“ፍልስፍናዬአገልግሎት፤ዓላማዬም ማገልገል ነው”የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዘመን መጽሔት ልዩ ዕትም እንግዳ ናቸው። በቆይታችን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለይም ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ የተከናወኑና እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የለውጥ ሥራዎችና ተያያዥ ጉዳዮችን አንሥተናል። ስለከተማዋ የልማት ሥራዎች አተገባበር፣ በኢኮኖሚ እና በሰው ተኮር ልማት ሥራዎች ላይም ገለጻ አድርገዋል። መልካም ንባብ።

ዘመን፡- በቅድሚያ ከዘመን መጽሔት ጋር ቆይታ ለማድረግ ስለፈቀዱ እና ስለሰጡን ጊዜ እናመሠግናለን።

ክብርት ከንቲባ አዳነች፡- እናንተም ከእኔ ጋር ቆይታ ለማድረግ ስለመጣችሁ እኔም አመሠግናለሁ።

ዘመን፡- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተሠሩ ያሉ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች አሉ፤ እነዚህ ሥራዎች ከትግበራ በፊት እንዴት ታሰቡ? ምን ዓይነት የአመራር አቅጣጫስ ተከተላችሁ?

ክብርት ከንቲባ አዳነች፡- “እንዴት ታሰበ?” ለሚለው ጥያቄ፣ የሥራ ሐሳብ የሚመነጨው ከሐላፊነት ነው። አንደኛው መነሻ የከተማዋን አጠቃላይ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጥያቄዎችን መመለስና መልካም ሥራዎችንም ማስቀጠል የሚቻለው እንዴት ብንመራው ነው? ከሚል መነሻ ነው። ሌላው፤ ከተማዋን እንደሚመራ ከንቲባ፤ እንደ ሴትም፣ እንደ እናትም በአዲስ አበባ እናቶችና ሴቶች ላይ ያሉ ጫናዎችና ሁኔታ ከግምት ማስገባትና ማየት ይገባል።

የሐሳቡ መነሻ በአንድ በኩል የሕዝቡን ጥያቄ መመለስ ነው። ከተማዋን ማሳደግ፣ ከተማዋን መለወጥ፣ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ ማድረግ

ነው። የማኅበራዊ ጫናዎቻቸውን መቀነስ የሚቻልበትን ስልትና ዕቅድ መንደፍ አስፈላጊ ነው። “የነዋሪዎችን ጥያቄዎች የመመለስ ጉዳይ ግዴታ ነው” ብለን ከመላው አመራር ጋር ትኩረት ሰጥተን ሠርተናል። ከተማዋ የሀገራችን መዲና፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሚናዋም ሰፊ ነው። ዓለም አቀፋዊ ሚና ያላት ከተማ እንደ መሆኗ ዘመናዊና ሁሉንም ያማከለ የአመራር ስልት ስለምትጠይቅ፤ በዚህ ልክ መጀመሪያ ሐሳባችንን አደራጅተን ነው ወደ ሥራ የገባነው።

የኢትየጵያ ምልክት የሆነች፣ አፍሪካዊ መልክ ያላት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ሚናዋን በሚገባ የምትወጣ፤ አስፈላጊ አገልግሎቶችን ማቅረብ የምትችል፣ ውበትና ከተሜነትን የተላበሰች ዘርፈ ብዙ ሚናዋን የምትመጥን ተወዳዳሪ ከተማ መሆን የምትችልበትን መነሻ ሐሳብ ይዘን፣ በተሠሩ መልካም ሥራዎችም ላይ ጨምረን፤ ጉድለቶቿን እየዘጋን እንድንቀጥል የሚያደርጉ መነሻዎች ይዘን ነው ወደ ሥራ የገባነው።

ዘመን፡- እርስዎ ሥራዎችን ሲመሩ፣ ሲያቅዱ፣ ሲያስተባብሩ የሥራ ፍልስፍናዎ ምንድነው?

ክብርት ከንቲባ አዳነች፡ በእኔ እምነት፣ እንኳን አንድ ትልቅ የሐላፊነት ቦታ ላይ እንድትመራ ሐላፊነት የተሰጣት አመራር ቀርቶ ማንም ግለሰብ የሚኖርለት ዓላማ ሊኖረው ይገባል። በዚህ ምድር ላይ ሰው ሆኜ የመኖሬ ዓላማ ምንድነው? መኖሬ ለምን አስፈለገ? ሰው ሲኖር እንዲሁ አድጎ፣ በልቶ ጠጥቶ ሥራ ሠርቶ የግል ጉዳዩን አሟልቶ ኖሮ ለማለፍ መሆን የለበትም። ከዚህ የሚበልጥ የሚኖርለት፣ ዋጋ የሚከፍልለት፤ የሚደክምለት፤ ጊዜውን የሚሰጠው ዕውቀቱንና ፈጣሪ የሰጠውን፣ አለኝ የሚለውን ነገር መልሶ መስጠት የሚችል መሆን አለበት። ሰው የሚኖርለት አንድ ዓላማ ሊኖረው ይገባል ብዬ አምናለሁ።

እኔ ፍልስፍናዬ አገልግሎት ነው፤ ዓላማዬም ማገልገል ነው። ወደ መንግሥት ሐላፊነት የሚመጣ ሰው ለማገልገል የቆረጠ መሆን አለበት። በአንድ ጊዜ ሁለት ዓይነት ሰው፣ በአንድ በኩል አገልጋይ፣ በሌላ በኩል ነጋዴ ወይም ሐብታም መሆን አይቻልም። አገልጋይ ለመሆን ቁርጠኝነት፣ ጊዜውን እና ያለውን ዕውቀት ያለስስት መስጠት አለበት። ወደ ሐላፊነት ከመጣንም ወዲህ አመራሩን መሠረት ያስያዝነው ትልቁ ነገር 24 ሰዓት፣ ሰባቱንም ቀናት ማገልገል አለብን የሚል ነው።

እሑዳችን አገልግሎት ነው፣ ቅዳሜያችን አገልግሎት ነው፣ ማለዳችን አገልግሎት ነው፣ ምሽታችን አገልግሎት ነው፣ ቀናችን አገልግሎት ነው፤ ክብራችን አገልግሎት ነው…ማገልገል… ማገልገል… ማገልገል። ለማገልገል በደከመንና በተሰላቸን ሰዓት ግን ሐላፊነታችንን መልቀቅ ነው ያለብን። አገልግሎት ውስጥ ልግመኝነት፣ አገልግሎት ውስጥ ሌብነት እና ሌሎች ነገሮች ደባል ሆነው ከመጡ ትክክለኛ አገልጋይ መሆን አይቻልም። አገልግሎት ደግሞ ከራስ በላይ፣ ከግል ፍላጎት በላይ ነው። እኔ በዚህ አምናለሁ፤ እየኖርኩትም ነው ብዬ ራሴን በዚህ ደረጃ መግለጽ እችላለሁ።

ዘመን፡ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ሰው ተኮር ሥራዎች በብዛት ተሠርተዋል፣ በእነዚህ ሥራዎች የተገኙ ለውጦችን እንዴት መግለጽ ይቻላል?

