የለውጡ ስኬትና ፈተና

ዮርዳኖስ ፍቅሩ1953 የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ፣ 1966 አብዮት፣ የቀይ ሽብር ክስተት፣ 1983 የሕወሓት ወደ ስልጣን መምጣት፣ 1993 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንቅስቃሴ እና 1997 ምርጫ ውጤት ያስከተለው ህዝባዊ አመጽ፣ ያለፉ ስልሳ ዓመታት የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አበይት ክስተቶች ናቸው። ክስተቶቹ እንደ አገር ሰፊ ሰብዓዊና ቁሳዊ ዋጋ እንደተከፈለባቸው ታሪክ ይናገራል፤ የየዘመኑ ነዋሪዎችም ያወሱታል።

ክስተቶቹ ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለባቸው ቢሆኑም፣ መነሻ ለሆኑ የህዝብ ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽን ማሰጠት ባለመቻላቸው የተከፈለውን ዋጋ ወደ ኪሳራ እንደቀየረው የፖለቲካ ምሁራን ይናገራሉ። ለህዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥያቄ ምላሽ እሰጣለሁ ብሎ ወደ ስልጣን የመጣው በሕወሓት የሚመራው ኢህአዴግም በተለይም፣ የተከተለው የብሔር ፖለቲካ ሰፊ ተቃውሞን እንዲያስተናግድ ምክንያት ሆኗል።

ባለፉ ስርዓቶች ሳይመለሱ ለቀሩ፣ እየተንከባለሉ ለመጡ የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት አልተቻለውም፤ በዚህም፣ በድርጅቱ ውስጥ ባሉ ለውጥ ፈላጊዎችና ከጫፍ እስከ ጫፍ የነበረው ህዝባዊ ንቅናቄ የፈጠረው ጫና የመጋቢት ወር 2010 .ምን ለውጥ አስከተለ። አምስት ዓመታትን ያስቆጠረው ለውጥ ምን ውጤቶችን አስገኘ፣ ምንስ ፈተናዎችን አስተናገደ፣ ከተነሳበት ዓላማ አንጻርስ ጉዞው ምን ይመስላል በሚለው ላይ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን አነጋግረናል፡ ኢህአዴግ በገባው ቃልና ወረቀት ላይ ባሰፈረው ልክ ዴሞክራሲን ማስፈን፣ ፍትሀዊ የሀብት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም መፍታት ባለመቻሉና ሲፈጽማቸው የነበሩ ከፍተኛ የሆነ የሀብት ምዝበራዎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተደማምረው፣ ጠንካራ በሆነ የህዝብ ግፊትና በራሱ በድርጅቱ ውስጥ በነበሩ የለውጥ ኃይሎች እንቅስቃሴ 2010 መጋቢት ወር ለውጥ እውን እንደሆነ የብልጽግና ፓርቲ ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ያስታውሳሉ።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ ተሾመ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ችግር ለብዙ ዘመናት የነበረና ከስርዓት ወደ ስርዓት እየተሸጋገረ የመጣ መሆኑን አንስተው ህዝቡ ለብዙ ዘመናት የታገለለት ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ በመቅረቱ፣ ያነሳውን ተቃውሞና አመጽ ተከትሎ፣ አገሪቱን ሲመራ በነበረው፣ በሕወሓት በሚመራው ኢህአዴግ ድርጅት ውስጥ የነበሩ አባላት የህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አለበት በማለት ውስጣዊ እርምጃ መውሰዳቸው ለውጡን እውን እንዲሆን እንዳደረገው አስታውሰዋል።የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉብርሃን ኃይሌ እንደተናገሩት ደግሞ፣ ህዝቡ በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ በተለያዩ ዘመናት፣ ለረጅም ጊዜ ታግሏል፣ በኢህአዴግ ሥርዓተ መንግሥትም በርካቶች ከአገር ውጪም ከአገር ውስጥም በመድረኮችና፣ በትጥቅም ሲታገሉ ቆይተዋል።

