ፍትህን- ከወረቀት በዘለለ!

የዲሞክራሲ መርሆዎች ተብለው በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካላቸው መሰረታዊ ነገሮች መካከል አንዱ ነጻ፣ጠንካራና ገለልተኛ የፍትህ ስርዓት መኖር ነው። በሰለጠነው ዘመን ደግሞ ማንኛውም ዲሞክራሲያዊ መንግስት ሦስት መዋቅሮች ይኖሩታል። እነሱም ህግ አውጪ፣ህግ አስፈጻሚና ህግ ተርጓሚ ናቸው። እነዚህ መዋቅሮች ደግሞ እርስ በርሳቸው የተያያዙና አንዱ ለሌላው መኖር የግድ ያስፈልጋሉ። በተለይ ደግሞ የወጣው ህግ በአግባቡ እንዲተረጎም እና ሰብዓዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ ለማድረግ የፍርድ ቤቶች ሚና የማይተካ ነው።

ለዚህም ነው ፍርድ ቤት ለዲሞክራሲ ስርዓት መጎልበት ካለው አስፈላጊነት አኳያ የመንግስት አንድ ሶስተኛው አካል ነው የሚባለው። ይሁን እንጂ እንደ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ምርጫ ቦርድ፣ እንባ ጠባቂ ተቋም እና ሌሎች የሲቪክ ማህበራትም ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጎልበት የየራሳቸውን ድርሻ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል። እነዚህ ተቋማት ግን እንደ መደበኛው ፍርድ ቤት ቀጥተኛ የማስፈጸም አቅም አይኖራቸውም። በፍትህ ስርዓቱ ላይ ግን ምርመራ አድርገው ሪፖርት ያቀርባሉ። ምርመራቸውን መነሻ አድርገውም በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ አስተዳደራዊ ውሳኔና ቅጣት የማስተላለፍ ሃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

ይሁን እንጂ ህግ በፓርላማ ወጥቶ በወረቀት ቢሰፍርም የዜጎች ትክክለኛ መብት ሊከበርና መሬት ሊነካ የሚችለው በመደበኛ ፍርድ ቤት ተገቢው ትርጉም ሲሰጠው መሆኑን የሚያብራሩት የህግ አማካሪና ጠበቃ፣ እንዲሁም የፌዴራል ጠበቆች ማህበር ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም ናቸው። እንደእሳቸው ገለጻ፣ ምንምዓይነት ህጎች እና አዋጆች ቢወጡም ትክክለኛ ፍርድ ቤቶች ኖረው ፍትህ እስካልሰፈነ ድረስ፣ ህጉ በወረቀት ላይ ከመስፈር የዘለለ ትርጉም አይኖረውም። ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ደግሞ የፍትህ ስርዓትን ማጠናከር በህገ መንግስቱ አንቀጽ 12 ላይ በግልጽ ተመላክቷል። አብዛኛዎቹ የህግ አንቀጾች ደግሞ ከሰብዓዊ መብት መከበር ጋር የተያያዙ ናቸው። ለእነዚህ ሰብዓዊ መብቶች መከበር ተፈጻሚነት ዲሞክራሲያዊ የመንግስት ስርዓትን ማጠናከር እጅግ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው።

በለውጡ ከፍትህ ስርዓቱ ጋር የተያያዙ ህጎችን፣ አዋጆችንና አሰራሮችን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። በማሻሻል ስራው ደግሞ በዘርፉ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች በማሳተፍ ትልቅ ስራ ተሰርቷል ተብሎም ይታሰባል። በእኛ አገር በተግባር እንደሚስተዋለው ግን ትክክለኛ ህግ ይወጣል፣ በሠነድ ደረጃም ይቀመጣል። ነገር ግን በፈጻሚው ሰው ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ችሎታ፣ ብቃት እና ስነ ምግባር ላይ ተሰርቷል ወይ የሚለው ትኩረት አይሰጠውም። በእነዚህ በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተቋማት ላይ የሚመደቡና የሚሾሙ የስራ ኃላፊዎች አመላመል ችግር እንደሚታይ ጠበቃው ይናገራሉ።

የፍትህ ተቋማትን በአግባቡ መርተው በአፈጻጸሙ ስኬታማ ማድረግ የሚችሉ ናቸው ተብለው በአንጻራዊነት የተሻሉ መሪዎች በእምባ ጠባቂ፣ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ በምርጫ ቦርድ እና በሌሎች ተቋማትም ተመድበዋል፣ተሹመዋልም። አሁን ላይ የፍትህ ተቋማት ኃላፊዎቸን በውድድር መመደብ መጀመሩም ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት የሚያመላክት ነው። አብዛኛዎቹ የፍትህ ተቋማት በተለይም ከመደበኛው ፍርድ ቤት ውጪ ያሉት የሚቀራቸው እና ወደፊት የበለጠ ማሻሻል የሚኖርባቸው ነገር ቢኖርም እንደ ምርጫ ቦርድየመሳሰሉ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዙ የሚያነሷቸው ጉዳዮች ጅምራቸው በበጎ ጎን ሊነሳ የሚገባው ነው። በፍርድ ቤቶችም ቢሆን አልፎ አልፎ ጥሩ የተሻሻሉ አፈጻጸሞች መኖራቸውን መካድ እንደማይቻል አቶ ፊሊጶስ ያስረዳሉ።

ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን በአገራችን በፍትህ ስርዓቱ ትልቅ ክፍተት የሚታይበትን ስራና ሰራተኛን ሙሉ በሙሉ ማገናኘት ተችሏል ማለት ግን አያስደፍርም። አብዛኛውን ጊዜ ትኩረት ሲሰጠው የሚስተዋለው ለፖለቲካው ነው። የተረጋጋ የፍትህ ስርዓት እና የዳኝነት ተቋማት ተፈጥረው የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ችግር ለማቃለል ደግሞ ፖለቲካ ብቻውን አቅም እንደሌለው አቶ ፊሊጶስ ያነሳሉ።

በመሆኑም በአገራችን ከሚስተዋሉ ከሰላም እጦትና ከተለያዩ ጦርነቶች ጋር በተያያዘ ሙሉ በሙሉ የሰብዓዊ መብትን የሚያስከብሩ ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ተፈጥረው በፍትህ ስርዓቱ መሰረታዊ ለውጥ መጥቷል ለማለት አይቻልም። በፍትህ ስርዓት ውስጥ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሲባል የሰው ልጅ እንኳን በህይወት የመኖር መብት ቀርቶ፣ ከዚያም አልፎ የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት እና በነጻነት የመንቀሳቀስ መብቱ ሙሉ ለሙሉ እንዲከበርለት ይጠበቃል። የዲሞክራሲ መብቶች ደግሞ ሰብዓዊና ዴሞክራሲ መብቶች ተብለው በሁለት ይከፈላሉ። የዴሞክራሲ መብት ዋናው አስፈላጊነቱ የሰውን ልጅ የሰብዓዊ መብት በዕኩልነትና በፍትሃዊነት ማስከበር መቻል ነው። ከዚህ አንጻር በአገራችን በተለይም በክልሎች ከጦርነትና ከተለያዩ የሰላም ችግሮች ጋር በተያያዘ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በህይዎት የመኖር መብትን ከማሳጣት ጀምሮ፣ሀብትና ንብረቱን የመዘረፍ፣የመፈናቀል እና የአካል መጉደል ችግሮች ይታያሉ።

ስለሆነም የህግ የበላይነትን ለማስፈንቋሚና ወጥ የሆነ የፍትህ ስርዓት በዳኝነቱ ዙሪያ አልተፈጠረም። ምክንያቱ ደግሞ ዳኝነት የሁለት ተቃራኒ ወገኖችን ጉዳይ የሚመለከት ከባድ ስራ በመሆኑ ነው። ይሁን እንጂ በዘርፉ ባለሙያዎች ሲሾሙና ሲመደቡ ግን በትክክል ለዳኝነቱ የሚስማሙ፣ በችሎታቸውም፣ በስነ ምግባራቸውም ሆነ በልምዳቸው የተሻሉት የሚመረጡበት ሁኔታ የለም ይላሉ አቶ ፊሊጶስ። የህግ ምሁሩ አያይዘውም፣ በሌላ መልኩ ደግሞ ስራውን በአግባቡ የሚያውቁትን፣ ችሎታና ስነ ምግባር ያላቸውን ባለሙያዎች በስራው ላይ ከማቆየት ይልቅ ከቦታው ማንሳት እየተለመደ መጥቷል። በቅርቡ እንኳ በ100 የሚቆጠሩ ዳኞችና ዐቃቤ ህጎች ከፍትህ ሚኒስቴር ስራ ለቀዋል። ከስራ ለመልቀቃቸው እንደ ምክንያት ከሚነሳው መካከል ደግሞ ምቹ የስራ ሁኔታ ካለመፈጠሩ በተጨማሪ፣ ከደመወዝና ጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ በባንክ፣ በኢንሹራንስ እና በጥብቅና መስራት የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑን ያነሳሉ።

ዳኞችን ለማስተዳደር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1233/2013ዓ.ም ግን ነጻ፣ የህዝብ አመኔታ ያተረፈ፣ የስነ ምግባር እሴት የተንጸባረቀበት ፍ/ቤት መቋቋም እንዳለበት እንደሚደነግግ፣ በዚህ ተቋም የሚሰሩ ዳኞችን አመላመልና አመራረጥ፣በአጠቃላይ ሂደቱ ግልጽነት የተላበሰ እንዲሆንም አዋጁ በግልጽ የሚያስቀምጥ ስለመሆኑ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዜዳንት እና የፌደራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ተስፋየ ንዋይ ያስረዳሉ። እንደርሳቸው ማብራሪያ፣ አንድን ዳኛ ለመሾም ወይም ለመመደብ ደግሞ በአዋጁ ከተደነገጉ አጠቃላይ መስፈርቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ፣ ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ የሆነ፣ ከፍተኛ የግብረ ገብነት ሞራል የተላበሰ፣ ጨዋነቱ፣ ቅንነቱና ሀቀኝነቱ የተረጋገጠ፣ ህዝብ ከሚነቅፈው ሞራል ነክ ልምዶች እና ሱሶች የራቀ፣ ከፍያለ የህዝብ ስሜት ያለው እና ለህግ የበላይነት መከበር ቁርጠኛ የሆነ የሚሉት ይገኙበታል። እንደየፍርደ ቤቶቹ ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ ከስራ ልምድ ጋር በተያያዘ በአቃቢ ህግነት፣ በህግ አማካሪነት፣ በጠበቃነት ወይም በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ረዳት ዳኛነት ቢያንስ ሶስት አመት ያገለገለ፣ ዕድሜው 30 ዓመት የሞላው እና በህግ ቢያንስ የመጀመሪያ ድግሪ ያለው መሆን እንዳለበትም ህጉ ያስቀምጣል።

