አዲስ አበባ ከተማ ከባህር ጠለል በላይ በሦስት ሺሕ ሜትር ከፍታ ላይ ትገኛለች። የአየር ጠባይዋ ለነዋሪዎቿም ሆነ ለእንግዳ ጎቢኝዎች ተስማሚና ተመራጭ ነው። አዲስ አበባ ከሌሎች የአፍሪካ ከተሞች አመሠራረት በተለየ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን የተቆረቆረችና የለማች ከተማ መሆኗን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህች የአፍሪካ መዲና በየዘመኑ የተከሠቱትን አዳዲስ የሥልጣኔ ውጤቶችን በመቀበልና በመላ ሀገሪቱ በማሠራጨት የተጫወተችው ሚና ከፍተኛ ነው።
ከአዲስ አበባ ከተማ መመሥረት ጥቂት ጊዜ በፊት እ.ኤ.አ በ1884 ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ እንጦጦን የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አድርገው ነበር። ከጊዜያት በኋላ ግን እንጦጦ የማያረካ ሆኖ ተገኘ። የዚህም ዋናው ምክንያቱ ቀዝቃዛ አየር፣ የውሃ እጥረትን የመሳሰሉ ነገሮች ነበሩ።
እ.ኤ.አ በ1886 አዲስ አበባ የሸዋ ግዛት ዋና ከተማ ሆነ። እ.ኤ.አ በ1887 ምኒልክ የባለቤታቸውን ቤት ቤተ መንግሥት ይሆን ዘንድ ሰፊ አድርገው አሠሩት። ይህም ቦታ እስከዛሬ ድረስ የመንግሥት መቀመጫ ነው። እ.ኤ.አ በ1889 ምኒልክ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሲሆኑ አዲስ አበባም የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆነች። ከተማይቱም በፍጥነት ማደግ ጀመረች። አካባቢው ይማርክ የነበረው መኳንንትን ብቻ አልነበረም። ነገር ግን ባለሙያዎችን፣ ነጋዴዎችንና የውጭ ጎብኚዎችንም ይማርክ ነበር።
አዲስ ማለዳ እ.አ.አ. ታኅሣሥ 12 ቀን 2018 አዲስ አበባን በተመለከተ ባሥነበበው ጽሑፍ ፒትር ጋረስተን የተባሉ የታሪክ አጥኚ ስለከተማዋ ያስቀመጡትን ምልከታ ይዞ ወጥቷል። የታሪክ አጥኚው ለሦስተኛ ዲግሪ (PhD) ማሟያቸው ‹የአዲስ አበባ ታሪክ ከጽሕፈትዋ 1879 እስከ 1902› በሚል ርእስ ያቀረቡት የጥናት ጽሑፍ አዲስ አበባ አገር በቀል (indigenous) ከተማ እንደሆነች ያትታል። ይሄው ጥናታዊ ጽሑፍ በመደምደሚያ ክፍሉ አዲስ አበባ እንዴት በጊዜ ሒደት ለንጉሣዊው ግዛት የምጣኔ ሀብት እምብርት እየሆነች እንደመጣች ዘርዝሮ አስቀምጧል።
ዕውቁ የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስ ‹ሚኒልክ እና የአዲስ አበባ መቆርቆር› በሚል ርእስ እ.ኤ.አ. በ1961በጻፉት ጥናታቸው እንደሚነግሩን፥ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ በማገዶ እጥረት የተጠቃችውን አዲስ አበባን በአዲስ ዓለም ሊተኳት አስበው ነበር። ዐፄው ቤተ መንግሥታቸውን በአዲስ ዓለም ማሳነጽ ሲጀምሩ፣ የጣሊያን መልእክተኞች ለጋሲዮናቸውን “አይቀሬ” ወደምትመስለው ዋና ከተማ አዲስ ዓለም ቸኩለው አዛውረው ነበር። የሆነ ሆኖ ለማገዶ ፍጆታ የሚውል ቶሎ፣ ቶሎ የሚበቅል የባሕር ዛፍ ወደ ኢትዮጵያ በመግባቱ የማገዶ ችግሩ በመቀረፉ እንዲሁም ውኃ ከጉድጓድ ማውጣት እና በቧንቧ ማጓጓዝ በመቻሉ፣ እና ሌሎችም የመገናኛ ዘዴዎች ወደ አገር ውስጥ በፍጥነት በመግባታቸው አዲስ አበባ ዘለቄታን አግኝታለች።
