ስብራቱን ለመጠገን…

“ትምህርት” የሰው ልጅን አስተሳስብ ወደተሻለ የሚቀይር፣ ባሕሪውን የሚያርቅ፣ የችግር መፍቻ ቁልፍ፤ ትውልድ ለራሱና ለሀገሩ እንዲበጅ አድርጎ መቅረጽ የሚያስችል መሣሪያም ነው። የተሻለ ትምህርት የተሻለ ትውልድን ይፈጥራል። የተሻለ ትውልድም ሀገሩን የተሻለች አድርጎ መሥራት ይቻለዋል። አዕምሯቸው በትምህርት የለማ፤ ዕይታቸው በዕውቀት የሰላ፣ ከራሳቸው አልፈው ለሀገራቸው ትላልቅ አስተዋፅዖን ያበረከቱ በርካቶች መኖራቸው እሙን ሆኖ ሳለ፣ በተለይ ካለፉት ጥቂት አስርተ ዓመታት ወዲህ ግን፣ የትውልዱ ነገሮችን የማመዛዘን አቅም፣ በተማረበት ሙያ ውጤታማ የመሆኑ ጉዳይ፣ በየፈተናው የሚመጡ ውጤቶች የትምህርት ሥርዓታችን ላይ ጥያቄ የሚያስነሱ ሆነዋል።

በነሐሴ ወር 2010ዓ.ም የወጣው የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ፣ በቅድመ መደበኛ፣ በመጀመሪያ ደረጃና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ፕሮግራሞች ላይ ያሉ ችግሮችን አመላክቷል። ከዓለም አቀፍ (ዩኔስኮ) መመዘኛና ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት አንጻር የአፈጻጸም እጅግ ዝቅተኛ መሆን፣ ፕሮግራሞቹ ፍትሐዊነትን ያረጋገጡ አለመሆናቸው፣ ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ በርካታ ሕጻናት መኖር፣ በክልሎች መካከል ያለው የአፈጻጸም ልዩነት እጅግ የከፋና ኢ-ፍትሐዊነቱ የሰፋ መሆኑ፣ የትምህርት ተሳትፎ እድገቱ በጣም አዝጋሚ መሆኑና ደረጃውን በጠበቀ ሥርዓተ ትምህርት፣ መምህራንና ተቋማት የተመራ አለመሆኑ ከተመላከቱ ችግሮች መካከል ይጠቀሳሉ።

በ2015 ዓ.ም ታኀሣሥ ወር የቀረበው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ረቂቅ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተደራሽነትን በማስፋት በኩል ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሶ፣ ነገር ግን አብዛኛዎቹ ተቋማት የሚፈለገውን ስታንዳርድ ያልጠበቁና ብዙ መሠረተ ልማት ያልተሟላላቸው መሆኑ በትምህርትና ሥልጠና ሥርዓቱ ጥራትና አግባብነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጿል። የትምህርት ጥራት እያሽቆለቀለ መምጣቱንም አንስቶ፣ ለዚህም በየደረጃው ያለው የአብዛኛው ተማሪ የትምህርት ውጤት በፖሊሲው ላይ የተቀመጠውን 50 ከመቶና ከዚህ በላይ ማምጣት አለመቻሉን በማስረጃነት አመላክቷል።

