‹‹ኢትዮጵያን የሚወድ፣ ፈተናዎችን ወደ ድል የሚቀይር የለውጥ አመራር አለን›› – የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የፓርቲው ዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ

የለውጥ ወር በሆነው መጋቢት የዘመን መጽሔት ልዩ ዕትም እንግዳ ያደረግናቸው የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ የሆኑትን አቶ አደም ፋራህን ነው። በዘመነ ኢህአዴግ አጋር እየተባሉ ይጠሩ ከነበሩት አምስት የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ የነበረው የኢሶዴፓ አባል ከነበሩትና ከአሁኑ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ አደም ፋራህ ጋር ባደረግነው ቆይታ አምስተኛ ዓመቱን የደፈነው ለውጥ የመጣበትን ሂደት፣ ያስመዘገባቸውን ውጤቶች፣ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶችና ቀጣይ ተስፋዎቹን የተመለከቱ ጥያቄዎችን አቅርበንላቸው፡ እንደሚከተለው መልሰዋል።

ዘመን፡- ኢትዮጵያ በለውጥ ጉዞ መራመድ ከጀመረች አምስት አመታት ተቆጥረዋል። ወደ ኋላ ልመልስዎትና በለውጡ ዋዜማ የነበረው ትግል ምን ይመስል ነበር ?

አቶ አደም፡- በለውጡ ዋዜማ አካበባቢ አጠቃላይ አገራችን የነበረችበት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ሁኔታ በጣም አስቸጋሪና ፈታኝ ነበር። በጥቅሉ የነበሩት ችግሮች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ቅቡልነት ካለው ጠንካራ ሀገረ መንግስት አለመፈጠር ጋር የተያያዙ ነበሩ። የመንግስትና የህዝብ ግንኙነት እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የገባበት ሁኔታ ነበረ። ከኢኮኖሚ አኳያ የቁልቁለት ጉዞ የተጀመረበትና በፖለቲካውም እጅግ በጣም አስቸጋሪ የሆኑ የሀገራችንን ህልውና የሚፈታተኑ ሁኔታዎች የነበሩበት ነበር። ማህበራዊ ትስስሩ ላልቶ ለረጅም ዘመናት ሲገነቡ የነበሩ የአብሮነት እሴቶች እየተሸረሸሩ የሄዱበትና እነዚያም የሀገር ህልውና አደጋ እንዲጋረጥበት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ነበሩ። ስለዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ነበሩ።

ያን ተከትሎ በሀገራችን ለውጥ መጥቷል። የመጣውን ለውጥ ባለፉት ዘመናት በሀገራችን ሲከሰቱ ከነበሩት ለውጦች ልዩ የሚያደርጉት ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች አሉት። ለውጡ ህገ መንግስታዊና በመሪ ድርጅት ውስጥ የነበሩ የለውጥ አመራሮች የመሩት ከመሆኑም ባሻገር በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰላማዊ የህዝብ ትግል የመጣ ለውጥ መሆኑ የመጀመሪያው ልዩ የሚያደርገው ነው። ሁለተኛው ሀገራዊ ለውጡን ልዩ የሚያደርገው በሪፎርም አቅጣጫ የተመራ መሆኑ ነው። ይሄም ማለት የነበሩትን ድሎችና ስኬቶች አስጠብቆ የማስፋት፤ የነበሩ ስህተቶችን የማረምና ለዛሬና ለነገ ትውልድ የሚጠቅሙ ስራዎችን የመስራት አቅጣጫን የያዘ፣ ማጥቃትና ማሳደድ ያልነበረበት፤ ትብብርን ያስቀደመ ለውጥ ነበር። ስለዚህ እነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ለውጡን ከዚህ በፊት ከነበሩት ለውጦች ልዩ ያደርጉታል። የነበረው ሂደት በሁሉም ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ለሁሉም የምትመች የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠር አለበት የሚል ፍላጎት በህዝቡም በለውጥ አመራሩም ዘንድ ነበር። ለውጡም ለዚያ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

ዘመን፡- እርስዎ አንዱ የለውጡ ኃይል እንደመሆንዎ መጠን ከውጭ ሆኖ ህዝቡ ይታገላል እናንተ ደግሞ ከውስጥ የምታደርጉት ትግል ነበረ። ትግሉ ምን ያህል ከባድ ነበር? ምን ያህልስ ጊዜ ወሰደ ?

አቶ አደም፡- እንደሚታወቀው እንደ ሀገር መሪ ፓርቲ የነበረው ኢህአዴግ ነው። እንደሁም አምስት አጋር ድርጅቶች ይባሉ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነበሩ። እኔ የኢህአዴግ አባል አልነበርኩም፤ ከአጋር ድርጅቶቹ አንዱ የነበረው የኢሶዴፓ አባል ነበርኩ። ነገር ግን በኢህአዴግ ውስጥ ስለነበረው የውስጥ ትግል በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ መረጃዎች ይደርሱን ነበር። እጅግ በጣም ፈታኝ የሆነ ትግል ነበር ሲካሄድ የነበረው። የሀገር ህልውናን አደጋ ላይ ይጥሉ የነበሩ ሁኔታዎች ስለነበሩ የኢትዮጵያን ህልውና ለማስቀጠል ለውጥ ያስፈልጋል የሚል ጽኑ አቋም የያዙ አመራሮች ከፍተኛ ትግል አድርገዋል። ትግላቸውም ፍሬ አፍርቶ ለውጡን እንውን እንዲሆን አድርጓል።

ሌሎች አጋር ይባሉ የነበሩ ፓርቲዎችም በየአካባቢያቸው ከሌሎች የለውጡ አመራሮች ጋር በመተባበር ትግል ሲያደርጉ ነበር። በኢኮኖሚው የቁልቁለቱን ጉዞ ገትተንና ቀልብሰን ኢኮኖሚው አገግሞ ወደትክክለኛ መስመር እንዲመለስ፤ በፖለቲካውም የሀገር ህልውናን የሚፈታተኑ ጉዳዮች መልክ እንዲይዙ ማድረግ፤ በማህበራዊና ዲፕሎማሲውም ረገድ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ትግል በሁሉም ዘንድ ሲደረግ ነበር። በአጠቃላይ ለውጡ የሁሉም ትግል ድምር ውጤት ያመጣው ለውጥ ነው።

ዘመን፡- ለውጡ ምን ተስፋ ይዞ መጣ ?