በ1900ዎቹ ገደማ የአዲስ አበባ ሕዝብ 65,000 ገደማ እንደነበር ሪቻርድ ፓንክረስት ዶክተር መረብ ‹ኢምፕሬሽን ደ ኢትዮፒ› በሚል የጻፈውን መጽሐፍ ጠቅሰው ዘግበዋል።
በአዲስ አበባ የመጀመሪያዎቹ ነዋሪዎች ቤታቸውን ክብ ቅርፅ ባለው ጎጆ መልክ ይሠሩ ነበር። ግድግዳውን ከሳር ጋር በተቀላቀለ ጭቃ እንጨት ላይ ተጣብቆ፣ ጣራውም የሳር ክዳን ነበር። የአዲስ አበባ ሕዝብ ቁጥር መጨመር የጀመረው ብዙ ሰው ከገጠር ወደ ከተማ ባደረገው ፍልሰት ነበር። ይህም የታቀደበት አልነበረም። በዚህ ጊዜ ነበር መኳንንቱ አንድ ቦታ ላይ ለመስፈር ያተኮሩት።
ከጣሊያን ወረራ በፊትም ከተማው ጠንካራ መዋቅር የያዘ ነበር። በታሪክ አጥኚው በሪቻርድ ፓንክረስትም እይታ የአዲስ አበባ ሕዝብ ቁጥር የጨመረው በክፍለ ሀገር መሪዎችና በወታደሮቻቸው እ.ኤ.አ በ1892 በነበረው ድርቅ ምክንያትና በመጨረሻም በዓድዋ ጦርነት ምክንያት ነበር። ሌላው ምክንያት ደግሞ እ.ኤ.አ በ1902 የወጣው የመሬት ሕግና በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተጀመረው ባቡር፣ የታየው የትራንስፖርት ዕድገትና በ1909 ዓ.ም. የተቋቋመው ማዘጋጃ ቤት እንዲሁም ሌሎችም ዕድገቶች ናቸው። ከእነዚህ የከተማዋን ይዘት ከቀየሩ ተጠቃሽ ምክንያቶች መካከል የማዘጋጃ ቤት መቋቋምን በዝርዝር መመልከት ተገቢ ይሆናል።
የአዲስ አበባ ከተማ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እና የቆዳ ስፋት እያደገ በመምጣቱ እንዲሁም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ ከተማዋ የሚመጡ ባለጉዳዮችን በአግባቡ ለማስተናገድ በማስፈለጉ በ1909 ዓ.ም የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ተቋቋመ። የማዘጋጃ ቤት አስተዳደር ከተቋቋመም በኋላ ሊሎ ሽፋኑ በተባለ ፈንረሳዊ እና አድለቢ በተባለ ሶሪያዊ ግፊት ማዘጋጃ ቤቱ ዓድዋ ሲኒማ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ እንዲመሠረት ተደረገ። ማዘጋጃ ቤቱም የከተማው “የማኅበር ቤት” ተብሎ ይጠራ ነበር። ስያሜውየተሰጠውም ማዘጋጃ ቤቱ እንዲመሠረት ግፊት ሲያደርጉ በነበሩት በሶሪያው አድሊቢ ነው። በኋላም “የከተማ ማኅበር ቤት” የሚለው ስያሜ “municipality” የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል አይወክልም በሚል በኅሩይ ወልደ ሥላሴ አማካኝነት በ1920 ዓ.ም ማዘጋጃ ቤት የሚል ስያሜ እንደተሰጠው በታሪክ ሰፍሯል።
በወቅቱ የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ለአዲስ አበባ ከተማ ዕድገትና ለከተማዋ ሕዝብ ደኅንነት ሲባል የሚያከናውናቸውን ተግባራት በ16 ዋና ዋና ክፍሎች ከ250 ባልበለጡ ሠራተኞች ይፈጽም ነበር። የሥራ ክፍሎቹም የከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ የርስት ክፍል፣ የካርታ ማንሣትና የግምት ክፍል፣ የዳኝነት ክፍል፣ የአራዳ ዘበኛ የተሽከርካሪና የመንጃ ፈቃድ ክፍል/የቁማር ጨዋታ ቁጥጥር ክፍልን ጨምሮ/፣ የጽዳት ክፍል፣ የገንዘብና የሥራ መቆጣጠሪያ ክፍል፣ የምስጢር ክፍል/የሕክምና ክፍል ወይም ልዩ ጓዳ/፣ የውል ክፍል፣ የእሳትና አደጋ መከላከል ክፍልና የጋራዥ ክፍል የተባሉት ነበሩ። እነዚህ የሥራ ክፍሎች ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ እያንዳንዱ ክፍል ንኡስ ቅርንጫፎች ነበሩት። ማዘጋጃ ቤቱ ከላይ የተዘረዘሩት ዋና ዋና ክፍሎች ይኑሩት እንጅ ለከተማዋ ዕድገት የነበረው አስተዋፅኦ አመርቂ እንዳልነበር የተለያዩ ጽሑፎች ያስረዳሉ። የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ከከተማዋ ዕድገት ጋር ተያይዞ የመጣውን የነዋሪዎች ችግር ለማሻሻል እና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አደረጃጀት እና ሕንጻ በማስፈለጉ ዛሬ በማገልገል ላይ የሚገኘው ማዘጋጃ ቤት ሕንጻ ተገንብቷል።
አዲስ አበባ ከተቆረቆረች ጊዜ ጀምሮ ሌሎች ጉልህ የሥልጣኔ ተግባራት ተከሥተዋል። በአክሱም ነገሥታት ከታተሙት የመገበያያ ሳንቲሞች በኋላ ብሔራዊ ገንዘብ ታትሞ ለዝውውር የበቃውና የቴሌፎን አገልግሎት የተጀመረው ከአዲስ አበባ መመሥረት በኋላ በ1986 ዓ.ም ነው። በ1890 የሩስያ ቀይ መስቀል ሆስፒታል፣ በ1894 ዓ.ም. የኢትዮ ጅቡቲ የምድር ባቡር ኩባንያ፣ በ1897 ዓ.ም. የአቢሲንያ ባንክ፣ 1898 ዓ.ም. ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት፣ በ1900 ዓ.ም. የእቴጌ ጣይቱ ሆቴልና የመጀመሪያው ሲኒማ ቤት እንዲሁም በ1902 ዓ.ም. የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ሥራቸውን እንደጀመሩ በታሪክ ተመዝግቧል። የዘመናዊ መንገድ ግንባታና የመኪና መምጣት፣ የቧንቧ ውሃ መዘርጋት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መመሥረት፣ የትላልቅ ሕንጻዎች መገንባት፣ የዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት፣ ዩኒቨርስቲዎች መከፈት፣ የጤና ተቋማት መበራከት፣ የመንግሥት አስተዳደር ቅርጽ እየያዘ መምጣት አዲስ አበባን ወደ ሥልጣኔ ማዕከልነት ያሸጋገሯት የዘመኑ ክሥተቶች ናቸው።
እ.ኤ.አ በ1917 ራስ ተፈሪ መኮንን እንደራሴ ተደርገው ሲሾሙ የከተማው መዘመንና መስፋፋትም የሚያመጣውንጥቅምም ስለተረዱ ራሳቸውን እያሳደጉ ላሉ ሰዎች ሀብት ማከፋፈል ጀመሩ። እ.ኤ.አ በ1918 ግልፅ በሆነ ሁኔታ የእንደራሴነት ሥልጣንን አገኙ። እ.ኤ.አ በ1926 እና በ1927ም ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ አብዮት ተካሄደ። ከካፒታል መጨመርም ጋር ተያይዞ የቡና ምርት በከፍተኛ ምርት ተመረተ። በዚህም የተጠቀሙት መሪዎች አዲስ እና በድንጋይ የተገጠሙ ቤቶችን ገነቡ። ከአውሮፓ በአስመጧቸው የቤት ዕቃዎች ቤታቸውን አስዋቡ። አውቶሞቢሎች አስገቡ። እንዲሁም ባንኮችንም አስፋፉ።
እ.ኤ.አ በ1930 ዓጼ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ሲሆኑ በአዲስ አባባ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማስገባትና ግንባታዎችን ማከናወናቸውን ቀጥለዋል። ከእነዚህም መካከል የኤሌክትሪክና የስልክ መስመሮች ዝርጋታ እንዲሁም የተለያዩ ተቋማት ግንባታዎች ይጠቀሳሉ። ዶክተር ሺመልስ ቦንሣ “አዲስ አበባ፣ ከየት ወደየት?” በሚል ርእስ ባዘጋጁት ጽሑፍ እንደሚገልጹት፤ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ከተማዋ ዘመናዊ ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ሆና እንድትፈጠር ወይንም እንድታድግ አቅደው ይሠሩ ስለነበር አዲስ አበባ ከተማም፣ የሀገርም ምልክት ሆና በእሷ ውስጥ ኢትዮጵያን በኢትዮጵያ ውስጥም እሷ እንድትታይ ሆና ነበር የተቀረጸችው።
