አባይን የመገደብ ህልም በዘመን አንጓዎች

ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በርካቶች የአባይን መነሻ የማወቅ ምኞት ነበራቸው። ታሪክ ፀሐፊው ሔሮዶተስ፣ የፖርቱጋሉ ሚሲዮናዊ ፓድሬ ፔሬዝ፣ ሳሙኤል ቤከር፣ ከሪቻርድ በርተን፣ ጆን ሀኒንግ እና ሌሎችም የአባይ መነሻ የት ነው ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ሞክረዋል። ነገር ግን በ18ኛው ክፍለ ዘመን ስኮትላንዳዊው ጄምስ ብሩስ ከካይሮ እስከ ጣና ድረስ ተጉዞ የአባይ መነሻ ጣና ሀይቅ መሆኑን እስኪያውጅ ድረስ፣ ኢትዮጵያ የታላቁ ወንዝ ምንጭ መሆኗን ዓለም አልተረዳም ነበር።

በተመሳሳይ መልኩ ከዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያን በተለያዩ ዘመናት ያስተዳደሩ መሪዎች አባይን የመገደብ ህልም ነበራቸው። አጼ ላልይበላ፣ አጼ ተክለሃይማኖት፣ አጼ ምንሊክ፣ አጼ ኃይለ ሥላሴ እና ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም አባይን ለሀገር ልማት የማዋል ምኞታቸውን በተለያየ መንገድ ገልጸዋል። ነገር ግን ይህ የዘመናት ህልም መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዘመን እውን እስኪሆን ድረስ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም አባይንመገንባት እንደሚችሉ ዓለም አልተረዳም ነበር።

ይህ ጽሁፍ በየዘመናቱ የተነሱ የኢትዮጵያ መሪዎች አባይን ለመገደብ የነበራቸውን ፍላጎት፣ ያደረጉትን ጥረት፣ ያጋጠሟቸውን ውስጣዊና ውጪያዊ ፈተናዎች እንዲሁም በትውልዶች ቅብብሎሽ የዘለቀው ጥያቄ መልስ ያገኘበትን መንገድ ይዳስሳል። የታሪክ ጉዟችንን የሚሾፍሩት ዶክተር አብዲ መሀመድ አሊ ይሆናሉ። ዶክተር አብዲ በዲላ ዩኒቨርስቲ የታሪክና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች መምህርና ተመራማሪ ናቸው። አረብኛ ቋንቋን አቀላጥፈው ይናገራሉ። በአባይ ጉዳይ ዙሪያ በግላቸው ብዙ ምርምሮችን አድርገዋል።

አባይ ሲነሳ በብዛት ስማቸው የሚጠቀሰው ኢትዮጵያና ግብጽ መሆናቸውን በመጥቀስ ሀሳባቸውን የሚጀምሩት ዶክተር አብዲ፣ ቀደም ወዳለው ዘመን መለስ ብለን ስናይም ከተቀሩት የተፋሰሱ ሀገራት ተለይተው ሁለቱ ሀገራት ጎልተው ይወጣሉ ይላሉ። ግብጽ ለቁሳዊ ህልውናዋ ትናንትም ዛሬም አባይን ትፈልገዋለች። ምክንያቱም 98 በመቶ የግብጽ ህዝብ የአባይ ውሃ ተጠቃሚ ነው። እስከ 1951 ዓ.ም. ድረስ ደግሞ ኢትዮጵያ ለመንፈሳዊ ህልውናዋ ስትል የግብጽ ጥገኛ ነበረች። ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ 1950 ዓ.ም. ድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያሪኮች ግብጻውያን ነበሩ። ስለዚህ የኢትዮጵያና ግብጽን ግንኙነት ከመንፋሳዊና ቁሳዊ ግንኙነት አንጻርም ማየት ይገባል ሲሉ ይመክራሉ።

ዶክተር አብዲ እንደሚገልጹት ኢትዮጵያና ግብጽ በአባይ ጉዳይ ውዝግብ ውስጥ መግባት የጀመሩት በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ነው። ከዘጠነኛው እስከ 12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አልፎ አልፍ ድርቅ ይከሰት ስለነበር፣ ግብጽ የሚደርሰው የውሃ መጠን በጣም ይቀንስ ነበር። ግብጽ ምድር የሚደርሰው የውሃ መጠን ሲቀንስ ግብጻውያን ይሄ የኢትዮጵያውያን ተንኮል ነው፤ ግድብ ሰርተው ወይም የወንዙን ፍሰት አቅጣጫ በማስቀየር ሊጎዱን እየተንቀሳቀሱ ነው ብለው ያስቡ ነበር። ይሄን ሀሳባቸውን በመጽሐፈ ስንክሳር ላይ መቅሰፍት እያመጡብን ያሉት ኢትዮጵያን ናችው ብለው በግልጽ አስቀምጠውታል።

ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በአንድ ጽሁፋቸው እ.አ.አ. ከ1889 እስከ 1890 ባለው ጊዜ በሱልጣን አል-ሙስታንሲር ዘመን ከፍተኛ የሆነ የውሃ እጥረት መከሰቱን የግብጽ የመረጃ ምንጮች እንደሚያመለክቱ ገልጸዋል። ሱልጣኑም ይሄንን ችግር ለመፍታት ፓትሪያርክ ሚካኤልን ወደ ኢትዮጵያ መላካቸውንና የወቅቱ የዛጉዬ ንጉሥ የነበረው የኢትዮጵያ መሪ ውሃውን የዘጋውን ደለል እንዲያስወግድ መደረጉን ታዋቂው የአረብ ጸሐፊ አልማኪን ጽፈዋል። ይሄ በግብጾች በኩል የተጻፈና ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትና ሌሎችም የዘገቡት መረጃ ነው የሚሉት ዶክተር አብዲ፣ በአልማኪን ትንታኔ መሰረት ኢትዮጵያውያን ወንዙን ገድበዋል ተብሎ ታምኖ ነበር። ሆኖም በኋላ ፓትሪያርክ ሚካኤል ወደ ኢትዮጵያ ተልከው ውሃውን ሲያዩት አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደለል ሞልቶ ውሃው እንዳይሄድ እንደከለከለው ሌላው ደግሞ በተፈጥሮ ምክንያት የዝናብ እጥረት በመኖሩ የተፈጠረ ችግር መሆኑን መገንዘባቸውን ይገልጻሉ።

ነገር ግን ይሄ የአልማኪን ትንታኔ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመጡ የአውሮፓ ተጓዦችና ጸሐፊዎች ተቀባይነት አግኝቷል። ዶክተር አብዲ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲያስረዱ እ.አ.አ. ከ1453 ጀምሮ በምዕራቡ ክርስቲያንና በምስራቁ ሙስሊም መካከል ከፍተኛ የሆነ የጥቅም ግጭት እንደነበር ያወሳሉ። የጥቅም ግጭቱን ምክንያት ሲያብራሩም በ1453 የኦቶማን ቱርኮች የምስራቅ ሮማ ዋና ከተማ የሆነችውን የያኔዋን ቆስጣንጢኖስ የአሁኗን ኢስታንቡልን ተቆጣጥረው ነበር። አውሮፓውያን ከምስራቁ ዓለም የሚገናኙበት ብቸኛ መንገድ በጠላታቸው እጅ በመውደቁ ቀን ጨልሞባቸው ነበር። በዚህ ወቅት ሙስሊሞችን ማሸነፍ እንድንችል በህንድ ውቅያኖስና በቀይ ባህር አካባቢ አጋር ያስፈልገናል የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ። በአካባቢው ደግሞ ቄስ ዮሐንስ የተባለ አንድ ክርስቲያናዊ ንጉስ ነበረ። እሱን ብንቀርበው ከታች እና ከላይ ሆነን ልናዳክማቸውና ያጣነውን ዓለም አቀፋዊ ፈላጭ ቆራጭነት መቀጠል እንችላለን ብለው አመኑ።

ስለዚህ እንደ አንድ ክርስቲያን ኃይል ሙስሊሞችን ማዳከም የምንችለው አባይን ኢትዮጵያውያን ሲቆጣጠሩ ነው የሚል እምነት ይዘው ነበር። በወቅቱ የኦቶማን ቱርክ ግዛት ከሆኑት ቦታዎች መካከል ትልቋ ስትራቴጂክ ጠቀሜታ የነበራት ግብጽ ነች። ስለዚህ ይህን ሚናዋን ማዳከም የሚቻለው ኢትዮጵያን አጋር በማድረግ ነው የሚል እምነት ስለነበራቸው የአልማኪን ትንታኔ አስተጋብተዋል። ጀርመናዊው ሂዮብ ሉዶልፍ እና ስኮትላንዳዊው ጀምስብሩስ ስለኢትዮጵያ ሲጽፉ ኢትዮጵያውያን አባይን የመገደብ አቅሙ አላቸው ብለው የአልማኪን ትንታኔ እንደ እውነት የተቀበሉት በዚህ ምክንያት ነው ይላሉ።

በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በነገሱት በአጼ ላሊይበላ ዘመን ኢትዮጵያ አባይን ለመገደብ ተንቀሳቅሳለች ተብሎ በስፋት ይነገራል። ወቅቱ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ያደገችበት ስለነበረና ክርስቲያኖች ግብጽ ውስጥ በጣም ይጨቆኑ ስለነበረ አጼ ላሊይበላ የክርስቲያኖችን ስቃይ ለማስቆም አባይን ገድባለሁ ብለዋል በሚል የሚነገር ትርክት አለ። ይሄ ገድለ ላሊይበላ ላይም ሆነ ሌሎች የኢትዮጵያ ድርሳናት ላይ የለም የሚሉት የታሪክና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ምሁሩ

በወቅቱ አጼ ላሊይበላ ከአባይ አካል ሊቆጣጠሩ የሚችሉት ቦታ ተከዜን ብቻ እንደነበረ ያስረዳሉ። ስለዚህ አቅጣጫውን እንዲቀይር ማድረግ የሚችሉት አንድ ገባሪውን ተከዜን ብቻ ነው። በእነዚህ ምክንያቶች አጼ ላሊይበላ ከፉከራ ባለፈ አባይን ለመገደብ አንድ አይነት እርምጃ ወስደዋል ለማለት የሚያስችል ምንም አይነት ታሪካዊ ማስረጃ እንደሌለ የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑት ሪቻርድ ፓንክረስትና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎችም ያረጋገጡት ሀቅ ነው። ስለዚህ የጀምስ ብሩስም ሆነ ሂዮብ ሉዶልፍ ትርክት ትክክል አይደለም።

