የሽግግር ፍትህ ለምን?

የሽግግር ፍትህ አስከፊ ግጭቶችን፣ ጭቆናዎችን እና የመብት ጥሰቶችን ተከትሎ ተጠያቂነት እንዲኖር፤ ፍትህ እና እርቅ እንዲሰፍን በማድረግ ዘላቂ ሠላም የሚፈጥሩ ሥራዎችን የሚያጠቃልል ሂደት መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ይገልጻል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአገራትና ማህበረሰቦች ከደረሰባቸው መጠነ ሰፊ የመብቶች ጥሰት ሁኔታ በመውጣት ተጠያቂነትን፣ ፍትህን እና እርቅን ባማከለ መልኩ የሚያከናውኑት የሽግግር ፍትህ ሂደትን መደገፍ እንደሚገባው በመግለጽ በተለያዩ አገራት የተሞከሩ የሽግግር ፍትህ ሂደቶችን ማገዙ በ “United Nations Approach to Transitional Justice, Guidance Note of the Secretary- General, 2010.” ተገልጿል።

በአፍሪካም በ2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ የፀደቀው የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ማዕቀፍ (The AU Transitional Justice Policy 2019) ፣ የሽግግር ፍትህ – አገራት የተለያዩ መደበኛ እና ባህላዊ እንዲሁም መደበኛ ያልሆኑ የፖሊሲ እርምጃዎችን እና ተቋማዊ አሠራሮችን ተጠቅመው ያለፉ ጥፋቶችን፣ ክፍፍሎችንና አለመመጣጠኖችን ለማስወገድና ለደኅንነትም ሆነ ለዴሞክራሲያዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሥርዓት ግንባታ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚደረግ ጠቃሚ እና አስፈላጊ ሂደት እንደሆነ ይገልጻል።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በተለያዩ የዓለም አገራት የተለያየ ይዘት ያላቸው የሽግግር ፍትህ ስራዎች ተግባራዊ ሆነዋል። በተለይም በደቡብ አሜሪካና በአፍሪካ አገራት የሽግግር ፍትህ አሰራሮች በተለያየ መጠን ተተግብረው በርካታ ተሞክሮዎች ተቀምረዋል። ከነዚህ አገሮች የተሳካ የሽግግር ፍትህ ልምድም ሌሎች አገራት ሊያከናውኗቸው የሚገቡ ተግባራት እና ሊከተሏቸው የሚገቡ ሂደቶችን ለመለየት ተችሏል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት ለተፈጸሙ በደሎች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በማሰብ ሊተገበር ለታቀደው የሽግግር ፍትህ ሂደት አማራጮች የቀረቡበት ሰነድ ይፋ መደረጉ ይታወሳል። በፖሊሲ አማራጮቹ ላይ ብሔራዊ ምክክር ለማስጀመር በተሰናዳ መድረክ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን፣ በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ የሽግግር ፍትህን ተግባራዊ ማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው ነበር። የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጤሞቲዎስ በበኩላቸው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ጨምሮ ባለፉት አራት ዓመታት በነበሩ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች በፌዴራል ደረጃ ብቻ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች መከሰሳቸውንና ይህ ቁጥር ከቀይ ሽብር ተከሳሾች በላይ መሆኑን በመጥቀስ ክስተቱ የሽግግር ፍትህ አስፈላጊነትን ያጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢ.ፌዴ.ሪ. ፍትህ ሚኒስትር “የሽግግር ፍትህ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች” በሚል ርዕስ ጥር 2015 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው ከባለድርሻ አካላት ግብዓት ለመሰብሰብ የተዘጋጀው ሰነድ ላይ እንደተገለጸው፤ ከእርስ በእርስ ጦርነት፣ ግጭት እና ጭቆና በመውጣት በፖለቲካና በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትርጉም ያለው ሽግግር ለማድረግ በሞከሩ አገራት የሽግግር ፍትህ ሂደቶች ተግባራዊ ተደርገዋል። የሽግግር ፍትህ ስርዓት መዘርጋቱ ዘላቂ ሰላም፣ እርቅ እና ፍትህ በማስገኘት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክቷል።

ኢትዮጵያም በተለያዩ ጊዜያት በሽግግር ሁኔታ ውስጥ ብታልፍም በተሟላ መልኩ የሽግግር ፍትህ አላባዎች ተተግብረው አያውቁም። በእነዚህ የሽግግር ሂደቶች ያለፉ ጉልህ የሰብዓዊ መብቶች ጥስቶች፣ በደሎች እና ጭቆናዎችን መንስኤ፣ ምንነት፣ አይነት እና የጉዳት መጠን በበቂ መንገድ በማጣራት፣ እውነትን በማውጣት እና እውቅና በመስጠት በተጠያቂነት፣ በይቅርታ እና በእርቅ ላይ የተመሰረተ የተሟላ ሂደት አልተከናወነም።

