አፈርን የማልማት፣ ሰብልን የማምረትና እንስሳትን የማርባት ጥበብ «ግብርና» ይሰኛል። ግብርና፤ የእጽዋትና የእንስሳት ምርቶች ለሰዎች ጥቅም ይውሉ ዘንድ ማዘጋጀትና ለገበያ ማቅረብንም ያካትታል። ሮጀር ሞሪሰን (2021) “History of Agriculture from the Beginning to the Present” በሚል ርዕስ ባዘጋጀው መጣጥፉ እንዳሰፈረው ግብርና አመጋገባችንን ብቻ ሳይሆን፣ የአኗኗር ዘይቤያችንን የቀየረ በመሆኑ፣ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ግኝቶች መካከል ዋናው ተደርጎ ይወሰዳል። የመጀመሪያዎቹ ማረሻዎች ከክርስቶስ ልደት በፊት በ3000 ዓ.ዓ. ጥቅም ላይ መዋላቸውን የአርኪዮሎጂና የምስል ማስረጃዎች ያስረዳሉ።
ቻይና፣ አሜሪካ፣ ግሪክ፣ ሜሶፖታሚያና ሱመራዊያን ግብርናን በመጀመርና በማዘመን ታሪክ ውስጥ ቀዳሚነትን ይወስዳሉ። የኤፍራጠስና የጢግሮስ ወንዞች ለዓለም የግብርና እና የሥልጣኔ ታሪክ ምንጭ ሆነው ይጠቀሳሉ። አፍሪካዊቷ ግብጽም ዓባይን ተንተርሳ በከፍተኛ የግብርና ሀብት ላይ የተመሠረተ ግዛትን ገንብታለች። ከዘመን ዘመን በርካታ የለውጥ ደረጃዎችን እያሳለፈ የመጣው ግብርና፣ በእጅ ከሚካሄድ ቁፋሮ ተነስቶ፣ እንጨትን በመቅረጽና ብረትን በማቅለጥ የተሠሩ መሣሪያዎችና ሌሎችንም ዘዴዎችን አልፎ በ16ኛው እና 19ኛው ክፍለ ዘመን መካከል እንግሊዝ በዘመናዊ ግብርና የላቀ የግብርና ምርት እድገትን አስመዝግባለች። እ.ኤ.አ. በ1843 ሳይንሳዊ የማዳበሪያ ምርምር ከመጀመሩም ባሻገር እንደ ሶዲየም ናይትሬትና ፎስፌት ያሉ ማዳበሪያዎችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎችም ተገንብተዋል። ግብርና በከፍተኛ ደረጃ መዘመን በታየበት፣ በ20ኛው ክፍለ ዘመን በ1901 የመጀመሪያው በቤንዚን የሚሠራ ትራክተር ከተመረተ በኋላ የግብርና ሥራ በፍጥነትም በጥራትም ማደግ ችሏል። በመካናይዜሽንና በምርምር እየበለፀገ የመጣው ግብርና ከመነሻው አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ የሰው ልጅ መሬትን አልምቶ፤ እንስሳን አልምዶ ህልውናውን ያስቀጥልበት ዘንድ ከተፈጥሮ የተሰጠው ስጦታው ነው ማለት እንችላለን። ባለንበት ዘመን፣ በሀብት የበለጸጉ አገራት የረቀቀ ግብርናን የመወዳደሪያ ዘርፍ አድርገውታል፤ በየጊዜው ለሚከሰቱ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮችም በምርምር የታገዘ መፍትሔን እየሰጡ ተጉዘዋል። በዚህም ሕዝባቸውን ከመመገብ አልፈው ለሌሎችም መትረፍ ችለዋል።
ግብርና ለኢትዮጵያም የህልውናዋ መሠረት፤ ገበሬም የሕዝቧ የዘመናት ባለውለታ ነው። የተለያዩ ዝርያዎችን ለማብቀል ምቹ የሆነ ሥነ ምህዳርንም ታድላለች። ዶ/ር አስናቀ ፍቅሬ፣ ‹‹ግብርናችን ሥልጣኔው ከእኛ እስከ ነጩ አብዮት›› (2010 ዓ.ም.) በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት፣ ኢትዮጵያ ዕድሜ ቆጠር ማረሻን ፈልስፋ 100 ሚሊዮን እስክንደርስ ለነበሩት 1500 ዓመታት መግባናለች። በአሁኑ ሰዓትም 17 ሚሊዮን ያህል አርሶ አደሮች 100 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ይመግባሉ። መጽሐፉ እንደሚናገረው፣ አገራችን በተፈጥሮ ሀብትም ሆነ በሰው ኃይል ያላት አቅም በቀላሉ ምርታማ መሆን የሚያስችላት ነው። ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ ግብርናችን መዘመንን ይሻል። ግብርናችንን የማዘመኑ ጉዞ ረጅም ርቀት የሚቀረው ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ዘርፉ በጉልህ የሚታዩ ለውጦችን እያስመዘገበ ይገኛል። ኢትዮጵያም ህልውናዋ ከግብርና ጋር የተቆራኘና ለግብርና እሴት ሰንሰለት ልማት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠች በመሆኗ ዘርፉን በጠንካራ ምርምርና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማገዝ የግድ ይላል። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ምርትና ምርታማነትን በዓይነትና በጥራት የሚጨምሩ፣ የአካባቢ ጉዳትን ለመቋቋምና ለመቀነስ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በማመንጨትና በማቅረብ በዋናነት የግብርናውንና የግብርና ኢንዱስትሪውን አዋጭነትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ አገራዊ ኃላፊነትና ወሳኝ ሚና ያለው ተቋም ነው።
በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር አጀማመር ከአምቦ፣ ጅማ እና ሃረማያ ኮሌጆች እንዲሁም ከግብርና ሚኒስቴር አመሠራረት ጋር ይያያዛል። ተቋሙ የካቲት 18 ቀን 1958 ዓ.ም. የእርሻ መካነ ጥናት ተብሎ በእርሻ ሚኒስቴር ስር በአዋጅ ትዕዛዝ ቁጥር 42/1958 በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ሲመሰረት፣ ዋና ዓላማው የአገሪቱን የግብርና ምርምር ፖሊሲ ለማዘጋጀት ብሎም የሰብል፣ የእንስሳትና የደን ልማትን ለማሻሻል እና ከሌሎች የአገሪቱ የልማት ዕቅዶች ጋር ለማጣጣም ነበር። ቆይቶም ስያሜው እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ተብሏል፤ አሁን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት በሚል የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። የምርምር ሥራዎቹ ውጤትም ለግብርና ምርት ማደግ ከሚሰጡት ጠቀሜታ በተጨማሪ ኢኮኖሚው እንዲያድግ እገዛ እያደረጉ ነው።
የእርሻ መካነ ጥናት ተብሎ ሲቋቋም በወቅቱ ለአገሪቱ እስትራቴጂክ ናቸው ተብለው የተመረጡ ስንዴና ገብስ ሰብሎች ላይ ሆለታ እና መልካሳ የምርምር ማዕከላት የተለያዩ ምርምሮችተከናውነዋል። የእርሻ መካነ ጥናቱ ከሁለት ማዕከላት በመነሳት የተለያዩ ስያሜዎችና ተልዕኮ ሲሰጠው ቆይቶ አሁን ሃያ የምርምር ማዕከላት እና አስራሁለት የምርምር ዘርፎች አሉት።
ኢንስቲትዩቱ ለግብርና ልማቱ ግብዓት የሚሆኑ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማላመድና በምርምር በማውጣት እንዲሁም፣ በተጠቃሚው ዘንድ ፍላጎት በመፍጠር እና ፍላጎት የተፈጠረባቸውንና ተቀባይነት ያገኙ ቴክኖሎጂዎችን ለተጠቃሚዎች በማቅረብ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። የምርምር ተቋሙ ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል የሰብል ምርት ምርምር አንዱ ነው። አገራችን ሰፊ የሆነ ሥነ ምህዳር ባለቤት እንደሆነች የጠቀሱት በኢንስቲትዩቱ የሰብል ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ታዬ ታደሰ፣ በአገራችን ለምግብ፣ ለኤክስፖርት እና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ የተለያዩ ሰብሎች