ክብርት ከንቲባ አዳነች፡– ይሄ “የሥራችሁ መነሻ፣ ሐሳባችሁ ምንድን ነው? ከሚለው ጥያቄህ ጋር የሚያያዝ ነው። መነሻ ሐሳባችን የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄዎች እና ጫናዎች ምን እንደሆኑ ከመረዳት የሚነሣ ነው። ከዚያ ደግሞ ዓላማችን ማገልገል ነው ካልን አዲስ አበባን በጥቅሉ ስናይ ለነዋሪዎቿ የከተማ አቀፍ ሚና ያላት እና ለኑሮ ምቹ ማድረግ ይኖርብናል። ከተማን ምቹ ማድረግ ስንል ጥሩ መንገድ፣ የጤና አገልግሎቶችና ትምህርት ቤቶች እንዲኖሩን ማድረግ ብቻ አይደለም። ምቹነትን የመፍጠር ሥራ የእያንዳንዱ ማኅበረሰብ አኗኗር ምን እንደሚመስል፣ ጫናው ምን እንደሆነ፣ ምን ተመቸው? ምንስ ጎደለበት? የሚለውን ከማወቅ የሚነሣ ነው። ይህንን መነሻ አድርገን ስናይ የአዲስ አበባ ሕዝብ የተለያየ የገቢ ደረጃ ያለው ነው። በአንድ በኩል ቁጥራቸው አናሳ ቢሆንም የተሻለ ገቢ ያላቸው ትልልቅ ሀብታሞች የሚኖሩባት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉና ፈጽሞ ምንም ገቢ የሌላቸው፣ የመንግሥትን ድጋፍ የሚሹ የነዋሪዎችም ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑባት ከተማ ናት። ሁሉንም ማገልገል አለብን። አደጉ በምንላቸው ትልልቅ ሀገራት፣ የገቢ ዐቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ነዋሪዎችን ዜጎቻቸው በመሆናቸው ብቻ ዐቅም ያለው ዜጋ የሚያገኘውን አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋሉ። አዲስ አበባም ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ነዋሪዎች ያሏት ከተማ ናት። ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሚናዋ ትልቅ መሆኑን ማየትም ያስፈልጋል። እነዚህን ባማከለ መንገድ ትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ዐቅደን መሥራት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና ምንም ገቢ የሌላቸውን የከተማችን ነዋሪዎች አገልግሎት በትክክል የሚደርሳቸው፣ የሚታሰብላቸው ማድረግ መቻል አለብን።

የሰው ተኮር ሥራችን ዓላማ የተቸገሩ የከተማ ነዋሪዎች ከገቢ የሚካፈሉ፣ ከልማቱ የሚቋደሱ እና ፍትሐዊነት የነገሠባት ከተማ ማድረግ አለብን የሚል ነው። የምንሠራው ለሰው ነው። የፓርቲያችን የብልጽግናም ፍልስፍና አንዱ መርሕ “ትኩረታችንን ሰው ላይ እናድርግ” የሚል ነው። ከምንሠራቸው ሥራዎች በፊት፣ በቅድሚያ ሰው እናስቀድማለን። ስለዚህ ዝቅ ብለን የሰውን ኑሮ ማየት፣ የነዋሪውን ጫና ስሜቱን መጋራት አንዱና የመጀመሪያው ነው። ይህን መነሻ አድርገን ስንነሣ በከተማችን ላይ ትልልቅ ሰው ተኮር ሥራዎች እንዲሠሩ ውሳኔ ተወስኖ የተሄደባቸው ናቸው። ሰው ላይ ያልዋለ፤ ለሰው ሕይወት የማይደርስ የአዲስ አበባ በጀት በፍትሐዊነት ለነዋሪው ደርሷል አይባልም። እጅግ በጣም ዘመናዊ መንገዶችን ልንሠራ እንችላለን።

ዘመናዊ ሕንጻዎችን ልንገነባ እንችላለን። ብዙ ታሪካዊ ነገሮችን ልንሠራ እንችላለን። ይሁንና ዛሬ ላይ ለሰው ሕይወት መድረስ የሚችል የሚቆረስ ነገር ከሌለው ግን ሙሉ ሊሆን አይችልም። ግንባታው የራሱ አስተዋፅኦና ድርሻ ቢኖረውም ሙሉ ሊሆን አይችልም። ለዚህ ነው “መጀመሪያ የአዲስ አበባ ሕፃናት፤ ነገ ይህችን ሀገርና ከተማ ተረክበው የሚያሳድጉ ልጆች እየተራቡ ትምህርት ቤት ውስጥ መዋል የለባቸውም” ብለንየተነሣነው። ልጆች ተርበው ሲወድቁ ከማየት በላይ ሕመም የለም። እዚህ ላይ እንደ ከተማ አስተዳደር ብቻ አይደለም፣ እንደ ፓርቲም ተመክሮበት፣ የአዲስ አበባ ተማሪዎች ትኩረት ይገባቸዋል፣ በተለይ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎችን መመገብ አለብን በሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሶ በጀቱን በይፋ ከተማ አስተዳደሩ ወስኖ ነው ተማሪዎችን መመገብ የጀመረው።

