የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቷልን?

የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት በአገሪቱ ውስጥ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በህገ መንግሥቱ መሰረት በትክክል መስተናገድ እንደሚችሉ የሚገልጽ አጠቃላይ የሕግ ድንጋጌ ነው። ምንነቱን ስናነሳ ደግሞ የአማራጭ ሃይል ሥርዓት የሚስተናገድበት የፓርቲ አደረጃጀትና አሰራር ማለት ነው። በዚህም በአገሪቱ ውስጥ አማራጭ ፕሮግራም እና የፖለቲካ ሥርዓት የሚያቀርቡ የአማራጭ ሃይሎች መኖርን ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ነጻ የሆነ የመድብለ ፓርቲ አደረጃጀትና አሰራር እንዲኖር ይፈቅዳል። በኢህአዴግ ሥርዓት ወቅት ግን ሕግ መንግሥቱ ከሚያስቀምጠው ሕግ ውጪ አንድ ፓርቲ /ገዢው ፓርቲ/ ብቻ የበላይ የሆነበት ጊዜ ነበር። የመንግሥት ምስረታውም ቢሆን፣ የኢህአዴግ ፓርቲ ብቻ በሶስት ተከታታይ ምርጫዎች የበላይ ሆኖ ነበር አገሪቱን ያስተዳደረው። በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ የሚለውና በተግባር ይከናወን የነበረው የተጣጣሙበት ጊዜ አልነበረም።

ሕገመንግሥቱ የሚፈቅደው የመድብለ ፓርቲ አደረጃጀት ደግሞ የፓርቲዎችን በስም መኖር ብቻ አይደለም። በትክክል በተግባር የሚታይ / functional/ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲኖር እንጂ። ይህ ማለትም፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይኖራሉ፣ የመወዳደሪያ ሜዳውም ለሁሉም እኩል ክፍት ይሆናል። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሁሉም ሃሳባቸውን እኩል ለሕዝብ አቅርበው ወደ ሥልጣን እንዲመጡ፣ በሂደቱም አማራጭ ሃሳቦች እንደሚታዩ ነበር የሚታሰበው። ይሁን እንጂ፣ ሕገ መንግሥቱ የሚፈቅደው አሰራር በተግባር ሲፈጸም ስላልነበረ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት በስሙ እንጂ በተግባር አልነበረም። ይህን ሃሳብ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሶሻል ሳይንስና ሂዩማኒቲ ኮሌጅ የፌዴራሊዝምና መንግሥት አስተዳደር መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ያሲን ሁሴን ይጋሩታል። እንደሳቸው ሃሳብ፣ በኢህአዴግ መንግሥት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሰረት የተጠናከሩ አልነበሩም። በመሆኑም በጠንካራ ጎን የሚነሳ፣ ከዚህ ግባ ሊባል የሚችል አደረጃጀትና ተሳትፎ አልነበራቸውም። በአጠቃላይ አንድ የበላይ ፓርቲ/one dominant party/ ኢህአዴግ ብቻ ተዋናይ የነበረበት ወቅት ነበር። የኢዜማ ፓርቲ ብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉም፣ ከ “ለውጡ” በፊት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠው የመድበለ ፓርቲ አደረጃጀት፣ አሰራርና አተገባበር ከወረቀት የዘለለ አልነበረውም ይላሉ።

ሁኔታውን ሲያስረዱም፣ ሕገ መንግሥቱ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፍልስፍና ተቀይሮ ፓርቲው በሚሰጠው አቅጣጫ ይመራ ነበር። የፍልስፍናው ይዘት ደግሞ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለመንቀሳቀስ እግር እስኪያወጡ ድረስ መጠበቅ፣ እግር አውጥተው መንቀሳቀስ ሲጀምሩ ደግሞ እንዳይራመዱ እግራቸውን መቁረጥ የሚል እንደነበር ያወሳሉ። ተፎካካሪ ፓርቲዎች አሉ ለማስባልም እንዲደራጁ ከመንግሥት ክፍያ ይፈጸምላቸው የነበሩት ቀላል የሚባሉ አልነበሩም።

በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተፈልፍለው እንደነበር መረጃዎች የሚያመላክቱ መሆኑን ያነሳሉ። በተለይም ኢህአዴግ ለምርጫ ማስፈጸሚያ የሚውል ከምርጫ ቦርድ የሚቀበለውን ገንዘብ ለሚላላኩት ፓርቲዎች ራሱ ምርጫ ቦርድ እንዲያከፋፍልለት ያደርግ ነበር። በተቃራኒው አማራጭ የፓርቲነት ቁመና መያዝን የመረጡ ጥቂት ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ደግሞ መንግሥት ከምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር አፈና ሁሉ ያካሂድባቸው ነበር። በመሆኑም ከ“ለውጡ” በፊት ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሰረት የመድበለ ፓርቲ አሰራርና አደረጃጀት በአግባቡ ተግባራዊ አልተደረገም ብለዋል።

በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ የመድብለ ፓርቲ አደረጃጀትና አሰራር ሲታይ አጠቃላይ ዝርዝር የሆነው ድንጋጌ በምርጫ ሕጉ በወረቀት ደረጃ ሰፍሯል። በፓርቲዎቹ ፕሮግራም ውስጥም ጽንሰ ሃሳቡ ይንሸራሸራል። ወደ ተግባራዊነቱ ሲመጣ ግን መሬት ወርዶ የሚታይ፣ በጎላ መልኩ የሚገለጽ ነገር የለም የሚሉት የተፎካካሪ ፓርቲዎች ምክር ቤት ጸሃፊ እና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ራሄል ባፌ ናቸው። እንደ ዶክተሯ ማብራሪያ፣ በተቀመጠው የሕግ አግባብ መሰረት ለፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል የሆነ የፖለቲካ ምህዳር አልተፈጠረላቸውም። ተአማኒነትን እና አካታችነትን የሚያረጋግጡ አሰራሮችም አልሰፈኑም። በመሆኑም በሕዝብ ደረጃ ተአማኒነቱ የተረጋገጠ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ነጻ የሆነ ምርጫ አልታየም። ስለዚህ የመድብለ ፓርቲ አደረጃጀትና አሰራር ተግባራዊነቱ ሲታይ በጣም ገና ነው።

ከለውጡ በኋላ ያለውን የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሁኔታ ደግሞ አቶ ግርማ ሲያስረዱ፣ እውነቱን ለመናገር ቀደም ሲል እንደነበረው ክፍያ የሚፈፀምላቸው ፓርቲዎች አሉ ለማለት አያስደፍርም። ይህም በመሆኑ አሁን ያሉት የፓርቲዎች ቁጥር ከመንዛዛት በመውጣት በመጠኑም ቢሆን እየቀነሱ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን በተገቢው መንገድ የፓርቲዎች ቁጥር ቀንሷል ማለት ከሚቻልበት ደረጃ ላይ ገና አልደረሰም። ምርጫ በሚካሄድበት ጊዜም ቢሆን የመድብለ ፓርቲ ምህዳሩን ለማስፋት ሲባል ከአሰራሩ ወጣ በማድረግ ልዩነቱን ለማቻቻል የሚደረገው ጥረትም በተወሰነ መልኩም ቢሆን ተቀባይነት ያገኘ አሰራር ነው ይላሉ።

ዶ/ር ያሲን ደግሞ ለውጡን ለውጥ እንዲሆን ካስቻለው ሁኔታ አንዱ የለውጥ እንቅስቃሴው ከራሱ ከገዢው ፓርቲ ውስጥ ተፈጥሮ የወጣ አዲስ አስተሳሰብ በመሆኑ እንደሆነ ያሰምሩበታል። እንደ ዶክተሩ አገላለጽ፣ አገራችን ያለችበት ሁኔታ ሲታይ በአዲስ የፓርቲ አደረጃጀትና አሰራር ላይ ነው። አሁን ላይ በተግባር እየተከናወነ የሚገኘው የፓርቲ አደረጃጀትና አሰራርም ቀደም ሲል ከነበረው በተለየ ሁኔታ የአዲስ ፓርቲ መወለድን ማሳያ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። በተፎካካሪ ወገን ያሉ ፓርቲዎች ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ጥፋተኝነት የተፈረጁ ፓርቲዎች እና በትጥቅ ትግል አገርን ሲወጉ የነበሩ ፓርቲዎች ጭምር የተካተቱበት ነው። ፓርቲዎቹ ከጦርነት ይልቅ ሃሳባችንን በሠላማዊ ትግል እንሸጣለን ብለው ወደ ሀገር የገቡበት ሁኔታ ነው የተከሰተው። በምሳሌነት ኢዜማ/ግንቦት 7/ እና ኦነግን መጥቀስ ይቻላል። በዚህም የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳው ትንሽ ሰፋ ያለበት፣ በፓርላማ ውስጥም በጣም የተለያዩ የምንላቸው ሃሳቦች / Idea pluralism/ መሰማት የጀመሩበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።

