የዘመን መጽሔት የሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም ዕትም የዐብይ ርዕስ አምድ እንግዳ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ናቸው። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሁለት ወራት እረፍት ተዘግቶ ተመራጮች ወደ ምርጫ ክልላቸው መጓዛቸውን በማስመልከት ከምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ጋር ያደረግነው የምክር ቤቱ አክራሞትና ወቅታዊ ጉዳዮች የተዳሰሱበት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል።
ዘመን፡- በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ተግባርና ኃላፊነት ምንድነው በሚለው እንጀምር ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡ የመንግሥት ተጠሪ ኃላፊነት የመንግሥት ፖሊሲዎች እና ፕሮግራሞች እንዲሁም መንግሥት ለሀገርና ህዝብ ይጠቅማል ብሎ የሚያወጣቸውን አዋጆች በምክር ቤቱ ተቀባይነት እንዲያገኙና እንዲጸድቁ ማድረግ ነው። ፓርቲዎች ሲወዳደሩ ፕሮግራምና እቅድ ይዘው ነው የሚወዳደሩት። ህዝቡ ከተቀበላቸውና አሸናፊ ከሆኑ የያዙት ፕሮግራምና እቅድ ወደ ፖሊሲ፣ ህግና አዋጅ ይቀየራል። በፕሮግራምና እቅድ ደረጃ ተቀምጠው የነበሩት ሃሳቦቻቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየቀረቡ ተቀባይነት እያገኙ እየጸደቁ ሀገርን ለማሸጋገር እንዲያግዙ የመንግሥት ተጠሪ መንግሥትንና መሪውን ፓርቲ ወክሎ በምክር ቤቱ ውስጥ አቋሞችን በማራመድ የማስተባበርና የመምራት ሥራ የሚሰራ ነው። ስለዚህ አስፈጻሚውን አካልና ምክር ቤቱን በመሃል ሆኖ የሚያገናኝ ድልድይ ነው።
ዘመን፡- አሁን ያለው ምክር ቤት ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ክርክሮችን የሚያደርግና አስፈጻሚ አካላትን በሚገባ የሚቆጣጠር ነው ብለው ያምናሉ ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- በህገ መንግሥታችን አንቀጽ 50 ንዑስ ቁጥር ሁለት ላይ በሰፈረው መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥቱ ትልቁ የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት ነው። ምክር ቤቱ በህገ መንግሥቱ የተሰጡት አራት ዋና ዋና ተልዕኮዎች አሉት። አንደኛው ህግ ማውጣት ነው። ሁለተኛው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በሌሎችም በህግ በተፈቀደላቸው አካላት የሚወጡ ህጎችና የሚጸድቁ እቅዶች አፈጻጸም ላይ ክትትል እና ቁጥጥር ማካሄድ ነው። ሦስተኛው በህገ መንግሥቱ የተጣለበት ኃላፊነት ከመራጩ ህዝብ ጋር የምክር ቤት አባላት የሚወያዩበትና የሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ እንዲሄዱ የማድረግ የምርጫ ክልል ሥራ ነው። አራተኛውና የመጨረሻው የፓርላማ ዲፕሎማሲ መስራት ነው። ከእነዚህ አራቱ ተልዕኮዎች አኳያ በ2013 ሀገራዊ ምርጫ አሸንፈው ወደ ምክር ቤቱ የገቡ የምክር ቤት አባላት ባለፉት ሁለት ዓመታት ጠንካራ ሥራዎችን ሰርተዋል።
ይሄ ምክር ቤት የለውጥ ሂደትን እየመራ ያለ እንደመሆኑ መጠን በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥእያለፈ ያለ ነው። በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ምክር ቤቱ ሀገራዊ ተልዕኮ ይዞ በኢትዮጵያዊ ጥበብ ችግሮችን እንደ ሀገር ለመሻገር መንግሥት እያደረገ ባለው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ ነው።
ዘመን፡- ማሳያዎች መጥቀስ ይችላሉ ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- የክትትልና ቁጥጥር ስራን ብንመለከት የወጡ ህጎችና የጸደቁ እቅዶች እንዴት እየተፈጸሙ እንዳሉ በቋሚ ኮሚቴዎች በኩል በዝርዝር ክትትልና ቁጥጥር ይካሄዳል። የሚስተካከሉ ጉዳዮች እ ን ዲ ስ ተ ካ ከ ሉ ፤ የተሻሻሉ ጉዳዮች ደግሞ የበለጠ ጎ ል ብ ተ ው እ ን ዲ ቀ ጥ ሉ ብዙ ስራዎች ተ ሰ ር ተ ዋ ል ። ስለዚህ ምክር ቤቱ በሁሉም ዘርፍ ጥሩ ሥራ እየሰራ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
ዘመን፡- ምንም እንኳን የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተወከሉበት ቢሆንም እምብዛም ህይወት ያለው ሙጉት የማይታይበትና በኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. ዘመን ከነበረው ምክር ቤት የማይለይ ነው ለሚሉ ወገኖች የሚሰጡት ምላሽ ምንድን ነው ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡ – አሁን ያለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንቅስቃሴው በኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. ዘመን እንደነበረው ነው፤ ምክር ቤት ብዙ አይነት ፍጭትና የሃሳብ ክርክር አይካሄድበትም እንዲሁም ነፍስ ያለው ወይም ጠንካራ ምክር ቤት አይደለም የሚል አስተያየት አለ። ከዚህ አኳያ የማነሳው ነገር ምርጫ የተካሄደባቸውን