አቶ ተስፋየ አያይዘውም፣ በቅርቡ በ2012 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ የተደረገውን የፌዴራል ዳኞች ሹመት በምሳሌነት ያነሳሉ። ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች 40 ዳኞች እና ለመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች 50 ዳኞች መሾማቸውን የሚናገሩት አቶ ተስፋየ፣ በሹመቱ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ ስለመያዙ ወይም ደግሞ የስራ ልምዱ ብቻ አልታየም። የስነ ምግባር መስፈርቶችን፣ በተለይም ከፍያለ የህዝብ ስሜት ያለው፣ በወንጀል ተከሶ ጥፋተኛ ያልተባለ፣ ታማኝ የሆነ፣ ስራ የሚወድ፣ የመሳሰሉ ታይተዋል ይላሉ።

ምክንያቱን ሲያስረዱም፣ ዳኝነት በባህሪይው ሁለት ተከራካሪ ወገኖች እና ባላንጣዎች የሚፋለሙበትን ጉዳይ ገለልተኛ፣ከግል ፍላጎቱ ነጻ ሆኖ ውሳኔ የሚሰጥ፣ ከፍተኛ የስነምግባር እሴት የተላበሰ ባለሙያ መሆን ስለሚገባው መሆኑን ይገልጻሉ። በእሳቸው እምነት፣ የዳኞች ምልመላ፣ ምደባ እና ሹመት እየተከናወነ የሚገኘው በበቂ የህግ ማዕቀፍ ተደግፎና በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ነው።

የዲሞክራሲ ስርዓት እንዲጎለብት ደግሞ የዳኝነት ተቋማት የየድርሻቸውን ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል። የዲሞክራሲ ስርዓት ከሚገለጽባቸው መንገዶች መካከል ደግሞ አንዱ ሰብዓዊ መብቶችን ማክበርና ማስከበር ነው። በመሆኑም በወንጀልም ሆነ በፍትሃብሄር ጉዳዮች ዙሪያ በፓርላማው የወጡና በህገ መንግስቱ የተቀመጡ የዲሞክራሲ ህጎችና መርሆዎችን የዳኝነት ስርዓቱ ሊያስጠብቅ የግድ ነው። ከምርጫ፣ከሰብዓዊ መብቶች፣ከእንባ ጠባቂ እና ከመሳሰሉ የፍትህ ስርዓት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማድረግ መስራት ይጠበቅበታል። ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ የፍትህ ስርዓቱ የሚጠበቅበትን ተግበርና ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ ነው ብሎ ማሰብ ይከብዳል።

ጉዳዩ የዳኝነት ነጻነትን ከማክበርና ማስከበር ጋር ይያያዛል ተብሎ ይታሰባል። የዳኝነት ነጻነት ደግሞ በተለያየ መልኩ ሊገለጽ ቢችልም፣በዋናነት በሁለት ከፍሎ ማየት እንደሚቻል በጅማ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት አቶ ፍራኦል ታደሰ ያስረዳሉ። እንደሳቸው ማብራሪያ፣ የመጀመሪያው የዳኝነት ነጻነት የዳኛው የራሱ ግለሰባዊ ነጻነቱን የሚመለከት ነው። ይህም ማለት የዳኛውን የመወሰን ነጻነት/ decitional indpendent/ በተመለከተ ያለውን ነጻነት ይዳስሳል። ዳኞች የዳኝነቱንም ሆነ ሌሎች በህግ የተሰጣቸውን ስልጣን፣ስራ ላይ በሚያውሉበት ወቅት ከማንኛውም አካል ተጽዕኖ እና ጫና ነጻ መሆናቸው መረጋገጥ አለበት። ዳኞች የዳኝነት ስራቸውን ሲሰሩ ያለምንም የውጭ አካል ጣልቃ ገብነት መፈጸም መቻል አለባቸው ከሚል ሃሳብ የሚነሳ ነው። የዳኝነት ነጻነት ሲባል ደግሞ በዳኝነቱ ስራ ላይ እንኳን የሌላ ሰው ጣልቃ መግባት ይቅርና ጉዳዩን የያዙት ዳኞች ራሳቸውም ጭምር ከግል ፍላጎት እና ስሜት ነጻ መሆን መቻል እንዳለባቸው ሙያው ይጠይቃል። ዳኛው የራሱን ፍላጎት እና ስሜት ወደ ጎን ትቶ፣ ህግና ህጉ የሚለውን ብቻ ተከትሎ መወሰን ይኖርበታል። ዳኛው በጉዳዩ ላይ የራሱን ፍላጎትና ስሜት ወደ ጎን ሊተወው የማይችል ከሆነ ደግሞ፣ በዳኝነት ስራው በያዘው ጉዳይ ላይ ውሳኔ ከመስጠት ራሱን ማግለል ይገባዋል ማለት ነው።

ከዳኛው ግላዊ ነጻነት ጋር በተያያዘ ሊነሳ የሚገባው ሌላው ጉዳይ ከውድድርና አመዳደብ ጋር የተያያዙ ሊከበሩ የሚገባቸው የአሰራር ነጻነቶች ናቸው። ዳኞች ዝውውር፣ ዕድገትና ሹመት የሚያገኙት የስራ ቆይታቸውን፣ የአገልግሎትዘመናቸውን፣ዕውቀታቸውን፣ችሎታቸውን፣ ስነ ምግባራቸውን፣ ወዘተ መሰረት ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ ህገ መንግስቱ ያስቀምጣል። ይህ ማለት ደግሞ የዳኞች ነጻነት በህግ አሰፈጻሚው ወይም በህግ አውጪው የግል ፍላጎት ተጽእኖ ስር ሊወድቅ አይገባውም የሚል ሃሳብን የያዘ መሰረታዊ ጉዳይ ነው።

