መጋቢት 24/2003 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ የተጣለው ታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ በ13 ተርባይኖች 5 ሺህ150 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል። በዓመት ደግሞ 15 ሺህ 760 ጊጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ የማመንጨት አቅም አለው:: ፕሮጀክቱ በዓለም ካሉ ከፍተኛ የኃይል ማመንጫዎች ተርታ የሚሰለፍ ነው።
ፕሮጀክቱ ይፋ ሲደረግ አብዛኛው በጀቷ በብድርና በድጎማ የምትደገፈው አገራችን ይህን ትልቅ ግድብ ለመገንባት የሚችል የገንዘብ አቅም እንዳልነበራት ይታወቃል። ይህ ወደ አራትና አምስት ቢሊየን ዶላር የሚፈጅ ታላቅ ግድብ ደግሞ ከዓለም ባንክና ሌሎች ከዓለም የገንዘብ ድርጅቶች፣ አበዳሪ ተቋማት እና ከምዕራብ አገራት ድጋፍ ውጪ ግንባታው የሚታሰብ አልነበረም የሚሉት አቶ ኃይሉ አብርሃም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ም/ቤት ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት፣ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው።
ከእነዚህ አበዳሪ ተቋማትና አገራት የገንዘብ ብድርና እርዳታ ድጋፍ ለማግኘት ደግሞ የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ አገራት፣ በተለይም ወንዙ የሚሻገርባቸው የሱዳንና ግብጽ ስምምነትን ማግኘት የግድ ነበር። ግብጽ ደግሞ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ እንዲገነባ በምንም ዓይነት መንገድ አትፈልግም። ስለሆነም መንግስት ከድህነት ለመላቀቅ ከቁጥ ቁጥ ፕሮጀክቶች በመውጣት ትላልቆቹን እንድፈር በሚል ሃሳብ፣ በተለይም በሕዝብ ተሳትፎ ከፍተኛ እምነትና አቋም በመያዝ፣ ገንዘቡም፣ ጉልበቱም፣ ዕውቀቱም፣ ሁሉም ነገር ራሳችን ሆነን ግድቡን እንገነባዋለን የሚል ከባድ፣ ግን ደግሞ ቆራጥ ውሳኔ በመወሰን ወደ ተግባር ገብቷል።
እንደ አቶ ኃይሉ ገለጻ፣ ይህን በታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ ግንባታ የመንግስትን ቆራጥ ውሳኔ ተከትሎ በመላው የአገራችን ክልሎች፣ ዞኖች፣ ከተሞችና ወረዳዎች ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ የሆነ የድጋፍ ሰላማዊ ስልፍ ተከናውኗል። በሁሉም ደጋፊ አካል የተስተጋባው የድጋፍ ድምጽ ደግሞ እንችላለን፣ እንገነባዋለን የሚል ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ማለት በሚቻልበት ሁኔታ በአገራችን የይቻላል መንፈስ በጋራ የተፈጠረበት ወቅትም ነበር። ለልማት ከፍተኛ የሕዝብ የተሳትፎ ማዕበል እና የሰው ጎርፍ የታየበት ሁኔታም ተስተውሏል። ይህ የሕዝብ ከፍተኛ ድጋፍ የሚያመለክተውም በልማት ጉዳይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪ ተደርጎለት በከፍተኛ ስሜት የተነሳሳበት ጊዜ እና በደረጃውም በጣም ትልቁ መሆኑን ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሕዝቡ ለኢትዮጵያ ታላቁ የዓባይ ግድብ ግንባታ ዕውን መሆን የሚያደርገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ያልተቋረጠና በሞራል የታጀበ ነበር። ሞራሉ ደግሞ መንግስት ካቀረበው የልማት ጥያቄ ባሻገር፣ የፖለቲካ ድጋፍ ምላሽም ጭምር ነው።