የጥር ወር የዘመን መጽሔት ዐቢይ ርዕስ ዓምድ እንግዳችን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ናቸው። ዘመን መጽሔት ከዋና ኮሚሽነሩ ጋር ባደረገችው ቆይታ ከተቋቋመ ዘጠኝ ወራት ያስቆጠረው ኮሚሽን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ያከናወናቸውን ዓበይት ተግባራት፣ ያጋጠሙትን ችግሮች፣ ቀጣይ ሥራዎቹን፣ ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት ከተለያዩ አካላት ጋር እያደረገ ያለውን ግንኙነት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄዎች አንስታለች፣ መልካም ቆይታ።
ዘመን፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፣ በቅድሚያ ከዘመን መጽሔት ጋር ቆይታ ለማድረግ ስለፈቀዱ በዝግጅት ክፍላችን ስም ምስጋና አቀርባለሁ።
ፕሮፌሰር መስፍን፡- እኔም እናንተ ወደ ኮሚሽናችን ጽሕፈት ቤት ስለመጣችሁ አመሰግናለሁ።
ዘመን፡- ሀገራዊ ምክክር ከሚያልፍባቸው ቅድመ ዝግጅት ፣ ዝግጅት፣ ምክክር እና ትግበራ ከሚባሉት አራት ሂደቶች ሁለቱ ደረጃዎች ተጠናቀው ወደ ሦስተኛው ለመሸጋገር ጫፍ የተደረሰበት ጊዜ ላይ ነን። ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ያከናወናቸው ዐበይት ተግባራት ምንድን ናቸው?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- እንዳልከው የዚህ ሀገራዊ ምክክሩ የሥራ ሂደት አራት ደረጃዎች አሉት። የመጀመሪያው የቅድመ ዝግጅት የምንለው ነበር። በቅድመ ዝግጅት ወቅት አዲስ ተቋም እንደመሆናችን መጠን ቢሯችንን በሰው ኃይል ማደራጀት ነበረብን። ምክክሩን ለማሳለጥ የተመረጥነው 11 ኮሚሽነሮች ከተለያየ ቦታ ነው የመጣነው። የምክክርን ጽንሰ ሀሳብ በሚገባ ተረድተን አንድ ወለል ላይ እንድንሆን የማስቻል ራሱን የቻለ ሥራ ነበር። ከዚያ ጋር ደግሞ ሀገራዊ ምክክሩ የተቋቋመበትን አዋጅ ዓላማና ተግባራትን እንዲሁም ያሉትን 33 ገደማ አንቀጾች በሚገባ መረዳት ተያያዥ ጉዳይ ነው። ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር የሚሠሩ ብዙ ተቋማት አሉ፣ እነዚህን ተቋማት የመለየትና ራሳችንን እና ሥራችንን የማስተዋወቅ ሥራ ሠርተናል። በዚህ ረገድ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፤ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የአካል ጉዳተኛ ማኅበራት፣ የሴቶች ማኅበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም እዚህ ሀገር ያሉትን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተወካይ አምባሳደሮችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን የሚመሩ ኃላፊዎች የመሳሰሉትንሁሉ አግኝተናል። በዚህ ቅድመ ዝግጅት ወቅት በተለያዩ ሀገሮች የተካሄዱ ውይይቶች ምን ያህሉ ተሳካላቸው፤ ምን ያህሉ ደግሞ ከሸፉ፤ እንዴት ተዋጣላቸው እንዲሁም ለምን ከሸፉ የሚለውን መጽሐፍቶችንና መጣጥፎችን በማሰባሰብ ስንፈትሽ ነበር። በሀገራችን በዚህ ግዝፈት ደረጃ በአዋጅ ተቋቁሞ የምክክር ሥራ ሲሠራ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሆኑ በቅድመ ዝግጅት ጊዜ ውስጥ ብዙ የሠራናቸው ሥራዎች ነበሩ። በተጨማሪም አዋጁን በመንተራስ ለሥራዎቻችን የሚሆኑ የኮሚሽነሮችና የጽሕፈት ቤት የሥነ ምግባር መመሪያዎችን እና የተለያዩ ድንጋጌዎችን አዘጋጅተናል።
ከቅድመ ዝግጀት ተቀጥላው ወደ ሆነው ዝግጅት ስንመጣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማግኘት ወደፊት ምን አይነት ሥራዎችን በጋራ መሥራት እንደምንችል በተለያዩ ጊዜዎች በመወያየት ከአንዳንዶቹ ጋር የስምምነት ማዕቀፍ መፈራረም ደረጃ ደርሰናል። የሦስት ዓመት ስልታዊ (ስትራቴጂ) ዕቅዳችን ተነድፎ ውይይት ተደርጎበት ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ጸድቆ ወደ ሥራ ገብተንበታል። የ2015 ዓ.ም. የበጀት መርሐ ግብራችንን አውጥተን አጸድቀን በዚያ መሠረት እየሄድን ነው ያለነው። በእነዚህ ሁሉ የሥራ ሂደቶች ውስጥ የሰው ኃይል ስለሚያስፈልግ በአሁኑ ሰዓት በፊት ከሁለቱ ኮሚሽኖች የተረከብናቸውን ሠራተኞች መደበኛ አድርገን ከወጭ ባገኘነው እርዳታ ከፍተኛ እውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች ቀጥረን ሥራ ለማስጀመር በመንደርደር ላይ ነን። ምናልባት በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ የቀጠርናቸው 17 ከፍተኛ ባለሙያዎች ሥራ ይጀምራሉ። በዚህ በዝግጅት ምዕራፍ ውስጥ ከሄድንባቸው ዋና ዋና ዓበይት ጉዳዮች አንዱ አስራ አንዳችንም ኮሚሽነሮች በዘርፍ በዘርፍ ተከፋፍለን ሥራ እንድንሠራ ማድረግ ነው።
ዘርፎቹ አራት ናቸው። አንዱ የሚዲያ ኮሙኒኬሽን እና አጋርነት ዘርፍ ነው። ብዙ ጊዜ ኮሙኒኬሽን ተግባቦት ይባላል። ነገር ግን በኮሙኒኬሽን ተግባቦት ብቻ አይደለም ያለው የዛ ተቃራኒም እዛው ኮሙዩኒኬሽን ውስጥ ስላለ ዘርፉ አለን። ሁለተኛ የሥርዓት ድንጋጌና የስልጠና ዘርፍ አለን። ሦስተኛ የውይይት /ዲያሎግ/ የምንለው ዘርፍ አለ። እንዲሁም የአመራር ዘርፍም አለን። እነዚህ አራት ዘርፎች በተለያዩ ኮሚሽነሮች ነው የሚመሩት። የሚዲያ ኮሙኒኬሽን እና አጋርነት ዘርፉ በአራት ኮሚሽነሮች ሲመራ ሁለቱ በሦስት ሦስት ኮሚሽነሮች ይመራሉ። የአመራሩ ደግሞ በእኔ እና በምክትል ኮሚሽነሯ ይመራል። በዚህ መንገድ የየራሳችንን ሥራዎች ተከፋፍለን ሂደቱን በየጊዜው እያስገመገምን ነው በዚህ በዝግጅት ወቅት በመሥራት ላይ ያለነው።
የኮሚሽኑ አወቃቀር አስራ አንዱም ኮሚሽነሮች አባላት የሆኑበትና ዋና ኮሚሽነሩ የሚሰበስቡት ካውንስል አለው። በዚያ ስር ደግሞ ዋና ኮሚሽነር፣ ምክትል ዋና ኮሚሽነር እና ጽሕፈት ቤቶች አሉ። ስለዚህ የሚሰበሰበው አጀንዳ አንድ ሺህም ይሁን አንድ ሚሊዮን ወደዚህ ምክር ቤት ይመጣና እጅግ መሠረታዊ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ተለቅመው ወጥተው ወደ ሀገራዊ ውይይት ይቀርባሉ።