ኢህአዴግም ትግሉን ለመግታት፤ የህዝቡን ፍላጎት ለማፈን ብዙ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቶ፣ በድርጅቱ ውስጥ ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፍላጎት የነበረው የለውጥ ኃይል መፈጠሩ 2010 ለተካሄደው ለውጥ መነሻ ሆኗል።ሞትና መፈናቀል ይብቃ፣ ሁሉም ዜጋ እኩል ይታይ፣ አንዱ በይ ሌላው የበይ ተመልካች አይሁን፣ በአገራችን እንደ ሁለተኛና ሶስተኛ ዜጋ አንቆጠር ብሎ ሲታገል የቆየው ህዝብ እነዚህን ችግሮች ያስቀርልኛል በሚል እምነት፣ ለውጡን በጉጉት ሲጠብቀው እንደነበር ያስታወሱትና ለውጥ ስንናፍቅ የነበርን ሰዎች የለውጡን እውን መሆን እንደ ትልቅ በጎ ክስተት ነው የተቀበልነው ያሉት፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ ናቸው። ለውጡ አብዮት እንዳይሆን፣ ተጨማሪ ነውጥ፣ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጥፋትን እንዳያስከትል ያሉት ተቋማትም በሠላማዊ መንገድ ተረጋግተው እንዲቀጥሉ ፍላጎት እንደነበራቸው ይናገራሉ።

አቶ ቶሌራ ለውጡ የመጣበት መንገድያለውን ስርዓት በማሻሻልና ዴሞክራሲያዊ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ለውጥ ማምጣትበሚል መሆኑን ይጠቅሳሉ። ይህም እንደ አገር ከተለመደው የለውጥ ሂደት አንጻር እንግዳ በመሆኑ፣ አብዮት መሰል ለውጥ ሲፈልጉ በነበሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዘንድ ያን ያህል ቅቡልነት አላገኘም። የለውጥ ኃይሉ ከውጪም ከውስጥም ጫና ቢበዛበትም፣ በዚህ መንገድ ወደ ኃላፊነት የመጣው የለውጥ ኃይል በወቅቱ የነበሩትን ችግሮች ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲፈቱ ሰፊ ጥረቶች ማድረጉንና፣ በርካታ እርምጃዎችንም መውሰዱን ይናገራሉ። ለዚህም በፕሬስ ነጻነት ላይ የመጣውን ለውጥ፣ የፖለቲካ እስረኞች መፈታትና ምርጫ ቦርድ የተቋቋመበትን መንገድ በማሳያነት ያነሳሉ።እርሳቸው እንዳሉት፣ ከለውጡ በፊት የነበረው አመራር ውስጡ ዴሞክራሲያዊ አልነበረም። ግንባር ቀደም ሆነው አገሪቱን ሲመሩ ከነበሩ አራት ፓርቲዎች መካከል የበለጠ የመቆጣጠርና የመወሰን ኃላፊነት ሕወሓት ነበረው።

ሌሎች የብሔር ብሔረሰቦች ተወካይ ፓርቲዎች ደግሞ በአገር ደረጃ ተሰሚነት የሌላቸው፣ ውሳኔ የመስጠት መብታው የተገደበና በአጋርነት ተገልለው የቆዩ ናቸው። ይሄና ሌሎችም በድርጅቱ ውስጥ የነበሩ ችግሮች ስር እየሰደዱ መምጣታቸው፣ ለለውጡ ገፊ ምክንያት ሆነዋል። ለውጡ ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እየጣረ ባለበት ወቅት፣ ከለውጥ ኃይሉ ጋር አብሮ መጓዝ ያልቻለውናየለውጥ ኃይሉ በጀመረው መንገድ ወደ ልማት የሚያመራ ከሆነ ጥቅሜ ይቋረጥብኛልየሚል ስጋት ውስጥ የገባው ኃይል ለጦርነት ዳርጎናል፣ ጦርነቱ እንደ አገር ያመጣብን ፈተናም፣ ለውጡ በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይጓዝ አዘግይቶታል።አቶ አዲሱ፣ በሚፈለገው ልክና ፍጥነት ባይሆንም ለውጡ በርካታ ተጨባጭ ስኬቶች ማስመዝገቡን ይናገራሉ። እንደ እርሳቸው ማብራሪያ ከፖለቲካ ሪፎርም አኳያ በኢህአዴግ ጊዜ የነበረው ከፋፋይ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ እሳቤን በአዲስ እይታ መቀየር ተችሏል። አርሶ አደር፣ አርብቶ አደር፣ የከተማ ነዋሪ እና የገጠር ነዋሪ በሚል ሳይለይ ሁሉንም ዜጋ በአንድነት አቅፎ፤ በአንድ ጥላ ስር አሰባስቦ የሚጓዝ ፓርቲ መፈጠሩ ትልቅ የለውጡ ስኬት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