እንደ አቶ ፍራኦል ገለጻ፣ሁለተኛው የዳኝነት ነጻነት አስተዳደራዊ ወይም ተቋማዊ የዳኝነት ነጻነትን ይመለከታል። አንድ ዳኛ በሚያከናውነው ስራ ላይ ውሳኔያዊና ግላዊ ነጻነት አለው ቢባል እንኳ፣በተቋማዊ ነጻነት እስካልተጠናከረ ድረስየዳኝነት ነጻነቱ የተሟላ ነው ማለት አይቻልም። በመሆኑም በአጠቃላይ ሃሳቡ የዳኝነት አስተዳደር ወይም ተቋማት ከህግ አውጪውና ከህግ አስፈጻሚው አካል ፍጹም ነጻ መሆን እንደሚኖርባቸው የሚያመላክት ነው። ስለዚህ የዳኝነት ነጻነት ሲባል አንድም ዳኛን እንደግለሰብ ብቻውን፣ሁለትም ተቋምን በአጠቃላይ በማካተት የፍትህ ስርዓቱን ከማንኛውም ውጫዊ አካል ጣልቃ ገብነት ፍጹም ነጻ መሆን እንደሚኖርበት የሚገልጽ ነው።

በተመሳሳይ መንገድ አቶ ፍሊጶስም፣ የዳኝነት ነጻነት ሲባል ዳኛውን እና ተቋሙን በሁለት ከፍሎ ለየብቻ የዳኞችን እና የተቋሙን የፍትህ ስርዓትን ከማስፈን አንጻር የሚኖራቸውን ነጻነት ማየትን የሚጠይቅ መሆኑን ይስማሙበታል። የዳኝነት ነጻነት ሲባል የዳኛውን በህግ የተሰጠውን የግል ነጻነቱን ይመለከታል። ዳኛው ልክ እንደ ፓርላማ አባላት እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በቀር በአዋጅ የተሰጠው ያለመከሰስ መብቱ መጠበቁን የሚመለከት ነው። ዳኛው የሚሰጠው ውሳኔ ደግሞ ነጻ ሆኖ ህጉንና ህጉን ብቻ መሰረት ያደርጋል። በወንጀልም ሆነ በፍታብሄር ጉዳይ የቀረበለትን ክርክር ፍሬ ነገርና ማስረጃ ላይ ብቻ ይመሰረታል። ማንኛውም ሰው በህግ ፊት ዕኩል ነው የሚለውን በህገ መንግስቱ አንቀጽ 25 ላይ በተቀመጠው ህግ መሰረት፣ አስፈጻሚውም ሆነ ፕሬዚዳንቱ፣ ማንኛውም ዓይነት ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ተጽዕኖ ጣልቃ ሳይገቡበት በነጻነት መወሰን መቻሉን የሚመለከት መሆኑን ያብራራሉ።

የዳኝነት ተቋሙ ከአስተዳደራዊ ነጻነት ጋር በተያያዘ ከደመወዝ፣ከሰራተኛ ቅጥር እና ከአሿሿም ጋር በተገናኘም ከአድልዎ እና ብልሹ አሰራር ነጻ እንዲሆን ይጠበቃል። በዚህ ደረጃ በ2013 ዓ.ም የፍርድ ቤት ማሻሻያ አዋጆች 12/33 እና 12/34 ላይ ቀደም ሲል ያልነበሩ ጉዳዮች ተካተውበታል። ሠራተኞችን ከሲቪል ሰርቪስ ተቋም ይልቅ ፍርድ ቤቱ ራሱ እንዲያስተዳደር፣ በጀቱን ለፓርላማ አቅርቦ ማስጸደቅ እንዲችልና የዳኞች አስተዳደር ጉባኤም የበለጠ በፍትህ ስርዓቱ ተሳትፎ እንዲኖርበት ከግምት ውስጥ ያስገባ እና የመሳሰሉ ማሻሻያዎች የተካተቱበት መሆኑን አቶ ፍሊጶስ ያስረዳሉ።

ይሁን እንጂ እንደ አቶ ፊሊጶስ እይታ፣የዳኝነት ነጻነት አለመከበርን በተመለከተ ብዙ ችግሮችን ማንሳት ይቻላል። ነጻነትን የመጋፋቱ ሁኔታ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ የሚፈጸመው በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ በእጅ አዙር ነው። በመሆኑም በአንዳንድ አካባቢዎች ዳኞች በፈረዱት ፍርድ በህግ አግባብ ተጠያቂ ሳይሆኑ የማሰር፣ በቁጥጥር ስር ማዋል እና ማፈን ሲፈጸምባቸው ይታያል። ለምሳሌ፣በፍርድ ቤት ይህ ቤት እንዳይፈርስ ተብሎ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ወረዳው ወይም ክፍለ ከተማው በራሱ ጊዜ ሲያፈርሰው ይታያል። ያለ ፍርድ ቤት የትዕዛዝ ወረቀት ደግሞ ቤት የሚበረበርበት እና ሰው የሚታሰርበት ሁኔታአለ። ፍርድ ቤት ይፈታ ያለውንና የዋስትና መብቱ ይጠበቅለት ብሎ የወሰነውን ተጠርጣሪ ሌላ ክስ አዘጋጅቶ ማሰር፣ ወደ ሌላ የእስር ቦታ ማንቀሳቀስና ሳይፈቱ እንደፈለጉ ማዘግየትም መደበኛ አሰራር እስኪመስል ድረስ እየተዘወተረ ይገኛል።

