ዓባይ በጥበብ ሥራዎች

ለውበቱና ለኃያልነቱ ብቻ ሳይሆን ዓባይ የተገጠመለት ለአገር ሊጠቅም የሚችል ውሃ፣ አፈር እና ማዕድን እንዲሁ ያለአገልግሎት ዝም ብሎ ይሄዳል በሚል በቁጭት የሚገጠሙ አሉ፤ በተለይ የቃል ግጥሞቹ ቁጭት ብቻ ሳይሆን ምኞትና ተስፋ ያለባቸው በቅጡ የተሰናዱና የተፈተጉ ናቸው፡፡

ዓባይና ጣና ተጣልተው በድንበር

ዓባይ አሸንፎ ሲጎማለል ነበር (ቃል ግጥም)

በዚህ የመዝናኛ ዓምዳችን በዓባይ ወንዝ ላይ የህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከመጣሉ በፊትና ከተጣለ በኋላ በዝርውና በዜማ የቀረቡ የጥበብ ሥራዎችን መነሻ በማድረግ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ምሁራን የሰጡትን አስተያየት እናቀርባለን።

ዶክተር ባይለየኝ ጣሰው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ መምህር ናቸው። ዓባይ ላይ በጽሑፍ ቀርበው ከምናገኛቸው ትርክቶች መካከል በዝርው የተነገረው ሚቶሎጂ አንዱ ነው ይላሉ። ሚቶሎጂ የሚለው ቃል በአማርኛ ጥርት ያለ ፍቺ ተሰጥቶት የሚገኝ ባይሆንም ሀተታ ታሪክ ወይም መለኮታዊ ታሪክ ማለት ይቻላል። በዋናነት ስለመለኮት፣ ስለፍጥረት ግላዊ አፈጣጠር የሚተርክ ነው። ማን ፈጠረው፣ እንዴት ተፈጠረ፣ ከዚያስ፣ ወዘተ. በሚል በአጠቃቀሙ፣ በፍልስፍናው እንዲሁም በትረካው ለየት ብሎ የሚቀርብ ታሪክ መያዙን ያስረዳሉ። ለምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው «ኦሪት ዘፍጥረት» አንዱ ሚቶሎጂ ሲሆን፤ ዓለም እንዴት እንደተፈጠረች የሚተርክል ነው። በቃል የነበረውን ሚቶሎጂ በጽሑፍ ካቀረቡልን መካከል የግሪኮች ጥንታዊ ሚቶሎጂ አንዱ ሲሆን በጣም የሚገርሙና የሚደንቁ ትርክቶች ቀርበውበታል። ከጥንት ጀምሮ ስለተከናወኑ ድርጊቶች ማወቅ ለሚፈልግ ይህን ተጽፎ የሚገኝ የጥንታዊ ግሪክ ሚቶሎጂ ማንበብ፣ ማጥናት እና መተንተን ተገቢ ነው ብለውም ያምናሉ። ዶክተር ባይለየኝ ሀተታ ታሪክ ወይም መለኮታዊ ታሪክ ብለው የገለጹት በሥነ-ቃል ክፍል ውስጥ ለሚገኙት አፈ ታሪክ ወይም ሀተታ ተፈጥሮ ለሚሉት ቅርበት አላቸው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነጽሑፍ መምህር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ‹‹የሥነጽሑፍ መሠረታውያን›› በሚለው መጽሐፋቸው አፈ ታሪክ ለሚለው ብያኔ ሲሰጡ ባለፈ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የሚነገር ሲሆን በአብዛኛው በአንድ በተወሰነ አካባቢ ከተፈፀመ እውነተኛ ታሪክ አንድ ገፅታ በመውሰድ ሥነቃላዊ ፈጠራ ተጨምሮበት የሚነገር ነው ብለውታል። ሀተታ ተፈጥሮ የሚለውን ደግሞ ሰዎች የሰውነታቸውን ምስጢር፣ በዓለም ለመኖር የቻሉበትን ምክንያት ለማወቅ ይሻሉ። አካባቢያቸውን በመመልከት የተፈጥሮ ልዩ ልዩ ገጽታዎችንና መልክዓ ምድራዊ ቅርፆችን አፈጣጠር ለመረዳት ይጓጓሉ። ከዚህም የተነሳ እንደየባህላቸውና እንደየእምነታቸው ለተፈጥሮ ትርጓሜ የሚሰጡበት ነው በማለት ያስቀምጣሉ።