የደርግ መንግስት የአፄ ኃይለስላሴን መንግስት ከስልጣን ካስወገደ በኋላ በንጉሱ ሥርዓት ዘመን መጠነ ሰፊ በደል ፈፅመዋል፤ ካለአግባብ በልጽገዋል እና ለወሎው ረሃብ እልቂት ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን መኳንንቶች፣ መሳፍንቶች፣ ሚኒስትሮች እና ሌሎች ባለስልጣናትን አስሯል። የነዚህን ባልስጣናት ጉዳይ እያጣራ ለፍርድ የሚያቀርብ አምስት አባላት ያሉት አጣሪ ኮሚሽንም ተቋቁሞ ነበር። አጣሪ ኮሚሽኑ ምርመራውን ማካሄድ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ምርመራውን ከማጠናቀቁ በፊት ደርግ ከ50 በላይ በሚሆኑት ባለስልጣናት ላይ የሞት ፍርድ ውሳኔ በማስተላለፍ እርምጃ እንዲወሰድ አድርጓል።

በ1983 ዓ.ም ኢህአዴግ በትረ-መንግስቱን ጨብጦ የሽግግር መንግስት ሲመሰርት ሲሆን በደርግ አስተዳደር ዘመን ለተፈጸሙ ጥሰቶች ምላሽ ለመስጠት የወንጀል ክስ መመስረትን እንደ ዋነኛ መንገድ ተጠቅሟል። በአዋጅ ቁጥር 22/1985 መሰረት ተጠሪነቱ በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ ልዩ የዓቃቤ ሕግ ፅህፈት ቤት የተቋቋመ ሲሆን በስሩም ከ400 በላይ ሰራተኞች ነበሩት። የፅህፈት ቤቱ ዋና ስራም የደርግ ባለስልጣናት የፈጸሟቸውን ወንጀሎች መመርመር፣ ክስ መመሰረት እና ማስቀጣት ነበር። በዚህም መሰረት በተለያዩ ሰዎች ላይ ምርመራዎችን በማጣራት፣ በመደበኛው ፍርድ ቤት ክስ በመመስረት እና በመከራከር ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምን ጨምሮ በበርካታ ተጠርጣሪዎች ላይ የቅጣት ውሳኔ እንዲሰጥ አድርጓል። በዚህ ሂደት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ምስክሮች እና የሰነድ ማስረጃዎችን የማደራጀት እና ክስ የመመስረት ስራ ተሰርቷል።

በ2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ መንግስት ያለፉ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን፣ ቁርሾዎችን እና በደሎችን በእውነት፣ በእርቅ እና በፍትህ ላይ ተመሰርቶ በመፍታት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መንገዱን ለማመቻቸት በርካታ የሽግግር ፍትህ እርምጃዎችን ወስዷል። ለደረሱ በደሎች እንደመንግስት በይፋ ይቅርታ የመጠየቅ፤ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን የማቋቋም፤ ክስ፣ ምህረት እና ለሽግግር ፍትህ ሂደት አስተዋፅዖ የሚያደርጉ የህግ እና የተቋማት ማሻሻያ ስራዎችን የማሻሻል ተግባራት ተከናውነዋል። ይሁንና የሽግግር ፍትህ በተሟላ እና ወጥ በሆነ መልኩ የሚተገበርበት የፖሊሲ አቅጣጫ ባለመኖሩ እንዲሁም የተወሰዱት እርምጃዎች የየራሳቸው ጉድለቶች ስለነበሩባቸው የሽግግር ፍትህ ሂደት ዓላማን ማሳካት አልተቻለም።

በየትኛውም አገር ተግባራዊ የሚደረግ የሽግግር ፍትህ የሚተገበርባቸው አማራጮች እና መንገዶች በአገሩ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበረሰባዊ እና ፖለቲካዊ አውድ እንዲሁም በሽግግር ሂደቱ ባህሪ ላይ ተመስርቶ ሊወሰን ይገባል። የሽግግር ፍትህ ሂደት ክስን፣ እርቅን፣ ምህረትን፣ እውነትን፣ ማካካሻን፣ ተቋማዊ ማሻሻያን እና ሌሎች ተገቢነት ያላቸው የሽግግር ፍትህ አላባዎችን በአንድነትና በተመጋጋቢነት ያካተተ ሁለንተናዊ አካሄድ ነው። እነዚህ ስልቶች የአገራትን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት እና ተገቢ ተቋማዊ አደረጃጀትን በመጠቀም ሲተገበሩ የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ። ኢትዮጵያ አሁን በሽግግር ሂደት ውስጥ ያለች አገር እንደመሆኗ መጠን የሽግግር ፍትህን ተግባራዊ ማድረግ ይገባታል።

