የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልብ

ኅብረብሔራዊነቷ ትንሿ ኢትዮጵያ የሚል ስያሜን የአጎናጸፋት አዲስ አበባ የሀገራችን የኢኮኖሚ ማዕከልም ናት። በከተማይቱ የሚሰበሰበው ከፍተኛ ገቢ፣ ግዙፍ የገበያ እንቅስቃሴ፣ የትራንስፖርት ትስስሩና ቱሪዝም ወዘተ… የአዲስ አበባን የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማእክልነት አጉልተው ያሳያሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማዋ ለሀገራችን የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት የምታደርገው አበርክቶ የላቀ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ይህን ሚናዋን የበለጠ ማጎልበት የሚያስችሉ በርካታ የልማት ሥራዎችን ሠርቷል፤ እየሠራም ይገኛል። በከተማችን የተጀመሩና በተወሰነላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ አምረው የተጠናቀቁ ትላልቅ ፕሮጀክቶች የከተማ አስተዳደሩ ብሎም የመላው አመራርና ሠራተኛ ጉልህ የትጋት ማሳያ ናቸው። ማኅበራዊ ፍትሕን ለማስፈን፣ በሕዝቦች መካከል የቆየውን የመደጋገፍ ዕሴት ለማጽናት የተሠሩና ዛሬም የቀጠሉ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችም የከተማ አስተዳደሩና የለውጡ ዘመን መገለጫዎች ናቸው ማለት ይቻላል። ሌሎችም በከተማዋ የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት አዲስ አበባን በማስዋብ፣ ኢኮኖሚዋን በማንቃት፣ በዓለም መድረኮች እንድትታይ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚናን ተጫውተዋል።

በ2015 በጀት ዓመት የአዲስ አበባ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች

 • 2000 ፀረ ሰላም ኃይሎች በሕግ ተጠያቂ ተደርገዋል
 • 21 ወረዳዎች ስማርት ሆነዋል
 • 112 ሚሊዮን 754 ሺህ ተማሪዎች ቅበላ ተደርጓል
 • 28 የጤና ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ 3 ሆስፒታሎች እተገነቡ ነው
 • 39 ቢሊዮን ብር ከውጪ ሀገር ቱሪስቶች ገቢ ተገኝቷል
 • 416 ሺህ 999 የሥራ ዕድል ተፈጥሯል
 • 415 ሺህ 923 ዜጎች የምግብ ዋስትና ተጠቃሚ ሆነዋል
 • 172 የቅዳሜና እሑድ ገበያዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን ለነዋሪው አቅርበዋል
 • 4 ሚሊዮን ዳቦ በቀን የማምረት ዐቅም ተፈጥሯል
 •  

የከተማዋ ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤ ከዘመን መጽሔት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳብራሩት፣ የመዲናይቱን የኢኮኖሚ ዐቅም ለማጎልበት የማምረት አቅሟን ማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል። መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ ባለሀብትነት እንዲያድጉ ተደርጓል። ትላልቅ የሥራ ዕድል የፈጠሩና ኢኮኖሚውን የሚያሳልጡ የማምረቻና የመሸጫ ሥፍራዎችንም በኢንደስትሪ ፓርክ ደረጃ መገንባት ተችሏል። መልከ ብዙ ሚና ያላቸው ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶችም በመገንባት ላይ ይገኛሉ።