እንደሚመረቱ ይጠቁማሉ። እርሳቸው እንደተናገሩት፣ ከምግብ ጋር በተያያዘ ወሳኝ ሰብሎች ከሚባሉት መካከል በቀዳሚነት የሚታወቀውና የሚመረተው ጤፍ ሲሆን፣ በቆሎም በስፋት ይመረታል። ስንዴ፣ ማሽላና ገብስም ጤፍና በቆሎን ተከትለው በብዛት ሲመረቱ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በተለይም ከከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ሩዝ በጣም ወሳኝ የምግብ ሰብል ሆኗል። ከጤፍ ጋር ቀላቅሎ የመጠቀም ሁኔታም እየሰፋ በመምጣቱ ከፍተኛ የሩዝ ፍላጎት ተፈጥሯል።
ለአገራችን ሕዝብ የምግብ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት በዋናነት በምግብ ሰብሎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ የመሥራት አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። አገራችንን በምግብ ራሷን ለማስቻል እንደ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ስንዴና ገብስ ያሉ የምግብ ሰብሎችን ምርት ከፍላጎት ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል። ከኑሮ ዘይቤ መለወጥ ጋር ተያይዞ ከቅርብ አመታት ወዲህ የስንዴ ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል። በአገር ውስጥ የሚመረተው ምርት የሕዝቡን የስንዴ ፍላጎት የሚያሟላ ባለመሆኑ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ከአጠቃላይ በጀቷ ቀላል የማይባለውን መዋዕለ ነዋይ ስንዴን ከውጭ ለማስገባት ታውል ነበር። ዶ/ር ድሪባ ገለቲ (2010 ዓ.ም.) ባደረጉት ጥናት እንደገለጹት ስንዴ በቤት ውስጥ ለሚጋገር ባህላዊ ዳቦና በኢንዱስትሪ ለሚመረቱ ዳቦ፣ ፓስታ፣ ማካሮኒና ብስኩት እንዲሁም ከሌሎች እህሎች ጋር ተቀላቅሎ ለእንጀራ ግብዓትን የሚያገለግል ሲሆን፣ በአገራችን ያለው የስንዴ ምርት ፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠንን ተከትሎ የጠቅላላውን የአገር ውስጥ ምርት ዘጠኝ ከመቶ ያህል ከውጭ ለማስገባት ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ይደረጋል። በእርዳታ የሚገኘው ስንዴ መጠንም ቀላል የሚባል አይደለም። በዚህ ቁጭት በመነሳሳት በአገራችን በተለይም ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት መንግሥት በልዩ ትኩረት በያዘው በስንዴ ምርት ልማት ከፍተኛ ምርት ማግኘት ችለናል። የስንዴ ምርት በተሰጠው ልዩ ትኩረት ትልቅ እመርታ እያሳየና ምርታማነቱ እየጨመረ የመጣ ዘርፍ ነው። ከሁለትና ሦስት ዓመት ወዲህ ስንዴ ከዚህ ቀደም በስፋት ከሚያመርቱ አካባቢዎች ውጪ በሌሎችም አካባቢዎች መዝራት እየተለመደ መምጣቱ ለውጤቱ መገኘት ትልቅ አበርክቶ አለው።
ከአራትና ከዚያም አመታት በፊት ስንዴ በሄክታር 15 ኩንታል ይገኝ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ይህንን ምርታማነት በሄክታር ከሦስት እጥፍ በላይ ማሳደግ ተችሏል። በተጠናቀቀው 2014 ዓመት በበጋ መስኖ የስንዴ ምርት ፕሮግራም አርሶ አደሮች በአንድ ሔክታር ከ40 እስከ 50 ኩንታል ምርት መሰብሰብ ችለዋል። በ2015 ዓ.ም. ደግሞ መስኖን በመጠቀም ምርቱን ከአምናው በእጥፍ በማሳደግ በአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ 52 ሚሊዮን ኩንታል፣ 101 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆነውን ደግሞ በመኸር በመዝራት በድምሩ 153 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማምረት ግብ ተጥሏል። ይህም የኢትዮጵያን የስንዴ ተረጂነት ታሪክ የሚለውጥ ግዙፍ የልማት ሥራ ነው።
