የሕትመቶቹ ጥሪ

ዘመናዊ የሕትመት መሣሪያ የኢትዮጵያን መሬት የረገጠው የዛሬ 500 ዓመት እ.ኤ.አ በ1556 ዓ.ም እንደነበር፣ አዲስ አየለ፣ “የኢትዮጵያ ሚዲያ ታሪክ ከጥንት እስከዛሬ” በሚል በ2010 ዓ.ም ባሳተመው መጽሐፉ አስፍሯል። ጀርመናዊው ጆን ጉተንበርግ እ.ኤ.አ በ1439 የሕትመት ማሽንን ከፈለሰፈ በኋላ፣ መረጃን በጽሑፍ ለመቀባበል፣ ታሪክንም ለመከተብ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። የሕትመት ማሽን ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት በእንጨት፣ በድንጋይና መሰል ቁሶች ላይ ስዕሎችንና ምልክቶችን በመጠቀም መረጃን የማስቀረት ልማድ ለዘመናት ሲሠራበትም ቆይቷል።

ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የሕትመት ቴክኖሎጂ የሬዲዮና ቴሌቪዥን የ480 ዓመት ዕድሜ ታላቅ ነው። ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ቴክኖሎጂው እጅግ ዘመናዊ የሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ጥቁርና ነጭ ቀለማትን ብቻ ያትም የነበረው የሕትመት ቴክኖሎጂ ዛሬ ሁሉንም ቀለሞች በሚያትሙ ማሽኖች ተተክቷል። ጥቂት የሕትመት ቅጂዎችን ለማተም ብዙ ጊዜን ይጠይቅ የነበረበት ጊዜም አልፎ በጥቂት ሰዓታት በርካታ ቅጂዎችን ማተም ተችሏል።

ቴክኖሎጂው የደረሰበት ደረጃ በእጅጉ የላቀ ቢሆንም፣ በሀገራችን፣ ለሕትመት ሥራ መሠረታዊ የሆነውን “ወረቀት” ማግኘት ግን ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል ሆኗል። የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት፣ አቶ ተፈራ ስዩም፣ የወረቀት በሀገር ውስጥ በበቂ መጠንና ጥራት አለመመረትና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው ወረቀት ላይ የሚጣለው ተደራራቢ ታክስ፣ ከውጭ ምንዛሪ ጭማሪ ጋር ተዳምሮ፣ የሕትመት ዋጋን እያናረ፣ አታሚና አሳታሚዎችንም ከኢንዱስትሪው እያራቀ እንደሚገኝ ይናገራሉ። ከጥቂት ዓመታት በፊት 400 እና 500 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ እሽግ ወረቀት ዛሬ እስከ 6ሺ ብር እየተሸጠ ይገኛል፤ ይህም የሕትመት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል። በዚህ ሳቢያም፣ ብዙ አሳታሚዎች መጽሐፍ ከማሳተም ተቆጥበዋል። ችግሩን ተቋቁመውና ደፍረው የሚያሳትሙትም በጥቂት ቅጂዎች ብቻ እንዲወሰኑ አስገድዷቸዋል። ቀደም ባሉ ጊዜያት 10ሺ እና 5ሺ ቅጂ ያዙ የነበሩ አሳታሚዎች 1ሺ እና 500 ቅጂ ማዘዝም ጀምረዋል። ይህ የቅጂ ብዛት ደግሞ፣ አይደለም ከኢትዮጵያ ህዝብ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ብዛት አንጻር እንኳ ሲታይ፣ በጣም የወረደና አንድ መጽሐፍ አሳትሞ ለጓደኛና ለሰፈር ሰው የማከፋፈል ያህል ነው በማለት ሕትመት የደረሰበትን አስጊ ደረጃ ያስረዳሉ።