በፍትህ ስርዓቱ በተለያየ መንገድ የዳኝነት ነጻነት መጣስ እና ያለመከበር ሁኔታ ብዙ አመላካች ነገሮች መኖራቸውን አቶ ፍራኦልም ይስማሙበታል። እንደሳቸው ማብራሪያ፣ ዳኛ የፈታውን ፖሊስ የማሰር ሁኔታ እየተለመደ ከመምጣቱ በላይ የዳኛ መታሰርም ይስተዋላል። በዚህም የዳኝነት ነጻነት በአግባቡ መከበር ካልቻለ፣ የዜጎች መሰረታዊ የሰባዓዊ መብቶች ይከበራሉ ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ይህ ማለት ደግሞ ፍርድ ቤቱ በተቋም ደረጃ ነጻነት ከሌለው፣ ችግሩ ወደ ዳኞች እና ወደ ግለሰቦች መውረዱ የማይቀር መሆኑን መገንዘብ አይከብድም። የዚህ ችግር መሰረታዊ መነሻው ደግሞ፣ የአስፈጻሚ አካላት በፍትህ ስርዓቱ ላይ የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት መሆኑ ብዙ አመላካች ነገሮች አሉ። ህግ ተርጓሚው ዳኛው የፈታውን ተከሳሽ፣ ህግ አስፈጻሚው ፖሊስ የሚያስረው ከሆነ፣በምንም ዓይነት መልኩ የፍትህ ስርዓት ሊሰፍን አይችልም። ስለዚህ ዋናው የፍትህ ስርዓቱ ችግር አስፈጻሚ አካላት በፍርድ ቤት ጉዳዮች ጣልቃ መግባታቸው መሆኑን ማመን የግድ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ለችግሩ የበለጠ መስፋት ምክንያት የሚሆነው ደግሞ አስፈጻሚ አካላት በፍትህ ስርዓቱ ላይ ችግር ሲፈጥሩ ለምን ተብለው የሚጠየቁበት አሰራርም ሆነ የሚወሰድባቸው እርምጃ አለመኖሩ ነው። ችግር ሲፈጥሩ የሚጠየቁበት አሰራር አለመኖሩ ደግሞ ህግ መጣሱን በራሱ ጭራሽ እንደመብት ይቆጥሩታል።

በህገ መንግስቱ አንድን ዳኛ ለማሰር መከናወን የሚገባቸው የህግ አግባቦች በአግባቡ ተቀምጠዋል። በመጀመሪያ ደረጃ ዳኛውን መያዝ ተገቢ ሆኖ ከተገኘ በህግ ያለመከሰስ መብቱ በአግባቡ መነሳት ይገባዋል። ይህ ካልሆነ ደግሞ ዳኛው ወንጀል ሲሰራ እጅ ከፍንጅ መያዝ ይኖርበታል። ከዚህ ውጪ አንድን ዳኛ መያዝ፣ ከስራ ማገድና ማሰር ፈጽሞ አይቻልም። ነገር ግን አሁን ላይ ከዚያም አልፎ በተግባር ዳኞች በችሎት ላይ እያሉ ሁሉ ከችሎት ተነስተው ሲታሰሩ የሚታዩበት ሁኔታ መኖሩን አቶ ፍራኦል ያሰምሩበታል። ይህ አሰራር ደግሞ ለፍትህ ስርዓቱ አለመስፈን የአስፈጻሚው አካል ጣልቃ ገብነት በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አመላካች ነው እንደ አቶ ፍራኦል አስተያየት።

ፍርድ ቤት በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ አካላት ፍላጎት አለበት የሚሉት አቶ ተስፋዬ፣ ለፍርድ ቤት የቀረቡ ጉዳዮች ደግሞ ያለማንኛውም አካል ጣልቃ ገብነትና ተጽኖ መፈጸም ይኖርባቸዋል ይላሉ። ይሁን እንጂ ከፖሊሶች ጋር በተያያዘ የዋስትና ጉዳዮች በተለያየ አግባብ በተደጋጋሚ፣በሚዲያ ሳይቀርየሚነሱ ችግሮች መኖራቸውን፣ ተጠርጣሪዎችም አልተለቀቅነም የሚል አቤቱታ እንደሚያቀርቡና የዳኛን ውሳኔ ያለማክበር አዝማሚያዎች ስለመኖራቸው በአንዳንድ መዝገቦች መገንዘብ መቻላቸውን አልደበቁም። በተለይም የጊዜ ቀጠሮ ችሎቶችን በተመለከተ በህገ መንግስቱ በግልጽ እንደተቀመጠው ማንኛውም ሰው በልዩ ሁኔታ የሚከለክለው ጉዳይ ከሌለው በስተቀር የዋስትና መብት ሊጠበቅለት እንደሚገባ አቶ ተስፋየ ያስረዳሉ።

እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ፣የፖሊስ ተግባር ዳኛ የሰጠውን ውሳኔ በትዕዛዙ መሰረት መፈጸም ነው። ተከሻሹን በሌላ ወንጀል ከጠረጠሩት ደግሞ የዳኛውን ውሳኔ አክብረው፣ በሌላ ክስ እንደገና ማቅረብን ህጉ ይፈቅድላቸዋል። ተጠርጣሪን አልለቅም ማለት ግን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ማጓተትና መሻር ነው። በሌላ መንገድ የፍርድ ቤትን ነጻ ሆኖ የመወሰን ህገ መንግስታዊ ኃላፊነት መቃረን ነው። ስለሆነም አዋጅ ቁጥር 1234/2013 የፍርድ ቤትን ውሳኔ ማንኛውም አካል የማክበር፣የማስከበር እና እንዳይደናቀፍ የማድረግ ሃላፊነት አለበት ይላል። ሃለፍነቱን የማይወጣን አካል ደግሞ ዳኛው በህጉ መሰረት እንዲቀጣና ተጠያቂ እንዲያደርገው ሃላፊነት ሰጥቶታል። ይህን መነሻ በማድረግም ተገቢ ትዕዛዝ፣ማስጠንቀቂያና ቅጣት የተሰጠባቸው ጉዳዮች አሉ። ይሁን እንጂ ጉዳዩ እስከታችኛው የዳኝነት እርከን ድረስ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አቶ ተስፋየ ያምናሉ።

አቶ ፍራኦል እንደሚሉት ዳኞች ሲሾሙ በአብዛኛው ማለት በሚቻልበት ሁኔታ ስርዓቱን የሚደግፉና ለስርዓቱ ታማኝ የሆኑ ናቸው። የባለስልጣናቱን ሃሳብ የሚደግፉና የሚያዟቸውን የሚፈጽሙትን እየለዩ መሾም ተለምዷል። ይህ አሰራር ደግሞ ከፌደራል ጀምሮ ወደታች ወደ ክልልም የወረደና ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኝ ነው። በተለይም ደግሞ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛና ፕሬዚዳንት አሿሿ ላይ፣ስራ አስፈጻሚው ሊያሳካቸው የሚፈልጋቸውን ግቦች ሊያሳካልኝ ይችላል ብሎ የሚያስባቸውን እና የሚያምናቸውን ሰዎች ለይቶ መሾም ተበራክቷል። በመሆኑም ለስርዓቱና ለአስፈጻሚው አካል ምቹ የሆነ ሰው ከተሾመ ደግሞ ስርዓቱን መምሰሉ የግድ ነው። ለዚህም ነው የፍትህ ስርዓቱ የወቅቱን ስርዓት ይመስላል የሚባለው ይላሉ።

እንደ አቶ ተስፋየ ገለጻ ግን፣ ከ2010ዓ.ም በኋላ ነጻ፣ጠንካራ እና ከአስፈጻሚው አካል ተጸዕኖ የተላቀቀ ፍርድ ቤት ለማቋቋም ጥረት ተደርጓል። የዳኞች የስነ ልቦና ዝግጅት እንዲኖር የማድረግ ስራም ተሰርቷል። ለፍርድ ቤት የሚያስፈልገውን በጀትም በቀጥታ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ማስወሰን ተችሏል። በአብዛኛው በለውጡ በነጻ ፍርድ ቤት ግንባታ ላይ አወንታዊ የሚባል ተግባር ተከናውኗል ማለት ይቻላል። በፍርድ ቤት የተወሰኑ አንዳንድ ጉዳዮችም ቀደም ሲል ከነበረው የአስፈጻሚው አካል ጣልቃ ገብነትአንጻር እንዴት ሊሆን ቻለ የሚያስብሉ ናቸው። በምሳሌነት፣ ከምርጫ ጋር በተያያዘ የተከሳሽ መብቶችን ለማስጠበቅ ፍርድ ቤቶች ጉዳዮችን ነጻ ሆነው ለመወሰን ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። በዚህም አስፈጻሚው አካል ነጻ የሆነ ፍርድ ቤት እንዲኖር ዕድል ሰጥቷል ብሎ መናገር ይቻላል።

ነጻ መሆን ሲባል ደግሞ ከውጭ የሚመጣ ጣልቃ ገብነት ብቻ ሳይሆን፣ከውስጥ ከዳኛው የተሰጠን ስልጣን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ካለመጠቀም፣ ከራስና ከሚያውቁት ሰው ፍላጎት ነጻ መሆን፣ገለልተኛ በሆነ መልኩ ጉዳዮችን ማስተናገድንም እንደሚያካትት አቶ ተስፋየ ያስረዳሉ። እንደ እርሳቸው ሃሳብ፣ከዳኝነት ስራ ጋር በተያያዘ ክፍተቶች የሉም ማለት አይቻልም። የውጪ ጣልቃ ገብነት የቀነሰውን ያህል፣ ከውስጥ ግን ነጻ ሆኖ መስራት ላይ ችግሮችአሉ። ስለሆነም በዳኝነት አሰራር ነጻነት ላይ የለውጡ መንግስት የተሻለ ስለነበር መንግስት የሚመስል የዳኝነት ተቋም ሙሉ ለሙሉ አለ ለማለት የይከብዳል። በመሆኑም የነጻነት መርሁ ከተጠያቂነት መርሁ ጋራ ሚዛኑን እንዲጠብቅ ለማድረግ በቀጣይ ብዙ መሰራት እንደሚኖርበትም ያምናሉ።

