ትኩረት የሚሻው የመድሃኒት አቅርቦት

ጤና ይስጥልን! ከሀብት ሁሉ የሚልቅ ሀብት ጤና ነው። የአገሬ ሰው ሲመርቅ ረጅም እድሜ ከጤና ጋር ይስጥህ ይላል፤ ፈጣሪውንም `ጤናዬን አትንሳኝ` ብሎ ይለምናል። በሕይወት ለመቆየት፣ ሰርቶ ለመለወጥ፣ ቤተሰብና ሀብት ለማፍራት ጤና መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታ ነውና በተቻለን መጠን ጤናችንን ለመጠበቅ እንሞክራለን። ጤናችንን የሚያቃውስ ሕመም ከገጠመን ደግሞ ወደ ጤና ተቋማት እናመራለን፤ ከፈጣሪ ቀጥሎ ፈውስ እናገኛለን ብለን የምናምነው በእነዚህ ተቋማት ነውና። የጤና ተቋማቱ አገልግሎት የመጨረሻ ግብ ደግሞ የታካሚዎችን ህመም የሚያስታግሱና የሚፈውሱ መድሃኒቶችን ማዘዝና የታዘዙላቸውን መድሃኒቶች በታከሙበት ጤና ተቋም እንዲያገኙ ማስቻል ነው።

ይሁን እንጂ፣ በአሁኑ ጊዜ በግልጽ እንደሚስተዋለው ማህበረሰቡ ወደ ህክምና ተቋም ለምርመራ ሄዶ የታዘዘለትን መድሃኒት እዚያው ምርመራ ባደረገበት፣ በተለይም፣ በአብዛኛው የመንግስት የጤና ተቋማት ማግኘት ከባድ እየሆነበት መጥቷል። ከጤና ተቋማቱ ዘንድ “መድሃኒቱ የለም” ማለትና አንዳንድ ጊዜም ከመርማሪ ሃኪሞች መድሃኒቱን ውጪ ግዙ ብሎ መታዘዝም እየተለመደ መጥቷል። በዚህም ምክንያት ህብረተሰቡ ለተጨማሪ ወጪ ከመዳረጉም ባሻገር በመድሃኒት ፍለጋ የሚያሳልፈው ውጣ ውረድ ከበሽታው ለመፈወስ የሚወስድበትን ጊዜ እያራዘመው፣ ለተጨማሪ በሽታ እየዳረገውም ይገኛል።

ከዚህ አንጻር፣ በአገራችን የመድሃኒት ግዢ ሂደትና አቅርቦት ምን ይመስላል፤ በመድሃኒት አቅራቢ አገልግሎትና በጤና ተቋማት መካከል ያለው ግንኙነትስ ምን መልክ አለው፣ በሚሉና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸውን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ንጉሴ፣ ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ፋርማሲ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ደበላ ገመዳ እና ከአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ፋርማሲ ዳይሬክተር አቶ አበራ ገላና ጋር ቆይታ አድርገናል።

የመድሃኒት ግዢ

ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት፣ የመድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ለመንግሥት የጤና ተቋማትና ክፍተት ላለባቸው የግል የጤና ተቋማት መድሃኒቶችን የሚያቀርብ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ግን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እየሰራ ያለው ለመንግሥት የጤና ተቋማት ብቻ ነው። አገር ውስጥ ከሚገቡት ጠቅላላ መድሃኒቶች መካከልም ተቋሙ 86 ከመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይወስዳል።

ከሶስት ዓመታት በፊት፣ 75 ከመቶ የሚሆኑ መድሃኒቶችን ከውጪ አቅራቢዎች 25 ከመቶ ያህሉን ከአገር ውስጥ ይገዛ የነበረ ቢሆንም፣ የአገር ውስጥ ምርት በመዳከሙ ምክንያት በዚህ ዓመት 92 ከመቶ መድሃኒት ከውጪ አቅራቢዎች፣ ሲገዛ ስምንት ከመቶ ብቻ ከአገር ውስጥ አቅራዎቢዎች ለመግዛት ተገዷል። ቀደም ሲል በአገር ውስጥ ይመረቱ የነበሩ፣ እንደ ሽሮፕ፣ በደም ስር የሚሰጡ ፈሳሾች የመሳሰሉት፣ አሁን ላይ እየተመረቱ ባለመሆናቸው የአገር ውስጥ ግዢ ቀንሷል። ቢሆንም፣ የአገር ውስጥ አቅምን አሟጦ ከመጠቀም አንጻር መጀመሪያ የአገር ውስጥ ጨረታ በማውጣት፣ የአገር ውስጥ አቅራቢ እድል እንዲያገኝ ከተደረገ በኋላ፣ ዓለም አቀፍ ጨረታ እንዲወጣ ይደረጋል። የአገር ውስጥ አቅራቢዎች ለብቻቸው ከሚሳተፉበት በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ጨረታም ተሳታፊ ይሆናሉ። ዋጋቸው እስከ 25 ከመቶ ከፍ ቢል እንኳ ቅድሚያ የማግኘት እድል አላቸው። እነዚህ እድሎች ተመቻችተውም የአገር ውስጥ አቅራቢ ድርሻ ግን ከ10 ከመቶ በታች ነው።

