ዘላቂ ትኩረትለአገር ውስጥ አምራቾች

ኢትዮጵያ አሁን በያዘችው የእድገት ጎዳና የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነት ለመጨመር፣ በዘርፉ የሚታዩትን ተግዳሮቶች ለማስወገድ እና የዜጎቿን የሥራ ዕድል ፍላጎት ለማሟላት አልማ እየሠራች ትገኛለች። ይህን እቅዷን ለማሳካት ደግሞ ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጀምሮ ገቢራዊ እየሆነ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ አንድ ዓመት አልፎታል። ንቅናቄው ዓላማዬ ብሎ የተነሳው የአምራች ኢንዱስትሪውን ማነቆዎች በቅንጅት መፍታት፤ የኢንዱስትሪውን ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ማሳደግ እንዲሁም ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ዘርፉ የበኩሉን አስተዎፅዖ እንዲያደርግ ማስቻል ነው። ለንቅናቄው መነሻ የሆኑ ሁኔታዎች ደግሞ የአምራች ኢንዱስትሪው ለጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) ድርሻው ከ7% በታች መሆን፤ የአማካይ ማምረት አቅም ዝቅተኛ መሆን፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በአምራች ኢንዱስትሪ ላይ ያደረሰው ተጽዕኖ እና ጉዳቶች፤ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የፀጥታ እና ኢኮኖሚ አለመረጋጋት እንዲሁም ሌሎች ተግዳሮቶች መሆናቸውን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያሳያል።

የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንቅናቄውን አስፈላጊነት በተመለከተ ለከተማ እና ክልል ኢንዱስትሪ ቢሮዎች ገለፃ በማድረግ ንቅናቄውን ከጀመረ በኋላ ከፌደራል እስከ ክልል ተቋማት አደረጃጀትን በማጠናከር የፋይናንስና የጉምሩክ ጉዳዮች፣ የግብዓትና የመሰረተ ልማት፣ የከተሞችና የክልል፣ የአቅም ግንባታና የምርምር ስርፀት እንዲሁም የኢንቨስትመንትና የግል ዘርፍ ሞቢላይዜሽን በተሰኙ አምስት ክለስተሮች በማደራጀት ትኩረት ሰጥቶ ሠርቷል። በዚህም በማህበረሰቡ፣ በኢንዱስትሪው እና በመንግስት ተቋማት መካከል የተቀናጀ ባለቤትነት በመፍጠር ሰፊ ንቅናቄ ማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮች መዘርጋት ተችሏል። በፌደራል፣ በክልል፣ በከተማ አስተዳደሮች እና በልማት አጋራት መካከል በቅንጅት የመሥራት ባህልና ጥረቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ማዳበር ተችሏል።

በተሠራው የተቀናጀ ሥራም የ4063 አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ ከቀላል እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያሉ ችግሮችን በየደረጃው በመቀናጀት መፍታት ተችሏል። በዘርፉ 3020 ባለሀብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዲያወጡ ተደርጓል። 700 አዲስ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል። ሥራ አቁመው የነበሩ 352 አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲመለሱ ተደርጓል፤ ከነዚህ ውስጥ በፀጥታ ምክንያት ሥራቸውን ዘግተው የሄዱ ይገኙበታል። በተጨማሪም 6624.6 ሄክታር መሬት ለአምራች ኢንዱስትሪ የለማ መሬት ማዘጋጀት ተችሏል።

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪና የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ዋና አስተባባሪ የሆኑት አቶ አስፋው አበበ ኢትዮጵያ ታምርት የሚለውን ሀሳብ አጠር

ባለ ሁኔታ ሲያስቀምጡት፣ በጥሬ እቃነት ብቻ ይወጡ የነበሩ ምርቶችን እሴት በመጨመር በአገር ውስጥ በማምረት ለአገርና ለውጭ ገበያ ማቅረብን በዋናነት ይመለከታል ይላሉ። ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ታምርት አስተሳሰብ በደንብ ያልተቃኘ አካሄድ በመከተላችን የፀጥታ አካላት የደንብ አልባሳት ከውጭ ነበር የሚመጡት፣ አሁን ይህ እየተቀየረ ነው በማለት በኢትዮጵያ ታምርት አስተሳሰብ አገር ውስጥ ባሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች በማምረት ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማዳን መቻሉን በማሳያነት ይጠቅሳሉ።