በትምህርት ሥርዓታችን ላይ ያለው ችግር ዘመናትን ያስቆጠረ እንደሆነ በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶ/ር አማኑኤል ኤሮሞ ይናገራሉ፣ እንደ እርሳቸው ሐሳብ፣ ባለፉት 30 ዓመታት የነበረው ትልቁ የትምህርት ዘርፉ ፈተና፣ የላቀ የትምህርት አገልግሎትን አለመስጠት ነው። የትምህርት ጥራት አንዱና ዋነኛው ማሳያ ደግሞ የተማሪዎች ውጤት እንደመሆኑ፣ ያለፉ ጊዜያትን ጨምሮ በቅርቡ የተመለከትነው የ12ተኛ ክፍል ውጤት የትምህርት አገልግሎታችን ምን ዓይነት ደረጃ ላይ እንዳለ፣ ራሳችንን እንድናይ አድርጎናል። እንደ እርሳቸው ዕይታ፣ ትምህርት ቤቶች የዕውቀት ማዕከል ሳይሆኑ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ያለባቸው መሆናቸው በትምህርት ሥርዓቱ ለተመለከትነው የውጤት መዋዠቅ አንዱ መንስዔ ሆኖ ይጠቀሳል። ይህ ችግር ያለፉት ሥርዓተ መንግሥታትን ጨምሮ አሁንም ድረስ የዘለቀ ሲሆን፣ ያለንን ሀገር በቀል እውቀት ከውጪው ዓለም ዕውቀት ጋር በሚገባ አጣጥሞ አለመጠቀም፣ ሙያዊ እውቀት ያላቸውና ትውልድን መቅረጽ የሚችሉ ምሑራኖቻችንን መጠቀም አለመቻላችን፣ የምሑራንና የትምህርት አመራሩ ከሀገርና ከትምህርት ሥርዓቱ እየሸሸ ዘርፉ የሰለጠነና ክህሎት ያለው ሰው እያጣ መሄዱ የዘርፉ ተደራራቢ ውድቀት መንስዔዎች ናቸው።

ባለፉት 30 ዓመታት በትምህርት ዘርፉ የሚደረገው ሩጫ ከትምህርት ጥራት ይልቅ የትምህርት ተደራሽነት ላይ ያተኮረ መሆኑም ሌላው የዘርፉ መሠረታዊ ችግር መሆኑን ዶ/ር አማኑኤል ጠቁመዋል። ይሄን ያህል ትምህርት ቤት ተከፍቷል፣ ይህን ያህል መምህራን ተቀጥረዋል ከማለት ውጪ፣ ትምህርት የዜጎች ጉዳይ እንደመሆኑና በተማሩበት መስክ ተቀጥረው የሚሠሩበትን እውቀት የሚጨብጡበት እንደመሆኑ መጠን የትምህርት ጥራት ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት አጀንዳ አለመደረጉንም ይናገራሉ።

የትምህርት ጉዳይን አጀንዳ የማድረግ ኃላፊነት የሀገር መሪዎች ነው ያሉት መምህሩ፣ ለዚህም አሜሪካና መሪዎቿን ማሳያ አድርገው ይጠቅሳሉ። የአሜሪካን 40ኛው ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገን እ.ኤ.አ በ1983 ለትምህርት ጥራት ትኩረት ሰጥተው “ሀገር በአደጋ ላይ ነው” የሚል ስሜት ያለው ፖሊሲ አውጥተው ትምህርትን ለመታደግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። 43ተኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽም “ማንም ተማሪ ወደኋላ አይቀርም” በሚል በትምህርት ላይ ጠንካራ ሥራ ሰርተዋል፣ 44ተኛው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም “ሁሉም ተማሪ ስኬታማ ይሆናል” በሚል አዋጅ፣ በከፍተኛ ሁኔታ ተንቀሳቅሰው በዓለም ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ችለዋል በማለት የአሜሪካን መሪዎች የሀገራቸውን ትምህርት ለመታደግ የወሰዱትን እርምጃ አስታውሰዋል።