አቶ አበራ እንደነገሩን ደግሞ፣ አማኑኤል ሆስፒታል የመድሃኒት ግዢ የሚፈፅመው ከመድሃኒት አቅርቦት አገልግሎት ጋር የዓመት ውል በመዋዋል ሲሆን፣ አገልግሎቱ ለጤና ተቋሙ በየሳምንቱ መድሃኒት ያቀርብለታል። ከአገልግሎቱ ያጣውን መድሃኒት ደግሞ ጨረታ በማውጣት ከግል አቅራቢዎች ይገዛል። በተጨማሪም ከሌሎች የጤና ተቋማት አገልግሎት ላይ የማይውሉ መድሃኒቶችን በቅያሬ መልክ ወይም በልገሳ ይቀበላል።

አገልግሎቱ ለመድሃኒት ግዢ ምን ያህል ያወጣል?

የመድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት የመግዛት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ይህም ቢሆን፣ በሌሎች ሸቀጦችላይ የሚታየው የፍላጎትና የአቅርቦት አለመመጣጠን በመድሃኒትም ላይ አለ ይላሉ። ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፣ አገልግሎቱ ባለፈው ዓመት ለመደበኛ መድሃኒት ግዢ ብቻ 10 ቢሊየን ብር አውጥቷል። ከዚህ፣ የተገላባጭ መድሃኒት ፈንድ በተጨማሪ የ40 ቢሊየን ብር ግዢና ድጋፍም አከናውኗል። ተገላባጭ መድሃኒት ፈንድ የሚባለው አገልግሎቱ መድሃኒቶችን ገዝቶ፣ ጥቂት ትርፍ ጨምሮበት እያገላበጠ የሚያስተዳድረው ገንዘብ ሲሆን፣ ተቋሙ ለትርፍ የተቋቋመ ባለመሆኑ ጭማሪው አስተዳደራዊ ወጪዎችን ብቻ መሸፈንን ታሳቢ ያደረገ ነው። የጤና ፕሮግራም ገዝቶ የሚያገኘው የአገልግሎት ክፍያም ለመደበኛ በጀቱ እድገት ትልቅ አስተዋፅዖ ያደርግለታል። ሌላው፣ ከጤና ሚኒስቴርና ከተለያዩ ለጋሽ ተቋማት ጋር ተግባብቶ ውል በመግባት፣ የኤች አይቪ፣ ቲቪ፣ ወባ መድሃቶችና ክትባቶችን በማሰራጨት የሚያገኘው ገቢ ሲሆን፣ አገልግሎቱ፣ በጥቅሉ ባለፈው ዓመት የ51 ቢሊየን ብር ያህል ግዢ፣ አገልግሎትና ድጋፍ አከናውኗል። አቶ ደበላ በበኩላቸው የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ባለፈው ዓመት ከተለያዩ አቅራቢዎች የ135 ሚሊየን ብር መድሃኒት ግዢ እንደፈጸመ ይናገራሉ። አማኑኤል ሆስፒታል ደግሞ የ60 ሚሊየን ብር መድሃኒት ግዢ መፈጸሙን አቶ አበራ አሳውቀዋል።

የዱቤ ሽያጭና ግዢ ምን ይመስላል?

