዝኩ እና ትከሻዬን እያንዘፈዘፍኩ ወደሆነ ባዶ ወንበር ተምዘገዘኩ። ተደላድዬ ሳልቀመጥ እንዲሁም ሐሳቤን ፈር ሳላሲዝ አንዲት ጸጉሯን ቀለም ያጠጣች፣ ደረቷ ላይ የእሾህ አክሊል ያለበትን የኢየሱስን ምስል የአተመች ሴት ልትታዘዘኝ ፊቴ ተዘባና ቆመች። ማንም ከዚህ በፊት እንዲያ ባለ ዝብናኔ አስተናግዶኝ አያውቅም። በዝብናኔዋ አልተቀየምኳትም ይልቅስ አዲስ ሐሳብ አጋባችብኝ እንጂ። ‹ወተት አልኩ› ብዙ ሳላለፋት። ካፌ ገብቼ ከወተት ውጪ የምጠጣው ነገር የለም። አንዳንድ ወዳጆቼ ሲቀልዱብኝ የእናት ጡት ስላልጠገበ ያንን እየተካ ነው ይሉኛል። እኔ ምን ገዶኝ..አንድ ብርጭቆ ወተት ለመጨረስ በሚሳቀቁ ቄንጠኛ ወዳጆቼ ፊት ሁለት..ሦስቱን ደርግሜ እመለሳለሁ። ከእንስሳ የላም አፍቃሪ ነኝ። ከሰው ደግሞ የራሴና የኢየሱስ። ያቺን የመሥሪያ ቤታችን ቆንጆ ዘናጭ ሴት ሦስተኛ ላደርጋት ከራሴ ጋር ምክክር ላይ ነኝ።

ከቡሀቃ መለስ ባለ አንዳች በሚያክል ጥንታዊ ብርጭቆ ትኩስ ወተት መጣልኝ። በዛ ዘመነኛ ቤት ውስጥ ያን ብርጭቆ መኖሩ ዙሪያ ገባዬን እንድቃኝ አደረገኝ። ቤቱ ባህላዊ ቤት እንደሆነ በተቀመጥኩበት ወንበርና፣ ግድግዳው ላይ በተሰቀሉ አንዳንድ ባህላዊ ጌጦች አረጋገጥኩ። ትልቁ ብርጭቆ ውስጥ ይመጥነዋል ብዬ ያሰብኩትን ስኳር በስሌት ጨምሬ ወደአፌ አስጠጋሁት። በአንዲት ቀብራራ ሴት የመጣ ነጭ ወተት..ወደሆዴ ሲሰርግ በተለየ እርካታ ነበር። ተስገብግቤ ጠጣሁት። እንደዛሬ ወተት ጠጥቼ አላውቅም..። አጠጣጤን እየታዘበች ይሆን እንጃ ላጋሳ ቀና ባልኩበት አስተናጋጇን ዐይኗን አነጣጥራብኝ አገኘኋት። ደረቷ ግድም በእሾህ አክሊል ኢየሱስን ወደአንድ ጎን አዘንብሎ አየሁት። ካልጠፋ ቦታ የዓለምን ንጉሥ እዛ ቦታ ማኖሯ ፈጣሪ በንፍር ውሃ ሊጠብሰን እያኮበኮበ እንደሆነ እንዲሰማኝ አደረገኝ። በሴት ርቃን ላይ፣ ለዛውም በጡት ሰፈር ኢየሱስን ተሥሎ ሳየው ስምንተኛው ሺ መድረሱን አወኩ። ‹ከፍቅሯ ነው ከድፍረቷ ያን ማድረጓ?› ስል ጥያቄ መጣብኝ። ከማንም ቀድሞ ኢየሱስ ያያት ዝሙተኛዋ መቅደላዊት ፊቴ ላይ አንጃበበች።