ጣሊያኖች ኢትዮጵያ ላይ ዳግም ወረራ ሲፈጽሙ እ.ኤ.አ. በ1936 ወታደሮቻቸው ቀኝ ይገዟት ከነበረችው ኤርትራ ተነሥተው አዲስ አበባ ገቡ። ከጅቡቲ ጋር የተሳሰረው የባቡር መንገድም ሳይሰበር ቆየ። ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ከያዙ በኋላ እ.ኤ.አ እስከ 1941 ድረስ አዲስ አበባን የጣሊያን ምሥራቅ አፍሪካ ዋና ከተማ አድርገው ቆይተዋል ።
እ.ኤ.አ በ1941 ሜጀር ኦርዴዊንጌት በኃይለ ሥላሴ የጌዲዮን ጦርና የኢትዮጵያ ነጻነት ተዋጊዎች አማካኝነት ኢትዮጵያ ከጣሊያን አገዛዝ ነጻ ወጣች። ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ከኢትዮጵያ ከወጡ በአምስት ዓመታቸው ተመለሱ። በከተማዋ እምብርት አራት ኪሎ ላይ የሚገኘውን ሚያዚያ 27 (የድል ሐውልት) እንዲሠራም አደረጉ። ኢትዮጵያ ነጻ ከወጣች በኋላ አዲስ አበባ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ቁጥር መጨመርና የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ገጠማት።
እ.ኤ.አ በ1946 ኃይለ ሥላሴ አዲስ አበባ የአፍሪካ ዋና ከተማ ትሆን ዘንድ ሞዴል ለማስያዝና ለማሳመር ታዋቂውን ማስተር ፕላነር ሰር ፓትሪክ አቤርክሮምቢን ጠሩት። አቤርክሮምቢ በተቀናጀ ሁኔታ ማስተር ፕላኑን ጀመረ። እ.ኤ.አ በ1943 ከነበረው የለንደን ትራፊክ ችግርም በመነሣት ማስተር ፕላኑን በዋናው የትራፊክ መንገዶች ሠፈሮችን በመከፋፈል ሠራው።
በኋላም የዐፄ ኃይለ ሥላሴ ህልም እውን ሆኖ እ.ኤ.አ በ1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረት እውን ሆነ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማ ዕከልነቷ አንድ ብሎ ጀም ሯል።
እ.ኤ.አ በ1974 ወታደራዊው ኃይል ደርግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በአዲስ አባባ ለሽያጭ ከተዘጋጁ ቤቶች ውስጥ ሁለት ሦስተኛው ወደ ኪራይ ቤት ተቀየረ። በ6 ነጥብ 7 በመቶ እያደገ የነበረው የሕዝብ ቁጥር ወደ 3 ነጥብ 7 በመቶ ቀነሰ። ሲኬ ፖሎኒ የተባለ ሀንጋሪያዊ አርክቴክትም የከተማይቱን ማስተር ፕላን እንዲሠራ በደርግ መንግሥት ተጠራ። ፖሎኒም መስቀል አደባባይን እንደአዲስ አስገነባው። የደርግ መንግሥትም መስቀል አደባባይን አብዮት አደባባይ በማለት ስሙን ቀየረው።
14ቱ ክፍለ ሀገራት በነበሩበት የደርግ ዘመን ደግሞ አዲስ አበባ እንደ 15ኛ ክፍለ ሀገር ትቆጠር ነበር። በ1980 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) ሲመሠረት ኢትዮጵያ የተካለለችው በ25 አስተዳደር አካባቢና በአምስት ራስ ገዞች ነበር። አዲስ አበባም ራሷን የቻለች የአስተዳደር አካባቢ እንድትሆን ተደርጎ ነበር። ደርግ በዘመኑ አዲስ አባባ ላይ (በተለይም አቃቂ አካባቢ) በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሠራተኞችን የሚያቅፉ በርካታ ፋብሪዎችን በማቋቋም በከተማዋ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