ፍትህ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው የጥናት ሰነድ እነደገለጸው በኢትዮጵያ አሳታፊ የሆነ፤ ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ፤ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት መርሆችንና ድንጋጌዎችን ያከበረ፤ በሌሎች አገራት እና በአገራችን ከነበሩ ልምዶች ትምህርት የሚወስድ እንዲሁም የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ አውድ ግንዛቤ ውስጥ የሚያስገባ የሽግግር ፍትህ ሂደት በመቀመር እና በግልፅ የፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲመራ በማስቻል ተግባራዊ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ የሚሆንባቸው አራት ምክንያቶች አሉ።

የመጀመሪያው የአገራዊ አውዱ ሁኔታ የተሟላ የሽግግር ፍትህ ስርዓት ሂደትን መተግበር አስፈላጊ እንደሆነ የሚያመላክት መሆኑ ነው። በኢትዮጵያ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ስልታዊና መጠነ ሰፊ በሆነ ሁኔታ ሲፈጸሙ የነበረ ስለመሆኑ በርካታ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ የፍትህ ማሻሻያ ስራዎች ቢሰሩም፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ አለመረጋጋት፣ ግጭቶች እና የእርስ በርስ ጦርነት በመቀጠሉ አሁንም ዜጎች ለሞት፣ ለስደትና ለንብረት ውድመት እየተጋለጡ ይገኛሉ። ከዚህ የጥፋት አዙሪት እንዳንወጣ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል በአገራችን የነበሩ የተደራረቡ በደሎች፤ የመብት ጥሰቶች፣ የተዛነፉ የታሪክ አረዳዶች፤ ለእነዚህ ጥሰቶች የተሰጡ ምላሾች ምሉዕ አለመሆን፤ በዜጎች ላይ ለተፈፀሙ ጥሰቶች ፍትህ አለማግኘት፤ ተጎጂዎች አለመካሳቸው እና አገራዊ እርቅ አለመከናወኑ ተጠቃሽ ናቸው።

የአጥፊዎች እና የተጎጂዎች ብዛት፤ የበደሎች መደራረብ እና የጥፋቶች ማህበረሰባዊ ቅርፅ መያዝ ህዝቡ ለፍትህ ተቋማት ካለው ያነሰ ቅቡልነት ጋር ተዳምሮ በመደበኛው የፍትህ ሥርዓት እና አካሄድ ለሁኔታዎች ፍትህ መስጠትም ሆነ ይቅርታና እርቅ ማከናወን እንዳይቻል አድርጎታል። ይህም የአገሪቱን አሁናዊ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ፤ ያለፈውን በአግባቡ የሚያስተናግድ፤ ለነገም መሰረት ለመጣል የሚያስችል፤ በዓለም አቀፍ እና አገራዊ ልምዶች የተቀመረ እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተለያዩ አጀንዳዎችን ይዘውና ነፍጥ አንግበው የሚታገሉ ቡድኖችን ትጥቅ አስፈትቶ ከማህበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ የሚያደርግ፣ የተሟላ የሽግግር ፍትህ ሂደት መተግበር ግድ ይላል። ይህ አይነቱ አካሄድ ኢትዮጵያ ካሉባት ውስብስብ ችግሮች አዙሪት እንድትወጣ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋል።

ሁለተኛው ምክንያት የተሳካ የሽግግር ፍትህ ሂደት ለአገረ መንግስቱ ግንባታ እና ቀጣይነት የሚኖረው ሚና ከፍ ያለ መሆኑ ነው። በአገራችን ከነበረው የጥፋት አዙሪት ለመውጣት እና ለተፈጠሩ ጥሰቶች አግባብ ያለው ምላሽ ለመስጠት በእውነት፣ በፍትህ፣ በሰላም እና በእርቅ ላይ በመመስረት ማህበራዊ ግንኙነቶችን ማደስ እጅግ አስፈላጊ ነው። በታሪክ ኢትዮጵያ እውነተኛ የእርቅ ሂደትን አድርጋ የምታውቅበት ወቅት ወይም አጋጣሚ የለም። በዚህም ምክንያት በአገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ቁርሾዎች አግባብነት ባለው መልኩ ሳይፈቱ እየተንከባለሉ ያለንበት ዘመን ላይ ደርሰዋል።

