አንዳንድ የፌዴራል መ/ቤቶች ሲቋቋሙ የማስፈጸም ስልጣን ብቻ ይዘው ይቋቋማሉ። ሌሎቹ ደግሞ የልማት ድርጅት ሆነው ሊደራጁ ይችላሉ። የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ፣ እንደሌሎች ተቋማት ሁሉ የማስፈጸም ስልጣን በህግ ተሰጥቶታል። በተሰጠው ስልጣን መሠረትም ተቋማት ምን ያህል ሠራተኛ እንደቀጠሩ፣ የጡረታ መዋጮ መክፈልና አለመክፈላቸውን ያጣራል፣ ምን ያህል ገንዘብ እንደከፈሉም ኦዲት ያደርጋል። በኦዲት ግኝቱ መሰረትም ያልገባ የጡረታ መዋጮ ካለ እንዲገባ ያደርጋል፤ የጡረታ መዋጮ ገንዘብን በየወሩ ይከታተላል፣ ምርመራ ያደርጋል፣የገንዘብ መዋጮውንም በአግባቡ ሰብስቦ ያስተዳድራል። የጡረታ መዋጯቸውን በጊዜና በመግባባት ማስገባት ያልቻሉትን፣ በትዕዛዝ ከባንክ አካውንታቸው እንዲቀነስ በማድረግ፣ አልያም ንብረታቸውን እስከማሸጥ በሚያደርስ ቅጣት እንዲከፍሉ ያስገድዳል። በዚህም ለጡረተኞች በየወሩ የጡረታ አበላቸውን ይከፍላል፤ ጡረታ ለሚወጡት ደግሞ የአበል ውሳኔ ይሰጣል።
ተቋሙ፣ የአበል ውሳኔ ሲሰጥ የሚሰራው የዳኝነት ስራ ነው። የዳኝነት ተግባሩም የጡረታ ገንዘቡን ከመመዝገብ ጀምሮ መርምሮ ውሳኔ እስከመስጠት ይደርሳል። ለዚህም ነው “ተቋሙ በከፊል የዳኝነት ስልጣን አለው” የሚባለው። በአስተዳደሩ ውሳኔ አሰጣጥ ቅር የተሰኘን አካል አስተዳደሩ መልሶ ውሳኔውን እንዲያየው አሰራሩ ይፈቅድለታል። አሁንም በተሰጠው ውሳኔ ቅሬታ የሚያቀርብና ይግባኝ የሚል ተገልጋይ ካለ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾሙ አባላት ባሉት ለይግባኝ ሰሚ ጉባዔ ቅሬታውን በቀጥታ ያቀርባል። ከዚያ በኋላ ውሳኔው መሰረታዊ የህግ ስህተት ካለበት ጉዳዩ ወደ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይሄዳል።
አሁን ላይ ደግሞ ተቋሙ ስራ አላሰራ ያሉ የአዋጅ አንቀጾችን በማሻሻል እና ሌሎች ተጨማሪ ተግባራትን ማከናወን በሚያስችለው የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። እንደ አቶ ሀሰን መሃመድ፣ በመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የህግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ገለጻ፣ የተቋሙ ለውጥ ከተቋሙ ስያሜ ይጀምራል። የፌደራል ተቋማትን ለማደራጀት በወጣው 1263/2014 አዋጅ፣ የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ይባል የነበረው፣ በኋላ በተሻሻለው፣ በአዋጅ ቁጥር 1267/2014 “አስተዳደር” የሚለው ስያሜ ጸንቶለታል። ቀደም ሲል ለሲቪል ሠርቪስ የነበረው የተቋሙ ተጠሪነትም በማሻሻያው የፋይናንስ ተቋማትን ለሚቆጣጠረው ለብሔራዊ ባንክ ሆኗል።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፣ አንቀጽ 14፣ ንዑስ አንቀጽ ሁለት “ለ” ላይ ለጡረተኞች የሚሰበሰበውን ገንዘብ በቦርድ እያስጸደቀ አስተማማኝ በሆነ ኢንቨስትመንት ስራ ላይ እንዲያውለው ተፈቅዶለታል። በዚህም ከኢንቨስትመንት ተግባር ጋር በተያያዘ ተቋሙ በከፊል የገንዘብ ተቋም ሆነ ማለት ነው። በመሆኑም የሚሰበስበውን ገንዘብ ለጡረተኞች ከፍሎ፣ መጠባበቂያ ካስቀመጠ በኋላ የተረፈው ገንዘብ ዋጋ እንዳያጣ፣ የመግዛት አቅሙን ጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ በተመረጡ እና አዋጪ በሆኑ የኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ያውለዋል።
የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ በንጉሱ ዘመን የነበረ ተቋም እንደሆነና ለውጡ የሚጀምረውም ከዚያ ጊዜ ወዲህ ነው ያሉት ደግሞ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ህግ ፋካሊቲ መምህርና ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር መሃሪ ረዳኢ ናቸው። እንደ ዶ/ር መሃሪ ማብራሪያ፣ በንጉሱ ዘመን የጡረታ መውጫ ዕድሜ ለወንድ 60፣ ለሴት ደግሞ 50 ነበር። ይህም ሴቶች ቀደም ብለው ከስራ ቢገለሉ ይሻላል በሚል ዕምነት የተተገበረና የጾታ ዕኩልነትን የሚያንጸባርቅ አልነበረም። የደርግ መንግስት ሲመጣ የሁለቱንም ጾታዎች የጡረታ መውጫ ዕድሜ 55 ዓመት ያደረገ ሲሆን፣ በኢህአዴግ ሥርዓት ደግሞ 55 ዓመት የነበረውን የጡረታ መውጫ ዕድሜ ከጊዜ በኋላ የሁለቱንም ጾታ ዕድሜ ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ወደ 60 ዓመት ከፍ አድርጎታል።
ከአዋጅ ለውጡ ጋር በተያያዘ መነሳት የሚገበው ጉዳይ የግል ዘርፉም የጡረታ ሥርዓት የተበጀለት መሆኑ ነው። ድሮ የጡረታ መብት የነበረው የመንግስት ሠራተኛና የመንግስት የልማት ሠራተኛ ብቻ ነበር። ከቅርብ አመታት ወዲህ፣ የግል ዘርፉም ወደ ጡረታ ዕቅድ ውስጥ መግባት ችሏል። ቀደም ሲል ሠራተኛው የተሻለ የስራ ዕድል ቢያገኝም የጡረታ አገልግሎቴ ይቀርብኛል በሚል ስጋት ከመንግስት መ/ቤት ሳይወጣ እዚያው የመቀጠል አዝማሚያ ይታይበት ነበር። ሰራተኛው ከግል ዘርፉ ወደ መንግስት መ/ቤት እንዳይሄድም የተለያዩ ጥቅማጥቅሞች ይቀሩብኛል በሚል ፍርሃት የዝውውር እንቅስቃሴው ተገድቦ ቆይቷል። አሁን ግን አንድ ሠራተኛ ከየትኛውም መ/ቤት ያጠራቀመውን ገንዘብ፣ ያገለገልክበትን ዕድሜ እና የጡረታ መለያ ቁጥሩን ይዞ ወደ የትኛውም ተቋም መሄድ የሚችልበት አሰራር ተፈጥሯል። የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት፣ ሁለቱም አደረጃጀቶች ተጠሪነታቸው ለብሔራዊ ባንክ ስለሆነም ሰራተኛው ከስራ ጋር በተያያዘ ወደ የትኛውም ተቋም እንዳይንቀሳቀስ የሚገድበው አሰራር አለመኖሩ በለውጡ ሂደት የተገኘ አንዱ በበጎ ጎኑ የሚታይ ጉዳይ ነው።
በቅርቡ የወጡት የ2003 ዓ.ም እና የ2014 ዓ.ም አዋጆችም ቢሆኑ አጠቃላይ መርሃቸው ተመሳሳይ እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር መሃሪ፣ በሁለቱም አዋጆች 60 ዓመት ዕድሜ የመጦሪያ ጊዜ ሲሆን፣ ከ60ዓመት በታች በጤናም ሆነ በአካል ጉዳት ምክንያት የመጦር ዕድል እንዳለ በሁለቱም አዋጆች መቀመጡን፣ ለጡረታ ብቁ ለመሆን ደግሞ ዝቅተኛው መነሻ የአገልግሎት ዘመን 10 ዓመት መሆኑን ይገልጻሉ።