በ1983 ዓ.ም. ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ በ1984ዓ.ም. የሽግግር መንግሥት ሲመሠረት አዲስ አበባ ክልል 14 ተብላ የራሷ አስተዳደር እንዲኖራት ተደረገ። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) መንግሥት በ1987 ዓ.ም. እውን ሲሆን ክልልነቷ ቀርቶ በሕገ መንግሥቱ የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫ ዋና ከተማ መሆኗ ተደነገገ። በ1989 ዓ.ም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ራስን በራስ ማስተዳደር የምትችልበት ሕግ ወጥቶላት በአዲስ አበባ ቻርተር እየተዳደረች ትገኛለች።
በዘመነ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. አዲስ አበባ ብዙ መሻሻሎችን አሳይታለች። የከተማዋን ኗሪዎች የቤት ችግር ለመቅረፍ የኮንዶሚኒየም የቁጠባ ቤቶች በስፋት ተገንብተዋል። ከቀለበት መንገዶች ጀምሮ የተለያየ ደረጃ ያላቸው የአስፋልትና የውስጥ ለውስጥ የኮብልስቶን መንገዶች ግንባታ ተካሂዷል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጤና ጣቢያዎችና ትምህርት ቤቶች ተሠርተዋል። በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች በአንጻራዊነት ለነዋሪዎች የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ የአገልግሎት መስጫ ሕንጻዎች ግንባታ ተከናውኗል። ቤተ መጻሕፍትን ጨምሮ ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጡ የወጣት ማዕከላት በእያንዳንዱ ወረዳ ተከፍተዋል። ይሁንና ኢፍትሃዊነት አድልዎና በተለየም አርሶ አደሩን ማፈናቀል የሥርዓቱ ደክመት ሆኖ ለለውጥ ሕዝብን አነሣስቷል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ አዲስ አበባ በተለየ የዕድገት ጎዳና ላይ መጓዝ ጀምራለች። ሸገርን እናስውብ በሚል መሪ መልእክት ብዙ ፕሮጀክቶች በአዲስ አበባ ተሠርተዋል። በአምስት ዓመታት ውስጥ እንጦጦ የተፈጥሮ ፓርክ፣ አንድነት፣ ወዳጅነት ፓርክንና የሳይንስ ሙዚየምን የመሳሰሉ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰባቸው፤ ዘመኑን የዋጀ መሠረተ ልማት የተሟላላቸው እና እጅግ የተዋቡ የኗሪዎቿን እና ጎብኚዎቿን መንፈስ እያደሱ በደስታ የሚሞሉ መስሕቦች ባለቤት ሆናለች። የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ በቅጥር ግቢው ውስጥ አዳዲስ መገልገያዎችን በሚያካትት መልኩ ሙሉ ሕንጻው እድሳት ተደርጎለት የከተማዋ ምልክትነቱ ይበልጥ መጉላት ችሏል።