በአገሪቱ የነበሩና የቀጠሉ ውስብስብ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ካልተበጀላቸው ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነትን የሚያሳዩ ተፃራሪ ትረካዎች ህብረተሰቡን በተለያየ መንገድ ማቁሰላቸውን እንዲቀጥሉ ያደርጋል። በመሆኑም የተከፋፈለውን ህዝብ ለማቀራረብ፣ የሻከረውን ግንኙነት ለመጠገን፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና እርቅ ለመፍጠር የሽግግር ፍትህ ዘዴዎችን መጠቀም ያስፈልጋል።

ሦስተኛው ምክንያት የተሳካ የሽግግር ፍትህ ሂደት ሳይተገበር የዲሞክራሲ ሽግግርም ሆነ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የማይቻል መሆኑ ነው። በተለያዩ አገሮች እንደተስተዋለው ያለፉ በደሎች እና ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአግባቡ ሳይፈቱ፤ ሙሉ እውነት ሳያወጣ፤ ተጠያቂነት ሳያሰፍን እና እውቅና ሳይሰጥ በእርቅ፣ በሰላም እና በፍትህ ላይ የተመሰረተ የተሳካ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ማድረግ አዳጋች ነው። ስለዚህ በአገራችን በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙ ጉልህ የመብት ጥሰቶች እና ቁርሾዎች አግባብነት ባለው መልኩ ተፈተው በደሎቹ እንዲሽሩ፤ ቁርሾዎች እንዲጠገኑ፤ ወደ ዲሞክራሲ የሚደረገው ሽግግር እንዲሳካ እንዲሁም ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ እንዲቻል የተሟላ የሽግግር ፍትህ ሂደት መተግበር እጅግ ጠቃሚ ነው።

አራተኛውና የመጨረሻው የሽግገር ፍትህ አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት፣ የሽግግር ፍትህ ሥርዓትን መተግበር ለሰብዓዊ መብት መከበር እና ለህግ የበላይነት መረጋገጥ የሚኖረው አስተዋጽዖ የማይተካ መሆኑ ነው። በኢትዮጵያ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈፀመ ቢሆንም ሁሉንም አጥፊዎች እንደየጥፋታቸው በእኩል ደረጃ ተጠያቂ የሚያደርግ ሥርዓት አለመኖሩ ጥሰቶቹ ተደጋግመው ለመከሰታቸው አንዱ ምክንያት ሆኗል። በአብዛኛው እነዚህ ጥሰቶች የተፈፀሙት ምንም አይነት የፖለቲካ ተሳትፎ በሌላቸውና ስለነገሩም ምንም ግንዛቤ ባልያዙ ኢትዮጵያውን ላይ ነው። ድርጊቶቹ እንዳይፈፀሙ የመቆጣጠር ወይም የመከላከል ኃላፊነት ያለባቸው የመንግስት ኃላፊዎች እና የማህበረሰብ ልሂቃኖችም ነገሮች እንዲባባሱ ጉልህ አስተዋፅዖ ሲያደርጉ ታይተዋል።

እነዚህ ድርጊቶች ተደጋግመው ስለሚፈፀሙ እና ከተፈፀሙ በኋላም ምርመራውም ሆነ የክስ ሂደቱ ተጎጂዎችን ያላማከለ እና በህብረተሰቡም እምነት የተጣለበት ባለመሆኑ በሂደት ህዝቡ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ያለው እምነት አናሳ እንዲሆን አድርጎታል። ስለሆነም ሁሉን አቀፍ የሽግግር ፍትህ ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረግ ተቀባይነት ያለው የክስ ሂደት እንዲኖር፤ ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተገቢ ትኩረት እንዲሰጥ፤ የተጠያቂነት ሥርዓት እንዲጠናከር፤ ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረግ የይቅርታ፣ እርቅ እና ማካካሻ ስርዓት እንዲኖር በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች ባህል መዳበር እና ለህግ የበላይነት መረጋገጥ መሰረት ይጥላል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ የሽግግር ፍትህ አራት ዓላማዎች እንዳሉት ያናገራሉ። ቀዳሚው እውነትን መፈለግ እና ማወቅ ሲሆን፣ ሁለተኛው የተጎዱት ሰዎችን መልሶ ማቋቋም ነው። ሦስተኛው የወንጀል ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንዲሁም አራተኛውና የመጨረሻው ዓላማ ደግሞ ዳግም ተመሳሳይ ነገር እንዳይከሰት ምን አይነት ለውጥ እና ማሻሻያ ያስፈልጋል? የሚለውን በመመርመር የሕግ ማሻሻያ ወይም የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ ነው።