ከ15 ዓመታት በላይ በሕትመት ኢንዱስትሪ የቆየው የጃጃው ማተሚያ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ነብዩ በለጠም፣ የወረቀት ዋጋ ጭማሪው የምንቋቋመው አይነት አይደለም ይላሉ። 400 ብር ይሸጥ የነበረው ለየትኛውም መጽሐፍ ሕትመት የሚያገለግለው ባለ 60 እና 70 ግራም አንድ እሽግ ወረቀት፣ ዛሬ እስከ ሰባት ሺ ብር፣ 135 ብር ይሸጥ የነበረው የባንክ ወረቀት ደግሞ 4ሺ ብር መድረሱንም ይናገራሉ።

“ጸሐፊዎች መጽሐፍ የማሳተም ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ የዋጋ ጭማሪው ሞራላቸውን ገድሎታል፣ ብዙ አታሚዎችም ማሽኖቻቸውን እየሸጡ ከኢንዱስትሪው ለመውጣት እየተገደዱ ነው፤ በ90 እና 70 ብር ይሸጥ የነበረ አንድ ትንሽ መጽሐፍ ዛሬ 400 እና 500 ብር ገብቷል፤ ቀድሞ በነበረው ዋጋ የኅብረተሰብ የንባብ ባህል ባልዳበረበት ሁኔታ ዛሬ በዚህ ዋጋ ገዝቶ ያነባል፤ የንባብ ባህሉንም ያሳድጋል ማለት ከባድ ነው” የሚሉት አቶ ነብዩ፣ ለዚህም፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ 1000ሺ እና 500 ቅጂ የሚታተሙ መጽሐፍት በ6ወራት ውስጥ እንኳ ተሸጠው አለማለቃቸው ማሳያ ነው በማለት፣ የወረቀት ዋጋ ጭማሪው ከንባብ ባሕል አለመዳበር ጋር ተዳምሮ አታሚና አሳታሚው፣ ብሎም ማኅበረሰብ ላይ የፈጠረውን ጫና ያስረዳሉ። በተለይ፣ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ የሚተላለፉ ፈጣን፣ አጭርና ፍሬ አልባ ጽሑፎች በተበራከቱበት በዚህ ጊዜ፣ የሕትመት ኢንዱስትሪው መዳከም ሲታከልበት መጽሐፍት፣ ጋዜጣና መጽሔቶችን ለማንበብ ይሞክር የነበረውን ጥቂት ትውልድ፣ ጨርሶ እንዳያጠፋው የሚል ስጋት እንዳደረባቸውም ገልጸዋል። በሌላው ዓለም ሕትመት በጣም አድጎ እጅግ ዘመናዊ ደረጃ ላይ መድረሱን የጠቀሱት አቶ ነብዩ፣ እንዲያውም በብዙ ሀገራት የሕትመት ዘርፍ ሰፊ ትኩረት የሚሰጠው፣ እንደ ቡናና ነዳጅ ሁሉ ኢኮኖሚን የሚደግፍ ትልቅ የጀርባ አጥንት ነው ብለዋል።