“የግል አቅራቢዎች ክፍያ ወዲያውኑ ስለሚጠይቁና በጠየቁ ጊዜ ክፍያ ለመፈጸም የበጀት ጉዳይ እጃችንን ስለሚይዘው በዚህ ምክንያት የማንገዛቸው መድሃኒቶች ይኖራሉ” ያሉት አቶ ደበላ፣ የዱቤ ግዢ ለመፈጸም የማይቸገሩት ከመድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት መሆኑን ይናገራሉ። አያይዘውም፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በአሁኑ ሰዓት፣ ከአገልግሎቱ የ50 ሚሊየን ብር እዳ እንዳለበት፣ ይህም መድሃኒት ለማቅረብ ለኮሌጁ ተግዳሮት እንደሆነበት ይገልጻሉ። የአገልግሎቱ ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን በበኩላቸው፣ የመድሃኒት አቅርቦት ስርጭት በቀጥታ ክፍያና በዱቤ ሽያጭ እንደሚካሄድ ጠቅሰው፣ የዱቤ ሽያጭ መጠን ከቀጥታ ክፍያ ሽያጭ መጠን እንደሚበልጥም አንስተዋል። እርሳቸው እንዳሉት፣ የዱቤ ሽያጭ አከፋፈል በጣም ትልቅ ችግር የፈጠረ፣ አገልግሎቱንም አጣብቂኝ ውስጥ የከተተ ነው። ይህንን ችግር ለመቅረፍ በቅርብ ጊዜያት የማስተካከያ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። የዱቤ ሽያጭ ስርዓት እንደ ስርዓት ችግር ባይኖርበትም፣ አስተዳደሩ ላይ ግን ከአገልግሎቱም ሆነ ከጤና ተቋማት ዘንድ ክፍተት አለ ያሉት አቶ ሰሎሞን፣ በተለይም፣ ከጤና ተቋማቱ ዘንድ ገንዘቡ የመንግሥት ነው በሚል እሳቤ ወደ ክፍያ አለማተኮር፤ በቂ በጀት ይዞ ከማስተዳደር አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል። እርሳቸው እንደገለጹት፣ አገልግሎቱ በአሁኑ ሰዓት 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ያልተከፈለው ዱቤ በጤና ተቋማት ዘንድ ሲኖረው፣ከዚህ ውስጥ ወደ 600 ሚሊየኑ በአንድና በሁለት ወራት ውስጥ ይከፈላል ተብሎ የሚጠበቅ ነው። ሌሎች እስከ አምስት ዓመታት የቆዩ ውዝፍ ክፍያዎች ካሉባቸው ተቋማት ጋር ደግሞ በመመካከር ወደ ክፍያ እንዲመጡ፣ በምክክር አልመጣ ያሉትን ደግሞ ክስ በመመስረት ወደ ሕግ በመውሰድ ክፍያዎችን የመሰብሰብ ሥራ እየተሰራ ነው።

ከዱቤ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመፍታት፣ “ውል የተገባለት የአቅርቦት ሥርዓት”ን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ በሥርዓቱ የጤና ተቋማት ከአገልግሎቱ ጋር ውል በመግባትና ቅድመ ክፍያ በመክፈል ፍላጎታቸውን በተመጠነ መንገድ የሚያገኙበት ሲሆን፣ ይህም ተጠያቂነት ያለው አሰራር እንዲኖር፣ መድሃቶችንም ከብክነት የሚከላከል፤ የአገልግሎቱን የመግዛት አቅም በመጨመርም የክምችት መጠኑን ከፍ እንዲያደርግ የሚረዳው እንደሆነ አስገንዝበዋል።

የመድሃኒት ስርጭቱ ምንን መነሻ ያደረገ ነው?

አገልግሎቱ በመላው አገሪቱ 19 ቅርንጫፎች ሲኖሩት፣ ሁለቱ በትግራይ ክልል የሚገኙና ወደ ስራ እየገቡ ያሉ ናቸው፤ “እኛ ከቅርንጫፎቻችን ጋር የምንገናኝበት፣ ቅርንጫፎቻችን ከጤና ተቋማት ጋር የሚገናኙበት የኮምፒውተር ሥርዓት አለ” ያሉን ዳይሬክተሩ፣ በእነዚህ ቅርንጫፎቹ አማካኝነት የሚደርሰውን የትመናና ምጠና ስራ እንዲሁም የመግዛት አቅምን ታሳቢ በማድረግ መድሃኒቶችን እንደሚያቀርብ፣ በዚህ አሰራር በአገራችን ካሉ ከ4000 በላይ ጤና ጣቢያዎችና ከ600 በላይ ሆስፒታሎች መካከል ለ80 ከመቶ ያህሉ ተደራሽ መሆን እንደቻለ፣ የመረጃ ሥርዓት መዘርጋቱም የት ቦታ የትኞቹ መድሃኒቶች አሉ ወይም የሉም የሚለውን ለማወቅ እንዳስቻለው ገልጸዋል።

አገልግሎቱ ምን ያህል መድሃኒቶችን ያቀርባል! ምን ያህልስ በክምችት ይዟል!