አቶ አደም፡- ለውጡ ይዞ የመጣውን ተስፋ ለማየት እንደ ሀገር በፖለቲካውም በኢኮኖሚውም ሆነ በሌሎች መስኮች የነበርንበትን ሁኔታ ማስታወስ ያስፈልጋል። ያንን ለመለወጥ የተደረገውን ጥረት ማየትና የመጣውን ውጤት እንዲሁም እንደ ሀገር የተፈጠረውን ተስፋ በሂደት ከገጠሙ ተግዳሮቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ጋር አያይዞ በደምብ ማየት ይጠይቃል።

ከፖለቲካ አኳያ በሀገራችን ከለውጡ በፊት ሰፋፊ ችግሮች ነበሩ። ችግሮቹ በዋናነት ከሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ናቸው። የመጀመሪያው ከነበረው ፀረ ዴሞክራሲያዊ አካሄድና እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ችግሮች ናቸው። ሁለተኛው ደግሞ የወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴት በሂደት እየተመናመነ በመሄዱ የተፈጠሩ ችግሮች ናቸው። ከመጀመሪያው ጋር በተያያዘ ከነበሩት ጸረ ዴሞክራሲያዊ አካሄድና እንቅስቃሴዎች አንጻር የተፈጠሩ ችግሮችን ስናይ አንደኛው የፖለቲካ የዴሞክረሲ ምህዳሩ እንዲጠብ ሆኗል። ከፍተኛ የሆነ የነጻነት እጦት ተፈጥሯል። ከነበረው ጸረ ዴሞክራሲ አካሄድ ጋር ተያይዞ የዴሞክራሲ ተቋማት እጅጉኑ ተዳክመዋል። ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነበረ። የግጭትና አለመግባባት መንስኤዎችን በአግባቡ ከመለየት ይልቅ በኃይል የማፈንና አሉታዊ ሰላምን የማስፈን አዝማሚያዎች ነበሩ። ይሄ ደግሞ ሄዶ ሄዶ የሀገረ መንግስትን ቅቡልነት እንዲያዳክም ሆኗል ማለት ነው።

ሁለተኛው ከወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴት መመናመን ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሆነ የአግላይነትና የመገፋፋት ሁኔታ ነበረ። ከአካታችነት ይልቅ አግላይነት የሰፋበት፣ ከህብረብሔራዊ አንድነት ይልቅ ጽንፈኝነት እጅጉኑ የሰፋበት ሁኔታ እነዲፈጠር አድርጓል። አንዱ በሌላው ጫማ ውስጥ ሆኖ ከማሰብ ይልቅ የራሱን ብቻ በመመልከት እኔ የማለት ሁኔታ ሰፊ ነበር። ስለዚህ ያንን ሁኔታ መለወጥ ይጠይቅ ነበር።

ይህን ሁኔታ ለመለወጥ በዋናነት ከፖለቲካ አኳያ የተወሰዱት ሦስት መሰረተዋ ርምጃዎች ናቸው ። የመጀመሪያው ከትርክት ለውጥ ጋር ተያይዞ ያለ ነው። እንደሚታወቀው በሀገራችን ከሚያለያዩን ጉዳዮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉንና የሚያቀራርቡን ጉዳዮች ይበዛሉ። ነገር ግን ከነበረው የፖለቲካ ስርዓት ጋር በተያያዘ የልዩነት ትርክት ሰፊ ቦታ ይዞ የቆየበት ሁኔታ ስለነበር ያንን መቀየር ይጠይቅ ነበር። ስለሆነም በወንድማማችነትና እህትማማችነት ላይ የተመሰረተ ህብረብሄራዊ አንድነት የትስስር ትርክት ትልቅ ቦታ እንዲይዝ ተደርጓል። ከፓራዳይም አኳያም የመደመር ፓራዳይም ወደፊት የመጣበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ያሉንን መልካም ነገሮች በአንድ ላይ ደምረን በሀገራችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያስችል ስራ መስራት አለብን የሚለው ትልቅ ቦታ እንዲይዝ ሰፊ ስራ ተሰርቷል። ውጤትም አምጥቷል። እንደሚታወቀው የሀገራችንን ህልውና ለመፈተን የተደረጉ ጥረቶች ነበሩ። እንዚያ ጥረቶች የከሸፉትና ያልተሳኩት በዋናነት በተደረገው የፓራዳይምና የትርክት ለውጥ ነው። ሰዉ በጋራ አገራዊ ጉዳዮች እና በጋራ ጥቅሙ ላይ በጋራ ለመቆም የሚችልበት ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ ነው።

ሁለተኛው የተወሰደው የፖለቲካ እርምጃ የፖለቲካ ተሳትፎን አካታችነት የሚያሳድግ ነው። ይሄ በአንድ በኩል በመሪ ፓርቲ ደረጃ የነበረውን የአካታችነት ችግር መቅረፍ፤ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የመወሰን እድል ያጡ አካላትም የሃገራዊ መሪ ፓርቲ አካል እንዲሆኑ አንድ ወጥ በአንድ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደምብ የሚመራ ሀገራዊ ፓርቲ እንዲመሰረት ስራ ተሰርቷል። እንደሚታወቀው ብልጽግና አጋርና ዋና ፓርቲ ሳይባል ሁሉም ኢትዮጵያውያን በዕኩልነት የሚሳተፉበት እዲሆን ተደርጓል። ከዚህም በተጨማሪ የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቶ የፖለቲካ ተዋንያን ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲያራምዱ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የፖለቲካ እስረኞች ተፈትተዋል። ምህረት ሊደረግላቸው የሚገቡ ምህረት ተደርጎላቸዋል። ውጪ ተሰደው የነበሩ የፖለቲካ አመራሮች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የፖለቲካ ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲያራምዱ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል። ስለዚህ በአጠቃላይ የፖለቲካ ተሳትፎንና አካታችነትን የሚያሳድጉ እርምጃዎች ተወስደዋል፤ ሰፊ ውጤትም ተገኝቷል።

ሦስተኛው የተወሰደው የፖለቲካ ርምጃ የፖለቲካ ስርዓታችንን ለማዘመንና የዴሞክራሲ ስርዓታችንን ለማዳበር የሚያስችል የህግና የተቋም ሪፎርም ስራ ነው። በተለይ ከህግ ሪፎርም አኳያ የምርጫ ህጉ፣የጸረ ሽብር ህግ እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የሲቪል ማህበራት አዋጅ እንዲሻሻል ተደርጓል፤ ሌሎችም የህግ ማሻሻል ስራዎች ተሰርተዋል። እነዚህ የፖለቲካ ስርዓታችን እንዲዘምንና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ስራችን አንዲዳብር ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ ናቸው። ሌላው ደግሞ የተቋማት ሪፎርም ነው። በተለይ የህግ፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ተቋማት በነጻነትና በገለልተኝነት መንግስታዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሚያስችሉ የተቋም ሪፎርም ስራዎች ተሰርተዋል። ምርጫ ቦርድና የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በአመራርም በህግም እንዲጠናከሩ ሰፊ ጥረት ተደርጓል። ሌሎች ህግ አስከባሪ ተቋማትም ህገመንግስታዊ ተልዕኳቸውን በነጻነትና በገለልተኝነት እንዲወጡ የሚያስችሉ የተቋም ሪፎርም ስራዎች ተሰርተዋል። በሌሎች ተቋማትም ሰፋፊ ስራዎች ተሰርተዋል። የተቋም ግንባታ ስራችን በሀገራችን የህግ ማስከበር ስራን በብቃት መወጣት ከማስቻሉ በተጨማሪ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ፣ ፖለቲካችን እንዲዘምንና የዴሞክራሲ ባህላችን እንዲጎለብት ምቹ ሁኔታዎች የፈጠሩ ነበሩ።

እነዚህ ስራዎች በመሰራታቸው በፖለቲካው ዘርፍ አመርቂ ውጤት ተገኝቷል። የመጀመሪያው የነጻነትና የዴሞክራሲ ልምምዳችን በከፍተኛ ደረጃ አድጓል። በተሰሩት የተቋማት ሪፎረም ስራዎች ብቁና ገለልተኛ ተቋማት እየተፈጠሩ ይገኛሉ። ተልዕኳቸውንም በብቃት እየተወጡ የሚገኙበት ሁኔታ ነው ያለው። ይሄም በመሆኑ የፖለቲካ ተሳትፎ አድጓል። ሌላው ውጤት ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነጻ፣ ፍታዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ምርጫ ተካሂዶ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በሕዝብ የተመረጠ ፓርቲ ስልጣን እንዲይዝ ሆኗል። እነዚህ ትልልቅ ውጤቶች ናቸው።

እነዚህ ስኬቶች ቢሆኑም በሂደት ግን ለውጡ በርካታ ተግዳሮቶች ገጥመውታል። በተለይ ከፖለቲካው አንጻር የገጠሙን ተግዳሮቶች በሦስት ሊገለጹ ይችላሉ። የመጀመሪያው በነጻነት አጠቃቀምና አስተዳደር ዙሪያ ያለ ጉድለት ነው። በነጻነት ልምምድ፣ በዜጎች ደህንነትና በህግ ማስከበር ረገድ ሚዛን ከመጠበቅ አኳያ ክፍተት ተፈጥሯል። ለውጡ እንዲመጣ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የነጻነት መብትን ማክበርና ማስከበር አንዱ በመሆኑ መሪው ፓርቲ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ስለሆነም፣ ዜጎች ነጻነትንና የዴሞክራሲ ባህልን እንዲለማመዱ ሰፊ እድል ፈጥሯል፤ ነገር ግን ነጻነታቸውን ህግና ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ እንዲጠቀሙ የሚፈልጉ አካላት ያገኙትን ነጻነት በአግባቡና ህግና መርህን በጠበቀ መልኩ ከመጠቀም አካያ ክፍተት ታይቷል። ያ ደግሞ እንደ ሀገር ዋጋ አስከፍሎናል። ማንኛውም በህገ መንግሥቱ የነጻነት መብት የተሰጠው አካል በዛው ልክ ግዴታዎች ስለተጣሉበት በዛ መካከል ሚዛን መጠበቅ አለበት።

የነጻነት መብቱን መጠቀም ያለበት ህግና ስርዓትን በጠበቀ መልኩ ነው፤ ከዛ ወጣ ያለውን ደግሞ፣ መንግሥት ነጻነትን የማስከበርና የማስተዳደር ኃላፊነት አለበት።

ሁለተኛው ችግር በጽንፈኝነት ምክንያት የተፈጠሩ ጉዳቶችና አደጋዎች ናቸው። እንደሚታወቀው ዴሞክራሲ በራሱ የሚፈጥረው ተፈጥሯዊ የሆነ ውጥረት አለ:: ይህ ተቀባይነት ያለው ነው። ዴሞክራሲ በሀሳብ ልዕልና ላይ የተመሰረተ ፉክክርን ይጠይቃል፤ በሐሳብ መፋጨትን ይጠይቃል። ይህ ተፈጥሯዊና ዴሞክራሲን ለመገንባት ቆርጠን እስከተነሳን ድረስ አይቀሬ ነው የሚሆነው። ነገር ግን ከዚህ ውጪ የሆኑ ጽንፈኝነት የወለዳቸው አደጋዎችና ጉዳቶች አሉ:: እነዚህ ደግሞ ለዜጎች አካል መጉደል፣ መፈናቀል ንብረታቸው መውደም ምክንያት ሆነዋል። ይህንንም በአግባቡ መታገል ይጠይቃል።

ሶስተኛው የገጠመን ተግዳሮት ከመረጃ ዘመን አመጣሽ ድህረ እውነት ፖለቲካ ጋር እና ከስነ ልቦና ዘመቻ ወይም ጦርነት ጋር በተያያዘ ለፖለቲካ ገበያ ተዋናዮች እና ለጽንፈኛ ኃይሎች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ ነው። ከዚህ ጋር ታያይዞ የጥላቻ ንግግሮችና የሀሰት መረጃዎች በስፋት የሚሰራጩበት፣ ለኢትዮጵያ መልካም ነገር የማይመኙ አካላት በሥነ ልቦና ጦርነቱ ሚዲያ የፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የሀገራችንን ሰላም የሚያውኩ ህዝብን ከህዝብ የሚያቃቅሩ፣ የሚያራርቁ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ እድል አግኝተዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሰፊ ስራ መስራት ይጠይቃል። ከዚህ አንጻር በቀጣይ ትኩረት እናደርጋለን ብለን ያሰብነው በሶስት ጉዳዮች ላይ ነው። የመጀመሪያው በህግ ማስከበርና የነጻነት አስተዳደር ስራ ላይ ውጤታማ ስራ መስራት አለብን የሚል ነው። ሁለተኛው ደግሞ ወንድማማችነትን፣ ሕብረብሔራዊነትን እና ሚዛናዊነትን በማጎልበት ጽንፈኝነትን መታገል ነው። በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ መሠረታዊ በሚባሉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት የተፈጠረበት ሁኔታ ስለሌለ ብሔራዊ ምክክሩ አካታችና የተሳካ ሆኖ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ማድረግ በሚገባ ትኩረት የምናደርግባቸው ጉዳዮች ናቸው።

ዘመን፡- ከሕወሓት ጋር የነበረው ጦርነት ጥሎት ያለፈው አሻራ ከኢኮኖሚ አኳያ ኢትዮጵያን ምን ያህል ፈትኗታል?

አቶ አደም፡- ጦርነቱ በከፍተኛ ሁኔታ ነው ሀገራችንን የፈተነው። በመጀመሪያ ደረጃ ጦርነቱ ወደን ሳይሆን ተገደን የገባንበት ነው። የሀገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት አደጋ ላይ የወደቀበት ሁኔታ ስለነበረ ሀገር በማዳን የሀገር ህልውናን የማስቀጠል ጉዳይ ሆኖ የተጀመረ ጦርነት ነው። ጦርነቱን ማን እንደጀመረው በግልጽ የሚታወቅ ነው። ጦርነቱን ተከትሎ ሰፋፊ ጉዳቶች ደርሰዋል። ጦርነት ሰው ይበላል፤ ሀብት ያባክናል እንዲሁም ትኩረት ያዛባል። ስለዚህ በጦርነቱ ምክንያት የህይወት መስዋዕትነት ተከፍሏል፤ አካል ጎድሏል፤ ንብረት ወድሟል። በተጨማሪም በርካታ ለልማት ሊውል ይችል የነበረ ሃብት ለጦርነት እንዲውል ሆኗል። ከዚያም ባሻገር ትኩረት የሚያዛባ ስለሆነ አመራሩ ሙሉ አቅሙን በሀገራችን ዘላቂ ልማት የሚያመጡና ልማትን ለማፋጠን የሚያግዙ በአጠቃላይ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚረዱ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የብልጽግና ጉዞን የማፋጠን ስራ መስራት ሲገባው ጦርነቱ ትኩረት የተሸማበትና በየደረጃው ያለ አመራር በሙሉ አቅሙ በሀገራችን ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ስራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ሆኗል።

ጦርነቱ የኢትዮጵያን መልካም ማየት የማይሹ አካላት እድል እንዲያገኙ አድርጓል። የውጪ ጫናዎችም የጨመሩበት ወቅት ስለነበር እነዚህ አካላት ጦርነቱን እንደ ሰበብ በመጠቀም በሀገራችን ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን ለማድረስና ጫናዎችን ለማሳደር እድል ተፈጥሮላቸዋል። መጨረሻ ላይ መንግሥትና መሪው ፓርቲ ምንግዜም ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ የሚሰጥ ስለሆነ፤ ከግጭትና ጦርነት አዙሪት የሚያስወጣን አቅጣጫ መከተል ያስፈልጋል የሚል እምነት አሳድሮ ጦርነት ለአንድ ሰከንድ አንኳ አስፈላጊ አይደለም የሚል አቋም ይዟል። ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በሰላም አማራጭ ችግሩ እንዲፈታ ጥረት ሲደረግ ስለነበረም መጨረሻ ላይ እድሉ ሲገኝ እድሉን በአግባቡ በመጠቀም የሰላም ስምምነት ተፈርሞ ሀገራችን እፎይታ ያገኘችበትና ትኩረታችንን ዋናው ግባችን በሆነው የብልጽግና ጉዞ ማፋጠን ላይ ያደረግንበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ዘመን፡- ኢትዮጵያ በለውጡ አመታት ያጓጠሟትን ተደራራቢ ፈተናዎች እንዴት አለፈች ?

አቶ አደም፡- የፓርቲያችን ብልጽግናና የመንግሥታችን መለያ ባህሪ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው አንዱ ጉዳይ ፈተናዎች ወደ እድል መቀየር ነው። በአንድ በኩል ችግሮች የሚያደርሱትን ጉዳት መቀነስ፣ እንደ እድልም በመጠቀም ለሀገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ስራዎችን መሥራት ነው። ጦርነት ውስጥ ሆነን በአንድ በኩል እየተዋጋንና የሀገር ህልውናን እያስከበርን በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች የልማት ስራዎቻችን ለአንድም ሴኮንድ እንዳይቆሙ የማድረግ አቅጣጫን ነው የተከተልነው። ስለዚህ በተወሰነ ደረጃ ጦርነቱ የሚያዛባው ትኩረት ቢኖርም አጠቃላይ የተከተልነው የትኩረት አቅጣጫ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎችን ጦርነት እንደሌለ አድርገን የመስራት፤ የኢትዮጵያን ህልውና ለማስከበር ተገደን የገባንበትን ጦርነት ሌላ ስራ እንደሌለን አድርገን ሳንወስድ ሁሉም ስራዎች ጎን ለጎን በውጤታማነት እንዲሰሩ ማድረግ ነው።

ጦርነት ውስጥ ብንሆንም ትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ለአንድም ሴኮንድ እንዳይቋረጡ በማድረግ አመርቂ ለውጥ ታይቷል። ለምሳሌ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንደሚታወቀው ከለውጡ በፊት በከፍተኛ ችግር ውስጥ የወደቀ ፕሮጀክት ነበር። በሚፈለገው ፍጥነት እየተከናወነ አልነበረም፤ በርካታ የጥራት ችግሮችም ነበሩበት። ስለዚህ አጠቃላይ ፕሮጀከቱ ያለበትን ሁኔታ ቆም ብሎ በመገምገም ስራውን እንዴት ማፋጠን ይቻላል፤ የጥራት ችግሮችን እንዴት መቅረፍ ይቻላል፤ ለሐብት ብክነት የሚዳርጉን ነገሮችን እንዴት መቅረፍ ይቻላል፤ በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ በሚፈልገው ፍጥነት እና ይጥራት ደረጃ እንዲካሄድ ምን አይነት አቅጣጫ መከተል አለብን የሚለው ታይቶ ስራው እንዲቀጥል የተደረገበትና የጥራት ጉድለቶቹ ተፈተው ውጤታማ በሆነ አግባብ ፕሮጀክቱ እየተፈጸመ ነው ያለው። በጦርነት ውስጥ ሆንን የሙሌት ስራዎች ተሰርተው እስከ ኃይል ማመንጨት ተደርሷል። በአሁኑ ውቅት ፕሮጀክቱ በጥሩ አፈጻጸም ደረጃ ላይ ስለሚገኝ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ የታለመለትን ዓላማ ያሳካል ብለን ነው የምናምነው።

በዓለም ላይ በተከሰቱ የኮቪድ 19ኝ ወረርሺኝ ብሎም ከሩሲያና ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የግብርና ምርቶች እጥረት ተፈጠሯል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ሀገራዊ እምቅ አቅሞቻችንን ወደመለየት ነው የሄድነው። ከማኅበረሰቡ ፍላጎት በመነሳት አቅርቦቱን ለማሳደግ ምን አለን የሚለውን ገልጠን ወደ ማየት ነው የሄድነው። ሀገራችን ስንዴ ለማሰገባት ከፍተኛ ወጪ ስታወጣ ነበር፤ ስንዴ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ይፈልግ ነበር። በሌላ መልኩ ደግሞ ሀገራችን ለስንዴ ምርት ምቹ ሀገር ነች። በስንዴ ራሳችንን ችለን ከዛ አልፈን ወደ ኤክስፖርት መሄድ እንችላለን የሚል አቋም ነው የተያዘው። በዛው መሠረት ተፈጽሞ ዘንድሮ ሁላችሁም እንደምታውቁት ስንዴ ኤክስፖርት ወደማድረግ ሄደናል።

የተመረተው ምርት ተጠቃሚው ጋር እንዲደርስ ከግብይት ጋር የተያያዙ ችግሮች ነበሩ። በመሃል ያሉ ህገ ወጥ ደላሎች ችግር የፈጠሩና የኢትዮጵያ ከስንዴ ጥገኝነት መላቀቅ ያላስደሰታቸው አካላትም አጠቃላይ ሂደቱን ለማደናቀፍ ሰፊ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ስንዴ ኤክስፖርት ማድረግ ተችሏል። ከገበያ ጋር የተያያዘውንም ችግር በመፍታት የተመረተውን ስንዴ ተጠቃሚው በአግባቡ እንዲጠቀም የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው ያለው። የመጣው ለውጥ የነበሩብንን ፈተናዎች ወደ እድል በመቀየር በሀገራዊ ለውጡ ብልጽግናን ለማምጣት መስራት አለብን ካልነው ጋር የሚጣጣም ነው። በሌሎች የግብርና ምርቶችም በተመሳሳይ መልኩ ለውጥ መጥቷል።

ዘመን፡- አሁናዊ የኢትዮጵያ ፈተናዎች ምንድናቸው ? እነዚህን ፈተናዎችስ ለመሻገር መንግሥት ምን እየሰራ ነው ?

አቶ አደም፡- አሁናዊ የኢትዮጵያ ፈተናዎች በፖለቲካው ስንወስድ በነጻነት አስተዳደርና አጠቃቀም ዙሪያ ያለው ክፍተት፤ በጽንፈኝነት ምክንያት የሚፈጠሩ አደጋዎች ሞት፣ መፈናቀል፣ አካል መጉደል እና ንብረት መውደም የመሳሰሉት፤ ከመረጃ ዘመን አመጣሽ ድኅረ እውነት መረጃ ጋር፤ ከሥነ ልቡና ጦርነት ጋር ተያይዞ የሀሰተኛ መረጃዎች መሰራጨት እና የጥላቻ ንግግሮች ስርጭት መብዛት ወዘተ ይጠቀሳሉ። በኢኮኖሚው ደግሞ በመጀመሪያ ሀገራዊ አቅምን በሚገባ ከመጠቀም ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን መፍታት ነው። እንደ ሀገር ትልቅ አቅም አለን። ያንን አቅም አሟጦ ከመጠቀም አኳያ የተደረገ ጥረት ቢኖርም አሁንም ይቀራል። የኢኮኖሚ ፈተና የኑሮ ውድነቱ ስለሆነ አሁንም በሀገር ውስጥ ልናመርታቸው የምንችላቸው ምርቶች እና የኑሮ ውድነቱንና የዋጋ ግሽበቱን ሊያቃልሉ የሚችሉ ሥራዎች በሚፈለገው ደረጃ ከመስራት አኳያ የሚቀረንን ማረም አለብን። የኑሮ ውድነቱ ለማቃለል የሚያስችል አቅም አለን። ያንን ሀገራዊ አቅም በማሳደግ መፍታት ይኖርብናል።

በሌላ በኩል ደግሞ የውጭ ጫናውም ቀላቀል አይደለም። የውጭ የልማት አጋሮችን የማስፋት ሥራ መሥራት አለብን። በዲፕሎማሲም ሰፊ ሥራ መሥራት አለብን። ሆነ ብለው የጀመርነውን የብልጽግና ጉዞ ለማስተጓጎል ጥረት የሚያደርጉ አካላት አሉ። የእነዚህ አካላት እኩይ እንቅስቃሴ ወደፊትም መቀጠሉ አይቀርም። በሌላ በኩል ደግሞ በደንብ ስላልሠራንበት ድጋፋቸውን ያላገኘናቸው አካላት ላይ ከሠራን ደግሞ ለውጥ ማምጣት እንችላለን። ባለፉት የለውጥ ዓመታታም በተለይ ከዲፕሎማሲ አኳያ በውስን ሀገራት ላይ ከማተኮር ይልቅ ከዚህ ቀደም ተገቢውን ትኩረት ያላገኙ ግን ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና ጉዞ ጠንካራ አጋር ሊሆኑ የሚችሉ አካላትን የማግኘት ሥራ በስፋት ተሠርቷል፤ ውጤትም ተገኝቷል። ስለዚህ የውጭ ጫናዎችን ለመቀነስ የሚያስችል ሥራ መሥራት አለብን። ከውጭ ጫና ጋር የተያያዘው ሁለተኛው ፈተናችን እንዲፈታ በትኩረት ሊሰራ ይገባል።

በሶስተኛ ደረጃ በተለይ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ አካላት ተሳትፎ የሚፈጠሩ የኢኮኖሚ አሻጥሮች አሉ። እነዚያንም ለመቅረፍ የሚያስችል ሥራ መሥራት ይኖርብናል። በእነዚህ ላይ ትኩረት ካደረግን የሕዝብ አንገብጋቢ ጥያቄዎች የሆኑትን የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ግሽበት እና ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል ብለን እናምናለን።

ዘመን፡- ለውጡ እውን እንዲሆን መላው ኢትዮጵያውያን ያደረጉትን አስተዋጽኦ እንዴት ይገልጹታል ?

አቶ አደም፡- ለውጡ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ተሳትፎና ትግል የመጣ ለውጥ ነው። ለውጡ እንዲመጣ ምክንያት ከሆኑ መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል በሕዝቦች መካከል የነበረው አንድነት ዋነኛው ነው። በተለይ እንደሀገር ቅቡልነት ያለው ጠንካራ ሀገረመንግሥት እና ብሔረመንግሥት እንዲኖረን፤ የነበሩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ችግሮችን

እንዲቀረፉ፣ በዜጎች ላይ ይደርሱ የነበሩ ኢ- ሰብዓዊ ድርጊቶች እንዲቆሙ፣ በዚህም ምክንያት ሀገራችን ዲሞክራሲያዊ ሆና፣ የዜጎችና የቡድኖች ነጻነት በአግባቡ ተረጋግጦ ሁሉም አቅሙ በፈቀደ መጠን በሀገር እድገትና ብልጽግና ላይ የሚሳተፍበት፣ ከውጤቱም ፍትሃዊ በሆነ አኳሃን የሚጠቀምበት ሁኔታ እንዲኖር መሻት ነበረ። በመሆኑም በሁሉም አካባቢ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሚችሉት አቅም የነበረውን ሥርዓት ሲታገሉ ቆይተዋል። ለውጡ እንዲመጣም የተለያዩ አካላት በተለያየ መልኩ ትብብር ሲያደርጉ ቆይተዋል። ያ የሁሉም ተሳትፎ፣ ትብብርና አንድነት ነው ለውጡ እውን እንዲሆን ያደረገው። በአጠቃላይ ለሕዝቦች ትስስርና አንድነት መጠናከር ጥሩ መሰረት ጥሎ ያለፈ ለውጥ ነው ማለት ይቻላል።

ዘመን፡- ከዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች አንጻር ሀገራዊ ለውጡ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጥቷል?

አቶ አደም፡- ከዲፕሎማሲ አኳያ ሀገራዊ ለውጡ ይዟቸው ከመጣቸው ጉዳዮች መካከል የመጀመሪያው ዜጋ ተኮርና የሀገር ክብር ተኮር አቅጣጫ በመከተል በሁሉም አካባቢ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ክብራቸው ሊጠበቅ ይገባል። ስለዚህ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ዜጎቻችን ያሉበት ሁኔታ በማወቅ ችግር ውስጥ ያሉትን ከችግር እንዲወጡ ማድረግ ያስፈልጋል። ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ድጋፍ ተደርጎላቸው ችግራቸው እንዲቃለል። ወደሀገር ውስጥ መግባት ለሚፈልጉ አካላትም ወደሀገር ውስጥ እንዲገቡ አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላቸው እንዲገቡ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል።

ሁሉም ኢትዮጵያውያን ባሉበት ቦታ የዜግነት ክብራቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ በማድረግ በዚህ መልኩ ሀገራዊ ክብርን ማስጠበቅ ይቻላል የሚል አቅጣጫ ነው የተከተልነው። ዜጋ ተኮር እና የሀገር ክብር ላይ የሚያተኩር አቅጣጫን መከተላችን ውጤት አምጥቷል። ይሄን አቅጣጫ በመከተላችን በርካታ ችግር ውስጥ የነበሩ ዜጎቻችን ችግራቸው እንዲቃለል ሆኗል። በተለያዩ ሀገራት ተቸግረው ወደሀገራቸው መመለስ ያልቻሉ ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል። ከተለያዩ መንግሥታት ጋር ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ በመሥራት ኢትዮጵያውያን ባሉበት ሀገር መብታቸውና ጥቅማቸው እንዲከበር የማድረግ ሥራ ተሠርቷል። የእኛ ኢምባሲዎችና ሚሲዮኖችም በዚህ አቅጣጫ በመጓዝ ባሉበት አካባቢ ያሉ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ አውቀው ድጋፍ የሚፈልጉትን እንዲደግፉ የመከተል አቅጣጫ ተግብረዋል። ይሄም ትልቅ ውጤት አምጥቷል ብለን ነው የምናምነው።

ሁለተኛ ለውጡ ይዞ የመጣው ከዲፕሎማሲ አኳያ ጎረቤት ተኮር የሆነ አቅጣጫ መከተል ነው። ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና ጉዞ ከጎረቤቶች ጋር የሚኖረን የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር፣ የኢኮኖሚ ትስስር፣ በአጠቃላይ ቀጠናው ሰላማዊ ሆኖ ለብልጽግና ጉዞ የሚመች እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ስለሆነ ለጎረቤቶቻችን ቅድሚያ መስጠት አለብን ብለን አቅጣጫ አስቀምጠናል።

በዚያ መሰረት ከኤርትራ ጋር እርቅ ተፈጽሟል። በእርቁም ኢትዮጵያም ኤርትራም ብዙ ጥቅም አግኝተዋል። ከሌሎች ጎረቤት ሀገራትም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ የበለጠ እንዲጎለብትና የኢኮኖሚ ትስስሩ እንዲጠናከር በጋራ ጥቅም ዙሪያ ሥራ ተሠርቷል፤ ትልቅ ውጤትም አምጥቷል። በዚህ ምክንያትም ባለፉት ዓመታት እንደሀገር የተደቀኑብንን የህልውና አደጋ እንድንቀለብስ ትልቅ ድጋፍ አድርጎልናል። ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች ላሳካናቸው ስኬቶችም ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ ሰጥተን በጋራ መሥራታችን ትልቅ እና ውጤታማ የዲፕሎማሲ ድል አስገኝቶልናል ብለን ነው የምናስበው።

ሌላው ለውጡ ይዞልን የመጣው አቅጣጫ ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነታችንን እና አጋርነታችንን የማስፋት ነው። ከለውጡ በፊት ከውስን አካላት ጋር ብቻ የነበረው ግንኙነት እንዲሰፋ፣ በኢኮኖሚም በተለያየ መልክ ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ የሚያስገኙ ግኑኝነቶችን የመጀመር፤ መካከለኛ ምስራቅ ሀገራትን ጨምሮ ከዚህ ቀደም በሚፈለገው ደረጃ ትኩረት ያልተሰጣቸው አካባቢዎች ትኩረት በመስጠት ሌሎችም ጋር ግንኙነታችንን የማስፋት አካሄድ ተከትለናል። ከዚያም የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳዎችን የማሳደግ ሥራ ነው የተሠራው። ይህም ውጤት አስገኝቶልናል ብለን ነው የምናምነው።

እነዚህን አቅጣጫዎች በመከተላችን ባለፉት ዓመታት በተለያዩ አካላት ሲደረጉብን የነበሩ ጫናዎችን ተቋቁመን እንድናልፍ ረድቶናል። ለአብነት በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት 13 ጊዜ አካባቢ ኢትዮጵያ አጀንዳ ሆናለች። ያ እንዳይሳካ የተሠራው ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ውጤት አስገኝቷል። በሌላ በኩል ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ግብጽ በተለያየ መልክ ጫና ስታደርግ ቆይታለች። ይሁንና ከለውጡ ጋር ተያይዞ የተከተልናቸው አዳዲስ አቅጣጫዎች በግብጽ በኩል የነበሩ ጫናዎችን እንድንቋቋም አግዞናል። የእኛ የዲፕሎማቲክ ተቋማት እንዲጠናከሩ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል። ለውጥ ተደርጎም በአመራር፣ በአሠራር፣ በአደረጃጀት እንዲጠናከሩ እና አቅጣጫዎችን በብቃት የሚፈጽሙ እንዲሆኑ ጥረት ተደርጓል፤ ውጤትም ተገኝቷል።

ዘመን፡- ለውጡ የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ የሚያስችል መስመር ላይ መሆኑን የሚያመላክቱ ማሳያዎች ምንድን ናቸው ?

አቶ አደም፡- ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ያላት ሀገር ነች። ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ያላት ሀገር እንደሆነች፣ በጀመረችው ከቀጠለች የብልጽግና ግባችንን እውን እንደምናደርግ የሚያሳዩ ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች አሉ። የመጀመሪያው እሳቤዎቻችን እና ያለን ሀብት ነው። እንደሀገር እንደፓርቲም ጥራት ያላቸው ሀሳቦች አሉ። ሀገር በቀል የሆኑ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ግልጽና ጥራት ያላቸው እሳቤዎች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ለኢትዮጵያ ለብልጽግና ጉዟችን መፋጠን እና ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን መሆን የሚያስችሉ ሀብቶች አሉ። የተፈጥሮ ሀብቶች አሉ፤ ሰው አለን። ጂኦግራፊያዊ አቀማመጣችንም ለብልጽግናችን ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው። ስለዚህ እሳቤዎቻችን እና ሀብቶቻችንን ስናይ ኢትዮጵያ ለመበልጸግ ትልቅ ዕድልና ተስፋ ያላት መሆኑን ያሳያሉ። ባለፉት የለውጥ ዓመታትም እሳቤዎቻችን እንዲጠሩ ሀገራዊ እንዲሆኑ ኢትዮጵያን የሚያበለጽጉ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ መሰረት ያደረጉ እንዲሆኑ፤ ያሉንን ሀብቶች መጠቀም የሚያስችሉ እንዲሆኑ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል። ሀብቶቻችንን የማወቅ፣ ያለንን እምቅ አቅም መጠቀም የሚያስችል አቅጣጫ ጀምረናል። ለማሳያም ያህል በስንዴ እና በአረንጓዴ አሻራ አሳይተናል። ይሄ አንደኛው ነው።

ሁለተኛው ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ያላት የብልጽግና ጉዞን አሳክታ ለሁለንተናዊ ጉዞ ለማድረግ የምትችል መሆኑን የሚያሳየው አመራር ነው። ሀሳቡና ሀብቱ ቢኖርም፣ ይህን አቀናጅቶ በውጤታማነት ለመፈጸም የሚያስችል አመራር ከሌለ በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። አሁን ኢትዮጵያን የሚወድ ቁርጠኛና ውጤታማ አመራር አለን። በፈተናዎች የማይሸነፍ፤ ፈተናዎችን ወደ ድል የሚቀይር፤ በተለያዩ አካላት የሚደቀኑብንን አደጋዎች ለመቀልበስ በቁርጠኝነትና በጊዜ የለንም መንፈስ የሚሠራ አመራር አለን። ስለዚህ ይሄ የሚያሳየው ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ እንዳላት ነው።

ሶስተኛው ማሳያ ደግሞ ለብልጽግና መሰረት የሚሆኑ ጉዳዮች እየተጣሉ እና መሰረቱ በማይናወጥ መልኩ እየተገነባ ነው ያለው። ከብልጽግና መሰረት ግንባታ አኳያ የምናነሳው የመጀመሪያ ጉዳይ የዴሞክራሲና የነጻነት ልምምዱ እየተጠናከረ ሄዷል። ባለፉት ስርዓቶች በርካታ የሕዝብ ጥያቄዎች ነበሩ። ከእነዚያ መካከል ዋና ዋናዎቹ የኢኮኖሚ ጥያቄ ነበሩ፤ የብሔሮች መብት በተሟላ መልኩ የመጠበቅ ጉዳይ ነበር፤ የዲሞክራሲ ጥያቄ ነበር። በእኛ እምነት የኢኮኖሚ ጥያቄዎችና የብሔሮች ጥያቄዎች በተሟላ መልኩ ምላሽ ያላገኙት በዋናነት በሁለት ምክንያት ነው።

አንደኛ የዴሞክራሲ ባህል ስላልተገነባ ነው፤ ሁለተኛ ደግሞ የወንድማማችነትና የእህትማማችነት እሴት ስላልዳበረ ነው። ባለፉት ዓመታት ከዴሞክራሲ አኳያ ሰፊ ልምምድ ነበረ። የዴሞክራሲ ባህልን የሚገነቡ፣የዴሞክራሲ ስርዓቱን የሚያዳብሩ ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። ይህም የዴሞክራሲ ልምምዱ እንዲዳብርና የሕዝቦች የኢኮኖሚ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ፣ የብሔር ብሔረሰቦች የፖለቲካ ጥያቄዎች በተሟላ ምላሽ እንዲያገኙ መሰረት የሚጥል ስለሆነ ለብልጽግና ጉዟችን መሰረት ነው።

ሁለተኛ የሚነሳው ጉዳይ የተቋማት ግንባታና የፕሮጀክቶች አፈጻጻም ላይ ያለው ለውጥ ነው። እንደሚታወቀው ባለፉት የለውጥ ዓመታት ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የተቋማት ግንባታ ነው። ተቋማት መሪው ፓርቲ ማንም ይሁን ማን ሕገ መንግሥታዊ ተልኳቸውን

በነጻነት፣ በገለልተኝነት እና በብቃት የሚወጡ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ ነው ሲሠራ የቆየው። ተቋማትን በአመራር፣ በአደረጃጀት፣ በአሠራር እና በቴክኖሎጂ በማጠናከር የተሰጣቸውን ሕጋዊ ተልኮ በብቃትና በውጤታማነት የሚወጡበት ሁኔታ የመፍጠር ሥራ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል። የተቋማት ግንባታ ለሀገረመንግሥት ግንባታ ዋነኛ መሰረት ስለሆነና ለሁለንተናዊ ብልጽግና ግንባታ ደግሞ የሀገረመንግሥት ግንባታ ወሳኝ ስለሆነ እሱ ደግሞ በተቋማት ግንባታ ላይ የሚመሰረት ስለሆነ ለተቋማት ግንባታ የተሰጠው ትኩረት እና የተመዘገበው ውጤት የኢትዮጵያ ብልጽግና እውን እንደሚሆን ተስፋ የሚሰጥ ነው።

ከፕሮጀክቶች አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ብልጽግና እውን ሊሆን እንደሚችል የሚሳዩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሠራሉ ተብለው የማይታሰቡ አሻራ የሆኑ ፕሮጀክቶች ተሠርተዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሰራሉ ተብለው የማይታሰቡ የብልጽግና መሰረት እና አሻራ የሆኑ ፕሮጀክቶች ተሰርተዋል። በዚህ ረገድ አዲስ አበባ ላይ የተሰሩ የተለያዩ የቱሪስት መስህቦችን እና በገበታ ለሀገር የተሰሩትን ማንሳትና ከሌሎች ትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ጋር ተያይዞ ያለውን አፈጻጸም ማየት ይቻላል። ከፕሮጀክቶቹ ጋር በተያያዘ ደግሞ ሊነሳ የሚችለው በአንድ በኩል ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የነባር ፕሮጀክቶች አፈጻጸሞች የነበሩባቸው ችግሮች ተፈትተው በፍጥነትና በጥራት እንዲከናወኑ ለማድረግ የተከተልነው አቅጣጫ ነው። በሌላ በኩል ፈጠራ የታከለባቸው የኢትዮጵያ ብልጽግና ማሳያዎች የሆኑ እና ብልጽግናን በኢትዮጵያ የማረጋገጥ አቅሙ እንዳለን የሚያመላክቱ ፕሮጀክቶች ተሰርተዋል። እናም እነዚህ ተግባራት ወደፊት በትክክልም የኢትዮጵያ ብልጽግና እውን ሊሆን እንደሚችል ማሳያዎች ናቸው።

ባለፉት ኣመታት ስንከተል የነበረው የፕሮጀክቶች የፍጥነት ፣የጥራትና የዘላቂነት መርሆ በራሱ በኢትዮጵያ ብልጽግና ሊረጋገጥ እንደሚችል ያመላክታሉ። በምንሰራቸው ስራዎች ሁሉ ደግሞ በአንድ በኩል መፍጠን እንደሚጠበቅብን፣ እየፈጠን ግን ጥራት ላይ መደራደር የለብንም በሚል አቋም የተያዘባቸው ተግባራት ነበሩ። በመሆኑም የትኩረት አቅጣጫዎቻችን ሁሉ ጥራትንም ሆነ ዘላቂነትን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው። ስለሆነም የፍጥነትንና የጥራትን ጉዳዮች በተመለከተ በሰራናቸው ፕሮጀክቶች ሁሉ በትክክል ማሳየት ችለናል። ነባሮቹም ሆኑ አዲሶቹ ፕሮጀክቶች ጥራታቸውን በጠበቀ መልኩ በፍጥነት እንዲከናወኑ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ ተሰርቷል ብሎ መናገር ይቻላል።