ከቀይ ዳማ ሸሸት ከጠይምነት መለስ ያለ መሐል ላይ ያለ ስም የሌለው መልክ አላት። ከውበቷ ሁሉ ቶሎ ዐይን ውስጥ የሚገባው ጡቷና ቆፍጣናነቷ ነው። የሐበሻ ቀሚስ ለብሳ ቢሆን ፊቴ የቆመችውና የምትታየኝ እቴጌ ጣይቱ በወጣትነቷ ትሆን ነበር። ጡቶቿ ለእይታ እንዲመቹ ሆነው መልኩን በሚያሳብቅ ጥቁር ጡት ማሲያዣ ተጠፍረዋል። ደረቷን ለሁለት ገምሰው ተነፋፍተው እና አጮልቀው። ከአንዴ ልቀው ለዘላለም እንዲታወሱ በኃጢአተኛ ሴት መላ ተዘባነዋል። አማረችኝ። ከወተቱ ጋር እሷን የሚያሰኝ መስተፋቅር ሰታኝ ይሆን? አይቻት የማላውቃትን ሴት በአንድ ጊዜ መከጀሌ ስል አሰብኩ። ከሴት ውበት መድከሚያዬ ጡት ነው። ትልቅ ጡት ያላት ሴት ሰፊ ዓለሜ ናት። ሴት ጡት ከሌላት ሴት አትመስለኝም። አብሬአት ተጋድሜ እንኳን አምሮቴን ለማውጣት የማውቃቸውን ትልቅ ጡት ያላቸውን ሴቶች በሐሳቤ አምጥቼ ነው የምረካው። የዚህ ዓለም ዕድለኛዋ ሴት ትልቅ ጡት ከትልቅ መቀመጫና ከትሑት ልብ ጋር ያላት ናት የሚል ምልከታ አለኝ።

ሒሳብ ልከፍላት በዛውም በደንብ ልረዳት በምልክት ጠራኋትና መጣች። ስትራመድ ለማንም ዝቅ እንዳትይ ተብላ የአደገች ነው የምትመስለው። ቆፍጣናነቷ ተጋብቶብኝ ትሕትናዬን ነጥቆ ‹ሒሳብ ስንት ነው?› ስል ተጀነንኩባት። ለሠላሳ ብር ወተት ያን ያክል መጀነን..

‹ተከፍሏል› አለችኝ። በማውቀው ቆፍጣናነቷ።

ምን እንደአስደነገጠኝ እንጃ ተከፍሎልኝ የማያውቅ ይመስል ድንግጥ አልኩ። ማን አባቱ ነው የከፈለልኝ በሚመስል አኳኋን ፊቷ ላይ አንጃበብኩ። የጠጣሁበትን ባላገር ብርጭቆ አንሥታ፣ የአዝረከረኩትን ወተት ጠረጴዛውን አባብሳ ከፊቴ እብስ አለች። ቁፍጣኔዋ ራሷ የከፈለችልኝ እንደሆነ እንዳስብ አደረገኝ። ደግሞ አሁን የመጣ አይደለም ስገባ ጀምሮ የማውቀው ቁፍጣኔ ነው። ከዐይኔ ከመሰወሯ በፊት ‹ማነው የከፈለው? ስል ዘለግ ያለ ድምፄን ወረወርኩላት። ትታኝ ትሄዳለች ብዬ ስፈራ ጣቷን ከገባሁ ጀምሮ ወደአላየሁት ቦታ ቀስራ ወደከፈለችልኝ ሴት ጠቆመችኝ። እኔና ሐሳቤ፣ እኔና ምኞቴ..ዘላለሜ ሳይቀር እዛ ቦታ የጨው ሐውልት ሆነን የበደንን ይመስለኛል። ከአልሆነ ለምን መራመድ አቃተኝ? በዛ ቦታ ለክፍለ ዘመናት የቆምኩ ይመስለኛል። ብርሃናማዋን የመሥሪያ ቤታችንን ሴት እያስተዋልኩ። ፊቷን ለግድግዳው ሰጥታ፣ እጇን ደረቷ ላይ አጣጥፋ በሆነ ሐሳብ ተወስዳለች። የማውቀው ፈገግታዋ የለም። ግድግዳውን እያናገረች መሰለኝ። ሊስማት ከንፈሯ ሥር በደረሰው ግድግዳ ቀናሁ። ግድግዳውን ባደረገኝ አልኩ።

አመሰግናለሁ ሳልላት ወጣሁ..

የያዝኩትን መጽሐፍ ረስቼ ኖሮ በነጋታው ቢሮ አምጥታ ስትሰጠኝ ከፈጣሪ ስጦታ የተበረከተልኝ ነበር የመሰለኝ።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

ዘመን ሚያዝያ 2016 ዓ.ም

Recommended For You