አገር የሚበላው ነቀዝ

በአማርኛ ቋንቋ “ሙስና” የሚለው ቃል “corruption” ለሚለው የእንግሊዝኛ ቃል አቻ ትርጉም የሚሰጥ ሆኖ ግልጋሎት እየሰጠ ነው። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ያሳተመው አማርኛ መዝገበ ቃላት ገጽ 67 ላይ “ሙስና” የሚለውን ቃል በስልጣን ወይም በስራ ድርሻ አላግባብ የመገልገል፣ የመጠቀም ወይም የመጥቀም ድርጊት ነው ሲል ይበይነዋል። የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 404 ንዑስ አንቀጽ ሦስት ‹ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የማይገባ ጥቅም ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው መብት ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ በተሰጠው ኃላፊነት ወይም ተግባር ማድረግ የሚገባውን እንዳያደርግ ወይም ማድረግ የማይገባውን እንዲያደርግ ከሌላ ሰው ላይ ጥቅም የተቀበለ ወይም የጠየቀ፣ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ጥቅም ለማስገኘት የተሰጠውን ስልጣን ወይም የሕዝብ አደራ ያላግባብ የተገለገለበት እንደሆነ ወይም ማንኛውም ሰው ለራሱ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው መብት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማሰብ፣ ለመንግስት ሰራተኛ የማይገባ ጥቅም ለመስጠት ቃል የገባ፣ ያቀረበ፣ የሰጠ፣ ወይም ለማቅረብ የተስማማ እንደሆነ› ሲል የሙስናን ምንነት ይገልጻል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች በተለያዩ አደረጃጀቶች ሙስናን ለመከላከል ስትታገል ቆይታ በ1993 ዓ.ም የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ- ሙስና ኮሚሽንን ተቋቁሞ የፀረ-ሙስና ትግሉን በፌዴራል ደረጃ እንዲያስተባብርና እንዲመራ ተደርጓል። በተዋረድም በክልሎችም ተመሳሳይ ስልጣንና ተግባር ያላቸው ኮሚሽኖች ተቋቁመው የጸረ ሙስና ትግሉን በክልል ደረጃ የመምራትና የማስተባበር ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል። በኋላም በአዋጅ ቁጥር 1236 /2013 የፌዴራል የስነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ እንደገና ለማሻሻል አዲስ አዋጅ ወጥቷል።

በአዲሱ አዋጅ እንደተጠቀሰው የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ሙስና እና ብልሹ አሰራር የአገራችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እድገት የሚገታ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ የህግ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ፤ በአገራችን የተጀመረውን የልማት፣ የሰላም እና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ሙስና እና ብልሹ አሰራርን መከላከል በመልካም ስነ ምግባር የተገነባ፣ ሙስናን የሚፀየፍ፣ በፅናት የሚታገል ህብረተሰብ መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ፤ የኮሚሽኑ አሠራር የግልጽነት እና የተጠያቂነት መርሆዎችን የተከተለ እንዲሆን በማድረግ ኮሚሽኑ ተቋማዊ እና የአሰራር ነፃነት እንዲኖረው ማድረግ ተገቢ በመሆኑ፤ ለኮሚሽኑ በተለያዩ አዋጆች የተሰጡትን ስልጣንና ተግባራት በአንድ ላይ ማሰባሰብ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እና ኮሚሽኑ በአገር ደረጃ የፀረ ሙስና ትግሉን የመምራት እና የማስተባበር ሚናውን ለመወጣት የሚያስፈልገውን የኃላፊነት ወሰን በህግ መደንገግ በማስፈለጉ፤ የሙስና መከላከል ተግባር በአንድ ተቋም ተጀምሮ የሚጠናቀቅ ባለመሆኑ ኮሚሽኑ ከሌሎች ተቋማት ጋር የሚኖረው ግንኙነት የህግ ድጋፍ እንዲኖረው በማድረግ ከፀረ ሙስና ትግል አኳያ በዓለም አቀፍ እና በአህጉር ደረጃ አገሪቱን በብቃት እንዲወከል ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው ማሻሻያው ያስፈለገው።