ከዚህም ባለፈ፣ ወዳጅ ጠላት የሚል ከፋፋይ አስተሳሰቦችና ሰነዶች ተቀይረው ወንድማማችነት፣ ህብረ ብሔራዊነትና ኢትዮጵያዊነትን ጥሩ መሠረት ላይ የሚጥል ትርክት መጀመሩም ከስኬቶቹ መካከል ተጠቃሽ ነው። 68 በላይ የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸው፣ ከአገር እንዳይወጡ ታግደው የነበሩ ብዙ ሺህ ሰዎች ከአገር የመውጣት ነጻነታቸውን መጎናጸፋቸው፣ ከመገናኛ ብዙሃን አንጻርም በእስር ሲማቅቁ የነበሩ ጋዜጠኞች መፈታት፣ በርከት ያሉ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎች መከፈት፣ በሚዲያ ማንም ሰው እንደፈለገ ሀሳቡን የሚገልጽበት ሁኔታ መፈጠሩ ከዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አኳያ ትልቅ ስኬት ነው። በርካታ በውጪ አገር የኖሩና የትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገራቸው መመለሳቸው፣ ያላቸውን የፖለቲካ አጀንዳ በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲወያዩና እንዲከራከሩ እድል መስጠቱ፣ አፋኝ የሆኑና የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያጠቡ የፀረ ሽብር እና የበጎ አድራጎትና የሲቪል ማኅበራት ህጎች እንዲሻሻሉ መድረጋቸው በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተስፋ እየፈነጠቀ መሆኑን ያመላክታሉ። በህግ አስከባሪ ተቋማት እንዲሁም፣ በፌደራል መስሪያ ቤቶች የተገኙ ሪፎርሞች፣ ቀደም ሲል የነበረውን ፍትሐዊ የስልጣን ክፍፍል ለማስተካከል የተሄደበት መንገድና ኢትዮጵያን በሚመስል መልኩ ተቋማትን ለማደራጀት የተደረገው ውጤታማ እንቅስቃሴ ከለውጡ ስኬቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። 

ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የተዋቀረበት መንገድ ሁላችንም የምናውቀው ነው ያሉት አቶ አዲሱ፣ የምርጫ ቦርድን የሚመሩት ግለሰብ የትምህርት ዝግጅታቸውንና ከብልጽግና ፓርቲ ስርዓት ውጪ መሆናቸውን ሁሉም ያውቃል፤ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚባል ደረጃ በምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ላይ የጋራ የሆነ አቋም ነው ያላቸው ይህም የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት ለምናደርገው እንቅስቃሴ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥና ሂደቱ ተቋማዊ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችል ነው ይላሉ። በዚህ ሀሳብ ላይ አቶ ግርማ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ ከለውጡ ወዲህ በተካሄደው የምርጫ ሂደት ላይ ምርጫው ወደ ተሻለ እና ወደሚያስማማው ውጤት ያመጣል ብለን በምናስብብት ጊዜ መቶ ከመቶ በማይተናነስ ሁኔታ መንግሥት ጡንቻውን ያሳየበትን ውጤት ነው የመጣው በማለት በምርጫ ሂደት የነበራቸውን ቅሬታ ያነሳሉ።

ከተቋማት ሪፎርም በተጨማሪ ከኢኮኖሚ አኳያም ለውጡ በተደረገበት ማግሥት አገር የሠራተኛ ደመወዝ ለመክፈል እንኳ በሚቸግር ሁኔታ ውስጥ እንደነበረች የሚያስታውሱት አቶ አዲሱ፣ ከነበረብን የእዳ ጫና በመነሳት፣ የኢኮኖሚ መርህን ወደ አገር በቀል ኢኮኖሚ በመቀየር በተሠሩ በርካታ ሥራዎች የተመዘገበው ውጤት ቀላል የሚባል አይደለም ብለዋል። ሊከፈሉ የደረሱ ብድሮችን በማራዘም፣ የተወሰኑ ብድሮችም እንዲሰረዙ በማድረግ፣ ከወዳጅ አገራት ሀብትን በማሰባሰብ የአገራችን ኢኮኖሚ ሳይንገራገጭ እንዲቀጥል የተሄደበት መንገድም ለውጡ በኢኮኖሚው ዘርፍ ያስገኘው ውጤት መሆኑን ይናገራሉ። በኩታ ገጠም እርሻ አገራችን በስንዴ ራሷን እንድትችል በተካሄደው የስንዴ አብዮት አመርቂ ውጤት መምጣቱና በዓመት በአማካይ ስንዴን ከውጪ ለማስገባት ይወጣ የነበረውን አንድ ቢሊየን ዶላር ያስቀረ፣ በጥቂቱም ቢሆን ስንዴን ወደውጪ ለመላክም ያስቻለ አመርቂ ሥራ መሆኑን አንስተው በአረንጓዴ ልማት የተገኘው ውጤትም በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ይዘረዝራሉ።