ሥራውን ስንጀምር ምገባ ያገኙ ተማሪዎች ቁጥር ወደ መቶ ሺህ ያህል ነበሩ። ከአንድና ከሁለት ዓመት በኋላ ሦስት መቶ ሺህ መድረስ ተቻለ። ዛሬ 2015 ዓ.ም ላይ 750ሺ ተማሪዎችን በቀን ሁለት ጊዜ እንመግባለን። ከምገባው በተጨማሪ ለትምህርት አስፈላጊ የሆኑ ዩኒፎርም፣ ደብተር፣ እስኪሪብቶና ሌሎችም መሠረታዊ ግብዓቶችይቀርብላቸዋል። በዚህም ከ20ሺ በላይ እናቶች ሥራ አግኝተው ልጆቻቸውን እየመገቡ፣ በእናትነት ፍቅር እየተንከባከቡ ያገለግሏቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ እነኚህ ተማሪዎች ሀገራቸውን የሚወዱ ነገ ላስተማረችኝ፤ ለመገበቺኝ ለሀገሬ ነገር መሥራት አለብኝ የሚል ህልም ይዘው እንዲያድጉና በአካልም በእምሮም ብቁ የሆኑ ተማሪዎች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፤ እያደረጋቸውም ነው።

በተመሳሳይ ደግሞ እኩልነት ተሰምቷቸው አንዱ የበላይ አንዱ የበታች ሳይሆን፣ ማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው የገቢ ልዩነት አእምሯቸውንና ሥነልቦናቸውን እንዳይጎዳ ትልቅ መከላከያ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው። በእኩልነት አብረው ይጫወታሉ፤ ይቦርቃሉ ትምህርታቸው ላይ ትኩረት አድርገው ይማራሉ። የወላጆችም ጫና በዛው ልክ ቀንሷል ማለት ነው።

የአዲስ አበባ ሕዝብ የኑሮ ጫና በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። ትናንት ሀገር አገልግለው በተለያየ ምክንያት የኑሮ እክል ገጥሟቸው ለችግር የተጋለጡ ብዙ ወገኖች አሉ። እነዚህ ወገኖች ጉልበት ባላቸው ጊዜ ሠርተው ገቢ ያገኙ የነበሩ፣ ዛሬ ግን በጤና እና በዕድሜ ጫና ምክንያት ሠርተው መብላት የማይችሉ ናቸው። ኗሪዎቻችን ስለሆኑ እኛ ካልተመለከትናቸው ማንም ሊመለከታቸው አይችልም።

እኛ በቀን ሦስት ጊዜ የምንበላባት፣ ምግብ ተርፎ የሚደፋባትና እኅት ወንድሞቻችን ከቆሻሻ ላይ ምግብ እየፈለጉ የሚበሉባት ከተማ ሌሎች ሥራዎችን ሠራሁ ብላ ብዙ ልትኮራ አይገባም፤ አያስችልምም። መንግሥት ብቻውን ሠርቶ እነዚህን ማኅበራዊ ጫናዎች ስለማይቀንስ በባለሀብቱና ነዋሪው በትብብር 19 የምገባ ማዕከላትን ገንብተናል። ዛሬ ምግብ የቸገረው የራበው የአዲስ አበባ ነዋሪ እጁን ታጥቦ ማናችንም ቤት የሚቀርብ ዓይነት ንጹሕ ምግብ ከ19ኙ የምገባ ማዕከላት በአንዱ መመገብ ይችላል። ከምገባ ማዕከላቱ ተደራሽነት አንጻር ስናየው አዲስ አበባን ሰው ተርቦ የማያድርባት ከተማ ማድረግ የተቻለበትን ትልቅ ስኬት ማግኘት ተችሏል።

በተጨማሪም ዝናብና ፀሐይ የማይከላከሉ፤ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ወንዝ ዳር የሚገኙ የፈራረሱ የቀበሌ ቤቶች ውስጥ ለሚኖሩ እናቶችና አባቶች 21 ሺ ቤቶችን ሠርተን በእርጅና ዘመናቸው ዐረፍ ብለው ሀገራቸውንና ትውልዱን እየባረኩ መኖር የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር ችለናል። እነዚህን ቤቶች የሠራነው እንደ መንግሥት ማቅረብ ያለብንን ግብአቶች አቅርበን ማኅበረሰቡን በማስተባበር ነው። ቤቶቹ መታጠቢያ ቤት፣ ማብሰያ ክፍል እና መኝታ ቤት ያላቸው ናቸው።

እኛ ወደዚህ የለውጥ ሥርዓት ውስጥ በምንገባበት ሰዓት አዲስ አበባ ላይ ዳቦ በጣም ችግር ነበር። አዲስ አበባ ግን ዳቦ ብርቅ ሊሆንባት የሚገባ ከተማ አይደለችም። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ነገር ከዚህ በፊት ሥራዎች አልተሠሩም ማለቴ አይደለም፤ ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል። ነገር ግን በዚህ ደረጃ በብዙ ጫና ውስጥ እያለፍን የሠራነው ሥራ ትልቅ እንደሆነ ደግሞ እውነቱን መናገር ያስፈልጋል። እስከ 2011 ዓ.ም. ድረስ በአዲስ አበባ ከፍተኛ ዳቦ የማምረት ዐቅም ከ300 ሺህ የማይበልጥ ነበር። ከተማዋ ዛሬ ላይ በቀን ከአምስት ሚሊዮን በላይ ዳቦ የማምረት ዐቅም ላይ ደርሳለች። 27 አዳዲስ የዳቦ ፋብሪካዎች ተገንብተዋል። ሰው ተኮር በምንለው የልማት ሥራችን ለሰው በመድረስ፤ ተመግቦ እንዲያድር፤ ደስ ብሎት እኩልነትና ፍትሐዊነት ያለው አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ እንደ ዜጋ ተገቢውን ክብርና ፍቅር የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት ተችሏል፤ ውጤቶችንም ደግሞ ማየት ችለናል። ስለ ሰው ተኮር ልማትን ስናነሣ ሌሎችንም ጉዳዮች መጥቀስ ይቻላል ነገር ግን እነዚህ ትልልቅ ማሳያዎቻችን ናቸው።

ዘመን፡- የማዕድ ማጋራት ሥራ ላይ የአገኛችሁት ውጤት እንዴት ይገለጻል?