በሀገራችንም፣ ቀደም ብሎ የነበረው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ከአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጋር ተጣጥሞ የትምህርት ሕግ ረቂቅ ተዘጋጅቷል። የሥርዓተ ትምህርቱ ዝግጅት ደግሞ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ ማዕከል አድርጓል። የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ራሳቸውን በማብቃት የዕውቀት ማዕከል እንዲሆኑ እየተሠራ ያለው ጅምር ሥራ፣ የ12ተኛ ክፍል ፈተና በገለልተኛ አካል እንዲሰጥ መደረጉና በአጠቃላይ በትምህርት ዘርፉ ያለውን ችግር ለመረዳት የተደረገው ጥረት ብሎም፣ በአጠቃላይ በትምህርት ዘርፉ እየታዩ ያሉ ለውጦች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ዶ/ር አማኑኤል አንስተዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚ ጉዳዮች ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ኤባ ሚጀና፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በትምህርት ሥርዓቱ በርካታ የለውጥ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ይገልጻሉ፤በተለይም፣ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የትምህርት ሥርዓታችን ማነቆዎች ምንድናቸው በሚል በተደረገ ጥናት፣ ከመምህራንና ከትምህርት አሰጣጥ ዘዴ፣ ከትምህርት አመራሩና ከአደረጃጀት ጋር የተያያዙ ችግሮች ተለይተው፣ መሠራት እና መስተካከል ያለባቸው ተብለው የተለዩ አጀንዳዎችን መነሻ በማድረግ የለውጥ ሥራዎች በመሠራት ላይ እንዳሉም ተናግረዋል። የትምህርት ሥርዓታችን መታመሙን ሁላችንም እንደ ዜጋ የምንረዳው ነው ያሉት ደግሞ፣ የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ብርሃነ መስቀል ጠና ናቸው። ዶክተሩ፣ባለፉት ዓመታት ሲተገበር የቆየው የትምህርት ሥርዓት ብዙ ተመራቂዎችን የሚያወጣ እንጂ ተማሪዎችን የሚለውጥ እንዳልነበረ ይናገራሉ። በየጊዜው በርካታ ኮሌጆች ቢከፈቱም፣ ሰኔ በመጣ ቁጥር ብዙ ተማሪ የሚፈበርኩ እንጂ፣ በተማሩበት መስክ ሀገርን የሚጠቅሙ፣ ብቁ ዜጋን የሚያፈሩ አልነበሩም ያሉት የኮሌጁ ፕሬዚዳንት፣ ለዚህም የትምህርት ሥርዓታችን የሚያወጣቸው ተማሪዎች የሚያመጡት ውጤት የወረደ መሆኑ ማሳያ እንደሆነ ያነሳሉ። እርሳቸው እንዳሉትም፣ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ባለፉት አምስትና አራት ዓመታት የትምህርት ሥርዓታችን ወዴት መጓዝ አለበት የሚል መነሻ ተይዞ ፍኖተ ካርታ ተነድፏል። የትምህርት ሥርዓቱንም ለመቀየር ተሞክሯል። ከዛም ባለፈ አማራጭ የትምህርት ቋንቋዎችም በትምህርት ፍኖተ ካርታው ተመላክተዋል። ይህም፣ ተማሪዎቻችን ልሳነ ክልዔ (Multilingual) እንዲሆኑና የበለጠ ለማወቅም ሆነ ያወቁትን ለሌላው ለማካፈል የበለጠ አቅም የሚፈጥርላቸው ይሆናል።