አሁን ላይ አገልግሎቱ 262 መድሃኒቶችንና 151 የህክምና መገልገያዎችን በግዢ ያቀርባል። እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ እነዚህ መድሃኒቶች ወደ ተጠቃሚው እስኪደርሱ ድረስ ግን ያለው ችግር በጣም ሰፊ ነው። አገልግሎቱ መድሃኒቶችን ሙሉ በሙሉ ቢገዛም እንደ በጀት፣ ከፋርማሲወደ ስቶር ያለው ሂደት፣ የሀኪሞች መድሃኒቶችን በብራንድ የማዘዝ ሁኔታ፣ በአጠቃላይ ያለመናበብ ችግሮች ከአገልግሎቱ ተነስቶ ወደ ጤና ተቋሙ ፋርማሲ፣ ከዚያም እስከ ተጠቃሚው እስኪደርስ ድረስ ረጅም ሂደቶችንና ተግዳሮቶችን ያሳልፋል። ስለሆነም አገልግሎቱ መድሃኒቶችን 100 ከመቶ አቀርባለሁ ቢልም፣ የተለያዩ አስቸጋሪ ሂደቶችን አልፎ ወደ ፋርማሲና ተጠቃሚው እስኪደርስ ያለው ሂደት አፈጻጸሙን ከመቶኛ ይቀንሰዋል። አቶ ደበላም አገልግሎቱ መድሃኒቶችን በበቂ መጠን አቀርባለሁ ቢልም፣ የሚያቀርቡት መድሃኒት ሆስፒታሉ ከሚፈለገው ከ50 እስከ 60 በመቶ ያህሉን ብቻ እንደሆነ፤ ይህ ልዩነት ለምን መጣ የሚለውን ደግሞ ማጣራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ከክምችት ጋር ተያይዞ ዳይሬክተሩ እንዳሉት፣ አገልግሎቱ ከሚያቀርባቸው ከላይ ከተጠቀሱ መድሃኒቶችና የህክምና መገልገያዎች መካከል 84 ከመቶ ያህሉ በክምችት ይገኛሉ። በመሆኑም 16 ከመቶ የሚሆኑት በግዢ ሂደት ላይ ያሉ ናቸው። አገልግሎቱ፣ በክምችት አለኝ የሚለው የመድሃኒት አቅርቦት ቢያንስ ለአንድ ወር የሚያቆይ የመድሃኒት ክምችትን ነው።ይሁን እንጂ መሠረታዊና ሕይወት አድን የሚባሉ ቅድሚያ የሚሰጣቸው መድሃኒቶች ግን ሁሉም በሚባል ደረጃ በክምችት ውስጥ ይኖራሉ። መድሃኒቶች በክምችት በማይኖሩበት ጊዜ የተለያዩ እርምጃዎች ይወስዳሉ። አንደኛው፣ ከግዢ ኤጀንሲ ጋር በመሆን የቀጥታ ግዢ ሥርዓትን መተግባር ሲሆን፣ ሁለተኛው፣ በባህር ሳይሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ በአየር ትራንስፖርት አገር ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ዓለም አቀፍ ጫናዎች እየቀነሱ ስለመጡና ከሰላም መስፈን ጋር ተያይዞ ሰፊ ስራ መስራት ስለሚጠበቅ፣ የሚስተዋሉ ችግሮችን በሂደት እየተፈቱ የክምችት መጠንንም መጨመር ይቻላል።