አካባቢዎች ወክለው ወደፓርላማ ከገቡ አባላት ውስጥ የአምስት ፓርቲዎች ተወካዮች ይገኛሉ። እነዚህ ፓርቲዎች ብልጽግና፣ ኢዜማ፣ አብን፣ ጌህዴድ እና ቁዴፓ ናቸው። ይሄ ከፖለቲካ ፓርቲዎች አኳያ ነው። ሌሎች ደግሞ ወደ ምክር ቤቱ የገቡ ሦስት የግል ተመራጮች አሉ። የምክር ቤቱን አሰራር ብንመለከት፣ ምክር ቤቱ ራሱ አለ፤ ቀጥሎ ሁሉንም የምክር ቤት ሥራዎች በበላይነት የሚከታተል አማካሪ ኮሚቴ አለ። ከአማካሪ ምክር ቤቱ ቀጥሎ አስተባባሪ ኮሚቴ አለ። ከዚያ ቀጥሎ ቋሚ ኮሚቴዎች አሉ። በዚህ መልኩ ባለ አደረጃጀት ነው ምክር ቤቱ የሚሰራው። በሁሉም አደረጃጀቶች በአማካሪ ኮሚቴ ውስጥ፣ በአስተባባሪ ኮሚቴ ውስጥ እና በቋሚ ኮሚቴ ውስጥ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት እንዲገቡ ተደርጓል። ስለዚህ አንዱ ምክር ቤቱ በቆይታው ውጤታማ ነው የሚባልበት ምክንያት የተለያዩ ድምጾች እንዲሰሙ፤ የተለያዩ ሃሳቦች እንዲራመዱ እና የዴሞክራሲን ባህል እንድንለማመድ በለውጡ ማግስት በመንግሥት የተያዘው አቋም በተግባር ተገልጾ ልምድ ያገኘንበት መሆኑ ነው። ስለዚህ አሁን ያለው ምክር ቤት የሃሳብ ብዝሃነት እየተስተናገደበት ያለና የተለያዩ ድምጾች የሚሰሙበት መድረክ ነው።
ዘመን፡- አንዳንድ ቋሚ ኮሚቴዎች በዕቅድ አፈጻጸምና ተልዕኮን ከመወጣት አንጻር ድክምት የታየባቸው መስሪያ ቤቶች ላይ ጠንካራ ግብረ መለስ የሰጡበትና ዕቅድ ሳይቀር ውድቅ ያደረጉበት ሁኔታ ነበር። ሁሉም ቋሚ ኮሚቴዎች መሰል አቅም እንዲፈጥሩ ለማስቻል እየተደረገ ያለ እንቅስቃሴ አለ ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- ይሄ ምክር ቤት የዴሞክራሲን ባህል የምንለማመድበት ነው። አንዳንድ ሰዎች የምክር ቤቱ አባላት ሥራ በመደበኛ ስብሰባዎች ላይ እየተገኙ አዋጆች ላይ እጅ ማውጣትና ማጽደቅ ብቻ ይመስላቸዋል፤ እንደዛ አይደለም። አመቱን ሙሉ ነው እንቅስቃሴ ያለው። ለምሳሌ የማህበራዊ ሚዲያ ገጻችንን ብትመለከተው ዓመቱን ሙሉ የቀጥታ ስርጭት ላይ ነው። ቋሚ ኮሚቴዎች ስራቸውን ሲከታተሉ፤ ሲገመግሙ እና የመስክ ምልከታ ሲያደርጉ በቀጥታ ህዝብ እንዲመለከት እየተደረገ ነው። በዚህ ሂደት የተጀመሩ ጥሩ ነገሮችና አብነቶች አሉ። እነዚህ ነገሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና ተቋማዊ እንዲሆኑ ለማድረግ የተሻሉ ልምዶችን መውሰድ እና ድክመቶችን ማረም ላይ አተኩረን እየሰራን ነው። የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት በስልጣን መባለግ ፤ ከህግ ውጭ አሰራር እንዲሁም በቡድን እና በግል ፍላጎት የሚሰሩበት ሁኔታ እንዳይኖር ለመከላከል ነው። የክትትልና ቁጥጥር ሥራ አንዱ የፓርላማው ቁልፍ ተግባር ስለሆነ ሁሌም ተጠናቅሮ ይቀጥላል።
ዘመን፡- የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በየምርጫ ክልላቸው ተገኝተው ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር ውይይቶች አድርገዋል። በእነዚህ ውይይቶች ሕዝቡ በዋናነት የኑሮ ውድነትን፣ የጸጥታ ጉዳዮችን እና ከመሰረተ ልማት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን አቅርቧል። ምክር ቤቱ እነዚህን የሕዝብ ጥያቄዎች አጀንዳ አድርጎ ከመወያየትና መንግሥት አስፈላጊውን ትኩረት እንዲሰጥ ከማድረግ አንጻር ምን ያህል ሥራ ተሰርቷል?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- ከላይእንደጠቀስኩት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንዱ ተልዕኮ የምርጫ ክልል ሥራ ነው። የምርጫ ክልል ሥራ በዓመት ሁለት ጊዜ መጋቢትና ክረምት ላይ ነው የሚሰራው። የምክር ቤት አባላት ከህዝብ ጋር ለመነጋገር የአሰራር ሥርዓት፣ ዕቅድ እና ሥራዎችን የሚከታተሉበት ቼክ ሊስት ይዘው ነው የሚሄዱት። አባለቱ ከመረጣቸው ህዝብ ጋር ተገናኝተው ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ተወያይተው ከተመለሱ በኋላ በመጀመሪያ ደረጃ ህዝብ ያነሳቸው ጥያቄዎች በየመስኩ ፍሬም ይደረጋሉ። ቀጥሎ ከቀበሌ አንስቶ እስከ ክልል ድረስ በየደረጃው ለሚመለከተው አካል የህዝቡን ጥያቄዎች የዕቅዳቸው አካል እንዲያደርጉ ዝርዝር ግብረ መልስ እየሰጡ ይመጣሉ።
በፌዴራል ደረጃ መልስ ማግኘት ያለባቸው ጉዳዮች ደግሞ በየዘርፉ በሚገባ ተለይተው ይቀመጣሉ። ለምሳሌ የመንገድ፣ የመብራት፣ የቴሌኮም፣ የፍትህ አካላት ወይም የውሃና መስኖ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ነገሮች ከሁሉም አካባቢዎች ከተለዩ በኋላ ምክር ቤቱ በአፈ ጉባዔው ፊርማ በሚወጣ ደብዳቤ እያንዳንዱ ተቋም መልስ እንዲሰጥ ይጠይቃል። ተቋማቱም ከህዝብ በተነሱት ጉዳዮች ላይ የሠሩትን ሥራ፣ የያዙትን እቅድ እና የተጠየቀው ጉዳይ ያለበትን ደረጃ የሚያሳይ ምላሽ አቅርበው ሚኒስትሮችና የተቋማት ኃላፊዎች ከምክር ቤት አባላት ጋር በዝርዝር ውይይት ያካሂዳሉ። ለምሳሌ በዚህ ዓመት መጋቢት ወር ላይ የምክር ቤት አባላት በየምርጫ ክልላቸው በመገኘት ከመረጣቸው ህዝብ ጋር ዝርዝር ውይይቶችን አካሂደዋል። ሲመለሱ ከየተቋማቱ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ምክር ቤት ተገኝተው ህዝቡ ባነሳቸው ጥያቄዎች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል። አሁን ደግሞ በክረምቱ መጋቢት ላይ የተነሱ ጥያቄዎች አፈጻጸም ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚያሳይ ዝርዝር ምላሽ ይዘው ነው ወደ መራጩ ህዝብ እየወረዱ ያሉት። ስለዚህ በዚህ መልክ መራጩ ህዝብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል።