የ101 ዓመት እድሜ ባለፀጋው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነትና ማኅበራዊ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ኃይሌ በበኩላቸው፣ የወረቀት ዋጋ መናር ለሕትመት ኢንዱስትሪው ዳገት ሆነ እንጂ፣ ዛሬም ከፍተኛ የሕትመት ፍላጎት መኖሩን ያነሳሉ፤ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያን በመጠቀም በሰፊው የሚበልጡን ያደጉ ሀገራት እንኳ የሕትመት ሚዲያውንም አጠናክረው እንደያዙት የጠቀሱት ኃላፊው፣ በሀገራችን የወረቀት ዋጋ በከፍተኛ መጠን መጨመሩ፤ የሕትመት ውጤቶች ዋጋ እንዲንር ማድረጉን ይናገራሉ። እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ የአንድ ኪሎ ሕትመት መሸጫ ዋጋ 13 ብር እንደነበር አስታውሰው፤ ከ2010 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ 13 ብር ከነበረው የመሸጫ ዋጋ ላይ የ115 ከመቶ ጭማሪ በማድረግ 28 ብር፣ ከመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ 28 ብር ከነበረው የአንድ ኪሎ ሕትመት መሸጫ ዋጋ ላይ ከእጥፍ በላይ በመጨመር ወደ 62 ብር ከፍ ማድረጉንም አውስተዋል። ድርጅቱ ለዓመትና ሁለት አመት የሚያስፈልገውን ወረቀት በአንድ ጊዜ ገዝቶ ማስገባት መቻሉ፣ በወረቀት ላይ የታየው ከፍተኛ ጭማሪ የፈጠረው ውጥረት እንዲቀንስለት ያደረገ ቢሆንም፣ ጭማሪው አሳታሚዎች ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ይጠቁማሉ። ድርጅቱ በአጠቃላይ 14 የግልና የመንግሥት ጋዜጦችን የሚያትም ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በተለያየ ቋንቋ የሚያሳትማቸው 6 ጋዜጦች፣ 4 የመንግሥት ተቋማት የሚያሳትሟቸው ጋዜጦችና አዲስ አድማስ፣ ፎርቹን፣ ካፒታልና ሪፖርተር የተሰኙ የግል ጋዜጦች በዋጋ ጭማሪው ምክንያት በአማካይ ከ40 ከመቶ በላይ የቅጂ ብዛት መቀነሳቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።

እርሳቸው እንዳሉት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የወረቀት ዋጋ ጭማሪ ከውጪ ምንዛሪ ዋጋ መጨመር ጋር ተዳምሮ የሕትመት ዋጋ ላይ ጫና መፍጠሩ እንዳለ ሆኖ፣ ወረቀት ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባና በድጋሚ፣ ታትሞበት ጋዜጣና መጽሔት ሆኖ ሲወጣ የሚጣልበት ተደራራቢ ታክስ ለሕትመት ኢንዱስትሪው ፈተና ሆኗል።

“ነጋዴ እንደመሆናችን ሌላውንም ዘርፍ እናያለን፣ ከሕንጻ ተቋራጭ፣ ከኤሌክትሪክ እቃዎች እና ከሌሎችም ዘርፎች አንጻር ወረቀት ላይ የታየው ጭማሪ የተለየ ነው” ያሉት አቶ ነብዩ፣ ወረቀት ላይ ከሚጣለው ታክስ በተጨማሪ ለሕትመት ሥራ ፈተና የሆነው፣ ወረቀት በውስን አስመጪዎች እጅ መሆኑ ሲሆን፣ ይህም ዋጋ አወዳድሮ ለመግዛት ምቹ ሁኔታ አለመፍጠሩን ያስረዳሉ።

የሕትመቱ ዘርፍ ትኩረት የተነፈገው ነው ያሉት አቶ ተፈራ፣ ወረቀት ከሚጣልበት ተደራራቢ ታክስ የተነሳ ከውጪ አታሚዎች ጋርም በዋጋ ተወዳዳሪ መሆን አለመቻሉን ጠቅሰው፣ በዚህ ሳቢያ፣ መንግሥት በየጊዜው በዓመት 100 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ በማውጣት የተማሪ መጽሐፍትን በውጪ ሀገራት እያሳተመ እንደሚገኝም አንስተዋል። እንደእርሳቸው ገለጻ፣ መንግሥት የተማሪዎችን መጽሐፍት ከሀገር ውጪ ማሳተምን የመረጠው በሦስት ምክንያቶች ነው። የመጀመሪያው፣ ወረቀት ላይ የሚከፈለው ቀረጥ፣ መጽሐፍ ከውጪ ሀገር ሲገባ ስለማይከፈልበት፤ መንግሥትም ይህን አማራጭ መጠቀሙ ሲሆን፣ በዚህም ሀገር ውስጥ ካለው የሕትመት ዋጋ አንጻር ሲታይ እስከ 50 ከመቶ ቅናሽ ያስገኛል። ሌሎቹ ምክንያቶች ደግሞ የሕትመት ፍጥነትና ጥራት ጉዳዮች ናቸው። መንግሥት “የሀገር ውስጥ አታሚዎች መጽሐፍቶቹን በፍጥነትና በሚፈለገው ጥራት አያደርሱልኝም” የሚል ምክንያት እንደሚያስቀምጥ የሚናገሩት አቶ ተፈራ፣ ይሁን እንጂ ችግሮቹ ቢኖሩም እንኳ፣ አንድ ሰው የቤቱ በር ችግር ቢኖርበት፤ በር ማስተካከሉን ትቶ ውጭ እንደማያድረው ሁሉ፣ መንግሥትም የሀገር ውስጥ አታሚዎችን ችግሮች ለይቶ በመፍታት ዘርፉን ለማበረታታት ቋሚ መፍትሔ መስጠት እና አላስፈላጊ የውጭ ምንዛሪንም ማውጣት እንዳልነበረበት ያሰምሩበታል።አቶ ተፈራ አያይዘውም፣መንግሥት የተማሪ መጽሐፍትን ለማሳተም በየጊዜው በርካታ ገንዘብ ከሚያወጣ አንድ ጊዜ መከፈል ያለበትን ዋጋ ከፍሎ ጥራትና ብዛት ላለው ሕትመት የሚያገለግሉ ማሽነሪዎች በሀገራችን እንዲኖሩ ቢያግዝ ለኢንዱስትሪውም ሆነ ለሀገር እጅግ መልካም ይሆን ነበር ብለው ይመክራሉ።