በአዋጅ ማሻሻያው ከተዳሰሱ አንኳር ጉዳዮች መካከል አንዱ የጡረታ መዋጮ የተሰበሰበውገንዘብ ለተጠቃሚው እስኪከፈል ድረስ ምን ላይ መዋል አለበት የሚለው ነው። ቀደም ብሎ በነበረው አሰራር የሚሰበሰበው መዋጮ ገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ መሰረት ለቦንዶችና ሌሎች አትራፊ የንግድ ዘርፎች ኢንቨስት እንዲደረግ ያዝ ነበር። ገንዘብ ሚኒስቴር ደግሞ ሌሎች ትልልቅ ተግባራትን የሚያከናውን ተቋም ስለሆነ መመሪያውን ሳያወጣ በመቅረቱ ገንዘቡ በባንክ ተቀምጦ ከዚህ ግባ የማይባል ወለድ ብቻ እየተሰበሰበበት፣ አትራፊ በሆነ ተግባር ላይ እንዳይውል ገድቦት ቆይቷል።
አሁን ግን፣ ይህን ችግር ለመቅረፍ ሲባል የማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ቦርድ የሚባል ተቋቁሟል። ቦርዱ፣ ገንዘቡ ምን ምን የኢንቨስትመንት ዓይነቶች ላይ ቢውል የተሻለ ውጤታማ ይሆናል ብሎ ወስኖ ኢንቨስት እንዲያደረግ ያዛል። በተለይም፣ ቦርዱ ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ባንክ መሆኑ፣ ልክ እንደ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ሁሉ የተሻለ የኢንቨስትመንት አትራፊነት አቅጣጫን የማመላከት ዕድሉን ያሰፋለታል።
በተገኘው መረጃ መሰረት ከተቋሙ እና ከአዋጅ ማሻሻያው ጋር በተያያዘ፣ ወደ ዝርዝር ጉዳይ ሲገባ በለውጡ ከተዳሰሱት መካከል አንዱ የጡረታ ”መለያ ቁጥር” ነው። የጡረታ መለያ ቁጥር ቀደም ሲል ይሰጥ የነበረው በተቋሙ ወይም በግብር ሰብሳቢው አካል ነበር። በመሆኑም የጡረታ መለያ ቁጥር ድግግሞሽ እንዳይኖር፣ አንድ ሰው ሁለት ቁጥር እንዳይኖረው፣ ሁለት ሰዎች ደግሞ አንድ ዓይነት ቁጥር እንዳይኖራቸው እና ቁጥሮቹን ወጥ ለማድረግ ሲባል ብሔራዊ መለያ ቁጥር የሚሰጥ ተቋም እንዲቋቋም ተደርጓል።
የወታደር /የፖሊስ፣ የመከላከያ ሠራዊት፣ የመሳሰሉት/ መዋጮን በተመለከተ አሰሪው ይከፍለው የነበረው መዋጮም ከ25 ከመቶ ወደ 33 ከመቶ አድጓል። ምክንያቱ ደግሞ በእነዚህ ተቋማት የሚሰሩ ሰራተኞች የጡረታ መውጫ ዕድሜ እንደ ሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች 60 ዓመት ሳይሆን፣ የጡረታ መውጫቸው በመቋቋሚያ ደንባቸው፣ ወይም ህጋቸው መሰረት ነው ስለሚል፣ በተለያየ ጊዜ በ55፣ በ45፣ ወዘተ ዕድሜያቸው ጡረታ እንዲወጡ ስለሚፈቅድላቸው ነው። የወታደር ስራ እንደሚታወቀው አደገኛ /Risk area/ ነው። በመሆኑም፣ በእነዚህ ምክንያቶች የሠራተኛውን መዋጮ መጨመር ሳያስፈልግ፣ የአሰሪው መዋጮ ብቻ እንዲጨምር ሆኗል።
በ714/2003 አዋጅ ተቋማት የአሰሪውንም ሆነ የሰራተኛውን መዋጮ በወቅቱ ሰብስበው ወደ ባንክ እንዲያስገቡ ደንግጓል። ይሁን እንጂ፣ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እኛ ባንክ አይደለንም በሚል ምክንያት ለአዋጁ ተገዥ ባለመሆን ለአሰራር ችግር ፈጥረው ቆይተዋል። በማሻሻያ አዋጁ ላይ ግን፣ ማንኛውም የፋይናንስ ተቋም ጉዳዩ እንደሚመለከተው ተደንግጓል። በመሆኑም አንዳንድ በመንግስት በጀት የማይተዳደሩ ገንዘቦችን በማይክሮ ተቋማት በማስቀመጥ የጡረታ ፈንዱ በአግባቡ ስራ ላይ እንዳይውል ያደርጉ የነበሩ ተቋማትንም የህግ ማዕቀፉ በአግባቡ ዳስሷቸዋል።