አቶ ፊሊጶስ እንደሚያስረዱት፣ኦሮሚያ ክልል አማራና ትግሬ፣ትግራይ ክልል አማራውና ኦሮሞው፣ወዘተ ከክልሉ ብሄር ዕኩል መብት ሲያገኝ አይስተዋልም። ህጎቹ ደግሞ በራሳቸው በክልሎቹ ስለሚወጡ አድሏዊ ለመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው። ዳኛ፣ዐቃቤ ህግ፣ፖሊስ፣ የመሳሰሉት ህግ ተርጓሚውና አስፈጻሚው የሚሾመውም ሆነ የሚመደበው ከብሄሩ ስለሆነ፣ በክልሉ የሚኖረው ሌላው ብሄር ብዛቱ ለምን በሚሊዮን አይቆጠርም፣ ህጉ የሚቆመው ግን ለብሄሩ ብቻ ነው። ስለሆነም የዳኝነቱ ስርዓት ያንን ስርዓት ይመስላል የሚለው ሃሳብ በተግባር ስለሚታይ አባባሉ ትክክል ስለመሆኑ ያሰምሩበታል።

የፍትህ ስርዓቱ ደግሞ በሁሉም ነገር ለስራ ምቹ የሆነ እና ደረጃውን የጠበቀ ጽ/ቤት ያስፈልገዋል። በዚህ ረገድ በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ የፍርድ ቤት ጽ/ቤት ከመኖሩ ጋር በተያያዘ፣በተለይም በፌዴራል ፍርድ ቤቶች፣ በክልሎችና በከተሞች ደረጃ ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ዳኞች ፍትህ የሚያስችሉበት በቂ ጽ/ቤት አለ ብሎ መውሰድ እንደሚቻል አቶ ፍራኦል ይገልጻሉ።

በዚህ ሃሳብ ግን አቶ ፊሊጶስ አይስማሙም። በእሳቸው እይታ፣ ጥቂት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ህንጻዎች ተገንብተዋል። ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጠባብ ቢሆኑም ለእያንዳንዱ ዳኛ የራሱ ቢሮ አለው። የከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ቢሮዎች ግን ብዙዎቹ የኪራይ ናቸው። አብዛኛዎቹ ደግሞ ለዳኞች፣ለሰራተኞች እና ለባለ ጉዳዮች፣ ቀላል ነገር ግን በጣም አስፈላጊ የሆነው መታጠቢያ ውሃና ሽንት ቤት ሳይቀር የላቸውም። ጽ/ቤቶቹ በቂ፣ ለስራ ምቹ እና ከድምጽ ብክለት ነጻ አይደሉም። አብዛኛዎቹ ከተለያዩ ሁከቶች እንደ መኪና ጩክት በመሳሰሉት ይረበሻሉ።

ብዙዎቹ ጽ/ቤቶች ጠባብና ሶስት የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች በጋራ የሚገለገሉባቸው ናቸው። በዚህች ጠባብ ክፍል ውስጥ ደግሞ ችሎት ሁሉ ያስችሉባታል። በዚህም አንዱ አቤቱታ ሲያስተናግድ ሌላው መረበሹ የግድ ነው። ለድጋፍ ሰጪዎችም ሆነ ለባለጉዳዮች የሚቀመጡበትና የሚስተናገዱበት ወንበርና ቦታ ሁሉ በበቂ ሁኔታ የሌላቸው በረካታ ናቸው። ከዚህ የተነሳ በአጠቃላይ ከፍትህ ስርዓት አገልግሎት አሰጣጥ አንጻር ሲታዩ የፍርድ ቤት ተቋማት የፍርድ ቤትን ክብርና ደረጃ አይመጥኑም።የፍትህ ስርዓቱን ችግር የፍርድ ቤት አመራሩ መርምሮ መፍትሄ ለመስጠትም ከባድ የሚያደርጉት በርካታ ጉዳዮች አሉ የሚሉት ደግሞ አቶ ፍራኦል ናቸው። እንደሳቸው ገለጻ፣ በመጀመሪያ ደረጃ የፍርድ ቤት አመራሮች የዳኝነት ጥራት ችግርን የሚመረምሩበትና የሚለኩበት ችግር ፈቺ የሆነ መመሪያ በበቂ ሁኔታ የለም። ይሁን እንጂ የዳኞችን ችሎታ በአግባቡ መርምረው፣ይህ ዳኛ የተቀመጠው በሚገባው ቦታ ላይ አይደለም የሚሉበት ግልጽነት ያለው መመሪያ ግን ሊኖር የግድ ነው። በአንዳንድ ክልሎች አንዳንድ ጥሩ ጅምሮች ቢኖርም እንኳ መመሪያዎቹ በቂና ችግር ፈቺ አለመሆናቸው በችግርነት ይነሳል። ሁለተኛው ችግር የዳኛውን የስነ ምግባር ችግር ለመመርመርም አስቸጋሪ መሆኑ ነው። ምክንያቱም አንድ ዳኛ ራሱን አሳምኖ ወደዚህ ዓይነት የስነ ምግባር ችግር ሲገባ በራሱ ላይ ችግር እንደሚያስከትልበት ስለሚያውቅ ይጠነቀቃል። በመሆኑም ገና ከመጀመሪያው ጀምሮ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ስለሚያጠፋ ተጠያቂ ሊያደርጉት የሚችሉ መረጃዎች አይገኙበትም። በዚህም ምክንያት የዳኞችን የስነ ምግባር ችግር አመራሩ መርምሮ ውሳኔ ለመስጠትና መፍትሄ ለመፈለግ ከአቅሙ በላይ ሆኖበታል።በዳኞች አሰራር ላይ ክፍተቶች የሉም ማለት እንደማይቻል፣ ዳኞችም ሰዎች በመሆናቸው የስነ ምግባር ችግርና የህግ አተረጓጎም ስህተት ሊፈጽሙ እንደሚችሉ የሚናገሩት አቶ ተስፋየ ናቸው። እንደእርሳቸው ገለጻ፣ዳኞችን የሚገዛ የዳኞች የስነ ምግባርና የክስ ስነ ስርዓት ደንብ ወጥቷል። በዚህ ደንብ ላይ ዳኞች በችሎት፣ከችሎት ውጪና በግል ህይወታቸው ማድረግ ያለባቸውንና የሌለባቸውን ነገሮች በዝርዝር አስቀምጧቸዋል። በመሆኑም አብዛኛዎቹ ዳኞች የስነ ምግባር ደንቡን እንደሚያከብሩት ቢታመንም፣አንዳንድ ዳኞች ግን ደንቡ ከሚፈቅደው ውጪ እንደሚንቀሳቀሱ መረጃዎች መኖራቸውን ያነሳሉ። መረጃዎቹ ደግሞ እኛን ፕሬዚዳንቶችን ጨምሮ፣ከተከራካሪ ወገኖች ለዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የሚቀርቡ ሲሆን፣ ቅሬታዎቹ እከሌ የሚባለው ዳኛ ገለልተኛ ሆኖ አላስተናገደም፣ ይህ ደግሞ በመዝገቡ ላይ በዚህ አግባብ ይንጸባረቃል፣ከአንደኛው ተከራካሪ ወገን ጋር ተገቢ ያልሆነ ግንኙነት ዳኛው አለው የሚሉ ይገኙበታል ይላሉ።