 • የአዲስ አበባን ኢኮነሞሚያዊ አንቅስቃሴ በተመለከተ ከዘመን መጽሔት ጋር ቆይታ ደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩ ያልተስተካከለ የግብይት ሥርዓት ያመጣውን ሰው ሠራሽ ችግር ለመቅረፍ፣ ምርት ወደ አዲስ አበባ እንዲገባ በማድረግ ትልቅ ሥራ ሠርቶ ትልቅ የሚባል ውጤት ተገኝቶበታል። በተጨማሪም ታክስ የማይደረጉና ሌላው ነጋዴ ከሚሸጥበት ዋጋ አንጻር ከ20 እስከ 30 ከመቶ የዋጋ ልዩነት ያላቸው 179 የእሑድ ገበያዎችን በመክፈት እሑድና ቅዳሜ ሕዝቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ የፍጆታ ሸቀጦችን እንዲሸምት እየተደረገ እንደሚገኝም አንሥተዋል።
 • በንግድ ዘርፍ፣ ከተማ አስተዳሩ በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ የንግድ አሠራር በመዘርጋ በከተማዋ ዘመናዊ፤ ፍትሐዊና በውድድር ላይ የተመሠረተ የንግድ ሥርዓት የማስፈን ተልዕኮ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ በመካከለኛ ዘመኑ ዘመናዊ፣ ተደራሽና ቀልጣፋ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሠራርን ማሻሻል፣ የንግዱንና የሸማቹን ኅብረተሰብ ዐቅም ማሳደግ፣ በግል ባለሃብቱና በመንግሥት አጋርነት ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት እንዲገነቡ መደረጉንም ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘ ሪፖርት ያመለክታል።
 • በየዘርፉ በርካታ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ስታደርግ የቆየችው መዲናችን አዲስ አበባ ገቢዋ እመርታዊ ለውጥ ማሳየቱን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ በ2010 ዓ.ም የከተማዋ ዓመታዊ ገቢ 30 ቢሊዮን የነበረ ሲሆን፣ በ2015 ዓ.ም የ79 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቶ 109 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል። በቀጣዩ 2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ደግሞ 140 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነውን ለካፒታል ፕሮጀክት ለማዋል ታስቧል። የበጀት ብክነትና አስተዳደራዊ ወጪዎችን እየቀነሰ በጀትን ለዘላቂ ልማት ለማዋል አስተዳደሩ ጠንክሮ እነደሚሠራ ነው ክብርት ከንቲባዋ የገለጹት።
 • ከነፍስ ወከፍ ገቢ አንጻር ደግሞ በሪፖርቱ እንደተገለጸው፣ የከተማዋ አመታዊ ጠቅላላ የምርትና አገልግሎቶች ቋሚ ዋጋ ግምት ለጠቅላላ ነዋሪዎች ተካፍሎ የሚገኝ አማካይ ዓመታዊ ገቢ ወይም ነፍስ ወከፍ ገቢ በ2012 በጀት ዓመት ከነበረበት ብር 149ሺ 801፣ በ2015 ወደ ብር 178ሺ 18 ብር አድጓል።
 • ለኢንተርፕራይዞች እና ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የተቀናጀና ውጤታማ ድጋፍ በማድረግ የምርት ጥራት እንዲያረጋግጡና ምርትና ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንዲችሉ በተሠራው ሥራ፣ በሦስት ዓመታት ወደ ውጪ ገበያ ምርቶቻቸውን የሚልኩ ኢንተርፕራይዞች ቁጥር መጨመሩም በሪፖርቱ ተመላክቷል።
 • ክብርት ከንቲባዋም፣ ከተማሪዎች ምገባና ሌሎችም ሰው ተኮር ሥራዎች ጋር ተያይዞ የተሠሩ ሥራዎችን አስመልክቶ እንደገለጹት፣ የሰው ተኮር ሥራዎች አንደኛው ዓላማ መላው የከተማዋ ነዋሪ ከከተማዋ በሚገኘው ገቢ ተጠቃሚ መሆን አለበት የሚለው ሲሆን፣ በዚህም አዲስ አበባን ሰው ተርቦ የማያድርባት ከተማ ማድረግ የተቻለበት ትልቅ ስኬትመሆኑን አስምረውበታል።
 • ድጎማን በተመለከተ 

1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለሕዝብ ትራንስፖርት

 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለተማሪዎች ምገባና የትምህርት ቁሳቁስ

 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለሰብል ምርቶች

2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለመንግሥት ሠራተኞች መኖሪያና ካፍቴሪያ

300 ሚሊዮን ብር ዐቅም ለአነሳቸው ዜጎች ሕክምና

300 ሚሊዮን ብር ለሸገር ዳቦ

በድምሩ 9 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ድጎማ ተደርጓል::

120 ሺህ 167 ቶን የሰብልና የእንስሳት ምርት በከተማ ግብርና ተመርቷል፡፡

97 ነጥብ 82 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰበስቧል፡፡

ለ2 ሺህ 877 ባለሃብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡

5 ሺህ 256 የመንገድ፣ የውሃ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የሼዶች እና የስፖርት ማዘውተሪያ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ተመርቀዋል፡፡

