ጽጌረዳ ቢጫ ሮዝ ቀይ.. ቀለማት አሉት። እነዚህ የቀለማቱ መለያየት ጽጌረዳ የሚለውን ስያሜ አሳጥተው ሌላ ስያሜ እንዲኖረው አለአደረጉትም፤ ይልቁኑ ተጨማሪ ውበትና ድምቀት ሆነውለት መወደዱንና መፈለጉን ጨመሩለት እንጂ! ኢትዮጵያም እንዲሁ ናት አንዲት ግን ብዙ ቀለም፣ ባህል፣ ሃይማኖትንና ቋንቋን የአቀፈች። የሥነ ልቦና ሳይንቲስቶች ልዩነት የውበት መገለጫና ስልቹነትን ማስወገጃ ፍቱን መድኃኒት ነው ይሉታል።
ብዝኃነት ጌጥ ከሆነላቸው ጥቂት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ተጠቃሽ ነች። ብዙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚኖሩባት፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የሃይማኖት፣ የመልክአ ምድራዊ አሠፋፈርና መሰል ልዩነቶች የታደለች ናት። በልዩነት ውስጥ የዳበረው አንድነት በዓለም ላይ ካሉ ውስን ሀገራት ቀዳሚ ያደርጋታል። የበርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች መኖሪያ በመሆኗ የአያሌና ማራኪ ባህላዊ ዕሴቶች፤ እደ ጥበብ ሀብቶች፤ ሀገር በቀል ዕውቀቶችና አስደማሚ ቅርሶች ባለቤት በመሆኗ በርካቶቹን የሚዳስሱና የማይዳሰሱ ቅርሶቿን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤ የሳይንስና የባህል ድርጅት/ UNESCO/ በዓለም ቅርሥነት አስመዝግባለች።
በኅብረ-ብሔራዊነቷ ምክንያት ‹‹ትንሿ ኢትዮጵያ›› በመባል የምትጠራው አዲስ አበባም የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ነጸብራቅ በመሆኗ በውስጧ አቅፋ ያልያዘችው የሀገራችን ብሔር ብሔረሰብ አለ ለማለት ያዳግታል። የእነዚህ ብሔሮችና ብሔረሰቦች በከተማዋ መኖር ለከተማዋ ልዩ ውበትና ድምቀት ከመሆን ባለፈ ከተማዋ የራሷ መለያ ጠባይ እንዲኖራት አስችሏል። አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን መልክ ያላት እና ከብሔረሰቦች ባህል መዋሐድ ባለፈ እጅግ በረቀቀ መልኩ በፍቅር፣ በጋብቻ እና በመሳሰሉት ሁኔታዎች የተዋሐዱ ሰዎች መኖሪያ ከተማ እንድትሆን አድርጓታል።
አዲስ አበባ ስትመሠረት ጀምሮ የነበራትን የኅብረ ብሔራዊነት ረጅም ታሪክ በ19ኛው እና በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሀገርኛና በጎብኚዎች የተፃፉ ሥራዎች ዘግበውታል። በስቶኒ ብሩክ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ታሪክና የፖለቲካ መምህር ዶክተር ሺመልስ ቦንሳ፤ አዲስ አበባ ከብዙ የአፍሪካ ከተሞች በተለየ ድሃና ሀብታም ተሰባጥረው የሚኖሩባት፤ ነዋሪዎቿን ከነብዝኃነታቸው አቅፋ የኖረች፣ ያኖረች፣ የምታኖር የኢትዮጵያ የልብ ትርታና የነርቭ ማዕከል የሆነች ከተማችን ማረፊያችን፣ ችግሯም ችግራችን፣ ፍቅራችን እንደገናም ተስፋችንሆናለች። ይህች ድንቅ ስብጥር የሆነች ከተማ ንብርብር ታሪክ የተሸከመች ምድር ከመሪዎቿ በላይ የብዙኃን ነዋሪዎቿ ድምር ውጤትና የእጅ ሥራ ነጸብራቅ ናት ሲሉ ይገልፃሉ።
