ዋናው ነገር ጤና!

አሜሪካዊው ፈላስፋ ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን ‹‹ቀዳሚው ሀብት ጤና ነው›› የሚለውን ጥልቅ ሐሳብ እንደተናገረ ይገለፃል። በተለይ በዚህ ጉዳይ ላይ እ.ኤ.አ. በ1860 በቀረበው ትንተና በእርግጥም የዓለም ሕዝቦች የድህነትና ሀብት፣ የኋላ ቀርነትና ሥልጣኔ፣ የመታደልና ያለመታደል ዋነኛ ማነጻጸሪያ ጤናና የጤና ዋስትና ቀዳሚው መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል። በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ መሠረታዊ የሚባሉት ፍላጎቶች ምግብ፣ መጠለያና አልባሳትም ቢሆኑም እነዚህ ሁሉ ግን ያለጤና ከንቱ ናቸው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የጤና ጉዳይ የመኖር፣ የልማትና የብልጽግና መሠረት መሆኑን አጽንዖት ሰጥቶ ለከተማዋ ነዋሪ የሚመጥን የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በአለፉት ጥቂት ዓመታት በትኩረት እየሠራ ይገኛል።

‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያዉ ሦስት ዓመት (2013-2015 ዓ.ም.) የልማት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት›› ላይ እንደተገለጸው፤ የከተማ አስተደደሩ ጤና ቢሮ የአገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽነትን ለማስፋፋት የተመላላሽ ሕክምና ተጠቃሚ ኅብረተሰብ ቁጥርን በ2010 ዓ.ም. በጀት ዓመት እኩሌታ ከነበረው 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዓመታዊ አሐዝ በ2015 ዓ.ም. ወደ 9 ነጥብ 5 ሚሊዮን በማሳደግ ከፍተኛ የተደራሽነት መሻሻልን ማምጣት ችሏል።

የአስተኝቶ ሕክምና ታካሚዎች ቁጥርንም በ2010 ዓ.ም. ከነበረው 149 ሺህ 596 በአሁኑ ጊዜ ወደ 197 ሺህ 386 ማሳደግ ተችሏል። በጤና ተቋማት የታዘዙላቸውን መድኃኒቶች በዚያው የመንግሥት ጤና ተቋም ውስጥ 100% ያገኙ ተገልጋዮች በመቶኛ በ2010 ዓ.ም. ከነበረው 60 በመቶ አፈጻጸም በ2015 ዓ.ም. ወደ 84 በመቶ አድጓል። አጠቃላይ ኦፕሬሽን ያገኙ ተገልጋዮች ብዛት በ2010 ዓ.ም. በጀት ዓመት እኩሌታ ከነበረው 38 ሺህ 429 በ2015 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት ብቻ ወደ 54 ሺህ 638 በማሳደግ የኦፕሬሽን አገልግሎት የሚፈልጉ ታካሚዎች ይበልጥ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በስፋት ተንቀሳቅሶበት ውጤት ከተመዘገበበት ዘርፍ አንዱ በሆነው በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ፕሮግራም ይበል የሚያሰኙ ተግባራት ተፈጽመዋል። በ2010 ዓ.ም. በጀት ዓመት እኩሌታ ከነበረው 10 ወረዳዎች ሽፋን፤ 15 ሺህ886 አባወራዎችና 71 ሺህ 487 አጠቃላይ የአባልነት ሽፋን፣ በ2015 ዓ.ም. ሁሉንም ወረዳዎች በማጠቃለል የአባዎራዎችን ቁጥር ወደ 271 ሺህ 038 እንዲሁም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ኅብረተሰብን ወደ 2,002,130 አባላት ማድረስ ተችሏል። በ2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት የከተማ አስተዳደሩ የድሃ ድሃ ተናጠል ድጎማ እና 50 በመቶ ለእያንዳንዱ ከፋይ አባል በድምሩ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ድጎማ በማድረግ ለፕሮግራሙ መሳካትና ለኅብረተሰቡ ተጠቃሚነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል።

የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ከማሻሻል አንጻር በተመለከተም የአስተኝቶ ሕክምና ታካሚዎች ሞት መጠን በ2010 ዓ.ም. በጀት ዓመት እኩሌታ ከነበረበት 3 ነጥብ 9 በመቶ፣ በ2015 ዓ.ም. ወደ 2 በመቶ መቀነስ ተችሏል። እንዲሁም የድንገተኛ ታካሚዎች ሞት መጠንን ከነበረው 0 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 0 ነጥብ 5 በመቶ በመቀነስ የሚሰጠው አገልግሎት ጥራትከጊዜ ወደ ጊዜ ከመሻሻሉ በተጨማሪ የሞት ምጣኔ አመላካቾቹ የዓለም ጤና ድርጅት የአስቀመጣቸውን ስታንዳርዶች በአግባቡ አሳክቷል።

በጤናው ዘርፍ ሌላው ተጠቃሽ ስኬት የአበበች ጎበና እናቶችና ሕፃናት ሕክምና መስጫ ማዕከል ነው። ማዕከሉ፤ የእናቶችና ሕፃናት ጤናን ከማሻሻል፣ አገልግሎቱንም ይበልጥ ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ የወሊድ አገልግሎት ለማግኘት ረጅም ርቀት ይጓዙ ለነበሩ እናቶች የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት የእናቶችና ጨቅላ ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ ሥራዎችን በስፋትና በጥራት ለማድረስ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ከተማ አስተዳደሩ ባደረገው ቁርጠኛ ውሳኔ ለሌላ ዓላማ ይውል የነበረውን ይህን ግዙፍ ማዕከል ለሕክምና አገልግሎት እንዲሆን በመወሰን በ400 አልጋዎች ለእናቶችና ለሕፃናት ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ማዕከሉ ከተመሠረተ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለ35 ሺህ 996 እናቶች የወሊድ አገልግሎት መስጠት ችሏል።

ጤና ጣቢያዎች የቀዶ ሕክምና የማወለድ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል። በቀዶ ሕክምና የማዋለድ አገልግሎት ፍላጎትን ለማሟላት የማዋለድ ምጣኔያቸው ብዙ በሆኑ፣ በተመረጡና ከሆስፒታሎች ርቀት ላይ ባሉ ጤና ጣቢያዎች ተጀምሯል። ሥራው እየተከናወነ ያለው ከተለያዩ ሆስፒታሎች ጋር ትስሥር በመፍጠርና የባለሙያ ዝውውሮችን በማካሄድ ከዚህ ቀደም አገልግሎቱ ከሚሰጥባቸው አካባቢዎች ተሞክሮ በመቅሰም ነው። አገልግሎቱ የእናቶችና የሕፃናት ሞት ለመቀነስ ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ ባሻገር የጤና ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ለማሳካት ይረዳል።

የእናቶችን ጤና አገልግሎት ለማሻሻልና ሞትን ለመቀነስ በ19 ጤና ጣቢያዎች የኦፕሬሽን ማዋለድ አገልግሎት(C/S Delivery) እየሰጡ ይገኛሉ። የሕፃናት ጤናን ከማሻሻል አንጻር በአለፉት ሦስት ዓመታት ለ235 ሺህ 893 (100%) ሕፃናት ሁሉንም ክትባት ለመስጠት ታቅዶ ለ345 ሺህ 142 (146.3%) ሕፃናት መስጠት ተችሏል። ለአፈጻጸሙ ከፍተኛነት በዘመቻ ወቅት ክትባት ያላገኙ ሕፃናትን የማፈላልግ ሥራ መሠራቱና የክትባት አቅርቦት ማሻሻል መቻሉ ይጠቀሳሉ።

ቤት ለቤት የወላጆች የምክር እና የዐቅም ግንባታ 5 ሺህ ሴት ወጣቶችን እና 67 የክትትል እና ድጋፍ ባለሙያዎችን (Supervisors) በሌቭል ደረጃ 2 በማሠልጠን ወደ ሥራ ተገብቷል። በዚህም ከፅንስ እስከ 6 ዓመት ባለው የሕፃናት ዕድገት ጊዜ ውስጥ ሕፃናት ጤናማ አካላዊ እና አእምሯዊ ዕድገት እንዲኖራቸው፣ የሥርዓተ ምግብ ልየታ፣ ክትባትና ሌሎች የቤት ለቤት ክብካቤዎችን በሁሉም ጤና ጣቢያዎች እየተተገበረ ይገኛል። በዚህም ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ እስከ ዘንድሮ 2015 ዓ.ም. ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕፃናትና ወላጆች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል።