መስቀል አደባባይ የቀድሞ ይዘቱን ሳይቀይር ከመሬት ሥር ሁለት ወለል ወደ ውስጥ በመግባት፣ የመኪና ማቆሚያ እንዲሁም አደባባዩንና ጎዳናዎችን የማስዋብ ሥራ ተሠርቶለት ይበልጥ ግዝፈትን ነስቶ የከተማዋ ግርማ ሞገስ ሆኗል። በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ 10 ቤተ-መጻሕፍት መካከል አንዱ የሆነ፣ በ4 ወለሎቹ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን መጻሕፍትን መያዝ የሚችልና 1 ነጥብ 5 ኪ.ሜ መደርደሪያ የያዘ፣ በ19 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሁለገብ የሆነው አብርሆት ቤተ መጻሕፍት ተገንብቶላታል። 1400 ሜትር ስኩየር ስፋት የሚሸፍን ውስጣዊ ክፍል ያለው ድምፅ የማያስተላልፍ ቋሚ እና ጊዜያዊ የዐውደ ርእይ ቦታዎችን የያዘ የሳይንስ ሙዚየምም ባለቤት ሆናለች። በዓይነቱ ልዩ ከሆነው የሳር ቤት ጎፋ ማዞርያ የፑሽኪን ጎተራ ማሳለጫ ዘመናዊ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥተጠናቆ አግግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል።
ከላይ በወፍ በርር በተመለከትነው የታሪክ መንገድ ተጉዛ ዛሬ ላይ የደረሰችው አዲስ አበባ የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን አጠናክራ ቀጥላለች። በዓለማችን ከሚገኙ በርካታ ቁጥር ካላቸው ከተሞች በዲፕሎማቶች መቀመጫነት እንዲሁም በኤምባሲና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች መናኸሪያነት በአንደኛነት የምትጠቀሰው የአሜሪካዋ ኒውዮርክ ከተማ ስትሆን ጀኔቭ በሁለተኛነት ትከተላለች። ሦስተኛዋ ደግሞ የእኛዋ አዲስ አበባ ከተማ ናት። አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረትና የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ የበርካታ ሚሲዮኖችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ ናት። አዲስ አበባ የዲፕሎማቶች መኖሪያ ብቻ ሳትሆን የበርካታ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች፣ ኮንፈረንሶች፣ ወርክሾፖችና ኤግዚቢሽኖች የሚሰናዱባት እና የንግድ፣ የጤና፣ የልማት፣ የኢንቨስትመንት፣ የሰላምና የጸጥታ ጉዳዮች ላይ የሚመከርባትም መድረክ ናት።
“አዲስ አበባ ባለፈውና በአዲሱ ሚሌኒየም” በሚል ርእስ በ2000 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽሕፈት ቤት የታተመ ጽሑፍ የአዲስ አበባ ሠፈሮችን አሰያየም በሚገባ ያስረዳል። በርካታዎቹ የከተማዋ ቀደምት ሠፈሮች ስያሜያቸውን ያገኙት በቤተ መንግሥቱ ዙሪያ መሬት በጉልት መልክ በተሠጣቸው መሳፍንትና መኳንንት ስም ነው። በዚህ መልክ ስያሜያቸውን ከአገኙት ሠፈሮች መካከል ራስ መኰንን ሠፈር፣ ራስ ተሰማ ሠፈር፣ ራስ ብሩ ሠፈር፣ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ሠፈር፣ ራስ ሥዩም ሠፈር፣ ራስ ሙሉጌታ ሠፈር፣ ደጃዝማች ውቤ ሠፈር፣ ጌጃ ሠፈር ነጋድራስ ኃይለ ጊዮርጊስ ሠፈር፣ ደጃዝማች ዘውዱ አባኮራን ሠፈር እና ሸጎሌ (የአሶሳ ገዢ በነበሩት በሼክ ሆጀሌ አል ሐሰን የተሰየመው) ሠፈር ይጠቀሳሉ።
ከመላው የሀገሪቱ ማዕዘናት መጥተው አዲስ አበባ በሠፈሩ ብሔረሰቦች የተመሠረቱ ሠፈሮች ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ይቀመጣሉ። በዚህ መልክ ከተመሠረቱት ሠፈሮች መካከል ለአብነት አደሬ ሠፈር፣ ጎፋ ሠፈር፣ ወሎ ሠፈር፣ ወርጂ ሠፈር፣ መንዜ ሠፈርና ሱማሌ ተራ ይገኙበታል።