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ታላቁ የዓባይ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያውያንን ያለ ልዩነት በፖለቲካ አንድ ማድረግ ችሏል። መላ ህብረተሰቡንም በዕድሜ፣ በጾታ፣ በሃይማኖት፣በብሔር እና በቋንቋ ሳይለይ በአንድ አሰልፎታል። የኢትዮጵያን ሕዝብም በኑሮ ደረጃ ሳይከፋፈል በአንድነት እንገነባዋለን የሚል ወጥ አቋም እንዲይዝ አድርጎታል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ደግሞ በገንዘብ፣ በንብረት / በዓይነት/፣ በጉልበት፣ በዕውቀት እና በፐብሊክ ዲፕሎማሲ የተገለጸ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ኃይሉ፣ ባለሀብቱ፣ የመንግስት ሰራተኛው፣ የግል ድርጅት ሰራተኛ፣ ተማሪ፣ አርሶ አደር፣ የፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ ዲያስፖራው፣ በአጠቃላይ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ ሞራልና ወኔ ድጋፍ ለማድረግ ተረባርቧል። በደመወዝ የሚተዳደረው የሕብረተሰብ ክፍል የወርና የሁለት ወር ደመወዙን በዓመት ለመክፈል በፈቃደኝነት በመወሰን መክፈል ችሏል። ሌላው የሕብረተሰብ ክፍልም እንደ አቅሙና የገቢ መጠኑ የየድርሻውን ተወጥቷል ብለዋል።
በዓይነት ከሚደረጉ የድጋፍ ዓይነቶች መካከል በዋናነት ወርቅ፣ ቤት፣ መኪና፣ ባጃጅ፣ ሞተር ሳይክል፣ እንስሳት /በተለይም ግመልና ሰንጋ/፣ እህል /በተለይም ሰሊጥ/፣ አትክልትና ፍራፍሬ/በተለይም ቡና/፣ ጨው፣ የመሳሰሉት በብዛት ይገኙበታል። አርብቶ አደሩ በተለይ ደግሞ እንደ አፋር በመሳሰሉ አካባቢዎች ለግመሎቻቸው ያላቸው ፍቅር በጣም ከፍተኛ ቢሆንም ለታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ ግንባታ ግን የሚሳሱላቸውን ግመሎች ከመለገስ አላገዳቸውም።
ለታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ ከተከናወኑ የሕዝብ ተሳትፎ ተግባራት ውስጥ በጉልበት የተካሄዱ የሕዝብ ድጋፎች ይጠቀሳሉ። በዚህ ረገድ የተከናወነው ተግባር ግድቡ በደለል እንዳይሞላ አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን በማስተባበር ጠንካራ የተፋሰስ ስራ መስራት መቻሉ ነው። ከግብርና ሚኒስቴር በተገኘው መረጃ መሰረት ማህበረሰቡ “ለግድቤ” በማለት በአማካይ በዓመት 30ቀን ለስራ አውሏል። በዚህ የሕዝብ ተሳትፎ ደግሞ ከ120 ቢሊየን ብር በላይ ሊገመት የሚችል የሰው ኃይል ጉልበት በአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ በተፋሰስ ስራ ላይ ውሏል።
በዕውቀት ከተደረጉ ሕዝባዊ ድጋፎች መካከል ደግሞ አርቲስቶች፣ የኪነ ጥበባት ባለሙያዎች፣ የሙዚቃ ሰዎች፣ ኮሚዲያን፣ ወዘተ የተለያዩ ማስታወቂያዎችን በመስራት፣ የሙዚቃና የስነ ጽሁፍ ምሽት፣ ሁነቶችን እና ኮንሰርቶችን የመሳሰሉትን በማዘጋጀት፣ ሕዝብ በማነሳሳት፣ በመቀስቀስና በማነቃቃት የተጀመረው የሕዝብ ተሳትፎ ተጋግሎ በሞራል እንዲቀጥል ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል።
በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ረገድ፣ ዲያስፖራው ለታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ ድምጽ ሆኖ ላለፉት አመታት በመከራከር ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያለማቋረጥ አስተጋብቷል። በተለያዩ መንገዶች ግድቡ ላይ በሚከሰቱ አሉታዊ ነገሮች ሁሉ፣ ዲያስፖራው ለመላው ዓለም ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነት መርህን የተከተለ ስለመሆኑ፣ ግንባታው ደግሞ ለተፋሰሱ አገራት ለጋራ ጥቅም እንደሆነ በማስረዳት ተሟግቷል። ይሁን እንጂ የተፋሰሱ አገራት በተለይም ግብጽ ግድቡን በዚህ ደረጃ ልታየው አልቻለችም። በመሆኑም ይህን የግብጽ የተዛባ አቋም ተከትሎ ብዙ አገራት የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይኖራቸው፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ መላ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ጊዜ፣ ምሁራን በተለያዩ እንደ ጆርናል በመሳሰሉ ህትመቶች ለማስረዳት ጥረት አድርገዋል። ከዚህ ባለፈ በአውሮፓና አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት ጭምር ለዓባይ ግድብ ያልተቋረጠ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥም አንዱ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግብጽ ግድቡን ታደባየዋለች ብለው በተናገሩ ጊዜ ዋሽንግተን ላይ ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት የፕሬዝዳንት ትራምፕን ንግግር መቃወማቸውን ያስታወሱት አቶ ኃይሉ፣ በዚህ መልኩ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ግድብ እውን መሆን በመቆርቆር ፊርማ እያሰባሰቡ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ለተለያዩ ዲፕሎማቶች አስገብተዋል። በአካል በማነጋገር ጭምር የኢትዮጵያን ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም መርህ ለማስረዳት እና የተቻላቸውን ተጽዕኖ ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ አገራችን በተከሰሰችበት ወቅት፣ “እኔ የውሃ ግድብ እንጂ የኒኩለር ማብላያ አይደለም እየገነባሁት ያለሁት” ብላ ስትመልስ፣ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ኒዮወርክ አደባባይ ላይ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ውጭ አድረዋል። በተለያየ መንገድ ዲያስፖራው አቅሙ የቻለውን ያህል ለታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ ከመንግስት ጎን ቆሟል። ይህ ደግሞ ለመደበኛው የመንግስት ዲፕሎማሲ ግንኙነት ከፍተኛ እገዛ አድርጓል ብለዋል።
አቶ ኃይሉ አያይዘውም፣ ዲያስፖራው ግድቡን በመደገፍ በዓለም አቀፍ መድረኮች ከሚሟገተው እና ከሚከራከረው በላይ፣ በተለይም በአረብ አገራት ያሉ የሱዳን ጋዜጠኞችን ጨምሮ፣ በተደጋጋሚ በግብጽ እና በቱርክ በአረብኛ ሚዲያዎች እና በሶሻል ሚዲያዎች ላይ ሳይቀር የግድቡን ምንነት ለማስረዳት ጥረት አድርገዋል። የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ ግብጽን እንደማይጎዳ፣ ግድቡ ለጋራ ተጠቃሚነት የሚገነባ እንደሆነ፣ በቡድን ተደራጅተው ጭምር መሟገት መቻላቸውን ያስረዳሉ። ከእነዚህ ተዋናዮች መካከል አንዱ የበጎ ሰው ሽልማት የተሸለመው መሀመድ አላሩሲ እንደሚገኝበትም ገልጸዋል።
ይህንን የሕዝብ ከፍተኛ የድጋፍ መነሳሳት መነሻ በማድረግም መንግስት የድጋፍ ብሩን ወስዶ ከማስቀረት ይልቅ ድጋፍ አድራጊው ብሩን መልሶ የሚያገኝበትን ሁኔታ በመፍጠር የታላቁ ዓባይ ግድብ ቦንድ አሰራርን ይፋ አድርጓል። ቦንድ ማለት ዘመናዊ የባንክ ሲስተም ሲሆን፣ እንደ ገንዘብ ሆኖ ለብድርም ሆነ ለሌላ አገልግሎት ማዋል የሚያስችል አሰራር ነው። በዚያ ላይ በቦንድ የሚቀመጠው ገንዘብ በወቅቱ ከነበረው የባንክ ተቀማጭ ብር በተሻለ ሁኔታ ወለዱ ከፍ ያለ ነበር። የቦንዱ ዓላማም የአገሪቱን የቁጠባ ባህል ለማሳደግ፣ እየቆጠብን – እንገነባለን፣ እየገነባን እንቆጥባለን፣ ቁጠባው – ለግንባታው፣ ግንባታው ለቁጠባው፣ እየተጋገዝን ኢኮኖሚያችንን እናሳድጋለን፣ ግድባችንም እንገነባለን የሚል ሃሳብን የያዘ ነው።
በመሆኑም የታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ ቦንድ በገንዘብ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ውክልና እንዲሸጥ እና እንዲያስተዳደር ነው የተደረገው። ስርጭቱ እየተከናወነ የሚገኘው ግን በርካታ ቅርንጫፍ ባለው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጭምር ነው። ባንኮች በማይደርሱባቸው የአገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች ደግሞ እንደ አብቁተ፣ ኦሞ፣ ደደቢት እና በመሳሰሉ ወደ ሰባት በሚደርሱ ማይክሮ የፋይናንስ ተቋማት አማካኝነት ቦንዱ እንዲሸጥ በመደረግ ላይ ይገኛል።
ቦንዱ ለገዢው የሚመለስበት አነስተኛው የቆይታ ጊዜ አምስት አመት ነው። ለዓባይ ግድብ ድጋፍ እያደረጉ፣ የቁጠባ ባህልንም እያሳደጉ፣ ከቁጠባ ደግሞ ወለድ ማግኘት መቻሉ ደጋፊውን የበለጠ እንዲበረታታ አድርጎታል። በቦንዱ አሰራር አንዳንዱ ከቁጠባው ወለድ አልፈልግም ሲል፣ ሌላው ደግሞ ቦንዱን ከነወለዱ ያለ ምንም ችግር የመውሰድ መብቱ ተጠብቆለታል። የቁጠባ ጊዜው አልቆ ብሩን ሲወስድ ደግሞ በደጋሚ እንደገና ኩፖን በመግዛት ድጋፉን ያስቀጠለውም በርካታ ነው።
አቶ ኃይሉ እንደሚያስረዱት፣ ከገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶች መካከል አንዱ በታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ም/ቤት ጽ/ቤት የተዘጋጀው 8100A የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ነው። በዚህ ፕሮግራም ገንዘብ እየተሰበሰበ በወቅቱ ሕዝቡ በዓይነት የለገሳቸው ሀብቶች አሸናፊዎች እንዲሸለሙ ተደርጓል። በዚህም ከስድስት ያላነሱ መኪናዎችና መኖሪያ ቤቶች ለሽልማት ቀርበዋል። በተለይ ደግሞ በዓይነት ድጋፍ የሚደረጉና ለሽልማት የሚቀርቡት መኪናዎች፣ በአብዛኛው በአረብ አገራት የሚኖሩ ሴት ኢትዮጵያውያን ገዝተው የሚልኳቸው መኪኖች ነበሩ።
ሌላው የዓባይ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ የብሔር ብሔረሰቦች ተብሎ የተሰየመው ዋንጫ ነው። ይህ ዋንጫ ከክልል ወደ ክልል በዞረ ቁጥር ከፍተኛ ሕዝባዊ ድጋፍ በማነሳሳት፣ በቦንድም ሆነ በስጦታ ከፍተኛ ሀብት በማስገኘት ላይ ይገኛል። ዋንጫው በየክልሎቹ እየተዘዋወረ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ 33 ሚሊየን፣ ከአፋር 71ሚሊየን፣ ከትግራይ 89 ሚሊየን፣ ከአማራ 432 ሚሊየን፣ ከኦሮሚያ 607 ሚሊየን፣ ከደቡብ አንድ ነጥብ 6 ቢሊየን የሚጠጋ፣ ከሱማሌ 18 ሚሊየን ሀብት አሰባስቧል። ዋንጫው ጋምቤላ ክልል ገና ሳይሄድ፣ ኦሮሚያ ክልል በድጋሚ ይሰጠኝ በማለት ዋንጫውን ወስዶ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ 1 ቢሊየን 50 ሚሊየን ብር ማሰባሰብ ችሏል።
ከዚህ በተጨማሪ ጎልፍ ክለብ ሻምፒዮን የሆነበትን በጣም ትልቅ ዋንጫ የዓባይ ግድቡን የብሔር ብሔረሰብ ዋንጫ ይተካ፣ ሀብትም ይሰባሰብበት ብለው በስጦታ ያበረከቱት ነው። ዋንጫውን መከላከያ ሰራዊትና ፖሊስ ለዓባይ ግድብ ዝግጁ ነኝ በማለት “የሰላማዊ ኃይል ሰልፍ” በሚል ባካሄዱት የእግር ጉዞ ላይ ተሰጥቶ፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከመከላከያ ሰራዊት 167 ሚሊየን ብር ሊሰባሰብበት ችሏል።