የመድሃኒት ግዢ ሂደትና አቅርቦት ተግዳሮቶች

አቶ ሰሎሞን በሰጡን ገለጻ፣ ኮቪድ፣ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ላይ የነበረው ጦርነትና በዚህ ሳቢያ የዓለም አቀፍ አቅራቢዎችና የፋይናንስ ተቋማት እምነት ማጣት፣ በግዢ ሂደት የተዋናዮች መብዛት፣ ለሎጂስቲክ አደጋ ተጋላጭነት የመድሃኒት ግዢ ሂደት ተግዳሮቶች ነበሩ። ሌላው አሁንም ያለ ችግር ደግሞ የአቅራቢ ማነስ ነው። ከውጪ ከሚገዙ መድሃኒቶች 78 ከመቶ ያህሉ ውስን አቅራቢ ያላቸው፣ የተቀሩት ደግሞ አንድ ብቻ አቅራቢ ያላቸው ናቸው። ምንም አይነት አቅራቢ የሌላቸው ልዩ መድሃኒቶችም አሉ። በዚህ ሁኔታ ውድድር አይኖርም፣ ከፍተኛ የሆነ የአቅርቦት መቆራረጥም ያጋጥማል።

አገልግሎቱ አቅርቦት ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን አካሂዷል። ህንድና ቻይና አገራትም በአካል በመሄድ መስተካከል ያለባቸውን ነገሮች ለማስተካከል ጥረት አድርጓል። ከኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ጋርም ምቹ ሁኔታን የመፍጠር ሥራ እየሠራ ነው። በዚህም፣ ብዙ አቅራቢዎች በመመዝገብ ላይ ስለሆኑ፣በዚህ ዓመት የተሻለ ለውጥ ይኖራል የሚል ተስፋ አለ። በጣም ውስን አቅራቢ ያላቸው የካንሰር፣ የኩላሊት ንቅለ ተከላ፣ የልብ መድሃኒቶች አገር ውስጥ ስለማይመረቱ፣ አቅራቢዎቻቸውም በጣም ጥቂት በመሆናቸው፣ ውል ይዞ የማቋረጥ ፈተናዎች ያጋጥማሉ። ለዚህ መፍትሔ የሚሆን ሥርዓት እየዘረጋን ነው ያሉት አቶ ሰሎሞን፣ ቀዳሚው ተግባር ከአቅራቢዎች ጋር ተቀራረቦና ተቀናጅቶ መስራት ሲሆን፣ ሌላኛው የማዕቀፍ ግዢ ስርዓት መዘርጋት ነው። በዚህ ሥርዓት አቅራቢዎች አንድ ጊዜ ተወዳድረው እስከ ሶስት ዓመት መድሃኒት ማቅረብ የሚችሉበት ሥርዓት ተዘርግቷል። በዚህም ከባድ የአቅርቦት መቆራረጥ የነበረባቸው መድሀኒቶች ላይ የመጣው ለውጥ በጠንካራ ጎን የሚታይ ነው።

ቀደም ሲል በነበረው የበጀት እጥረት ከመድሃኒት አለመገኘት ጋር ተያይዞ ትልቅ ክፍተት እንደነበረ የተናገሩት አቶ አበራም፣ በዚህ ዓመት የውስጥ ገቢን በማጠናከር የፋርማሲውን መድሃኒት የማቅረብ አቅም የተሻለ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። አቶ ደበላም፣ የሆስፒታሉ የመድሃኒት አቅርቦትን ለማሳደግ ከሚሰሩ ስራዎች በተጨማሪ፣ በተለይም በቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓትን በመተግበር መድሃኒቶች ሲጠፉ፣ ከሌሎች ሆስፒታሎች፣ ጤና ተቋማትና በሆስፒታሉ ውስጥ ካሉ ፋርማሲዎች መድሃኒቱ ወደ ተፈለገበት ቦታ እንዲመጣ ማድረግ ተችሏል። በዚህም ታካሚዎች መድሃኒት ፈልገው እንዳያጡ በተደረገው ሥራ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንደተቻለ አስረድተዋል።

ተቋሙ ማቅረብ ያልቻላቸው መድሃኒቶች አሉ ወይ?