ዘመን፡- በሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲወከል የዜጎች ተሳትፎ በገዢው ፓርቲ የመጠለፍ ዕድል ባላቸው ነባር መዋቅሮች ብቻ የተገደበ እንዳይሆን በሚል ስጋታቸውን የሚገልጹ ወገኖች አሉ። የተሳታፊዎች መረጣው በምን መልኩ እየተከወነ ነው?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- አጀንዳ የሚሰበሰበው ከሕዝብ ነው ብዬሃለሁ። ሕዝብ ያለው ወረዳና ቀበሌ ውስጥ ነው። የትኛው ሕዝብ ስንል አዋጁ አሳታፊ በሆነ መልኩ ማንንም ወደኋላ ሳይተው ይላል። ኢትዮጵያ 86 እና 87 ወይም ከዚያም በላይና በታች ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ብሔሮች ያሉባት ሀገር ነች። ስለዚህ እያንዳንዱ ወገናችን መወከል አለበት። በብሔር ብሔረሰብ እና በሕዝቦች መወከል ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ደግሞ ይኖራሉ። በእነዚህ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የአካልና አዕምሮ ጉዳተኞች እንዲሁም እጅግ በጣም የተረሱ ሩቅ ያሉ ሕዝቦቻችን አሉ። ብዙ ጊዜ እንዲህ አይነት ነገር ሲካሄድ ከማዕከል ወይም ከላይ ነው የሚጀምረው። ለምሳሌ ሕገ መንግሥት ሲረቀቅ ካለቀለት በኋላ ወደ ሕዝብ ይወርዳል። ሕዝብ ተወያየበት ይባልና ተወያየም ምንም አለም አላለም ሕገ መንግሥቱ ይጸድቃል። በእኛ ሂደት ግን ዋናው የዚህ ውይይት ባለቤት ሕዝባችን ነው። ስለዚህ አጀንዳውን ራሱ ማምጣት አለበት። አርሶ አደር፣ አርብቶ አደር፣ ቅጠል ሻጭ ወይም ሸማኔ ሳይባል ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ስለሀገሩ የመናገር የመወያየትና የመወሰን ኃላፊነት አለበት።
በዚህ መሠረት ስናደርግ የከረምነው በየክልሎች እየሄድን ከአካባቢ መንግሥታት መስተዳድሮችና ካቢኔዎቻቸው ጋር መነጋገር ብቻ ሳይሆን በየአካባቢው ያሉትን የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ሌሎችንም በመንግሥታዊ መዋቅር ውስጥና ውጪ ያሉትን የኅብረተሰብ ክፍሎች ማግኘት ጭምር ነው። ብዙ ጊዜ በመንግሥታዊ መዋቅር ሲኬድ ከመንግሥታዊ መዋቅር ውጪ ያሉት ይረሳሉ። በመንግሥታዊ መዋቅር ብቻ ከሆነ የምንሄደው ገዢውን ፓርቲ ብቻ የሚያውቁና የመንግሥትን አጀንዳ ይዘው የሚሄዱ ብቻ ሊሆኑብን ይችላሉ። ከመንግሥት መዋቅር ውጭስ ያሉትስ ? እነሱም ኢትዮጵያውያን ናቸው። እነሱም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የመናገርና በዕጣ ፈንታዋ ላይ የመወሰን መብት አላቸው።