“የዓባይ ግድብ ችቦ ማቀጣጣል” የሚለው እና ዳግም የዓድዋ ድል በሚል ዓባይ ግድብ ላይ የተለኮሰው ችቦም ከገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶች መካከል አንዱ ነበር። ችቦው ጋምቤላ ላይ ብቻ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወርቅን፣ ቡናን፣ የቀንድ ከብትን ጨምሮ አንድ ሚሊየን የሚጠጋ ብር ድጋፍ አሰባስቧል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ በሕይወት እያለ ያደገችና የበለጸገች የነገይቱን ኢትዮጵያን ለማየት በሚጓጓ ዜጋ ብቻ የተገደበ አልነበረም። ለግንባታው ዕውን መሆን ካላቸው ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ ሙታን ሳይቀሩ የግንባታውን መጨረሻ ማየት ባይችሉም ከሀብትና ንብረታቸው ላይ እንዲሰጥላቸው የተናዘዙ ሰዎች ጭምር ነበር። የአዲስ አበባ ነዋሪ የነበሩት አቶ ታደሰ ኃይሉ በምሳሌነት ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው። ግለሰቡ በሞት አፋፍ ላይ ሳሉ ከንብረቴ ላይ ለግድቡ አስር ከመቶ የሚሆነው ይሰጥልኝ ብለው ተናዘው ነበር። ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቶ ከአምስት ዓመት በኋላ ውሳኔ ሲያገኝ ከ124,500 ብር በላይ ገቢ ሆኗል። በዚህ ዓመትም አሜሪካን አገር አቶ ውብሸት አሰፋ የተባሉ አገር ወዳድ ግለሰብ በሞት አፋፍ ላይ እያሉ ለወንድሞቻቸው ከንብረቴ ላይ ለዓባይ ግድብ 100ሺ ዶላር ይሰጥልኝ ብለው ተናዘው አርፈዋል። በኑዛዜው መሰረት ዶላሩ ገቢ ተደርጎ በቤተሰቦቻቸው አማካኝነት ማስረጃውን ማግኘት ተችሏል። ከጀርመን አገር የመጡ አንዲት እናት ደግሞ የአባታቸውን የሙት ዓመት ድግስ ገንዘብ ለምን ለዓባይ ግድብ አናውለውም በሚል፣ ከቤተሰብ ጋር በመመካከር ወስነው በስጦታ አበርክተዋል።
በአጠቃላይ ለታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ በደጋፍ መልክ ያልተሰጠ ነገር የለም። ሰው ያለውን ሁሉ በመስጠት ለግድቡ በከፍተኛ ሁኔታ ተረባርቧል። ህጻናት ሳይቀሩ ከማስቲካና ከከረሜላ ወጪያቸው ላይ እያዋጡ ቦንድ ገዝተዋል። ከዚያም አልፈው፣ “እኛ የአባይ ፈርጥ ነን” በማለት አጀንዳ ቀርጸው፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ ጎረቤቶቻቸውን፣ መምህራኖቻቸውን፣ ቦንድ እንዲገዙ አድርገዋል። የመንግስት ሰራተኛው፣ ባለሀብቱ፣ ዲያስፖራው ርቀትና ድንበር ሳያግድበው፣ በተለይም ድሃው ሕብረተሰብ ከሌለው ላይ ከዕለት ቁርሱ፣ ከዓመት ልብሱ ቀንሶ ደግፏል። መከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስና የክልሎች የጸጥታ ኃይሎች ግድቡን ከመጠበቅ አልፈው በተደጋጋሚ ሳይሰለቹ ከደመወዛቸው ለግሰዋል። አገራችን አሁን ባለው የለውጥ ሂደት ውስጥ በየቦታው በፖለቲካ ግጭት ምክንያት የጸጥታ ችግር እዚህም እዚያም በተበራከተበት ወቅት እንኳ ሳይቀር ለግድቡ የሚደረገው ድጋፍ ሳይበርድና ግለቱ ሳይቀንስ መቀጠሉ የሚገርም ነው የሚሉት አቶ ኃይሉ፣ እስከ ዛሬ ድረስ በተደረገው ሁሉን አቀፍ የድጋፍ ርብርብ 17 ቢሊየን 650 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሆኑን ያብራራሉ።