በመቀጠልም፤ በፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ የነበሩ ውድቀቶችን ለማቃናት በተሠራው ጠንካራ ሥራም የህዳሴ ግድብን የፕሮጀክት አመራር ሥርዓት አስይዞ በሜይቴክ እና በዋናው ኮንትራክተር ሳሊኒ መካከል የነበረውን አለመግባባት በመፍታት፣ አሁን ህዳሴ ውሃ ተሞልቶለት በሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት እንዲጀምር ሆኗልም ብለዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ በኮንሻና በገበታ ለአገር የተገኙ ውጤቶችም ኢትዮጵያ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በጥራት መፈጸም እንደምትችል ያሳዩ ናቸው። ሌላው ትልቅ ስኬት የተመዘገበበት ዘርፍ ዲፕሎማሲ ሲሆን፤ ለዚህም ከኤርትራ ጋር የነበርንበትን ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት በእርቅ መፍታት መቻሉ፣ ጎረቤት አገራት በውስጣቸው ያለውን ቅራኔ በሰላማዊ መንገድ በራሳቸው አቅም እንዲፈታ ኢትዮጵያ የተጫወተችውን ሚና እንዲሁም ህዳሴ ግድብ ላይ የግብጾችን ጫና የተቋቋምንበት ሁኔታ ትላልቅ ማሳያዎች ናቸው።

እነዚህን ነገሮች ሰብሰብ አድርገን በምንመለከትበት ጊዜ የለውጡ ጉዞ አንዱ ገጽታ ትላልቅ ስኬቶች እንደሆኑና የኢትዮጵያ ህዝቦች ለጠየቋቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት መሰረት የሚጥሉ ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል።ከዚህ በተጨማሪ፤ ለውጡ በርካታ ተጨባጭ ስኬቶችን ያስመዘገበ ቢሆንም፣ ጉዞው በበርካታ ፈተናዎችና በወድቆ መነሳት የተሞላ መሆኑን መካድ አይቻልም ያሉት አቶ አዲሱ፣ ፈተናዎቹ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ገጽታ እንዳላቸው በመጥቀስ ያብራራሉ። ከተፈጥሯዊ ፈተናዎች መካከል አንዱ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሲሆን፣ ወረርሽኙ የዓለምን የምርትና ሸቀጥ ገበያ በከፍተኛ ሁኔታ የጎዳ፣ በዓገራችን አጠቃላይ ኢኮኖሚ ላይም ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ሁለተኛው ተፈጥሯዊ ፈተና፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በተከታታይ ለአምስትና ለስድስት ጊዜ በአገራችን ቆላማ አካባቢዎች የተጠበቀው ዝናብ አለመገኘቱና ይህም ከፍተኛ ለሆነ የምግብ እጥረት መዳረጉና የእንስሳት ሀብታችን ላይም ጉዳት ማድረሱ ነው።

ሌላኛው ተፈጥሯዊ ፈተና የአንበጣ ወረርሽኝ ነበር። ወረርሽኙ በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ምርት ላይ ትልቅ ጉዳት ማድረሱም ይታወሳል። የአዋሽ ወንዝ ያስከተለው ጎርፍ በደቡብ ኦሞም ላይ ያደረሰው ጉዳት ቀላል አልነበረም።ከሰው ሰራሽ ፈተናዎች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው ሕወሓት የቀሰቀሰው ጦርነት ነው። በይቅርታና በመደመር እሳቤ እጅ ለእጅ ተያይዘን ያለፈውን አርመን ወደፊት እንራመድ፣ በእኩልነት እንኑር የሚለውን መርህ፣ በርካታ የአገሪቷን የህግ የበላይነት የሚጻረሩ ተግባራትን ሲፈጽም የነበረውሕወሓትእኩልነትን አንሶ እንደመታየት በመቁጠሩናእኔ ያላማሰልኩት አይጣፍጥምየሚል ጽንፍ የያዘ አስተሳሰብን በመያዙ የለውጡ አካል እንዲሆን የተደረገውን ጥረትና የቀረበለትን ተማጽኖ ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። በኋላም ሰሜን እዝ ላይ የወሰደውን አሳዛኝና አስደንጋጭ እርምጃ አስታውሰዋል። አቶ ሙሉብርሃንም፣ የለውጡ ኃይል ከለውጡ በተጻራሪ የቆመውን ኃይል ወደ ውይይት ለማምጣት በርካታ ጥረቶችን ቢያደርግም፣ ቀደም ሲልም በድርጅቱ ውስጥ በነበረው ፍትሐዊ ያልሆነ መዋቅርና ሌሎችም ችግሮች ተደራርበው ወደ ጦርነት እንዳስገቡን ይናገራሉ። ያለፈውን ጉዳታችንን ትተን፣ የኋላውን ተምረንበት ወደፊት እንሂድ፣ ያጠፋም ካለ በይቅርታ እንለፍ፣ ለኢትዮጵያ ስንል በፍቅር እንሻገር በሚለው ተስማምተን የነበረ ቢሆንም፣ በለውጡ ምክንያት ጉዳት ይደርስብኛል ብሎ የሰጋውና ጥቅሜ ተነካብኝ ያለው ኃይል ጡንቻውን እያፈረጠመ መጥቶ የገባንበት ጦርነት በለውጡ የነበረንን ተስፋ አርቆብናል ያሉት አቶ ግርማ፣ ለደረሰው ጥፋት ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ ባለመወጣታችን ተጠያቂዎች ነንም በማለት ቁጭታቸውን ገልፀዋል።