የጸረ ሙስና ትግሉን የሚያግዙ የህግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ተቋማዊ ስራዎች ሲከናወኑ ቢቆዩም የሚወሰዱት እርምጃዎች የዘመቻ መልክ የነበራቸው ነበሩ። ይህ ደግሞ፣ ሙስና እና ሙሰኞች ጉልበት እንዲያገኙና ለአገር ፈተና የሆኑበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል። በየዓመቱ የአገራትን የሙስና ተጋላጭነት ይፋ የሚያደርገው ዓለምአቀፉ ፀረ-ሙስና ጥምረት ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2022 ባወጣው መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ ከ180 አገራት 87ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ይሄው ተቋም ከ10 ዓመታት በፊት በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር የ2012 ባወጣው የአገሮች የሙስና ደረጃ ከተፈተሹት ከ174 አገሮች ኢትዮጵያን 113ኛ ላይ አስፍሯት ነበር። ዛሬ የኢትዮጵያ መንግስት ሙስና የአገር የደኅንነት ሥጋት መሆን ደረጃ ላይ እንደደረሰ እየገለጸ ባለበትና የተፈታሽ አገራት ቁጥር ከ174 ወደ 180 ከፍ ባለበት ሁኔታ ኢትዮጵያ 26 ደረጃዎችን ማሻሻሏ በሌሎች አገራት ሙስና ፍጹም ያየለበት ሁኔታ ካልኖረ በቀር አጠያያቂ ይመስላል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ይፋ ሲያደርጉ ሙስና ዛሬ የአገራችን የደኅንነት ሥጋት ሆኗል። ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ እጅ ተወርች አሥሮ ለመያዝ ከጠላቶቻችን እኩል ሙሰኛው እየታገለን ነው። የተስተካከለ ቢሮክራሲ፣ የተቀናጀ መዋቅርና ዘመናዊ አሠራር ለሙስና ተጋላጭነትን ስለሚቀንሱ፣ እነዚህን ለማጥፋት ወይም ለማሰናከል ሙሰኛው ቀን ከሌት እየሠራ ነው።

ሕዝባችን በአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከመሬት ጋር በተያያዙ አሠራሮች፣ በፋይናንስ ዘርፍ፣ በሽያጭና ግዥ ሂደቶች፣ በፍትሕ አደባባዮች፣ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶች፣ የህዝብ ተቋማት ወዘተ. በሚያጋጥመው ሙስና እየተማረረ ነው። በተለያዩ ጊዜያት ከሕዝብ ጋር በተደረጉ ውይይቶች ከጸጥታ ሥጋቶች እኩል ሙስና የብልጽግና ጉዟችን ዋናው ዕንቅፋት መሆኑን አንሥቷል በማለት ሙስና የደረሰበትን ደረጃ ገልጸዋል።

የህግ ባለሙያው አቶ አመሃ መኮንን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ መንግስት ኃላፊነታቸው እንዲህ አይነት መግለጫ ሲሰጡ የአሁኑ የመጀመሪያ አለመሆኑን ይገልጻሉ። ሙስና በተባለው ደረጃ ምናልባትም ከተባለው ደረጃ በከፋ ሁኔታ በአገራችን ተንሰራፍቷል። በተለይም በመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና በፍርድ ቤቶች አካባቢ ህዝቡን ያማረረ እንደነበረና አሁንም እንደሆነ የሚታወቅ ሀቅ ነው። ህዝቡም በብዛት በምሬት የሚናገረው ጉዳይ ነው። አሁን መንግስት የሚታገሰው አይደለም የአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አደጋ ደቅኗል ብሎ ከመምጣቱ በስተቀር በበርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አካባቢ ያለጉቦ አገልግሎት መስጠት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ሲሉም ያክላሉ።

ሙስናን ለመታገል በሚል ቀደም ሲልም የጸረ ሙስና ኮሚሽን ተቋቁሞ እንደነበር በማስታወስም፣ ይሄ ተቋም በአንድ ወቅት ከማስተማርና ከመከታተል ባለፈ በሙስና የሚጠረጠሩ የመንግስት አካላትን የመመርመርና የመክሰስ ስልጣን ሁሉ ነበረው በኋላ ይህ ስልጣን ከእጁ ወጥቶ ወደ ፌዴራል አቃቢ ህግ የዞረበትን ሁኔታ እናውቃለን። ይሄ ተቋም ያደረገው አስተዋጽኦ ነበረ፣ ነገር ግን የሙስና ወንጀልን የመመርመርና የመክሰስ ስልጣኑን ካጣ በኋላ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ ነበር ለማለት ያስቸግራል። መንግስት አሁን ይህንን ተቋም በሚያጠናክርና በሚያግዝ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጥታ የሚከታተሉት ራሱን የቻለ ኮሚቴ እንዳቋቋመ ነው የገለጸው። መንግስት “ችግሩን ተረድቼዋለው፤ ህዝብ ተማሯል፤ በአጠቃላይ የመንግስትን አሰራር በማሽመድመድ ህዝብ በመንግስት ላይ እምነት እንዳይኖረው እያደረገ ነው በሚል የተነሳበት አግባብ ጥሩ ነው” የሚል ግምገማ እንዳላቸው ይናገራሉ።