በሀገራችን የተለያዩ ዩኒቨርሲዎች መምህራንን ቢያስመርቁም፣ ተቋማቱ፣ ያስመረቅናቸው መምህራን ምን እየሠሩ ነው? ምን ብቃት ይጎድላቸዋል? የሚል ጥናት አይሠሩም ያሉት ዶ/ር አማኑኤል፣ የተቋማቱ ትኩረት ምን ያህሉ ተማሪዎቻችን የሥራ እድል አገኙ የሚለው እንጂ በተሠማሩበት የሥራ ዘርፍ ምን ያህል ውጤታማ ሆነዋል የሚለው አለመሆኑን ይገልጻሉ። ከዚህ በመነሳትም በቀጣይ አንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ያስመረቀው ተማሪ በሥራ ላይ የሚያመጣውን ውጤት የሚያጠናበት ሥርዓት ሊኖር ይገባል ብለዋል። አሁን ያሉ መምህራን የብቃት ችግር አለባቸው የሚል መረጃ ወጥቶ እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር አማኑኤል፣ መምህራን በየጊዜው አቅማቸውን እንዲያሳድጉ የሚደረግበት ሥርዓት አለመዘርጋቱ ሌላው በትምህርት ሥርዓታችን ትኩረት ያልተሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ጠቁመዋል። ትምህርት ቤት የሚማር ኅብረተሰብ ያለበት ተቋም እንደመሆኑ፣ በትምህርት ተቋም ውስጥ ያለው አካል፣ ተማሪው፣ መምህሩ የትምህርት ቤት አስተዳደሩ በሙሉ ተማሪ እንደሆነ ሊረዳ፣ እውቀትና ቴክኖሎጂ በየጊዜው እያደገ የሚሄድ በመሆኑም ራሱን ከጊዜው እውቀት ጋር ሊያሳድግ እንደሚገባው ምክራቸውን ለግሰዋል።

አቅም ለማሳደግ ጥረት ተደርጎ እያለ መምህሩ ለትምህርት ሥርዓቱ በቂ አይደለም ብሎ መደምደም ተገቢ እንዳልሆነ የሚናገሩት ዶ/ር አማኑኤል፣ ይልቁኑ የሌለው መምህሩን መጠቀም የሚችል አመራር ነው ይላሉ። አመራሩ ከመምህር የተሻለ፣ በክፍል ውስጥ ምን እየተከናወነ ነው የሚለውንም በቅርበት የሚከታተል፣ ሙያዊ እውቀት ያለው መሆን ሲገባው ሩጫው ለፖለቲካ ጉዳይ ብቻ መሆኑና በቦታው ላይ የሚመደበውም ለቦታው ተገቢ እውቀት ያለው ሆኖ ሳይሆን ፖለቲካዊ ሚናን እንዲጫወት ታስቦ መሆኑ የዘርፉ ፈተና እንደሆነ ያብራራሉ። ይህንኑ የእርሳቸውን ሐሳብ፣ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ረቂቅም “ከፌደራል እስከ ትምህርት ቤት ድረስ ያለው አብዛኛው በየደረጃው ያለው የትምህርት መዋቅር፣ አመራርና ባለሙያ ኃላፊነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው በመሆኑ የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓቱን በአግባቡ በመምራት ለተሻለ ውጤት ያበቃ አልነበረም፤ ለዚህም ሙያዊ አቅም ያላቸውን በውድድር አለመመደብ፣ ውጤታማነትና የሥልጠና ጥራት እያሽቆለቆለ እንዲመጣ አንዱ ምክንያት ሆኗል” በማለት ያጠናክረዋል።

“ትምህርት ቤቶችን በዕብነ በረድ አሳምረን ብንገነባ፣ ብዙ ወንበሮችን ብንገዛ፣ ግቢውን በሳርና በአበባ ብናስጌጠው መምህሩ ላይ ካልሠራን እነዚህ በሙሉ ለተሻለ ትምህርት ግብዓት እንጂ፣ ግብ ሊሆኑ አይችሉም” ያሉት ዶ/ር ብርሃነ መስቀል፣ መምህሩ ለትምህርት ሥርዓቱ መቃናት ሰፊ ድርሻ እንዳለው ያነሳሉ። “እኔ ጥሩ ጥሩ መምህራን ናቸው ያስተማሩኝ ስለዚህ ጥሩ አስተማሪ ነኝ ብዬ አስባለሁ” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ጥሩ መምህር ያስተማረው ሰው ጥሩ መሐንዲስ፣ ጥሩ ፓይለት፣ ጥሩ ሐኪም ይወጣዋል የሚል ሐሳብ አክለዋል። ከዚህ አንጻር መምህራኖቻችንን የሚያወጡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞቻችን ላይ ትልቅ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው ያሳስባሉ።