ለውጡ ለትግል መነሻ ለነበሩ የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት፤ አገራችን በዋናነት የምትፈልገውን የዴሞክራሲ ስርኣት መገንባት አልቻለም ያሉት አቶ ሙሉብርሐን፣ የህዝቡ ጥያቄዎች ዛሬም አለመመለስ በቀጣይም ትግል የሚፈልግ መሆኑን ያሳያል ይላሉ። በለውጥ ኃይልና በፀረ ለውጥ ቡድን መካከል የነበረው እስከ ጦርነት ደርሶ፣ በርካታ የሰው መስዋዕትነትና የንብረት ውድመትንም አስከትሎ አብቅቷል ብለዋል።አቶ ሙሉብርሃን እንደተናገሩት፣ መንግሥት ብዙ ስኬቶች አሉት፤ በርካታ ፈተናዎችም ገጥመውታል። ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበት ትግል መነሻው ምክንያት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባትና እንደ አንድ አገር ዜጋ እኩል ሆኖ ለመኖር በመሆኑ ይህን ለማሳካት ብዙ የቤት ሥራ እንደሚቀረው ያሳስባሉ። ለውጡን ራስ ተኮር የሆኑ፣ በቀድሞው ስርዓት የሥነ ምግባር ችግር የነበረባቸውን ሰዎች በመካተታቸው አደጋ ውስጥ ከተውታል ብለው እንደሚገመግሙት ገልፀው፤ ለውጡን መጠቀሚያ የማድረግ አካሄድ ለማንም ስለማይጠቅም መንግሥት ችግሮችን ለማረም ጨከን ያለ እርምጃ መውሰድ፣ መዋቅሩን በቁርጠኝነት በመፈተሽ የሥርዓትና የመዋቅር ለውጥ ሊያደርግ ይገባል የሚል ምክርም ሰጥተዋል።

ከፀረ ሙስና ጋር ተያይዞም ባለፉት ጊዜያት ጠንካራ እርምጃዎች ይወሰዳሉ ብለን ብንጠብቅም ሳይሆን ቀርቷል የሚሉት አቶ ሙሉብርሃን መንግሥት ካለፉ ችግሮች በመማር ሥር ነቀል ለውጥ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ቁርጠኛ አቋም መውሰድ አለበት በማለት አበክረው ያስረዳሉ። እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ በዋናነት፣ አንድ አገር የሚገነባው በህዝቦች ተሳትፎ ነውና ያለፉ መስዋዕትነቶችን ደግመን እንዳንከፍል የሀሳብ የበላይነትን ማክበር፣ ግልጽ ጥያቄዎችን መመለስ፣ ከህዝብ ጥቅም በተቃራኒ የቆሙ ቡድኖችና ግለሰቦችን ስርዓት በማስያዝ ተጠያቂነትን ማስፈን ከመንግሥት ይጠበቃል። ተስፋ ሳንቆርጥ ያሳካናቸውን ድሎች እያሰፋን የሥርዓት ግንባታ ላይ በትኩረት መስራት መቻል አለብን፤ በማለት አሳስበዋል።ጦርነቱን ጨምሮ የገጠሙን ፈተናዎች ቀላል አልነበሩም ያሉት አቶ አዲሱ፣ የውጪ ጫናን ጨምሮ አገራችን ላይ የጂኦ ፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው አገራትና ከታላቁ የህዳሴ ግድብ አኳያ ተዋናይ የሆኑ አካላት የተሳተፉበት ኢትዮጵያን የመበታተን ትላልቅ ሴራዎችና ሙከራዎች መደረጋቸውን አስታውሰዋል።