አቶ ተስፋየ አያይዘውም፣ በዘንድሮ ዓመት እንኳ የፌደራል ፍርድ ቤቶችን በምሳሌነት ብናነሳ፣ ሁለት ዳኞች ከዳኝነት ሙያ እንዲሰናበቱ የተወሰነባቸው መሆኑን ያስራዳሉ። በሌላ መልኩ ከአምስትና ስድስት ያላነሱ ዳኞች ውሳኔ እስከሚሰጥ ከስራቸው እንደታገዱ፣ እስከ ስድስት ወር ድረስ ከደመወዛቸው የተቀጡ እና በየደረጃው ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ዳኞች ስለመኖራቸውም ይናገራሉ። እንደሳቸው አስተያየት ደግሞ፣ ይህ የሚያሳየው አሁንም ቢሆን የስነ ምግባር እሴትን ተላብሰው የማይሰሩ ዳኞች ስለመኖራቸው እና ችግር ያለባቸውን ዳኞች ደግሞ ተጠያቂ ለማድረግ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ነው።

በመሆኑም በፍትህ ስርዓቱ በተለይም፣ ፍ/ ቤቶች የራሳቸውን የጥናትና ምርምር ክፍል በአግባቡ በመምራት ወጥነት ያለው ስራ እንዲሰራ በማድረግ በፍትህ ስርዓቱ የሚስተዋለውን ችግር ለይቶ መፍትሄ መስጠት ይጠበቅባቸዋል። ስለሆነም ጥናቶችንና ምርምሮችን ከስህተት መማሪያ፣ ደካማ ጎንን ማሻሻያ፣ጠንካራ ጎንን ደግሞ የበለጠ ማጎልበቻ አጋዥ ሀይል አድርጎ ማሰብና ለተግባራዊነታቸው መትጋት ያስፈልጋል። በዚህም የዛሬ ሃያና ሰላሳ አመት በፍትህ ስርዓቱ ይስተዋል የነበረው የአሰራር ችግር ዛሬ ላይ እንዳይደገም በማድረግ የዳኝነት ስርዓቱን ከሰለጠነው ዘመን ጎን ማሰለፍን ይጠይቃል። በተለይም ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው እንደ ዩኒቨርስቲዎች እና የጠበቆች ማህበራት ከመሳሰሉ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ እና ተቀራርቦ መስራትም ያስፈልጋል።

አቶ ፊሊጶስ እንደሚያብራሩት የፍትህ ስርዓቱን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት፣ ጥናትን መሰረት ያደረጉ የህግ ማሻሻያዎችን ማከናወን ያስፈልጋል። በዳኝነት ስርዓቱ ዙሪያ የሚነሱ የህዝብ ሃሳቦችንም ትኩረታ መስጠትና መመለሰ የግድ ነው። በዘርፉ የሚሾሙና የሚመደቡ የስራ ኃላፊዎች ስራውን በአግባቡ የሚያውቁ፣ ችሎታ፣ዕውቀት እና ስነ ምግባር ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግም ተገቢ ነው። አይነኬ ተብሎ የሚታሰበውን የፍርድ ቤት ውሳኔ ህዝባዊ መሆኑን ተገንዝቦ ለሚዲያ ማብቃት እና ተጠያቂነትን ለማስፈን መስራት ይገባል። ዩኒቨርሲቲዎች፣የምርምር ተቋማት እና የጠበቆች ማህበር የፍርድ ቤት ውሳኔን ማገዝና ክፍተትን በማሳየት የፍትህ ስርዓቱ ከወረቀት በዘለለ በተግባር የሚገለጽበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል። ለዳኞች በህግ የተሰጣቸው የዳኝነት ነጻነት እንዳይሸራረፍ በሚመለከተው አካል በአግባቡ መጠበቅ አለበት። ዳኞች ደግሞ የዳኝነት ተግባር የሁለት ተቃራኒ ወገኖችን ጉዳይ ስለሚመለከት ስራው ለትችት የተጋለጠ ስለሆነ ለሙያቸው፣ ለህሊናቸው፣ ለአገራቸውና ለህዝባቸው ለመታመን ከራሳቸው ጋር መታረቅ ይኖርባቸዋል።

ዘመን መጽሔት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም

Recommended For You