ዘመን፡- ባለቀው በጀት አመት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የነበረውን አክራሞት እንደ ምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ እንዴት ይገመግሙታል?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- አሁን የምንገኝበት ጊዜ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም አስቸጋሪ ነገሮች አሉት። አንደኛ ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከፍተኛ ጫና ውስጥ ነው የሚገኘው። አንዳንድ ሀገራት በጎርፍ ሌሎች ደግሞ በድርቅ ምክንያት ዋጋ እየከፈሉ ያሉበት ነው። እኛ ሀገርም በዚህ አመት በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ሶማሌ ክልል፣ በኦሮሚያ ቦረና፣ በደቡብ አንዳንድ አካባቢዎች እና በሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ድርቅ የተከሰተበት ጊዜ ነው። ሁለተኛ በዓለም ደረጃ የተነሳው የኮሮና ወረርሽኝ የዋጋ ግሽበትና የምርት መቀነስን ጨምሮ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ያስከተለበት ወቅት ነው። ሦስተኛ በሩሲያና ዩክሬን መካከል የተፈጠረው ጦርነት የማዳበሪያና የነዳጅ ዋጋ በብዙ እጥፍ እንዲጨምር አድርጓል። የዓለምን የንግድ ሥርዓት አዛብቷል። በዚህ ምክንያት እንደኛ ያሉ ብዙ ነገሮችን ከውጭ የሚያስገቡ ሀገራት በጣም በብዙ መልኩ እንዲጎዱ አድርጓል። እነዚህ ችግሮች ተደምረው የዓለም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በጣም እንዲቀዛቀዝ አድርገዋል። ነገር ግን ኢትዮጵያ በእነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆና ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የአመቱ መዝጊያ ሪፖርት ላይ እንደገለጹት፣ በእድገት ጎዳና ውስጥ ነው እየተጓዘች ያለችው። ምክር ቤቱ በዚህ ውስጥ የራሱ የሆነ ድርሻ አለው።
በክትትልና ቁጥጥር የታቀዱ ስራዎች በአግባቡ እንዲካሄዱ በማድረግ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም እና የሀብት አጠቃቃም እየተሻሻለ እንዲሄድ የክትትልና ቁጥጥር ስራው ትልቅ ድርሻ ነበረው። ስለዚህ የክንውን እድገታችን እንዲቀጥል በማድረግ በክትትልና ቁጥጥር ሥራ ምክር ቤቱ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ማለት ይቻላል። ሌላው ምክር ቤቱ የመጨረሻው የሀገሪቱ የፖለቲካ ስልጣን ያለው አካል እንደመሆኑ ሰላምን የሚያደፈርሱ የጸጥታ ችግሮች እዚህም እዚያም በሚከሰቱበት፤ ኢኮኖሚውን ከፍተኛ ጫና ውስጥ የሚያስገቡ ነገሮች ባሉበት፤ ሶሻል ሚዲያውና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዐቢዮት ያስከተሏቸው ተግዳሮቶች በበዙበት፤ እኛ የምንገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ጂኦ ፖለቲካ በጣም ውስብስብና የውጭ ኃይሎች ከራሳቸው ፍላጎት ተነስተው በሀገራቱ ውስጥ መረጋጋት እንዳይኖር እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ሁኔታ ውስጥ ምክር ቤቱ በሰከነ መንገድ ሀገር ለማሻገር የሰራው ሥራ በጣም ትልቁ ሥራ ነው። ኢትዮጵያውያን አሁን እያጋጠሙ ካሉ ጊዜያዊ ችግሮች በተረጋጋ መንገድ በአባቶቻችን ጥበብ አንድ ሆነን እንድንሻገር የምክር ቤቱ አባላት በጣም ትልቅ ሥራ ሠርተዋል።
ምክር ቤቱ በማህበራዊ ሚዲያ እና በተለያየ መንገድ ከፍተኛ ጫና ሲደረግበት ነበረ። የምክር ቤቱ አባላት ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ ናቸው፤ ነገር ግን የሚወክሉት በምርጫ ክልላቸው ካርድ የሰጣቸውን ሰው ብቻ አይደለም። እንደ ሀገር ኢትዮጵያን ነው የሚወክሉት። ይህን ትልቁን ስእል በማየት የግል ፍላጎታቸውን ወደጎን ብለው ለመንግሥትና ህዝብ ፍላጎት በመገዛት ሀገር የምትፈልገውን ተልዕኮ ወስደው በመንቀሳቀስየሚያስመሰግን ሥራ ሠርተዋል። ከዚህ አኳያ ስመለከተው ቆይታችን በጣም ውጤታማ ነው። በሂደቱ ደግሞ የለየናቸው ክፍተቶችና መጠናከር የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ የአመቱ ማጠቃለያ ላይ በጋራ ገምግመናል፤ በሚቀጥለው ዓመት እያሻሻልናቸው እንሄዳለን። ስለዚህ በኢኮኖሚ ልማት፣ በማህበራዊ ልማት፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ በፕሮጀክቶች አፈጻጻምና በአጠቃላይ በክትትልና ቁጥጥር የሚሰሩ ሥራዎችን እንዲሁም የዴሞክራሲ ልምምድን በመጀመር ረገድ ምክር ቤቱ የሠራቸው ሥራዎች ትላልቅ ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