አያይዘውም፣ የኮሚቴው ዝርዝር ኃላፊነት እና አሰራሩን የተመለከቱ መረጃዎች እስካሁን ይፋ ባለመደረጋቸው እንዴት ታች ድረስ ወርዶ ሊሰራ እንደተዘጋጀ የሚያሳይ ነገር የለም። ምናልባት፣ በአገራችን የቅርብ ጊዜ ታሪክ እንደሚታወቀው አንዳንድ ጊዜ ሙስና ላይ የሚደረግ ዘመቻ የፖለቲካ መሳሪያ የሆነበት አጋጣሚ እንደነበረ ስናስብ አዲስ የተቋቋመው ኮሚቴ ዝርዘር ኃላፊነቱ ብዙም ካለመታወቁ ጋር ተደምሮ የሚነሱ አንዳንድ ጥርጣሬዎች አሉ። መጀመሪያም የፌዴራል ጸረሙስና ኮሚሽን ሲቋቋም፣ ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው። እንደሚታወቀው ሙስና በባህሪው የመንግስት ባለስልጣናት ስልጣናቸውን ተጠቅመው ከሚፈጽሙት ወንጀል ነው። ከመንግስት መዋቅር ውጭ ያሉ ሰዎች በተባባሪነት ሊሳተፉ ይችላሉ። ከዚህ አንጻር ጥርጣሬ መኖሩና የገለልተኛነት ጥያቄ መነሳቱ አግባብ ነው ብለው እንደሚያምኑ ይገልጻሉ።

ነገር ግን፣ በአስፈጻሚው አካል መቋቋሙ ብቻ በቀጥታ ገለልተኛ አይሆንም ለማለት ላያስደፍር ይችላል የሚሉት የህግ ባለሙያው፣ ገለልተኛ ነው ወይም አይደለም የሚያሰኙት በተግባር የሚወስዳቸው እርምጃዎች ናቸው። ስለዚህ በተግባር ገለልተኛነቱን የሚያሳዩ እርምጃዎችን ሲወስድ መታየት መቻል አለበት። ይህ ካልሆነ ግን፣ የፖለቲካ ፍላጎትን ለማሳካት የተወሰደ እርምጃ ተደርጎ ስለሚወሰድ ማህበረሰቡ እምነት ሊያጣበት ይችላል። የተቋቋመው ኮሚቴ በተነገረው መጠን ወደስራ ገብቶ ውጤት ማየት መቻል አለብን። በርግጥ ኮሚቴው እንደተቋቋመ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ በተወሰዱ እርምጃዎች የታሰሩ ሰዎች እንዳሉ አውቀናል። የተነገረውና የተወሰዱ እርምጃዎች መጠን እና አይነት ሲታይ እውነት ለመናገር ብዙ የሚያኩራራ ሆኖ አላገኘወትም። ብዙ ስራ ስለሚጠይቅ ምናልባትም ከዚህ በኋላ በተከታታይ የምንሰማቸው ነገሮች ይኖራሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ይላሉ።