አቶ በቀለ አብርሃም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የቢዝነስ አማካሪ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ናቸው። የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፈ ብዙ ችግር ያሉባቸው መሆኑን ያስቀምጣሉ። የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም በ2021 ካወጣው ሪፖርት በመነሳት ዋና ዋና የሚባሉትን ችግሮች ሲጠቅሱ፣ የውጭ ገበያ ያለማግኘት፤ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት ስላለባቸው ግብዓት በወቅቱ ማቅረብ ስለማይችሉ ከአቅማቸው በታች ማምረት፤ የተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎች እየበዙ መምጣታቸውን ተከትሎ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር መኖር፤ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የቢሮክራሲ ችግር፤ የሎጅስቲክ ሂደቱ የተራዘመና ወጪው ከፍተኛ መሆኑ እንዲሁም የውጭ ገበያ ያለማግኘት እንደሆኑ ያመላክታሉ።

አቶ በቀለ እንደሚሉት ችግሮችን ማግኘት ሃምሳ በመቶ መፍትሔ ማግኘት ነው። መንግሥት አሁን ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ቅድሚያ በመስጠት የተለያዩ የፋይናንስ አማራጮች በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል መስጠቱ፣ አበረታችና በበጎ ጅማሮነት የሚታይ መሆኑን ይገልጻሉ። በልማት ባንኩ በኩል አነስተኛና መካከለኛ ለሚባሉ ኢንተርፕራይዞች ስልጠና በመስጠት፣ የቢዝነስ ሀሳቦች ቀርበውላቸው ፋይናንስ የሚያገኙበት ሁኔታ በተጨባጭ እየተመቻቸላቸው መገኘቱን በአብነት ያስቀምጣሉ።

የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪዎች ዋና ችግር ስለሆነው ከፋይናንስና ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዘ ተግዳሮት ሲናገሩ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የበጀት ቀመር አንደኛው አገር ውስጥ ከሚገኝ ገቢ ነው፤ ሁለተኛው የውጭ ብድር ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ የውጭ እርዳታ ነው። መንግሥት የበጀት ጉድለት ሲያጋጥመው በአብዛኛው ጉድለቱን መሸፈን የሚችለው ከብሔራዊ ባንክ በመበደር ነው። የሚበደረው የገንዘብ መጠን ከፍተኛ በሆነ ቁጥር ባንኮች ለአምራች ኢንዱስትሪዎችም ሆነ ለሌላው የሚሰጡት ገንዘብ ያንሳቸዋል። በተለያዩ ምክንያቶች ከነበርንበት ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ሁኔታ አንጻር የውጭ ብድርና እርዳታ በግልጽ በሚታይ መልኩ ቀንሷል። በዚህም ምክንያት ጉድለቱ ከ3.2 በመቶ ወደ 4.1 በመቶ አድጓል። ይህን ጉድለት መሙላት የሚቻለው ከባንክ በመበደር ነው።

አሁን የአገር ውስጥ ሁኔታ እና የውጭ ዲፕሎማሲው በመሻሻሉ መንግሥት ሲበደር የነበረውን ገንዘብ ያህል አይበደርም። ባንኮች ገንዘቡን ለአምራች ኢንዱስትሪውም ሆነ ለሌላው በማከፋፈል ሥራ እንዲሠሩበት ይሆናል። ሰላም ሰፍኖ ሥራ ከተሠራ መንግሥትም የሚያገኘው ገንዘብ ይጨምራል። ሠራተኛውም ኑሮውን የሚደጉምበት ሁኔታ ስለሚመቻች ሰላም መስፈኑና ዲፕሎማሲው መሻሻሉ ከፍተኛ ጥቅም አለው ይላሉ።

የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ዋና አስተባባሪ አቶ አስፋው አበበ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የፋይናንስ ችግርን ለመፍታት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቁ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች እንዲተኩ ለማድረግ ሰፊ ሥራ መሠራቱን ይጠቅሳሉ። በዚህም አንዱን ኢንዱስትሪ ከሌላው ጋር በማስተሳሰር ውጤት ተገኝቷል ይላሉ። በተለይ ትላልቆቹን ኢንዱስትሪዎች ከአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር በአገር ውስጥ ግብዓት እንዲገኝ ተደርጎ የተሠራው ሥራ ከፍተኛ ውጤት የተገኘበት ስለሆነ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትን መቀነስ ተችሏል። የተቀነባበሩ የመጠጥና የምግብ ምርቶች እና የተለያዩ አልባሳት በአገር ውስጥ በብዛት እየተመረቱ መታየታቸው ኢንዱስትሪዎች እርስ በእርስ የመተሳሰራቸው ውጤት እንደሆነ ይገልጻሉ። ከውጭ የግድ መምጣት ያለባቸውን ግብዓቶች ደግሞ ለይቶ በማውጣት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲመጡ ከብሔራዊ ባንክና ከሚመለከታቸው የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመነጋገር በልዩ ሁኔታ ቅድሚያ እንዲያገኙ እየተመቻቸላቸው ይገኛል። በቀጣይ ይህ መተሳሰር ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ወጪን ከማዳን በተጨማሪ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶችን በማስፋት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ይሠራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አካል የሆነው አገር ውስጥ ለሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ዓለም አቀፍ የገበያ እድሎችን መፍጠር እና ለአገር ውስጥ ተጠቃሚዎችም ምርቶቻቸውን ማስተዋወቅ ዋና ዓላማ አድርጎ የኢትዮጵያ ታምርት 2015 ኤክስፖ ከሚያዚያ 28 እስከ ግንቦት 2 ድረስ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ተዘጋጅቷል። በዚህ ኤክስፖ የኢትዮጵያ ምርቶችን ለአገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ገበያ ማስተዋወቅ እንዲሁም የገበያ ትስስር መፍጠር ተችሏል። ዜጎች አገራዊ ምርት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አበረታቷል። በኢትዮጵያ ያሉ ምቹ የኢንዱስትሪ ፀጋዎችን በመለየት ለማስተዋወቅ ተችሏል። በዘርፉ ያለውን ፖሊሲ ለማስፈፀም በሚወጡ አሠራሮችና የህግ ማዕቀፎች ዙሪያ የግል ባለሀብቱን ያሳተፈ ፓናል ውይይቶች ተደርገው የጋራ ግንዛቤ ተወስዷል።

በኤክስፖው 124 አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማሳተፍ ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋዉቁ ተደርጓል። ከ68 በላይ አምራች ባለሃብቶች በዘርፉ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎታቸውን አሳይተዋል። ከ40ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ጎብኝተዋል፤ ከነዚህም መካከል ከ800 በላይ የሚሆኑት የ1ኛ ደረጃ፣ የ2ኛ ደረጃ እንዲሁም የኮሌጅ ተማሪዎች ናቸው። በሂደቱም ኤክስፖውን መሰረት ያደረገ ከ3000 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙበት የ5 ኪሎ ሜትር ታላቅ ሩጫ በእንጦጦ ፓርክ ተከናውኖ በዘርፉ ያሉ ባለድርሻ አካላትን ቅርርብ አጠናክሯል።