የታሪክና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ምሁሩ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደግሞ ከ1706 እስከ 1708 የነገሱት የኢትዮጵያ ንጉሥ አጼ ተክለሃይማኖት አንድ ፈረንሳዊ ዲፕሎማትና ሙራድ የተሰኘ አርመናዊ ነጋዴ ወዳጆቻቸው ሱዳን አካባቢ በመታገታቸው ለግብጽ የማትለቋቸው ከሆነ አባይን በመገደብ እንቀጣቸዋለን ብለው ደብዳቤ መጻፋቸውን ይናገራሉ። በጥቅሉ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ባለው ጊዜ የነበሩ ኢትዮጵያውያን የአባይን ጉልበት የተረዱበት ሁኔታ እንደነበርና ወንዙን የመገደብ ምኞት እንደነበራቸው እነዚህ ትርክቶች ያስረዳሉ። ነገር ግን ያን ጊዜም ቢሆን አባይ በኢትዮጵያና ግብጽ መካከል ወንዝ ብቻ ሳይሆን መዘዝም እንደነበር ከማሳየት በዘለለ ግን የተወሰዱ ተግባራዊ እርምጃዎች አልነበሩም ሲሉ ይደመድማሉ። ቀጥሎ ዳግማዊ አጼ ምንሊክ አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ ከመሰረቱ በኋላ በዙሪያቸው ከነበሩት የቅኝ ገዢ ኃይላት ጋር የተለያዩ ውሎች መፈራረማቸውን ከእነዚህም አንዱ በ1902 ዓ.ም. የተፈረመው አባይን የተመለከተ ውል ነው የሚሉት የታሪክ ምሁሩ፣ በዚህ ውል አጼ ምንሊክ ግድብ አንገድብም አላሉም። ስምምነቱ ውሃ አንነፍጋችሁም የሚል ነው። አንዳንድ ግብጻውን ጸሐፍቶች ግን በአረብኛና እንግሊዝኛ በሚጽፏቸው ጽሑፎች ላይ ቀደም ብለው ንጉሠ ነገሥቱ ወስነውልናል የሚሉት ነገር አለ። ስምምነቱ ግን የሚያሳየው ወደ ግብጽ የሚፈሰውን ውሃ እንዲቆም አናደርግም እንጂ ግድብ አንገነባም ወይም ወደፊት አንጠቀምበትም የሚል አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ ። ዶክተር አብዲ እንደሚያብራሩት ከአጼ ምኒልክ ዘመን በኋላ በ1922 ዓ.ም. የወቅቱ አልጋወራሽ የነበሩት ራስ ተፈሪ መኮንን (በኋላ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ) በሊግ ኦፍ ኔሽን ጣና ሃይቅን በሚመለከት ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ወክለው የተዋዋሉትን ውል ተቃውመዋል። ራስ ተፈሪ ከ1920ዎቹ ጀምሮ በአልጋ ወራሽነት ዘመናቸውና ቆይቶም ንጉሥ ከሆኑ በኋላ እስከ ጣሊያን ወረራ ዋዜማ ድረስ ኢትዮጵያ አባይን የመጠቀም መብቷ እንዲከበርላት ይጠይቁ ነበር። በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ኢትዮጵያ ግድብ የመገደብ ህልሟን ይፋ ያደረገችባቸው ሁኔታዎች እንደነበሩ በኢትዮጵያ ግብርና ታሪክ ላይ ብዙ መጽሐፍቶችን ያሳተሙ ጄምስ መካን የተባሉ ተመራማሪ በተለይ እ.አ.አ. በ1981 በጻፉት አንድ ጦማር ላይ በግልጽ አስቀምጠውታል። ከጣሊያን ወረራ በፊት በኢትዮጵያ በኩል ወንዙን የመገደብ ህልም ነበር። ጣሊያን ኢትዮጵያ ውስጥ ከቆየባቸው አምስት አመታት በኋላም ያ ህልም አልተቋረጠም። ህልሙን እውን ለማድረግ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በኩል ብዙ ሙከራዎች ነበሩ። ነገር ግን እንግሊዝ የረጅም ጊዜ ህልሟ የነበረውን አባይን ሙሉ ለሙሉ የመቆጣጠር ሀሳቧን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላም አልተወችም ነበር። ለዚህ ዋቢ የሚሆነው በእንግሊዝ ተዘጋጅቶ በሱዳንና ግብጽ መካከል የተፈረመው ኢትዮጵያን የማያካትተው ውል ነው። ይሄንንም ውል ኢትዮጵያ ተቃውማለች። ዶ/ር አብዲ ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችም ሆኑ የፖለቲካ ተንታኞች ከአባይ ጋር በተያያዘ ትኩረት ሰጥተው የማያዩት ነገር አለ ይላሉ። ጉዳዩን ሲያስረዱም በአባይ ታሪክ ውስጥ እ.አ.አ. 1959 እጅግ በጣም ወሳኝ ዓመት ነው። ምክንያቱም እ.አ.አ. በ1959 ኢትዮጵያ ራሴን ችዬ በራሴ ፓትሪያርክ እመራለሁ ብላ ከኢትዮጵያ ቤተክህነት ሰዎች በተጨማሪ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ከፕሬዚደንት ገማል አብዱልናስር እና ከግብጽ መነኩሳትና የሃይማኖት አባቶች ጋር በግልጽ ተነጋግረው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትሪያርክ የተሾመበት ወቅት ነው። ከላይ እንዳነሳሁት ኢትዮጵያ ለመንፈሳዊ ህልውናዋ ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንስቶ እ.አ.አ. 1959 ድረስ የግብጽ ጥገኛ ነበረች። እኛ ይሄን ሁኔታ ለታሪክ ተማሪዎች የምንገልጸው ኢትዮጵያ የግብጽ ሃይማኖታዊ ቅኝ ተገዢ ነበረች እያልን ነው። ኢትዮጵያ ነጻነቷን ባወጀችበት እ.አ.አ 1959 ነው ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያን ያገለለ ውል የተዋዋሉት። ስለዚህ ሁለቱን ነገሮች አብሮ ማስተያየት ይገባል ብለው እንደሚያምኑ ይገልጻሉ።