የዘላቂነት መርሆን በተመለከተ ደግሞ በዋናነት ሁለት ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል። በአንድ በኩል የአረንጓዴ አሻራ ተግባርን ይመለከታል። አረንጓዴ አሻራ የዛሬን ብቻ ሳይሆን መጪውን ትውልድም ታሳቢ ያደረገ ነው። በዚህ ረገድ በቀጣይ ሊገጥመን የሚችለውን ፈተና ሳይቀር ከግምት ውስጥ ማስገባት ተችሏል። ስራው ደግሞ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችል ነው። ዘላቂ ግቦቻችንን ታሳቢ ያደረገው በተቋም ግንባታ ላይ የተከተልነው አካሄድም ሌላው ነው።

በተጨማሪ ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ በቀጣይ በዓለም ላይ በዋናነት አሉ ተብለው የሚጠቀሱ ሶስት ስጋቶችን ታሳቢ ያደረገው ክንውን ነው። የመጀመሪያው ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች ናቸው። ሁለተኛው ከጥቅማቸው በዘለለ ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር ተያይዞ በጎጅነት መልክም ሊመጡ ለሚችሉ ችግሮች መዘጋጀትን ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው። ሶስተኛው ከወረርሽኞች /pandemic/ ከመፈጠር ጋር የሚገናኝ ችግርን ለመከላከል የሚከናወን ዝግጅትን ይመለከታል።

በመሆኑም አንድ ሀገር ለብልጽግና ተስፋ ያለው ሊሆን እንዲችል፣ ከዚህ ቀደም ያስመዘገባቸውን ስኬቶች ጠብቆ ለማስፋት የሚያስችል አቅም መፍጠር ተችሏል። ከዚያም አልፎ የብልጽግና ጉዞውን አፋጥኖ ዕውን ለማድረግም ቁርጠኛ መሆን ከተቻለበት ደረጃ ተደርሷል። ከዚህ አኳያ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተቀርጾ በአራት ዓመት ውስጥ ከ25 ቢሊየን በላይ ችግኝ መትከል ተችሏል። አሁንም ቢሆን ተግባሩ ተጠናክሮ የቀጠለበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ ከአየር ንብረት ለውጥ አኳያ ትልቅ ዝግጅት እየተደረገበት ይገኛል።

ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር ተያይዞ በአንድ በኩል ቴክኖሎጂን በአግባቡ የመጠቀም፣በሌላ በኩል ደግሞ ጎጂ የሆኑትን ለይቶና የሚያደርሱትን ጉዳት ቀንሶ የብልጽግና ጉዞን ለማፋጠን የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ መቻሉ ነው። ከዚህ አኳያም ቴክኖሎጂን ለመጠቀምም ሆነ ጉዳቶቹን ለመቀነስ የሚያስችል ስራ በተቋም ግንባታ ስራዎቻችን በአግባቡ ያየነው ጉዳይ ነው። በዚህ ዙሪያ የሚመለከታቸው ተቋማት ጠንካራ ዝግጅት እንዲያደርጉ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ። ከዚህ አንጻር ሲታይ ሀገራችን ትልቅ ተስፋ ያላት መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል።

ከወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችለው ጉዳይ በኮቪድ 19ኝ ወቅት የተከናወነው አፈጻጸም ነው። በዚህ ረገድ ሁሉንም ነገር ሳንዘነጋ፣ በአንድ በኩል ጥንቃቄ የማድረግ ስራ እየተሰራ፣በሌላ በኩል ደግሞ በስጋት ምክንያት በፍራቻ ሁሉንም ነገር በመዝጋት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው መስተጓጎል የለበትም በሚል፣ የተወሰደው ጥበብ የተሞላበት አቅጣጫና የተሰጠው አመራር ትልቅ ትምህርት ሰጥቶናል። በቀጣይም ተመሳሳይ ችግሮች ቢፈጠሩ ተቋቁመን የብልጽግና ጉዟችንን ለማፋጠን የሚያስችል ብዙ ስራ ተሰርቷል፣አሁንም ቢሆን እየተሰራ ይገኛል።

ሌላው ለብልጽግና ጉዟችን ዕውን መሆን መሰረት የሚሆነው እንደ ሀገር ብሄራዊ መግባባት ልንፈጠርባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር የተሰራው ስራ ነው። እንደ ሀገር እጅግ መሰረታዊ በሚባሉ የሀገረ መንግስትን ህልውና የሚፈታተኑ ጉዳዮች ላይ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር አካታች ምክክር ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞም በነጻነትና በገለልተኛነት የተሰጠውን ተልዕኮ እያከናወነ ነው። እንደ መንግስት፣ እንደ ገዥ ፓርቲም አካታች ሃገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ ድጋፍ እያደረግን ነው። የምንፈጥረው ብሄራዊ መግባባት ደግሞ ለብልጽግና ጉዟችን ትልቅ መሰረት እንደሚሆን ይታመናል።

በአጠቃላይም በሀገራችን የብልጽግና መሰረቶች እየተጣሉ ስለሆነ፣ አገራችን ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግናዋን በማረጋገጥ ራዕይዋን ለማሳካት የሚያስችሉ ማሳያዎች አሉ። ከእኛ የሚፈለገው ነገር የብልጽግና ጉዟችንን የሚፈታተኑ ጉዳዮችን በመለየት በንቃት እያረምን መልክ እያስያዙ መሄድ ነው። ከዚህ አኳያ ዜጎች ሃላፊነት በተሞላበት አኳኋን መንቀሳቀስ መቻል አለባቸው። የተለያዩ ግለሰቦችና የፖለቲካ ቡድኖችም እኔ ከሚል ግላዊ አስተሳሰብ ወጥተው፣አዕምሯቸውን ክፍት በማድረግ፣ የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ሃሳብ ለመረዳት እና ለማወቅ በሌላው ጫማ ውስጥ ሆነው ነገሮችን ማየት ይገባቸዋል። እንደ ሀገርም አንድ ላይ የብልጽግና ጉዟችንን እንድናፋጥንና የሁላችንንም ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅጣጫ መከተል ያስፈልጋል። ከጽንፈኝነት መራቅና የህግ የበላይነትም መከበር አለበት።

ለተግባራዊነቱ ደግሞ መንግስት የሚጠበቅበትን ሚና መወጣት ይኖርበታል። ዜጎችም ህገ መንግስታዊ ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው።

ነጻነትን በአግባቡ የመጠቀም ሁኔታ ላይም መሰራት እንደሚኖርበትም እናምናለን። በተለይም የነጻነት አጠቃቀምን በአግባቡ ማስተዳደር መቻል የግድ ነው። ይህን ከሰራን ደግሞ በታሰበው ልክ የብልጽግና ጉዟችንን የምናፋጥንበት፤ በሀገራችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ዕውን የሚሆንበት፤ ዘላቂ ሰላምና የዳበረ ዴሞክራሲ ያላት ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ብልጽግና የተረጋገጠባት እንዲሁም መልካም አስተዳደር የሰፈነባት በዓለም መድረክ ላይ የሚገባትን ቦታ የያዘች ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ እንችላለን።

ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በጣም እናመሰግናለን።

አቶ አደም፡- እኔም አመሰግናለሁ።

በዝግጅት ክፍሉ

ዘመን መጽሔት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም  

Recommended For You