በመድኃኒት አቅርቦት በኩል ሕይወት አድን መድኃኒት አቅርቦት በ2013 ዓ.ም.(92%)፣ በ2014 ዓ.ም.(85%)፣ በ2015 ዓ.ም.(92%) መሆኑን ያሳያል። አስፈላጊ ወይም ኢሴንሻል መድኃኒት አቅርቦት ደግሞ በ2013 ዓ.ም(86%)፣ በ2014ዓ.ም(89%)፣ በ2015 ዓ.ም (90%) በመቶ አቅርቦት እንዲኖር ተደርጓል።

በሀገራችን እንዲሁም በከተማችን ያለውን ከፍተኛ የዐይን ሕክምና አገልግሎት ፍላጎት ጥያቄ ለመመለስ በዳግማዊ ሚኒልክ ሪፈራል ሆስፒታል የዐይን ሕክምና ማዕከል ለመመሥረት አዲስ ግንባታ ተከናውኗል። ማዕከሉ በዘመናዊ መልኩ ተቋቁሞ ግብአቶች ተሟልተውለት ከመስከረም 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ እንዲጀምር ተደርጓል። የአገልግሎት ማስፋፍያ ከተደረገለት ጊዜ ጀምሮ የተመላላሽና አስተኝቶ ሕክምና ክፍልን በ4 እጥፍ፣ የኦፕሬሽን አገልግሎት መስጫ ክፍልን በ2 እጥፍ አሳድጓል። በያዝነው 2015 ዓ.ም. በአጠቃላይ ለ72,991 ታካሚዎች አገልግሎት መስጠት ተችሏል።

የኩላሊት ሕክምና ተገልጋዮች ከኩላሊት እጥበት ጋር በተያያዘ ይገጥማቸው የነበረውን ወረፋና እንግልት ለመቀነስ ከ2014 ዓ.ም. ነሐሴ ወር ጀምሮ በዳግማዊ ምኒልክ ሪፈራል ሆስፒታል ከአጋር ድርጅት ጋር በመተባበር(Public Private Partnership) የኩላሊት እጥበት ማዕከልን በተደራጀ መንገድ ማቋቋም ተችሏል። በዚህም ተጨማሪ 30 ማሽኖችን በመጨመር ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለ108 ታካሚዎች 31,000 ጊዜ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት ተሰጥቷል። የከተማ አስተዳደሩ ዐቅማቸው ለማይችሉ የኩላሊት ታካሚዎች ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ በመፈፀም ነጻ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል።

በጤናው ዘርፍ የተጀመሩና በሂደት ላይ ያሉ የግንባታ ሥራዎችን በተመለከተ የኅብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ጥያቄ ይበልጥ ለማርካትና ተደራሽነትን በይበልጥ ለማስፋፋት በኮልፌ፣ በንፋስ ስልክ እና በቦሌ ክፍለ ከተማዎች ውስጥ ሦስት አጠቃላይ ሆስፒታሎች በግንባታ ላይ ይገኛሉ። እነዚህም ሆስፒታሎች እያንዳንዳቸው ከ450 በላይ የአስተኝቶ ሕክምና አልጋ የሚኖራቸው ሲሆን ዘመኑን በዋጁ እጅግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እንዲገነቡና እንዲደራጁ ተደርገው ወደ አገልግሎት የሚገቡ ይሆናሉ።

ነባር ሆስፒታሎችንም ከማስፋፋት አንጻር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሥር የሚገኘው የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ማስፋፊያ ሕንጻ ግንባታ Basement+G+8 ሲሆን ይህም 1.6 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞለታል። በአሁኑ ጊዜ ግንባታው ተጀምሮ በሂደት ላይ ይገኛል። ግንባታው ሲጠናቀቅ አገልግሎት ከማስፋፋትና ጥራትን ከማሻሻል አንጻር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግም ይጠበቃል። በጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ድንገተኛ አደጋዎችን እና ተያያዥ የጤና እክሎችን(Trauma Center) በተቀላጠፈ መንገድ የሕክምና አገልግሎት መስጠት ያስችል ዘንድ G+6 (ባለ2 ቤዝመንት) ሕንጻ ግንባታ 50% ደርሷል። ሲጠናቀቅም በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ የሚፈጠሩ ድንገተኛ አደጋዎችን በአፋጣኝና በጥራት አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል።

ዘመን መፅሄት ነሃሴ 2015

Recommended For You