ከደስታ ባሻገር

ወርሃ ጥር በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል አርሶ አደራችን በከፍተኛ ትጋት ሲለፋበት የቆየው የግብርና ስራ የሚጠናቀቅበትና አዝመራ ተሰብስቦ ጎተራ አስገብቶ እፎይ የሚልበት የዕረፍት ወቅት ነው። ከዕረፍቱ ጋር ተያይዞ ደግሞ ወሩ የተለያዩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ስርዓቶች ይከናወኑበታል። በደስታና ጭፈራ የተሞሉት ክዋኔዎቹም ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ከፍተኛ የሆነ ሀብትና ገንዘብ የሚፈስባቸው ናቸው።

በዚህ ረገድ የመጀመሪያው ተጠቃሽ የጥምቀት በዓል ነው። የጥምቀት በዓል ላጤው የትዳር ጓደኛ የሚመርጥበት/ሎሚ የሚወረወርበት/ እና በሁሉም ተወዳጅ የሆነችን ልጃገረድ ለግል ለማድረግ ከፍተኛ ፉክክር የሚያደርግበት፣ ጓደኛ ያለው ደግሞ በትዳር የሚጣመርበት በመሆኑ ይለያል። ለበዓሉ “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ….” በሚል ሁሉም ለጌጣጌጥና ለአልባሳት ተጨንቆና ተጠቦ በመዘጋጀት የደስታውና የጭፈራው ተካፋይ ይሆናል። ከጓደኛ እና ከአካባቢው በልጦ ለመገኘት ሲባልም ከትልቅ እስከ ትንሽ ሁሉም የሚያወጣው ወጪ ከፍተኛ ነው። በጥምቀት በዓል ዕለት አምሮና ደምቆ መታየት ለትዳርም ሆነ ለከንፈር ወዳጅነት ለመታጨት አንድ መስፈርት ነው። በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ ከመጠን በላይ መዋቡ መራጭን በማሳሳት ወቅቱ ካለፈ በኋላ ቁጭት ላይ የሚጥልበት አጋጣሚም ይስተዋላል። እዚህ ላይ አንድ ጨዋታ ትዝ አለኝ። አንድ የወንድ እናት በበዓሉ ዕለት ተውባ ያዩዋትን ልጃገረድ ለልጃቸው አጭተው ካጋቡ በኋላ ሁኔታዋን ሲያዩዋት እንደጥምቀቱ ዕለት አላስደስታቸውምና በስህተታቸው ሲያዝኑ ይቆያሉ። በዓመቱ ጥምቀት ላይ የተዋቡ ልጃገረዶችን ሲያዩ ‹‹የባለፈው ጥምቀት እኔን ገድለሃል፤ የዘንድሮው ደግሞ ማንን ትገድል ይሆን?›› አሉ ይባላል።

በጨዋታ ያነሳነው ጋብቻ በወርሃ ጥር በስፋት ይፈፀማል። ከሠርግ ድግስ ጋር በተያያዘ የሚወጣው ወጪ በእጅ ያለን ሀብትና ገንዘብ ከማራቆት በዘለለ ብድር ውስጥ የሚዘፈቁ ብዙዎች ናቸው። ከሠርጉ በኋላ ከሚመጣው ዘርፈ ብዙ ጣጣ ይልቅ ከትላንት ደጋሾች ከእነ እገሊትና ከእነ እገሌ እንዴት አንሳለሁ በሚል ሀሳብ መጨነቁ ያመዝናል። በማህበረሰባችን በግልጽ እንደምናስተውለው የዚህ አስተሳሰብ ተገዥ ሙሽራውና ሙሽሪት ብቻ አይደሉም። ቤተሰብ፣ ወዳጅ፣ ዘመድ እና አካባቢውም ጭምር የአስተሳሰቡ ሰለባ ናቸው። የሚገርመው ደግሞ ደጋሹ ነገ የሚያጋጥመውን ችግር ከወዲሁ እያወቀውም ቢሆን በይሉኝታና በተለያዩ ተጽዕኖዎች ምክንያት የቋጠረውን ሀብቱን አሟጥጦ፣ የሌለው ደግሞ ተበድሮ ወደ ችግሩ የሚገባ መሆኑ ነው።