እንደ ዶክተሩ ማብራሪያ፣ ለውጡ ቀደም ሲል ከነበረው የመድብለ ፓርቲ አደረጃጀትና አሰራር ጋር ሲነጻጸር በጣም ብዙ ሊነሱ የሚችሉ ልዩነቶች አሉት። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች “የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተሳተፉ አይደለም። በበቂ ሁኔታም ፓርላማ ውስጥ አልገቡም” ይላሉ። ይህ ሃሳብ የሚነሳው ግን የሃሳብ ብዙሃነትን የሚፈቅድ የፖለቲካ ሥርዓት ለምርጫ ያለውን አስተዋጽኦ ካለመረዳት ነው። ስለሆነም አሁን ላይ መነሳት የሚገባው ጉዳይ ምን ዓይነት የፖለቲካ ሃሳቦች ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ የሚለው ነው። እነዚህ ሃሳቦች ደግሞ በየትኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች መወከላቸውን ማየት ያስፈልጋል። መንግሥት ደግሞ እነዚህ ሃሳቦች በአግባቡ እንዲንሸራሸሩ፣ ፓርቲዎች ይህን ሃሳባቸውን ያለ ችግር ለሕዝብ እንዲሸጡ፣ በሰላማዊ መንገድ አባሎቻቸውን እንዲመለምሉ እና የፖለቲካ ስራ እንዲሰሩ ፈቅዷል ወይስ አልፈቀደም የሚለውን ማጤንም ይገባል። በመሆኑም፣ ይህ የተለየና አዲስ የመድብለ ፓርቲ አሰራር በትክክል ከተሰራበት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያሸጋግር የሚችል ነው።

የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት ደግሞ የረጅም ጊዜ ልምምድን፣ ጠንካራ የሆነ ገዥ እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ይፈልጋል። ከዚህ አንጻር የእኛ አገር የፖለቲካ ሁኔታ ሲታይ ልምዱ በጣም አነስተኛ ነው። ታሪካችንን ብንመለከት እንኳ በደርግም ሆነ በኢህአዴግ መንግሥት በየሥርዓቶቹ አንድ፣ አንድ የበላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ነው የነበሩበት ። ዶ/ር ራሄልም፣ ከለውጡ በኋላ የመድብለ ፓርቲ አደረጃጀትና አሰራርን በተመለከተ በዋናነት ከ2010ዓ.ም በኋላ ከአገር ውጪ የነበሩና የትጥቅ ትግልን አማራጭ አድርገው በጫካ ሲታገሉ የነበሩ ታጣቂ ቡድኖች አገር ውስጥ መግባታቸውን አልካዱም። በዚህ ረገድ ከለውጡ በኋላ ጥሩ ጅምር መታየቱንም ያምናሉ። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሀገር ውስጥ በመግባታቸው ብቻ ፍትህ አግኝተው መንቀሳቀስ ችለዋል ማለት ግን አይደለም ይላሉ። እንደ ዶክተሯ ገለጻ፣ የአገራችን የፖለቲካ ምህዳር የተለወጠ እና ከነበረው የተሻለ ቢሆን ኖሮ አሁንም ወደ ጫካ የሚገቡ የፖለቲካ ቡድኖች አይኖሩም ነበር። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ታርቀናል ብለው ገብተው ተመልሰው ወደ በርሃ የወጡ ቡድኖች አሉ። ኦነግ ሸኔንና ሕወሃትንም ጭምር በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል። ይህ የሚያሳየው፣ አሁንም ቢሆን በፖለቲካ ምህዳሩ ዙሪያ ገና ያልተፈታ ነገር መኖሩን መሆኑን ይናገራሉ።