አገልግሎቱ ማቅረብ ያልቻላቸው መድሃኒቶች አሉ ወይም የሉም ስንል ተቋሙ የሚያቀርበው ምንድነው የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ አገልግሎቱ 262 መድሃኒቶች፣ 151 የህክምና መገልገያዎችና ሌሎች ኬሚካሎች በአጠቃላይ 1ሺህ 20 ዝርዝሮችን እንደሚያቀርብ አንስተው፣ ይህ ዝርዝር ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በየሁለት ዓመቱ የሚከለስ፣በሂደቱ ደግሞ ቁጥሩ ሊቀንስም ሆነ ሊጨምር እንደሚችል ይጠቁማሉ። በመሆኑም የሉም ተብለው የሚነሱ መድሃኒቶች በተቋሙ የአቅርቦት ዝርዝር የማይታቀፉ ብራንድ መድሃኒቶች ናቸውም ብለዋል። አቶ ደበላ ደግሞ፣ አገልግሎቱ ለሁሉም ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ተመሳሳይ መድሃኒቶችን እንደሚያሰራጭ ጠቅሰው፣ ስርጭቱ የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የሚሰጠውን ዘርፈ ብዙ የህክምና አገልግሎት ታሳቢ ያደረገ አይደለም ይላሉ። ሆስፒታሉ ለግዢ የሚያቀርባቸው 1 ሺህ 400 መድሃኒቶች፣ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችና ኬሚካሎች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ 360ዎቹ መድሃኒቶች ናቸው። በመሆኑም ከላይ እንደተገለጸው ከአገልግሎቱ ማግኘት ያልቻላቸውን ከግል አቅራቢዎች በመግዛት ታካሚዎች ከሚፈልጓቸው መድሃኒቶች መካከል 70 ከመቶ በላይ የሚሆኑትን በሆስፒታሉ በሚገኙ 12 ፋርማሲዎች ውስጥ እንዲያገኙ ማድረግ ችሏል። አቶ ተፈራም በተመሳሳይ ሁኔታ አማኑኤል ሆስፒታል ለሚሰጠው የህክምና አገልግሎት የሚጠቅሙ፣በተለይም የሚጥል በሽታ/Epilepsy/ መድሃኒቶችን ማግኘት ከባድ እንደሆነ ተናግረዋል።

የአገልግሎት ጊዜያቸው የሚያልፉ መድሃኒቶች

ከመድሃኒት ጋር ተያይዞ ብክነት አንዱ ፈተና እንደሆነ ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ፣ በተቻለ መጠን የመድሃኒት ብክነትን ለመቀነስ አገልግሎቱ ጥረት እንደሚያደርግም ይጠቁማሉ። እርሳቸው እንደገለጹት፣ አገልግሎቱ መድሃኒቶችን ሲገዛ ከሚከተላቸው የግድ ከሚባሉ መስፈርቶች ቀዳሚው አቅራቢው የጥራት ማረጋገጫ አለው ወይ የሚለው ሲሆን፣ ሁለተኛውእንደየመድሃኒቱ ባህርይ ከተመረተበት ጊዜ አንጻር 80 ከመቶ እድሜ ያለው መሆኑ ነው። እነዚህን መስፈርቶች አሟልቶ አነስተኛ ዋጋ የሰጠ አቅራቢ መድሃኒቶችን እንዲያቀርብ ይደረጋል። በዚህም የመድሃኒቱ የአገልግሎት ዘመን የሚያልፍበት ሁኔታ አይፈጠርም። ነገር ግን በተለያየ ምክንያት፣ ለምሳሌ፡- አቅራቢ የሌላቸውን መድሃኒቶች በመጠን ከፍ ተደርጎ ተገዝቶ፣ ጤና ተቋማት ሳይጠቀሙበት ሲቀሩ ጊዜው የሚያልፍበት መድሃኒት ሊኖር ይችላል። በሌላ መንገድ፣ተቋሙ ከሚገዛቸው መድሃኒቶች መካከል 2 በመቶኛው የአገልግሎት ዘመናቸው ሊያልፍ ይችላል በሚል የተቀመጠ መስፈርት መኖሩን ዳይሬክተሩ ይጠቅሳሉ። አያይዘውም፣ አገልግሎቱ ባለፈው ዓመት ከገዛቸው መድሃኒቶች መካከል 0.74ቱ የአገልግሎት ጊዜያቸው ማለፉን አንስተዋል። “ነገር ግን የዓለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠውን መስፈርት ተግባራዊ ማድረግን በተመለከተ፣ አገራዊ ምልከታን መነሻ ያደረገ ምላሽ ለመስጠት ተቋሞች ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም መድሃኒቶቹ አገልግሎቱ ላይ እያሉ የአገልግሎት ዘመናቸው ገና ሆኖ፣ በጤና ተቋማት በሚኖራቸው ቆይታ ግን ጊዜያቸው ሊያልፍ ይችላል” ብለዋል።