በሦስተኛ ደረጃ በተለያዩ ሙያዎች ተሠማርተው በተለይም በቤተ መንግሥቱ የተለያዩ የሥራ ድርሻዎች በነበራቸው ባለሙያዎች የተቆረቆሩ ሠፈሮችን እናገኛለን። እነዚህም ሠራተኛ ሠፈር፣ ዘበኛ ሠፈር፣ ሥጋ ቤት ሠፈር፣ ኩባንያ ሠፈር፣ ጠመንጃ ያዥ ሠፈር፣ ካህን ሠፈር (በኋላ ገዳም ሠፈር)፣ ገባር ሠፈር፣ ሠረገላ ሳቢ ሠፈርና ውሃ ስንቁ ሠፈርን ያካትታሉ። ሠራተኛ ሠፈር በዐፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት በዕደ ጥበባት ሙያ በተሠማሩ ነዋሪዎች የተመሠረተ ሠፈር ነው። የሠፈሩ መሥራቾች ዋነኛ ሙያ የብረታ ብረት ሥራ እንደነበረ ይነገራል። ይኼም የተለያዩ የብረታ ብረት ውጤቶችን ለምሳሌ ማረሻ፣ የፈረስ እርካብን፣ የቤት እቃዎችን፣ የጋሻና ጦር እና የጠመንጃ እድሳትን ይጨምራል። በቤተ መንግሥቱ በአናጢነት የተሠማሩ ባለሙያዎችም የሚኖሩት በሠራተኛ ሠፈር እንደነበር ይነገራል።
በሌላ በኩል ጥቂት የማይባሉ የአዲስ አበባ ሠፈሮች ስያሜያቸውን ያገኙት በተለያዩ አጋጣሚዎች፣ ክሥተቶችና ታሪካዊ ክንዋኔዎች ነው። ሰባራ ባቡር፣ እሪ በከንቱ፣ ዶሮ ማነቂያ፣ አፍንጮ በር፣ አራት ኪሎ፣ አምስት ኪሎ፣ ስድስት ኪሎ፣ ጣሊያን ሠፈር፣ ሃያ ሁለት ማዞሪያ፣ ሽሮ ሜዳና ነፋስ ስልክ ተብለው የሚጠሩትን ሠፈሮች በዚሁ ዘርፍ መፈረጅ ይቻላል። ሰባራ ባቡር ሠፈር ስያሜውን ያገኘው ሙሴ ሰርኪስ ተርዚያን በሚባሉ አርመናዊ ነጋዴ አማካይነት ከውጭ አገር መጥቶ አሁን ስያሜውን ባገኘበት ቦታ ተበላሽቶ በቀረው የመንገድ መሥሪያ ተሽከርካሪ (ሮለር) ምክንያት ሠፈሩ ሰባራ ባቡር በመባሉ ነው።
በተጨማሪም በከተማው ከሚገኙ ዋና ዋና ሠፈሮች መካከል በኦሮሞ ተወላጆችና የቦታ ስሞች የተሰየሙ ሠፈሮችን እናገኛለን። ከነዚህም መካከል ጉለሌ፣ ጎርዶሜ፣ ቀበና፣ ኮተቤ፣ የካ፣ እንዲሁም ገርጂ እና ላፍቶ የተባሉት ሠፈሮች ለአብነት ይጠቀሳሉ።
እንዲሁም ሠፈሮችን በከተማዋ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያን እና አጥቢያዎች መሰየም ሌላ መንገድ ነወ። በዚህ ዘርፍ ከሚገኙ ሠፈሮች መካከል ተቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዘው አራዳ ጊዮርጊስ ሠፈር ነው። አራዳ በተለይም ከጣሊያን ወረራ ቀደም ባለው ጊዜ የአዲስ አበባ የኢኮኖሚ ማዕከል ከመሆኑ አኳያና በርካታ ማኅበራዊ ክንዋኔዎችን ያስተናግድ የነበረ ሠፈር እንደመሆኑ በሥነቃል ብዙ ተብሎለታል። በተመሳሳይ መንገድ ከተሰየሙ ሌሎች ሠፈሮች ደግሞ አማኑኤል፣ ዮሴፍ፣ ኪዳነ ምሕረት፣ ቀራኒዮ መድኃኔ ዓለም፣ እና ቀጨኔ መድኃኔ ዓለም ይገኙበታል።
ከ1888 ዓ.ም. የዐድዋ ጦርነት ድል እና ከአዲስ አበባው ስምምነት በኋላ ጣሊያን፣ ሌሎች የአውሮፓ መንግሥታትና አሜሪካ የአገራችንን ሉዓላዊነት በመቀበል ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሥርተዋል። በዚህ ሂደት በርካታ አገሮች የእነዚህን አገሮች ፈለግ በመከተል ኤምባሲዎቻቸውን በአዲስ አበባ ከፍተዋል። ከአዲስ አበባ በርካታ ሠፈሮች መካከል አንዳንዶቹ ስያሜያቸውን ያገኙት ከእነዚህ ኤምባሲዎችና ቀደም ሲል ደግሞ ከሌጋሲዮኖች ነው። ፈረንሣይ ሌጋሲዮንና ሩዋንዳ ሠፈሮች ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው።