የተዘጋጀውን ኤክስፖ አስመልክቶ አስተያየት የሰጡት አቶ በቀለ፣ ከኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዓላማ ጋር የተያያዘ ሆኖ እንዳገኙት ይናገራሉ። አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን አስተዋውቀውበታል፤ አምራቾች እርስ በእርሳቸው የሚተሳሰሩበት ዕድልም ፈጥሮላቸዋል። በአገር ውስጥ ያሉ ተጠቃሚዎች ምርቶችን በማየት የአገር ውስጥ ምርቶችን እንዲጠቀሙ አነሳስቷል። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ዓይነት የኢንቨስትመንት አማራጭ እንዳለም ፍላጎትና አቅሙ ላላቸው ኢንቨስተሮች ማሳየት ተችሏል በማለት ኤክስፖው ግቡን ማሳካቱን ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኤክስፖ ከቀረቡ አዲስ ግኝቶች ውስጥ ለአብነት ሊጠቀስ የሚችለው ለወረቀት ማምረት ሥራ በግብዓትነት የሚያገለግለው ፐልፕ በአገር ውስጥ ለማምረት የሚደረገው እንቅስቃሴ ነው። ዶክተር ዲሲሳ ያደታ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የምርምርና ቴክኖሎጂ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። እሳቸው እንደሚናገሩት የኢትዮጵያ የወረቀት አምራች ኢንዱስትሪዎች ዋና ችግር የጥሬ እቃ እጥረት ነው። ከእነዚህ ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሱት ፐልፕ እና የአገለገሉ ወረቀቶች እጥረት ናቸው። እነዚህን ጥሬ እቃዎች በተደራጀና ተቋማዊ በሆነ መልኩ የሚያቀርብ ባለመኖሩ ወረቀት አምራቾች አሁን ማምረት በሚችሉበት ልክ እያመረቱ አይደለም። ፐልፕ ከዛፍና ከግብርና ተረፈ ምርት ሊገኝ የሚችል ሆኖ በወረቀት ማምረት ሂደት ውስጥ ከ10 እስከ 15 % የሚፈልግ ነው። ከ85 እስከ 90% ያገለገሉ ወረቀቶች ናቸው እንደገና እንደጥሬ እቃነት በመጠቀም ከፐልፕ ጋር ተዋህደው ማንኛውም አይነት ወረቀት የሚመረተው። በዶላር እጥረትሳቢያ ጥሬ እቃ ማስገባት ስላልተቻለ የወረቀት አቅርቦት እና ጥራት ችግር በሰፊው እየታየ ነው።

ዶክተር ዲሲሳ ገለጻቸውን በመቀጠል፣ በአቅርቦት ችግር ምክንያት የኢትዮጵያ የወረቀት ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም በአብዛኛው 20% ነው። ስለዚህ ይህን ችግር ለማቃለልና የማምረት አቅማቸውን ለማጎልበት ከዚህ በፊት ፐልፕ በአገር ውስጥ ለማምረት እንደአገር ከ18 እስከ 20 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ፕሮጀክት ተጀምሮ ጣና እና ቤኒሻንጉል ላይ ለማምረት ከ10 ዓመታት በላይ የፈጀ ወደውጤት ያልተሸጋገረ ጥረትን በማየት፣ መጀመሪያ እንደ ግለሰብ ዜጋ በቁጭት በመነሳት የጥሬ እቃውን ችግር ለመፍታት ከግብርና ውጤት ተረፈ ምርት ፐልፕ ለማዘጋጀት ዕቅድ በመንደፍ ወደምርምር ተገባ። በሙከራ ደረጃ ውጤት ሲመጣ በግል የተያዘውን ምርምር ወደመሥሪያ ቤት ደረጃ በማሳደግ ውጤቱ ሲረጋገጥ ኢትዮ ፐልፕ በሚባል ድርጅት የኬሚካል፣ የውሃ እና የእንሰት ተረፈ ምርቱን ምጣኔ በመጠቀም በብዛት በማምረት ስኬት ከመገኘቱ በተጨማሪ ፐልፑ በኤክስፖው ለዕይታ መቅረቡን ያነሳሉ።

ይህም ስለሆነ ከእንሰት ተረፈ ምርት ፐልፕ በማምረት ለወረቀት ምርት ግብዓት መሆን እንደሚችል በማረጋገጥ ከሙከራ ደረጃ በመውጣት በኢንዱስትሪዎች ማምረት እንዲቀጥል አርጎባ ትሬዲንግ አ.ማ. ከሚባል የወረቀት ፋብሪካ ጋር በመተባበር ፐልፑን (ጥሬ እቃውን) በመጠቀም የወረቀት ምርት ማምረት እንደሚቻል በተግባር ታይቷል ይላሉ። ከሁለት ዓመት በፊት በተገኘ የእስታክስቲክስ መረጃ በኢትዮጵያ 206 ሚሊዮን የእንሰት ተክል እንዳለ፤ የዳሰሳ ጥናት በተደረገው መሰረት ከአንድ የእንሰት ተክል እስከ 20% ተረፈ ምርት ነው ተብሎ እንደሚጣል፤ ይሄ በስፋት ፐልፕ ለማምረት ከበቂ በላይ እንደሆነ ዶክተር ዲሳሳ ያስቀምጣሉ። ፐልፕ ከእንሰት ተረፈ ምርት በተጨማሪ ከጥጥ ተረፈ ምርት እና ከስንዴ ገለባ ማምረት እንደሚቻል በቤተ ሙከራ ደረጃ እንደተረጋገጠም ይናገራሉ።

