ትምህርት ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ዕድገት ቁልፍ መሣሪያ ነው። ይህ አጠቃላይ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ ትምህርት በአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት የአለውም ፋይዳ በርካታ ነው። ዓለም አንድ መንደር በሆነችበት በዚህ ዘመን በሀገራት መካከል ያለው ውድድር በቴክኖሎጂ ዐቅም ላይ የተመሠረተ መሆኑ የታወቀነው። ቴክኖሎጂን ለመፍጠርም ሆነ ለመጠቀም ደግሞ ዋናው ጉዳይ ትምህርት ነው።
ስለሆነም በሀገራት መካከል የሚካሄደው ውድድር በዕውቀት ላይ የሚመሠረት መሆኑ አይቀርም። የሰው ሀብትን ለማልማት ዋነኛው መሣሪያ ትምህርት በመሆኑ አዲስ አበባ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች።
የትምህርት ዘርፉ ዋና ትኩረት የትምህርት ተሳትፎና ፍትሐዊነት በማሳደግ በዕውቅትና በሥነ- ምግባር የታነፀ ትውልድን ማፍራት ነው። ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያዉ ሦስት ዓመት (2013-2015 ዓ.ም.) የልማት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት›› ላይ እንደተገለጸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የትምህርት ሽፋንን በተመለከተ ከ2013- 2015 ዓ.ም. በቅድመ አንደኛ ትምህርት 266,559 ተማሪዎች ለመቀበል ዐቅዶ 299,732 ወይም የዕቅዱን (112%) ማከናወን ችሏል። ይህ ስኬት የተገኘው ከተማ አስተዳደሩ በአመቻቸው የምገባ ሥርዓት ምክንያት ቤት ይውሉ የነበሩ በርካታ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት በመግባታቸው ነው።
ከቅድመ አንደኛ በመቀጠል ያለውን ስንመለከት ደግሞ ከ2013- 2015 ዓ.ም. በአንደኛ ደረጃ ትምህርት 548,323 ተማሪዎች ለመቀበል ታቅዶ 607,369 (95.93%) ማከናወን ተችሏል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት (9-12ኛ) ቅበላ በተመለከተ ሲታይ ከ2013- 2015 ዓ.ም. 222,166 ተማሪዎች ለመቀበል ታቅዶ 226,549 (101.9%) ማከናወን ተችሏል።ዜጎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ፣ በ2014 ዓ.ም. 16,890 ተማሪዎች በአፋን ኦሮሞ ትምህርት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ለመቀበል ታቅዶ 16,890 (100%)፤ በ2015 ዓ.ም. 30,583 ተማሪዎች ለመቀበል ታቅዶ 18,556 (60.6%) መቀበል ተችሏል። እንዲሁም በ2014 ዓ.ም. 34,184 ተማሪዎች በአፋን ኦሮሞ ትምህርት የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ለመቀበል ታቅዶ 34,184 (100%)፣ በ2015 ዓ.ም. 52,142 ተማሪዎች ለመቀበል ታቅዶ 42,692 (81.88%) መቀበል ተችሏል። ከዚህ በተጨማሪ በ2014 ዓ.ም. 12,769 ተማሪዎች በአፋን ኦሮሞ ትምህርት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለመቀበል ታቅዶ 12,769 (100%)፣ በ2015ዓ.ም 20,729 ለመቀበል ታቅዶ 16,041 (77.4%) መቀበል ተችሏል።
ከትምህርት ቅበላና ተሳትፎ ጎን ለጎን የከተማዋን ሴቶች የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል። በቅድመ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ወንዶች በተወሰነ ልዩነት የሚበልጡ ሲሆን በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ግን ሴቶች የተሻለ ብልጫ አላቸው። በልዩ ፍላጎት ከ2013- 2015 ዓ.ም. 31,950 ተማሪዎች ለመቀበል ታቅዶ 37,198 (116.4%) ተማሪዎች የትምህርት ዕድል አግኝተዋል። በልዩ ፍላጎት በአፋን ኦሮሞ 500 ተማሪዎች ለመቀበል ታቅዶ 459 (91.8%) መቀበል ተችሏል።