ፕሬዚዳንቱ እንደገለጹት ባለፉት ጊዜያት የመምህራን፣ የጤና፣ የግብርና፣ የአመራርና ሌሎችም የትምህርት ኮሌጆች ሲኖሩን፣ እነዚህ ኮሌጆች ውስጥ የሚያስተምረውን መምህር የሚያፈራ አንድም ዩኒቨርሲቲ ግን አልነበረንም። “የትምህርት ዩኒቨርሲቲ” መሠረታዊ የትምህርት ሙያ እውቀት እንዲኖር የሚያስችል ተቋም ነው። ዩኒቨርሲቲዎቻችን የተልዕኮ ልዩነት እንዲኖራቸው በተሠራው ሥራ ተቋማትን መልሶ በማደራጀት ሂደት ውስጥ ቀድሞ የመምህራን ኮሌጅ፣ ከዛም የመምህራን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ በኋላም ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ይጠራ የነበረውንና በ100ሺ የሚቆጠሩ መምህራንን አስተምሮ ለኢትዮጵያ ያበረከተው አንጋፋ ተቋም ከመስከረም 25 ቀን 2014ዓ.ም ጀምሮ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በሚል በአዋጅ በማቋቋም መልሶ የማደራጀት ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ዩኒቨርሲቲው የሀገራችንን የትምህርት ስብራት ማዕከል ያደረገ፣ ስብራቱን መጠገን የሚያስችል የውጪ ባለሙያዎችን ያሳተፈ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ፣ ከትምህርት ሚኒስቴርም ይሁንታን አግኝቶ ወደ ሥራ እንደገባ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ብርሐነ መስቀል ተናግረዋል። ሞዴል የሆኑ፣ ክልሎች ተሻምተው የሚቀበሏቸው መምህራንን እናፈራለን ብለን እየሠራን ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በቀጣይ ዩኒቨርሲቲው ከሚያወጣቸው አዲስ መምህራን በተጨማሪ በአሁን ሰዓት በማስተማር ላይ ለሚገኙ የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ጨምሮ፣ ከ800 ሺ በላይ ለሚሆኑ መምህራንም በየጊዜው የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን የመስጠት እቅድም ይዟል። ለትምህርት ዘርፍ መቃናት በጋራ ሆነን ካልተሰለፍን በውስን አካላት ጥረት ብቻ ለውጥ ማምጣት አይቻልም ያሉት ዶ/ር ብርሐነ መስቀል፣ በዘርፉ ትልቅ ኃላፊነት ለተጣለበት የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲው መጠናከርና ለመሠረተ ልማት መሟላት ከገንዘብ ሚኒስቴር ጀምሮ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፋቸውን እንዲያደርጉና ለትምህርቱ ዘርፍ የሚመጡ ድጋፎች ለትክክለኛው ዓላማ እንዲውሉ

ከትምህርት ሚኒስቴር በኩል አስፈላጊው ክትትል እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎቻችን ፕሮግራሞቻቸው ከአንድ ዩኒቨርሲቲ የተቀዳና ተመሳሳይ መሆኑ፣ አንዱ የከፍተኛ ትምህርት ችግር መሆኑ ተመላክቶ ዩኒቨርሲቲዎቻችን እንዴት መደራጀት አለባቸው በሚለው ላይ ጥናት መደረጉን ዶ/ር ኤባ ይናገራሉ። እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፣ ተቋማቱ ያላቸውን ውስጣዊ አቅም፣ የሰው ኃይል፣ የአካባቢያቸውን ፀጋ ወይም ልዩ አቅም መነሻ በማድረግ በተልዕኳቸው በአምስት ዘርፍ እንዲለዩ ተደርገዋል። በዚህም ዩኒቨርሲቲዎቻችን የምርምር ዩኒቨርሲቲ፣ የአፕላይድ ሳይንስ፣ አጠቃላይ ዩኒቨርሲቲ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲና የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በሚል ተለይተው በአዲስ መልክ የማደራጀቱ ሥራ በሂደት ላይ ይገኛል።

ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኳቸውን ከግብ ከማድረስ አኳያ ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፣ የዚህን ሀገር የትምህርት ሥርዓት ለማስተካከል ከሁሉም በላይ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ትልቅ ኃላፊነት እንደተሰጠው ያስረዳሉ። የትምህርት ሥርዓታችን እንዲቀየር ካስፈለገ ዩኒቨርሲቲው ብቁ መምህራንን በመገንባት፣ የሚገነባበትን ሥርዓትም በማበጀት፣ ብቁ የትምህርት አመራሮችን በማሰልጠን ረገድ ኃላፊነቱ ልዩ እንደሆነ ተረድቶ መሥራት፣ ብቁ የሆነ የትምህርት ሥርዓት እንዲዘረጋ በማድረግም እንደ ሀገር ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ተረድቶ መንቀሳቀስ ይኖርበታል የሚሉት ዶ/ር ኤባ፣ ተቋሙ በሀገራችን የትምህርት ሥርዓት ላይ አሻራ የሚያሳርፉ መምህራንን ያፈራል የሚል ትልቅ ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውጤታማ ተማሪዎችን ለማፍራት የትኞቹን የቤት ሥራዎች ሊሠሩ እንደሚገባቸው ከላይ የጠቆሙት፣ ዶ/ር አማኑኤል፣ በቅርቡ የተመዘገበውን የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት አንስተው ችግሩ የሚጀምረው ከቅድመ መደበኛ ትምህርት እንደሆነ ይጠቁማሉ። አንድ ልጅ በቅድመ መደበኛ መያዝ ያለበትን እውቀት ሳይዝ ቀጥታ ወደ አንደኛ ክፍል እንዲገባ ማድረግ፣ መሠረት የሌለው ፈጥኖ ፈራሽ ቤት እንደ መገንባት ይቆጠራል ያሉት ዶ/ር አማኑኤል፣ በቅድመ መደበኛ ትምህርት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ አለመሠራቱና ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች መያዝ የሚገባቸውን እውቀት ሳይጨብጡ በዝቅተኛ ውጤት ከክፍል ወደ ክፍል እያለፉ መምጣታቸው፣ እስከ ስምንተኛ ክፍል ውጤታቸውን ከግማሽ ነጥብ በታች እያመጡ ያለፉ መሆናቸው በ12ተኛ ክፍል ፈተና ላይ ለተመለከትነው የወረደ ውጤት ምክንያት እንደሆነ ያብራራሉ። የመምህሩ አቅም፣ ለተማሪዎቹ የሚያደርገው ክትትል፣ ተማሪዎችም ለትምህርት ጥራት ያላቸው ግንዛቤ፣ ትምህርት የመቀበል ዝግጁነታቸው፣ ወላጆችም ኃላፊነታቸውን አውቀው ከራሳቸው ኑሮ ባለፈ የልጄ ጉዳይ ያገባኛል ብለው ክትትል አለማድረጋቸው፣ በየትምህርት ቤቱ የሚታየው ግጭትና የሀገር ሰላም ማጣት፣ የአመራሩም በቁርጠኝነት በክፍል ውስጥ ምን እየተሰጠ ነው የሚለውን የሚመለከት አለመሆኑም ተደማምሮ የተመከትነው ውጤት እንዲመጣ ሆኗልም ብለዋል።