ብዙ ጊዜ ውይይት የሚመስል ነገር ስናካሂድ የምንሰባሰበው ፊደል የቆጠርን ነን። ምሑራን ተሰባሰቡ፤ ልሂቃን ተሰባሰቡ፤ ሀሳብ አፍላቂዎች እንዲህ አደረጉ የሚል ቋንቋ ሁሉ አለን። እኔ የአዕምሮ ሐኪም ነኝ፣ በተፈጥሮ የሰው ልጅ አዕምሮ የተስተካከለ እስከሆነ ድረስ ሀሳብ ያፈልቃል። እኛ ሰዎች የምንለየው እሳቤና እይታችን ከሌሎቹ እንስሳት የላቀ በመሆኑና ንቃተ ሕሊና /ኮንሺየስነስ/ የሚለው እሳቤ ያለን ብቸኛ ፍጡሮች በመሆናችን ነው። ስለዚህ ሁላችንም እናስባለን። ልዩነቱ አንተ በተሻለ አንደበት ወይም በተባ ብዕርህ ታወጣዋለህ እኔ በጎለደፈ አንደበት እለዋለሁ ወይም ላወጣው አልችልም። ከዚህ በስተቀር አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ ሀሳብ አለው። አንዳንድ ጊዜ በትምክት የምንናገራቸው ነገሮች አሉ። አርብቶ አደርና አርሶ አደር ከአስተዳደር ጥያቄ ውጭ ምን ጥያቄ ይኖሯቸዋል ይባላል። ይሄ ትክክል አይደለም። አርብቶ አደሮችና አርሶ አደሮች ናቸው ብዙ ሺህ ዓመታት አኑረው እዚህ ያደረሱን። ስለዚህ ሁላችንም ሀሳብ እናፈልቃለን። ሁላችንም ሀሳብ እስካፈለቅን ድረስ ደግሞ ሁላችንም ተሰሚ መሆን አለብን። ብሔረሰብ እንኳን ብለን የማንጠራቸው ሕገ መንግሥቱ ሕዝቦች የሚላቸው፤ እኔ ብሔር ነው የምላቸው፣ እነኚያ ጠረፍ ላይ ያሉ የተረሱና የተገፉ ትንንሽ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ ስለ ሀገራቸው መናገር መቻል አለባቸው፤ ድምጽ ሊኖራቸው ይገባል። ያንን ስናደርግ ነው አንተ የእንደዚህ አይነት ልጅ እኔ የእንደዚህ አይነት ልጅ ተባብለን ሳንገፋፋ የምንኖረው።
ዘመን፡- አጀንዳ የምትሰበስቡት እንዴት ባለ መንገድ ነው ?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- ዋናዎቹ ተዋንያን ሕዝቦች ስለሆኑ አጀንዳ አሰባሰባችን ከታችወደላይ ነው። አጀንዳ ከሕዝብ ተሰብስቦ ወደ ኮሚሽኑ ምክር ቤት ይመጣል። ይሄ ማለት ግን ከታች ወደ ጎን አንሄድም ማለት አይደለም። የክልል ፓርቲዎች እንዳሉ ሁሉ በፌዴራል ደረጃ የተደራጁ ፓርቲዎች ይኖራሉ። የክልል የተለያዩ የሲቪል ማኅበራት እንዳሉ ሁሉ በሀገር ደረጃ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህኅበራት ኮንፌደሬሽን አለ። ስለዚህ በሀገር ደረጃ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌደሬሽን ምንድን ነው ማቅረብ የሚፈልገው አጀንዳ የሚለውን እናያለን ምክንያቱም በአካባቢ ደረጃና በሀገር ደረጃ የሚነሱ አጀንዳዎች ሊለያዩ ይችላሉ።
በሀገራችን በአሁኑ ሰዓት 11 ክልሎች አሉ፤ የክልሎች ቁጥር እየጨመረ ነው። በተጨማሪም ሁለት ትልልቅ ከተማዎች አሉ። አዲስ አበባ 11 ክፍለ ከተሞች አሉ፣ በዚያ ውስጥ ደግሞ 125 ወረዳዎች አሉ። እነዚህ ሁሉ ይካተታሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ 1 ሺህ 300 ገደማ ወረዳዎች ስላሉ ሁሉም ይካተታሉ። ነገር ግን 1 ሺህ 300 ወረዳዎች እንሂድ ካልንና እያንዳንዱን ቀበሌና ጎጥ እናሳትፍ ካልን ምናልባት 10 እና 15 ዓመታት ሊፈጅብን ይችላል።