በቀጣይ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተሰጠው አቅጣጫ ከእንሰት ተረፈ ምርት በአንዱ የወረቀት ፋብሪካ በ2015 ዓ.ም. መጨረሻ በስፋትና በብዛት ማምረት ይጀመራል። ውጤቱንና የምርቱን አስተማማኝነት በማየት በ2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የሚገኙ የወረቀት ፋብሪካዎች በሙሉ ፐልፑን እያመረቱ ወረቀት መሥራታቸውን ይቀጥላሉ። የጥሬ እቃ ችግራቸውም ስለሚቃለል የማምረት አቅማቸውም ያድጋል፤ ቀጥረው የሚያሠሩትም ሠራተኞች ብዛት ይጨምራል። ኢትዮጵያም የአበባን ተክል በወረቀት ጠቅልላ ወደውጭ አገር ስትልክ ኢትዮጵያ ውስጥ ከእንሰት የተመረተ ወረቀት በማለት አገራችን እንድትታወቅ ማድረጊያም ይሆናል በማለት ፐልፕ በአገር ውስጥ ማምረት የሚሰጠውን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ዶክተር ዲሲሳ ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በወረቀት ኢንዱስትሪ እንደተስተዋለው ሁሉ በቆዳው ኢንዱስትሪ ውስጥም ገብቶ ይታያል። አቶ ሚሻሞ ዋካሶ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ቴክኖሎጂ ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። የቆዳ አምራች ኢንዱስትሪዎች ዋና ችግሮች ከሆኑት ውስጥ በበቂ ሁኔታ የጥሬ እቃ አለማግኘት እና ተረፈ ምርታቸውን በአግባቡ ማስወገድ አለመቻላቸው ተጠቃሽ ናቸው በማለት ይጀምራሉ። በቆዳ ማምረት ሂደት ከ75 እስከ 80% ተረፈ ምርት ሆኖ የሚወገድ ነው። ከ20 እስከ 25% የሚሆነው ነው ያለቀለት ለሥራ ዝግጁ የሚሆን ቆዳ የሚወጣው። አንዳንድ ፋብሪካዎች የተረፈ ምርት አወጋገድ ስርዓታቸውን ህብረተሰቡን በማይጎዳ ሁኔታ ባለማከናወናቸው ድርጅታቸው ምርት እንዳያመርት የተደረገባቸው አሉ። ስለሆነም ይህን ተረፈ ምርት ለምን ጥቅም ሊሰጥ ወደሚችል ነገር አንቀይረውም በሚል በትኩረት ለመሥራት መነሳሳታቸውን ያስታውሳሉ። በላብራቶሪ ደረጃ በመፈተሽ ከተረፈ ምርቱ ጥቅም ሊሰጡ የሚችሉ በርካታ ምርቶች ተገኝተዋል ይላሉ። ከእነዚህ ውስጥ ከቆዳ ፋብሪካዎች ጋር በመተባበር ቆዳን ለማልፋትና ወጥ የሆነ ውፍረት እንዲኖረው የሚያደርግ ኬሚካል፣ ጀላቲ ማዘጋጃ የሚሆን ግብዓት፣ ኮላ፣ ለቆዳ ማዘጋጃ የሚሆን ጨው፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እና ለችፑድ ማዘጋጃ የሚሆን ምርት አምርተን አሳይተናል በማለት ይገልጻሉ።