ጥንታዊ የግሪክ ሚቶሎጂ የአማልክቶቻቸውን ህልውና እና ኃይል የሚያሳዩበት ነው። ዶክተር ባይለየኝ በጥንታዊ ግሪክ ሚቶሎጂ ስለዓባይ ተጽፎ ካነበቡት ውስጥ ከፌቦስ (የፀሐይ አምላክ) ታሪክ ጋር የተያያዘውን ከዚህ እንደሚከተለው ይተርኩልናል። ግሪኮች ፌቦስን የፀሐይ አምላክ አድርገው ይወስዱታል። ፀሐይን ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ በማምጣት ምሽት እንዲሆን የሚያደርገው እንዲሁም ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ በማዞር ንጋት እንዲሆን የሚያደርገው የፀሐይ አምላክ በሰረገላው እያዞረ ነው ብለው ያምናሉ።

ፌቦስ ኪለመን ከምትባል ኢትዮጵያዊ ልጅ ይወልዳል። ስሙም ፌጦ ይባላል። ፌጦ አባቱ ማን እንደሆነ እናቱ አልነገረችውም። አድጎ ከዕድሜ እኩዮቹ ዘንድ ሲጫወት አባቶቻቸው ያደረጉላቸውን ነገሮች ሲነግሩት እንዲሁም ጓደኞቹ ከአባታቸው ጋር ሲሄዱ ሲያይ ይቀና ነበር። በኋላ ላይም ስለአባቱ ምንም ስለማይናገር ፀብ ሲፈጥሩ አንተ አባትህን የማታውቅ ብለው ይሰድቡታል። በዚህ ምክንያት እናቱን ሄዶ አባቱ ማን እንደሆነ ይጠይቃል። እሷም አጥጋቢ ምላሽ ስላልሰጠችው ይናደዳል።