ክብርት ከንቲባ አዳነች፡- የኮሮና ቫይረስ ሀገራችን ላይ ስጋት በደቀነበት ሰዓት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ለመላው ኢትዮጵያውያን “ማዕድ አጋሩ” የሚል ጥሪ አደረጉ። ያንን ጥሪ ተከትሎ ማዕድ ማጋራትን አዲስ አበባ ባህል አድርጋዋለች። ለዚሁ ተግባር በየዓመቱ ከሦስትቢሊዮን ብር ያላነሰ ይሰበሰባል። ባለሃብቶች ይሄ በረከት ነው እያሉ በጣም ደስ ብሏቸው ነው የሚሳተፉት። ስለዚህ በከተማችን ማኅበራዊ ሐላፊነትን የመወጣት ባህል እየዳበረ መሆኑን መናገር የምንችልበት ነው። በዚህ መንገድ በየዓመቱ በሚኖሩ በዓላት ከ600 ሺ በላይ ዜጎችን ማዕድ እናጋራለን።

ይኼን ቁጥር በድግግሞሽ ስናየው በሚሊዮን የሚቆጠር ዜጋን ማገልገል የተቻለበት ነው። ይኽ በዓል ሲሆን ወይም የኑሮ ውድነቱ ሲንር በምናካፍለው ማዕድ ማጋራት ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ሰው ካለው ነገር ላይ በማካፈል ጎረቤቱን መርዳት እንዲችል የማድረግ ሥራ ሠርተናል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አብዛኛው አመራርም ወርኀዊ ወጪውን የሚሸፍንለትና ማዕድ የሚያጋራው ቤተሰብ አለው። በማዕድ ማጋራት የተካተቱት በበቂ መሥፈርት ተለይተው፣ “ይገባቸዋል” የተባሉ ቤተሰቦች ናቸው።

ከማዕድ ማጋራት ባሻገር ሕፃናት ተወልደው እዚህም እዛም የሚጣሉ አሉ። በፍጥነት ወደ ሕፃናት ማሳደጊያ ክፍላችን እንወስዳቸዋለን። ቀጥሎ የከተማዋን ነዋሪና ባለሀብቱን በማሳመን ከቻሉ ልጆቻቸው አድርገው ወስደው እንዲያሳድጓቸው፣ ያ የሚከብዳቸው ከሆነ ደግሞ በሕፃናት ማቆያዎቻችን ውስጥ የሚስፈልጋቸውን ወጪ እንዲሸፍኑ በማድረግ ለሕፃናትም የተሻለ ሁኔታ እየተፈጠረ እንዳለ በዚሁ በሰው ተኮር እንቅስቃሴዎቻችን ውስጥ ማንሳት ይቻላል።

ዘመን፡- የአዲስ አበባን የኢኮኖሚ ዐቅም ከማሳደግ አንጻር ምን ምን ሥራዎች እየተሠሩ ነው ? ምን ዓይነት ለውጥስ መጣ ?

ክብርት ከንቲባ አዳነች፡- አዲስ አበባ ለሀገራችን በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት /ጂዲፒ/ የምታደርገው አስተዋፅኦ እጅግ ትልቅ ነው። ዋና የኢኮኖሚ ማዕከል ናት። ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ያለባትና ወጪ ገቢ እቃዎችም የሚንቀሳቀሱባት ከተማ ናት። ከዚህ አንጻር አንደኛ ይኼን ሚናዋን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ መፍጠር አለብን በሚል መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ ባለሀብትነት እንዲያድጉ የማድረግ ሥራዎችን ሠርተናል። አዲስ አበባለመጀመሪያ ጊዜ በኢንዱስትሪ ፓርክ ደረጃ የማምረቻና የመሸጫ ሥፍራዎችን መገንባት ችላለች። 90 ሄክታር መሬትና አንድ ቢሊዮን ብር መድበን ኢኮኖሚዋን እና የማምረት አቅሟን ለማሳደግ እየሠራን ነው።

ሁለተኛ ትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እየገነባን ነው። እነዚህ ሜጋ ፕሮጀክቶች ሚናቸው ትልቅ ነው። በአንድ በኩል ቱሪዝምን በመሳብ የሀገር ውስጥ ጎብኚ ቁጥር ከፍ እንዲል በማድረግ ገቢን ይጨምራሉ፣ የውጪ ጎብኚዎችን ፍሰት በመጨመርም የውጭ ምንዛሬ ያስገኛሉ። በሌላ በኩል ትልልቅ የሥራ ዕድል እየፈጠሩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ያሳልጣሉ። የዓድዋ ሙዚየም ፕሮጀክትን ካየነው ነገ የሚፈጥረው ብቻ ሳይሆን ዛሬ የፈጠረውም የሥራ ዕድል በኢኮኖሚው ውስጥ ትልቅ ሚና ያለው ነው። ነገ ደግሞ ትልቁ የሀገራችን የመስሕብ ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል ምንም ጥርጣሬ የለንም።

በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ድጋፍ የተሠሩትን አንድነት፣ ወዳጅነት፣ ወንድማማችነትና እንጦጦ ትልልቅ የመስህብ ማዕከሎች ሆነዋል። አዳዲስ እየጨመርንም ነው የአለነው። ከተማዋን ከማጽዳትና ከማስዋብ ጋር አያይዘን የምንሠራው ሥራ ኢኮኖሚውን በማነቃቃት በኩል ጉልህ ሚና አለው። ወደ ከተማዋ መጥቶ መዋዕለንዋይን የማፍሰስ ፍላጎት እየጨመረ ነው ፤ የግል ግንባታዎች ብቻ ሳይሆኑ ፋብሪካዎች እና ኢንዱስትሪዎች በጣም ተነቃቅተዋል። እነዚህን ደምረን ስናይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ዕድገት በግልጽ እንመለከታልን።

የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ለማሳደግና ለመደገፍ አሠራር እያዘመንን ነው። በዚህ ረገድ ቅድሚያ የሰጠናቸው ዘርፎች አሉ። ለምሳሌ፡- የገቢ አሰባሰቡ ዲጂታል እንዲሆን በኢ-ታክስ ጀምረን አሁን በቴሌ ብር እየሆነ ነው ያለው። ድካምን እየቀነስን በቀላሉ ሰው ከቤቱ ሆኖ የንግድና የግንባታ ፈቃድ ማግኘት የሚችልበትን ሥርዓት እየዘረጋን ነው። ይሄ የንግድ ሥርዓቱን በማሳለጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ፈጣን ያደርጋል።

በቅርብ ጊዜ የጀመርናቸውና በፍጥነት እንሠራቸዋለን ብለን ለሕዝባችን ቃል የገነባናቸው ፕሮጀክቶችን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋን ማሳደጊያ ናቸው። የአፍሪካ መስኮት ብለን ወደ 84 ሔክታር መሬት ላይ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ የጀመርነው ፕሮጀክት አንዱ ትልቅ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን የሚያሳድግ፣ ቱሪዝምን የሚጨምር ነው። በቅርቡ የተፈራረምነውና ይፋ የአደረግነው ‹‹አዲስ ቱሞሮ›› ፕሮጀክትም ሌላው ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ነው። አዲስ አበባን አዲስ ገጽታ ሊያላብሳት የሚችል የአዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ሴንተር ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ላይ የመጀመሪያውን ምዕራፍ ፕሮጀክት እየጨረስን ነው።