በ1959 የተፈራረሙትን ውል ተከትሎ ግብፆች ተጨማሪ ፕሮጀክት ውስጥ መግባታቸውንም እንደሚከተለው ያወሳሉ። በ1960 ካይሮ ላይ ገማል አብዱልናስር የኤርትራ ተማሪዎችንና ፖለቲከኞችን ሰብስበው የኤርትራ የነጻነት ግንባር ወይም ደግሞ በዘልማድ ጀባሃ የሚባለውን ድርጅት እንዲመሰረት አደረጉ። እ.አ.አ በ1961 መስከረም ወር ላይ ጀባሃ የኤርትራን የነጻነት ትግል ጀመረ። በዚህ ወቅት የቁስና የቴክኒክ ድጋፍ ያገኝ የነበረው ከግብጽ ነበር። የኤርትራ ሪፐብሊክ ድምጽ ይባሉ የነበሩት በአረብኛና በትግሪኛ ለኤርትራ ህዝብ ይሰራጩ የነበሩት ሁለቱ የሬዲዮ ጣቢያዎች ይተላለፉ የነበረው ከግብጽ ነው። ዓላማቸው የኤርትራን ነጻነት ማስገኘት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ማዳከም ነበር። በኤርትራ ጉዳይ ላይ በግላቸው ብዙ ጥናቶች ማድረጋቸውን የሚገልጹት ዶክተር አብዱ አንድ ድምዳሜ ላይ መድረሳቸውን ይናገራሉ። የደረሱበት ድምዳሜ ኤርትራን ያጣናት በአባይ ምክንያት ነው የሚል ነው። ከገማል አብዱል ናስር ወደ ኮሎኔል አንዋር ሳዳት ከዚያም ሁስኒ ሙባረክ ተሸጋገረ እንጂ ግብጽ በኤርትራ ጉዳይ ላይ የነበራት አቋም የጸና እንደነበር በመግለጽ፣ ግብጽና ሱዳን ለጀብሃም ሆነ ለሻቢያ ያን ያህል የመሳሪያና የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጉ የነበረው ኢትዮጵያን ማዳከም ስለፈለጉ መሆኑን ያስረዳሉ። አጼ ኃይለሥላሴ በ1960ዎቹ መጀመሪያ ከአሜሪካ ጋር ከተወዳጁ በኋላ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ለአሜሪካኖቹ በማቅረብ እገዛቸውን ጠይቀው አንዳንድ ጥናቶች ተሰርተዋል። ዶክተር አብዱ እንደሚናገሩት አሜሪካኖች ድጋፉን ለኢትዮጵያ እንዲያደርጉ ግብጽ የተጫወተችው ሚና አለ። እስከ እ.አ.አ 1952 ድረስ አሜሪካ ኢትዮጵያን አታውቃትም ነበር ብሎ መናገር ይቻላል። በእርግጥ በአጼ ምኒልክ ዘመን ሮበርት ስኪነር መጥቶ በ1903 ዓ.ም. ዛሬ አሜሪካን ግቢ የምንለው ቦታ ላይ የአሜሪካ ኤምባሲ ተከፍቷል። ነገር ግን አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ከዚህ ያለፈ ግንኙነት አልነበራትም ነበር። ይህን ሁኔታ የሚቀይር ክስተት እ.አ.አ 1952 ላይ ተፈጠረ። ግብጽ ውስጥ አብዮት ተካሄደና ኮሎኔል ገማል አብዱልናስር ስልጣን ያዙ። አፍቃሪ አሜሪካ የነበረው የቀድሞ ንጉሥ ስርዓት ተገረሰሰና ገማል አብዱልናስር ኮሚኒዝምን መከተል ጀመሩ። በሂደቱ ሩሲያውያኖች ወደ ግብጽ ሲመጡ አሜሪካ አየር ላይ ቀረች። በዚሁ ወቅት 1952 ላይ የተባበሩት መንግስታት ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እድትወሃድ አደረገ። አሜሪካ ቀይ ባህር ላይ አንድ ስትራቴጂካዊ አገር አገኘች ማለት ነው። ስለዚህ ወዲያውኑ 1952 እና 1953 ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ሁለት ስምምነቶችን በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ መጥታ አስመራ ላይ ቃኘው ቤዝን ተቆጣጠረች። ግብጽን በማጣቷ ኢትዮጵያን የግብጽ ምትክ አድርጋ በመቀበል ለኢትዮጵያ ሁሉን ነገር ማድረግ ጀመረች።