ይህን ሃሳብ ታጠናክራለች ብየ የማስባትን አንዲት ትንሽ ገጠመኝ ላቅርብ። ጥንዶቹ ከተዋወቁ ረጅም ጊዜ አልሆናቸውም። ይሁን እንጂ በጣም ይዋደዳሉ። ይህን ፍቅራቸውን ደግሞ ወደ ትዳር ለመቀየር ተስማምተዋል። በጋብቻው ላይ የሚያራምዱት ሃሳብ ግን የተለያየ ነበር። ሴቷ ገና ተማሪና ለድግስ የሚሆን ገንዘብ ባይኖራትም ለግሏ፣ ለቤተሰቧና ለአካባቢው ማህበረሰብ ክብር በመጨነቅ ጋብቻው በሠርግ ይሁን የሚል ጽኑ አቋም ነበራት። ወንዱ ደግሞ የመንግስት ሠራተኛ ቢሆንም ሠርግ ለመደገስ የሚያበቃው ደመወዝ የለውም። ያጠራቀመው ገንዘብም ሆነ ሀብት ስለሌለው መደገሱን አልፈለገውም። ይህን የሰፋ የሃሳብ ልዩነታቸውን ለማጥበብ ብዙ ጊዜ ተወያይተውበታል። ጉዳዩን በተደጋጋሚ ያውጡት ያውርዱት እንጂ በሃሳብ መቀራረብ ግን አልቻሉም። መጨረሻ ላይ የሴቷ ሃሳብ አሸነፈና የድግስ አነስተኛ ባይኖረውም፣ ለአነስተኛ ድግስ የሚሆን ገንዘብ በሚል ለመበደር ተስማምተው ሠርጉ ተደግሶ ተጋቡ።

ጥንዶቹ ተጋብተው ብዙ ሳይቆዩና ብድራቸውን ከፍለው ሳይጨርሱ፣ ሴቷ ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ታመመችና ሆስፒታል ገባች። “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ለህክምና የሚሆን ገንዘብ በማስፈለጉ በብድር ላይ ሌላ ብድር የግድ ሆነ። ከብዙ የህክምና ወጪ በኋላ ልጁ በጤና ተወልዷል። ይሁን እንጂ የተደራረበን ዕዳ እየከፈሉ ልጅ ማሳደግና በልቶ ማደር መቻልን በተመለከተ ያለውን ጭንቀትና ችግር እናንተ ራሳችሁ አስቡት።

የሰው ልጅ ካስተዋለው፣ ካዳመጠውና ካነበበው ብዙ መማር እንደሚኖርበት ይታሰባል። ድግስን በተመለከተ በገሃዱ ዓለም እየተከናወነ ያለው ሀቅ ግን በአብዛኛው ማለት በሚቻልበት ሁኔታ መሆን ያለበት ነገር አይደለም። ምናልባትም በዚህ በኩል ማህበረሰቡ ተምሯል ከተባለ በሌላው ሳይሆን በራሱ ውድቀት ነው “ከወደቁ ወዲያ መፈራገጥ ለመላላጥ” እንዲሉ። በመሆኑም ከአቅም በላይ ወጪ አውጥቶ በመደገስ ለጊዜው ተደስቶ በማግስቱ ሊወጡት ከማይችሉት ችግር ውስጥ ገብቶ መዳከር ትላንት ነበር፤ ዛሬ አለ፤ ነገም እንደሚኖር በገሀዱ ዓለም ብዙ አመላካቾች ይስተዋላሉ። ከዚህ በመነሳት ሰው መቼ ነው ቆም ብሎ ስለ ራሱ ማሰብ የሚጀምረው? እላለሁ።

ቀደም ሲል በአንዳንድ ክልሎች አርሶ አደሩ ዓመት ሙሉ የለፋበትን ሀብት በአንድ ወር ደግሶ እየጨረሰ ራሱንና ቤተሰቡን ለከፍተኛ ችግር ማጋለጡ ተገቢ አይደለም በሚል የአንድ ወቅት አጀንዳ ሆኖ ነበር። ችግሩን ለማቃለልም ድግሱን በአግባቡ እንዲደግስ የግንዛቤ ፈጠራና የማስተማር ስራ መሰራት ተጀምሮ እንደነበርም መረጃው ነበረኝ። ከዚያም አልፎ በአካባቢው ማህበራዊ አደረጃጀቶች እንደ ዕድር ዓይነቶች አማካኝነት ለድግስ ከፍተኛ ወጪ ማውጣት ጎጂ ባህል ነው በሚል እንዲወገዝና እንዲስተካከል አስገዳጅ አሰራርም ተቀምጦ ነበር። ይህ ጥሩ ጅምር ግን ዘላቂ ሆኖ አልቀጠለም።