የስንዴንም ሆነ የሌሎች ሰብሎች ምርታማነት ለማሳደግ የምርምር ዘርፉ ትልቅ ሚና አለው፣ የሰነድ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ ውስጥ ያልተሻሻለ የሰብል ዝርያ የለም፣ የበጋ ስንዴ ተብሎ እየተዘራ ያለው ዘር ከአገር ውስጥ የተገኘ ዝርያ ነው። በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የብሔራዊ ስንዴ ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ነጋሽ ገለታም ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር የሚያደርገው ምርምር ነው በማለት ቀደም ሲል የተነሳውን ሐሳብ ያጠናክራሉ፣ እርሳቸው እንደገለጹት፣ በየአመቱ ከአምናው የተሻለ ምርት የሚሰጥና በሽታዎችን መቋቋም የሚችል ዝርያን ለማውጣት የዝርያ ማሻሻያ ምርምር ይካሄዳል። በዚህም ኢንስቲትዩቱ በየአመቱ ከ5 እስከ 10 ኩንታል ብልጫ ያለው ምርት መስጠት የሚችሉ ዝርያዎችን ያወጣል። ምርታማነትን ከመጨመር ባለፈ በየጊዜው የሚመጡ በሽታዎችን የሚቋቋም ዝርያ ማምረት ካልተቻለ ምርትና ምርታማነትን ማስቀጠል አይቻልም። ለ2015 ዓ.ም. መኸር ወቅትም የተሻሻሉ ዝርያዎች ወደ ደብረ ማርቆስ፣ ሆለታና ሌሎችም የግብርና ምርምር ማዕከላት እየተሰራጩ እንዳሉ ጠቁመዋል። የኢንስቲትዩቱ ሥራ ዝርያ በማሰራጨት ብቻ ሳይወሰን የምርት ሂደቱም እንዲሳካ ክትትል ያደርጋል።
ኢትዮጵያ ያላት የማምረት አቅምና እያ መረትን ያለነው የምርት መጠን በንጽጽር ሲታይ ትልቅ ክፍተት ያሳያል ያሉት ዶ/ር ታዬ፣ አገራችን መልማት የሚችል 37 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ያላት ብትሆንም እኛ የተጠቀምነው ግን እስከ 17 ሚሊዮን ሄክታር ብቻ መሆኑን ያስረዳሉ። እንደ አገር ያለንን የማምረት አቅም በሚገባ ለመጠቀም የምርምር ዘርፉን ማጠናከር እንደሚያሻም አጽንዖት ሰጥተው ይናገራሉ። የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትም ምርታማነትን ለመጨመር እንደ ምርምር ተቋም በርካታ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በየጊዜው እያወጣ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ለማሳያ ያህል ነባሩ የስንዴ ዝርያ በሄክታር 28 ኩንታል ይሰጥ የነበረ ሲሆን፣ ምርታማነትን በእጥፍ በሚያሳድግ ዝርያ በመተካት ዛሬ በሄክታር ከ50 እስከ 55 ኩንታል ስንዴ ማግኘት ተችሏል። በቆሎም ባለፉት ጊዜያት በሄክታር 42 ኩንታል ብቻ ይገኝ የነበረ ሲሆን፣ ተቋሙ ያወጣቸው ዝርያዎች ግን በሄክታር እስከ 90 ኩንታል ማስገኘት ችለዋል።
አገራችን በምታበቅላቸው ሰብሎች ላይ በተደረጉ ምርምሮች በአገር ደረጃ እስካሁን ከ1400 በላይ ዝርያዎች የተመዘገቡ መሆናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በወሳኝ የምግብና የጥራጥሬ ሰብሎች ላይ የሚሠሩ የምርምር ሥራዎች ባለፉት አምስት አመታት ሼልፍ ላይ የሚቀሩበት ሁኔታ በእጅጉ ቀንሷል። አንድ ቴክኖሎጂ እንደወጣ ወደ ተጠቃሚው የመሄዱ ዕድልም እየሰፋ መጥቷል።