አዲስ አበባ ከተማ ለንግድና ለኢግዚቢሽን ትልቅ የስበት ማዕከል ነች። በተለይ ለአፍሪካውያን የትኩረት ማዕከል እንድትሆን፤ በከተማችን አሉን የምንላቸው ዲፕሎማቶች፣ የእንግዳና የዓለም አቀፍ ተቋማት እንቅስቃሴዎች መሸመት ሲፈልጉ ወይም መዝናናት ሲፈልጉ ከአዲስ አበባ ወጥተው ነው የሚሄዱት። ነገር ግን በዶላር ወይም በውጭ ምንዛሪ ገቢያቸውን የሚያገኙት እዚህ እየሠሩነው። ወጪውን የሚያወጡት ግን ሌላ ሀገር ነው። አዲስ አበባ የዚያን ዓይነት አገልግሎት ስላልገነባች ነው፤ ይሄ ገብቶናል። ስለገባንም በፍጥነት እየገነባን ነው።

የአዲስ አበባን አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በአደገው ገቢዋ መግለጽ ይቻላል። የአዲስ አበባ ዓመታዊ ገቢ በ2010 ዓ.ም. 30 ቢሊዮን ብር ነበር፤ ዛሬ 140 ቢሊዮን በጅተን እየሠራን ነው። በ2015 ዓ.ም. ብቻ ወደ 109 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ችለናል። ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው አንጻር በጣም ገና ነን። በትክክል የንግድ እና የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን ፍትሐዊ ካደረግን፣ ሥራችንን ውጤታማና ቀልጣፋ ካደረግን ከዚህ በላይ ማሳካት እንችላለን። ትልቁ ሀገራዊ ገቢ የሚሰበሰበው ከአዲስ አበባ ነው። አዲስ አበባ ግብር የምትሰበስበው ከግለሰብ ግብር ከፋዮች ነው። የገቢዎች ሚኒስቴር ደግሞ አጠቃላይ ከተቋማት አዲስ አበባ ላይ ገቢ ይሰበስባል። ሀገራዊ የገቢ ዕድገቱን ስናየው ዋናው ማዕከሉ አዲስ አበባ ላይ ነው።

ዘመን ፡- የከተማዋ ገቢ በአስቀመጡት ልክ ከተገለፀ በጀቱስ እንዴት ይታያል?

ክብርት ከንቲባ አዳነች፡- የአዲስ አበባ ገቢና የአዲስ አበባ በጀት ሁል ጊዜ የተጣጣመ ነው። ምክንያቱም አዲስ አበባ የምትተዳደረው በራሷ ገቢ ነው። የተወሰኑ ትንንሽ የውጭ ርዳታዎች በአንዳንድ ፕሮጀክት ላይ ይገኛሉ። ነገር ግን እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም። ለማሳያ ያህል የ2010 ዓ.ም እንኳን ብንወስድ የከተማዋ ገቢ 30 ቢሊዮን ብር ነበር፤ ወጪዋ ደግሞ ወደ 32 ቢሊዮን ብር አካባቢ ነበር። ከዚያ በኋላ ካየነው ወጪና ገቢዋ እኩል ነው። በሚቀጥለው ዓመትም በ2016 ዓ.ም. 140 ቢሊዮን ብር ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ዐቅደናል። ከዚያ ውስጥ ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ለካፒታል ፕሮጀክት እንዲሆን፣ አስተዳደራዊ ወጪያችንን እየቀነስን፣ ብክነት እየቀነስን ለዘላቂ ልማት በጀታችን እንዲውል እያደረግን እየመራን ነው ።

ዘመን፡- በአጠቃላይ የለውጥ ሥራችሁ ውስጥ ያጋጠሙ ፈተናዎች ምንድን ናቸው? ፈተናዎቹስ እንዴት ታለፉ?

ክብርት ከንቲባ አዳነች፡- በዚህ የለውጥ ዘመን ውስጥ ያጋጠመን ፈተና እንደ ሀገር የሁሉም የጋራ ፈተና ነው በሚል መግለጽ ይቻላል። አዲስ አበባ ላይ ግን የተለየ ጫና ነበረው። አንዱ እና ዋናው ፈተና ነገሮችን በትክክለኛው ገጽታቸው ከመግለጽ ይልቅ ሆን ብሎ የማዛባት ስትራቴጂና ስልት በመከተል ብዥታ በመፍጠር ብዙ ጉዳቶችን ማስከተሉ ነው። እውነትን ከመግለጽ ይልቅ እውነት የሚመስሉ ሐሰተኛ መረጃዎችን በማዛባት በብዙ መንገድ በተለያዩ ሚዲያዎች፣ በሕዝብ ላይ የሚደረጉ ዘመቻዎች የተጋረጡት ተግዳሮትና ፈተና ሆነው የተከሠቱበት ሁኔታ ነው። እኛም ወደ እዚህ ሐላፊነት ስንመጣ አንዱ የጠበቀን ፈተና አመራሩ ጭምር በተለያየ ጎራ ቆሞ በተለያየ ቡድንተኝነት ውስጥ የሚታይበት ሁኔታ ነበር።

ይኼ እንዲሁ የመጣ ፈተና አይደለም። አጠቃላይ እሳቤው እውነታን የማዛባት፣ መልካም ነገሮችን የማጠልሸት፣ የሚሠራውን ሥራ በትክክለኛው ገጽታ ሳይሆን በተዛባ ገጽታ ሕዝቡ ጋር እንዲደርስ ማድረግፍላጎት የፈጠረው ነው። የእኛ ኮሙኒኬሽን ስልትና ብቃት ደግሞ በዚያ ልክ ዝግጁ ሆኖ ተመጣጣኝ ያልሆነበት፣ ሕዝቡም፣ አመራሩም ይሄ ሁኔታ ጫና የሚያደርስበት መሆኑ አንዱ ተግዳሮት ሆኖ የተገለጠበትና ያለፍንበት ሁኔታ አለ። ዛሬም ተግዳሮቱ ያለ ቢሆንም በበርካታ የሕዝብ ተሳትፎ፣ ከሕዝብ ጋር ባደረግናቸው ውይይቶች፤ በአመራሩ መካከል በመነጋገርና በመወያየት የማይረባውን እና ጊዜ የሚያባክንብንን ወደ ጎን እየተውን ጊዜያችን ሳያልፍና ሳይባክን ዐሻራችንን እናስቀምጥ በሚል መግባባት ደርሰናል።