እነዚህን ሁሉ ፈተናዎች ተቋቁሞ፤ በለውጡ ሂደት የተገኙ ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ፋይዳ ያላቸውን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በተቋማት ሪፎርምና በዴሞክራሲ ዘርፍ የተገኙ ለውጦችን ማስመዝገብ መቻል ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል። ይህንን ማድረግ ያስቻለውየህዝባችን በአንድነት ከለውጥ ኃይሉ ጋር መቆሙ፣ ጦርነቱን ተቋቁሞ ለማለፍ ያደረገው ጥረትና የከፈለው ዋጋ ነውበማለት ለተገኘው ውጤት የህዝቡ ሚና የላቀ ስለነበር ያመሰግናሉ። ሁሉም አካላት ከለውጡ የተገኙትን መልካም ነገሮች እንደ መነሻ ወስደው፣ ያጋጠሙ ፈተናዎችን በአግባቡ በመለየት ትምህርት እየወሰዱና እየፈቱ መሄድ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡ለዘመናት የቆዩ ብዙ ጥያቄዎች ባሉበት አገር ውስጥ በአንድ ጊዜ ምላሽ ማግኘት አይቻልም፤ የሚሉት ደግሞ አቶ ቶሌራ ናቸው። ለውጡን በትዕግስት አለማየትና ቅጽበታዊ ለውጥ እንዲመጣ የመፈለግ አዝማሚያ፣ ለውጡ ለገጠሙት ፈተናዎች መባባስ አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ። እርሳቸው እንደተናገሩት፤ በለውጡ ጉዞ፣ የእኩልነት ጥያቄ ሲያነሱ የነበሩ ህዝቦች ምላሽ ማግኘት ችለዋል። አጋር በሚል ይጠሩ የነበሩ ፓርቲዎችም ወጥ በሆነ ፓርቲ ውስጥ ተደራጅተው በአገር እጣ ፈንታ ላይ ድምጽና ሀሳባቸውን መስጠት መቻላቸው ትልቅ ለውጥ ነው። ሌሎች ያልተመለሱ ጥያቄዎች ደግሞ ጊዜን የሚጠይቁ በመሆናቸው ይህንን ተረድቶ በተቻለ መጠን በሰለጠነ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት ለውጡንም በትዕግስት መጠበቅ ያስፈልጋል የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።ያሳለፍናቸው ፈተናዎች የኢትዮጵያን ህልውና የሚገዳደሩ የውስጥም የውጪም ኃይሎች በስፋት መኖራቸውን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ሰላምን የማስፈን ጉዳይን የአንድ ፓርቲ ብቻ ጉዳይ አድርጎ ባለመውሰድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን እንደሚገባው አቶ አዲሱ ያሳስባሉ።

በዚህም የጸጥታ ተቋሞቻችንን በማጠናከር በትጥቅ ትግልና በጉልበት ሀሳባቸውን ለማስረጽ የሚፈልጉ ኃይሎችን ወደ ሰላም እንዲመጡ ማድረግ፤ ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም መንቀሳቀስ የአገሪቷን ኢኮኖሚ ከነበረው ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ፈተናዎች መልሶ እንዲያገግምና ወደ ተሻለ አካሄድ እንዲሄድ ማድረግ እንዲሁም በምርትና ምርታማነት ላይ አተኩረን የምንቀሳቀስበትን ሁኔታ በደንብ ማጤን እንደሚያሻ ያነሳሉ።አቶ ግርማ በበኩላቸው፣ የአገርን ሰላም ለማስፈን እንደ አገር ያሉብንን ችግሮች ለመፍታትና የተሻለ የለውጥ ሂደት ለመዘርጋት አገራዊ ምክክር መድረኩን ቁልፍ አድርገው በተስፋ እንደሚጠብቁት ተናግረዋል። እርሳቸው እንደተናገሩት፣ እንደ አገር በዜጎች መካከል ስምምነት ኖሮ በአንድነት ለመቆም ፍላጎቱ ካለን አገራዊ የምክክር መድረኩን ልንጠቀምበት፣ በቅን ልቦናም ልንሳተፍበት ይገባል። መንግሥትም በዚህ የምክክር መድረክ ምንም አይነት አሻጥር ሳይሰራ ለስኬቱ መስራት ይጠበቅበታል። ምክክሩ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ያደርሰናል ብለን መጠበቅ የለብንም ያሉት አቶ ግርማ በመሠረታዊነት ልንግባባባቸው በምንችላቸው ጉዳዮች ላይ ተግባብተን፣ በምንወዳደርባቸው ጉዳዮች ላይ ደግሞ ተወዳድረን ብንቀጥል አገር ወደ ሰላም ትሄዳለች ብዬ አስባለሁ ብለዋል።አገራዊ ምክክሩ፣ አሁን በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉትን ጥያቄዎች ወደ መድረክ በማውጣት፣ ህዝብ በግልጽ እንዲወያይና የሚነሱ ችግሮችም መፍትሔ እንዲበጅላቸው ለማስቻል፣ ችግሮቻችንን በተለመደው አካሄድ ሳይሆን በሰላማዊ ሁኔታ ለመፍታት የሚያስችል አዲስ መንገድ ለመክፈት እድል የሚሰጠን እንደሆነ አቶ ቶሌራ እምነት አላቸው።