የአቶ ግርማ ሃሳብ ደግሞ፣ በለውጡ ገዢው መንግሥት ከምርጫው በፊት ጀምሮ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን የማሳተፍ ፍላጎት አሳይቷል የሚል ነው። ከምርጫ በኋላም ቢሆን የምርጫውን ያልተጠበቀ ውጤት ተከትሎ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ በመሥራት አገርን ማረጋጋት ይቻላል የሚል እምነት ማሳደሩን ይናገራሉ። በተግባር እየታየ ያለውም የመንግሥት የስራ ኃላፊነት ቦታዎችን ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ለማከፋፈል ጥረት መደረጉ ሌላው ማሳያ መሆኑን ያነሳሉ። ይህም ሁኔታ ወደፊት የጋራ መንግሥት የመመስረት ሁኔታ ቢመጣ በፓርቲዎች መካከል መፈራራት እንዳይኖር የሚያግዝ ስለመሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መገለጹን ያስረዳሉ።

በለውጡ ሂደት የተፎካካሪ ፓርቲዎች መኖር ለተሻለ ፖሊሲና ፕሮግራም ግብዓት ማግኘት ማለት ነው የሚሉት ዶ/ር ራሄል፣ ከዚህ አንጻር ቢያንስ በጋራ መነጋገር፣ መወያየት እና ሃሳቦችን የማንሸራሸር ሁኔታ ሙከራና ጥረት ይታያል ይላሉ። በአንዳንድ ዋና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያም ስምምነት ላይ የሚደረስበት ሁኔታ መኖሩን፣ ከዚያም አልፎ የቃል ኪዳን ሰነድ መፈራረም መቻሉን ይናገራሉ። በመሆኑም የተሳትፎ መድረክ መፈጠሩ በራሱ ለውጡን በበጎ መልክ እንዲታይ የሚያደርገው ስለመሆኑ ያነሳሉ። ይሁን እንጂ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የሚስተዋለው የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ሳይሆን የገዢ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች መኖርን መሆኑን ዶ/ር ራሄል ይናገራሉ። ምክንያቱን ሲያብራሩም፣ ተፎካካሪ ፓርቲ ማለት ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ ተሰጥቷቸው፣ በአንድነት እኩል ቆመው የሚፎካከሩበት ማለት ነው ይላሉ። ነገር ግን፣ በተጨባጭ ያለው የመፎካከሪያ ሜዳ ለሁሉም እኩል አይደለም። በዚህም አንደኛው አሳሪ፣ ሌላኛው ደግሞ ታሳሪ፣ አንደኛው አሳዳጅ፣ ሌላኛው ተሳዳጅ የሆኑበት የመወዳደሪያ ሜዳ መሆኑን ያስረዳሉ። ዶክተሯ አያይዘውም፣ ተፎካካሪ ፓርቲን እንደ መስተዋት አድርጎ በመቁጠር ገዢው ፓርቲ ችግሩን የሚያይበት ሁኔታም ገና አለመፈጠሩን ያነሳሉ። አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ በፌዴራል ደረጃ የሚከበሩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳትፎ ክልል፣ ዞንና ወረዳ ሲወረድ ፈጽመው እንደሚጠፉ ጭምር ያስረዳሉ።

ሌላው ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ ሚኒስትር እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ሆነው የተሾሙ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች የወከላቸውን ሕዝብ ሃሳብ እንዴት እያራመዱት ነው የሚለው ነው። የተፎካካሪ ፓርቲ አባላቱ በኃላፊነት እየሰሩ ያሉት በገዢው ፓርቲ ተሹመው ነው። ነገር ግን የተመደቡበት ቦታ የፓርቲያቸውን ሃሳብ የማቅረቢያ ዕድልን ፈጥሮላቸዋል። ሃሳባቸውን በመንግሥት አስተዳደር እና በመንግሥት ውሳኔ አሰጣጥ እንዲያቀርቡም ያግዛቸዋል። በመንግሥት በሚነሱ የተለያዩ ጉዳዮች ላይም የራሳቸውን ሃሳብ አቅርበው በማስረዳት ለመግባባት ያስችላቸዋል ተብሎ ይታሰባል። በተለይም፣ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተግባብቶ ተመሳሳይ አቋም ይዞ በጋራ ለመስራት ከማስቻሉም በላይ፣ የፓርቲያቸውን ሃሳብ በተለያዩ አጋጣሚዎች እንዲያቀርቡ መንገድ ስለሚከፍትላቸው አሰራሩ የሚደገፍና የሚበረታታ ነው።