ሐላፊነት ላይ እስከአለን ድረስ ምን አዲስ ነገር እንጨምራለን? ለትውልድ የምናሻግረው ምንድን ነው? የሚለው ጉዳይ ገዢ ሊሆን ይገባዋል እንጂ በማይረባና በማያዛልቀን ነገር ጊዜያችንን ማባከን ተገቢ እንዳልሆነ ተማምነን ጥሩ ጥሩ የሆኑ ሥራዎች ተሠርተዋል። ሁለተኛው ያጋጠመን ፈተና ትንሽ ሠርቶ መርካት ነው። ጉዟችን በጣም ሩቅ ነው፤ መዳረሻችን ብልጽግና ነው ብለናል። የምንሠራው ለመበልጸግ ነው። ጥቂት የሚቆጠሩ ሥራዎች ሠርተን፣ ዘንድሮ ዕቅድ ተከናወነልን፣ ጥሩ ተፈፀመልን ብለን ረክተን ዕረፍት ዓይነት ስሜት እንዲሰማን የሚያስችል ሁኔታ ውስጥ አይደለንም የአለነው። መወዳደር አለብን፤ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ እና ሦስተኛዋ የዲፕሎማቲክ ማዕከል በመሆናችን፣ አጠቃላይ ተወዳዳሪነታችንን የሚፈታተኑ ነገሮች እየመጡ ነው። በደምብ ጥረን ግረን ካልያዝን በስተቀር ይኼም ነገ ሊጠፋ የሚችል መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ሥራ መሥራት አስፈላጊ ነው።

የሕዝቡን የኑሮ ጫና ከማቃለል አንጻር ገና ብዙ መሥራት አለብን። የሕዝባችንን ብልጽግና ማረጋገጥ ነው ዓላማችን፤ ግባችንም መበልጸግ ነው። ስለዚህ እሱን ታሳቢ ካደረግን በቀላሉ መድከም አይገባንም፤ ብዙ ወደ ርካታ ሊያስኬድ የሚችልም ውጤት ላይ አይደለንም። “ድሎቻችን መሥራት እንደምንችል፣ ተግዳሮቶችን ማለፍ እንደምንችል ማሳያ ብቻ ናቸው” እያልን ነው በጥቂት ከመርካት ጋር ያሉትን ፈተናዎች ያለፍናቸው እንጂ የከተማው አመራር ቶሎ ብሎ ወደ ርካታ የመምጣት ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ነበሩብን።

በሌላ በኩል ደግሞ ሌብነትና ብልሹ አሠራሮችም ተግዳሮቶች ነበሩ፤ አሁንም ተግዳሮት መሆናቸው ቀጥሏል ብለን ነው የምንገልጸው። አመራር ሆኜ በሌላ ቦታ ከሠራሁባቸው ይልቅ፤ አዲስ አበባ መስተዳድር ሌብነት የተለመደ ሆኖ ወደ ታች ሠርጿል። ለአገልግሎት መማለጃ መቀበል፣ ምስጋናን በቃል ሳይሆን በዓይነት ወይም በገንዘብ ለመቀበል መፈለግ ያጋጠመን ተግዳሮት ነው። “አገልግሎት በነጻ መስጠት አለብን” የሚለው ሐሳብ በዋናነት መሠረት መያዝ የሚኖርበት በሲቪል ሰርቫንቱ ቢሆንም ለዚህ አስተሳተብ ተግበራዊ መሆን የመሪዎቹ ሚናም ወሳኝ ነው። መሪዎቹ ለዚህ ቆርጠው የሚታገሉ ከሆነ እስከ ታች ድረስ እየለወጡ መሄድ ይቻላል።

በዚህ በኩል ያሉትን ብልሹ አሠራሮች፣ ብልሹ አስተሳሰቦችና ተግባሮች መቀየር ላይ ብዙ ርብርብ ማድረግ እንዳለብን፤ ጫናውም ቀላል እንዳልሆነ ተረድተን እየሠራንበት እንገኛለን። ፈተናው የነበረ እና የተሻገረ ቢሆንም ዛሬ በትናንትናው ልክ አይደለም። ዛሬ አዲስ አበባ ላይ መሬት በሔክታር አይወሰድም፤ አዲስ አበባ ላይ ባለቤቱ ፈልጎ በድብቅ ካላደረገው በስተቀር የተለየ ጫና አሳድሮ ብር ካልከፈልከኝ በስተቀር ላገለግልህ አልችልም ማለት አይችልም። ባለቤቱ መጥቶ ማጋለጥ እስከቻለ ድረስ ተገቢውን አገልግሎት አግኝቶ ተጠያቂነት መስፈን የሚችልበትን አሠራር ዘርግተናል። ተግዳሮቱ ግን ዛሬም አለ። መተባበር፣ መተጋገዝ የሚፈልግ ጉዳይ ነው።

ሦስተኛው ተግዳሮት የኑሮ ውድነት ነው። የገበያው መዛባት በአንድ በኩሉ አርቴፊሻል የሆነ የዋጋ ጭማሪ በሌላ በኩል የከተማው የሕዝብ የኑሮ ጫና ሰፋ ያለ መሆኑ ነው። አራተኛ የግብይት ሰንሰለቱ ያልተስተካከለ መሆኑና ሌሎች ምክንያቶች ተጨማምረው አንድ ላይ የኑሮ ውድነቱን ትልቅ አደረጉት።ይኼንን ተግዳሮት ለማለፍ የተለያዩ ስልቶችን ተጠቅመናል። አንደኛ ምርት ወደ አዲስ አበባ ከተማ በስፋት በማስገባት ሰው ሠራሽ ጭማሪውን ለመዋጋት ያደረግነው ጥረት ብዙ ውጤት አስገኝቷል። ወደ 179 የሚሆኑ የእሑድ ገበያዎችን በመክፈት እሑድና ቅዳሜ ታክስ የማይደረጉ ከነጋዴው ዋጋ ጋር ሲተያዩ ከ20 እስከ 30 በመቶ ልዩነት ያላቸው እንዲሆኑ በማድረግ ሕዝቡ እንዲሸምት ተደርጓል። ሕዝቡ ቅዳሜና እሑድ መሸመት እንዲችል ዕድል ፈጥረናል። አሁን ደግሞ አምስት የሚሆኑ ትልልቅ የገበያ ማዕከላት በአዲስ አበባ መግቢያ በሮች ላይ እየተገነቡ ነው። አንዱን አጠናቀናል። ሌሎቹ ሰሞኑን ተጠናቀው ወደ ሥራ ይገባሉ።