የትምህርት ጥራትን ማሻሻል በተመለከተ ደግሞ ከ2013- 2015 ዓ.ም. የተማሪ መጽሐፍ ጥምርታ ምጥጥን በሁለተኛ ደረጃ (በዲጂታል) 1፡ 1 ለማድረስ ታቅዶ 1፡1 (100%) ማድረስ ተችሏል።
የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት የመምህራን ተማሪ ጥምርታ በተመለከተ ከ2013- 2015 ዓ.ም. 1፡35 ታቅዶ 1፡21፤ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የመምህራን ተማሪ ጥምርታ 1፡20 ታቅዶ 1፡19፤ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የመምህራን ተማሪ ጥምርታ 1፡18 ታቅዶ 1፡19 ማድረስ ተችሏል።
ከ2013- 2015 ዓ.ም. በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት የተማሪ የመማሪያ ክፍል ጥምርታ 1፡35 ታቅዶ 1፡39፤ በመጀመሪያ ደረጃ 1፡55 ታቅዶ 1፡ 45፤ በሁለተኛ ደረጃ 1፡40 ታቅዶ 1፡49 ደርሷል።
በቅድመ አንደኛ ደረጃ እና በ1ኛ ደረጃ ትምህርት መጠነ ማቋረጥ የቀነሰ ሲሆን በተለይ በ1ኛ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል። ይህም ለቅድመ 1ኛ እና 1ኛ ደረጃ የተሰጠው የምገባ ድጋፍ ውጤታማ እንደሆነ ማሳያ ነው።
የትምህርት መጠነ መድገምን መቀነስ በተመለከተ በሁለት የዕቅድ ዓመታት (ከ2013- 2014 ዓ.ም.) በመጀመሪያ ደረጃ (1-8) ትምህርት ተማሪዎች መጠነ መድገም በ2012 ዓ.ም. ከነበረበት 3.8% በ2014 ዓ.ም ወደ 3.12% ታቅዶ 1.6% (195%) ዝቅ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ከ5 ዓመት ዕቅድ አንጻር ሲታይ ከ100% በላይ መሆኑን ያሳያል። በሁለተኛ ደረጃ በ2012 ዓ.ም. ከነበረው 9.7% በ2014 ዓ.ም ወደ 4% ለማድረስ ታቅዶ 2.42% (165%) ዝቅ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ከ5 ዓመት ዕቅድ አንጻር ሲታይ ከ100% በላይ ሆኗል።
የትምህርት መጠነ ማለፍ በተመለከተ በሁለት የዕቅድ ዓመታት (ከ2013- 2014 ዓ.ም.) በ8ኛ ክፍል ትምህርት ተማሪዎች መጠነ ማለፍ በ2012 ዓ.ም. ከነበረበት 50.5% በ2014 ዓ.ም. ወደ 58.24% ታቅዶ 64% (110%) ማከናወን ተችሏል።
በዜጎች ተኮር ልማት ከተማ አስተዳደሩ በአመቻቸው የምገባ ሥርዓት እና የመማሪያ ቁሳቁስ መሟላት ምክንያት፣ ቤት ይውሉ የነበሩ በርካታ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት በመግባታቸው የተማሪ ቅበላ ከ100% በላይ አድጓል። የተማሪ ወላጆች ኢኮኖሚያዊ ጫና ከማቃለል ባሻገር የተማሪ ውጤት ማሳደግ እና የቅድመ አንደኛ ደረጃ እንዲሁም የአንደኛ ደረጃ አቋራጭ ተማሪ ቁጥር መቀነስ ተችሏል። ዕድሜው ለትምህርት የደረሰን ዜጋ ሁሉ ከቅድመ 1ኛ እስከ 2ኛ ደረጃ በተቀመጠው የቅርበት፣ የቅበላና ተሳትፎ ስታንዳርድ መሠረት ምቹና አካታች በሆነ ትምህርት ቤት በፍትሐዊነት ማዳረስ በመቻሉ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ቅበላም ማሳደግ ተችሏል።
በቢሮው ትኩረት ከተሰጠባቸው መስኮች መካከልም ውስጣዊ ብቃትን ማሟላት፣ ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ፣ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ እና የትምህርት ሥርዓት ዐቅምን መገንባት ቢሆንም የትምህርት ፍትሐዊነትን የማረጋገጥ ተግባር ቅድሚያ ትኩረት አግኝቶ እየተሠራበት ይገኛል። የትምህርት አሰጣጡን በማዘመን እና በዕውቀትና በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት የከተማ አስተዳደሩ እየሠራቸው ያሉ ሥራዎች እጅግ አበረታች ውጤት ተገኝቶበታል።
ዘመን መፅሄት ነሃሴ 2015