ልክ እንደ አቶ ግርማ ሁሉ፣ በምክክሩ ሂደት በአገራችን ያሉ ችግሮች መሉ በሙሉና ወዲያው መፍትሔ ያገኛሉ ብሎ መጠበቅ እንደማይገባም ያሳስባሉ። ያሉብን ችግሮች በሁሉም አካል ተሳትፎ እንጂ በአንድ ፓርቲ ብቻ የሚፈቱ እንዳልሆኑ ከግንዛቤ ማስገባትና የሌላውን ሐሳብ ለማዳመጥም ከሁሉም ዘንድ ዝግጁነት ሊኖር እንደሚገባም አስምረውበታል።አገራችን ዘመናዊት ኢትዮጵያ ሆና ከተመሰረተችበትና የሥርዐተ መንግሥት ግንባታ ካካሄድንበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ቅራኔዎች፣ ጦርነቶች፣ ጠባሳዎች መኖራቸውን ያነሱት አቶ አዲሱ፣ እንደ ለውጥ መንግሥት እነዚህ ጠባሳዎች በፍቅርና በይቅርታ መታከም አለባቸው ብለን እናምናለን። በፖለቲካችን፣ በአስተዳደር ሥርዓታችን፣ በምልክቶቻችን፣ በሰንደቅ ዓላማችን፣ በታሪካችንና በመጻዒ እድላችንም ላይ የማይታረቁ የሚመስሉ ጫፍ የረገጡ ትርክቶች ላይ ከመግባባት አኳያ ያሉብንን ሰፋፊ ክፍተቶች ሞልቶና ችግሮችንም አርቆ ወደፊት መጓዝ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በመቀጠልም፤ እኛ ባለፍንባቸው አይነት ቀውሶች አልፈው ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት የተሻገሩ እንደ ሩዋንዳና ደቡብ አፍሪካ የመሳሰሉ አገራትን ታሪክ ካየን ችግሮቻቸውን በጥናት ለይተው፣ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ እየተወያዩ፣ መግባባት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ እየተግባቡ፣ ህዝበ ውሳኔ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ህዝበ ውሳኔ እያደረጉ ነው ችግሮቻቸውን እየፈቱ የሄዱት። እኛም ከዚህ ተምረን በኢትዮጵያዊነት ባጎለበትናቸው አገር በቀል እሴቶቻችንና ባህሎቻችንን በመጠቀም ጭምር የምክክር ሂደቱን በአግባቡ ማስኬድና ማሳካት አለብንም ብለዋል።አያይዘውም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ማንኛውም አካል ሐሳቡን በነጻነት እንዲያንሸራሽር የፖለቲካ ምህዳሩ በመስፋቱና፣ የመገናኛ ብዙኃንም ለዚህ ምቹ በመሆናቸው የትኛውም ቡድን የራሱን ፍላጎት ለማሟላት ጠብመንጃ ማንሳት የለበትም። የገጠሙን የሠላም ማጣት ክስተቶች ከዚህ በኋላ ደግመው እንዳይከሰቱ ትምህርት ልንወስድባቸውና የዴሞክራሲ ስርዓት ለመትከል የጀመርናቸውን መንገዶች በደንብ ይዘናቸው ሀሳቦች የሚንሸራሸሩበት ሁኔታ ላይ በመስራት ዴሞክራሲን የማስፈኑ ተግባር ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል።እንደ ብልፅግና በአገራችን ብሔራዊ ምክክር እንዲደረግ ሙሉ ቁርጠኝነት አለን ያሉት አቶ አዲሱ፣ ኮሚሽኑን ከሚመሩ ሰዎች ጥቆማ ጀምሮ ኮሚሽኑን ከማዋቀር እና ከማደራጀት አንጻር ግልጽነት በተሞላበት፣ ሰፊውን ህዝብ ባሳተፈና ተጠሪነቱም ለፓርላማ ሆኖ እንዲቋቋም የተሄደበት ሂደት ለዚህ ማሳያ ነው ይላሉ።