አቶ ነብዩም በተመሳሳይ፣ መንግሥት የተማሪ መጽሐፍትን በየጊዜው ሕንድና ቻይና እንደሚያሳትም ጠቅሰው፣ ይሁን እንጂ መንግሥት በርካታ የውጪ ምንዛሪ አውጥቶ መጽሐፍቱን ውጪ ሀገር ከሚያሳትም፣ ሀገር ውስጥ ላሉ አታሚዎች አከፋፍሎ ቢያሠራ ኢንዱስትሪውን ከማበረታታት ባሻገር የውጪ ምንዛሪንም ለማስቀረት ይጠቅም እንደነበር ይናገራሉ። ውጪ ሀገር ታትመው የሚመጡ አንዳንድ መጽሐፍትም በጉልህ የሚታይ የጥራት ችግር ያለባቸው መሆናቸውን ጭምር መታዘባቸውን ያስረዳሉ።

በአታሚዎችና አሳታሚዎች ማኅበር አማካኝነት ለሕትመት ሴክተሩ ኢንዱስትሪ መንደር የሚሆን ቦታ ይዘጋጅልን ብለው መጠየቃቸውን ያወሱት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት፣ ጥያቄያቸው መልስ ካገኘ፣ ወደ ውጪ ሀገር የሚላኩ ሕትመቶችን ሀገር ውስጥ ማሳተም እንደሚቻል፣ በርካታ የሥራ እድልም እንደሚፈጠር፣ የውጭ ምንዛሪን ማስቀረት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርንም መፍጠር ይቻላል ይላሉ። ዘርፉን ለማበረታታት ተብሎ የማተሚያ ማሽን ከቀረጥ ነጻ እንዲገባ የተደረገበት ሥርዓት መኖሩንም ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰው፣ ይህም ጅምርለዘርፉ ዕድገት መልካም መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሌሎች አጋዥ አሠራሮችንም በመተግበር ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚቻል ጠቁመዋል። እንዲህ ዓይነት ኢንዱስትሪዎች ጥሬ እቃ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲኖር ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ያሳሰቡት አቶ ነብዩም፣ ወረቀት በሀገር ውስጥ በበቂ መጠንና ጥራት መመረት ቢችል ኖሮ የሕትመት ኢንዱስትሪው የተጋረጡበትን ችግሮች ማለፍ ይችል ነበር በማለት ቁጭታቸውን ያጋራሉ። እንደእርሳቸው አስተያየት፣ ከ90 ከመቶ በላይ የሚሆነው የሀገር ውስጥ የወረቀት ፍላጎት ከውጪ ሀገር የሚገባ ሲሆን፣ በሀገር ውስጥ የሚገኙ በጣት የሚቆጠሩ የወረቀት ፋብሪካዎች ቢኖሩም፣ የማምረት አቅማቸው አነስተኛ፣ የሚያመርቷቸው ወረቀቶችም የምርት ጥራታቸው የወረደ፣ ለማሽን ሥራ የሚያስቸግሩ እና ለደንበኞች ለማቅረብም የማይመረጡ ናቸው።