በትምህርት ተቋማት የመማሪያ መጽሐፍት ለተማሪዎች አለመድረስም ሌላው የትምህርት ሥርዓቱ አሳዛኝ ፈተና ነው ያሉት ዶ/ር አማኑኤል፣ የመማሪያ መጽሐፍት በሌሉበት ሁኔታ ተማሪና መምህሩ ምን እየሠሩ ነው የሚለውን ለመከታተል፤ መምህሩም ለተማሪው የሚያስፈልገውን ትምህርት ለመስጠት አስቸጋሪ ነው በማለት የትምህርት ሥርዓቱ ያሉበትን ዘርፈ ብዙ ተጨባጭ ችግሮች ይዘረዝራሉ።

በ12ተኛ ክፍል ፈተና የመጣውን ውጤት ለመቀልበስ፣ ለትምህርት ውጤታማነት 35 ከመቶ ድርሻ ያለው መምህሩና ለውጤቱ 40 ከመቶ ድርሻ ያለው ተማሪው ከወላጅና ከሌላው የትምህርት አመራር ጋር በቅንጅት ሊሠሩና ለቀጣይ ፈተና የቀራቸውን ጊዜ በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ይመክራሉ። እርሳቸው እንዳሉት፣ መምህሩ በትምህርት አቀባበል ላይ ድክመት ያለበትንና ጎበዙን ተማሪ ለይቶ እያንዳንዱን ማገዝ ይኖርበታል። ይህን ማድረግ ይቻለው ዘንድም መምህሩ የያዘው ክፍለ ጊዜ መቀነስ አለበት። ወላጆችም የልጆቻቸውን ክፍተት በየእለቱ እየለዩ ከልጆቻቸው መምህራኖች ጋር መሥራት አለባቸው። የትምህርት ተቋማትም ሰላማቸው የተጠበቀ መሆን አለበት። አመራሩም ሙሉ ጊዜውን ለትምህርት ተቋማት መስጠት ይኖርበታል። ተማሪዎች ምን ተምረዋል፣ ምን ይዘዋል፣ ምንስ ይቀራቸዋል የሚለውን በሚገባ ለይቶ በመሥራት ያሳለፍነውን የ12ተኛ ክፍል አሳፋሪ ውጤት እንዳይደገም ሁሉም በቁጭት ሊሠራ ይገባል።

በ12ተኛ ክፍል ፈተና ለተመዘገበው አስደንጋጭና አሳፋሪ ውጤት፣ የተማሪ ወላጆች፣ ተማሪዎቹ፣ መምህሩ፤ በአጠቃላይ በየደረጃው ያለው የትምህርት አመራር ኃላፊነቱን መውሰድ አለባቸው ያሉት ዶ/ር ኤባ፣ በሚቀጥለው ፈተና ወላጆች ልጄ የ12ተኛ ክፍል ፈተና ለመፈተን ብቁ ነወይ ብለው መጠየቅ መቻል አለባቸው በማለት ይመክራሉ። ልጆቻቸው የሚማሩባቸውን ትምህርት ቤቶች ወጥረው መያዝ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል። እርሳቸው እንደተናገሩት፣ አንድ ተማሪ ትምህርት ቤት ውሎ ምንም እውቀት ሳይጨብጥ የሚመለስ ከሆነ፣ ጊዜና የመንግሥትን ገንዘብ ከማባከን ውጪ ፋይዳ አይኖረውም። ስለሆነም፣ መምህራኑም፣ ተማሪዎቻቸው የእነርሱ ውጤት ናቸውና እነርሱ በሚያስተምሩበት የትምህርት መስክ ተማሪዎቻቸው ሲወድቁ ራሳቸው እንደወደቁ ሊሰማቸው እና ሊቆጫቸው ይገባል፤ “እኔ በማስተምረው ትምህርት ተማሪ መውደቅ የለበትም” ብለው በቁርጠኝነት መሥራት አለባቸው። የትምህርት ቤት አመራሩም ትምህርት ቤቱን እየመራሁ ነወይ ብሎ ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል። በተለይም አንድም ተማሪ ያላሳለፉ ወደ 1900 ገደማ ትምህርት ቤቶች ውድቀታቸውን ፈጽሞ በቸልታ ሊያዩት እንደማይገባና በሚቀጥለው ራሳቸውን ለማስተካከል ትልቅ ሥራ እንደሚጠበቅባቸው አስምረውበታል፣ “ከየትምህርት ቤቶቹ አንደኛ ወጡ ተብለው ዋንጫ ሲሸለሙ የነበሩ ተማሪዎች፣ ስንሰጣቸው የነበረው ዋንጫ የውሸት፤ ውጤቱም የውሸት ነበር ማለት ነው” ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፣ ትምህርት ቤቶቹ የታየውን የወረደ ውጤት በሚቀጥለው ፈተና ሊደግሙ እንደማይገባም አሳስበዋል።