በሽግግር ፍትህ ሂደት መተግበር ከሚኖርባቸው ስልቶች አንዱ የወንጀል ምርመራ በማድረግና ክስ በመመስረት ጥፋት ፈፃሚዎች የሚቀጡበትን ሂደት መዘርጋት ነው። በሽግግር ፍትህ ሂደት የወንጀል ክስ ተገቢ ተደርጎ የሚወሰደው በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች በአገራት ላይ ከተጣሉ ግዴታዎች ውስጥ አንዱ ሰብዓዊ መብቶችን የመጠበቅ ግዴታ (duty to protect) በመሆኑ ነው። ይህም በተለይ የመክሰስ ግዴታን የሚያካትት ነው። በተጨማሪም ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈፀሙ፣ መንግስት ተጠያቂነትን የማስፈን ግዴታ ያለበት ስለመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጡት የጄኔቫ ኮንቬንሽን፣ የዘር ማጥፋትን የሚመለከተው ኮንቬንሽን እና ድብደባና ሌሎች ጉልህ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የወጣው ኮንቬንሽን ያመለክታሉ። የአፍሪካ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲም ለተወሰኑ የወንጀል ድርጊቶች የመክሰስ ግዴታን ያስቀምጣል። ይህን ኃላፊነት መወጣት ፍትህ የማግኘት መብትን ያረጋግጣል፤ በጥፋተኞች መካከል ግለሰባዊ ኃላፊነትን ስለሚያስከትል፣ በተደጋጋሚ ከሚያጋጥም የጅምላ ፍረጃ የሚጠብቅ ነው። የህግ የበላይነት እና ተጠያቂነት እንዲኖር ስለሚያደርግም ተመሳሳይ ክስተቶች እንዳይደገሙ ይከላከላል። በተጓዳኝም እውነቱን በመግለፅ እርቅን ሰላምን እና ዲሞክራሲን ያበረታታል።

በሽግግር ፍትህ ሂደት እውነት ማፈላለግ ያለፈን የሰብዓዊ መብት ረገጣ እና የደረሰን ጉዳት የማወቅ እና በይፋ እውቅና የመስጠት ሂደት ነው። ተጎጂዎች ወይም ቤተሰቦቻቸው እና ማህበረሰቡ በአጠቃላይ ያለፈውን እውነት የማወቅ መብት አላቸው። እውነትን ማፈላለግ እና ይፋ ማውጣት በራሱ ለተበዳዮች እና ለተበዳይ ቤተሰቦች የፍትህ አይነት ነው። በአገር ደረጃም የነበሩት ክስተቶች እውቅና ሲሰጣቸው በይፋ ተገልፀው የአገሪቱ ታሪክ አካል ሲሆኑ ለትውልድ እና ለብሔራዊ እርቅ መሰረት ይጥላሉ። በሽግግር ፍትህ ሂደት እውነትን የማጣራት ተግባር በዋናነት የተጎጂዎች እና ጥፋት ፈፃሚዎችን ቃል የመሰብሰብ (statement taking) እና ህዝባዊ መድረኮችን (public hearing) የማመቻቸት ስራን ያካትታል። በሌሎች አገራት ልምድ እንደታየው በሽግግር ፍትህ ሂደት እውነትን የማጣራት ተግባር በሂደቱ ለሚቋቋሙ የእውነት አጣሪ ኮሚሽኖች የሚሰጥ ስራ ነው።

እርቅ ሌላው የሽግግር ፍትህ ሂደት የሚያልፍበት መንገድ ነው። አንደኛው ግብ ወይም ዓላማ ተብሎም ሊገለጽ ይችላል። እርቅ በነበረ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ጦርነት፣ ግጭት፣ ወይም ጭቆና በተከተለ መጎዳዳት፣ ጥላቻና መፈራራት ምክንያት ተለያይተው፤ ተራርቀው እና ተቆራርጠው የነበሩ ሰዎችንና የህብረተሰቦች ክፍሎች የፈረሰውን የጋራ ኑሯቸውን እንዲሁም ግንኙነታቸውን እንደገና ለመገንባት የሚጓዙበት ሂደት ነው። በሽግግር ፍትህ ሂደት እርቅ የሚኖረው ሚና በሽግግሩ ባህሪ ላይ የሚመሰረት ነው። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈፀሙባቸው በነበሩ ስርዓቶች ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ አመራሮች ወይም ግለሰቦች ለእርቅ ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ ያስፈልጋል።