ሕዝብ በልቶ ለማደር እንዳይቸገር ማድረግ የቻሉ የከተማ ግብርና ሥራዎች ተሠርተዋል። በሌማት ትሩፋት ደግሞ ከተማዋ ራሷን እየቻለች ነው። አሁን የጀመርናቸው የእንጀራ ፋብሪካዎችም አሉ። በለሚኩራ ተጠናቆ ሥራ ጀምሯል፤ ጉለሌ ላይ ሁለተኛው የእንጀራ ፋብሪካ በቅርቡ ይጠናቀቃል። ገበያው ላይ እንጀራ የሚሸጥበትን ዋጋ አጥንተናል። በሙሉ ዐቅም እንጀራ ወደ ማቅረብ ሲገባ የእንጀራውን ዋጋ ማስተካከል፣ ገበያው ላይ ጣልቃ የምንገባበት ዕድል ነው እየፈጠርን የአለነው። እነዚህ ሥራዎች የሥራ ዕድልም ይፈጥራሉ፣ ሠርተው የሚበሉ ዜጎቻችን በስፋት እንዲመጡ እና ዕድል እንዲያገኙ ያደረገ ነው።

በአጠቃላይ በመተባበር በጋራ በመሆን ሠራተኝነትን፤ ማገልገልን፣ ተግቶ መሥራትን፣ አለመሥነፍን፣ ሃያ አራት/ሰባት የምንለውን ደጋግመን መመሪያችንና መርሐችን እያደረግን እንደዚህ ያሉ ተግዳሮቶችን የማለፍ ስልት ተከትለን ነው እየሠራን የአለነው።

ዘመን፡- ከይዞታቸው ተፈናቅለው የነበሩ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ያሉ አርሶአደሮች የተሻለ ኑሮ እንዲኖራቸው ከማድረግ አንጻር የተከናወኑ ተግባራት ምንድን ናቸው?

ክብርት ከንቲባ አዳነች፡– አዲስ አበባ በአሁኗ ስፋት ከመገለጧ በፊትም ዳርዳሯ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር የሚተዳደሩ አርሶ አደሮች አሉ። ነገር ግን ከተማዋ እየሰፋች በሄደች ቁጥር ተገቢው ትኩረት አልተሰጣቸውም። አርሶ አደሮች ምን ይሆናሉ? እንዴት ይኖራሉ? እንዴት ኑሯቸውን ይመራሉ? ከከተማዋ ጋር የሚያድጉትስ እንዴት ነው? የሚል እሳቤና ስትራቴጂ አዲስ አበባ ላይ አልነበረም። ይህ የመሪዎችና የአፈፃፀም ስሕተት ነው። በዚህ ስሕተት ምክንያት ብዙ ቁስሎች፣ ጫናዎችና ትልልቅ ጉዳቶች ደርሰዋል። አሁን እያስተካከልን የአለነው ያንን ነው።

ይህ ችግር እንዲፈታ የለውጡ አንዱ መሠረታዊ ጥያቄ ሆኖ ሕዝቡን ያንቀሳቀሰ በመሆኑ ምክንያት በትኩረት ሠርተንበታል። አንደኛ አርሶ አደሮቹ በተገቢው ሁኔታ መሬታቸው ላይ በባለቤትነት፣ የመጠቀም መብታቸው ጭምር ተረጋግጦ ለልማት በሚፈለግበት ጊዜ ሕግና ሥርዓቱን ጠብቆ መሬታቸውን ለልማት ማዋል የሚችሉበት፣ ልማቱ በሚሠራበት ጊዜ ደግሞ አርሶ አደሮቹ ኑሯቸውን በቀጣይነት የሚመሩበት ምን መሠረታዊ ነገር እንሥራላቸው? የሚለውን ታሳቢ ያደረገ ሥራ ነው እየተሠራ ያለው። አቃቂ ላይ የተሠራው የአርሶ አደር ግብርና ልህቀት ማዕከል ይህንን ያሳየናል። ትልቅ የግብርና ልህቀት ማዕከል በኢንዱስትሪ ፓርክ ደረጃ ሊገለጽ የሚችል ሠርተናል። እዛ ውስጥ አርሶ አደሮቹ ተደራጅተው ከብት ማደለብ የሚችሉበት፣ የወተት ምርትን ለከተማዋ ጭምር ትልቅ ፀጋ ሊሆኑ የሚችሉበት፣ የዶሮ፣ የእንቁላል ተመሳሳይ ማቀነባበሪያ ጭምር መሥራት የሚችሉበት፣ ከተማዋ ላይም ንጹህ አቅርቦት በሥርዓቱ ሊቀርብ የሚችልበት ዕድልን የፈጠረ አርሶ አደሮቹም ደግሞ ሕይወታቸውን በቀጣይነት የሚመሩበት ሥራ ተሠርቷል።

እስካሁን ድረስ በመረጃ በአረጋገጥነው መሠረት ወደ አምስት ሺህ የሚደርሱ አርሶ አደሮችን በመሬታቸው ላይ ተገቢውን የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል። ከተማው ውስጥም የመኖሪያ ቤት ጭምር ማግኘት እንዲችሉ፣ ከከተማዋ ጋር እንዲያድጉ፣ ከተማዋ ስትሰፋ መጣችልን፣ ከተሜነት መጣልን፣ ዘመናዊነት መጣልን የሚሉበት እንጂ፤ መፈናቀላችን ነው፣ መጥፋታችን ነው የሚል ስጋትና የጎሪጥ መተያየት መቅረት አለበት ብለን የሠራነው ሥራ ውጤታማ ሆኗል ማለት ይቻላል።

ዘመን፡- የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ በአለፉት ዓመታት በርካታ ዕውቅናዎችን አግኝታለች። የዕውቅናዎቹ አንድምታ ምንድነው ?