1 ሺህ 300 ወረዳዎች ብንሄድ ከፍተኛ የሰው ኃይልና ብዙ ገንዘብ ይጠይቀናል። እኛ ደግሞ ድሆች ነን። ስለዚህ ባነሰ ዋጋ በተቻለ መጠን ሁሉንም ሕዝባችንን ተደራሽ መሆን እንዳለብን ስለምናምን 1 ሺህ 300 ወረዳዎቹን እያመቻቸን እያጣመርን ክላስተር እያደረግን ጨርሰናል። የቀረን የመጨረሻው አዲስ አበባ ነው። የአዲስ አበባን አመራርና እስከታች ድረስ ያለውን ሕዝባችንን ከጥምቀት ማግስት ጀምሮ እናገኛለን ያንን ከጨረስን በኋላ ሁኔታዎቹ በተመቻቹባቸው ቦታዎች ላይ አጀንዳዎችን መሰብሰብ እንጀምራለን። ተስፋ የምናደርገው በድሬዳዋ እና በሐረር እንጀምራለን ብለን ነው፣ ወዲያው ደግሞ ሶማሌ እንቀጥላለን እንዲያ እያልን እንሄዳለን።
በጎንዮሽ ሂደት ውስጥ ከሕዝቦቻችን ጋር በውጭ ሀገራት የሚኖሩት በተለምዶ ትውልደ ኢትዮጵያውያን (ዲያስፖራ) በመባል የሚታወቁት ወገኖቻችን ይካተታሉ። ከሀገራችን ውጭ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ። ለእነኚያ ኢትዮጵያውያንም ኢትዮጵያ ሀገራቸው ነች። እነሱም የሀገራቸው ዕጣ ፈንታ ይመለከታቸዋል። ስለሚመለከታቸው ነው በስደት ውስጥ ሆነው መከራቸውን እያዩ በሚያጠራቅሙት ገንዘብ በቀጥታ በኢትዮጵያ ልማት የሚሳተፉት። ወገኖቻቸውን ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ወደ ሀገራቸው የሚልኩት ገንዘብም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለሀገር ልማት የሚውል ነው። ስለዚህ እነሱንም ማቅረብና አጀንዳቸውን ሰብስቦ ለውይይት ማቅረብና በውይይቱ እንዲሳተፉ ማድረግ ተገቢ ስራ ነው።
አጀንዳዎችን ስንሰበስብ በጣም ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ ግን ተመርጠው ተመርጠው መጨረሻው ላይ ጥቂት ይሆናሉ። ይሄ እንዳለ ሆኖ ከየአካባቢው ከታች የመጡት አጀንዳዎች ይጣላሉ ማለት አይደለም። በየአካባቢያቸው ችግራቸውን ለመፍታት የሚወያዩባቸው ይሆናሉ። ለምሳሌ አንዳንዶቹ በዚያው በሁለት ወረዳዎች መሐል ፤ ሌሎቹ ደግሞ በሁለት ዞኖች መሐል ፤ የተቀሩት ደግሞ በሁለት ክልሎች መሐል የሚፈቱና ወደ ፌዴራል የማያመጧቸው ሊሆኑ ይችላሉ። በየወረዳው ሕዝብ የመረጣቸው ተወካዮች ተሰባስበው ወደ ዞን ይመጡና ከታች ይዘዋቸው የመጡትን አጀንዳዎች እያሰባሰቡ በክልል ላይ መርጠው የመጨረሻውን ወደ ምክር ቤታችን ይላካሉ ማለት ነው።
ይሄ ሁሉ ሂደት በዝግጅት ምዕራፉ የሚጠናቀቅ ነው። የዝግጅት ምዕራፉ አለቀ የምንለው አጀንዳዎቹ ተሰብስበው ለምክር ቤታችን ሲቀርቡና ምክር ቤታችን ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሕዝብ ተወካዮች ባሉበት አጀንዳዎቹን አጣርቶ በመምረጥ የኢትዮጵያ ሀገራዊ አጀንዳዎች እነዚህ ናቸው ብሎ ለሕዝብ ሲያሳውቅ ነው። ይሄ ሂደት ሁሉ ወደፊት ለሕዝብ ግልጽ የሚሆን ነው። በማኅበራዊ እና በዋና መገናኛ ብዙኃን /ሜንስትሪሚንግ ሚዲያዎች/ ለሕዝብ ቀርቦ እንዲተች የሚደረግ ይሆናል። በተጨማሪም እነኚህ አጀንዳዎች በፖስታ፣ በስልክ ወይም ደግሞ በሌሎች አማራጮች ለሕዝብ ሊቀርቡ ይችላሉ።