ጊዜው ያለፈበት መድሃኒት በምንም ሁኔታ ወደ ጤና ተቋማት አይሰራጭም ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የአገልግሎት ጊዜያቸው የደረሱ መድሃኒቶችም እኛ ጋር ከሚበላሹ ጤና ተቋማት ሄደው ይበላሹ የሚል አቋምም የለንም ብለዋል። እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፣ ተቋሙ ላይ መድሃኒት በብዛት ተከማችቶ የአገልግሎት ጊዜው ሊያልፍ ሲል በመነጋገር የግሉ ዘርፍ በፍላጎት እጨርሳለሁ ብሎ ያመነበትን ያህል ግዢ እንዲፈጽም፤ የመንግሥት የጤና ተቋማትም በየሁለት ወሩ ይወስዱ የነበረውን መድሃኒት የአራት ወር እንዲሰጣቸው ይደረጋል፤ ይሁን እንጂ ያለ ጤና ተቋማቱ ፍላጎት የሚሰራጭ መድሃኒት ግን የለም።

አቶ ደበላ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ መድሃኒቶች የሚገዙት ተጠቃሚውንና የበሽታውን ባህሪ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ግምት ደግሞ ምንጊዜም ትክክል አይመጣም። በዚህ ምክንያት የመድሃኒቶች የአገልግሎት ጊዜ ሊያልፍ ይችላል። ለምሳሌ፡- ባለፉት ዓመታት የኮቪድ ህመምተኞችን ለማከም የተገዙ መድሃኒቶች፣ በሽታው በእጅጉ በመቀነሱና ተጠቃሚ ስለሌለው በብዛት የአገልግሎት ጊዜያቸው እያለፈባቸው ይገኛሉ። “ሌሎች፣ በብዛት የአገልግሎት ጊዜያቸው የሚልፍባቸው መድሃቶች ደግሞ እንደ ኤች አይ ቪ የመሳሰሉ የፕሮግራም መድሃኒቶች ሲሆኑ፣ እነዚህ መድሃኒቶች በበጀት ሳይሆን በዓለም አቀፍ ድጋፍ የሚገኙ ናቸው፤ ወደ ጤና ተቋማት በብዛት ስለሚገቡም ሳያልቁ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያልፋል፤ ተጠቅመንም ለሌሎች አካፋፍለንም የተረፉና የአገልግሎት ዘመናቸው ያለፉ ባለፉት አራት አመታት የገቡ 18 ሚሊየን ብር የሚገመት መድሃኒት አቃጥለናል” ያሉት የፋርማሲ ዳይሬክተሩ፣ ከመድሃኒት አቅራቢ አገልግሎትና ከግል አቅራቢዎች በበጀት ከተገዙ መድሃኒቶች መካከል አንድም መድሃኒት የአገልግሎት ዘመኑ ያለፈ የለም ብለዋል። የአገልግሎት ዘመናቸው የሚያልፉ መድሃኒቶችም ከጠቅላላው ከሚገዙ መድሃኒቶች አንጻር ያለው ምጣኔ የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው መስፈርት ያነሰ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ አቶ አበራ ገለጻ ደግሞ፣ የአገልግሎት ጊዜያቸው ቅርብ የሆኑ መድሃኒቶች አይገዙም። አማራጭ ከጠፋ ግን በጣም አስፈላጊ የሆኑ መድሃኒቶች በጥቂት መጠን እንዲገዙ ይደረጋል። እነዚህ ጥረቶች ተደርገው ግን ባለፈው ዓመት የፕሮግራም መድሃኒቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ 70 ሺህ ብር የሚገመት መድሃኒት የአገልግሎት ጊዜው ሊያልፍ ችሏል።

መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎቱ ጤና ተቋማት መድሃኒቶችን ያለፍላጎታቸው እንዲገዙ ያስገድዳል ወይ ለሚለው ጥያቄ አቶ አበራ፣ “የፕሮግራም መድሃኒቶችን ከፍላጎት ውጪ እንድንገዛ ቀላቅሎ ይልካል” የሚል ምላሽ ሲሰጡ፣ አቶ ደበላ ደግሞ “ሙሉ በሙሉ ያስገድዳል፣ ሙሉ በሙሉ አያስገድድም ለማለት ይከብዳል በማለት፣ “ተቋሙ የአገልግሎት ጊዜያቸው የደረሰ መድሃኒቶችን ትፈልጋለህ ወይስ አትፈልግም ብሎ ጥያቄ ሲያቀርብ ለስድስትና ለሶስት ወር የሚጠቀምበት ታካሚ ሊኖር ይችላል በሚል እንደ ጤና ተቋም አንፈልግም ብለን አንጨክንም ስለሆነም መድሃኒቶቹን የሚጠቀመው ይጠቀምና ሌላው ጊዜው የሚያልፍበት ይሆናል” በማለት ያስረዳሉ።

በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ

የአገር ውስጥ መድሃኒት ድርሻ ከ10 ከመቶ በታች ቢሆንም፣ ከመንግሥት በኩል ግን ትኩረት የተሰጠው በኢንደስትሪ ፓርክም እንዲደራጅ የተደረገ ዘርፍ መሆኑን ያነሱት አቶ ሰሎሞን፣ የመድሃኒት ምርት ትልቁ ችግር የዶላር አቅርቦት እጥረት እንደሆነ ይጠቅሳሉ። እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፣ የአገር ውስጥ ምርት አቅርቦትን ለመጨመር በዶላር በኩል ያለው ችግር በመመሪያ ጭምር እንዲፈታ አገልግሎቱ ከመንግሥት ግዢ ባለስልጣን፣ ከፋይናንስ ሚኒስቴርና ብሔራዊ ባንክ ጋር በመነጋገር የአገር ውስጥ አቅራቢዎች ላቀረቡት መድሃኒት ያሸነፉበትን 50 ከመቶ ዋጋ በብር፣ 50 ከመቶ የሚሆነውን ክፍያ ደግሞ በዶላር እንዲያገኙ ለማስቻል እየሰራ ይገኛል። ይህም፣ መድሃኒት በአገር ውስጥ ቢመረትም ጥሬ እቃው ከውጪ የሚገባ በመሆኑ የአገር ውስጥ አምራቾች ጥሬ እቃ የሚያመጡበትን ዶላር እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። በአሰራሩ ላይ ሁሉም አካላት መግባባት ላይ የደረሱ ሲሆን፣መመሪያውን ለማጽደቅ ደግሞ በሂደት ላይ ይገኛል።

አቶ አበራም፣ መድሃኒት አቅራቢ ድርጅቶች በባንኮች በኩል ዶላር ቅድሚያ እንዲያገኙ ቢመቻችላቸውና ለአገር ውስጥ አምራቾችም ፋብሪካዎችን በማደረጃት ምቹ ሁኔታ ቢፈጠርላቸው በመድሃኒት አቅርቦት በኩል የሚታየውን ችግር መፍታት ይቻላል የሚል አስተያየት አላቸው። በተጨማሪም መድሃኒቶች አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ፍጆታን መሠረት ባደረገ መልኩ ስርጭት እንዲደረግ የጤና ተቋማት ከመድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ጋር ተናበው ቢሰሩ ክምችትና እጥረት ያለባቸውን የጤና ተቋማት በተገቢው መንገድ ለማስተዳደር መልካም ዕድል ይፈጥራል የሚል ሐሳብም ሰንዝረዋል።

አቶ ደበላ ደግሞ፣ አቶ ሰሎሞንና አቶ ተፈራ እንደገለጹት ሁሉ የዶላር እጥረት ጉዳይ ለመድሃኒት አቅርቦት ማጠር አንዱ መንስዔ እንደሆነና ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ። የመድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት አገር ውስጥ ለሚገኙ የጤና ተቋማት ሁሉ መድሃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያ ለማቅረብ አቅም እንደሚያጠረው በማንሳት፣ ተጨማሪ ጠንካራ የአገር ውስጥ አስመጪ ማቋቋም እንደሚያስፈልግም ያሳስባሉ። የግዢ ባህሪና የበጀት ፖሊሲም ከመድሃኒት ባህሪይ ጋር የተናበቡ ሊሆኑ ይገባል የሚሉት አቶ ደበላ፣ ፖሊሲ አውጪዎች ለጉዳዩ ትኩረት ቢሰጡት የተሻለ እንደሚሆን ጠቁመዋል። የጤና ተቋማት መድሃኒቶቻቸውን ሸጠው በሚያገኙት ገቢ መልሰው የሚያስፈልጋቸውን መድሃኒት የሚገዙበትና ጥቂት ትርፍ ጨምረው በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚው የሚያቀረቡበት አሰራር ቢዘረጋ ለመድሃኒት አቅርቦት ችግር መፍትሔ ሊያመጣ ይችላል የሚል አስተያየትም ሰጥተዋል።

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

Recommended For You