አባቱ ማን እንደሆነ ባለማወቁ ከዕድሜ እኩያ ጓደኞቹ እየራቀ፣ እየራቀ በጣም እየተሰማውና እያዘነ እንዲሁም እየተሰቃየ መጣ። እያደገ ሲሄድም በጣም ከማዘኑ የተነሳ ቀን የትም በመዋል ማታ እራት አልበላም በማለት ይተኛል። ቀን አኩርፎ ይወጣል፤ ማታ ተመልሶ መጥቶ ሲተኛ ይባንናል። በመጨረሻም አባቱ ማን እንደሆነ ካልነገረችው ከገደል ዘሎ፣ ወይም ባህር ውስጥ ገብቶ ለመሞት እንደወሰነ ይነግራታል። እናቱም ልጇ በሚሆነው ሁኔታ በጣም እየተሰማት ይመጣል፤ አባቱ የፀሐይ አምላክ ስለሆነ የሚነግራት ነገር ከሌለ በስተቀር ደፍራ መንገር አልሆነላትም ነበር። በጊዜ ሂደት ግን ሁኔታው ስላስጨነቃት አባትህ እስኪነግርህ ወይም ንገሪው እስከሚለኝ ድረስ እየጠበኩኝ ነው እንጂ አባትህ ኃያሉ አምላክ ፌቦስ ነው ትለዋለች። ፌጦ አባቱ ማን እንደሆነ ባወቀ ጊዜ በጣም ይደሰታል። ለጓደኞቹም አባቴ ፌቦስ ነው እናቴ ነግራኛለች ይላቸዋል። ጓደኞቹም አባትህ አምላክ ሊሆን አይችልም፤ እናትህ ስታታልልህ ነው ስላሉት መጠራጠር ይጀምራል። ስለሆነም እኔን ዝም ለማሰኘት አስበሽ ይሆናል አባትህ አምላክ ነው ያልሽኝ፤ አባቴን ጠይቄ ምላሽ ካላገኘሁ በስተቀር ራሴን አጠፋለሁ ብሎ እናቱን ያስቸግራታል። እሷም ሄዶ እንዲጠይቅ ትፈቅድለታለች። ፌጦ፣ ፌቦስ ፀሐይን በሰረገላው እያንቀሳቀሰ ሳለ ያገኘውና ሲጠይቀው አባቱ መሆኑን ይነግረዋል። አባትህ ነኝ ስላልከኝ ብቻ አባትነትህን አልቀበልም፤ አባቴ መሆንህን እንድቀበል ሰረገላውን ስጠኝና እኔ ላንቀሳቅስ ይለዋል። ፌቦስም ሰረገላውን መዘወር አይሆንልህም፤ ምክንያቱም ከሀዲዱ ዝቅ ካልክ መሬት ይቃጠላል፤ በመሬት ላይ ያሉ ነገሮች ሁሉ ይነዳሉ። ከፍ ካልክ ደግሞ ዓለም ሁሉ ጨለማ ይሆናል። ስለዚህ ሥርዓቱን ጠብቀህ መዘወር ስለማትችል ልሰጥህ እቸገራለሁ ይለዋል። «ልሰጥህ እቸገራለሁ» ስላለው አባቴ ባይሆን ነው በማለት ፌጦ በጣም ያለቅሳል፤ ሊጽናናም አልቻለም። ፌቦስ በመጨረሻ ሁኔታው ስላሳዘነው ከፍተኛ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል በማስጠንቀቅ ሰረገላውን የሚያንቀሳቅስበትን መመሪያ በመንገር ለልጁ እንዲዘውር ይፈቅድለታል።

ከፌቦስ ተቀብሎ ሰረገላው ላይ ወጥቶ መዘወር ሲጀምር እየተንቀጠቀጠ መስመሩን ጠብቆ ማንቀሳቀስ አቅቶት ዝቅ ማለት ሲጀምር መሬት መቃጠል፣ ወንዞች መትነን ይጀምራሉ። በዚህ ጊዜ ዓባይ ከሜድትራኒያን ወደ ኢትዮጵያ ተጠቀለለ። እየተጠቀለለ መጥቶ ኢትዮጵያ ሰከላ ላይ ሲደርስ አንገቱን ይደፋል። በዚህን ጊዜ እናት ምድር ኢትዮጵያ ሁለት እጆቿን ወደ ላይ ዘርግታ እባክህ የዓለም ፈጣሪ ዚዮስ ሆይ እግዚኦ ምህረትህን አምጣ ብላ ለመነች። ልመናዋም ተሰምቶ ፌቦስ ወደ ሰረገላው ገብቶ ትክክለኛው መስመር ላይ አስገብቶ ሲዘውር ዓባይ ወደ ኢትዮጵያ መጠቅለሉ ቀርቶ ወደ ሜድትራኒያን መፍሰስ ጀመረ። ፌጦም ወድቆ ሞተ።