ዘመን፡- በዚህ አመት ምክር ቤቱ በዝግ የመከረባቸው አንዳንድ ጉዳዮች ነበሩ። የምክር ቤቱ ውሎ ከሚዲያዎች እይታ ውጪ እንዲሆን የሚወሰነው ምን ሲሆን ነው? የህዝብን መረጃ የማግኘት ነጻነት አይጋፋም ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- በምክር ቤቱ ውስጥ ባለን የአሰራር መመሪያ መሰረት አራት አይነት ጉባዔዎች አሉ። እነዚህም መደበኛ ጉባዔ፣ አስቸኳይ ጉባዔ፣ ልዩ ጉባዔ እና የዝግ ጉባዔ ናቸው። መደበኛ የሚባሉት በየሳምንቱ መቼ እንደሚካሄዱ ቀንና ሰዓት ተቀምጦላቸዋል። አስቸኳይ ጉባዔ አስቸኳይ ነገር ሲያጋጥም የሚጠራ ነው። ልዩ ጉባዔ የሚባለው ከመደበኛው ቀናት ውጭ ስብሰባዎች የሚካሄዱ ከሆነ ነው። የዝግ ጉባዔ የሚካሄደው የምክር ቤት አባላት በአንድ ጉዳይ ላይ መወያየት አለብን ብለው አንድ ሦስተኛ በሆነ ድምጽ ጥያቄ የሚያቀርቡ ከሆነ ወይም አስፈጻሚው አካል ሲጠይቅ ነው።
በዝግ ውይይት የሚካሄድባቸው ጉዳዮች ህዝብ ዘንድ ከመድረሳቸው በፊት መብሰል ያለባቸው ናቸው። ሳይበስል ጥሬው መረጃ ለህዝብ ቢደርስ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን ነው ተብሎ የሚታመን ከሆነ፤ የጸጥታ ጉዳይ ሲሆን እንዲሁም ጊዜው ሲደርስ ለህዝብ ይፋ መደረግ ያለበት ነገር ግን ቀድም ብሎ ምክክር ማድረግን የሚጠይቅ ነገር ሲኖር በዝግ ስብሰባ ይካሄዳል። ዋና መመዘኛ መስፈርቱ ከሀገር ሰላም፣ አንድነትና ብልጽግና አኳያ የሚታይ ነው። ከዚህ ውጭ ከለውጡ በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ትልቅ እምርታ ነው ብለን የምንወስደው ማናቸውም በምክር ቤቱ የሚካሄዱ ውይይቶች በአብዛኛው በማህበራዊ ሚዲያዎቻችን በቀጥታ እንዲተላለፉ መደረጉን ነው።
ዘመን፡- በቅርቡ በምክር ቤቱ በቀረበው የኦዲት ሪፖርት በርካታ ቢሊዮን ብሮች ተመላሽ እንዳልሆኑ ተገልጿል። የበጀት ጉድለቱን ባሳዩ ተቋማት አስፈፃሚዎች ላይ በቀጣይ ምን አይነት እርምጃ ይወሰዳል ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- የኦዲት ግኝቶች ሲገኙ የትኛውም ተቋም ተጠያቂ መሆን አለበት የሚል ጽኑ አቋም ስላለን በፍጥነት እየተራመደ እንዲሄድ ለማድረግ እየሰራን ነው። አንዳንዶቹ ላይ የተጀመረ የእርምት እርምጃ አለ፤ በአንጻሩ ደግሞ የዘገዩ እርምጃዎችም አሉ። የዘገዩ ጉዳዮች በፍጥነት እንዲያልቁ አቅጣጫ ተቀምጧል። መንግሥት በዚህ ላይ በትኩረት እየሰራ ነው ያለው፤ ተቋማትም በተመሳሳይ ደረጃ እንዲሰሩ አቅጣጫ ተሰጥቷቸዋል። ከረፍት መልስ በቀጣዩ መስከረም ምክር ቤቱ ሥራ ሲጀምር የመጀመሪያ ተግባሩ የሚሆነው ባለፉት ጊዜያት በምክር ቤቱ የተወሰኑ ውሳኔዎችና የተቀመጡ አቅጣጫዎች ከምን ደረሱ የሚለውን መመልከት ነው። ስለዚህ የኦዲት ግኝቱን ጨምሮ ከዛሬ ጀምሮ መታረም አለባቸው ተብለው የተቀመጡት ጉዳዮች ላይ የሚወሰዱት እርምጃዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ የሚል እምነት አለኝ።
ዘመን፡- በኢ.ህ.አ.ዴግ. ዘመን እንደነበረው ሁሉ በቢሊዮን የሚቆጠር የኦዲት ግኝት ይፋ እየተደረገ ቀጥሏል። ተመላሽ እንዲሆን ተጠይቆም ተፈጻሚ አልሆነም። ይህን እየተንከባለለ የመጣ ችግር ለመቅረፍ በተጨባጭ የወሰዳችሁት እርምጃ እና ያስቀመጣችሁት አቅጣጫ አለ ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- በመጀመሪያ ደረጃ በዚህ ለውጥ በመንግሥት በኩል የምንሰራቸው ሥራዎች ግልጽ መሆን፤ ህዝብን የሚጠቅሙ እና በሚታወቅ ሥርዓት መመራት አለባቸው ተብሎ የተያዘ እምነት እና ቁርጠኝነት አለ። የኦዲት ግኝት ሪፖርቱን ተከትሎ ባለፈውና በዚህ ዓመት ብዙ እርምጃዎች ተወስደዋል። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ ተወስዶ በጣም ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች አሁን መሻሻል አሳይተዋል። በሌሎች የፌዴራል ተቋማት ላይም እርምጃዎች ተወስደው መሻሻሎች ታይተዋል። የምክር ቤቱ አባል የነበሩትን ሰው ያለመከሰስ መብት ከማንሳት ጀምሮ የምክር ቤት አባል ያልሆኑ ከፍተኛ አመራሮች ተጠያቂ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው። በአጠቃላይ መንግሥት በሙስና ላይ የጀመራቸውን እርምጃዎች የሚያግዘው አንዱ ተቋም የፌዴራል ኦዲት መስሪያ ቤት ነው።
መንግሥት ሙስና ለእድገታችን ጸር ነው፤ እንደ ሀገር ችግር ውስጥ እንድንገባ ያደርጋል ተብሎ በመንግሥት ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት አንድ ግብረ ኃይል ተቋቁሙ እየሰራ ነው የሚገኘው። ለግብረ ኃይሉ እንደ ግብአት የሚጠቀመው አንዱ ነገር የኦዲት ግኝት ሪፖርትን ነው። ስለዚህ ብዙ እርምጃዎች እየተወሰዱና በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ከዚህ አንጻር በጣም ጥሩ የመሻሻል ሂደት ውስጥ የገቡ ተቋማት አሉ። ይሄም ሆኖ ግን ችግሮቹ ውስብስብ ስለሆኑና ተቋም የመገንባት ሥራ ላይ ስለሆንን አሁንም በበቂ ሁኔታ ያልተንቀሳቀሱ ተቋማት፣ አመራሮችና ግለሰቦች መኖራቸው ታይቷል። ከእነዚህ ጋር የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለት ነው። አንድ ነገር በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው የኦዲት ግኝቶች እንደ በፊቱ ባዶ ሜዳ ላይ የሚቀሩ አይሆኑም። አሁን ማስተካከል የሚገባን ነገር ፈጥኖ እርምጃዎች መውሰድ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ማረምና በተወሰኑ ተቋማት አካባቢ የታየው መልካም ነገር ወደ ሁሉም እንዲደርስ ማድረግ ነው።