በሽግግር ፍትህ ሂደት ምህረትን እንደ አንድ የመሸጋገሪያ መፍትሄ ይወሰዳል። ምህረት ለሰላም ግንባታ፤ ተጨማሪ ግጭቶችን ለመከላከል እና ማህበረሰቦችን ለማከም ከፍተኛ ፋይዳ አለው። ሆኖም ያለቅድመ ሁኔታ የሚሰጥ ምህረት የፍትህ መጓደልን ስለሚያስከትል እና ተጠያቂነት እንዳይኖር በማድረግ ለቀጣይ ቁርሾ መነሻ ስለሚሆን ተቀባይነት አይኖረውም። ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችም ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለፈፀሙ ሰዎች ያለቅድመ ሁኔታ የሚሰጥ ምህረት ሰብዓዊ መብቶችን የማረጋገጥ ግዴታን የሚጣረስ መሆኑን ይገልጻሉ።

ስለዚህ በተለያየ ደረጃ ጥፋት ለፈፀሙ ሰዎች ቅድመ ሁኔታዎችን ባሟላ መልኩ ምህረት የሚደረግበትን መንገድ መዘርጋት አስፈላጊ ይሆናል። ምህረት ለመስጠት የሚያስችሉ ቅደመ ሁኔታዎችን በግልጽ ማስቀመጥ፤ ምህረት የሚሰጥባቸውን የወንጀል አይነቶች መወሰን፤ የምህረት አሰጣጥ ስነ-ስርዓትና ሂደቶችን መዘርዘር እንዲሁም ምህረት የመስጠትን ሂደት ግልጽና ገለልተኛ በሆነ መንገድ የሚያስተናግዱ ተቋማት እና አደራጃጀቶችን መወሰን ያስፈልጋል።

አለማቀፍ ተመክሮዎች እንደሚያሳዩት ምህረት ለመስጠት የአጥፊዎች ተሳትፎ መጠን፣ የወንጀል ይዘት እና ክብደት እንደ ቅድመ ሁኔታ ሊቀመጡ ይችላሉ። በሽግግር ፍትህ ሂደት ምህረት ለማግኘት ግለሰቡ በወንጀሉ ያለው የተሳትፎ መጠን ግንዛቤ ውስጥ መግባት ይኖርበታል። ምህረት ከባድ በሆኑ ወንጀሎች ተጠያቂ የሆኑ ሰዎች ከተጠያቂነት ለማምለጥ የሚጠቀሙበት መሳሪያ መሆን የለበትም።

በሽግግር ፍትህ ሂደት ጥፋት ፈፃሚዎች እንዲሳተፉና ትብብር እንዲያደርጉ ይፈለጋል። ስለዚህ በምህረት የህግ ጥበቃ ማግኘታቸው በሂደቱ ተሳታፊ ለመሆን እንዲበረታቱ ያደርጋል። ስለሆነም በክስ፣ በእርቅ፣ በካሳ እና እውነትን በማፈላለግ ሂደት ተሳትፎ ማድረጋቸው እንደ ቅድመ ሁኔታ ሊቀመጥ ይችላል። በቅደመ ሁኔታ የሚሰጥ ምህረት እውነትን ለማጥራት ሁነኛ ሚና ይጫወታል። በዳዮች የወንጀሉን እቅድ፣ መሪ፣ ዓላማ እና አጠቃላይ ሁኔታ ምን መልክ እንደነበረው ለሚመለከተው አካል ቀርበው እውነቱን መንገር እና ያደረሱትን በደል በመዘርዘር፣ በመጸጸትና ይቅርታ በመጠየቅ የእውነትና የእርቅ ሂደቱን ማገዝ ይጠበቅባቸዋል።

በሽግግር ውስጥ ያለ ማህበረሰብ እና በደል የደረሰባቸው ሰዎች ለተፈፀመባቸው በደል ፍትህ ከማግኘት ባለፈ ያለፈው እንዳይደገም መተማመኛ ይፈልግሉ። ጥፋት አድራሾች ስለጥፋታቸው መጸጸታቸውን እንዲገልጹ እና ይቅርታ እንዲጠይቁ ማድረግ ያስፈልጋል። በተጨማሪም በዳዮች እንደ አስፈላጊነቱ እና አግባብነቱ ከሌሎች የፍትህ አካላት ጋር መተባበር፤ በመልሶ ማቋቋም ፕሮግራሞች መሳተፍ፤ በባህላዊ የፍትህ ሂደቶች ውስጥ መሳተፍ፤ በህገ ወጥ መንገድ የተገኙ ንብረቶችን አሳልፎ መስጠት፤ በቁሳቁስ ወይም በምሳሌያዊ ሁኔታ ለማካካሻ ስራ አስተዋፅዖ ማድረግ እና የመሳሰሉ ተግባራትን ማከናወናቸውን ማረጋገጥ ይገባል።