ዶክተር ባይለየኝ ጣሰው እንደሚሉት ይህ የጥንታዊ ግሪክ ሚቶሎጂ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከስድስት እስከ ስምንት ሺህ ዓመት ገደማ ሲነገር የነበረ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› (መዝሙር፣67፣31) የሚለው ከዚህ ታሪክ የተወሰደ ነው ይላሉ። ግሪኮች ያን ጊዜ (ከክርስቶስ ልደት በፊት ብዙ ሺህ ዓመታት) ስለዓባይና ኢትዮጵያ ብዙ ነገር እንደሚያወቁ ስለዓባይም ከመነሻው ከከሰላ ጀምሮ እውቀቱ እንዳላቸው ታሪኩ እንደሚያሳይ ይናገራሉ። ተጽፎ በሚገኘው በግሪክ ሚቶሎጂ ዓባይን እንደ አገር ስለሚጠሩት የኢትዮጵያ ሁለተኛ ስሟ ነበር ማለት ይቻላል። የግሪክ አማልክቶች በጥንት ጊዜ ደስታና ጤና ለማግኘት ወደኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት መምጣታቸው በብዛት ተተርኳል። ወደኢትዮጵያ በመምጣት እረፍት በማድረግ የሚደሰቱባት፣ የዓባይን ውሃ ከምንጩ በመጠመቅ ከህመማቸው ፈውስ የሚያገኙበት መሆኑ ተመዝግቧል በማለት በጥንታዊ ግሪክ ሚቶሎጂ ስለዓባይ ከፍተኛ ቦታ ተሰጥቶት የሚገራርሙ ትርክቶችና ፍልስፍናዎች እንደሚገኙ ያስረዳሉ። እነዚህ ትርክቶችና ፍልስፍናዎች ቢጠኑ ስለዓባይ የሚነግሩን ብዙ ነገሮች እንደሚኖሩም ያስገነዝባሉ።

በግሪክ ስለአማልክቶቻቸው ሲነሳ ስለዓባይም እንደሚነሳ የሚናገሩት ዶክተር ባይለየኝ የግብጾች ጥንታዊ ሚቶሎጂን ስንመለከት ሁለነገራቸው ከዓባይ ጋር የተያያዘ ስለሆነ የሥልጣኔያቸው ምንጭም በመሆኑ ብዙ ነገር ብለውለታል ይላሉ።

የዓባይ ውሃ እንዲመጣ (ፍሰቱ እንዲቀጥል) በሚል በየዓመቱ የግብረ ስጋ ግንኙነት ያልጀመረች ታዳጊ ልጃገረድ ወይም ከሴት ጋር ግንኙነት ያልጀመረ ታዳጊ ወጣት ለወንዙ በመሰዋት የዕምነት ሥርዓት ያደርጋሉ፤ አሁንም ያ ሥርዓት ይከናወናል። ሚቶሎጂያቸው ይህን ከማሳየቱ በተጨማሪ የዓባይ መነሻ በግብጽ ድንበር አካባቢ ፈልቆ እንደሚገኝ ተርከዋል። በፈርኦኖቹም ጊዜም ሆነ አሁን ድረስ ወጣቶቹን ይህን ትርክት እየነገሩ መነሻው ግብጽ እንደሆነ እስከማስረዳት ድረስ እንደሚሄዱ በማንሳት ግብጾችም በዓባይ ላይ ብዙ ሚቶሎጂ እንዳላቸው ይናገራሉ።

በግሪክና በግብጽ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ የሆነ በዓባይ ላይ የሚነገር ጥንታዊ ሚቶሎጂ የነበረ ቢሆንም ከዚያ በኋላ የመጡ ጠንካራ፣ ጠንካራ ሃይማኖቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ስለገቡ ታሪኮቹ የበዓድ አምልኮ ትርክት ናቸው በሚል እንዳይነገሩ ስለተደረገ ጠፍተዋል። በሥነ ቃሉ ግን በተለይ በቃል ግጥም ስለውበቱ፣ ጥንካሬው እንዲሁም ኃያልነቱ ብዙ ተብሏል። አሁንም እየተባለ ነው። ሸለቆው ውበት ነው፤ በጣም ያስደምማል። ሲሞላ ግንዱን፣ ምኑን አግተልትሎ መሬቱን ሰንጥቆ በዚህና በዚያ ማዶ ያለ እንዳይደማመጥ አድርጎ ይዞ ሲሄድ ለሰው ልጅ የሚያሳየው ኃያልነቱ የሚገርም ነው። ተፈጥሮን ማድነቅ ደግሞ የሰው ልጅ አንዱ ባህሪ ስለሆነ ለመግጠምና ለማዜም ይነሳሳል በማለት በዓባይ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ግጥሞች መቅረባቸው የሚደንቅ እንዳልሆነ ይገልጻሉ።