በቀጣይ በምክክር ሂደቱም የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ በታላቅ ቆራጥነት እንቀሳቀሳለን ብለዋል። በዚህም ደግሞ አገራችን ከፖለቲካ ሁከት፣ ከጎዳና ላይ ነውጥ፣ ከጠብመንጃ አፈሙዝ ተላቃ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት እንደምትመጣ፤ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደቱም ወደተሻለና ወሳኝ ወደሆነ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግር ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል። አቶ ሙሉብርሃንም ብሔራዊ ምክክሩ ላይ ትልቅ ተስፋ እንዳላቸው ያረጋግጣሉ። እርሳቸው እንደተናገሩት አገር የሚገነባው በውይይት ነው። የምክክር ኮሚሽኑ በሚገባ ጠንክሮ ከወጣና የችግሮች ባለቤት የሆነውን ህዝብ አሳታፊ ከሆነ፤ አገርን ማዕከል ካደረገ፣ ለአንድነታችን ስጋት የሆኑ ችግሮችን በቅደም ተከተል አስቀምጠን እየተወያየን ከሄድን መፍትሔ የሌለው ችግር ስለሌለ አንድነታችን ላይ የተጋረጡ ችግሮቻችንን እየፈታን ለመጓዝ ትልቅ ተስፋ አለን።

በተለይም የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጭ ብሎ የመነጋገር እድል አግኝቶ አያውቅም የሚሉት አቶ ሙሉብርሃን የኢትዮጵያ ህዝብ ችግሮቹን የሚፈታበት የበርካታ እሴቶች ባለቤት መሆኑን ያስቀምጣሉ። እስካሁንም በፖለቲካው የደረሰበትን በርካታ ሸፍጦች አልፎ በሰላም መኖር የቻለው አስተዋይ ህዝብ በመሆኑ ነውና የምክክር ሂደቱ ለህዝቡ የሚናገርበትን እድል ከከፈተ፣ በርካታ ችግሮቻችንን ይፈታሉ ብለው ያምናሉ።የለውጡ ኃይል ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚችለው በውስጡ ያለውን አንድነት መጠበቅ ሲችል ነው። ይህ አንድነት በውስጡ ከሌለ ለውጡን ማስቀጠል አይችልም በሚል ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚነሳውን አስተያየት አስመልክቶ አቶ አዲሱበብልጽግና ፓርቲ ውስጥ መሠረታዊ የሆነ የአይዲዮሎጂና የአስተሳሰብ አንድነት ችግር የለም። የብልጽግና አመራርም ሆነ የብልጽግና አባላት የምንገነባው ዴሞክራሲን እስከሆነ ድረስ የተለያዩ ሐሳቦች ሲሰነዘሩ፣ የተለያዩ እይታዎች ሲንጸባረቁ መመልከት የዴሞክራሲ ሥርዓት አንዱ ባህሪ ነው ብለን ነው የምናስበው።

የውስጥ ፓርቲ ሂደታችንም ፍጹም ዴሞክራሲያዊ ነው። በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የመሰለውን ሐሳብ በነጻነት የማራመድ፣ የመደመጥ መብት አለው። ብቻ ሳይሆን ሐሳቡ ክርክር ተደርጎበት በድምጽ ብልጫ የተወሰነውን ውሳኔ የፓርቲው ዲሲፕሊን አድርጎ የመያዝ ልምድም አለው። ከዚህ አኳያ እስካሁን ባለፍንባቸው ሂደቶች ፓርቲው በተዋቀረበት አጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችሏልየሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ይህ ማለት ግን የፓርቲው የውስጥ አንድነት ሙሉ በሙሉ አልቆለት ተደራጅቶ የወጣ ነው ማለት አይቻልም።

ብልጽግና በአዲስ እሳቤ በይዘትም በቅርጽም አዲስ የአደረጃጀት ለውጥ አድርጎ፣ በወንድማማችነትና በብሔራዊ አንድነት እየተንቀሳቀሰ ያለ ፓርቲ ነው። ከዚህ እይታ የወጡ ሀሳቦች ሲንጸባረቁ በውስጥ ፓርቲ አሰራር እያየናቸው እያራቅናቸው ያመጣናቸው በመሆኑ ከጊዜ ወደጊዜ አንድነቱ እየጠነከረ መጥቷል ብለዋል።በመጨረሻም፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩ መከፈቱን ተከትሎ ከተፈጠረው የማኅበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ጽንፈኛ ሚዲያዎች እንደፈለጉ ሳያገናዝቡ የሚያሰራጯቸውን ሐሰተኛ መረጃዎችን እንደ እውነት የመውሰድ ዝንባሌ ትልቅ ፈተና እየሆነብን ነው ያሉት አቶ አዲሱ እንደ አገር ይህን መቀየርና መረጃዎች አጣርቶ የመጠቀም ልምድ መዳበር እንዳለበት መክረዋል።

ዘመን መጽሔት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም

Recommended For You