በአለፉት ሦስት ዓመታት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህልን ለማጎልበት ከተከናወኑ ተግባራት በተፈጠረ ግንዛቤ እና የኅብረተሰብ ንቅናቄ ሥራዎች ምክንያት፤ በቤት እድሳት፣ በማዕድ ማጋራት፣ በደም ልገሳ፣ በመንገድ ትራፊክ አገልግሎት፣ በችግኝ ተከላ፣ በአካባቢ ጽዳት ወዘተ…. በመሳሰሉ ተግባራት ላይ የከተማችን ነዋሪዎች ተሳትፏቸው እያደገ መምጣቱ እንዲሁም በየደረጃው (ከማዕከል እስከ ወረዳ ድረስ) በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ተሳትፎ ለአደረጉ አካላት የሚሰጡ ዕውቅናና ሽልማቶች ይበልጥ የኅብረተሰቡን የበጎ ፈቃደኝነት ባህል እንዲጎለብት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነ በዕቅድ አፈጻጸሙ ተመላክቷል።

ቀልጣፋና ጥራቱን የጠበቀ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሥርዓት በመዘርጋት ረገድ በተለይ በአለፉት ሦስት ዓመታት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት አቅርቦትን ለማሳደግ በተሠራው ሥራ ዕድገት ተመዝግቧል። የመንገድ የትራፊክ ፍሰት እና ደኅንነትን በማሻሻል፣ የትራፊክ አደጋዎችን ከመቀነስ አንጻር የእግረኞች እንቅስቃሴ በሚበዙባቸው አካባቢዎች የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ በአለፉት 3 ዓመታት ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን በጥናት በመለየት የቦላርድና ብረት አጥር ሥራዎችን የማስፋፋት ሥራ ተከናውኗል። ይህም የሚከሠቱ የትራፊክ አደጋዎች እየቀነሱ እንዲሄዱ አስችሏል።

ከአዲስ አበባ ፈጣን ዕድገት ጋር እያደገ የመጣው የነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ጋር ተመጣጣኝ ምላሽ ለመስጠትና የቤት አቅርቦት ለማሟላት በተለያዩ የቤት አማራጫች ማለትም በኅብረት ሥራ ማኅበር፣ በግለሰቦች፣ በመንግሥት እና የግል ዘርፍ አጋርነት እንዲሁም በሪል ስቴት መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል። በኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚገነቡ ቤቶችን በተመለከተ የ2005 ዓ.ም 40/60 እና 20/80 ፕሮግራም ተመዝጋቢዎችን በ57 ማኅበራት እንዲደራጁ በማድረግ የግንባታ ቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቋል።

ከተማ አስተዳደሩ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ሥርዓትን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመገንባት ይዞት በነበረው ዕቅድ መሠረት፣ የመሬት አስተዳደር ሥርዓቱ በከተማ ደረጃ የሚመራበት ከካዳስተርና የአድራሻ ሥርዓት ከግንባታው ጋር የተናበበ ወጥ የሆነ የሕግ ማሕቀፍ እንዲዘጋጅ፣ እንዲጸድቅና እንዲተገበር በማድረግ በከተማው ወሰን ውስጥ የሚገኙ ቁራሽ መሬቶች እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሰነድ እና በመስክ አረጋግጦ መመዝገብ ችሏል።

ሌላው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ከተማዋን በዓለም አቀፍ መድረኮች እንድትታይ ያስቻሉ ሥራዎችን መሥራቱና ይህም ውጤት ማስገኘቱ ነው። አስተዳደሩ ከከተማ ገጽታ ግንባታ አንጻር ከውጭ እና ከሀገር ውስጥ ግንኙነት ሥራዎችን ለማሳደግ ከ14 ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ዐቅዶ ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ አሳክቶ ከ14 ተቋማት ጋር ግንኙነት መፍጠር ተችሏል። እንዲሁም ከ4 አዲስ የእኅት ከተማ ግንኙነት ለመመሥረት ታቅዶ ከ4 ከተሞች ጋር አዲስ የእኅት ከተማ (Sister City) ግንኙነት መመሥረት ችሏል። ከ16 አዲስና ነባር እኅት ከተሞች ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ዐቅዶም ከ9 የእኅት ከተሞች ጋር ጠንካራ ግንኙነት በማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን በጋራ ከውኗል።