ለውበቱና ለኃያልነቱ ብቻ ሳይሆን ዓባይ የተገጠመለት ለአገር ሊጠቅም የሚችል ውሃ፣ አፈር እና ማዕድን እንዲሁ ያለአገልግሎት ዝም ብሎ ይሄዳል በሚል በቁጭት የሚገጠሙ አሉ፤ በተለይ የቃል ግጥሞቹ ቁጭት ብቻ ሳይሆን ምኞትና ተስፋ ያለባቸው በቅጡ የተሰናዱና የተፈተጉ ናቸው። ዘመናዊ ትምህርት ከመጣ በኋላ ተጽፈው ከተገኙት ውስጥ የዓለም ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን እና የገጣሚና ባለቅኔ ኃይሉ ጎሞራው ግጥሞች ጥልቀት ያላቸው ናቸው በማለት ቁጭትን በተመለከተ የኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው) ተጠቃሽ እንደሆነ ዶክተር ባይለየኝ ያነሳሉ። የሚብሰከሰክ እና የሚታመስ ስሜቱ ምን ያህል እንደሆነ የምናይበት፣ እንዲሁም በሚገርም ሁኔታ ከስሜቱ ጋር አብረን ነጉደን እንድንጋራውየሚያደርግ ነው በማለት በአድናቆት ያነሱታል። በዘፈን የቀረበውን ደግሞ የእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ግጥም ልዩ መስህብ ያለው መሆኑን ይናገራሉ።

‹‹እናትክን!›› በሉልኝ

ይፈሳል ይሉኛል አባይ ዐይኑ ይፍሰስ

ያን ስንቱን ወገኔን የውሃ እጦት ሲያምስ

የድርቀት ጋንጩራ ሲበላ ስንቱን ነፍስ

ውሃ ውሃ እያለ ለጋው ሲቀነጠስ

ናይል ዓባያችን አለ ነበር ሲፈስ

ለፈፀመው ደባ ለሠራውም ግፉ

‹‹እናትክን!›› በሉልኝ በዚያ የምታልፉ

ገጣሚና ባለቅኔ ኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው)

ዓባይ

ዓባይ የምድር ዓለም ሲሳይ

የቅድመ ጠቢባን አዋይ

ዓባይ የጥቁር ዘር ብስራት

የኢትዮጵያ ደም የኩሽ እናት

የዓለም ስልጣኔ ምስማክ

ከጣና ስር እስከ ካርናክ

በጡትሽ እቅፍ እንዲላክ . . .

(የዓለም ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን)

ዓባይ

የማያረጅ ውበት የማያለቅ ቁንጅና

የማይደርቅ የማይነጥፍ ለዘመን የፀና

ከጥንት ከጽንሰ አዳም ገና ከፍጥረት

የፈሰሰ ውሃ ፈልቆ ከገነት. . .

እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)

ዶክተር ባይለየኝ ጣሰው የኢትዮጵያውያን የብዙ ሺህ ዓመታት ምኞትና ተስፋ እውን ሆኖ የተገለጸበት የግድቡ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን ዘመን ቀላል አድርጎ መመልከት እንደማይገባ አጽንኦት ሰጥተው ያሳስባሉ። በዓባይ ላይ የተገጠሙ አማርኛ ግጥሞች (በቃልም በጽሑፍም) ምን ይላሉ? የሚለውን ተመልክተው ጥናታዊ ጽሑፍ መሥራታቸውን አስታውሰው የግጥሞቹ ይዘት ማጠቃለያቸው ዓባይን ከየትኛውም አገር ጋር በእኩልነትና በመተሳሰብ እንጠቀም ማለታቸውን እንዳረጋገጡ ይጠቅሳሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት አቋምም ግጥሞቹ የሚሉትን ይዘት የሚያንጸባርቅ መሆኑንም ያወሳሉ።