ዘመን፡- በአዲሱ በጀት አመት የመንግሥት መስሪያ ቤቶች አዲስቅጥር እንደማይፈጽሙ ተገልጿል። ይህ የመንግሥት ውሳኔ በዜጎች ዘንድ ግራ መጋባትን አምጥቷል። ውሳኔው ምን ማለት ነው ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- በዚህ ዙሪያ ላይ ነገሩን በቁንጽል ከተመለከትን እንዳልከው ትንሽ ግራ የሚያጋባ ነው የሚሆነው። አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ በጣም ብዙ የህዝብ ጥያቄዎች አሉ ነገር ግን በአቅማችን ልክ ነው የምንቀሳቀሰውና የምንሰራው። የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አሉ እነዚህ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ አለባቸው። ሌላው የግብርናው ዘርፍ፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ፣ የቱሪዝም ዘርፍ እና ዋና ዋናዎቹ የብዝሃ እድገታችን ምንጭ ይሆናሉ የተባሉ ዘርፎች መንቀሳቀስና እድገት እያስመዘገቡ መሄድ አለባቸው። ስለዚህ አንዱ የበጀት አቅጣጫ ትኩረት መስጠት የሚገባን ዘርፎች ላይ የተለየ ትኩረት እንሰጣለን የሚል ነው።
ሁለተኛ በሀገሪቱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የመንግሥት ሠራተኞች አሉ። ከመንግሥት ሠራተኞች አኳያ የተለያዩ ጥያቄዎች ይነሳሉ። በአንድ በኩል የመንግሥት ሠራተኞች ዝቅተኛ ክፍያ ስለሚያገኙ ለመኖር ይቸገራሉ። ምን ታስቧል የሚል ጥያቄ በተለያየ ጊዜ ለመንግሥት ይቀርባል። በሌላ በኩል ደግሞ አሁን በመንግሥት ተቋማት ውስጥ በሚስተዋሉት የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የሌብነት እና የብልሹ አሰራር ችግሮች በለውጡ የሚጠበቁት ነገሮች በተፈለገው ልክ እንዳይሄዱ ያደረጉበት ሁኔታ አለ። በአጠቃላይ በሀገር ደረጃ ሲቪል ሰርቪሱን ውጤታማ በማድረግ ሰዎች በጣም ጥሩ አገልግሎት የሚያገኙበትና ልማትን የሚያቀላጥፍ የሰው ኃይል እንዲኖረው ራሱን የቻለ ዕቅድ ወጥቶ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ስለዚህ በዚህ ማዕቀፍ ዋነኛው የመንግሥት አቅጣጫ ሰው መቅጠርና ሰው መሙላት አይሆንም ማለት ነው እንጂ ለሥራ የሚያስፈልግ አንድም ሁለትም ሰው የትም ቦታ አይቀጠርም ማለት አይደለም። ትኩረት የሚሰጠው ያለው የመንግሥት ሠራተኛ በህዝብ ውስጥ የሚነሱ ቅሬታዎችን መፍታት የሚያስችል አመለካከት፣ እውቀት፣ ክህሎት፣ እየታና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲኖረው በማድረግ ውጤት እንዲያመጣ ነው። ነገር ግን ለሥራ የሚያስፈልግ ኃይል ሲኖር ቅጥር አይፈጸምም ማለት አይደለም።
ሌላው መታወቅ ያለበት ነገር በየትኛውም ዓለም ከዩኒቨርሲቲ የሚወጡ የተማሩ አምራች ዜጎች በሙሉ የመንግሥት ተቋም ውስጥ አይቀጠሩም። የመንግሥት ዋናው ሚና የግሉ ዘርፍ እየተጠናከረና እየሰፋ እንዲሄድ ማድረግ ነው፤ የሥራ ዕድል እንዲመቻች ማድረግ እንዲሁም ዜጎች ሥራ ፈጣሪ ሆነው ገበያ ውስጥ መግባት እንዲችሉ ነገሮችን ማመቻቸት ነው። መልዕክቱ የተዛባው ሆነ ተብሎ አንዳች የፖለቲካ ትርፍ ለማድረግ ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረው ስለተደረገ ነው። መንግሥት ዋና ስራዬ ቅጥር ነው እንኳን ቢል በዓመት ውስጥ ከሚመረቁት ስንት ሰው ነው የሚቀጥረው? ሁሉንም መቅጠር አይችልም። የመንግሥት ዋና ሥራና አቅጣጫ ብዙ የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር፤ ዜጎች ደግሞ ትምህርት ቤት ገብተው እውቀት አግኝተው ክህሎታቸውን አሻሽለው ራሳቸውን ብቁ በማድረግ ገበያ ውስጥ በደንብ እየሰሩ እያሸነፉ እንዲሄዱ ማድረግ ነው።
ዘመን፡- ዝቅተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍልና የመንግሥት ሠራተኛው የኑሮ ውድነቱን መቋቋም እንዲችል ምን እየተሰራ ነው ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው ሁኔታ በተለይ የዋጋ ግሽበቱና የኑሮ ውድነቱ እየጨመረ ሲሄድ በተለይ ዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍሉ ላይ ያመጣቸው ጫናዎች አሉ። ከዚህ አኳያ ጫናውን ለማቃለል የሚያግዙ ሥራዎች ተጀምረዋል፤ ከፍተኛ ዘመቻ እየተካሄደ ነው። ለምሳሌ የመንግሥት ሠራተኛውን ጨምሮ በኢኮኖሚ ዝቅተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚጎዳው አንዱ የግብርና ምርቶች ዋጋ መጨመር ነው፤ ይህንን ጫና ለመቀነስም የግብርና ምርቶችን በእጥፍ የመጨመር ሥራ ተጀምሯል። ሥራ አጥ የሆኑ ዜጎችም በኑሮ ውድነቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተጎጂ ስለሚሆኑ የሥራ እድል ፈጠራ ላይም ከፍተኛ ዘመቻ እየተካሄደ ነው። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የኑሮ ውድነቱን ከሚያባብሱ ነገሮች የምርት እጥረት ሳይኖር፣ ነገር ግን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ በገበያ ላይ እንዳይገኝ የሚያደርግ የግብይት ሥርዓት መኖሩ ነው፤ ይህንንም ለማስተካከል የሚያግዙ ሥራዎች ተጀምረዋል፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የህገ ወጥነትና የኮንትሮባንድ ንግድን መልክ ማስያዝ ዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚጎዳ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ችግሮች የሚቀረፍበት አንዱ መንገድ ነው።