ለዚህም በዋናነት አዳዲስ የሚወጡ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚውን ማዕከል ያደረጉ እንዲሆኑ በመደረጉና ባለፉት አመታት በግብርና ኤክስቴንሽን አደረጃጀቶች በተሠሩ ቴክኖሎጂን የማስተዋወቅ ሂደቶች የአርሶ አደሩ የግብርና ቴክኖሎጂ እውቀት ማደጉ ቴክኖሎጂ መጠቀምን እንዲሻ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖን አበርክቷል። የምርምር ውጤቶችን ወደ ተግባር በመለወጥ በኩል በርካታ ለውጦች ቢኖሩም፣ በምርምር የሚወጡ ዝርያዎች ሙሉ በሙሉ ወደተጠቃሚው ደርሰዋል ማለት ግን እንደማይቻል ዳይሬክተሩ ይናገራሉ።
እንደ እርሳቸው አባባል፣ ዝርያ መልቀቅ ትልቁ ሥራ ቢሆንም፣ ከተለቀቀ በኋላ የማስተዋወቅና ዝርያውን አባዝቶ የማቅረብ ሥራዎችም የተቀናጀ ሥራን ይጠይቃሉ። ለምሳሌ በስንዴ ላይ በየሁለት አመቱ ቢያንስ አንድ ዝርያ ይለቀቃል። በሌሎችም ሰብሎች ላይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በየጊዜው ይወጣሉ። ይህም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚወጡባቸው አጋጣሚዎች ሰፊ መሆናቸውን ያሳያል። 10 አመታትን ወደኋላ ተመልሰን ካለንበት ጊዜ አንጻር ስንመለከተው በብዙ ሰብሎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የምርታማነት እድገት ታይቷል። የምርምር ሥርዓቱ ብቻ ሳይሆን የአርሶ አደሩም ቴክኖሎጂን የመጠቀም ልምዱ እየዳበረ መጥቷል። ይህም ሆኖ፣ አንድ ቴክኖሎጂ ከወጣ በኋላ የማስተዋወቅና የማባዛቱ ሥራ በመንግሥት ደረጃ በትኩረት ተወስዶ ስላልተሠራበት ብዙ ዝርያዎች ከወጡ በኋላ ለረጅም አመታት ወደ ምርት ሳይገቡ ቆይተዋል። ካለፉት አራት አመታት ወዲህ ግን፣ የኢትዮጵያን የመልማት አቅም ታሳቢ አድርጎ መንግሥት በወሰደው እርምጃ በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል። በ72 ሄክታር ላይ የተጀመረውን የመስኖ ስንዴ ልማት አሁን ወደ 3 ሚሊዮን ሄክታር ማድረስ ተችሏል። ይህ ሥራ ውጤታማ እንደሚሆን ያመላከተው ደግሞ የምርምሩ ዘርፍ ነው። ከምርምር ዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ደግሞ ዘርፉን እንዴት እናሳድገው ያሉንን ቴክኖሎጂዎችስ እንዴት እናስፋ የሚሉት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው።
ለረጅም ጊዜ በእርሻ ላይ እንደቆየ አገር እና ረጅም ጊዜ እንዳስቆጠረ የምርምር ሥርዓት አሁን ያለንን ምርት ስናየው በቆይታችን ልክ ያደገ አይደለም ያሉን በኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ ሩዝ ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ሙሉጌታ አጥናፍ ናቸው። አክለውም ብዙ የሚቀረን ቢሆንም፣ በተለይ በተወሰኑ የሰብል ምርቶች ላይ እመርታዊ ለውጥ ተመዝግቧል ይላሉ። በቆሎን በምሳሌነት ጠቅሰው ሰብሉ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ሥርዓት ባመነጨው ቴክኖሎጂ አማካኝነት ምርታማነቱ በከፍተኛ መጠን መጨመሩን ጠቁመዋል። ከበቆሎ በተጨማሪ ሌሎችም ሰብሎች ምርታማነታቸው ከአመት አመት እየጨመረ እንደመጣም ተናግረዋል። እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፣ ከሌሎቹ ሰብሎች አንጻር ሲታይ በቅርቡ በሚባል