ባንኮች የሰበሰቡትን ገንዘብ ገቢ ሳያደርጉ ሲቀሩ የሚቀጡበት የህግ አግባብም በአዋጁ ላይ በግልጽ አልተቀመጠም ነበር። አሁን ግን ገንዘቡን በተቋሙ እንዲያስገቡ ታዘው ሳያስገቡ ገንዘብ ካወጡ ባወጡት ገንዘብ ልክ ተጠያቂ ይሆናሉ። የሚፈለገው ገንዘብ ባንክ ላይ የማይገኝ ከሆነም ተቋሙ ንብረት እስከማሸጥ የሚደርስ ስልጣን ተሰጥቶታል። ይህም፣ በገንዘብ ሚኒስቴር መመሪያ “ንብረት ይሸጣል” የሚለውን ለአሰራር ችግር ይፈጥር የነበረውን የበፊቱን አዋጅ በመሻር ተቋሙ ራሱ በሚያወጣው መመሪያ እንዲፈጸም ማድረጉ ሌላው የለውጡ አካል ነው።
የአዋጅ ማሻሻያው ዋና ዓላማ ተቋሙ የነበረበትን የአሰራር ክፍተት መቀየር እና ማስተካከል መሆኑን አቶ ሀሰን ያብራራሉ። እንደእሳቸው አገላለጽ፣ ይህ ተቋም በአፍሪካም ሆነ በዓለም ደረጃ ከሌሎች የመንግስት ተቋማት የተሻለ የፋይናንስ ተቋም ተደርጎ ይቆጠራል። ነገር ግን እስከዛሬ ድረስ በተግባር ሲታይ ተቋሙ ከአስፈጻሚነት ስራው በዘለለ ጠንካራ የፋይናንስ ተቋም መሆን አልቻለም ነበር፣ አሁን ላይ ግን፣ ቀድሞም ከነበሩት ኃላፊነቶቹ ላይ የገቢ ማስገኛ የሆነው የኢንቨስትመንት ስልጣን ተፈጥሮለታል።
የተቋሙ የለውጥ ዓላማ የጡረተኛውን ማህበረሰብ ለመጥቀምና ኑሮውን ለማሻሻል ነው። ተቋሙ በየጊዜው አሰራሩንና አደረጃጀቱን የሚያሻሽለውም ጡረተኛውን ማህበረሰብ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ስለሆነም፣ ተቋሙ የተቋቋመውም አረጋውያንንና የጡረተኛ ማህበረሰቡን ለማገልገል በመሆኑ ማሻሻያው ይህን ዓላማውን ለማሳካት የሚያደርገው እንቅስቃሴ አንዱ አካል ነው የሚሉት የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ማህበር ብሔራዊ ቦርድ ም/ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው ክፍሉ ናቸው።
አቶ ሀሰን ደግሞ፣ የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫና የለውጡን ጠቀሜታ አስመልክቶ እንደ ሀገር ሲታይ በዋናነት ከድህነት ወለል በታች የሚገኘውን የጡረተኛ ህይወት ማሻሻልና በኢንቨስትመንት ደግሞ ጠንካራ የገንዘብ ተቋም በመሆን አገሪቱን በኢኮኖሚ መደገፍ መሆኑን በማንሳት የአቶ ጌታቸውን ሃሳብ ያጠናክራሉ።
በቆዩት አዋጆች በተለይም በአዋጅ ቁጥር 714/2003 ተቋሙ ኢንቨስት እንዲያደርግ የተፈቀደለት የትሬዠሪ ቦንድ በመግዛትና የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ተፈጻሚ እንዲያደርግ የሚል ነበር። ይሁን እንጂ አዋጁ ከወጣ ከ10 ዓመት በላይ ቢሆነውም፣ገንዘብ ሚኒስቴር መመሪያ ባለማውጣቱ ምክንያት የኢንቨስትመንት ስራውን ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም። በዚህም ምክንያት የቆየውን አዋጅ፣ እንደገና እንዲሻሻል በማድረግ የኢንቨስትመንት ስራን ለመጀመር ተቋሙ በሂደት ላይ ይገኛል።