ከአዲስ አበባ ሠፈሮች መካከል አንዳንዶቹ በታዋቂ የውጭ አገር ዜጎች ስም የተሠየሙ ናቸው። ከእነዚህም መካከል ቤኒን ሠፈርና ተረት ሠፈር ይገኙበታል። ቤኒን ሠፈር ስያሜውን ያገኘው ከጣሊያን ወረራ በፊት ታዋቂ ነጋዴ በነበሩት የአይሁድ ተወላጅ ቤኑን ሲሆን፣ ተረት ሠፈርደግሞ ስያሜውን ያገኘው በአዲስ አበባ ከተከፈቱት ከመጀመሪያዎቹ ሆቴሎች አንዱ በነበረው በሆቴል ዳፍራንስ ባለቤት ፈረንሣዊው ሙሴ ቴረስ ስም ነው።
የታሪክ መምህሩ ዶክተር ሺመልስ ቦንሣ ከላይ በተጠቀሰው ጽሑፋቸው “የአዲስ አበባ ማንነት” በሚል ንኡስ ርእሥር በአፈሯቸው አንቀጾች የአዲስ አበባን መልክ እንደሚከተለው ይገልጹታል። “ስብጥር የሆነች ከተማ፣ ንብርብር ታሪክ የተሸከመች ምድር፣ የብዙኃን ነዋሪዎቿ ድምር ውጤት፣ የእጅ ሥራ ነጸብራቅ ሆና የኖረች ግማደ-ኢትዮጵያ … በብዝኃነት ጥልፍልፍ ተፀንሳ የተወለደች፣ አድጋም የጎለመሰች። አዲስ አበባ ምንነቷና የማንነቷ ምስጢር በአንድነት ተጋምዶ፣ በልዩነት ውበት አሸብርቆ ደምቆ የተፈጠረ የሃገርነት ቋጠሮ ነው።
የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ድረ ገጽ ላይ የሠፈረ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ አዲስ አበባ ከምስረታዋ አንሥቶ እስከአለንበት ጊዜ ድረስ በ32 ከንቲባዎች ተዳድራለች። ከተማዋን በከንቲባነት የአገለገሉት ባለታሪኮች በቅደም ተከተል ወልደ ጻዲቅ ጎሹ-1882 ዓ.ም.፣ ኃይለ ጊዮርጊስ- 1909 ዓ.ም.፣ ወሰኔ ዛማኔል- 1910 ዓ.ም.፣ ይገዙ በሀብቴ- 1910፣ ማተቤ -1910 ዓ.ም.፣ ኅሩይ ወልደሥላሴ ከ1910-1914 ዓ.ም፣ ነሲቡ ዛማኔል ከ1914-1923 ዓ.ም.፣ መኮንን እንዳልካቸው ከ1924-1926 ዓ.ም.፣ ጠና ጋሻው ከ1926- 1928 ዓ.ም.፣ አበበ አረጋይ ከ1926- 1933 ዓ.ም.፣ ታከለ ወ/ሐዋርያት ከ1933-1934 ዓ.ም.፣ ከበደ ተሰማ 1934 ዓ.ም.፣ መስፍን ስለሺ ከ1934- 1938፣ ደምሴ ወ/አማኑኤል 1938 ዓ.ም.፣ ዘውዴ በላይነህ ከ1947-1948 ዓ.ም.፣ ትርፌ ሹምዬ ከ1948-1950 ዓ.ም.፣ ዘውዴ ገ/ሥላሴ ከ1950- 1952 ዓ.ም.፣ ዘውዴ ገ/ሕይወት ከ1952-1961 ዓ.ም.፣ ኃ/ጊዎርጊስ ወርቅነህ ከ1961-1966 ዓ.ም.፣ መኮንን ሙላት ከ1966-1970 ዓ.ም.፣ ዓለሙ አበበ ከ1970- 1973 ዓ.ም.፣ ዘውዴ ተክሉ ከ1974-1981 ዓ.ም.፣ ግዛው ንጉሴ ከ1981-1983 ዓ.ም.፣ ሙሉዓለም አበበ ከ1983- 1985 ዓ.ም.፣ ተፈራ ዋልዋ ከ1985-1989 ዓ.ም.፣ አሊ አብዶ ከ1990-1995 ዓ.ም.፣ አርከበ ዕቁባይ ከ1995- 1998 ዓ.ም.፣ ብርሃነ ደሬሳ ከ1998-2000 ዓ.ም.፣ ኩማ ደመቅሳ ከ2000-2005 ዓ.ም.፣ ድሪባ ኩማ ከ2005- 2010 ዓ.ም.፣ ታከለ ኡማ 2010-2012 እንዲሆም ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ከተማዋን እያስተዳደሩ የሚገኙት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ናቸው።
አዲስ አበባ ዛሬ ላይ ከተከናወኑላት እጅግ አበረታችና ተስፋ ሰጪ ልማቶቿ በተጨማሪ ለነገ የታሰቡና እየተገነቡ ያሉ እንደ አዲስ ቱሞሮው፣ ዊንዶው ኦፍ አፍሪካ፣ የግብርና ምርት ሽያጭ ማዕከላት፣ ሆስፒታሎችና መንገዶች የከፍታዋና የብልጽግናዋ መዳረሻ እጹብ ድንቅ መሆኑን አፍ አውጥተው ይመሰክራሉ!
ተስፋ ፈሩ
ዘመን መፅሄት ነሃሴ 2015