ጊዜ ወደ አገራችን የገባው የሩዝ ሰብል በአሁኑ ሰዓት በሄክታር 31 ኩንታል እየሰጠ ይገኛል። ይህም ከምርቱ አዲስ መሆን፣ አርሶ አደሮቻችንም ሩዝ የማምረት ልምድ የሌላቸው ከመሆናቸው አኳያ ሲታይ በጣም የተሻለ የሚባል ምርት እየሰጠ ያለና ለወደፊቱም ተስፋ የሚጣልበት ሰብል ነው። አገራችንም ለሩዝ ምርት የተመቸ ፀጋ አላት። እንደ ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎና ሌሎችም የተለመዱ ሰብሎች በጉልህ በሚታይበት ደረጃ ላይ ባደርስም ያለው ጅምር መልካም መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ሙሉጌታ በሰብሉ ላይ በርካታ ምርምሮች እየተሠሩ አሁን የደረሰበት ደረጃ ቢደርስም አሁንም ሁሉም ቴክኖሎጂዎች አርሶ አደሩ ጋር ደርሰዋል ማለት እንደማይቻል ይናገራሉ።
አስተባባሪው እንዳስረዱት፣ ሩዝ ልክ ለስንዴ ይወጣ እንደነበረው ሁሉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን የሚያስወጣ ሰብል ነው። የዓለምን ሕዝብ በመመገብ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የሩዝ ሰብል በአገራችን ፍላጎቱ እየጨመረ በመምጣቱ በአገር ውስጥ ምርት የሚሸፈነው 20 ከመቶ ብቻ ሲሆን፣ ሌላው ከውጭ በሚመጣ ሩዝ የሚሸፈን ነው። በሩዝ ምክንያት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ከማስቀረት አንጻር ስንዴ ላይ የመጣው ውጤታማነት ሌሎችም ሰብሎች ላይ መደገም አለበት በሚል መርህ በሰነድ ደረጃ ብዙ ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር ባይገባም እንቅስቃሴዎቹ ተስፋ የሚሰጡ መሆናቸውን አስተባባሪው ይናገራሉ። አገራችን ስንዴን ለማምረት የሚመች ፀጋ ያላት ስትሆን፣ የበለጠ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ አካባቢዎችና ቴክኖሎጂዎችን እየፈተሸን ነው ያሉን ዶ/ር ሙሉጌታ፣ እስከ 50 ኩንታል በሄክታር መስጠት የሚችሉ የሩዝ ዝርያዎች መኖራቸውንና ጥረቶቹ ተጠናክረው ከቀጠሉ በከፍተኛ ደረጃ ምርታማ የመሆን ዕድል አለን በማለት ተስፋቸውንም ገልጸዋል።
የልማት ሥራን በቴክኖሎጂ መደገፍ በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ በመግለጽ የግብርና ልማትን በቴክኖሎጂ መደገፍ ካልተቻል ውጤታማነታችን ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል ያሉት ዶ/ር ሙሉጌታ ልክ እንደ ዶ/ር ታዬ ሁሉ የምርምር ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ረገድ በብዙ ሰብሎች ላይ ምርምሮች እየተሠሩ ቢሆኑም በጠቅላላ ጥቅም ላይ ውሏል ወይም ተጠቃሚው አርሶ አደር ጋር ደርሷል ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር አያይዘውም የሚወጡ ቴክኖሎጂዎች በተጨማሪ ለውጥ እንዲያመጡ ዘርፉ አሁን ካለው የተሻለ ድጋፍ እንደሚያሻው አስምረውበታል።