በሂደት ላይ ካሉ ፕሮጀክቶች

ዓድዋ ሙዚየም 86 በመቶ

የትራንስፖርት ተቋማት ቢሮ 61 ነጥብ 5 በመቶ

የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ 71 ነጥብ 2 በመቶ

የየካ 2 መኪና ማቆሚያ 48 ነጥብ 2 በመቶ

አዲስ አፍሪካ ኤግዚቢሽን ማዕከል 80 በመቶ

አቃቂ ዓለም አቀፍ ስታዲየም 80 በመቶ ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

186 ነጥብ 52 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብንጹሕ ውሃ ተመርቷል፡፡

130 ሺህ ቤቶችን ሥራ በማጠናቀቅ ባለዕድለኞች እንዲገቡበት ተደርጓል፡፡

5000 ተገጣጣሚ ቤቶች ሥራ 30 በመቶ ተጠናቋል፡፡

6 ሺህ 415 ቤቶች ተገንብተው ለዐቅመ ደካማ ነዋሪዎች ተሰጥተዋል፡፡

በዚህም ከእሥራኤል ካምፓኒ በደንበኞች አገልግሎት (Customer Service) ዙሪያ ነጻ የቴክኖሎጂ አማራጭ አቅርቦ በከተማዋ ተቋማት ላይ ተግባራዊ እንዲሆን ስምምነት ላይ ተደርሷል። በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ ከፉጂያን ክፍለ ሀገር (ቻይና) ጋር አዲስ የእኅት ከተማ ጉድኝት ለመፍጠር የሚያስችል አጠቃላይ ቅድመ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ከተማ አስተዳደሩን በመወከል፣ በቻይና ቤጂንግ ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቆንጽላ ጽ/ቤት የስምምነት ሰነድ እንዲፈርም ተደርጓል።

በተጨማሪም፣ በከተማዋ የMilan Urban Food Policy Pact አባል እንድትሆን በማድረግና በዓለም አቀፍ ደረጃ የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብርን በስፋት በማስተዋወቅ በብራዚል ሪዮ ዴጄኔሪዮ ከተማ በተካሄደው የ2022 Milan Urban Policy Pact Awards ውድድር ከ133 ከተሞች መካካል አዲስ አበባ አሸናፊ ሆናለች።

ጉዟችን ሩቅ መዳረሻችን ብልጽግና ነው ያሉት የከተማዋ ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤ፣ በከተማችን የመጡ ለውጦች፣ መሥራትና ተግዳሮቶችን ማለፍ እንደምንችል ማሳያ እንጂ በራሳቸው በቂ ውጤት ናቸው ብለን ሳንረካ ያለድካም ለኢትዮጵያ ብልጽግና እንሠራለን ብለዋል!

 •  130 ሄክታር አዳዲስ አረንጓዴ ቦታዎች የማልማትና ማስዋብ ሥራ ተሠርቷል፡፡
 • 110 የአንበሳና 200 የሸገር ዘመናዊ አውቶቡሶች ተገዝተው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡
 • 90 ሄክታር በሕገ ወጥነት የተያዘ መሬት ወደ መሬት ባንክ እነዲገባ ተደርጓል፡፡
 • ለ3 ሺህ 451 አርሶ አደሮች የመኖሪየና የእርሻ ቦታ ማረጋገጫ ተሰጥቷል፡፡
 • 16 ሺህ እናቶች በትምህርት ቤቶችና በማኅበረሰብ ምገባ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡
 • 3 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ሀብት ከበጎ ፈቃደኞች ተሰባስቦ በዝቅተኛ ኑሮ ለሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደጎሟል፡፡
 • 7 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚገመት የበጎ ፈቃድ ሥራ ተከናውኗል፡፡
 • 632 ሚሊዮን 126 ሺህ ብር ለዓባይ ግድብ አስተዋፅኦ ድጋፍ ተደርጓል፡፡
 • 126 ሚሊዮን ብር በኮንሶና ቦረና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ተደርጓል፡፡ 

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

ዘመን መፅሄት ነሃሴ 2015

Recommended For You