ዶክተር አብዲ በ1950ዎቹና 60ዎቹ አካባቢ በአሜሪካኖች ተደረገ የሚባለውን ጥናት እንደ አንድ ታሪክ ተመራማሪ ሲመለከቱት ተግባራዊ ለማድረግ ታስቦ የተከወነ ሳይሆን በግብጽ ላይ በሲአይኤ የታወጀ ስነልቦናዊ ጦርነት ነው ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ። ለምን እንዲህ ያለ አቋም ለመያዝ እንደበቁ ሲያብራሩም፣ ገማል አብዱልናሱር እንዲህ ያሉ ነገሮች ሊያመጡባቸው የሚችሉትን ጣጣ ያውቃሉ። አሜሪካ ለኢትዮጵያ ግድብ ገነባች ማለት በዚያ ጊዜ በሶቬት ህብረት እርዳታ ያሰሩት አስዋን ግድብ ተጫዋችም ተመልካችም የሌለበት ባዶ ስታዲየም ነው የሚሆነው። ከዚህ ውጭ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም። ምክንያቱም ከወረቀት ወደ መሬት የወረደ ምንም አይነት ነገር የለም። ስለዚህ ግብጽን የማስፈራራት አጀንዳ አንድ አካል ነበር ብዬ ነው የማምነው ይላሉ።

አያይዘውም፤ እ.አ.አ. በ1960 አሜሪካ ለመላው አፍሪካ ከምትሰጠው የቴክኒክና የገንዘብ እርዳታ 60 በመቶ የሚሰጠው ለኢትዮጵያ እንደነበር በማስታወስ ይህ ሁሉ እርዳታ ለምን ለአንድ ሀገር ይሰጣል ተብሎ ቢጠየቅ፣ መልሱ ከኮሚኒስቶች ጋር ወዳጅነት የፈጠረችውን ግብጽን ለማዳከምና ለማስቀናት ነው። ከዚያ በኋላ 1970 ላይ የገማል አብዱልናስርን ሞት ተከትሎ አንዋር ሳዳት ሶቬቶችን አስወጥቶ አሜሪካኖችን መልሶ ሲያስገባቸው ኢትዮጵያ ለአሜሪካ የነበራት አጋርነት ትርጉም አልባ ሆነ ይላሉ። የደርግ መንግስትም አባይን የማልማት ሃሳብ ነበረው የሚሉት የታሪክና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ምሁሩ፣ አብዮቱ እንደፈነዳ ከሚዘመሩት መዝሙሮች አንዱ “ተነሳ ተራመድ” የሚል ነበር። ይህ መዝሙር ወንዞች ይገደቡ ይዋሉ ለልማት፣ ሲፈሱ ኖረዋል ለብዙ አመታት የሚሉ ስንኞች ነበሩት። ይሄ የሚያሳየው ደርግ እንደ መንግስት የአባይን ወንዝ የመገደብ ህልም እንደነበረው ነው። ይሄንን ህልሙን እውን ለማድረግ ደግሞ የጣና በለስ ፕሮጀክትን መጀመሩ የሚካድ ሀቅ አይደለም በማለት መሬት የነኩ እንቅስቃሴዎች ተደርገው እንደነበር ያስታውሳሉ። አክለውም፤ ደርግ እንደ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የትንፋሽ ጊዜ አልነበረውም። ወደስልጣን የመጣው “ያለምንም ደም እንከኗ ይውደም” እያለ ቢሆንም ለ17 አመታት ኢትዮጵያን ደም በደም አድርጎ የሄደ መንግስት ነው። በሀገር ውስጥ ኢህአፓ እና ኢዲዩን ከመሰሉ ኃይሎች ጋር ይዋጋ ነበር። በድንበር አካባቢ ደግሞ ከሕወሃት፣ ኦነግ፣ ሻቢያና ጀበሃ ጋር ይዋጋ ነበር። በዚህ ላይ ደግሞ የሶማሊያ ወረራ ሲታከልበት በጦርነት ጀምሮ በጦርነት ያከተመ ሥርዓት ነው የነበረው። በእነዚህ 17 አመታት ውስጥ ፍላጎቱ ቢኖርም ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለማቀድ ዕድሉ አልነበረውም። ሆኖም በጅምር የቀረው የጣና በለስ ፕሮጀክት ከአባይ የተወሰነውን ክፍል የሚጠቀም በመሆኑ ምንም አልሰራም ማለት እንደማይቻል ይገልጻሉ።