አቶ ኃይሉ እንዳስረዱት፣ ከታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ ድጋፍ ውስጥ የዲያስፖራው ድጋፍ አንድ ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ይሆናል። በ8100A የተሰበሰበው ብር ደግሞ ወደ 520 ሚሊየን ይደርሳል። በዘንድሮው ዓመት በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ የተሰበሰበው ከ867 ሚሊየን 191 ሺህ ብር በላይ ነው። ከዚህ ውስጥ ወደ 75 ሚሊየን የሚሆነው ብር በ8100A የተሰበሰበ ነው። ከዲያስፖራው ድጋፍ የአምናው ከፍተኛ እንደነበር መረጃው ያመለክታል። ምክንያቱ ደግሞ ገንዘቡ የተሰበሰበው በኢንተርኔት አፕ መሆኑ ነበር። አፖቹ ሁለት ሲሆኑ ግድቡ የእኔ ነው /It is my dam/ እና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የእኔ ነው /GERD is mine/ የሚሉ ነበሩ። አፖቹ ደግሞ ዲያስፖራውን ከስራ ጊዜው ውጪ ሲዝናና በቀጥታ ለማግኘት የሚያስችሉ በመሆኑ፣ በነጻነት የፈለገውን እና ደስ ያለውን እንዲለግስ ዕድል ፈጥረውለታል።
የታላቁን የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ እየገነባው ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ብቻውን ቢሆን ኖሮ የግብጽ ሕዝብና መንግስት ቀደም ሲል ይፈጽሙት እንደነበረው ሁሉ፣ ከፍተኛ ተንኮልና አሻጥር በመስራት ግንባታውን ለማስቆም ጥረት ያደርጉ ነበር። ነገር ግን ግድቡ እየተገነባ የሚገኘው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የግድቡ ባለቤት ሆኖ ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ መንግስት እንዳይዘናጋ እና በግንባታው ወደኋላ እንዳይል ከፍተኛ ጉልበት ሆኖታል። ይህም ለግብጽም ሆነ ለሌላው ከአንድ አገር ሕዝብ ጋር ተጋጭቶ ምንም ነገር ማድረግ እንደማይቻል ትልቅ መልዕክት አስተላልፏል። በተለይም በፐብሊክ ዲፕሎማሲው በአገር ውስጥና በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ አንድ ሆኖ መነሳቱ፣ ግድቡን መገንባት አትችሉም ከሚል ቀጥተኛ ተቃውሞ ተነስቶ፣ ግንባታው ደረጃውን የጠበቀ አይደለም እና የተገነባው ይፈርሳል የሚሉ የተለያዩ ውጫዊ ጫናዎችን አገራችን አሸናፊ ሆና እንድትወጣ አስችሏታል።
ሕብረተሰቡ መጀመሪያ አካባቢ በቦንድ አሰራር ላይ ዕምነት አልነበረውም። ቦንዱን ይገዛ የነበረውም በስሜት ተነሳስቶ እና ተገፋፍቶ ነበር። በኋላ ግን አሰራሩ ምን እንደሆነ ሲገነዘብ ከፍተኛ እምነት ጥሎበታል። በተለይም አምስት አመት ሞልቶት ወለዱን ሲያገኝና የቦንዱ ብር ሲመለስለት መተማመኑን አሳድጎለታል። ከለውጡ በፊት በውጭ አገር የሚኖሩ ዲያስፖራዎችም ቢሆኑ መንግስትን ደግፈው የሚያውቁበት ምንም ዓይነት አጀንዳ እንዳልነበራቸው ይታወቃል። የዲያስፖራ አባላቱ አብዛኛዎቹ ከአገራቸው የወጡት በተለያዩ ምክንያቶች ከፍቷቸው በመሰደድ ነው። አንዳንዶቹ በኢህአፓ ወቅት በነበረው የፖለቲካ ግጭት ከደርግ መንግስት ጋር በተያያዘ፣ በኢህአዴግም ጊዜ በተለያዩ የፖለቲካ አለመግባባት ምክንያቶች ተማረው ከአገር የወጡ ስለነበሩ መንግስት የሚሰራውን ስራ ሁሉ የሚያዩት በጥርጣሬ ነበር። ከዚህ የተነሳ የታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ ይፋ ሲደረግ በዲያስፖራው ዘንድ የተፈጠረው መከፋፈል ነው። በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ መሰራቱን ሁሉም ያለ ልዩነት ቢደግፉትም፣ መንግስት በግድቡ አሳቦ ዶላር ለመሰብሰብ ነው የሚል አስተሳስብ የነበራቸው ቀላል አልነበሩም። በዚህም ምክንያት አሜሪካን አገር ከተሰበሰበው ገንዘብ ስድስት ሚሊየን ዶላር የሚደርስ እንዲመለስ የተደረገበት ሁኔታም ነበረ። ይሁን እንጂ ከለውጡ በኋላ ሁሉም የዲያስፖራ አባላት ያለ ልዩነት በከፍተኛ ሁኔታ የታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ ደጋፊ ሆነዋል።