ገለጻቸውን በመቀጠል፣ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ከዚህ በኋላ ተረፈ ምርታቸው ወደ ውጭ ወጥቶ አካባቢ በመበከል ህብረተሰቡን ሳይጎዳ እንዴት ባለ መልኩ እናስወግድ በማለት መጨነቃቸው ቀርቶ ተረፈ ምርታቸውን በመጠቀም ለራሳቸው ግብዓት የሚሆን ምርት ያመርታሉ። እንዲሁም ለሌሎች አምራች ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን ምርት ማዘጋጀት በሚችሉበት ሁኔታ ይጠመዳሉ። ይህ እንዲሳካ ተግባራዊ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ያብራራሉ። የቆዳ ኢንዱስትሪዎችን ተረፈ ምርትን ወደ ምርት ግብዓትነት የመቀየር ተግባር በአገሪቱ ውስጥ በስፋት መተግበር ሲጀምር የአካባቢ ብክለትን መከላከል ባለመቻላቸው ምክንያት የተዘጉ ፋብሪካዎች ተከፍተው ማምረት ይጀምራሉ፤ በዝቅተኛ አቅምና ጥራት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች የሚያመርቱትን ምርት ከፍ ከማድረጋቸው በተጨማሪ ጥራታቸውንም ያሳድጋሉ፤ የኤክስፖርት አፈጻጸማቸውም የተሻለ ይሆናል ይላሉ።

በማጠቃለያቸውም፣ አሁን ያሉት ቆዳ ማልፍያና ማለስለሻ ፋብሪካዎች ከአቅማቸው በታች በዝቅተኛ መጠንና ጥራት የማምረት ሁኔታ ውስጥ ስለሚገኙ ከተረፈ ምርታቸው የተገኘውን ግብዓት በመጠቀም ለራሳቸው ምርት ማምረቻ ግብዓትነት እንዲውል ለማድረግ ከሞጆ ከተማ አስተዳደር ጋር በመነጋገር ሁኔታዎች እየተመቻቹ ነው። በቅድሚያም የከተማ አስተዳደሩ ለሚያቀርባቸው ሰልጣኞች ከተረፈ ምርት በዘመናዊ መንገድ ጥራቱን የጠበቀ ኮላ በስፋት ለማምረት እንዲቻል ወጣቶች ተለይተው ተደራጅተዋል፤ በቀጣይ ስልጠና እና ሌሎች ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቆዳ አምራቾች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ረድዋን በዳዳ ከላይ በቀረቡ የዘርፉ ችግሮች የሚስማሙ ሲሆን ጥራት ያለው ቆዳ በሚፈለገው መጠን አለማግኘት እና ከፋይናንስ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ዋነኞቹ ምክንያቶች መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። የቆዳ ፋብሪካዎች ለማምረት የሚጠቀሙበት ኬሚካል ከውጭ ማስመጣት ስለሚያስገድድ የውጭ ምንዛሪ መጠቀም ግድ የሚል ነው። በተለይ የብሔራዊ ባንክ እየተገበረ ያለው 30/70 የሚባለው አሰራር ከግብዓትና ከኬሚካል እንዲሁም ከሌሎች ነገሮች ጋር ተያይዞ ከቆዳ ማምረት ጀምሮ እስከ ጫማና ቦርሳ የሚሠሩ የዘርፉ ተዋናይ ፋብሪካዎች ማምረት ከሚችሉት አቅማቸው በታች ከ30 እስከ 50% እንዲያመርቱ አድርጓቸዋል። ስለሆነም ከፋይናንስና ከውጭ ምንዛሪ ጋር ተያይዞ የቆዳ ፋብሪካዎች የግብዓት ችግር እያጋጠማቸው ከአቅማቸው በታች ከመሥራት በላይ እየተዘጉም ስለሆነ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አለበት ይላሉ።