ዶክተር አብዲ ለዘመናት የኢትዮጵያውያን ቁጭት የነበረው አባይ ስለተገደበበት ዘመን ኢህአዴግ ሲያነሱ አንድ አጋጣሚን ያስታውሳሉ። መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. የታላቁ ህዳሴ ግድብ መሰረተ ድንጋይ ከመጣሉ 13 አመታት ቀድም ብሎ እ.አ.አ. በ1998 የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ “አልሃያት” የሚል የአርብኛ ርዕስ ላለው ነገር ግን በእንግሊዝኛ ለሚታተም ጋዜጣ የሠጡት አንድ ሰፊ ቃለ መጠይቅ ነበረ። አዘጋጆቹ አረቦች ስለነበሩ በአባይ ጉዳይ ወደፊት ምን እንደሚያስቡ ጠይቀዋቸው ነበር። ይህ ቃለመጠይቅ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሚያሳትመው ዘኢትዮጵያን ሔራልድ ላይ ወጥቶ ተመልክተውት ነበር። እዚህ ቃለመጠይቅ ላይ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ አባይን የመገንባት ህልም እንዳላትና ይሄ ውጥኗ ሱዳንን እና ግብጽን በፍጹም እንደማይጎዳ ገልጸዋል። ስታስቲካዊ መረጃ በመግለጽ ጭምር ሱዳን በአባይ ምክንያት በአመት ውስጥ ምን ያህል ጊዜ በጎርፍ መጥለቅለቅ እንደሚያጋጥማት ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ሱዳንና ግብጽ በግድቦቻቸው ውስጥ የሚገባውን ደለል ለማስወገድ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ እደሚያደርጉ በመግለጽ ኢትዮጵያ ግድብ ገድባ የተጣራ ውሃ የሚሄድ ከሆነ ከዚህ አላስፈላጊ ወጪ እንደሚድኑ አስረድተዋል። ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ በየትኛውም መስፈርት ሁለቱን አገራት የመጉዳት ህልም እንደሌላት ነገር ግን ከ85 በመቶ በላይ የአባይን ውሃ ድርሻ ይዛ ተጠቃሚ ሳትሆን መኖር እንዳማትችል በግልጽ ተናግረዋል። ይሄ ቃለመጠይቅ ለግብጽና ሱዳን የማንቂያ ደውል እንደሆነ የሚገልጹት ዶክተር አብዲ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያወቁ በድፍረት ወይም ሳያውቁ በስህተት በአባይ ላይ ግድብ ለመገንባት የተያዘውን እቅድ ጋዜጣው ላይ የዘረገፉት ይመስለኛል። በዚህ ምክንያት እኔ በግሌ ፕሮጀክት ኤክስ በዝርዝር ምን ይመስላል የሚለው ካልሆነ በቀር እንደ ትልቅ ፕሮጀክት ሚስጥር ነበር ብዬ ለመናገር አልችልም በማለት አቶ መለስ ዜናዊ ለአልሃያት የሰጡት ቃለመጠይቅ የተጀመረ ነገር እንዳለ የሚያሳይ ስለነበር ግብጽና ሱዳን ነገሮችን በተጠንቀቅ እያዩ እንደነበር ምሁራዊ እይታቸውን ያወሳሉ።

የአባይ ግድብ እውን የሆነበትን ሁኔታ ሲያስታውሱ፤ የአረቦች የጸደይ አብዮት መጣና ግብጽ ትልቅ መከራ ውስጥ ገባች። ይህ ወቅት ግብጽ እየታመሰች የነበረችበትና የሙባረክ መንግስትም ሆነ በኋላ የመጣው ጊዜያዊ መንግስት በግብጽ የውስጥ ጉዳይ የተጠመዱበት ስለነበር ወደ ኢትዮጵያ ጣታቸውን የሚቀስሩበት እድል አልነበራቸውም። ኢትዮጵያ ይህን ዕድል ተጠቅማ ተዘጋጅቶ ወቅት ይጠብቅ የነበረውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት መሰረተ ድንጋይ በመጣል ይፋ አደረገች። የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ይህን ወርቃማ ዕድል አለማባከናቸውን በማድነቅ ኢትዮጵያ አጋጣሚውን የተጠቀመችበትን አካሄድ ብስለት የተሞላበት ሲሉ ያሞካሹታል።

የግድቡን ግንባታ ስንጀምር ግብጾች በዲፕሎማሲው ረገድ ከእኛ የተሻለ አቅም ስላላቸው ምንም አይነት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ከውጭ እንዳናገኝ አድርገውናል የሚሉት ዶክተሩ፣ ግድቡን በራሳችን አቅም መገንባታችን አገራዊ እንድነትን የፈጠረና ኢትዮጵያውያን ከተባበርን ከፊት ለፊታችን የሚኖርን የትኛውንም ተራራ መሻገር እንደምንችል ለዓለም ያሳየንበት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። በመሆኑም ትርጉሙ መልከ ብዙ መሆኑን ይገልጻሉ።