በመሆኑም አሁን ላይ እየተደረገ ያለው የሕዝብ ድጋፍ ቀደም ሲል ከነበረው እየጨመረ መጥቷል። ለድጋፉ መጨመር የግድቡ የግንባታ ደረጃ በየጊዜው መፋጠኑና መንግስትም ለግድቡ የሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ምክንያት ሆኗል። ግድቡ ደግሞ ትውልድ ተሻጋሪ እንደሆነ፣ መሪ ቢቀያየርና ትውልድ ቢተካካ እንኳ ግንባታውን ሊያስቆመው የሚችል አንዳችም ኃይል ሊኖር እንደማይችል በሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ግንዛቤ ተይዞበታል። የዚህ የታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ የግንባታ ቅብብሎሽ መጀመሪያ ደግሞ ባለፉት መንግስታት ሊደፈር ያልቻለው ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ይፋ መደረጉ ነው። በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ደግሞ ካርቱም ላይ ከሱዳንና ግብጽ ጋር የሶስትዮሽ ስምምነት መፈራረም መቻሉ የግንባታውን ስራ ቀጣይነት ያሳያል። በለውጡ መንግስትም ግድቡ ላይ የነበሩ የአሰራር ችግሮችን እና የአቅም ክፍተቶችን ፈትሾ በማስተካከል፣ የተለያዩና ዘርፈ ብዙ ውጫዊ ጫናዎችን መክቶ በመቋቋም ግድቡ አሁን ላለበት የዕድገት ደረጃ መድረስ ችሏል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ የሕዝቡ ተሳትፎ አሁን ላይ ሲታይ፣ መላው ኢትዮጵያውያን የዓባይ ጉዳይ የፖለቲካም ሆነ የሃይማኖት አጀንዳ አለመሆኑን የጋራ አቋም የያዙበት ነው። ከዚያም አልፎ የሀገር ጉዳይ ነው፤ የተፈጥሮ ሀብትን የመጠቀም፣ ለትውልድ ቅርስ የማውረስ፣ ኢትዮጵያን የማቆየትና የማሻገር፣ የማንነት ጉዳይ ነው፣ ወዘተ፡ በሚል ከዳር ዳር መላው ሕዝብ በአንድነት የቆመበት ነው። ዲያስፖራው ድንበር እና ርቀት ሳያግደው በሁሉም መልኩ መደገፉ፣ ህጻናት ከወላጆቻቸው በላይ ስለዓባይ ግድብ መግለጽ መቻላቸው፣ የመከላከያ ሰራዊትና የፖሊስ አባላት ከአነስተኛ ደመወዛቸው በተደጋጋሚ ማገዛቸው፣ በፐብሊክ ዲፕሎማሲው ዓለም አቀፍ ጫናውን ታግሎ ለድል መብቃት መቻሉ፣ ሚዲያዎች ለግድቡ ዘብ መቆማቸውና ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ ሰጪነት መሸጋገራቸው በዓባይ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ በጠንካራ ጎን ሊነሱ እንደሚችሉ አቶ ኃይሉ ያብራራሉ።
ሁላችንም እንደምንገነዘበው ለታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ ድጋፍ የተፈጠረው ሕዝባዊ ተሳትፎ በጣም ከፍተኛ ነው። የሕዝቡ ተሳትፎ ደግሞ ከግድቡም በላይ ለአገር አንድነትና ገጽታ ግንባታ፣ እንዲሁም ለአገር ሰላም መረጋገጥ የሚኖረው ሚና ትልቅ መሆኑ አያጠያይቅም። ይህን ከፍተኛ የሕዝብ መነሳሳትና አንድነት ግን ወደ ሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ማስፋትና መጠቀም ያስፈልጋል። በተለይም መንግስት ይህን በታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ ግንባታ ላይ የተፈጠረውን ሕዝባዊ አንድነት እንደ ጥሩ ዕድል በመጠቀም ወደ ሌሎች የልማት እና የሰላም አጀንዳዎች ሊያውለው ይገባል እንላለን።
ንጉሤ ተስፋዬ
ዘመን መጽሔት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም