የለውጡ ጉዞ ፈተና፣ ድል፣ ተስፋ…የለውጡ ጉዞ

1825 ቀናትን… 260 ሳምንታትን… 60 ወራትን… አምስት ዓመታት በለውጥ መንገድ ላይ! እነዚህ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ግንቦት 20ን ከተካ ወዲህ የተሰፈሩ ጊዜያት ናቸው። በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተቀጣጠለውን አመጽ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የተቆጠሩ አምስት ዓመታት።

በእነዚህ አምስት አመታት በርካታ አገራዊ ክስተቶች ተስተናግደዋል። በዚህ ጽሁፍ በአምስቱ የለውጥ አመታት ከተስተዋሉት አያሌ ገጽታዎች መካከል ዓመታቱን በጉልህ ይገልጻሉ በተባሉ አራት ማዕቀፎች መስታወትነት ኢትዮጵያ ያለፈችባቸውን የለውጥ መንገዶች እንመለከታለን።

ማለዳ

የለውጡ ማለዳ ውበት እንዲታየን ምልከታውን ከዋዜማው እንጀምራለን። ግንቦት 1983 ዓ.ም. ሥልጣን የተቆጣጠረው ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ 27 ዓመታት በስልጣን ላይ ቆይቷል። እነዚህ አመታት በፈተና የተሞሉና የግፍ አገዛዝ የሰፈነባቸው ነበሩ። አፋኝ ህጎችና አዋጆች ስራ ላይ ውለው በርካታ ዜጎች በግፍ ታስረዋል፤ ተገድለዋል እንዲሁም ከሀገር ተሰደዋል። የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል። ሌብነት እንደ አንድ የስራ መስክ ተቆጥሮ ኢትዮጵያ ተበዝብዛለች። ከአንድነት ይልቅ መለያየት ላይ በስፋት ተሰርቶ ዜጎች በጥርጣሬ እንዲተያዩ ተደርጓል። “ኢትዮጵያ” የሚለው ስም “አገሪቱ” በሚል አጠራር ተተክቶ ዜጎች ለሀገራቸው ያላቸው ብሔራዊ ስሜት እንዲደበዝዝ ለማድረግ ያልተፈነቀለ ድንጋይ አልነበረም። ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በህወሓት መራሹ መንግስት የነበረውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ “በራሳቸው በፖለቲካ መሪዎቹ በህዝቡ ጭምር ተገምግሞ ብቃት ያጣ ፤ የወደቀ ፤ በአገሪቷና በህዝቦቿ ላይ ጉዳት ያደረሰ፣ የአገሪቷን ሀብት የመዘበረ ፣ያስመዘበረ፤ ሙሰኞችን ያበቀለ ፍትህ የተጓደለበት ነበር” ሲሉ ይገልጹታል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን ጭቆናና ኢፍትሃዊነት አምርሮ ተቃውሟል። የህይወትና የአካል መሰዋትነትም ከፍሏል። በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሲዳማ፣ በሶማሌና በሌሎችም ክልሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚፈሰው የአንዳችን ደም የሌላችን ደም ነው በማለት በታሪክ ጉልህ ስፍራን የያዘ ጠንካራ ትግል አካሂደዋል። በመጨረሻም በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለተከታታይ ዓመታት የተካሄዱ ተቃውሞዎች በኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠረው ተራማጅ ኃይል ታግዘው ሃገራዊ ለውጥ እንዲወለድ ሆኗል።

የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሥርዓቱ ላይ እየተካሄደ ላለው ሕዝባዊ ተቃውሞ “የመፍትሔው አካል ለመሆን” በሚል የስራ መልቀቂያ አቀረቡ። ከአንድ ወር በኋላም የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከመጋቢት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በተከታታይ ለስምንት ቀናት ያካሄደውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ በሰጠው መግለጫ በሃገሪቱ ውስጥ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን “የአመራር ድክመት የወለዳቸው” ሲል ለመግለጽ ተገደደ። በፓርቲው ውስጥ ይህንን ለማረም የሚያስችል “አመለካከት እና አንድነት” የሚፈጥር ሁኔታ እንዳለም ጠቆመ። መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. 180 አባላት ያሉት የኢህአዴግ ምክር ቤት ተሰብስቦ ሰዓታት ከወሰደና አዲስ አሰላላፍ ከታየበት ሂደት በኋላ ዶክተር ዐቢይ አሕመድን የግንባሩ ሊቀ-መንበር አድርጎ መምረጡን አስታወቀ።

የኢሕአዴግ ሊቀመንበር በመሆን የተመረጡት ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ ከስድስት ቀናት በኋላ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሰየሙ። እንግዲህ የለውጡ ጉዞ የሚጀምረው በዚህ ዕለት ጠቅላይ ሚኒሰተር ሆነው የተሾሙት ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ስልጣን ሲረከቡ ባደረጉት ንግግር ነው። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በብዙዎች ዘንድ የኢትዮጵያ መዳን የተበሰረበት አዋጅ ተደርጎ ተወሠደ። እንዲሁም ጠላትና ወዳጅ ገፊና ተገፊ በሚሉ ተቃርኖዎች ይመራ የነበረው የአቢዮታዊ ዲሞክራሲ መርህና ትርክት ተለውጦ በአዲስ ትርክት መተካቱ የተበሰረበት ንግግር መሆኑ በግልፅ ታይቷል። በንግግራቸው ካነሷቸው ሀሳቦች የብዙዎችን ቀልብ ከገዙት እና የአገሪቱን ቀጣይ ፍኖት ጠቋሚ ተደርገው ከተወሰዱት መካከል የተወሰኑትን እዚህ ማስታወስ ተገቢ ይሆናል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው በአንድነት እንደተዋደቁ በማስታወስ አንድነታቸውን በገለጹበት የበርካቶችን ልብ በነካ ንግግራቸው “…አማራው በካራማራ ለአገሩ ሉዓላዊነት ተሰውቶ የካራማራ አፈር ሆኖ ቀርቷል። ትግራዋዩ በመተማ ከአገሬ በፊት አንገቴን ውሰዱ ብሎ የመተማ አፈር ሆኗል። ኦሮሞው በዓድዋ ተራሮች ላይ ስለአገሩ ደረቱን ሰጥቶ የሃገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከዓድዋ አፈር ተቀላቅሏል። ሶማሌው፣ ሲዳማው፣ ቤንሻንጉሉ፣ ወላይታው፣ ጋምቤላው፣ ጉራጌው፣ አፋሩ፣ ሥልጤው፣ ከምባታው፣ ሐዲያውና ሌሎቹም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁሉ በባድመ ከአገሬ በፊት እኔን ብለው እንደወደቁ ከባድመ አፈር ጋር ተዋህደዋል። አንድ ኢትዮጵያዊ አባት እንዳሉት እኛ ስንኖር ሰዎች ስናልፍ ሃገር እንሆናለን። የየትኛውንም ኢትዮጵያዊ ክቡር ሥጋና ደም በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ አፈር ሆኖ ታገኙታላችሁ። ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን፤” ብለዋል።

“በዜጎቻችን ሕይወት እና በግልም በጋራም ንብረቶቻችን ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት ደርሷል። ይኸንን ሁላችንም ማስቀረት እንችል እና ይገባንም ነበር። በተለያየ ጊዜ መስዋዕትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎች ፖለቲከኞች፣ በቅጡ ሳይቧርቁ ሕይወታቸው ለተቀጠፈ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች፣ ለሥነ ልቦናዊ እና አካላዊ ቀውስ ለተዳረጉ ቤተሰቦችና ግለሰቦች ከልብ የመነጨ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ለተፈጠሩ ችግሮች እልባት በማበጀት ሕዝባችንን እንደምንክስም ጭምር በዚሁ አጋጣሚ ቃል እገባለሁ” በማለትም ከዚህ ቀደም ለተፈጸሙ በደሎች በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል። አክለውም “ታዳጊውን ዲሞክራሲያችንን ለማዳበር ተጨማሪ የህይወትም ሆነ የአካል መስዋዕትነት አያስፈልግንም” ሲሉ በእርሳቸው ዘመን መሰል አጋጣሚ እንዳይከሰት ያላቸውን መሻት ጠቁመው “መጪው ጊዜ በኢትዮጵያችን የፍቅርና የይቅርታ ጊዜ ነው” ሲሉ ተደምጠው ነበር።

መደማመጥ ካለ ልዩነቶች በሐሳብ ፍጭት ውስጥ መፍትሔ እንደሚያገኙ በመግለጽ “ተፎካካሪ” ብለው የጠሯቸውን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አብረዋቸው እንዲሰሩ ጠይቀዋል። በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባስተላለፉት መልዕክትም፣ “አንዳንድ ጊዜ ከኢትዮጵያ ያነሰ የተፈጥሮም ሆነ የታሪክ ሀብት ባላቸው፣ ነገር ግን እጅግ በበለፀጉ አገሮች ውስጥ ራሳችሁን ብታገኙት ስለአገራችሁ ቁጭት ሳይሰማችሁ አይቀርም። ሁላችንም ውስጥ ያ ቁጭት አለ። እንደ ሃገር ያለንን ሀብት አሟጠን ለመጠቀም የምናደርገው ጥረት በቂ ሳይሆን ሲቀር መቆጨታችሁ አይቀርም። መቆጨትም አለባችሁ። ይህንንም ሁኔታ ለመለወጥ ለሁላችሁም የምትበቃ በዚያው ልክ ግን የሁላችንንም ተሳትፎ የምትፈልግ ሃገር አለችን። ዕውቀታችሁንና ልምዳችሁን ይዛችሁ ወደ አገራችሁ መመለስና አገራችሁን አልምታችሁ መልማት ለምትሹ ሁሉ እጃችንን ዘርግተን እንቀበላችኋለን፤” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የስልጣን ማለዳ በሀገሪቱ የተለያዩ የለውጥ እርምጃዎች ተወስድዋል። ሞት ተፈርዶባቸው የነበሩትን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ተለቀዋል። ኢትዮጵያን ጥለው ለመሰደድ የተገደዱ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። በአንድ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር “አሸባሪዎቹስ አሳሪዎቹ ነን” ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ በአሸባሪነት ተፈርጀው በውጭ ሀገር በስደት እና በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ አድርገዋል። የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት በተጨማሪ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ የዜጎችን መብት በማጎናፀፉ ረገድ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተዘግተው የነበሩ ድረ ገፆች ተከፍተዋል። መቀመጫቸውን በውጭ አድርገው የነበሩ መገናኛ ብዙሃንም በሀገር ውስጥ ገብተው የመንቀሳቀስ ዕድል አግኝተዋል። ለሁለት አስርት ዓመታት ተቆራርጠው የቆዩት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል እርቅ አውርደው ዲፕሎማሲያዊ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነታቸውን መልሰዋል። ሁለቱን ሀገራት ዳግም ለማቀራረብ በሰሩት ስራም የኖቤል ሽልማትን አግኝተዋል። በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ድጋፋቸውን ያለስስት ችረዋቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም የለውጡን አንደኛ አመት በማስመልከት በተዘጋጀ መድረክ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ “ባለፈው አንድ ዓመት በሀገሪቱ የመጣው ለውጥ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድምር ውጤት ነው፤ ይህንን የመጠበቅና የማስጠበቅ ስራም የእያንዳንዱ ዜጋ ሃላፊነት መሆን አለበት” በማለት ለሚመሩት ሕዝብ ምስጋና እና አደራ አቅርበዋል።

የለውጡ መባቻ

በለውጡ መባቻ ከተከናወኑ አበይት ተግባራት መካከል በጉልህ የሚጠቀሰው የብልፅግና ፓርቲ ምስረታ ነው። ኢህአዴግ ከያዛቸው ዘጠኝ ፓርቲዎች መካከል ከአራቱ / ከህወሓት፣ከብአዴን፣ከኦህዴድ እና ከደህዴን/ ውጭ ያሉ አምስት ፓርቲዎች አጋር ተብለው መያዛቸው በፓርቲውም ሆነ በአገር ወሳኝ ጉዳይ ላይ የመወሰን መብትም ሀላፊነትም እንዳይሰጣቸው መደረጉና ፓርቲው ይጠቀምበት የነበረውን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህም ሆነ አካሄድ ዴሞክራሲን የሚያቀጭጭ፣ ሁሉንም እኩል የማያሳትፍ፣ጠላትና ወዳጅ የሚፈጥር መሆኑን ቀድመው የተረዱት የለውጡ አመራር ፓርቲውንም፣መርሁንም፣ትርክቱንም የሚለውጥ አዲስ ፓርቲ ለመመስረት ተስማሙ።

በዚህም መሰረት በወንድማማችነትና እህታማማችነት ላይ የተመሰረተ፣ ህብረብሄራዊ አንድነት የትስስር ትርክትን ያነገበ፣ በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ የመወሰን እድል ያጡ አካላትን ያቀፈ፣ ኢትዮጳያዊያን በእኩልነት የሚሳተፉበት፣ አንድ ወጥ፣ በአንድ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደምብ የሚመራውን ብልፅግና ፓርቲ ተመሰረተ። ፓርቲዉ የፌደራል ሥርዓቱ ዋና መሰሶ ብዝሃነትን ማስተናገድ መቻሉ ነው ብሎ ያምናል፤ለብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እውቅና የሰጠ የፌደራሊዝም ሥርዓት በመገንባት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት የተከበረባት እውነተኛ ህብረ-ብሔራዊት ፌዴራሊዝም የተገነባባት ሀገር ለመፍጠር እየሰራ ይገኝል። የቡድንና የግል መብቶች፣ማንነትና ኢትዮጵያዊ አንድነት ሚዛናቸዉን ጠብቀዉ የሚስተናገዱበት፣ በራስ አስተዳደር እና በጋራ አስተዳደር ማዕቀፍ የተቀመጡ መብቶች የሚከበሩበት የፌደራሊዝም ስርዓት እዉን ማድረግ የትኩረት ማዕከሉ እንደሆነም ይገልፃል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የሚመራው የለውጥ መንግሥት በማለዳ ሰፊ አዎንታዊ እርምጃዎችን የወሰደው ደካማ ተቋማት ባሉበት ሁኔታ ውስጥ ስለነበር ቀጣዩ ስራ የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታና የተለያዩ ተቋማት ሪፎርም ሆነ። በዚህም ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ስርዓት ለመዘርጋት በተደረጉ ጥረቶች ጠንካራ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት የሚያስችሉ ተቋማት ገለልተኛ ሆነው እንዲቋቋሙ ተደርጓል። ከለውጡ ማግስት አንስቶ ነጻና ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለመፍጠር፣ ጠንካራ ምርጫ ቦርድ ለማደራጀትና የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። በአገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት መፍጠር እንዲቻል ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል። በተለያዩ ተቋማት ላይ በስፋት ከተተገበሩት የሪፎርም ስራዎችም ውስጥ በጸጥታ ተቋማት በተለይም በሃገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የተሰራው ስራ ተጠቃሽ ነው።

ይህ ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማትን የመገንባት ሂደት ዓለምአቀፍ ዕወቅናን ማግኘት የቻለ ነው። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የተቋቋመበት ዓላማ ሰብአዊ መብቶችን ማስተማር፣ መብቶች እንዳይጣሱ መጠበቅ፣ መብቶች በምሉዕነት ሥራ ላይ እንዲውሉና እንዲተገበሩ ማድረግ እና ተጥሰው ሲገኙ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግን መሰረት ያደረገ ነው። በዚሁ መሰረት እንደገና በአዲስ መልክ የተቋቋመው ኮሚሽኑ ነፃና ገለልተኛ ተቋም ሆኖ በርካታ ሪፖርቶችን እያወጣ ይገኛል። መንግስት ኮሚሽኑ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች ላይ የራሱ ዕይታ እንዳለውና በአንዳንድ አጋጣሚዎች ሪፖርቶቹን እስካለመቀበል መድረሱ ቢታወቅም ኮሚሽኑ በነጻነት ስራውን እንዲከውን አስቻይ ሁኔታዎች መፈጠራቸው ትልቅ ስኬት ነው።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገለልተኛ ሆኖ ስራውን በማከናወኑ በሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ ተቀባይነትና ተዓማኒነት ማግኘት ችሏል። በዓለም አቀፉ የብሔራዊ ሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ኅብረት የአንደኛ ደረጃ ዕውቅና እስከማግኘት ደርሷል። ዕውቅናው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ ተቋሞች ውስጥ ነፃና ቀጥተኛ ተሳትፎ ለማድረግ ዕድል የሚሰጥ ነው።

ኢትዮጵያን የችግር አዙሪት ውስጥ እንድትቆይ ያደረጋት ጠንካራና እውነተኛ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሳይገነባ መቆየቱ ነው። የቀድሞው ምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት፣ ነጻነት፣ ተአማኒነትና ቅቡልነት ያላገኘ የየስሙላ ተቋም ስለነበር ከአዙሪቱ ለመውጣት አዲስ የምርጫ ቦርድ የማቋቋም እንቅስቃሴ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ሲደረግ ቆይቷል። በኋላም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 102 መሠረት ቦርዱ ገለልተኛ ሕገ-መንግሥታዊ ተቋም ሆኖ ተቋቁሟል። ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ገለልተኛ አመራርና ቦርድ እንዲኖረው የተደረገና የፌዴራል እና የክልል ጽህፈት ቤቶችን ያደራጀ ሲሆን፣ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ደረጃ ቢሮዎችን ከፍቷል።

በአዋጅ 1133/2011 መሠረት ዳግም ለተደራጀው ቦርድ የተሰጡ ሥልጣንና ተግባራት መካከል በሕገ መንግሥቱና በምርጫ ሕግ መሠረት የሚካሄድ ማንኛውም ምርጫና ሕዝበ ውሳኔ በገለልተኝነት ማስፈፀም፤ የመራጮች ትምህርት ለሚሰጡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ መስጠት፤ መከታተልና መቆጣጠር፤ የፖለቲካ ድርጅቶችን መመዝገብ፣ በሕጉ መሠረት መከታተልና መቆጣጠር፤ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግበትን መስፈርት ማውጣትና በዚሁ መሠረት ድጎማውን ማከፋፈል፤ በምርጫ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም መወሰን፤ የምርጫ ክልሎችን አከላለል በተመለከተ ጥናት አድርጎ ለፌደሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳብ ማቅረብ የሚሉት ይገኙበታል።

በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከሌሎች አካላት የፖለቲካ ፍላጎትና ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆኖ የአገሪቷን የምርጫ ሂደት እየመራ ይገኛል። ይህንን ገለልተኝነቱንም ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሄደው ስድስተኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ አረጋግጧል። ምርጫ 2013 በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተካሄደው ምርጫ ነዋሪዎች በስፋት በመሳተፍ ድምፃቸውን የሰጡበትና ከዚህ በፊት ከተካሄዱት አምስት ምርጫዎች ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተካሄደ እንደነበር በብዙዎች መመስከሩ የሚታወስ ነው።

የፍትህ ተቋማትም ነጻና ገለልተኛ ሆነው ዜጎችን እንዲያገለግሉ ከህግ ማዕቀፎች ማሻሻል ጀምሮ የሪፎርም ስራዎች ተሰርተዋል። በፍትህ ዘርፉ ለተሰሩት የሪፎርም ስራዎች መሰረት የሆኑት ሁለት አዋጆች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቀዋል። አንደኛው የፌደራል ፍርድ ቤቶችን አወቃቀርና የስልጣን ደረጃን የሚመለከት ነው። ሁለተኛው ደግሞ የዳኞች አስተዳደርን ይመለከታል። በተለይ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጥንቅሩ ምን ይመስላል እንዲሁም አላማው እንዴት መስፋት አለበት በሚል የጉባዔው ነጻነት የፍርድ ቤትን ነጻነት ማስከበር በሚያስችል መልኩ እንዲደራጅ የቀረበ ረቂቅ ነበር። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለቱን አዋጆች ማጽደቁ ለዘለቄታው የፍትህ ስርአቱን ለማከም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

ሌላው በሪፎርም ምላሽ ያገኛው ጉዳይ የዳኞች ደመወዝ መሻሻልና የቤት ሁኔታ መመቻቸት ነው የዳኞች ነጻነት ጉዳይም በስልጠና እና በተለያዩ መንገዶች ግንዛቤ እዲያዝበት እየተደረገ ይገኛል። በፍጥነት ጉዳዮችን የማየት ነገር ገና መሰራት ያለበትና ከፍርድ ቤት ፍርድ ቤት የሚለያይ ቢሆንም ብዙ መሻሻሎችን ግን አሳይቷል። የፍትህ ዘርፉ አሁንም የሚስተዋሉ የአሰራር ክፍተቶች ከተወገዱለትና ማሻሻያው በተጀመረው መልኩ ከቀጠለ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው እንዲፋጠን ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

አገር እንደ አገር ሉዓላዊነቷ ተጠብቆና ተከብራ እንድትኖር፤ ሕዝብም እንደ ሕዝብ የደህንነት ስጋት ሳይኖርበት ሙሉ አቅምና ትኩረቱን በልማት ስራዎች ላይ እንዲያውል ከፍ ያለውን ሚና የሚወጡት የፀጥታ ተቋማት ናቸው። በእነዚህ ተቋማት ላይ የተደረገው ሪፎርም ከዕለት ዕለት ከፍ እያለና የኢትዮጵያን የልማት ግስጋሴና ሉኣላዊነቷን የማስከበር ብቃት እያመላከተ የሚገኝ ነው። በዚህ ረገድ ከለውጡ ማግስት አነስቶ በመከላከያ፣ በፌዴራል ፖሊስ፣ በብሄራዊ መረጃና ደኅነንት እና በመረጃ መረብ ደኅነንት ኤጀንሲ ላይ የተደረገው ጥንቃቄ የተሞላበት ሪፎርም፤ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በተለይም በመጨረሻዎቹ ሁለት ዓመታት የገጠሟትን ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች በድል እንድትወጣ አድርጓታል። የተሰራው የሪፎርም ሥራ ኢትዮጵያ በውስጥም ሆነ በውጪ ጠላቶቿ የተቃጣባትን አደጋ በብቃት እንድትመክት እና ጠላቶቿን አሳፍራ ሉዓላዊነቷን አስከብራ እንድትሻገር ያደረገ ነው። ይህ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ልታሳካው እየተጋች ላለችበት የብልጽግና ጉዞ ወሳኝ ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ያለፉትን ዓመታት በፈተና ውስጥ ያሳለፈች ቢሆንም፤ በአንድ በኩል ሰላሟን ለማረጋገጥ እየሰራች በሌላ በኩል በተገኘው ፋታ የልማት ተግባራትን ሳታቋርጥ ዘልቃለች። ለሰላሟ መሰረት፣ ለልማቷም አጋዥ የሚሆናትን የሰላም አስከባሪና አጽኚ ኃይልም ኢትዮጵያዊ መልክን በተላበሰ መልኩ ገንብታለች። ይሄ ደግሞ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ ሂደት ውስጥ የማድረግ አቅም ያለው ኃይል የመፍጠር ዋናው እርምጃ ነው።

በኢህአዴግ ዘመን የሰራዊቱ አደረጃጀት ኢትዮጵያዊ መልክና ገጽታ አንዳልነበረውና ኢፍትሃዊነት ነግሶበት እነደነበር በብዙ መረጃዎች የተረጋገጠ ነበር። 8ዐ በመቶ የሚሆነው የሰራዊቱ አመራር ከአንድ አካባቢ በመጡ ሰዎች የተያዘ እንደነበር የሚያሳዩ መረጃዎች ይፋ መደረጋቸው ደግሞ ትችቱ መሬት እንዲነካ አድርጎታል። በመሆኑም የአገር መከላከያ ሠራዊት የህዝብ ወገንተኝነቱን አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ለማድረግ አዲስ የመከላከያ ሠራዊት ግንባታ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ የሪፎርም ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። ለአንድ ፓርቲ፣ ብሔር ወይም ቡድን የወገነ ሳይሆን የሕዝብን ጥቅም በማስቀደም ለአገር ሉዓላዊነትና ለሕገ-መንገስታዊ ሥርኣቱ የቆመ ሰራዊት ለመገንባት ጥረት ተደርጎ አጅግ አስደማሚ ውጤት ተገኝቷል። ለውጡን ተከትሎ በተሰራው የሪፎርም ስራ ሰራዊቱ ከመላ ኢትዮጵያ በተውጣጡ ልጆች ተደራጅቶ፣ የእኔነት ስሜት እየፈጠረና ትክክለኛ ህዝባዊነቱን እያረጋገጠ እንደሚገኝ በተለያዩ አውዶች እየታየ ነው።

በሪፎርም ስራው ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎችን ከብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ወደ መከላከያ ሚኒስቴር እንዲዛወሩ ተወስኗል። የደጀን አቪዬሽን ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የጋፋት አርማመንት ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የሆሚቾ አሚውኒሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪና የፊውል ነዳጅና ፕሮፒላንት ንዑስ ኢንዱስትሪ መዋቅራዊ አደረጃጀቱን በአንድ ኮርፖሬሽን ስር በማደራጀት ብቁና ተወዳዳሪ ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች መገንባት ይቻል ዘንድ የመከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክርቤት ለውሳኔ አቅርቦ በዚሁ መሰረት ተወስኗል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ በልሂቃን መካከል በአንዳንድ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ባለመኖሩ፣ በመካከላቸው ያለው አለመተማመን እና ጥርጣሬ የዴሞክራሲ የሽግግር ሂደቱን ፈታኝ በማድረጉ የኢትዮጵያ ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ሥራ ጀምሯል። ይህ ኮሚሽንም ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ መሠረታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር የማድረግና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችል ሂደትን የሚመራና የሚያስተባብር አካል ነው።

የለውጡ ፈተና

የመብረቅ መውደቅ፣የነጎድጓድ ድምጽ፣ ዶፍ ዝናብ ፣ በረዶ እና ጭጋግ የክረምት መገለጨዎች ናቸው። ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት የለውጥ ዓመታት በክረምት የሚመሰሉ አስቸጋሪ የፈተና ጊዜያትን አሳልፋለች። በለውጡ አኩርፎ መቀሌ በከተመው በሕወሓት እና በፌዴራል መንግስት መካከል የነበረው አለመግባባት ተካርሮ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ክህደት ኢትዮጵያን ጦርነት ውስጥ አስገብቷታል።

በጦርነቱ ሂደት በሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ልዩ ኃይሎች እና ሌሎች የጸጥታ አካላት ሃገር ለማዳን ሲደረጉ የነበሩትን ተጋድሎ ዜጎች በከፍተኛ ንቅናቄ ደግፈዋል። ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተወጣጡ ወጣቶች በገፍ መከላከያ ሰራዊትን ተቀላቅለዋል። የኢትዮጵያ እናቶች በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት ልጆቻቸውን መርቀው ሸኝተዋል። በሃብት ማሰባሰቡ ሂደት ግለሰቦች፣ የመንግስትና የግል ተቋማት እና በውጭ ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሃገራቸውና ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት በመግለፅ እነዲሁም ውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም ከፍተኛ ተሳትፎ አድርገዋል። ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተከታታይነት ያለው ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ አድርገዋል። በርካታ የመንግስትና የግል ድርጅት ሰራተኞች የወር ደሞዛቸውን ለመከላከያ ሰራዊት አበርክተዋል። በኢትዮ-ቴሌኮም በኩል በተከፈተ የሞባይል መልዕክት ገንዘብ ማሰባሰቢያ በሚሊየን የሚቆጠር ብር ተሰብስቧል። ይህም ሕዝቡና በየደረጃው ያሉ የፀጥታ አካላት በአገር ሉአላዊነት ጉዳይ ላይ ምን ጊዜም ቢሆን በአንድነት እንደሚቆሙ በተግባር የታየበት ነው።

እንዲህ ያለ የሕዝብ ደጀንነት ተጠናክሮ ቢቀጥልም የሕወሓት ታጣቂዎች ሰሜን ሸዋ ድርስ መጥተው ውድመት አድርሰዋል። በዚህም መነሻነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ኅዳር 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ምሽት ላይ ወደ ግንባር ለመዝመት መወሰናቸውን አሳወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያ የሚለውን የነጻነት ስም የማስጠበቅ የታሪክ አደራ አለብን” በሚል ርዕስ በማኅበራዊ መገናኛ ገፃቸው ላይ ባሠፈሩት ጽሁፍ “የኢትዮጵያ የውጭና የውስጥ ጠላቶች ተቀናጅተው መዝመታቸውን በመግለጽ አሁን ኢትዮጵያን ለመታደግ የመጨረሻውን ፍልሚያ የምናደርግበት ጊዜ ላይ ነን። ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ከነገ ጅምሮ ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ” አሉ። ለመላው ጥቁር ሕዝቦችና ለኢትዮጵያዊያን ሲሉ ባስተላለፉት መልዕክትም “ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለሀገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሡ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ” በማለት ሌሎችም ፈለጋቸውን እንዲከተሉ ጥሪ አቀረቡ።

በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነት ተባብሶ በአማራና በአፋር ክሎች ውስጥ በቀጠለበትና የትግራይ ታጣቂዎች በርካታ ቦታዎችን ተቆጣጥረው ሰሜን ሸዋ መግባታቸው እየተነገረ ባለበት ሁኔታ የቀረበውን ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ዜጎችና ታዋቂ ሰዎች በዘመቻው ተሳትፈዋል። ሰራዊቱም በከፍተኛ ደረጃ ተነቃቅቶ በላቀ ሞራል ግዳጁን ለመወጣት ተንቀሳቅሷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተለያዩ የጦር ግንባሮች ከሠራዊቱ ጋር በቆዩባቸው ጊዜያት ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና የክልል ኃይሎች ባካሄዱት ዘመቻ ቁልፍ የሚባሉ በርካታ የአፋርና የአማራ አካባቢዎች ነጻ ወጥተዋል። ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ “ጊዜው አገርን በመሥዋዕትነት መምራት የሚያስፈልግበት ነው” በማለት ራሳቸው ሠራዊቱ ወደተሰለፈበት ግንባር ተጉዘው ጦርነቱን ለመምራት መወሰናቸውን ገልጸው ጦር ሜዳ ከተገኙበት ማክሰኞ ኅዳር 14 ቀን 2014 ዓ.ም ጅምሮ ወደ ኋላ እግሬ አውጪኝ ያሉት የትግራይ ታጣቂዎች በጥቂት ቀናት ውስጥ በአፋርና አማራ ክልሎች ከያዟቸው ቦታዎች ለቀው ለመውጣት ከመገደዳቸውም በላይ በሀገር ላይ ተደቅኖ ነበረው የመፍረስ አደጋ ተቀልብሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የሰራዊቱን አንጸባራቂ ድል ተከትሎ ባደረጉት ንግግር “ያቀረብኩትን ጥሪ ተቀብላችሁ ሕይወታችሁን፣ ጉልበታችሁን፣ ሀብታችሁን፣ ዕውቀታችሁን፣ ጊዜያችሁንና ሙያችሁን ለሠጣችሁ ሁሉ በኢትዮጵያ ስም ላመሰግናችሁ እወዳለሁ” ሲሉ ምስጋና አቅረቡ። ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለክልሎቹ ልዩ ኃይሎች፣ ለፌዴራል ፖሊስ አባላት እና ለሚሊሻዎችና ታጣቂዎችም “በከፈላችሁት መሥዋዕትነት ለልጆቻችን የምንነግረው ድንቅ ታሪክ ሠርታችኋል” በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል። “ዛሬም ሆነ ወደፊት ጠላቶቻችን ጉልበታቸው ዝሎ፣ የጥላቻና የጠበኝነትን መንገድ ጥለው፣ የፍቅርና የሰላምን መንገድ እስኪመርጡ ትግላችን ይቀጥላል” ሲሉም የመንግስታቸውን ፈርጣማ አቋም ለወዳጅም ለጠላትም አሳወቁ።

ጦርነቱ ከተጀመረበት ከትግራይ ክልል ተሻግሮ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ በመላ ትግራይ፣ በአፋርና በአማራ ክልሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለተራዘመ እንግልት፣ ስቃይና ሰቆቃ ዳርጓቸዋል። በርካቶች በጦር ሜዳዎች ወድቀዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር ዋጋ ያላቸው የግለሰቦችና የመንግስት ንብረቶች ተዘርፈዋል፤ ወድመዋል። ብዙዎች ክብረ- ነክ ለሆነ ጥቃት ተጋልጠዋል።

በሦስት ዙር ከተደረገ ጦርነት በኋላ ረቡዕ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል በተደረሰ ስምምነት ጦርነቱ መቋጫ አግኝቷል። ባለ 12 ነጥቦችን በያዘው የሰላም ስምምነት በዘላቂነት የኢትዮጵያን የግዛት አነድነትና ህገመግስታዊ ስርዓቱን ባስከበረ መልኩ ግጭት ማቆም፣ የሕወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት እና የሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ የሚሉ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ተካተዋል። ስምምነቱን ተከትሎ መንግስትና ሕወሓት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ግጭቱ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሰራዎችን አስከትሏል። በዘላቂነት ግጭት ለማቆም መስማማታችንን የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ዓለም ይወቅልን። የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም ከግምት በማስገባት የግጭቱን ምዕራፍ ከኋላችን ትተን በሰላም እና በመቻቻል ለመኖር ተስማምተናል” ማለታቸው ይታወሳል። ባለፉት አምስት የለውጥ ዓመታት በኢትዮጵያ በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት አንዱ ፈተና ነበር። ችግሩ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለውና አንዳንዴም ሴራዎች የታከሉበት ሆኖ በርካታ ዜጎችን አቅም አሳጥቷል። በተለይ በምግብ ነክ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ በየጊዜው የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች እየፈተነ ይገኛል። ከምንም በላይ ከመሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች እስከ ሌሎች ቁሳቁሶች ድረስ የዋጋ ግሽበቱ በየጊዜው እየጨመረ ፣ የአብዛኛው ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ኅብረተሰብ የመግዛት አቅም በብርቱ ተፈታትኗል።

መንግስት ያቋቋመው የብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት የሚያወጣው መግለጫ እንደሚየመለክተውም በኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ፈተና እያገጠመ ያለው ከዋጋ ግሽበት ጋር በተገናኘ መሆኑን ነው። ነገሩን ይበልጥ ከባድ የሚያደርገው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እየተመዘገበ ያለው የምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ መሆኑ ነው። ምክር ቤቱ በኢኮኖሚው ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ጫናዎችን ለመቀነስ የተለያዩ አንቅስቃሴዎችን አድርጓል። የመድኃኒት፣ ነዳጅ፣ ማዳበርያ፣ ዘይት፣ እና ሌሎችም መሠረታዊ ሸቀጦች ግዥን በተገቢው ሁኔታ እንዲካሄድ እንዲሁም በሸቀጦች አቅርቦት ላይ መንዛዛት እንዳይኖር በግዥ ሥርዓቱ ላይ አስፈላጊውን ማስተካከያ ወስዷል። ይሁን እንጂ በተፈለገው መጠን የኑሮ ውድነቱን መቀነስ አልተቻለም። ባለፉት አምስት አመታት የኑሮ ውድነቱን አባብሰውታል በሚል ከሚጠቀሱ ምክንያቶች ዋነኞቹ ብልሹ የሆነ የግብይት ሥርዓት፣ ሥነ ምግባር የሌለው የንግድ አሠራርና የደላላ ጣልቃ ገብነት፣ የጥሬ ግብዓት ውድነት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እያጋጠሙ ያሉ አለመረጋጋቶች፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዲሁም የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ናቸው።

በተለይም በቅርቡ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ዘይት፣ ፓስታ፣ መኮሮኒ፣ ስኳር፣ ዳቦ፣ አትክልትና ሌሎች መሰል ምግቦች ላይ ጭማሪ መታየቱ ሕዝቡን እያማረረ ነው። ይህንን በቅጡ የተረዳው መንግስት የተለያዩ ርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነው። የምግብ እህል አቅርቦት በስፋትና በፍጥነት ለተጠቃሚ እንዲደርስ ጥረት አድርጓል። በተለይ ችግሩ በስፋት እየተስተዋለ በሚገኝበት አዲስ አበባ የከተማዋ አስተዳደር ግብረሀይል በማቋቋምና መሰረታዊ ምግብ ምርቶችን ክልሎች ያለምንም መደነቃቀፍ ወደከተሞች እንዲገቡ በማድረግ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴም በቅርቡ ባካሄደው ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ ባወጣው መግለጫ ትኩረት ከሰጣቸው አምስት ነጥቦች አንዱ የኑሮ ውድነት ነው። ፓርቲው በመግለጫው የኑሮ ውድነት መፈጠሩን አምኖ ችግሩን ለማስወገድ አፋጣኝ ስራ መሰራት አለበት ሲል አቅጣጫ አስቀምጧል።

ባለፉት አምስት የለውጥ አመታት ጐልቶ የወጣው ሌላኛው ፈተና ሙስና ነው። የኢትዮጵያ ሶሻል ዴምክራቲክ ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ እና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጸሃፊ ዶክተር ራሄል ባፌ በቅርቡ ከዘመን መጽሔት ጋር ባደረጉት ቆይታ በኢትዮጵያ ቀደም ሲል ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲባል ጉቦ የመስጠት አካሄድ እንደነበር በማውሳት ዛሬ ችግሩ ተንሰራፍቶ የደረሰበትን ደረጃ “አሁን ጉቦ እየተሰጠ ያለው ያልተገባ ጥቅም ለማግኝት ሳይሆን የተገባውንም መብት ለማስከበር ነው።” ሲሉ ገልጸውታል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክትር ዐቢይም የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ እስከ ማቋቋም ደርሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮሚቴው መቋቋሙን ይፋ ሲያደርጉ ሙስና ዛሬ የሀገራችን የደኅንነት ሥጋት ሆኗል። ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ እጅ ተወርች አሥሮ በመያዝ ከጠላቶቻችን እኩል ሙሰኛው እየታገለን ነው። የተስተካከለ ቢሮክራሲ፣ የተቀናጀ መዋቅርና ዘመናዊ አሠራር ለሙስና ተጋላጭነትን ስለሚቀንሱ፣ እነዚህን ለማጥፋት ወይም ለማሰናከል ሙሰኛው ቀን ከሌት እየሠራ ነው። ሕዝባችን በአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከመሬት ጋር በተያያዙ አሠራሮች፣ በፋይናንስ ዘርፍ፣ በሽያጭና ግዥ ሂደቶች፣ በፍትሕ አደባባዮች፣ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶች፣ የህዝብ ተቋማት ወዘተ. በሚያጋጥመው ሙስና እየተማረረ ነው። በተለያዩ ጊዜያት ከሕዝብ ጋር በተደረጉ ውይይቶች ከጸጥታ ሥጋቶች እኩል ሙስና የብልጽግና ጉዟችን ዋናው ዕንቅፋት መሆኑን አንሥቷል በማለት ሙስና የደረሰበትን እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ገልጸዋል።

የሀሰት መረጃ ስርጭትና ፅንፈኝነት ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በይበልጥ የተፈተነችባቸው ናቸው። ማንኛውም ሰው የፈለገውን ጉዳይና ሀሳብ፣ በፈለገው ቦታ ሆኖ ለብዙዎች ማጋራት የሚችልበት ዘመን ላይ በመሆናችን ያልተፈጠረን እና ያልተደረገን ነገር አቀነባብሮ ሀላፊነት በጎደለው አካሄድ አገርን የሚያፈርስ፣ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያበጣብጥ መረጃ በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ ማስተላለፍ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ዋነኛ ቸግር ሆኖ ታይቷል። በዚህም ዋልታ ረገጥ በሆኑ ኃላፊነት የማይሰማቸው የሚዲያ ተቋማት በተለይም አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ አለቆች፣አቅም የሌላቸው ፖለቲከኞች፣ሀሳባቸው ገንዘብ ብቻ የሆነ አንቂዎች እና ሌሎች መሰል ተግባራትን የሚፈፅሙ አካላት ሁሉንም ጉዳይ በራሳቸው መነፅር ብቻ በማየትና በመወገን ሌላኛውን አካል ሲወቅሱ፣ ሲከሱ፣ ሲያጣጥሉ፣ ሲያንቋሽሹ፣ አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳ ሲቀሰቅሱ መስማት፣ማየትና ማንበብ የየዕለት ተግባራቸው ሆኗል። እነዚህ አካላት ስራዬ ብለው የሀሰት መረጃ በማሰራጨት ጥላቻን በኅብረተሰብ ውስጥ እንዲነግስ በማድረግ የእርስ በርስ ግጭት እንዲፈጠር አንዱ ምክንያት ከመሆን ባሻገር የጽንፈኝነት መፈልፈያ ስፍራ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። እነዚህ ተግባራት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለተከሰቱ የእርስ በእርስ ግጭቶችና መፈናቀሎች አንድ መንስኤ ናቸው።

ባለፉት አምስት ዓመታት በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶችም በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን አጥተው በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትጵያዊያን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በተለይም በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንዲሁም በአማራ ክልል ድንበር አካባቢዎች በደረሱ ጥቃቶች ሞት የኣከል ጉዳትና መፈናቀሎች ታይተዋል።

በለውጡ ዘመን ሌላኛው ኢትዮጵያ የተጋፈጠችው ፈተና ድርቅ ነው። የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እንደሚገልጸው እ.ኤ.አ. በ2020 መገባደጃ ላይ የጀመረውና በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተው ተከታታይነት ያለው የድርቅ አደጋ በአፍሪካ ቀንድ ባለፉት 70 ዓመታት ከተከሰቱት ሁሉ የከፋ ነው:: ድርቁ በተለይም በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በሶማሊያ ከ36 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎችን ለከፋ ጉዳት የዳረገ ነው።

በኢትዮጵያ በደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅ፣ በምስራቅና በሰሜን ምስራቅ የሃገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ሰብል አብቃይ አካባቢዎች፣ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደር በሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የድርቅ አደጋ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል:: ድርቁ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰባቸው አካባቢዎች በኦሮሚያ ክልል ቆላማ በሆኑና አርብቶ አደር ማኅበረሰብ በሚኖርባቸው ዞኖች በሚገኙ ወረዳዎች፤ በሱማሌ ክልል ዳዋ፣ ሊበን፣ አፍዴር፣ ሸበሌ፣ ዶሎ፣ ኤረር፣ ጀረር፣ ሞጎትና ቆራኢ ዞኖች ፤ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጎፋ፣ ጋሞ፣ ኮንሶ፣ ደራሼ፣ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች የሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ናቸው::

የዝናብ መዘግየት፣ በመጠን አነስተኛና በስርጭት የተቆራረጠ መሆን፣ በሰብል ምርትና በእንስሳት ግጦሽ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ ጉዳቱን የከፋ አድርጎታል:: በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር በሆኑ አካባቢዎች ላይ በዋናነት ዝናብ የሚያገኙባቸው ወቅቶች ላይ ዝናብ አለማግኘታቸው ድርቁን አባብሶታል:: በአራቱ ክልሎች ባጋጠመው ሦስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች መጨናገፍ የተነሳም በተከሰተ ድርቅ በርካታ እንስሳት ሞተዋል። ይህን ተከትሎ በመንግሥት፣ በዓለም ምግብ ፕሮግራም እንዲሁም መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ጥምረት ድጋፎች እየተደረጉ ነው።

የለውጡ ፍሬ

ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆናም ቢሆን ከተያያዘችው የልማት ሀዲድ ፈቀቅ ማለትን አልመረጠችም። በለውጡ ዘመን በዴሞክራሲ ስርኣት ግንባታ፣ ነጻ የዴሞክራሲ ተቋማት በማቋቋም፣ ኢትዮጵን የሚመጥኑ ተቋማትን በማደራጀት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በኤክስፖርት ገቢ፣ በግብርና ልማት፣ በፕሮጀክቶች አፈጻጸም ወዘተ አመርቂ ውጤቶችን አግኝታለች። በለውጡ ዘመን ኢትዮጵያ በአጠቀላይ የግብርና ዘረፍ ስኬት ማስመዝገቧ እነደተጠበቀ ሆኖ በተለይም በስንዴ ምርት ከሃገር ውስጥ ፍጆታ አልፋ የወጪ ንግድ መጀመሯ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ታሪካዊ ስኬት ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ ከፍተኛ ስንዴ አምራች በሆነው በባሌ ዞን ተገኝተው ኢትዮጵያ የስንዴ ምርትን በይፋ ወደ ውጭ ገበያ መላክ ልትጀምር መሆኑን ባበሰሩበት ንግግራቸው የስንዴ ኤክስፖርትም አዲስ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማግኛ እንደሚሆን ተናግረዋል። “ኢትዮጵያ ስንዴ ከውጭ አታስገባም የሚለው ራዕይ ለብዙዎች የሚዋጥ አልነበረም፤” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ማኅበረሰቡም ሆነ በርካታ የመንግሥት አመራሮች ይህንን ሃሳብ ተጋርተው ለመሥራት ተቸግረው እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን ይህንን ውጥን ማሳካት ስለመቻሉ በተግባር ማሳየት ተችሏል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ስንዴን ወደ ውጭ አገራት ለመላክ እንቅስቃሴ የጀመረችው በተለይ በ2015 ዓ.ም. የምርት ዘመን ለአገር ውስጥ ከሚያስፈልገው ፍላጎት በላይ ትርፍ ምርት በመገኘቱ መሆኑን መንግሥት ገልጿል። የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው መለሰ መኮንን ራሷን መመገብ የማትችል አገር ተደርጋ ትወሰድ የነበረችው ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ ማስገባት አቁማ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ደረጃ ላይ መድረሷ ሕዝባችን ቀና ብሎ መሄድ እንዲችል የሚያደርግ ትልቅ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል። የግብርና ሚንስትር መራጃዎች እንደሚሳዩት ዘንድሮ በመኸር ምርት 112 ሚሊዮን ኩንታል፣ እንዲሁም በመስኖና በበጋ ስንዴ ምርት ደግም 52 ሚሊዮን ኩንታል ይገኛል ተብሎ ይገመታል። በባለሙያዎች ዝርዝር ጥናት መሠረት በ2015 ዓ.ም. የአገር ውስጥ ፍላጎት 97 ሚሊዮን ኩንታል ነው። የፍላጎት መጠኑ ይገኛል ተብሎ ከተተነበየው አጠቃላይ የስንዴ ምርት መጠን ጋር ሲነፃፀር ትርፍ ምርት በመኖሩ 32 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ይቻላል። መንግሥት እስከ አሁን ሱዳንና ኬንያን ጨምሮ ለስድስት ገዢ ሀገራት ስንዴ ወደ ውጭ ለመላክ የ3 ሚሊዮን ኩንታል ውል ተፈራርሟል። የረድኤትና ሌሎች የሀገር ውስጥ ድርጅቶችም ከውጭ የሚገዙትን ስንዴ በሀገር ውስጥ እንዲተኩ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል የውል ስምምነት በመፈረም ላይ ነው።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተመዘገበው ውጤትም የኢትዮጵያን ንጋት ነጋሪ ነው። ከሃገር ባለፈ ቀጠናዊና አለምአቀፍ ፋይዳ ያለው ይህ መርሃ ግብር እ.አ.አ. 2019 ላይ በ4 ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ የተጀመረ ነበር። በመርሃ ግብሩ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በአጠቃላይ 22 ቢሊዮን ችግኝ መትከል ተችሏል። ይህም በእያንዳንዱ ዓመት ከታቀደው በላይ ማሳካት መቻሉን የሚያሳይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ በመርሃ ግብሩ የተመዘገበውን ውጤት በቀጣይ የህዝቦችን አንደነት እና የጋራ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ለመድገም በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

ሌላው ተስፋ ፈንጣቂ እምርታ የታየው በሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከአራት ዓመታት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ በጅምር ላይ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልጋት ገልጸው ነበር። በወቅቱ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ለጀመሯቸው ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ከ400 ቢሊዮን ብር በላይ መበደራቸውን ጠቅሰዋል። በዚህም ምክንያት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ሳይጠናቀቁ በሚቀጥለው የበጀት ዓመት አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንደማይጀመሩ አስታውቀው ነበር። ከ77 ቢሊዮን ብር በላይ የሀገር ሀብት ፈሶባቸው አንዳችም ውጤት ያላስመዘገቡት የስኳር ፕሮጀክቶች ተቋራጮች ተፈትሸው መስራት የማይችሉት ለሌሎች እንዲያስተላልፉ፤ የሚችሉትን ደግሞ በፍጥነት እንዲፈፅሙ እንደሚደረግም ተናግረው ነበር።

ባለፉት አምስት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች በከፍተኛ ጫና ውስጥ የነበሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች (የስኳሮቹን ጨምሮ) ችግራቸው ተፈቶላቸው ወደ ስራ መግባት ችለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች ያከናውን የነበረውና ለግንባታው መጓተት ምክንያት እንደነበር ሲጠቀስ የቆየው ሜቴክ በግንባታው የነበረው ተሳትፎ እንዲቋረጥ አድርገዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ግድቡ የነበረበትን ደረጃ ገመግመው የማስተካካያ እርምጃዎችን ከወሰዱ በኋላ ባደረጉት ንግግር “ፕሮጀክቱ በነበረው አመራርና አካሄድ ቢቀጥል ኖሮ ምንም አትጠራጠሩ እንኳን ዘንድሮ በሁለት ሶስት ዓመታት ውሃውን መያዝ አይችልም። ግድቡም አይገደብም ስራውም አይሰራም” ብለውም ነበር። እናም በተከናወኑ ማስተካከያዎች ባለፉት ሶስት አመታት ግደቡ 22 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ መያዝ ችሏል። ሶሰት ተርባይኖቹም ኃይል ማንጨት ጀምረው ኢትዮጵያውያን ከዓባይ ብርሃን መቋደስ ችለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ሃሳብ አመንጪነት በተጀመረው የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት ባለፉት አምስት አመታት እንጦጦና አንድነት ፓርክ፣ ወዳጅነት አደባባይ፣ የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት፣ የሳይንስ ሙዚየም ፣ የታላቁ ቤተመንግስት ግራንድ መኪና ማቆሚያ እና አብረሖት ቤተመጻህፍትን የመሳሰሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዚ ተጠናቀው ወደስራ ገብተዋል። በተለይም በታላቁ ቤተ መንግስት አምስት ቢሊየን ብር ፈሰስ ተደርጎበት የተገነባው አንድነት ፓርክ እና በውስጡ የፈረስ መጋለቢያ ሜዳ እስከነ ፈረሶች ጋጣው፣ ባህላዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና በቀድሞ ነገስታት የግብር አዳራሽ አምሳል የተሰሩ ባህላዊ ምግብ ቤቶችን ጨምሮ ዘመናዊ ካፊቴሪያዎች እንዲሁም ለጥንዶችና በቡድን ለሚዝናኑ የተዘጋጁ መናፈሻዎች፣ የህዋ መመልከቻ ማማና፣ የብስክሌት መጓጓዣና ሌሎችንም ይዞ በአምስት ሳይቶች ተከፋፍሎ የተገነባው የእንጦጦ ፓርክ የቱሪዝሙ ዘርፍ እንዲነቃቃ ከማድረግ ባለፈ የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ይገኛል።

በገበታ ለሸገር የጀመረው የኢትዮጵያን አስደማሚና አስገራሚ ውብ ገፅታዎች የሚገልጡት በአይነቱ ልዮ የሆኑ የቱሪስት መስህቦችን ማስተዋወቅና ማልማት ስራ በ “ገበታ ለሃገር” ወደ ተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ዘልቋል። በዚህም የወንጪ፣ ጎርጎራ እና ኮይሻ ፕሮጀክቶች በቢሊየን ብሮች እየለሙ ይገኛሉ። አሁን ደግሞ በአዲስ ምእራፍ “ገበታ ለትውልድ” በሚል ስያሜ የቱሪስት መዳረሻዎች በዘመናዊና ጥራታቸውን በጠበቀ መልኩ በመገንባት የቱሪዝሙ ዘርፉን ለማስፋፋት ተጨማሪ እቅድ ተይዟል።

በ”ገበታ ለትውልድ” ስር የተካተቱት ስድስት ፕሮጀክቶች ናቸው። ሁለቱ ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻዎችን ደግሞ በግል ባለሐብቶች ለማልማት ዕቅድ ተነድፏል። ፕሮጀክቶቹ 7 ቢሊዮን ብር የሚጠይቁ ሲሆን እስካሁን ከአገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን አምስት ቢሊዮን ብር ሀብት ተገኝቷል። የተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎችን የሚሸፍኑት እነዚህ ፕሮጀክቶች አሁን ያለውን የትግራይ ሰላም እንደሚያጠናክር የሚታሰበው የገረዓልታ ፕሮጀክት፣ ወሎ ላይ የሐይቅ እስጢፋኖስ ዳርቻ ሪዞርት፣ በኦሮሚያ ላይ የጅማ ፕሮጀክት ፣ በአፋር ፓል በተባለ አካባቢ የሚገነባው ፕሮጀክት፣ በደቡብ ክልል አርባምንጭ እና በሶማሌ ክልል የሚገነቡ ናቸው። በግል ባለሐብቶች ከሚገነቡት ፕሮጀክቶች ደግሞ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ህዳሴው ግድብ አካባቢ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሚዛን አካባቢ ቦታዎች ተለይተዋል። ፕሮጀክቶቹ ከትንሳኤ እና ከኢድ አል ፈጥር በዓላት ማግስት በይፋ ይጀመራሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተካሄዱ የሚገኙት የሸገር ወንዝ ልማት፣ ትራፊክ ማኔጅመንት ማዕከል፣ ሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር፣ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን መልሶ ማቋቋሚያ እና 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ተበጅቶለት እየተከናወነ ያለው የአድዋ ሙዚየም ፕሮጀክት ህንፃ ግንባታና ሌሎችም ግዙፍ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ ይገኛሉ።

የእነዚህ ፕሮጀክቶች ዋነኛ ተዋንያን የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች መሆናቸው ደግሞ የኢትዮጵያን ንጋት የሚያመላክት ነው። የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ 8ኛው የአፍሪካ ማሃንዲሶች ሳምንት እና 6ኛው ኢንጂነሪንግ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሲካሄድ ባደረጉት ንግግር ለውጭ የዲዛይን ባለሙያዎችና ግንባታ ሰራተኞች ይሰጡ የነበሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች እንዲከናወኑ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ለአብነትም በአዲስ አበባ ዙሪያ የተሰሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች የዲዛይን ባለሙያዎች፣ የግንባታ ተቋራጮችና ባለቤቶች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ገልጸው ይህም አፍሪካውያን የሚገጥማቸውን የመሰረተ ልማት ችግር በራሳቸው ባለሙያዎች መፍታት እንደሚችሉ ማሳያ መሆኑን መጠቆማቸው ይህን የሚያስረዳ ነው። እውነተኛ ፌዴራሊዝምን እወን ከማድረግና ራስን በራስ የማሰተዳደር መብትን ከማረጋገጥ አንጻርም ለዘመናት ሲቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎች በለውጡ ዘመን ተግባራዊ ምላሽ ማግኘት ጀምረዋል። በዚህ መሰረት ሁለት ተጨማሪ አዳዲስ ክልሎች ተፈጥረዋል። የሲዳማ ዞን ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም በተካሄደ ሕዝበ ውሳኔ ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ተለይቶ ራሱን የቻለ ክልል መሆን ችሏል። ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በተካሄደ ማግስት አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ወጥተው የጋራ አንድ ክልል ለመመስረት ሕዝበ ውሳኔ አካሄደዋል። በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ መሰረትም የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ የምዕራብ ኦሞ ዞን፣ የቤንች ሸኮ ዞን፣ የካፋ ዞን፣ ዳውሮ ዞን እና የሸካ ዞን በጋራ 11ኛው ክልል በመሆን የደቡብ ምዕራብ ክልል በይፋ ተመስርተዋል። ከዚህም በተጫመሪ በደቡብ ክልል ተጨማሪ ክለሎች ለማደራጀት ድምጽ ተሰጥቶ ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

እንደ መውጫ

በኢትዮጵያውያን የተለያዩ አከባቢዎች በተካሄዱ መራር የተቃውሞ ትግሎችና በቀድሞ ኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠረው የለውጥ ኃይል እውን የሆነው ለውጥ አምስተኛ አመቱን ደፍኗል። ቀደምት ሀገራዊ ተሞክሮዎችን በመውሰድ ለውጡ በሰላማዊ መንገድ፣ በይቅርታ እና በመደመር መንፈስ ያለፉት አምስት አመታትን ተጉዟል። ለቀደመው ስህተት ሕዝብን ይቅርታ ከመጠየቅ ጀምሮ በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ለእስር የተዳረጉ ዜጎችን ተፈተዋል፤በስደት ከሀገር የወጡትን እንኳን ደህና መጣችሁ ተብለዋል፤ በብዙ መልኩ የተሸረሸረው ኢትዮጵያዊነት ደምቆ እንዲወጣ፤ የሕዝቡም የፖለቲካ ተሳትፎና በሃገር ጉዳይ የወሳኝነት ሚና ከፍ እንዲል ተሰርቷል። በሃገሪቱ ፖለቲካ ከተሳትፎ ባለፈ የወሳኝነት ሚና ያልነበራቸውና በሀገራቸው ጉዳይ አጋር በመባል ሲጠሩ የነበሩ ክልሎች በሃገራቸው ጉዳይ ተሳታፊና ውሳኔ ሰጪ የሆኑበትን አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ተከፍቷል። በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በፖለቲከኞች መካከል የሚስተዋለውን ልዩነት ወደ አንድ ለማምጣትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ቁልፉ መፍትሔ ምክክር መሆኑ ታምኖበት ብሄራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሟል። ምክክሩ አለመግባባትን ያረግባል፤ መተማመንን ይፈጥራል፤ ወደ ሠላም ያመጣናል በሚል ብዙዎች ተስፋን ጥለውበታል። መንግስት እንደ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ፍርድ ቤቶች ያሉ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ገለልተኛ ሆነው እንዲሠሩ ያሳየው ቁርጠኝነትም መልካምና አበረታች ነው። እነዚህ ተቋማት ከመንግሥት ገለልተኛ ሆነው እንዲሠሩ ያለው ዝግጁነት፣ ምክክሩ በተሻለ ሁኔታ ሊካሄድ እንደሚችል የሚያሳይ ተስፋ ሰጪ ተግባር ነው። በተለይም አካታች ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ የልዩነት ሀሳቦችን በአንፃራዊነት አቀራርቦ የይቅርታና የፍቅር ድልድይ በመዘርጋት፣ ዘላቂ ሠላምን ማረጋገጥ የሚያስችል አይነተኛ መሣሪያ በመሆኑ በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ተጥሎበታል።

ባለፉት አምስት አመታት በተለያዩ አካባቢዎች በሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች፣ በሰሜኑ ጦርነት ፣ በድርቅ፣ በኮቪድ 19፣ በኑሮ ውድነት እና በመልካም አስተዳደር ችግር ኢትዮጵያ ተፈትናለች። ኢትዮጵያ በእነዚህ ሁሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆናም ቢሆን የተሻለ ኢኮኖሚ በመገንባት ተስፋዋን በማጽናት ላይ ትገኛለች። በዚህም ተጨባጭ ለውጥ እና ውጤት ከመመዝገቡ ባሻገር የሚታይ ፈጣን የኢኮኖሚ ለውጥም መምጣቱን አለማቀፍ ተቋማት ሳይቀር እየመሰከሩ ነው። ባለፉት አመታት ኢትዮጵያ የጠነከረ የግሪን ኢኮኖሚ መገንባት በመቻሏ አለም አቀፍ እውቅና ተችሯታል። ትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ብቻ ሳይሆን በአጭር ጊዜ አጠናቆ ለፍሬ ማብቃትን ማሳየት ተችሏል። ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት አመታት ትልልቅ ስኬቶችን ብታስመዘግብም፣ ተጋርጠውባት የነበሩ በርካታ ችግሮች ለውጡ በታሰበው ልክ ውጤት እንዳይመጣ እንቅፋት ሆነዋል። ከመጣንበት መንገድ እየተማርን ስህተቶቻችንን እየቀነስን ወደፊት መጓዝ ከቻልን፣ ቀጣዮቹ ዓመታት የኢትዮጵያ ልዕልና አይቀሬ ነው።

ኢትዮጵያ ከተስፋ በላይ በእውን የሚታዮ ነገሮችን በውስጧ የያዘች ትልቅ ሀገር ነች። ባለፉት አመታት ተስፋን በስራ እየቀየሩ ከፍ ማለትና ማደግ እንደምትችል አረጋግጣለች። ኢትዮጵያ ከተሰራባት እንደምትለማ፣ መሬቱ ከታረሰና ከተጠቀምንበት የትኛውም አከባቢ ለኢትዮጵያ ንፍግ እንዳልሆነ በተግባር ታይቷል። ኢትዮጵያ በዘርፈ ብዙ ልማቶች በቅርቡ ብልፅግናዋን እንደምታረጋግጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አመላካች መሆናቸውን በርካቶች እየመሰከሩ ነው። የአገሪቱ ኢኮኖሚ በየወቅቱ ያጋጠሙትን ውስጣዊና ውጪያዊ አሻጥሮች ተሻግሮ አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢንቨስትመንት መሳብ የሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛል። ይህም አሁን ካለው አገራዊ ሰላም አንጻር በቀጣይ የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆን፤ በዚህም ዜጎች የለውጡን ትሩፋት የሚያጣጥሙበትን ዕድል የሚፈጥር ይሆናል!

ተስፋ ፈሩ

ዘመን መጽሔት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም  

Recommended For You