መሰል አደረጃጀቶችን ማቋቋም በሌሎች አገራትም የሚሰራበት መንገድ ነው። ሙስናን በመክሰስና በማስቀጣት ብቻ ሙሉ ለሙሉ መከላከል አይቻልም። ከአስተሳሰብ፣ ከባህልና ከማህበረሰብ እድገት ጋር ይያያዛል። የመንግስትን ንብረት እንደ ራሱ ንብረት አድርጎ የሚቆጥር ማህበረሰብ መፈጠር አለበት። ስለዚህ መጠነ ሰፊና ዘርፈ ብዙ ትግል የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። በአዋጅ የተቋቋመው የጸረ ሙስና ተቋም ዋነኛ ግቡ የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊና በማሳደግ ሙስናን የሚጠየፍ ትውልድ ለመፍጠር ተከታታይነት ያለው ስራ መስራት ያሉን አቶ አመሃ፣ በአንድ መልኩ ይሄ ስራ እየተሰራ በተለያየ ምክንያት የሙስና ደረጃው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገለጹት መጠን እጅግ ከፍተኛ ሁኔታ ላይ የሚደርስና የአገርን ኢኮኖሚ በእጅጉ የሚጎዳ ሆኖ ሲገኝ እንዲህ አይነት ጊዜያዊ ኮሚቴ በማቋቋም ጠንካራ እርምጃዎ መውሰዱ ተገቢ መሆኑንም ይገልጻሉ።

የኮሚቴው የቤት ስራዎች ሊሆኑ የሚችሉትን ጉዳዮች በተመለከት ግምታቸውን ሲያስቀምጡ፣ ዋነኛ አይነኬ በተባሉት አካባቢዎች ላይ ቆራጥ የሚባሉ እርምጃዎን በመውሰድ የሙስና ወንጀሎችን በመመርመር ተጠርጣሪዎች በህግ እንዲጠየቁ ውሳኔዎችን ማሳለፍና አቅጣጫ ማስቀመጥ ይሆናል ብዬ እጠብቃለሁ። እንዲሁም፣ በአዋጅ የተቋቋመው የጸረሙስና ኮሚሽን ከስራ አስፈጻሚው አካል ተፅእኖ ውጪ ስራውን ያለችግር እንዲሰራ ማስቻል ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ህብረተሰቡንም በጸረሙስና ትግል ላይ በማንቀሳቀስ ረገድም ትልቅ ሚና ይኖረዋል የሚል ግምት አለኝ ብለዋል።

ሙስናን መታገል የመንግስት ብቻ ኃላፊነት አለመሆኑ ሊሰመርበት እንደሚገባ የሚናገሩት አቶ አመሃ፣ አንድ ማህበረሰብ ላይ የሞራል ውድቀት እና የስነምግባር ብልሽት ካለ የተቀረው የሃይማኖትም ሆነ የፍትህ ተቋም ከዚህ ችግር ከገጠመው ማህበረሰብ ስለሚመነጭ የተሟሉ ተቋማትን መጠበቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት የሚመረጠው አካሄድ ሁለትዮሽ መሆን አለበት ብዬ ነው የማምነው። ሙስና አሁን የመጣ ቋንቋ ከመሆኑ ውጭ ስርቆት ማለት ነው። ስርቆት (ሌብነት) ደግሞ፣ በሁሉም እምነቶች የተወገዘና የተኮነነ ነው። ነገር ግን፣ ይኸው ችግር መልሶ በእምነት ተቋማት ውስጥም ጎልቶ የሚታይበት ሁኔታ አለ። የእምነት ተቋማት በአንድ በኩል ቤታቸውን በማጽዳት ራሳቸውን ምሳሌ በማድረግ መስራት አለባቸው። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ህዝብ በአብዛኛው በተለያዩ ቤተእምነቶች ውስጥ የሚሳተፍ ሃይማኖተኛ ነው ማለት ይቻላል። በክርስትናው በኩል በየበአላቱ የሚታየው ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ይታወቃል፤ እንደዚሁ በእስልምና በኩልም በሶላት ጊዜ የታየው ህዝብ ይታወቃል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ለመማር ተዘጋጅቶ የመጣን ህዘብ ማግኘት ትልቅ ዕድል ስለሆነ የሃይማኖት ተቋማት ሊጠቀሙበት ይገባል። አትስረቁ የሚል መልዕክት ከማስተላለፍ በዘለለ ቤተ እምነቶች ምሳሌ መሆን አለባቸው በማለት መክረዋል።