በግብፆች በኩል ያለው ግን የዓባይን ውሃ ኢትዮጵያ በፍጹም እንዳትነካ በመፈለግ ተንኮል ሲፈጥሩ ነው የሚታየው። ለምሳሌ ስለግድቡ ብቻ ኢትዮጵያን የሚያጥላላ 3400 ጽሑፎች ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በግብጾች ተጽፈዋል። የሚያዋጣው ግን የተፋሰሱ አገራት በግድቡ ዙሪያ በመረዳዳት መንፈስ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣ በሀሳብ፣ ወዘተ. መተጋገዛቸው ነው። ግብፆች ከዚህ በፊትም ይሁን አሁን የሚያደርጉት የኢትዮጵያን የመልማት እንቅስቃሴ ማደነቃቀፍ ትተው ወደፊት ተባባሪ እንዲሆኑ ለማድረግ በአንድነት ተግቶ በመሥራትልማቱን የማናቋርጥ መሆናችንን ማሳየት ስንችል ነው በማለት ያስረዳሉ። ሁለቱ አገሮች በታሪክ የተሳሰሩ ናቸው፤ ይበልጥ ደግሞ በልማት ተሳስረው አዲስ ምዕራፍ እንደሚጀምሩም ሁኔታዎች ያመላክታሉ በማለት ተስፋ ያደርጋሉ።በጅማ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር አስናቀች ደምሴ በ2007 ዓ.ም. የፒኤችዲ ዲግሪያቸውን ሲሠሩ የማሟያ ጽሑፋቸው በዓባይ ላይ የተገጠሙ ግጥሞች ሀቲት (ዲስኮርስ) በመመርመር ማህበራዊ እሴቶችን ማሳየት ላይ ያተኮረ ነበር። እንደሳቸው ገለጻ በሰበሰቧቸው ግጥሞች ውስጥ ያለው ይዘት ስር ነቀል ለውጥ አምጥቷል ወይ? የሚለውን መርምረው በሂደት ለውጥ እንዳመጣ የጥናቱ ውጤት መደምደሚያ አመላክቷል። ግጥሞቹ በመጀመሪያ ዓባይ ላይ ምሬትና ስድብ ሲያቀርቡ ቆይተው፣ በሂደት ተቃውሞና ቁጭት ከዚያም ወደ አንድነትና መተባበር እንዲሁም ወደ ውሳኔ በመምጣት የድል ብስራት የሚያሳዩ መሆኑን በግጥሞቹ ሀቲት ታይቷል።

የመመረቂያ ጽሑፋቸውን በዓባይ ላይ በቀረቡ ግጥሞች ላይ አተኩረው እንዲሠሩ ያደረጋቸው በ1963 ዓ.ም. የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ የአማርኛ አስተማሪያቸው ታሪክ አጣቅሰው የነገሯቸው ግጥም መነሻ ሆኗቸው ነው። ይኸውም፣ የሱዳን እና የግብጽ ወታደሮች ባልታሰበ ሁኔታ በኢትዮጵያውያን ላይ ወረራ ባደረጉ ጊዜ ከጎጃምና ከጎንደር እናቶች ልጆቻቸውን ይዘው ዓባይን ተሻግረው ወደ ወሎ ሊሄዱ ሲሉ ብዙ ሕፃናት በዓባይ ወንዝ መሙላት ምክንያት ስላለቁባቸው ከዚህ የሚከተለውን ግጥም በሙሾ አቅርበው ነበር።

ታላቁ ወንዛችን ጀማችን ዓባይ

አንተም የኛን ጉዳት ትወዳለህ ወይ?

በዶክተር አስናቀች ጥናታዊ ጽሑፍ ውስጥ በዓባይ ላይ የተገጠሙ የዘፈን ግጥሞች ይዘት ሲታዩ የህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከመጣሉ በፊትም ሆነ ከተጣለ በኋላ ያሉት ሲመረመሩ በአስራ ሰባት ክፍሎች ተከፍለው ይገኛሉ። እነዚህም ውበት፣ ፍቅር፣ ማንነት መገለጫ፣ ቁጭት፣ ናፍቆት፣ ሞገደኛነት፣ ቅናት፣ በቀል፣ ፍርሃት፣ ሰላም፣ ውሳኔ (ቁርጠኝነት)፣ ጠንክሮ መሥራት፣ ህብረት፣ ምልጃ፣ መመኪያ፣ ብሩህ ተስፋ እና የድል ብስራት ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹን እንመልከት።

ቀድቼ አልጨርሰው ዓባይን በእንስራ

ምነው ውዬ ባድር ስላንተ ሳወራ (ፍቅር)

የግሸ ዓባይ ውሃ አይጠጣም ጉሹ

የታደሉትማ ካንቺ ጋር አመሹ (ቅናት)

የሰው ውሃ ብጠጣው አነቀኝ

ሀገሬ ጊዮን ዓባይ ተቀበለኝ (ናፍቆት)

እንዲህ ወደ ዓባይ የተወለዳችሁ

ምን ይሆን ምስጢሩ የመወደዳችሁ (ማንነት መገለጫ)

ዓባይ ስምነው እንጂ ምንሠርቷል ላገሩ

ትርፉ ለሌላ ነው ወስዶ መገበሩ (ቁጭት)

ዓባይ ቢሞላ ቢፈስ

እኔ አልመለስ (ቁርጠኝነት)

ዓባይን አትንኩ ሲሉን የነበሩ

ሁሉም ጊዜ እንዳለው እንግዲህ ይማሩ (ቁርጠኝነት)

ዓባይ ለሀገሩ ዓባይ ለወገኑ ጥቅም ላይ ከዋለ

አይደለም ገንዘቤ አይደለም ዕውቀቴን

አጥንቴም ተፈጭቶ ለሥራ በዋለ (ቁርጠኝነት)

ድንቹ፣ሽንኩርቱ በገፍ እንዲታረስ

ዓባይ አትሂድብን በሀገርህም ፍሰስ (ምልጃ)

ቢሆንም ይሆናል ባይሆን ምን አባቱ

ዓባይ ተገድቦ ይታያል ውጤቱ (ውሳኔ)

ለዓባይ ለግንባታው አንድ ድንጋይ ጥዬ

ሞቴ ኑሮዬ ነው ኧረ እናንተ ሆዬ (ውሳኔ)

ዓባይ ተፈተሸ ጊዜው ደረሰና

ጊዜ መስታወት ያሳየናል ገና (ውሳኔ)

እኔ አልበላልሽም የጓያ ጭብጦ

የግድቡ ሥፍራ እዚህ ተቀምጦ (መመኪያ)

ጎበዝ ያገሬ ልጅ አካፋህን አንሳ

ዓባይን አልምተህ ችግርን ድል ንሳ (ህብረት)

በአንድ በሬ ስቦ ጎተራ አይሞላ

ዓባይን ለማልማት እንስራ በጋራ (ህብረት)

ተረባርቦ እንጂ ነው ትውልድን መቀጠል

መቼ ለምቶ ያውቃል ሀገር በተናጠል (ህብረት/ጠንክሮ መሥራት)

እስቲ ዲያስፖራ ሰብሰብ በልና

ልክ እንደዓባይ ወደ ሀገር ግባ (ህብረት)

ዓባይ ሙላ ሙላ ለምን ትጎላለህ

ቤኒሻጉል ገብተህ ብርሃን ትሆናለህ

(ብሩህ ተስፋ)

ዓባይ ተገድቦ ሊውል ነው ለልማት

ሲሳይ ወዲህ ግባ ደህና ሁን ድህነት

(ብሩህ ተስፋ)

ዓባይ ተገድቦ አበባው አበበ ንቦች ገቡልሽ

እንግዲህ ጉብሌ ማር ትበያለሽ

(ብሩህ ተስፋ)

ቤልጅጉ ለምን ነው? ክላሹ ለምን ነው?