ሌላው በመንግሥት ሠራተኛውና በህብረተሰቡ ውስጥ የሚመላለሱ ጥያቄዎችን እንዴት በተደራጀ መልኩ፣ በቅንነትና በብቃት እየመለስን ዜጎች እርካታ እንዲኖራቸው ለማድረግ ምን መሰራት አለበት የሚለው ነው። በአብዛኛው ከሙስናና ብልሹ አሰራር ጋር የሚያያዘው ከመንግሥት ተቋማት ጋር ነው። እዛ ላይ የሚሰራው ሰው ነው። ግዢ የሚገዛው ሰው ነው። የጨረታ ኮሚቴውም ሰው ነው፤ አቅራቢውም ሰው ነው። ኃላፊ የሚሾመውም ሰው ነው። በአጠቃላይ በየተቋሙ ካሉ የሚመለከታቸው አካላት ጋር ከሚነሱ የብልሹ አሰራር ጥያቄዎች ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በመንግሥት ተቋማት እንደ አንድ እቀድ ተይዞ ጥናት ተካሂዶ ሰፊ ዝግጅት እየተካሄደ ነው። የህዝብ ጥያቄ እንዴት ነው ምላሽ የሚያገኘው የሚለው ደግሞ በጥንቃቄ እና በጥናት ላይ የተመሰረተ ምላሽ ነው የሚፈልገው። ስለዚህ በአንድ በኩል በአጠቃላይ የኑሮ ውድነትን ሊቀርፍ የሚችል ሥራ እየተሰራ ነው ያለው። በተለይ ደግሞ ከመንግሥት ሠራተኛው ጋር በተያያዘ ጥናቶች ላይ የተመሰረተ ሥራዎችን ለመስራት በመንግሥት በኩል ጥረት እየተደረጉ ነው ያሉት።
ዘመን፡- ሌብነትን ለመከላከል መንግሥት የጀመረውን እንቅስቃሴ ፓርላማው በምን መልኩ እያገዘና እየተቆጣጠረ ነው ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- የክትትልና ቁጥር ሥራዎች ሲሠሩ አንዱ ተግባር አንድ በምክር ቤቱ የጸደቀ እቅድ ወደተግባር ሲገባ በጀት ይመደብለታል። አንደኛ የተመደበው በጀት ለታለመለት ዓላማ እየዋለ ነው ወይ የሚለውን ምክር ቤቱ ይከታተላል። ሁለተኛ ምክር ቤቱ በክትትልና ቁጥጥር ስራው በአስፈጻሚው ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ያለው አንዱ ሥራ በቴክኖሎጂ ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ አሰራሮችን ማረምና አውቶሜት የማድረግ ሥራ ነው። ከዚህ አንጻር ብልሹ አሰራርን ለመቅረፍ ምን ያክል በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ እየተሰራ ነው ?፣ የግዢ ሥርዓቱ ምን ያክል ግልጽ ነው ?፣ የሀብት አስተዳደር ሥርዓቱ ምን ያክል ግልጽ ነው? እንዲሁም ከዚህ ቀደም የነበሩ ከፍተኛ የሀብት ብክነት የሚያመጡ ልማዳዊ አሰራሮች ምን ያክል እየተቀየሩ ነው? የሚሉትን ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን በሁሉም ተቋማት በምናደርገው የክትትልና ቁጥጥር ሥራችን በሁሉም ቋሚ ኮሚቴዎቻችን እናከናውናለን። የመንግሥት አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ግን ይህ ሥራ በተለየመልኩ ይመለከተዋል። ይህን የበጀትና ፋይናንስ ቁጥጥር የሚያደርግ ቋሚ ኮሚቴ የሚመሩት የተፎካካሪ ፓርቲ አባል ናቸው። ይህን ያደረግነው የክትትልና ቁጥጥር ሥራው የበለጠ ጠንካራ እንዲሆን ነው።
ዘመን፡- የህዝብ መገናኛ ብዙኃን በነጻነት እንዲሰሩ ተጠሪነታቸው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሆን ተደርጓል። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዲሁም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በዚህ መስመር ላይ ነው ያሉት፣ እነዚህ የመገናኛ ብዙኃኑ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ ፓርላማው ምን እያገዛቸው ነው ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- በአጠቃላይ የዴሞክራሲ ተቋማት የሚባሉት ተጠሪነታቸው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። የመገናኛ ብዙኃን፣ ሰብዓዊ መብት፣ ምርጫ ቦርድና ሌሎችም ተጠሪነታቸው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ከተነሳው ጥያቄ አኳያ ተቋማዊ ነጻነታቸው እንዲጠበቅ ምን እያገዛችኋቸው ነው ለሚለው አንደኛ ሚዲያዎች ተቋማዊ ነጻነት ኖሯቸው ሥራቸውን እንዲሰሩ ለማድረግ ድጋፍ መስጠት ነው። ሁለተኛው ለስራቸው የሚያስፈልጉ አዋጆች፣ መመሪያዎችና ደንቦች በጥናት ላይ ተመስርተው ሲመጡ እነዚህን በዝርዝር አይቶ የሚሰራው ሥራ ተቋሙን ገንብቶ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚጠቅም መልኩ የሃሳብ ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚችሉ እንዲሆኑ ማስቻል ነው።