ሙስና ሊኖር የሚችለው ሰጪ ሲኖር ነው። ህብረተሰቡ ለምን በሙስና ውስጥ ይሳተፋል ብለን ስንጠይቅ የሚፈልገውን አገልግሎት በሚፈልገው ፍጥነትና ጥራት የማያገኝ በመሆኑ ነው። በዚህ ሁኔታ ማህበረሰቡ ላይ መፍረድ በጣም አስቸጋሪ ነው ነገር ግን፣ አንድ ትውልድ ተጎድቶም ቢሆን፣ ሙስናን የሚጠየፍ ማህበረሰብ መፍጠር መቻል አለብን። ዜጎች በተቻላቸው መጠን አገልግሎትን ከሙስና በጸዳ መንገድ ለማግኘት በየደረጃው የተዘረጉ የአቤቱታ መስመሮችን ተከትሎ በህጋዊ መንገድ ብቻ ለማግኘት ጥረት ማድረግ መቻል አለባቸው። የተቋቋመው ኮሚቴም ህብረተሰቡ አገልግሎት ለማግኘት በተቸገረ ጊዜ ወዲያውኑ አቤቱታ የሚያቀርብበትና መፍትሄ የሚያገኝበት ስርዓት መዘርጋት አለበት። ይሄ በሌለበት ሁኔታ ህብረተሰቡ ላይ የምንጥለው ኃላፊነት በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ አንድ ሰው የቀበሌ መታወቂያ ማግኘት በሆነ አጋጣሚ በጣም አንገብጋቢ ጉዳይ ሊሆንበት ይችላል። እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች ያ ሰው በአጭር ጊዜ ውስጥ መታወቂያ ሊያገኝ የሚችልበት መንገድ መዘርጋት አለበት። ምክንያቱም መታወቂያ ህክምናከማግኘት፣ ጉዞ ከማድረግ፣ ከባንክ አገልግሎት ጋር ይቆራኛል። ይህን ማድረግ የመንግስት ኃላፊነት ነው። አማራጭ ከሌለ ግን ያሰው መታወቂያውን ለማግኘት ያልተገባ መንገድ ለመሄድ ሊገፋፋና ሊደፋፈር ይችላል። ሲደመር አገልግሎት ሊሰጥ ከተመደበው ኃላፊ ስነ ምግባር ጋር ተያይዞ የሙስና ሂደት ውስጥ የመግባት ነገር ሊኖር ይችላል። ስለዚህ በመንግስት በኩል አገልግሎቶቹ የተፋጠኑ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉም ይመክራሉ።

ብሔራዊ የሙስና ኮሚቴው ታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ የወረደ አወቃቀር ሊበጅለት እንደሚገባ በመጠቆም የሙስና ተግባር ህብረተሰቡ ካልተሳተፈበት በአንድ አካል ብቻ የሚፈጸም አይደለም። ህብረተሰቡ ደግሞ፣ በአብዛኛው በሲቪክ ማህበራት የሚወክል ስለሆነ የተቋቋመው ኮሚቴ ማህበራቱ የሚጠበቅባቸውን ትልቅ ሚና እንዲጫወቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለበት። ሁለተኛ ሙስና በሁለት ደረጃዎች የሚፈጸም ነው። ከፍተኛ የገንዘብ መጠን የሚንቀሳቀስበትና በከፍተኛ የመንግስት የኃላፊነት ደረጃ ላይ ያሉ ባለስልጣናት የሚሳተፉበት ሙስና አለ። በሌላ በኩል የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ገትቶ ያለው በአነስተኛ ደረጃ ነገር ግን እጅግ በብዛት የሚፈጸመው ሙስና አለ። በዚህኛው የሙስና አይነት ላይ የሲቪክ ማህበራት ትልቅ ሚና ሊኖራቸው ስለሚገባ ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴምክራቲክ ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ እና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጸሃፊ ዶክተር ራሄል ባፌ በበኩላቸው መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ ለተንሰራፋው የሙስና ችግር እውቅና ሰጥቶ ለመታገል ውሳኔ ላይ ደርሶ ወደ ኮሚቴ ማቋቋም መሄዱ ጥሩ ነገር ነው። ሙስና የአገሪቱ ባህል እስኪመስል ስራ ተደርጎ የተወሰደበት ደረጃ ላይ ነው ያለው። በየደረጃው ያሉ የመንግስት ባለስልጣናትና ኃላፊዎች ከህዝብ በሚሰበሰብ ቀረጥ ደመወዝ እየተከፈላቸው ከስራ ማስኬጃው ባለፈ ተጨማሪ ክፍያ በመጠየቅ ህዝብ መብቱን በድጋሚ ክፍያ እንዲገዛ እያደረጉ ነው። ራሱን የቻለ ዘርፎች የመበልጸጊያ የስራ መስክ ተደርጎ ተወስዶ በአገር ደረጃ ከዳር እስከ ዳር እየተሄደበት ስለሆነ ትልቅ ቁርጠኝነትን እና የህዝብን ምላሽ ጭምር የሚጠይቅ ነው በማለት እርምጃውን በበጎ እንደሚመለከቱት ይገልጻሉ።