ክብርት ከንቲባ አዳነች፡- አዲስ አበባ ባላት ሚና ጭምር ግንኙነቷን በትልቁ ማጠናከር አለባት። ከተማዋ በቀደመው ጊዜም የተለያዩ ግንኙነቶች ነበሯት። ነገር ግን በአለፉት የለውጥ ዓመታት በተለይ 2014 እና 2015 ዓ.ም የነበሯትን ግንኙነቶች ከዓለም አቀፍ ከተሞች ጋር በምናይበት ጊዜ እጅግ በጣም ጎልቷል። በቅርብ ጊዜ በምገባ ከዓለም ከተሞች ጋር ተወዳድረን አንደኛ ወጥተን የተሸለምንበትን እንዲሁም የከተማዋን ቆሻሻ በምናስወግድበት ጊዜ በካይ ጋዝን እንዳያመነጭ አድርገን የምናስወግድበት ሥርዓት ላይ በጣም አደጉ ከሚባሉ ትልልቅ ከተሞች በላይ ዕውቅና ያገኘንበት ነው። ከቅርብ ጊዜዎቹ እነዚህን መጥቀስ ይቻላል። በተመሳሳይ ሌሎች በርካታ ዕውቅናዎች አግኝተናል። ሽልማቶቹ እና ስጦታዎቹ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ትብብርን፣ አብሮ መሥራትን፣ ልምድ መቀያየርን፣ ግንኙነታችንን ማጠንከርን እናበርታ፤ እናጠናክር ያሉበት ትልልቅ ስጦታዎችን የሚያመላክቱ ናቸው። እነዚህን ስንመለከት የአዲስ አበባ ተፈላጊነት፣ የስበት ማዕከል መሆን እየጨመረ እንደሆነ በደምብ መናገር ይቻላል።

ዘመን፡- “አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ተምሳሌት ነች” የሚሉ ወገኖች አሉ። በዚህ አባባል ይስማማሉ?

ክብርት ከንቲባ አዳነች፡- በእርግጥም ነች። አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መልክ ናት። ሁሉም ኢትዮጵያውያን ቤቴ ብለው የሚኖሩባት የሁላችን ከተማ ናት። የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እንቅስቃሴም ማዕከል ነች። የዲፕሎማሲውም ማዕከል ነች። የመገናኛ ብዙኃኑ አጠቃላይ እንቅስቃሴም ማዕከል ነች።

ዘመን፡- ነገዎን ይንገሩን እስኪ? ስለሚመሯት ከተማ መዳረሻ ህልምዎ ምንድን ነው?

ክብርት ከንቲባ አዳነች ፡- አዲስ አበባ ብዙ ሊያበለጽጓት የሚችሉ ሀብቶችና ዐቅሞች ያሏት ከተማ ናትና በልጽጋ ማየት እፈልጋለሁ። አዲስ አበባ ተወዳዳሪ ከተማ ሆና በዓለም ላይ ደምቃና ታውቃ እንድትታይ እፈልጋለሁ። ይህንን አመራሮቻችን ጭምር እንዲሰንቁትና እንዲያልሙት የሚያደርግ ሥራ እየሠራን ነው። “ለምን ህልም ነው የምንሠራው? የምንኖረው ? ዝም ብለን ደመወዝ ለማግኘት ነው የምንሠራው? አመራር ሆነን ተሸከርካሪ እና ቤት ስለሚሰጠን ነው የምንሠራው? ለምንድን ነው አመራር የሆንነው? በተቀመጥንበት ወንበር፣ የምንመራውን ተቋም ከየት ወዴት ነው የቀየርነው? ሁለት ዓመት በመኖሬ ምን ሠራሁ ? ብሎ አመራሩ ራሱን እንዲጠይቅ ይፈለጋል።

እኔ የአዲስ አበባ ከንቲባ ከሆንኩ ሦስት ዓመቴ ነው። “ምን ቀየርኩ?” የሚለውን ለኔ ለግሌ ሌጋሲ ብቻ አይደለም የምቆጥረው፤ አዲስ አበባ ላይ ነገ እኔ ብኖርም ባልኖርም በእኔ አመራርነት የመጣው ለውጥ ምንድን ነው ? የሚለውን ነው መቁጠር የሚያስፈልገው። ይኼን ያህል ብቻ ነበር መሥራት የነበረብኝ? ለምን ከዚህ በላይ አልሠራሁም? ብለን ህልም፣ ስንቅ፣ ቁጭት መያዝ ያስፈልጋል። እንደዛ ሲሆን ነው ትልቅ ሥራ መሥራት እና ትልቅ ማለም የሚቻለው። እንዲህ ዓይነት ህልም ደግሞ ሲታለም ሰውን ይዞ ነው።

ታች ያለውንም አይቶ ይዞ አብሮ መሆን አለበት። የሚሠራው ሥራ ለእኔ ነው፣ ፀጋ ነው፣ ሕይወቴን እየቀየረው ነው። ከዚህ በላይ ቢሠራ ከዚህ በላይ እቀየራለሁ የሚል በጎ አስተሳሰብ አብሮ እንዲዳብር እየተደረገ መሄድ አለበት። እነዚህ ተደማምረው አዲስ አበባ በዓለም ላይ ብቁና ተወዳዳሪ ከተማ መሆን እንድትችል ደግሞ መበልጸግ አለባት። የዜጎቿ ሕይወት መበልፀግ አለበት። አኗኗራችን፣ አስተሳሰባችን፣ አሠራራችን፣ ታታሪነታችን፣ ማደግ አለበት። እንደ ዓድዋ ሙዚየም ከተማዋ ላይ የሚታዩ ፕሮጀክቶችና ሥራዎች ዘላቂ ሆነው ለትውልድ የሚተላለፉ ዐሻራዎች እንዲሆኑ ሌት ተቀን መሥራት አለብን። ትላንት ዝም ብለን ታሪካችን ነው ብለን ዓድዋን ስንኮራበት ወይም አንዳንድ ጊዜም ስንረሳው / ዓድዋ የማይከበርበትን ጊዜ እናስታውሳለን/ እንደዛ ሆነን ሳይሆን የትላንትናው ጥሪት ወይም ደግሞ የትላንትናውን ወረት ይዘንና የዛሬውን ጥረት ጨምረንበት ነጋችንን አልመን አዲስ አበባን ማበልጸግ እንችላለን የሚል ህልም ሰንቀን ነው እየሠራን የአለነው። ይህ ለዛሬው ትውልድ ጥቅም፤ ለነገው ትውልድ ደግሞ ዐሻራ ማስተላለፍን ማዕከል ያደረገ ነው።

ዘመን፡- ክብርት ከንቲባ ለነበረን ቆይታ እጅግ አድርገን እናመሠግናለን።

ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።

ዘመን መፅሄት ነሃሴ 2015

Recommended For You