የአሰራር፣ የአደረጃጀትና የሰው ኃይል መምሪያ መመሪያዎችን አዘጋጅቶ ተቋማት እንዲደገፉ ማድረግ ነው። ከዚህ አኳያ በዚህ ዓመት ብዙ ሥራ ነው እየተሰራ ያለው። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ላይ የተሰራው ሥራ አንዱ ነው፤ አዋጃቸው እንዲሻሻል ተደርጓል፣ የሰው ሀብት ልማትም እንዲሻሻል ተደርጓል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም ላይ የሰው ኃይል እንዴት ነው ማስተዳደር ያለበት የሚለው ተጠንቶ ቀርቧል። ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም በተመሳሳይ ድጋፎች እየተሰጡ ነው። ስለዚህ እየተሰራ ያለው በአንድ በኩል ጠንካራ በሌላ በኩል ደግሞ ፕሮፌሽናል ተቋማት እንዲኖሩ ነው። ጠንካራ የምርምር ተቋማት እንዲሆኑና ለሁሉም የሚያገለግሉ ተቋማት እንዲሆኑ ነው ድጋፍ እየተሰጣቸው ያለው። እንደሚታወቀው የሀገራችን አንዱ ችግር ነው ተብሎ የሚወሰደው ጠንካራ ተቋማት አለመገንባታቸው ነው። ስለዚህ ተቋማት በተለይም የዴሞክራሲ ተቋማት ሁሉም ዜጋ የሚተማመንባቸው ተቋማት ሆነው እንዲወጡ መንግሥት ጠንካራ ሥራ እየሰራ ነው የሚገኘው። ሌሎችም የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የደህንነትና የሰላም ተቋማት ጠንካራ እንዲሆኑ መንግሥት ጠንካራ ሥራ ነው እየሰራ ያለው። ከዚህ አኳያ ተቋማትም እየተደገፉ ነው ያሉት የሚል አቋም ነው ያለኝ።
ዘመን፡- በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችንና ቀውሶችን ካለፉት መንግሥታት ጋር በማነጻጸር ሰላምን ከማረጋገጥ አንጻር የብልጽግና መንግሥት ደከም ብሏል ብለው የሚተቹ አካላት አሉ። እንደ መንግሥት ተጠሪነትዎ ለዚህ ምላሽዎ ምንድነው?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩ አንዳንድ ችግሮች አሉ፤ የጸጥታ ችግር አለ። ዘላቂ ሰላምን ከመገንባት አኳያ የሚታዩ ችግሮች አሉ። ተግዳሮቶች አሉ፤ ይህ እውነት ነው። እነዚህ ችግሮች ግን ምን አይነት ባህርይ አላቸው የሚለውን ስናይ ከትናንት የወረስናቸው ናቸው። ዛሬ ላይ ያለው መንግሥት፣ ዛሬ ያለው ትውልድ ዋጋ ከፍሎ ሊያስተካክላቸው የሚያስፈልጉ ናቸው።
የችግሮቻችን ምንጭ በጣም ብዙ ነው፤ ነገር ግን ዋናዎቹ ሁለት ናቸው ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል። አንደኛው ፖለቲካዊ ምክንያት ነው። ፖለቲካዊ ምክንያቱን ብንወስድ ኢትዮጵያ በተፈጥሮዋ የብዝኃነት ማዕከል ናት። የሃሳብ ፣ የባህል እና የመልክዓ ምድር ብዝኃነት ማዕከል ናት። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይህን ብዝኃነት በአግባቡ ማስተናገድ የሚችል አይነት የፖለቲካ ባህል አልተገነባም። የፖለቲካ ባህላችን ከአንድጽንፍ ወደ ሌላ ጽንፍ ሲሄድ ነው የቆየው። ስለዚህ አንዱ ተግዳሮት ለሀገርና ለህዝብ ሲባል ዜጎች ወደ አንድ እንዲመጡ የሚሰሩ የፖለቲካ ልሂቃን፣ የሚዲያ ተቋማትና አክቲቪስቶች ይልቅ፣ ልዩነትን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሰፋ የሚያደርጉ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ኃይሎች ይበዛሉ።
የአንድ ሀገር ዜጎች በጋራ ሊቆሙባቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ በምንም ተአምር የአንድ ሀገር ዜጎች በሰንደቅ አላማቸው ላይ መጣላት የለባቸውም። ሰንደቅ ዓላማ የግጭት መነሻ መሆን የለበትም። እንዲሁም በህገመንግሥት ዋና ዋና መሰረቶች ላይ መጣላት የለባቸውም። ህገመንግሥት አንዴ ከተቀረጸ በኋላ በየጊዜው እየተሻሻለ ሊሄድ ይችላል። የአንድ ሀገር ዜጎች ሀገራዊ በሆኑ በዓላት ላይ መጣላት የለባቸውም።
እኛ ሀገር እንደ አለመታደል ሆኖ እንደ አንድ ሀገር ዜጎች እጅግ አብዛኛው ሰው ሊግባባባቸው በሚገባ ጉዳዮች ላይ እንኳ መግባባት ያልተፈጠረበት ነባራዊ ሁኔታ ነው ያለው። ይሄ ከመጣንበት የፖለቲካ ባህላችን ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ችግር ነው። ስለዚህ ይህ ችግር ግጭትን ያመጣል፤ እዚህም እዚያም ተግባብቶ ለአንድ ሀገር መቆም ሳይሆን እያንዳንዱ የእኔ እውነት ከእከሌ እውነት ይበልጣል ብሎ በተናጠል የየራሱን እውነት ይዞ ሩጫ ውስጥ ይገባል። ይህ ደግሞ ከዘመን አመጣሹ የማኅበራዊ ሚዲያና ከኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አብዮት ጋር ተያይዞ የከፋ ችግር እንዲኖር ያደርጋል። ስለዚህ ከመጀመሪያው ይህ ችግር መፈታት መቻል አለበት።
ታሪካችን በእርስ በእርስ ጦርነትና ሽኩቻ አዙሪት ውስጥ ነው የቆየው። መሃል ላይ አንዳንድ ጊዜ ጋብ ይልና የሆነ ነገር ሲፈጠር ታምቆ የነበረው ይፈነዳና ብዙ ነገር ያበላሻል። በሌላ አባባል ከፖለቲካ ባህላችን በመነሳት በሀገራችን አዎንታዊ የሰላም ባህል ግንባታ በጣም ደካማ ነው የነበረው። አዎንታዊ የሰላም ግንባታ ሂደት ማለት እያንዳንዱ ዜጋ የሰላም ባለቤት መሆንኑ መረዳት፤ ሠላሙን ሊያደፈርሱ የሚችሉ ነገሮች ሲኖሩ በሰላማዊ መንገድ መፍታትን እንደ ባህል መውሰድ፤ ሰላም በእርስ በእርስ ጦርነትና በግጭትእንደማይመጣ መገንዘብ፤ የእርስ በእርስ ጦርነትና ግጭት አሸናፊን እንደማያረጋግጥ፣ ይልቁንም መቆረቆዝን ያመጣል ብሎ ማመን፤ በፖለቲካ ኃይሎች መካከልም የትኛውም የሃሳብ ልዩነት በጠረቤዛ ዙሪያ በውይይትና በንግግር መፍታት፤ አብዛኛው ሰው ለሚቀበለው ሃሳብ ተገዢ መሆን፤ እንዲሁም ሃሳቡ ተቀባይነት ያላገኘ ሰው በቀጣይ ተቀባይነት እስከሚያገኝ ድረስ በሰላማዊ መንገድ መስራት የሚሉት ባህሎች ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበሩም። ማንኛውም የሃሳብ ልዩነት የሚፈታው በግጭት ነው የሚል እምነት ነው የተያዘው፤ ዛሬ ላይ ያለው ዋነኛ የግጭት ምክንያት ከዚህ የፖለቲካ ባህላችን ጋር የተያያዘ ነው።