እጅግ በተራራቁ ዘመናት ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ መሪዎች አንድ ህልም መቀባበላቸውና መጋራታቸው ያለውን እንድምታ ሲያስረዱም፣ የትኛውንም ሳይንሳዊ ጥናት ስታደርግ በዘርፉ የተሰሩ ጥናቶች ምን ይመስላሉ በሚል ወደኋላ ሄደህ የምታደርገው የተዛማጅ ጥናቶች ቅኝት አለ። የኢህአዴግ መንግስት የአጼ ኃይለሥላሴን ዕቅዶችና ጥናቶች ተመልክቷል። ምክንያቱም በትልቅ ሀገር የተደረገ ጥናት በመሆኑ ትልቅ መነሻ መሆን የሚችል ግብዓት ነው። አባይን የመገደብ ህልም የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ወይም የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያምና የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ብቻ አይደለም። ባሉን ጥቂት ድርሰቶች ላይ እንኳን ካየነው በዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከነበረው የዛጉዬ መንግስት ጀምሮ የነበረ ህልም ነው። ይህ የሚያሳየው የኢትዮጵያ መሪዎች የአባይን ጠቀሜታ ከጥንት ጀምሮ የተረዱ እንደነበሩ የሚያሳይ ነው ይላሉ። ዶክተር አብዲ ሀሳባቸውን የሚቋጩት ኢትዮጵያ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጎን ለጎን ሁለት ግድቦችን መገንባት ላይ መበርታት እንዳለባት በመጠቆም ነው። ምን ማለታቸው እንደሆነ ሲያብራሩ፣ ኢትዮጵያ አሁን እየገነባች ያለችው በወንዙ ላይ የሚያርፈውን የግድቡን አካል ነው። ጎንለጎን መገንባት ያለባቸው የሞራል እና የዲፕሎማሲ ግድቦች አሉ። እስካሁን ለሞራል እና ለዲፕሎማሲ ግድቦቹ ትኩረት አልተሰጠም። የሞራል ግድብ መገንባት ማለት እኛ ከታችኛው የአባይ ተፋሰስ ሀገሮች ጋር እንደ ሰው ልጆች ወዳጆች መሆናችንና የነሱን ፍርሃትና ጭንቀት እንደምንረዳ የማስገንዘብ ስራ መስራት ነው። የእነሱን ፍርሃትና ጭንቀት ልንጋራው ይገባል። ያ ፍርሃታቸውና ጭንቀታቸው ደግሞ የእኛም ፍርሃትና ጭንቀት እንደሆነ ልናስረዳ የምንችልበት የዲፕሎማሲ ግድብ ያስፈልገናል። እነዚህ ሁለት ስራዎች ባልተሰሩበት ሁኔታ ግድቡን በአለት ገድበን ቁጭ ማድረጉ ብቻውን ለዘላቂ ሰላምና ተጠቃሚነት አያበቃንም የሚል ፍራቻ አለኝ። ስለዚህ ‹‹እኛ እየተራብን እናንተ ጠግባችሁ ማደራችሁ ፍትሃዊ እንዳልሆነ ሁሉ፤ እናንተ ተርባችሁ እኛ ጠግበን የምናድርበት ሁኔታ አይፈጠርም›› ብለን በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ብቻ ሊኖረን እንደሚገባ በሚገባቸው ቋንቋ ለሱዳንና ለግብጽ ህዝቦች ማስረዳት አለበን ሲሉ ይመክራሉ።

ቀደምት ኢትዮጵያውን አባይን ገድበው ለሀገር ልማት የማዋል ህልም ነበራቸው። ይሄን ህልም መሬት ማውረድ የቻለው ዕድለኛው የእኛ ትውልድ ነው። የምናደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረን በመቀጠል ግድቡን ከዳር በማድረስ ዘመን ተሻጋሪ አሻራችንን ለማኖር እንረባረብ የዘመን መጽሔት ዝግጅት ክፍል መልዕክት ነው።

ተስፋ ፈሩ

ዘመን መጽሔት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም

Recommended For You