ይሁን እንጂ ዶ/ር ራሄል፣ በገዢው ፓርቲ የተለያዩ የስራ ኃላፊነት የተሰጣቸውን የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት በሚመለከት ዓላማው ግልጽ አይደለም ይላሉ። እንደ እሳቸው ማብራሪያ፣ በዚህ ረገድ መንግሥት ለማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት ፓርቲያችን ወይም ገዢው መንግሥት በውድድር ያላሸነፉትን የፖለቲካ ፓርቲዎችንም ጭምር አቃፊ ነው ለማለት ነው። ሁኔታው ለሕዝብ የታሰበ ቢመስልም አሳታፊነቱ ግን ለውጥን በሚያመጣ መልኩ የሚገለጽ አይደለም። አንድ የተፎካካሪ ፓርቲ አባል ዝግጅቱ እና ልምዱ ሊኖረው፣ ለቦታውም ሊመጥን ይችላል። በምርጫ ሳያሸንፍ ወይም የሕዝብን ይሁንታ ሳያገኝ የስራ ቦታው ሲሰጠው፣ ማግኘት ሳይገባው የተሰጠው ነውና በስራው እርግጠኛ ሊሆን እና በራሱ ሊተማመን ግን አይችልም። ግለሰቡ በቦታው ቢቀመጥ እንኳ በራሱ የመወሰን መብት ስለማይኖረው ነጮቹ ኃይል የሌለው ስልጣን / Authority without power/ የሚሉት ዓይነት ነው የሚሆነው። የስራ ኃላፊውም ቢሆን ሁልጊዜ በመንግሥት የተደረገለትን ውለታ በማሰብ ራሱን መሆን አይችልም። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እውነትን ይዞ ለመቆም ሁሉ ይቸገራል።

በመሆኑም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከገዢው ፓርቲ የተሰጣቸውን ፕሮግራም ለማስፈጸም በሚያከናውኑት ተግባር ሁሉ፣ ሙሉ በሙሉ የራሳቸውን ውሳኔ ያሳርፋሉ ብሎ ማሰብ አይቻልም። እንዲያውም በሚሰጡት ውሳኔ ሁሉ ስጋት ስለሚያድርባቸው በእያንዳንዱ ተግባር ላይ ከመወሰናቸው በፊት የገዢውን ፓርቲ ይሁንታ ጠባቂ እስከ መሆን ይደርሳሉ። ስለሆነም በተለያዩ የመንግሥት የስራ ኃላፊነት የተሰጣቸው የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት በራሳቸው ተማምነው መስራት ስለማይችሉ በተሰጣቸው የስራ ኃላፊነት ውጤታማ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ እንደሚከብድ ዶ/ር ራሄል ይናገራሉ።

ዶ/ር ያሲን ደግሞ በዶ/ር ራሄል ሃሳብ ሙሉ በሙሉ አይስማሙም። እንደ ዶ/ር ያሲን አስተያየት፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳትፎ በበጎ መልኩ የሚታይ ነው። ምክንያቱም የእኛ አገር የፖለቲካ ሥርዓት አንዱን የፖለቲካ ፓርቲ ስንደግፈውም ሆነ ስንቃወመው በምክንያት ሳይሆን በጭፍን ነው። በዚህም ምክንያት ቀደም ሲል በፓርቲዎች መካከል መግባባት ስላልነበረ ደጋፊና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በአንድ መድረክ አብሮ የሚሰራበት ሁኔታ አልተለመደም። ስለዚህ ከምትቃወመው ፓርቲ ጋር አብረህ ስትሰራ ችግር ይፈጠራል ብለህ ትሰጋለህ። የተፎካካሪ ፓርቲ አባላቱ ግን ይህን ከፖለቲካ ተፎካካሪነታቸው አንጻር ሊያጋጥማቸው የሚችል ተግዳሮትን እያወቁ ወደ ኃላፊነት መግባታቸው ደፋር መሆናቸውን ያሳያል። በዚህም የኢትዮጵያን ፖለቲካ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለመቀየር ተፎካካሪ ፓርቲዎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የቆየ የፖለቲካ ባህላችንንም አዲስ መልክ እንዲኖረው ለማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።