ሁለተኛው ኋላቀርነት እና ድህነት ነው። ግጭቶች ሲኖሩ በድህነት ምክንያት ተስፋ የቆረጡ ሰዎች ይሳተፋሉ። ስለዚህ በአንድ በኩል እኔ ብቻ ልክ ነኝ፣ ከእኔ ውጪ ማንም ሊኖር አይችልም የሚል አመለካከትን መቀየር ያስፈልጋል። ይህ ሀገር የጋራ ነው፣ ወደ አንድ የሚያመጣን ሃሳቡ እንጂ የእኔ ብቻ የሚል እሳቤ ሊኖር አይችልም።
ሌላው በመካከል ደግሞ የፖለቲካ ነጋዴዎች አሉ። መንግሥት ነገሮችን በሆደ ሰፊነት ሲመለከት የብልጽግና መንግሥት ተዳክሟል የሚሉ ወገኖች፣ ተዳክሟል ያሉት መንግሥት ህገወጥ ተግባራት ላይ እርምጃ ሲወስድ ደግሞ፣ መንግሥት የኃይል እርምጃ አብዝቷል አምባገነን ሆኗል ይላሉ። መንግሥት ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር ሲሠራ መንግሥት ህግ ጨፍላቂ እንደሆነ በመስበክ መንግሥትን አጣብቂኝ ውስጥ በመክተት የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት ለማሳካት የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ።
በመንግሥት በኩል ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩል የሚታይበት፤ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እኩል የሚሆኑበት እንዲሁም ሁሉም ሃሳቦች ወደ መድረክ መጥተው የሚደመጡበት ሥርዓት እንዲኖር ነው የሚፈልገው።
ከዚህ አኳያ መንግሥት ሀገራዊ መግባባት ላይ እንዲደረስ ሁሉን አቀፍ አካታች ብሔራዊ ምክክር እንዲካሄድ እየሰራ ነው። በሀገራዊ ውይይት ብዙዎቹ ጉዳዮች በመግባባት ካለቁ መግባባትና የወል እውነት ይፈጠራል። ህዝብ በወከላቸው አካላት ደረጃ መግባባት ላይ የማይደረስባቸው ጉዳዮች ሲኖሩ ደግሞ ህዝበ ውሳኔ ይሰጥና ህዝቡ የወሰነው የሀገር (የወል) እውነት ይሆናል። ይህ ከሆነ እንደ ሀገር እንሻገራለን ብለን ይህንን እየሰራ ነው ያለነው። ስለዚህ መንግሥት አሁን ያጋጠመውን ችግር በሆደ ሰፊነት ሁሉንም አካል በማሳተፍ ለመፍታት እየሰራ ነው የሚገኘው።
ዘመን፡- በኢፕድ አስተናጋጅነት በክልል ከተሞች የተካሄደውን ስለኢትዮጵያ መድረክ ላይ እርስዎ ተካፋይ እንደነበሩ አውቃለሁ። በእርስዎ እይታ ይህ መድረክ ለሀገር ያለውን ፋይዳ እንዴት ተረዱት? በቀጣይስ ምን መደረግ አለበት?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- ስለ ኢትዮጵያ የውይይት መድረክ በጣም ጥሩ ነው የሚል እይታ አለኝ። እኛ ኢትዮጵያውያን የሚያስፈልገን እንዲህ አይነት ነገር ነው። የተለያዩ ሃሳቦች ወደ መድረክ እንዲመጡ እድል የከፈተ ነው። ስለ ሀገራችን የምንመካከርበት፣ የምንወያይበት፣ ልምዳችንን የምናካፍልበት እና እውቀታችንን የምናጋራበት መሰል መድረክ መስፋፋት አለበት። ከዚህ አኳያ በጣም ጥሩ ፕሮግራም ነው ብዬ አምናለሁ።
ሁለተኛው ስለ ኢትዮጵያ የሚለው ፕሮግራም በተለያዩ ከተሞች ነው ሲካሄድ የነበረው። ይህም ኢትዮጵያውያን ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ሄደው አንዱ ጋር ያለውን የኢትዮጵያ እሴት ሌላኛው እንዲመለከት ዕድል የሰጠ ነው። ኢትዮጵያ በጣም የምትገርም ትልቅ ሀገር ናት፤ ብዙ ገጽታ አላት። ስለዚህ በየአካባቢው ያለው ገጽታ ምንድነው የሚለውን ሰው መመልከት እንዲችል አድርጓል።
በሀገር ደረጃ ከለውጡ በኋላ ቱሪዝም አንዱ የእድገታችን ምንጭ መሆን አለበት ተብሎ ተወስዷል። ቱሪዝም እንደ አንድ እድገት ምንጭ የተወሰደበት ምክንያት ከውጪ የሚመጡ ፈረንጆች ብቻ እንደሚሳተፉበት ታስቦ አይደለም። በሀገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ከአንድ አካባቢ ወደሌላ አካባቢ ሄደው ሀገራቸውን በደንብ ማወቅ አለባቸው። አንድ ኢትዮጵያዊ ከሰሜን ጫፍ ወደ ደቡብ ጫፍ ከምስራቅ ጫፍ ወደ ምዕራብ ጫፍ እየተንቀሳቀሰ ሀገሩን የሚያውቅ ከሆነ ኢትዮጵያ እሱ የተወለደበት አካባቢ ብቻ ሳትሆን በሁሉም ጫፎች የሚታይ እውነታዎችን የያዘች መሆኗን ይረዳል፤ ይህ ለቱሪዝም ዘርፉ በተሰጠ ከፍተኛ ትኩረት በመንግሥት ደረጃ እየተሰራ ነው። ስለኢትዮጵያ የተሰኘው መድረክ ይህን እድል አስገኝቷል። ስለዚህ በእኔ እምነት ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መድረክ ነው።
እኔ ጋምቤላ ላይ በተካሄደው መድረክ ተሳትፌያለሁ። እዛ መድረክ ላይ አንድ የጥናት ጽሑፍ አቅራቢ ነበርኩ፤ አንዱ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው ተብሎ የሚታመነው የብዝኃነት አያያዝን በተመለከተ የሌሎች ሀገራት ልምድ ምን ይመስላል፤ እኛ ሀገር ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምንድን ነው እንዲሁም ከሌሎች ሀገራት ልምድ በመነሳት ከእኛ አኳያ አጣጥመን የራሳችን ማድረግ አለብን የሚሉ ጉዳዮች ላይ ምላሽ የሚሰጥ ውይይት ነበር ያካሄድነው። እኔም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የተሳተፍኩበት መድረክ በመሆኑ በጣም ጥሩ እንደሆነ መመስከር እችላለሁ።
ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናሁ!
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡-እኔም አመሰግናለሁ።
ተስፋ ፈሩ