በሀገራችን ትልቁ የሕትመት ማተሚያ ተቋም ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ነው። ድርጅቱ በዓመት በአማካይ 2 ሺህ 354 ቶን ወረቀት ከውጪ ያስገባል። 746 ቶን ወይም ድርጅቱ ከሚያስፈልገው የወረቀት ፍጆታ መካከል 30 ከመቶ የሚሆነውን ደግሞ ወንጂ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ፐልፕና ወረቀት ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበር እና አኒሞል ኢትዮጵያ ፕሮዳክትስ ሊሚትድ ኃ/የተ/የግል ማኅበር ከተሰኙ የሀገር ውስጥ አምራቾች እንደሚገዛ የሚናገሩት አቶ ዳንኤልም፣ የሀገር ውስጥ አምራቾች በጣም ጥቂት ከመሆናቸው ባሻገር የወረቀት ጥራታቸውም ከውጪ እንደሚገባው ደረጃውን የጠበቀ አለመሆኑን ገልጸዋል። በተለይ ደግሞ ድርጅቱ በብዛት የሚጠቀመው የጋዜጣ ወረቀት በሀገር ውስጥ እንደማይመረትም ጠቁመዋል። ከዚሁ ጋር በማያያዝም፣ ወረቀትን ጨምሮ፣ ለሕትመት ሥራ ጥቅም ላይ የሚውሉ ቀለም፣ ኬሚካል፣ ፕሌት፣ የመሳሰሉት በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ማድረግ፣ እነዚህን ግብዓቶች ለማምረት ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ሲኖሩም ማበረታታት ያስፈልጋል ለሚለው ሐሳባቸውም አጽንዖት ሰጥተዋል።

“የውጭ ምንዛሪን ከመፍቀድ አንጻር መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ስለሚደግፈን፣ ብዙ የሕዝብ ልሳኖችን ማተም፣ የሚያስፈልገንንም ወረቀት በብዛት ማስመጣት ችለናል” ያሉት አቶ ዳንኤል፣ በርካታ ገንዘብ ወጥቶበት፤ ረጅም ሂደትንም አልፎ የምናገኘውን ወረቀት እያንዳንዱ ሠራተኛ ከብክነት በፀዳ ሁኔታ በአግባቡ እንዲጠቀም የግንዛቤ ሥራ እንደሚሠሩም ይናገራሉ። በተጨማሪም ወረቀቶች ከሕትመት ማሽኖች ጋር የተመጣጠኑ እንዲሆኑና ከዚህ አልፈው የሚወጡ ወረቀቶችን በመፍጨት ለሌላ ጥቅም እንዲውል የማድረግ ሥራ ስለሚሠራ፣ ከዚህ በፊት ይከሰት ከነበረው የወረቀት ብክነት አንጻር ሲታይ ከፍተኛ መሻሻል አለ ብለዋል።

የሕትመት ኢንዱስትሪው ከተጋረጡበት ፈተናዎች መካከል አንዱ በቂ የውጪ ምንዛሪ አለማግኘት እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ነብዩ፣ የወረቀት አስመጪዎቹ የውጪ ምንዛሪውን የምናገኘው ኤክስፖርት ከሚያደርጉ ሰዎች ገዝተን ነው እንደሚሉና ይህ ደግሞ፣ ወረቀት ለመግዛት የሚከፈለውን ዋጋ ከፍ እንደሚያደርገው ይናገራሉ።