በተለያዩ የመንግሥት መዋቅር የስራ ኃላፊነት የተሰጣቸው የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ከሞላ ጎደል የተሰጣቸውን ሃላፊነት በብቃት እየተወጡ እንደሚገኙ የሚገልጹት ደግሞ አቶ ግርማ ናቸው። አቶ ግርማ በዋናነት እንደማሳያ የሚያነሱት በትምህርት ሚኒስቴር እየታየ ያለውን ለውጥ ነው። በደቡብ ክልል እና በአዲስ አበባ መስተዳድር ጭምርም በአርአያነት ሊጠቀሱ የሚችሉ አመራሮች መኖራቸውንም አቶ ግርማ ያስረዳሉ። ስለሆነም፣ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንጻር በጥንካሬ ጎን ሊነሳ የሚገባው ዋናው ጉዳይ የገዢውን የፖለቲካ ፓርቲ /ብልጽግና/ ግብዣ በመቀበል ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ችግር ሁሉ በጸጋ ተቀብለው ወደ ኃላፊነት መግባታቸው ነው። በተለያዩ የስራ ሃላፊነቶች የተሾሙ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት፣ በተለይም በፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ውስጥ የተመደቡ አባላትና ሰብሳቢዎችም ቀደም ሲል ከነበረው የቋሚ ኮሚቴ አሰራር ልዩነት ያለው እና የተሻሉ መሆናቸውን ለማሳየት ጥረት እያደረጉ ነው። ቀደም ሲል ሰምተን በማናውቀው ሁኔታ ተቋማትን ገምግመው ይህን ያህል የበጀት ጉድለት ታይቷል ተብሎ ሪፖርት መቅረብም ጀምሯል። ይህ ደግሞ የፓርላማው የጠያቂነት ሚና እና ስራ አስፈጻሚውን የመቆጣጠር አቅሙ እየጎለበተ መምጣቱን ያሳያል።

በፓርቲዎች መካከል የተፈጠረው ነገር ደግሞ እርስ በርሳቸው መተዋወቃቸውና አብሮ መስራት መቻላቸው ብቻ ሳይሆን የተሰጣቸውን የስራ ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ጥረት ማድረጋቸውን ጭምር ነው። በሂደቱም አንዳንድ የተሻሉ ሊባሉ የሚችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና አባላታቸውን ማየት እየተቻለ ነው። የዚህ አሰራር ውጤት ደግሞ የተለያዩ ሃሳቦችና አመለካከቶች በሂደት እንዲቀራረቡ፣ አገራዊ አስተሳሰብ እንዲጸናና ጠንካራ የሆነ አገራዊ መንግሥት ለመመስረትም መንገድ ለመክፈት ዕድል መፍጠር የሚያስችል ነው። በተለይም ሶስትና አራት የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት በመንግሥት አስፈጻሚ መ/ቤቶች ኃላፊ ሆነው መመደባቸውን ከቁጥር አንጻር አነስተኛ ናቸው ብሎ የሚያስብ አካል ሊኖር ይችላል። ነገር ግን መታየት ያለበት መድብለ ፓርቲን ከማለማመድና ከማጠንከር አንጻር ነው። በተለይም መንግሥት የሚያስገድደው ሕግ ሳይኖር የወሰደው ርምጃ በመሆኑ ጥሩ ጅምር ነው። ምክንያቱም በተለመደው አሰራር በፓርላመንታዊ ሥርዓት መንግሥት በሃላፊነት የሚመድባቸው የስራ ኃለፊዎች ወደ ፓርላማ ከገቡት የራሱ ፓርቲ አባላት እንጂ ከተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ጭምር እንዲሆን አስገዳጅ አሰራር የለም። በመሆኑም በመንግሥት የተውሰደው ርምጃ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መጎልበት ስለሚያግዝ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በተለያዩ የስራ ኃላፊነቶች የማሳተፍ አሰራር የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እና መስፋት እንዳለበት ዶ/ር ያሲን ያብራራሉ።

ከተፎካካሪ ፓርቲዎች አንጻር በድክምት ሊነሳ የሚችለው በዋናነት ከገዢው ፓርቲ ጋር አብረው ሲሰሩ በአሰራር መዋጣቸው ነው። የፓርላማ አባላቱም ሆኑ በሚኒስቴር ደረጃ የሚገኙት የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት እንደ ፓርቲ ጠንካራ የሆነ አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦችን በማቅረብ ጎልተው የሚታዩበት ሁኔታ አልተፈጠረም። የሕዝብንም ሆነ የገዢውን ፓርቲ ይሁንታ ሊያስገኝ የሚችል የልማትም ሆነ የሰላም አጀንዳ ሲያነሱ እያየንና እየሰማን አይደለም። ስለዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያገኙትን መልካም አጋጣሚና እድል ተጠቅመው ለወከላቸው ሕዝብ ሊሰሩና የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚኖርባቸው ዶ/ር ያሲን ያሰምሩበታል። አቶ ግርማም ቢሆኑ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አሁንም ቢሆን ከለውጡ በኋላ ቀደም ሲል ያካሂዱት እንደነበረው አደረጃጀታቸውን በተበታተነ መንገድ በማስቀጠል ላይ መሆናቸው ስህተት መሆኑን ይናገራሉ። በአሁኑ ጊዜ የሚሻለውና አዋጭ የትግል መስመር የሆነውን ልዩነትን በማጥበብ ጠንካራ ፓርቲን የመፍጠር ሁኔታን ማጠናከር ይገባቸዋል ይላሉ። ዶ/ር ራሄልም፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች አኳያ ብዙ ሊስተካከሉ የሚገባቸው ነገሮች መኖራቸውን ያነሳሉ። በዋናነት፣ በአገራችን በሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች ዙሪያ መስተካከል በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ በግልጽ መቃወም፣ በጎውን ነገርም መቀበል እና በጋራ አብሮ መስራትን መለማመድ ይገባቸዋል ይላሉ። አብዛኛዎቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በርዕዮተ ዓለም ላይ የተመሰረቱ አይደሉም። በተግባር እንደሚስተዋለው አንድ ዓይነት ርዕዮተ ዓለም እያራመዱ እንኳን የጎላ ልዩነት ሳይኖራቸው፣ 30 ዓመት ሙሉ ልዩነት ስለተሰበከ ብቻ፣ በቁጥር ወደ 10 የሚደርሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅተው ይገኛሉ። በመሆኑም ከዚህ ግባ የማይባልን የሃሳብ ልዩነታቸውን አጥብበው መሰባሰብና መጠናከር እንደሚኖርባቸው ያስረዳሉ። የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ እንዲጎለብት ከሚያደርጉት ወሳኝ ጉዳዮች መካከል አንዱ በፓርቲዎች መካከል ያለው ግንኙነት ጤናማ የሆነ የውድድር መልክ እንዲኖረው ማድረግ ሲቻል መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ያሲን፣ በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መተማመን መፈጠር /trust build/ ይኖርበታል ይላሉ። ምክንያቱን ሲያብራሩም፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወዳደሩት በአንዲት አገር ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። የሚያነሱትና የሚከራከሩበት አጀንዳ ደግሞ ለአንድ ሀገርና ሕዝብ በመሆኑ ከሚያለያያቸው ይልቅ የሚያመሳስላቸው ጉዳይ ስለሚበዛ ልዩነታቸውን ቢያጠቡት ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ይናገራሉ።

እንደ አቶ ግርማ ሃሳብ፣ ከምርጫ ቦርድ አሰራር ጋር በተያያዘ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሕግ የተቀመጠውን መስፈርት በአግባቡ ማሟላት መቻላቸውን ማረጋገጥ ይገባዋል። ለምርጫ ሲባል በተፎካካሪ ፓርቲዎች ውድድር ወቅት ያሳየውን መለሳለስ ከምርጫ በኋላ ላለመድገም መስራት አለበት። የመድብለ ፓርቲ ሕጉ ከሚፈቅደው ውጪ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እስከ መሰረዝ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚደራጁት የሕዝብ ውክልና ለማግኘት በመሆኑ አቅም ባላቸው አመራር መመራት እንዲችሉ አነስተኛ የትምህርት ዝግጅት እና የሥራ ልምድ መመዘኛን እንዲያሟሉ የሕግ ማዕቀፉ ቢዳስሰው ጥሩ ነው።