ዶክተር ራሄል፣ እንደሚናገሩት የአገልግሎት አሰጣጡ ሙስና የነገሰበት በመሆኑ ስርዓቱን መፈተሽና መሰረታዊ ምንጩን በማግኘት መሰረታዊ ለውጥ ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ እንዲሁ በቀላሉ የሚቆም አይደለም። በጣም ስር የሰደደ ችግር በመሆኑ መሰል ኃላፊነቶችን መወጣት የሚችል በአንጻራዊነትም ቢሆን፣ ነጻ የሆነ አካል አለ ወይ ብለን ለመጠየቅ እስክንገደድ ድረስ የደረሰበት ጉዳይ ስለሆነ ትልቅ ቁርጠኝነትን የሚጠይ ነገር ነው። ትግሉ ከአናት ጀምሮ እስከታች ድረስ የሚደርስ ስለሆነ ከራስ ጀምሮ በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስን ግድ የሚል ነው። የቦታው መጠን የሙስናውን መጠን ይወስናል እንጂ ሙስና ውስጥ የሚሳተፈው አካል ብዙ ነው።

ሙስናን መታገል የመንግስትን፣ የህዝብን፣ የሃይማኖት ተቋማትን እና የሌሎችንም አካላት ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው የሚሉት ፖለቲከኛዋ፣ እንደ አገር ትልቅ መፍትሄ ሊፈለግለት የሚገባ ጉዳይ ነው። አሁን ጉቦ እየተሰጠ ያለው ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሳይሆን የተገባውንም መብት ለማስከበር ነው። መንግስት አሁን በጀመረው ልክ ቁርጠኛነቱን ካሳየና ሙስና ላይ የተጀመረው ትግል ፕሮፓጋንዳና ንግግር ብቻ ከመሆን አልፎ የእውነት ከሆነ በእርግጠኝነት ህዝብ ይተባበራል። መንግስት አቋሙ እርግጠኛ መሆኑን የሚያመላክቱ ማሳያ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅበታል። መንግስት አቋሙን በተግባር ከገለፀ ህዝቡ መኖር የማይችልበት ደረጃ ላይ ስለደረሰ አመኔታ አድሮበት ትብብር እንደሚያደርግ በእርግጠኝነት መናገር እንደሚችሉ ይገልጻሉ።