ተቋሙ የኢንቨስትመንት ስራን እንዲያከናውን ለምን ተፈቀደለት? ለሚለው ጥያቄ በዋናነት የጡረተኞችን ጥቅም ለማስከበር መሆኑን አቶ ሀሰን ያስረዳሉ። አያይዘውም፣ በፊት የነበረው አዋጅ በአምስት ዓመት ውስጥ ለጡረተኞች የአበል ጭማሪ ይደረጋል የሚል ቢሆንም፣ በተግባር ግን ጭማሪው በየሁለት ዓመቱ እየተከናወነ መሆኑን ያብራራሉ። ምክንያቱን ሲገልጹም፣ የጡረተኞች የገቢ መጠናቸው ከጊዜው ሁኔታ ጋር አብሮ የሚሄድ ባለመሆኑ እና የወቅቱን የኑሮ ሁኔታና የገንዘቡን የመግዛት አቅም በማገናዘብ ነው ብለዋል፤ የጡረተኞችን ኑሮ ለማሻሻል፣ የመክፈል አቅምን በኢንቨስትመንት ማጠናከር እንደሚያሻም ያሰምሩበታል።
ቀደም ሲል የነበረው የአበል ማስተካከያ ሊደረግ የሚችለው በየ 5 ዓመቱ ሆኖ በሚኒስትሮች ም/ቤት ሲወሰን ነበር። በአሁኑ አዋጅ ግን፣ የአበል ክለሳው ወደ ሚኒስትሮች ም/ቤት መቅረብ ሳያስፈልገው በየ 3 ዓመቱ በቦርዱ እንዲወሰን ሆኗል። ለውጡ ገና በሂደት ላይ ስለሆነ ወደፊት የሚታይ ቢሆንም፣ በወረቀት ባለው ደረጃ ሲመዘን የተሻለ የአሰራር ነጻነትና የውሳኔ ተለዋዋጭነት እንዲኖር ዕድል የሚፈጥር ስለሆነ ተስፋ የሚታይበት መሆኑን ዶ/ር መሃሪም ያስረዳሉ።
ተቋሙ ለጡረተኛው አበል መደጎሚያ ሊሆን የሚችል የኢንቨስትመንት ተግባር ማካሄድ እንዲችል መፈቀዱ ትክክል መሆኑን በተመለከተአቶ ጌታቸው ሲገልጹ፣ ተቋሙ እሪ በከንቱ ላይ ዘጠኝ ወለል ያለው ፎቅ ለጽ/ቤት መገንባቱን ያስረዳሉ። ነገር ግን፣ ተቋሙ ለሰራተኛው ምቾት ሳይሳሳ ለአረጋውያንና ለጡረተኞች በማሰብ ለገቢ ማስገኛ ለማዋል መወሰናቸው በራሱ ለኢንቨስትመንት ስራ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያመላክታል ብለዋል። በተለይም፣ ሌላው ተቋም ለራሱ ቢሮ ምቹ መሆን በሚጨነቅበት ወቅት፣ እነሱ ግን ለጡረተኛው ማህበረሰብ ማሰብ መቻላቸው የሚደነቅ ተግባር መሆኑን ያብራራሉ። ተቋሙንም በቅርበት እንደሚያውቁት በማንሳት፣ በአዲሱ አደረጃጀት የኢንቨስትመንት ተግባሩን በአግባቡ በመወጣት ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው እንደሚችል እንደ ማህበር ከፍተኛ እምነት አላቸው። በመሆኑም ሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችም ይህንን አርአያነት ያለው ተግባር ቢከተሉ ያለ ጥርጥር ለችግር ተጋላጭ የሆነ የህብረተሰብ ክፍል ኢትዮጵያ ውስጥ ሊጠፋ እንደሚችል ያምናሉ።
ዶ/ር መሃሪም፣ ተቋሙ በነበረው አሰራር እንደ አንድ ዋና ችግር ይቆጠር የነበረው ለጡረተኛ ማህበረሰብ የሚሰበሰበው ገንዘብ ኢንቨስትመንት ላይ ውሎ ለሀገር ጠቅሞ ለጡረተኛውም ከኑሮ ውድነት እና ከገንዘብ የመግዛት አቅም ጋር የተገናዘበ የጡረታ አበል እንዲከለስ አለማስቻሉ መሆኑን ያነሳሉ። እንደ ዶ/ሩ ማብራሪያ፣ አሁን ላይ ተቋሙ ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ባንከ መሆኑ፣ ኢንቨስትመንቱ በገንዘብ ሚኒስቴር ከሚወሰን ይልቅ ራሱን በቻለ የአስተዳደር ቦርድ እንዲወሰን ስለሚያደርገው የተሻለ ገቢና ትርፍ ወዳለበት ዘርፍ መዋጮውን የማዋል ዕድልን ይፈጥርለታል። በኢንቨስትመንት የተሻለ ትርፍ ከተገኘ ደግሞ የመንግስት ካዝና ሳይጠበቅ የጡረታ አበሉ በየጊዜው እየተከለሰ ጡረተኛው ተጠቃሚ የመሆን ዕድሉን ያሰፋለታል።