በሽግግር ፍትህ ሂደት ማካካሻ መስጠት ሌላው ቁልፍ ጉዳይ ነው። ማካካሻ ለደረሱ የመብት ጥሰቶች ወይም የሐብት ውድመቶች ውጤታማና ተመጣጣኝ የገንዘብ ወይም ገንዘብ ያልሆነ ካሳ፣ መጠገኛ፣ ማደሻ ወይም ወደነበረበት ሁኔታ የመመለሻ መንገዶችን የያዘ ስልት ነው። የማካካሻ ፍትህ ዓላማ የተበዳዮችን ጉዳት መፈወስ እና የአጥፊዎችን ባህሪ ማስተካከል ነው።

ፍትህ ሚኒስትር “የሽግግር ፍትህ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች” በሚል ያዘጋጀው ሰነድ እንደሚገልጸው፤ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ በአገራችን የተሞከሩ የፍትህ ሂደቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጎጂዎች ማካካሻ የማግኘት መብትን ባስከበረ መልኩ ባለመዘርጋታቸው በተጎጂዎችና በህብረተሰቡ የፍትህ መጓደል ስሜትን ፈጥረዋል። የተሳካ እና ተቀባይነት ያለው የሽግግር ፍትህ ሂደት ለማከናወን ማካካሻን ሰፋ አድርጎ በመመልከት፤ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ፖሊሲ በመንደፍ፤ ሀብት በማሰባሰብና በመመደብ እንዲሁም የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም በቂ ውጤታማ እና ፈጣን የማካካሻ ስርዓት መገንባት ያስፈልጋል።

በመጨረሻም በሽግግር ፍትህ ሂደት አንድ አገር ከእርስ በእርስ ግጭት፣ ጦርነት ወይንም ጭቆና መላቀቅ በኋላ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥቃት ያደረሱ ወይም አድርሰዋል ተብለው የሚታመኑ ሰዎችን በኃላፊነት ቦታ ህዝብን እንዲያገለግሉ ማድረግ ለሚታሰበው የእርቅ እና የሰላም ሂደት እንቅፋት ይፈጥራል። ስለሆነም ተገቢ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በመቅረፅ በእንዲህ አይነት ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩ የመንግስት ኃላፊዎችንና ሰራተኞች መለየት፤ ማጣራት እና ከስራ በማሰናበት ወይም እንደ አስፈላጊነቱ በሌላ ቦታ እንዲሰሩ በማድረግ ተቋማዊ ማሻሻያ ማድረግ ይጠበቃል። ይህም ተቋማቱን በተገቢው መልኩ ለመቀየርና የተቋማቱን ተአማኒነት፤ ቅቡልነት እና አሰራር በመለወጥ ዘላቂ የሆነ ማሻሻያ እንዲኖር መሰረት ይጥላል።

ገመቺስ መኮንን የህግ ባለሙያ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የዓለም አቀፍ ህግ ድህረ ምረቃ እጩ ናቸው። እርሳቸው እድሚጠቅሱት፣ በግጭቶች ጉዳይ ጥናታዊ ጽሁፎች በማሳተም የሚታወቀው “Center for strategic and international studies” ከጦርነት ወደ ሰላም በሚደረግ ጉዞ በግጭቶች ተጎጂ የሆኑ አከባቢዎችን ቀድሞ ከጦርነት በፊት ወደ ነበሩበት አቋም ለመመለስ እና የኢኮኖሚ መነቃቃትን ለማምጣት ሶስት የመልሶ ማቋቋም ደረጃዎች እንዳሉ ይጠቁማል። የመጀመሪያው ደረጃ በግጭቶች ተጎጂ ለሆኑ ማህበረሰቦች አፋጣኝ የሰብዓዊ እርዳታ የማድረስ ተግባር ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ የፋይናንስ፣ የጤና፣ የፍርድ ቤት፣ ፋብሪካዎች እና ሌሎች የግልና የመንግስት ተቋማትን ስራ ማስጀመርን ያካትታል። በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ መረረጋጋት መቀየር እና የኢኮኖሚያዊ እድገትን ማምጣት ላይ ያተኮረ ነው።

ዓለማችን በተለያዩ ጊዜያት የተፈጠሩ ግጭቶች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የፍርድ ሂደት በመከተል ወንጀለኞችን ተጠያቂ የማድረግ ስራ አመርቂ ውጤቶችን ያስገኘ ስለመሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም የሚሉት የዓለም አቀፍ ህግ ድህረ ምረቃ ተማሪው ሆኖም ግን የፍርድ ሂደቶቹ የአሸናፊ እና ተሸናፊ ስሜቶች የመፍጠር እንዲሁም በግጭት ጊዜ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ተሳትፎ ያላቸው አካላቶች ብዙ ከመሆናቸው አንጻር ሁሉንም አካላት ላይ ምርመራ ከማድረግ እና የፍርድ ሂደትን ማድረግ ፍትህን እና ተጠያቂነት በአነሰ ጊዜ ውስጥ ለማስፈን አዳጋች የሚሆኑበት ዕድል አለ በሚል ስጋት እንደሚጠላባቸው ይጠቁማሉ።