ዶክተር ሺመልስ በጽሑፋቸው፤ በብዙኃነት ጥልፍልፍ ተፀንሳ የተወለደች አድጋም የጎለመሰች አዲስ አበባ ምንነቷና የማንነቷ ምስጢር በአንድነት ተጋምዶ፣ በልዩነት ውበት አሸብርቆ ደምቆ የተፈጠረ የውህደት ቋጠሮ ነው። አዲስ አበባ ልክ እንደ ኢትዮጵያ የነዋሪዎቿ ስብስብ ውጤት ብቻ ሳትሆን ከድምርነቷም በላይ እጅግ የጠበቀ፣ የጠለቀ የውሕደት ስብጥር ናት። አዲስ አበባን ለመፍጠር ያልተጋ የኢትዮጵያዊ እጅ የለም። ኦሮሞው ከአማራው፣ ጉራጌው ከትግሬው፣ ዶርዜው ከሐረሪው፣ ሶማሌው ከወላይታው፣ ምሥራቁ ከደቡብ፣ ሰሜኑ ከምዕራቡ፣ ወንዱ ሴቱ፣ ልጅ ዐዋቂው፣ ነጋዴው ምሁሩ፣ ሀገሬው ከሌላው ተዋዶ፣ ተዋልዶ፣ ተናግዶ የፈጠራት ከተማ ከሚባል ነገር በላይ የሆነች ምስጢርም ናት።
አዲስ አበባ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ታሪካቸው የተዋደቁባቸውና ጠንካራ አንድነታቸውን ያስመሰከሩባቸው ታሪኮች ሐውልት ተቀርጾላቸው በየቀናቸው ክብረ በዓል ተበጅቶላቸው እምነት፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ፆታ ሳይለይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በራሱ አለባበስ ተጊጦና ኅብር ሠርቶ በድምቀት የሚያከብርባት ከተማ ናት። ሀውልቶቹም የከተማዋ ውበት ብቻ ሳይሆኑ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የታሪክ ዐሻራን በደማቅ የሚያሳዩ ናቸው። ለአብነት ያህል 30 ሺህ የሚደርሱ በአዲስ አበባ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስለመጨፍጨፋቸው የሚያወሳው የየካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልትን፣ የዐፄ ምኒልክንና የድል ሐውልትን እንዲሁም የኢትዮ ኩባ የወዳጅነት ሐውልትን ብቻ ብንመለከት ትግሬው፣ ኦሮሞው፣ አማራው፣ ሐረሪው፣ ሱማሌው፣ አፋሩ፣ ሲዳማው፣ አጠቃላይ ሁሉም ብሔር ብሔረሰብ ለእናት ሀገሩ ኢትዮጵያ መሥዋዕትነት የከፈለበት የታሪክ ዐሻራዎቹ የሚገኙባት ከተማ አዲስ አበባ የማንነት ደብር መሆኗን ያስረዳሉ።
መዲናችን አዲስ አበባ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ መሆኗ የተለያዩ አልባሳት፣ ምግቦች፣ ጭፈራ እምነት ወዘተ መናኸሪያ እንድትሆን አድርጓታል። በከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች ስንዘዋወር የምናገኛቸው እና የተለያየ ስያሜ ያላቸው ክትፎ፣ ቁርጥ፣ ዶሮ ወጥ፣ ተጋቢኖ፣ ቦርሰሜ ጭኮን የመሳሰሉ ምግቦች የአዲስ አበባ የብዙኃን ከተማ መሆኗ የወለዳቸው ምርጥ ስጦታዎቻችን ናቸው።
እግር ጥሎን ወይም ደግሞ ለመሸመት ፈልገን ሽሮ ሜዳ ከሄድንም ትንሿን ኢትዮጵያን በተለያዩ አልባሳት ተወክላ እናገኛታለን። የጋሞ፣ አማራ፣ ኦሮሞ ትግሬ፣ ሲዳማ፣ ስልጤ……ወዘተ አልባሳትን የቀለምና የውበት ስብጥር ሽሮ ሜዳ ላይ ስንመለከት ኅብረ ብሔራዊነት ለአዲስ አበባ ጌጥና በረከት መሆኑ ፍንትው ብሎ ይታየናል።