በቅርቡ ደግሞ በአማራ ክልል የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር ምክር ቤት በዚህ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊት ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል። የውሳኔው ዋና ሃሳብ ዞኑ የበርካታ ጠቃሚ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት እንደሆነና በክልሉ ከሚታወቁ ትርፍ አምራች ዞኖች መካከልም አንዱ መሆኑን ጠቅሷል። ይሁን እንጂ ማህበረሰቡ የተንዛዛ እና ከአቅም በላይ ድግስ በመደገስ ለፍቶ ያገኘውን ምርት በማባከን የአመጋገብና የአለባበስ ስርዓቱን ከመጉዳት አልፎ፣ ለርሃብና ለስደት መጋለጡን አንስቷል። በመሆኑም ምክር ቤቱ ችግሩን በዘላቂነት ለማስወገድ እንዲቻል በየደረጃው የሚገኘው የወረዳና የቀበሌ ምክር ቤቶች አመራሮች ጉዳዩን ቁልፍ ተግባር አድርገው እንዲይዙት በማሳሰብ የውሳኔውን ሙሉ ቃል ጥር አንድ ቀን 2015 ዓ.ም በደብዳቤ አሳውቋቸዋል፤ እሰየው የሚያስብል ተግባር ነው።

በእኔ አስተሳሰብ ድግስ አይደገስ፣ ሰርግም አይሰረግ የሚል ዕምነት የለኝም። ድግሱም ሆነ ሠርጉ ግን የነገ ህይወትን ታሳቢ ያደረገ ይሁን ባይ ነኝ። ከ“ማን አንሼ” ከሚል ኋላ ቀር አስተሳሰብና ከማንኛውም ዓይነት ይሉኝታ በመላቀቅ አቅምን ያገናዘበ ድግስ መደገስ መልካም ነው። ተጋቢዎችም ቢሆኑ ለነገ ህይወታቸው ተመሳሳይ አስተሳሰብና አቋም ሊኖራቸው ይገባል። አንደኛው የዛሬን ደስታና ክብር ብቻ አስቦ “እኔ ያልኩት ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ” የሚል፣ ሌላው ደግሞ የነገውንም ኑሮ ጭምር አሳቢ በመሆን በሃሳብ መለያየት ተገቢ ነው ብየ አላስብም። ደግሞም ዛሬ ላይ በትዳር አመሰራረት በትዳር አጋሮቹ መካከል የሃሳብ ልዩነት ካለ መጪውን ረጅም የኑሮ ዘመን እንዴት መግባባት ይቻላል? የሚለውን ሳይቀር ከግምት ማስገባት የሚጠቅም ይመስለኛል።

የነገን ህይወት ያለችግር ተስማምቶ እና ተግባብቶ ለመኖር በተጋቢዎቹ መካከል ስምምነት ከተፈጠረ ደግሞ የሰርግ ዝግጅቱ ብዙ አያሳስብም። በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ በአነስተኛ ወጪዎች የሚፈጸሙ ጥሩ ጅምሮችን መከተል አንዱ አማራጭ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ አሁን ላይ አልፎ አልፎ እየታየ እንዳለው እንደ “መቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል“ ከመሳሰሉ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ጋር በአነስተኛ ወጪ የተለያዩ ዝግጅቶችን አብሮ ማሳለፍ እየተለመደ መጥቷል። በመሆኑም ሠርጉን ፎቶግራፍ በመነሳት፣ ምሳ በማብላት፣ አነስተኛ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ እግረ መንገዱን የበጎ አድራጊ ድርጅቶችን የተቀደሰ ዓላማ አግዞ፣ ረድቶና ዕውቅና ሰጥቶ ማለፍ እሰየው የሚያስብል ተግባር መሆኑን ማሰብ ተገቢ ነው። በዚህም ከደስታ ባሻገር የሰብዓዊነት ተግባር በመፈጸም የዜግነት ድርሻን በመወጣት በቀጣይ የህይወት ዘመን ሁሉ የመንፈስ እርካታን ማግኘት መታደል ነው።

ንጉሤ ተስፋዬ

Recommended For You