የዝርያ ለውጥ ብቻ በራሱ ምርት እንደማይጨምር የጠቆሙት ዶ/ር ታዬ፣ የመሬት ለምነትም ሌላው ዋነኛ ግብዓት መሆኑን ጠቅሰዋል። አንዳንድ ቴክኖሎጂዎች በአምራቹና አስመራቹ በአጠቃላይ በምርት ሂደት ውስጥ ባሉ አካላት ዘንድ ያለው የግንዛቤ አነስተኛ መሆን ቴክኖሎጂውን ወደ ተጠቃሚው ወስዶ ለማስፋትና ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ የራሱ ውስንነቶች እንዳሉት ያነሱት ዶ/ሩ፣ ከዚህ በተጨማሪም፣ ከፍተኛ ዝናብ ባለባቸው የአገራችን አካባቢዎች የአፈር አሲዳማነት የአፈር ለምነትን በመቀነስ ትልቅ ተግዳሮት እየሆነ እንዳለም አንስተዋል። የአፈርን ለምነት በመጠበቅ፣ የተለያዩ ዝርያዎችን በመጠቀም፣ ከዘር እና ከሌሎች ግብዓቶች አቅርቦትጋር የተያያዙ ችግሮችን በመቅረፍና አርሶ አደሩ አምርቶ በምርቱ ተጠቃሚ መሆን የሚችልበትን ሁኔታ በማጠናከር ምርትና ምርታማነትን አሁን ካለበት መጠን በተሻለ መጨመር ይችላል ብለዋል። አያይዘውም፣ አሁን በገበያ ላይ የሚታየው የሰብል ምርቶች የዋጋ ግሽበት ከምርት ማነስ ጋር የሚያያዝ ነው ብለው እንደማያስቡ ገልጸው፣ ተጨማሪ ጥናትን የሚጠይቅ ቢሆንም፣ በአገር ውስጥ ብቻ እየተመረተ ያለው ምርት ከአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር አንጻር ሲታይ በቂ ነው ብለው እንደሚያስቡ ያላቸውን አመለካከት ገልጸዋል። ለዚህም አገራችን ከበልግና ከክረምት ዝናብ በተጨማሪ በመስኖም በመታገዝ ሰፊ የስንዴ ልማት እየሠራች መሆኑን ለማሳያነት አንስተው «ይልቁኑ ለፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ዋነኛው ምክንያት፣ በሚገባ ሊፈተሽ የሚገባው የግብይት ሥርዓት ሰንሰለት» ነው በማለት ይጠቁማሉ። የግብይት ሥርዓቱን ከመፈተሽ ባሻገር፣ በአገር ውስጥ የሚመረተውን ሰብል በአግባቡ ለመጠቀም ምርቶች በኮንትሮባንድ ከአገር እንዳይወጡ መከላከል እንደሚያስፈልግም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዶ/ር ታዬ፣ በዘንድሮው መኸር ወቅት ከበልግ ጀምሮ በተለይ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ሰፊ የሆነ የዝናብ ስርጭትና መጠን መኖሩ በእርሻ ሴክተሩ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ስጋታቸውን ጠቆም አድርገው፣ ኢንስቲትዩቱ ግን እንደ ምርምር ተቋም ፍላጎትን መሠረት በማድረግ በ99 ዝርያዎች ላይ በደቡብ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሲዳማ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች የመነሻ ዘር አቅርቦት ሠርቶ ለአባዢዎች እያስተላለፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል። አክለውም የማዳበሪያ ስርጭትም በሰፊው እየተሠራ እንዳለ ጠቁመዋል። ለመኸር ወቅቱ ሰፊ ርብርብ ከተደረገና ወቅቱን ጠብቆ ግብዓት ለአርሶ አደር ከቀረበ የሚቀጥለው ዓመት የተሻለ ምርት የሚገኝበት አመት ሊሆን እንደሚችልም ተስፋቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለግብርና የተሰጠ ምቹና ሰፊ ፀጋ ያላት ብትሆንም፣ ይህን ፀጋ በተገቢ ልክ ሳትጠቀምበት ቆይታለች። ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን፣ ተስፋ ሰጪ ጥረቶች ይታያሉ። ጥረቶቹ ይበሉ የሚያሰኙ ቢሆኑም፣ ዛሬም ግብርናችንን ከበሬ ቀንበር ለማውረድ ረዥም ርቀት ይቀረናል። ስለሆነም፣ ዘርፉን ለማዘመን በመስኩ የሚካሄዱ ምርምሮችን ማበረታታት፣ የምርምር ሥራዎች በሰነድ ላይ ብቻ እንዳይቀሩና ወደ ውጤት እንዲቀየሩ በፋይናንስና በቴክኖሎጂ መደገፍ ያስፈልጋል። አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ በስንዴ የታየውን ምርታማነት በሌሎችም ሰብሎች ለመድገም እንበርታ የሚለው የዘመን መጽሔት የማሳረጊያ መልዕክት ነው።
ዮርዳኖስ ፍቅሩ