አቶ ተፈራም ለዚህ ሴክተር የውጭ ምንዛሪ ቢመቻችና አታሚው የሚያስፈልገውን ወረቀት ራሱ የሚያስገባበት ሁኔታ ቢፈጠርለት ኢንዱስትሪው ላይ ያሉ ችግሮች ሊቃለሉ እንደሚችሉ ያምናሉ። ስለሆነም፣ መንግሥት “ወረቀት” ኅብረተሰብ መረጃና እውቀት የሚያገኙበት ሀገር የሚገነባበት መሠረታዊ ነገር እንደሆነ ተረድቶ ዘርፉን ትኩረት ሰጥቶ ቢመለከተው መልካም ነው የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአታሚዎችና አሳታሚዎች ማኅበር ላለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ተዳክሞ መቆየቱን፣ ድምፁን የሚያሰማበት መድረክም እንዳልነበረው የሚናገሩት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ተፈራ፣ አሁን ላይ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አማካኝነት በድጋሚ እንዲጠናከር መደረጉንና ስትራቴጂ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ገልፀዋል። ድርጅቱ መንግሥት ለኅብረተሰቡ በጣም አስፈላጊ የሆኑ የዕቃ ዋጋዎችንለማረጋጋት የወሰዳቸውን እርምጃዎች በሕትመት ኢንዱስትሪውም እንዲደግመው፣ ከቀረጥ ጋር የተያያዙ ፖሊሲዎችም በድጋሚ የሚታዩበት ሁኔታ እንዲፈጠር የሚመለከታቸውን አካላት ለማነጋገር በጥረት ላይ እንደሚገኝና ጥረቱም መፍትሔ ያመጣል ብለው እንደሚያስቡ ፕሬዚዳንቱ ያስረዳሉ። የሕትመት ኢንዱስትሪውን ማበረታታት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የሀገርን ኢኮኖሚ ከማገዙ ባሻገር ብዙ መጽሐፍት እንዲታተሙና ወደ ገበያ እንዲወጡ፤በዚህም አንባቢና ነገሮችን በሚዛን የሚያይ አስተዋይ ትውልድ እንዲፈጠር ማስቻሉ ትልቁ ጠቀሜታ ነውም ብለዋል።

አቶ ነብዩም፣ የህትመት ኢንዱስትሪው የተጋረጠበትን ተደራራቢ ችግር ለመፍታት በማኅበር ሆነው እየተንቀሳቀሱ፣ በየጊዜው እየተሰባሰቡና እየመከሩ እንደሆነ አንስተው፣ ለሁሉም ነገር መሠረታዊ የሆነውን የሀገር ሰላም ማጽናት ከተቻለ፣ በኢንዱስትሪው ላይ ያሉ ችግሮች በሂደት እንደሚቀረፉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። አቶ ዳንኤልም በበኩላቸው ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት አንጋፋ እንደመሆኑ መጠን አንዳንድ ሕትመቶችን ምንም ትርፍ ሳያገኝ የሠራተኛና የጥሬ እቃ ብቻ በማስከፈል እንደሚሠራና በዘርፉ ያሉ ፈተናዎችና መፍትሔዎችን አስመልክቶ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር የፓናል ውይይቶችን በማካሄድ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንዳለ ገልጸው ወደፊትም ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የሥልጣኔ፣ የአዳዲስ ግኝቶችና ሐሳቦች መተላለፊያ፤ የትውልዶች መገናኛ ድልድይ፣ የዴሞክራሲ መለማመጃ መሣሪያ የሆነውን የሕትመት ዘርፍ ከተጋረጡበት ፈተናዎች ታድጎ መልካም እድሎችን መፍጠር፤ ትውልድ ሳይታነጽ፣ ትናንትን ከዛሬ ሳያጋምድ፣ የኋላውን ከፊቱ ሳያስተሳስር የእውር ድንበሩን ከመጓዝ መታደግ ነውና የሚመለከተው ሁሉ ይድረስለት የሚለው የዝግጅት ክፍላችን መቋጫ መልዕክት ነው!

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

Recommended For You