ፕሬዚዳንቱ፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ በኋላ በመንግሥት በኩል የታዩ አበረታች ሁኔዎች መኖራቸውን በማንሳት በተለይ ከተማሪዎችና ከወታደሮች ጫማ ጋር ተያይዞ የተደረገው የገበያ ማስተሳሰር ሥራ አበረታች መሆኑን ይጠቅሳሉ። በገበያ ማስተሳሰሩ ብቻ ሳይሆን ንቅናቄው ከተጀመረ በኋላ እየወጡ ያሉ አዳዲስ ፖሊሲዎች አነቃቂና አበረታች ናቸው። ለወደፊትም የሚወጡ በጥናት ላይ የሚገኙ አዳዲስ ፖሊሲዎች ተግባር ላይ ሲውሉ በአጠቃላይ ዘርፉን በማገዝ ለውጥ ያመጣሉ ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። ‹‹የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በቀጣይ አተገባበሩ እገዛ ካደረገልን ከሁለት እስከ ሦስት ሚሊዮን ማህበረሰብ በሥራ ላይ እንዲሰማራ ያደርጋል የምንለው የቆዳ ኢንዱስትሪ በከፍተኛ ሁኔታ ያድጋል፤ በተለይ የብሔራዊ ባንክ አሠራር እና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር ቢቃለል ዘርፉ በሙሉ አቅሙ በማምረት ለአገር የሚያበረክተው አስተዋጽኦም በዚያው ልክ ያድጋል›› በማለት ይገልጻሉ።

አያይዘውም፣ የቆዳ ፋብሪካዎች ግብዓቶች ሰፊና ብዛት ያላቸው ናቸው። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አገር ውስጥ እየተመረቱ አይደሉም። ከውጭ የምናስመጣቸው ግብዓቶች በማህበራችን እና በቆዳ ኢንስቲትዩት ተጠንተው የቀረቡት ወደ 48 የሚጠጉ ናቸው። በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ስር ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት የተለያዩ ሙከራዎች እየተደረጉ ይገኛሉ፤ ግኝቶችም አሉ። እነዚህ ግኝቶች በሰፊውና በብዛት ወደማምረት ደረጃ አድገው ወደ ገበያ የሚቀርቡበት ሁኔታ ሲፈጠር ዘርፉ የውጭ ምንዛሪ የሚፈልግበት መጠን ይቀንሳል። በአገር ውስጥ የተመረቱ ግብዓቶችን በመጠቀም ዘርፉ የማምረት አቅሙን ያሳድጋል። አብዛኞቹ ቆዳ ፋብሪካዎች ካለው እጥረት የተነሳ በግብዓትነት የተጠቀሙትን የማልፊያ ኬሚካልና ጨው መልሰው በግባትነት ይጠቀማሉ። በአገር ውስጥ ኬሚካሉና ጨው መመረት ይጀመራል እንደተባለው በስፋት መመረት ሲጀምር ችግራቸው ይቃለላል። አምራቾቹም የገበያ ስጋት ሳይኖርባቸው ያመርታሉ፤ የቆዳ ፋብሪካዎችም በተሻለ ሁኔታ የግብዓት ስጋት ሳይኖርባቸው የማምረት አቅማቸውን ለማጎልበት ይረዳቸዋል። ይህ ነው እንግዲህ ኢትዮጵያ ታምርት ማለት ይላሉ።

ከቆዳ ፋብሪካ የሚወጣውን ተረፈ ምርት ወደ ግብዓትነት የመቀየር እንቅስቃሴን በተመለከተ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ ከተረፈ ምርቱ ጋር ተያይዞ እየተሠሩ ያሉ ጥሩ ሥራዎችን እያየን ነው። ጅማሯቸው የሚያበረታታ ነው። ኮላና ጀላቲን በብዛት በማምረት ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ገቢ ማግኘት ተችሏል። ባለኝ መረጃ ከተረፈ ምርት ከተመረቱ ምርቶች ወደ ሶስት ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል። የምርምር ግኝቶች በስፋት ተግባራዊ ሆነው በብዛት ሲመረቱ ደግሞ ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን ጸጋዎች በመጠቀም የአምራች ኢንዱስትሪው አገራዊ የምርት ድርሻን ከ6.8 በመቶ በ2022 ዓ.ም. ወደ 17.2 በመቶ ለማሳደግ ግብ ጥላለች። ከዚህ በተጨማሪ በዘርፉ በዓመት ወደ ውጪ ከሚላክ ምርት አሁን ከሚገኘው 4 መቶ ሚሊዮን ዶላር ወደ 9 ቢሊዮን ዶላር ማሳደግ ዋነኛ ዓላማ ተደርጎ ታቅዷል። ይህ እንዲሳካ ከኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ምን ይጠበቃል በሚል መምህርና የቢዝነስ አማካሪውን አቶ በቀለ አብርሃምን ጠይቀናል። በምላሻቸውም፤ የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪ ዋና ችግር የፋይናንስ አቅርቦት ነው። የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግርን ከመፍታት አኳያ ከፖሊሲ ጀምሮ ችግር ፈቺ ሥራዎች መሠራት አለባቸው። በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን መላው ዜጋ በሙሉ ኃይሉ ተሳትፎ በማድረግ በቂ አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ ይገባዋል፤ ከውሃ በተጨማሪ ከንፋስ የሚገኘውንም ኃይል ማሳደግ ያስፈልጋል። ይህን ኃይል አምራች ኢንዱስትሪዎች በተገቢው መንገድ እንዲያገኙ ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ክትትል ማድረግ ይጠበቅበታል። በመንግሥት መሥሪያ ቤት ያሉትን የቢሮክራሲ ችግሮች እንዲሁም በጉምሩክና በሎጀስቲክ አቅርቦት ያሉትን ችግሮች የሚመለከታቸው አካላት ትልቅ የሥራ ድርሻ አድርገው መፍትሔ እንዲሠጡበት፣ የንቅናቄው ጽ/ቤት ከማስተባበር ጀምሮ ተግባራዊ ሆኖ እስኪታይ ድረስ ተሳትፎ በማድረግ መከታተል ይጠበቅበታል በማለት ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል።

የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ዋና አስተባባሪ አቶ አስፋው አበበ ደግሞ ሀሳባቸውን ሲያጠቃልሉ፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከመጀመሩ በፊት የኢትዮጵያ የማምረት አቅሟ በአማካይ 46% ነበር፤ የምርታማነት ማነስ ምክንያቶች ምንድን ናቸው በሚል ጥናት ተደርጎ መለካት በመቻሉ ችግር ፈቺ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ተደርገው አሁን 53% ማድረስ ተችሏል። በዚህ ዓመት መጨረሻ ምርታማነትን 60% ለማድረስ እየተሠራ ነው ይላሉ። ሌሎች ያደጉ አገራት በአማካይ 85% የደረሰ ምርታማነት አላቸው። ምርትና ምርታማነት በዚህ ልክ ካላደገ ከሌሎች አገራት ጋር ተወዳድሮ ገበያ ውስጥ አሸናፊ መሆን አይቻልም በማለት በንጽጽር ያቀርባሉ። በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአንድ ዓመት እንቅስቃሴው የአምራች ኢንዱስትሪውን በርካታ ችግሮችና ማነቆዎችን መለየት ተችሏል፤ ለተወሰኑት መፍትሔ ተሰጥቷል። ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ደግሞ በፌደራል ደረጃ የሚገኙ ሁሉም መሥሪያ ቤቶች ያሉበት አምስት ክላስተር በማዘጋጀት ችግሮችን ዘላቂና ተቋማዊ በሆነ መልኩ ተከፋፍለው እንዲፈቱ እየተደረገ ነው። ለዚህ ተግባር የልማት አጋራት ፈቃደኛ ሆነው አብረው መሥራት ጀምረዋል። በዚህ የተቀናጀ አሠራር እስከዛሬ ድረስ ችግር የሆኑ ተግዳሮቶች በቀጣይ ችግር የማይሆኑበት ሁኔታ በአጭር ጊዜ ይፈጠራል ብለዋል።

የዚህ አሠራር ውጤታማነት ከግብ የሚደርሰው በቅድሚያ ከፍተኛ አመራሩ ለአምራች ኢንዱስትሪው የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ሲያደርግ፤ የተዘረጉ አሠራሮች እስከታችኛው እርከን ድረስ አተገባበራቸው በየጊዜው በአፈጻጸም መለኪያ ተፈትሾ ማስተካከያ ሲደረግበት እና ዘላቂነት ባለው ሁኔታ ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት ሲሰጥ ነው የሚለው የዝግጅት ክፍላችን መልዕክት ነው።

ስሜነህ ደስታ

Recommended For You