የአዲስ አበባ የባህል ቤቶች ኢትዮጵያን በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ሥጋ ለብሳና አካል ተጎናጽፋ የምንመለከትባቸው ድንቅ የትዕይንት ማዕከላት ናቸው። በእያንዳንዱ የባህል ማዕከል የኢትዮጵያውያን ብሔሮችና ብሔረሰቦችን ሙዚቃና ጭፈራ ለማዳመጥ የታደልነው ከአዲስ ኅብረ-ብሔራዊነት በመነጨ ነው።
ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት የመጡ ዜጎች እና የውጭ ሀገር ሰዎች በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ታሪክን በሚያወሱ ሠፈሮች ኑሯቸውን መሥርተው ይገኛሉ። በዚህም ባህል፣ ጥበብ እና ታሪክ ተዋሕደው መላው ኢትዮጵያውያንን የሚገልፁ በርካታ ሠፈሮች በመዲናይቱ ይገኛሉ። የአዲስ ሠፈሮቿ የማይዳሰሱ ቅርሶች ናቸው። ስያሜያቸውም ከውጭ ሀገር ዜጎች ጋር፣ ከብሔረሰቦችና ክፍላተ ሀገራት እንዲሁም ከመኳንንቶች እና በዋነኝነት ከአርበኞች ጋር የበለጠ ቁርኝት አላቸው።
በሌላ በኩል የአንድ አካባቢ ማኅበረሰብ ሰዎች አንዱ አንዱን እየሳበ በብዛት የኖሩባቸው ሠፈሮች በብሔሩ ስም ተሰይሞ በአዲስ አበባ ውስጥ እናገኘዋለን፡ ቦሌ አካባቢ የሚገኘው ወሎ ሠፈር፣ መርካቶ የሚገኘው ጎጃም ሠፈር፣ በማዘጋጃ ጀርባ ፖስታ ቤት አካባቢ የሚገኘው ወለጋ ሠፈር፤ እሪ በከንቱ አካባቢ የሚገኘው ጅሩ ሠፈር፣ ሽሮሜዳ አካባቢ ጋሞ ሠፈር፣ አዲስ ከተማ ትምህርት ቤት ጀርባ ቸሃ ሠፈር፣ አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት አካባቢ ደግሞ ሶዶ ሠፈር፣ እንዲሁም ኮልፌ አካባቢ ምሁር ጉራጌ ሠፈር ተብለው ይጠራሉ። ቀድሞ ዘመድ እና ዘር እየፈለጉ የኖሩ ሰዎች ከተማዋን እየተላመዱ ሲመጡ ከሠፈሮቻቸው ወጥተው ወልደው፣ ተዋልደው፣ ትስሥራቸውን ጠብቀው፤ ባህል፣ እምነት፣ ወግ፣ እሴታቸውን በጋራ እያከበሩ የአብሮ መኖር ተምሳሌትነታቸውን እያንጸባረቁ በአራቱም አቅጣጫ ላይ ሠፍረው እናገኛቸዋለን።
በዚህም አዲስ አበባ ለኢትዮጵያ ትልቅ ምሳሌ ናት። የአንድ አካባቢ ነዋሪዎችን፣ የተቋም ሠራተኞች፣ የንግድ ሥፍራዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የእድር እና እቁብ አባላትን… በመመልከት አዲስ አበባ የብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ መሆኗን መመስከር ይቻላል። ለዘመናት ተቻችሎና ተከባብሮ እንደየዐቅሙ ሁሉም የሚኖርባት ከተማ መሆኗንም መግለጽ ቀላል ነው። ይህንን ሐቅ የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል፤ ነዋሪዎችም አጣጥመዋል። ይኼ በጣም አስፈላጊና በመላው ኢትዮጵያ ሊሰፋና ልናባዛው የሚያስፈልግ መልካም ተሞክሮ ነው።በዚህ ጉዳይ ላይ በአንድ ወቅት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ አዲስ አበባ የመንግሥት መናገሻና የሀገሪቷ የፖለቲካ ማዕከል በመሆኗ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ተሰባስበው የኖሩባት ከተማ መሆኗን ተናግረዋል። የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ፖሊሲ የሚመሩ ማዕከላት የሚገኙባት ከተማ በመሆኗ በሀገሪቱ ደረጃ ትልልቅ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች የሚወሰነውም በአዲስ አበባ ነው።
ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ማዕከል ከመሆኗ ባሻገር የመንግሥት መቀመጫነቷ እና መናገሻነቷ እንዲሁም በዘመናት በሄደችባቸው የዕድገት ጎዳናዎች ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የመጡ ኢትዮጵያውያን ሰፍረዋል። ተድረዋል፣ ወልደው አሳድገዋል። ልጆቹ ደግሞ የኢትዮጵያን መልክ በአዲስ አበባ የበለጠ እያደመቁ እና እያጎሉ ለዘመናት ተጉዘው አሁን ላይ ከተማዋ ልዩ ባሕርይ ያለው የአብሮነት ኅብረት እንዲኖራት ማስቻላቸውን አመላክተዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ምን ትመስላለች ብሎ መጠየቅ ለሚፈልግ ሰው ምላሹ ‹‹አዲስ አበባን›› የሚል ከሆነ ትክክል ነው። አዲስ አበባ ውስጥ የሌለ ሃይማኖት፣ የማይነገር ቋንቋ፣ የማይታይ ባህልና ብሔረሰብ የለም። ይሄ ሁሉ መስተጋብር አዲስ አበባን የባህሎች፣ የማንነቶችና የሃይማኖቶች መናኸሪያና መገለጫ ከተማ እንድትሆን አድርጓታል። ይኼ መስተጋብር እየተሻሻለ ለዘመናት ተጉዞ አሁን ላይ በጣም በብዙና በዝርዝር ሊጠና የሚችል የፍቅር እና የአንድነት ግንኙነት ፈጥሯል።
መርካቶ በንግድ የተሠማሩት የከተማ ነዋሪዎች ከመላው ኢትዮጵያ ከሚመጡ ሰዎች ጋር የፈጠሩት የራሱ ውብ የሆነ ቀለም አለው። ፒያሳ አካባቢ የጥንቱ የአዲስ አበባ መልክ እንደሚስተዋል ይናገራሉ። እንጦጦ አካባቢ ብዛት ያላቸው የሃይማኖት ተቋማት ያሉበት አሁን ደግሞ የለማው የእንጦጦ ፓርክ የሚገኝባት ናት። ቦሌ ደግሞ ዘመናዊነት እና ዓለም አቀፋዊነትን የተላበሰ አካባቢ መሆኑን አንሥተዋል። እነኚህ ሁሉ በየጊዜው የሚከናወኑ የከተማዋ ዕድገቶች አዲስ አበባ ኢትዮጵያውያንን እያቀፈች፣ እየጨመረች፣ ከሁሉም አቅጣጫዎች ሁሉንም እየአካተተች የባህሎች ኅብር መገለጫ መሆን ችላለች።
አዲስ አበባ የሀገራችን ዋና መዲና፤ የተለያዩ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ፤ የአፍሪካ ሕብረት ጽሕፈት ቤት መቀመጫ፤ ከዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማቲክ ከተማ፤ የበርካታ ኤምባሲዎች መቀመጫ፤ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ ከተማ፤ በርካታ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስሕብ የታደለች፤ የሁሉም ኢትዮጵያውያን መናኸሪያ ከመሆን ባለፈ የአፍሪካውያን መዲና መሆኗ ይታወቃል።
‹‹ኅብረ-ብሔራዊነት ልክ እንደ አትክልት ቁርጥ ነው!›› እንደሚባለው የተለያዩ አትክልቶች ሙዝ፣ አቦካዶ፣ ቲማቲም፣ ቃሪያ፣ ቆስጣ፣ ሰላጣ ወዘተ ተቀላቅለው ስንመገባቸው የሚፈጥሩት ጣዕም እጅግ ይለያል፤ የሚያስገኙት ንጥረ ነገርም ጤናማ ያደርገናል። በተመሳሳይም አዲስ አበባ የኅብረ ብሔራዊነትና የመቻቻል ከተማ ሆና ትንሿን ኢትዮጵያ መስላ ልጆቿን በፍቅርና በአንድነት ማኖሯን ቀጥላለች!
ሳሙኤል ይትባረክ
ዘመን መፅሄት ነሃሴ 2015