ገዢው ፓርቲ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንዳይጎለብት ተጽዕኖ ፈጣሪ አሰራርችን ማስተካከል ይገባዋል የሚሉት ደግሞ ዶ/ር ያሲን ናቸው። ዶክተሩ እንደሚያስረዱት፣ በገዢው ፓርቲ በኩል ሊነሳ የሚገባው ዋናው ጉዳይ በሁሉም ነገር ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማፈን፣ የራሱን የበላይነት አስተሳሰብ /dominant mentality/ በጎላ መልኩ እያሳየ መሆኑ ነው። ይህ የበላይነት አስተሳሰብ የተፈጠረው ደግሞ ቀደም ሲል በኢህአዴግ ሥርዓት የነበረው የአንድ ፓርቲ የበላይነት ተጽዕኖ ነው። ምክንያቱም በለውጡ ውስጥ የሚገኙ አመራሮች አብዛኛዎቹ የድሮው ፓርቲ የፖለቲካ ተዋንያን፣ አባላትና ካድሬዎች የነበሩ ናቸው። አብዛኛዎቹ የለውጡ የፖለቲካ አራማጆችም ከቆየው ሥርዓት ጋር በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ አብረው የቆዩና የሰሩ ሰዎች ስለነበሩ ጭምር ነው። የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ አሰራር ደግሞ ከተለየ ጥቅም ጋር ይያያዛል። የፓርቲ ሥርዓቱ ከሚፈቅደው ውጪ የበላይ ሆኖ የመውጣት አዝማሚያዎችም ይስተዋሉበታል። በመሆኑም እንደ አንድ ኃላፊነት እንደሚሰማው ገዥ ፓርቲ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱን ከማጽናት፣ የሚነሱ ሃሳቦችን ወካይ እና የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሃሳብ እንዲሰማ ከማድረግ አንጻር የሚጠበቅበትን መወጣት ይኖርበታል። የተጀመረውን የውድድር ሜዳም የበለጠ በማስፋት ጠንካራ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መፍጠር ይጠበቅበታል።

ዶ/ር ራሄል ደግሞ፣ በመንግሥት በኩል የሚስተዋለው ዋናው ችግር የመንግሥትና የፓርቲ አሰራር አለመለየቱ ነው ይላሉ። ዶ/ር ራሄል እንደሚያስረዱት፣ በአገራችን በከፍተኛ ደረጃ ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መጎልበት ከፍተኛ ማነቆ ሆኖ የሚገኘው የፓርቲና የመንግሥት አሰራር መደበላለቁ ነው። ይሁን እንጂ፣ አንድ አገር ማደግና እንደ ሀገር መቀጠል ካለባት የፓርቲና የመንግሥት አሰራር ሊለይ ይገባል። በአሰራር ላይ የፓርቲና የመንግሥት አለመለያየት ደግሞ ነገሮች በሁለት መነጸር መታየት እንዲችሉ አላደረጋቸውም። መንግሥት ለዜጋው ያለልዩነት አገልግሎት መስጠት አለበት። የሁሉንም ዜጋ መብት ማክበር እና ማስከበር ይጠበቅበታል። በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ግን በተግባር እየተገለጸ አይደለም። የፖለቲካ ፓርቲ አገልግሎት የሚሰጠው ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ለዚያ ፓርቲ አባላት፣ ከዚያም አልፎ ለደጋፊዎቹ ነው። ይህ ማለት ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲው ከዜጋው ውስጥ የማይፈልገው እና እኩል አገልግሎት የማይሰጠው አካል አለ ማለት ነው።

ከሁሉም ነገር በፊት ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ለሀገር ነው። ፖለቲካው ሊኖር የሚችለው ደግሞ አገር ስትኖር መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። በቅርቡ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተፈጠረው ችግር እንኳ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዴት ይደጋገፉና አብረው ይሰሩ እንደነበረ ማየት ችለናል። ተፈጥሮ የነበረውን ዓለም አቀፍ ጫናውንም ቢሆን በጋራ ለመከላከል የተደረጉ ጥረቶች ቀላል የሚባሉ አልነበሩም። በመሆኑም እነዚህን በአገራዊ ጉዳይ ላይ በጋራ የመስራት የተጀመሩ በጎ ሙከራዎችን የበለጠ ማስፋትና ማጠንከር የግድ ይላል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ከግላዊነት አስተሳሰብ ተላቀው ሕዝባዊነትን ሊላበሱ ይገባል። ገዢው ፓርቲም ቢሆን እንደ መንግሥት እየተገነባ ያለው አዲስ የፖለቲካ ባህል መሆኑን በመገንዘብ የሚከሰቱ የአሰራር ችግሮችን በሥርዓት መፍታት ይጠበቅበታል። ህግን ማክበርና ማስከበር፣ ለሚፈጠሩ የሕግ ጥሰቶችም ተጠያቂነትን ማስፈን ግዴታው መሆኑን መረዳት ይኖርበታል እንላለን።

ንጉሤ ተስፋዬ

ዘመን መጽሔት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም

Recommended For You