ዓባይ ተገድቦ መነሳት አሁን ነው

(የድል ብስራት)

ወንዝ ነፍስ አወቀ ወንዝ ሀገር መረጠ

ዓባይ በህዳሴ ታሪኩን ለወጠ

(የድል ብስራት)

እንደተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር አስናቀች ገለጻ በሰበሰቧቸው ግጥሞች ውስጥ የህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከመጣሉ በፊት ዓባይን ለልማት እናውል በሚል ቅስቀሳ እንደተደረገ ሁሉ ከህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለ በኋላ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፤ በግድቡ መጀመር ምክንያት ኢትዮጵያ የሚያጋጥማትን ጫና በህብረት ሰብሮ መውጣት ያስፈልጋል የሚሉ የሚያበረታቱ ግጥሞችም ተገጥመዋል። ቀደም ሲል ዓባይ ራሱ ውሃውን ገድቦ ለልማት ያውለው ይመስል ጥፋተኛ ተደርጎ በማቅረብ በግጥም ይወቀስ እንዳልነበረው፣ በኋላ ላይ እኛ ብንተባበር ለልማት ልናውለው እንችላለን የሚል ይዘት ያላቸው ግጥሞች በመግጠም ከሀገሪቱ መሪዎች ቀድሞ ተገኝቷል። ግጥሞቹ የሀገሪቱን አስተዳዳሪዎች ሕዝብ አብሮን አለ ብለው እንዲያስቡና እንዲጀግኑ በማድረግ በኩል የመሪነት ተግባር መፈፀማቸውን የጥናቱ ውጤት ያሳያል።

የዛሬ ስምንት ዓመት የድል ብስራት የሚያሰሙ ግጥሞችን በማየት የግድቡ መጠናቀቅ አይቀሬ መሆኑን ማየት ይቻላል። ለዚህም አብነት መጥቀስ ቢያስፈልግ ‹‹ወንዝ ነፍስ አወቀ ወንዝ ሀገር መረጠ፣ ዓባይ በህዳሴ ታሪኩን ለወጠ›› የሚለውን መመልከት ይቻላል። ግጥሞቹ ግድቡ መገደብ አለበት ብለው እንዳነሳሱት ሁሉ በቀጣይ ለግድቡ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ሕዝቡ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ ወዘተ. ማድረግ አለበት በማለት ከማነቃቃታቸው በላይ በሕይወት የሚከፈል መስዋዕትነት ካለም ለመክፈል ዝግጁነት እንዳለ ለመሪዎቹ ‹‹ቢሆንም ይሆናል ባይሆን ምን አባቱ፣ዓባይ ተገድቦ ይታያል ውጤቱ›› በማለት አሳይቷል። በከፍተኛ ደረጃ ለሚገኙ የአገሪቱ አስተዳዳሪዎች ብቻ ሳይሆን በየደረጃው ለሚገኙ ዝቅተኛ አስተዳዳሪዎች ሆነ ለሌላውም ኅብረተሰብ የተለያዩ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች በግጥሞቹ መተላለፋቸውን ዶክተሯ ያስረዳሉ።

ዓባይን በግጥም ከመውቀስ በመውጣት ወደ ልማት መግባት እንደሚያስፈልግ ሲገጠም ቆይቷል። በዚህም መሪዎቻችን ተበረታተው ወደ ተግባራዊ ሥራ ገብተዋል። ከዚህ በኋላ ይህ የመልማት ፍላጎት ቀጣይነት ያለው መሆኑን ህብረት ፈጥረን ለጠላቶቻችንም ሆነ ለወዳጆቻችን በተግባር በማሳየት ተባባሪያችን እንዲሆኑ ማድረግ ይጠበቅብናል የሚለው የዝግጅት ክፍላችን መልዕክት ነው።

ስሜነህ ደስታ

ዘመን መጽሔት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም

Recommended For You