አቶ ገመቺስ እንደሚናገሩት፣ በጦርነት ወቅት ለሚያጋጥሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነት እና ፍትሕ ለማስፈን በጥቅም ላይ የሚውሉ እርምጃዎች በዋናነት ለሁለት ይከፈላሉ። በቅድሚያ የፍርድ ሂደቶችን ያካተቱ እርምጃዎች ሲሆኑ ሌላው አማራጭ ደግሞ ከፍርድ ዘለል (ወጪ) የሚካሄዱ የተጠያቂነት እና ፍትህን የማስፈን ተግባራት ናቸው። የፍርድ ሂደቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሰብዓዊ መብት ጥሰት በፈጸሙ ግለሰቦች፣ ቡድኖች አልያም ድርጅቶቸች ላይ ያነጣጠረ ቀጥተኛ ምርመራ በማካሄድ ለፍትሕ የማቅረብ ተግባርን ይከተላል። የፍርድ ሂደቶች ዓለም አቀፋዊ ወይም አገር አቀፋዊ ሊሆኑ የሚችሉ ቢሆንም ከሁለቱ አማራጭ የፈለገውን መጠቀም የአንድ ሉአላዊ አገር ውሳኔ ነው። በፍርድ ሂደቱ ላይ ገለልተኛ ፍ/ ቤቶች ለሰብዓዊ መብት መጠበቅ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።

በሌላ በኩል ከፍርድ ዘለል (ውጪ) የሚካሄዱ ፍትሕ እና ተጠየቂነት የማስፈን ተግባራት ኢኮኖሚያዊ ድጋፎች፣ እውነት አፈላላጊ ኮሚሽን ማቋቋም እና ተቋማዊ ሪፎርሞችን ያካትታሉ። የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በኦኮኖሚ መደገፍ እና ማህበረሰቡ በግጭት ምክንያት ያጧቸውን የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎች ተቋማት መልሶ በመገንባት እና ተጨማሪ ሌሎች የአገልግሎት ተቋሞችን መገንባት ፍትሕን ከማስፈን በጥቅም ላይ የሚውሉ ተግባራት ናቸው። ማህበረሰቡን ያካተቱ እውነት አፈላላጊ ኮሚሽኖችን በማቋቋም የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በመግለጽ እንዲህ አይነት አለአግባብ ተግባራቶች በቀጣይነት እንዳይፈጸሙ ለማሳሰብ ይጠቅማሉ። እነዚህ ኮሚሽኖች በዋናነት ፍትሕን እና ተጠያቂነትን ለማስፈን እና በግጭት ምክንያት ለደረሱ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች መፍትሔ የማፈላለግ ሚና አላቸው። በዚህ ረገድ በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ዘመን ማብቃትን በማስመልከት ለተጎጂዎች ፍትሕን እና ተጠየቂነትን ለማስፈን የተቋቋመው “truth and reconciliation commission” የሚጠቀስ ሲሆን ይህ ኮሚሽን የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ ጥሰቶችን ማህበረሰቡ እንዲያውቅና በማህረሰብ መካከል ሰለም እና ፍቅር እንዲሰፍን አድርጓል።

የታሪክ ድርሳናት እንደሚስረዱት የህግ ባለሙያው አቶ ገመቺስ ከጠቀሷት ደቡብ አፍሪካ በተጨማሪ ሩዋንዳ፣ ቺሊ እና ዩጎዝላቪያ የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ አድርገዋል። በተለይም ሩዋንዳ እና ደቡብ አፍሪካ የተሳካ የሚባል የሽግግር ፍትሕ በማካሄድ የኋላ ቁስላቸውን ሽረው አዲስ ጎዳናን ተያይዘዋል። ተበዳዮች በደላቸው እንዲታወቅ ፤ አጥፊዎችም ለፍርድ እንዲቀርቡ ተደርጓል። በየምድራቸው የተፈጸመውን ዘግናኝ ታሪክ አስከፊነት ትውልዶች እንዲማሩበትም መታሰቢያ ሙዚየም ገንብተዋል። የኛዋ ኢትዮጵያም የሽግግር ፍትሕ የሚያስፈልጋት፣ የሁለቱን አገራት ተሞክሮ በተሻለ መንገድ ተግብራ ለዜጎቿ የተሻለ ነገን እንድትፈጥር ስለሚያስችላት ነው።

ተስፋ ፈሩ

Recommended For You