ከመምህራን ጋር በተያያዘ፣ መምህራን ለተማሪዎቻቸው መስጠት ያለባቸውን እውቀት እንዲያካፍሉና መልካም ዜጋን ማፍራት እንዲችሉ አቅማቸውን የማሳደግ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ኅብረተሰቡ ለመምህሩ የሚሰጠው ቦታ ምን አይነት ነው የሚለውን በሚገባ ማየት፣ መንግሥት ለመምህሩ የሚሰጠው ግምት ምን ዓይነት ነው፣ መምህሩ ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች አንጻር የሚያገኘው ገቢ ምን ይመስላል የሚሉትን በሚገባ ማየት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ዶ/ር አማኑኤል፣ መምህሩ ከኢኮኖሚ አቅሙ የተነሳ በሥራውና በገቢው የረካ አለመሆኑን፣ ሙያውን እየተወ ወደሌሎች ሙያዎች እየተሸጋገረ እንዳለ አንስተው፣ የመምህሩ ጉዳይ ሊታይ፣ ከመንግሥት፣ በየደረጃው ካለ አመራርና ከወላጅ ተገቢው ክብር ሊሰጠው እንደሚገባ ይመክራሉ።

መምህራንን ለማብቃት የሚሠሩ ሥራዎች እየተጠናከሩ እንደሚሄዱ የገለጹት ዶ/ር ብርሐነ መስቀል፣ ለመምህርነት ሙያ ያለው አተያይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መምጣቱ ለትምህርት ሥርዓቱ አንዱ ፈተና እንደሆነ አንስተው፣ መንግሥት ለሙያው ያለውን አተያይ የሚቀይር ሥራ ይሠራል የሚል ተስፋቸውን ገልጸዋል። ወላጅም መምህር የልጆቼ አባት ነው ብሎ ማክበር እንደሚገባው አሳስበው፤ “የእውቀት አባት ለሆነው መምህር የሚገባውን ክብር ከሰጠንና መምህርነት ወደቀደመው ክብሩ እንዲመለስ ካደረግን ሂሳብ የምናወራርደው እንደ ዜጋ፣ እንደ ሀገርም ነው፤ ውድቀታችን የሚጀምረው ግን የልጆቻችን አባት የሆነውን መምህር በናቅን ጊዜ ነው” በማለት አጽንዖት ሰጥተው አስገንዝበዋል።

በመጨረሻም፣ ዶ/ር ኤባ ተማሪው፣ አስተማሪው፣ ወላጅና አመራሩ ተባብሮ መሥራት ከቻለ በትምህርት ሥርዓታችን ላይ ከተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች ጋር ተዳምሮ የትምህርት ሥርዓቱ የሚቃናበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም በማለት ተስፋቸውን ገልጸዋል።

እኛም፣ እንደ ሀገር ትኩረት ልንሰጠው የሚገባውን የትምህርት ሥርዓት ከገባበት ማጥ የማውጣት ኃላፊነት የሁላችን ነውና፤ በያለንበት የየድርሻችንን እንወጣ በማለት ጽሑፋችንን ቋጨን !

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

ዘመን መጽሔት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም

Recommended For You