አያይዘውም፣ የተቋቋመው ኮሚቴ ገለልተኛ አቋም ይዞ ራሱንም ጭምር ቢሆን እያየ ለመሄድ የቆረጠ መሆን አለበት። አሁን ሙስና የድብብቆሽ ጨዋታ መሆኑ ቀርቶ በአደባባይ የሚፈጸም ግልጽ ጉዳይ ሆኗል። ስለዚህ የሚዘለል አካል ካለ፤ ከፍተኛ ኃላፊዎችን እየተወ የበታቾቹን ብቻ የሚያጠቃ ከሆነ፤ በዘር የሚሄድ ከሆነ እና በፖለቲካ ወገንተኝነት የሚሄድ ከሆነ ህዝብ ሁኔታውን ተመልክቶ ከመፍትሄው እንዲሸሽ ያደርገዋል። ስለዚህ ኮሚቴው በስፋት ወደ ስራ እየገባ ሲሄድ እንደ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ራሱን በተቻለ መጠን ገለልተኛ አድርጎ ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ከመሪ ጀምሮ ታች እስከሚገኘው ነዋሪ ድረስ በእኩል ደረጃ የህግ የበላይነትን የሚያስከብርበት አካሄድ መከተል አለበት።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የህዝቡና የመንግስት አካል ናቸው። የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ብልጽግና ፓርቲንም አቅፎ ነው ያለው። እውነት ነው ትግሉ ከፓርቲዎች መጀመር አለበት። በገዢው ፓርቲ ውስጥና በሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ያሉት አባላትም ሆኑ መሪዎች ምሳሌ መሆን መቻል አለባቸው። ሙስና እንደ አገር የጎዳን እና ከድህነት ወደ ባሰ ድህነት ያደረሰን ነገር ስለሆነ በጋራ ምክር ቤቱ ትኩረት ሰጥተን የምናየው ነገር ነው። ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ሌብነት ስራ እንደሆነ እና እስካልተያዘ ድረስ ሰው እየሰረቀ ቶሎ የሀብት ማማ ላይ መድረስ እንዳለበት እየመከርን እና በተግባርም ደግሞ ከመሪዎች ጀምሮ እስከበታች ሰራተኛ ድረስ እየፈጸምን ነው የመጣነው። በጉቦ መንገድ ካልመጣ እውቀትን እንኳን ማውረድና ማስረጽ የማንችልበት ደረጃ ደርሰናል። ለኢትዮጵያ እንደ አገር ይሄ በጣም ከባድ ነው። ነገር ግን፣ የግድ አንድ ቦታ ላይ ትግሉ መጀመር ስላለበት ነው አሁን እየተጀመረ ያለው። አንድን ነገር መካብ ነው የሚከብደው ማፍረስ ቀላል ነው ሲሉ የተጀመረው እንቅስቃሴ ወደ ኋላ መመለስ እንደሌለበት አስረግጠው ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሃይማኖተኛ ያልሆነ ዜጋ በጣም ጥቂት ነው። የሃይማኖት ተቋማት በንጽህና ችግሩን ለመቅረፍ ሰርተው ቢሆን ኖሮ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ባልተገኘ እና የመንግስት ስርዓትም እንደዚህ ባልደረሰ ነበር። የሃይማኖት ተቋማት በሙስና ውስጥ የሚኖሩ ናቸው ሲሉ የሚወቅሱት ዶክተር ራሔል፣ በህይወት እና ሞት መሃል ባለ ጉዳይ እንኳን ገንዘብ ማግኘትን እንዲያስቀድሙ አድርገን የትውልድን አእምሮ አበላሽተን ነው የቀረጽነው። የትውልዱን አእምሮ ለመለወጥ በጣም ልንተጋና ቆርጠን ልንነሳ ይገባል። የሃይማኖት መሪዎች ደግሞ በተቻለ መጠን በትክክል ማስተማርና መተግበር ካሳዩና ከዘረኝነት፣ ፖለቲካ እና ሌብነት ከወጡ ዋጋ ቢያስከፍለንምና ሂደትን ቢጠይቅም በእርግጠኝነት እየቀረፍነው እንሄዳለን። ወላጆችም ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስተማር አንደበት የላቸውም። ልጆቻቸው ከደሞዛቸው በላይ እንደሚያኖሯቸው ያውቃሉ። ወላጆችም ለልጆቻቸው አርአያ መሆን ይገባቸዋል። በተጨማሪ፣ በማስረጃ በትክክል የተያዘ ሰው አስተማሪ የሆነ እርምጃ የሚወሰድበት ከሆነ ሌሎችን ያስተምራል ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ አስተማሪ እርምጃዎችን በህግ አግባብ መውሰድ ያስፈልጋል ሲሉ ይመክራሉ።

መንግሥት አገርን የሚበላ ነቀዝ እና የአገርን አንጡራ ሀብት እየቦረቦረ ጥሪቷን ባዶ ለማስቀረት ሌት ተቀን የሚማስን ተባይ ሲል በገለፀው ሙስና ላይ በጸጥታው ዘርፍ እንዳደረገው ሁሉ ጠንካራና የማያዳግም ኦፕሬሽን ማድረግ እንዳለበት ጥናቶችንና የሕዝብ ውይይት ግምገማዎችን መሰረት በማድረግ አቋም መያዙን ገልጿል። በአንድ በኩል የመንግሥት ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና አሠራሮች ለሙስና ያላቸውን ተጋላጭነት የማጥፋት ሥራ እየተሰራ በሌላ በኩል ደግሞ የሙስና ተዋንያንን የማጋለጥና በሕግ የመጠየቅ ተግባር እንደሚከውንም አስታውቋል። የዘመን መጽሔት ዝግጅት ክፍልም ዜጎች ሙስናን ለመታገል የሚያደርጉትን ጥረት ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክረው በመቀጠል ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴው የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲደግፉ ጥሪውን ያቀርባል።

ተስፋ ፈሩ

Recommended For You