ለጡረተኛው ማህበረሰብ በመዋጮ የሚሰበሰበው ገንዘብ ቀላል የሚባል አይደለም። በመሆኑም ባንክ ላይ ቢቀመጥ በዓመት ወለዱ 7 በመቶ ብር ብቻ ነው። አንዳንድ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ግን 30 እና 35 በመቶ ገቢ የማስገኘት ዕድል አላቸው። ስለዚህ ገንዘቡ ወደ እነዚህ ዓይነት የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲውል መደረጉ፣ በንግድ ዘርፉ አገርን ጠቅሞ መንግስትን ሳያስቸግሩ የጡረታ ማስተካከያ ለማድረግ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል። በዚህ የኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚገኘው ገቢም የትርፍ ግብር የማይቀነስበት ስለሆነ፣ ወደ 35 በመቶ የሚደርስ ግብር የማይከፈልበት የገንዘብ ደጎማ ማግኘት መቻል በቀላሉ የሚታይ ለውጥ አለመሆኑን ዶ/ር መሃሪ ያሰምሩበታል።
ቀጣዩ የተቋሙ ተግባር ሊሆን የሚችለው፣ በነበረው የሲቪል ሰርቪስ ህግ ኢንቨስትመንቱን ማስተዳደር ስለማይቻል የሰው ሃብት አስተዳደሩን መቀየር መሆኑን አቶ ሀሰን ያብራራሉ። በመሆኑም፣ ተቋሙ ከአደረጃጀቱ ባህርይ አኳያ በከፊል የፋይናንስ፣ በከፊል ደግሞ የመቆጣጠር ስራውን ማከናወን እንዲችል የተለየ ደንብ አዘጋጅቶ የኢንቨስትመንት ባለሙያዎችን መቅጠር የግድ ይለዋል። የሚቀጠሩት ባለሙያዎችም፣ ያለውን ካፒታል መነሻ በማድረግ አዋጭ የኢንቨስትመንት ዘርፍ አጥንተው ለውሳኔ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ መንገድ የተቋሙ ገንዘብ የመክፈል አቅሙ ሲጠናከር ለጡረተኞች የሚደረገው የአበል ጭማሪ የወቅቱን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የመጨመሪያ ጊዜውን ያሳጥረዋል። የሚጨመረው የገንዘብ መጠንም የተሻለ ይሆናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለጡረተኞች ገንዘቡ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ እንዲሰጣቸው በማድረግ የኑሮውን ጫና እንዲቋቋሙ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል።
በቅርብ ጊዜም መንግስት የጡረታ ማስተካከያ አድርጓል። 1,258 ብር የነበረው ዝቅተኛው የጡረተኛ መነሻ ብር 2,218 ሆኗል። በዚህም ለዝቅተኛው ተከፋይ ወደ 1,000 የሚጠጋ ብር ተጨምሯል። ጭማሪው ከትልቁ ወደ ትንሹ በመሆኑ በመቶኛ ሲሰላ ከ76 ከመቶ በላይ ነው። ለዚህም ነው የኢንቨስትመንት ዋናው ጠቀሜታ የተቋሙን ገንዘብ የመክፈል አቅም በማሳደግ፣ በዚያው ልክ የጡረተኞችን ህይወት መቀየር ነው የተባለው።
የጡረታ አበል ማስተካከያውን በተመለከተ አቶ ጌታቸው ሲገልጹ፣ እንደ ማህበር ጥር 2014 ዓ.ም ጡረተኞች የኑሮውን ውድነት መቋቋም ስላልቻሉ ችግሩን እንዲቋቋሙ የጡረታ አበል ማስተካከያ ይደረግ በሚል ከተቋሙ ጋር ብዙ ውይይት አካሂደዋል። ውይይቱ ውጤት አምጥቶ ከመስከረም ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ የአበል ማስተካከያ ተደርጓል። ይህ ጭማሪ ደግሞ በየትኛውም ስርዓት ታይቶ አይታወቅም። ቀደም ሲል የ46 እና የ69 በመቶ ጭማሪ ቢደረግም፣ ይህ የአበል ማስተካከያ ግን ስር ነቀል ለውጥ ሊባል የሚችል ነው። ስለሆነም እንደ ማህበር የሚያስቡት በተቋሙ ከፍተኛ ለውጥ እየተካሄደ እንደሆነ ነው። አስተዳደሩ ደግሞ ከሃላፊዎቹ እስከ ሰራተኛው ለሚያቀርቡት ጥያቄ ሁሉ አወንታዊ የሆነ አመለካከት እንዳላቸውና ሃሳባቸውንም በቀናነት ስለሚመለከቱላቸው ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ 60 እና ከዚህ በላይ የሆኑ 6.8 ሚሊዮን አረጋውያን አሉ። ጡረተኛው ግን 7,000 ሺህ ብቻ ነው። ማህበራቸው በየጊዜው የወቅቱን የኑሮ ውድነት መቋቋም ላቃተው ጡረተኛ ማህበረሰብ የአበል ጭማሪና ማስተካከያ እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረባቸውን ይናገራሉ። መንግስት ደግሞ በፖለቲካ ሽኩቻ ከግራና ቀኝ በተወጠረበትና አገር ችግር ውስጥ በገባችበት፣ ከዚህም ከዚያም ተፈናቃይ በበዛበት፣ የመልሶ ማቋቋሙ ስራው ብዙ ወጪ በሚጠይቅበት፣ ለህዳሴ ግድብ ብዙ ብር በሚያስፈልግበት እና የተለያዩ ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ተግባራዊ በሚደረጉበት ወቅት ማስተካከያው ተግባራዊ መደረጉ መንግስት ለጡረተኛው ማህበረሰብ ችግር ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን አመላካች መሆኑን ያብራራሉ።
የተቋሙን አገልግሎት አሰጣጥ ዘመናዊ በማድረግ ጡረተኞች እንዳይጉላሉ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አቶ ሀሰን ይገልጻሉ። አሁን ባለው አሰራር አንድ ሰው ጡረታ ሲወጣ መረጃውን አሟልቶ ከተገኘ ውሳኔ ለመስጠት ከአንድ ሰዓት በላይ አይፈጅም። ወደ ፊትም ቢሆን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የበለጠ አሰራሩን ለማፋጠን እየተሰራ ነው።
ይህን ሃሳብ አቶ ጌታቸው ሲያጠናክሩት፣ ቀደም ሲል ጡረተኛው አበሉ ይከፈለው የነበረው በየቦታው ነበር። በፖስታ ቤት፣ ሌላ ጊዜ ጡረተኞች በሚሰበሰቡበት አካባቢ በሚል በጣም ከፍተኛ እንግልት ነበረው። በዚህም ጡረተኞች ለጸሀይና ዝናብ ይጋለጡ ፣ ከድካምና ልፋታቸው በተጨማሪም ለከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ ይዳረጉ ነበር። አሁን ላይ ግን፣ በአካባቢው ሊገኝ በሚችል በንግድ፣ በአቢሲኒያ፣ በኦሮሚያ እና በመሳሰሉ ባንኮች አማካኝነት የጡረታ አበላቸውን በመክፈል ከፍተኛ የሆነ ልፋትና ድካማቸውን፣ እንዲሁም የትራንስፖርት ወጪያቸውን መቀነስ መቻላቸው ትልቅ የአሰራራቸው ለውጥ ማሳያ ነው ይላሉ።
ከእጅ ወደ አፍ የሆነው የጡረተኛው ማህበረሰብ ኑሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጫናው እየበዛበት እንደሚሄድ ይታወቃል። መንግስት ደግሞ ይህን ችግር ለማቃለል የተለያዩ ርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል። በመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ተቋም ላይ የተካሄደው የአደረጃጀትና አሰራር ማሻሻያም የርምጃው አንዱ አካል ነው። በመሆኑም ለውጡን ዕውን አድርጎ የጡረተኞችን ህይወት ለመቀየር ለሚደረገው ትግል ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል እንላለን።
ንጉሴ ተስፋዪ