ዘመን፡- አጀንዳዎች ከተመረጡ በኋላ በተቀሩት ምዕራፎች በሚቀጥለው ሂደት የምትሠሯቸው ሥራዎች ምን ይሆናሉ ?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- አጀንዳዎችከተመረጡ በኋላ የሚቀጥለው ምዕራፍ የሚሆነው የውይይቱ ሂደት ነው። አጀንዳ መሰብሰብ ምናልባት ጥቂት ቀናት የሚወስድ ሥራ ሊሆን ይችላል። ውይይቱ ግን ሰፋ ያለ ጊዜ የሚወስድና በደምብ የሚካሄድ ነው። በውይይት ሂደት ውስጥ ሦስት ተዋንያን አሉ። የመጀመሪያዎቹ ተዋንያኖች ሕዝብና የተደራጁ ተቋማት ናቸው። ሁለተኛዎቹ አወያዮች ናቸው። ውይይት ማለት ክርክር አይደለም። በክርክር አሸናፊና ተሸናፊ አለ፣ በውይይት ግን አሸናፊ ብቻ ነው የሚኖረው። እኔና አንተ ወደ ውይይት ስንመጣ መጀመሪያ አዕምሯችን ውስጥ የሚመጣው ሰላም ነው። ቁጭ ብለን ስንወያይ ግን ሥርዓት ባለው መንገድ መወያየት መቻል አለብን። ምክንያቱም መሐላችን ለግጭት የዳረጉን ብዙ ነገሮች ስላሉና እኔም አንተም የለመድነው ጉልበትና ማሸነፍን ስለሆነ አወያይ ያስፈልገናል። ያ አወያያችን አንተንም እኔንም በእኩል የሚያይ ገለልተኛ እና እውቀት ያለው መሆን አለበት። በውይይታችን መሐል የድሮ ባሕሪያችን መጥቶ አንዳችን ጉልበተኛ ብንሆን አወያያችን ያቀዘቅዘናል እየበረድን ውይይታችንን እንቀጥላለን። ስለዚህ በእኔና በአንተ መካከል የሚንሸራሸሩት ሀሳቦች ይሆናሉ።
መጨረሻ ላይ ስናየው እኔም አንተም የአንድ እናት ልጆች ነን ዝም ብለን ነው መከራችንን ስናይ የከረምነው ብለን ውስጣችን ያለውን መርዝ ካወጣን በኋላ እርቅ እንፈጽማለን። እኔና አንተ እርቅ ስንፈጽም የአንተም ልጆችና ቤተሰቦች አብረው ካንተ ጋር ያቄሙ ሁሉ፣ አብረው ከእኔ ጋር ያቄሙ ሁሉ በነገሩ ያምኑበትና በጋራ ወደፊት እንቀጥላለን። አንተ ከበደልከኝ ለካ ይሄ ሁሉ ነገር ደርሷል ብለህ አንተም ጋር ጸጸት ይመጣል እኔም ጋር ጸጸት ይመጣል፣ ስለዚህ እርቃችን የተሟላ ይሆናል። አንተ አቅም ካለህ እኔን ትክሰኛለህ፤ እኔ የተሻልኩ ከሆንኩ ተበዳይ እንኳን ብሆን አንተን አግዝሃለሁ። ውይይት የሚባለው ይሄ ነው።
በውይይቱ መጠናቀቂያ ላይ የተግባባንባቸውም ሆኑ ያልተግባባንባቸው ነጥቦች በደምብ ይሰበሰቡና ተቀምረው ወደ ትግበራ ይላካሉ። የሚተገብረው አካል ማን ነው ? ብዙ ጊዜ መንግሥት ነው። ስለ ሕገ መንግሥት ከሆነ ሕግ አውጪው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። የፍትሕ መጓደል ከሆነ ደግሞ ሕግ አስከባሪው ወይም ሕግ ተርጓሚው ነው። ለዚህ ሕዝብ የሰጠው ሀሳብ ተሰንዶ ወደ ሚመለከታቸው አካላት ይላካል። እስከዚህ ድረስ አዋጁ መብት ይሰጠናል። እንዲተገብር የላክንለት ፈጻሚው አካል የሚፈጽም ከሆነ ይኸው ፈጽሟል ብለን ለሕዝባችን እናሳውቃለን። ፈጻሚው አካል አልፈጽምም ካለም አልፈጽምም ብሏል ብለን ለሕዝባችን እናሳውቃለን። ያን ጊዜ የትግበራና የክትትል ምዕራፍ ሥራችን ይጠናቀቃል ማለት ነው።
ዘመን፡- ሥራችሁን የምታከናውኑት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚመደብላችሁ በጀት ብቻ ነው ወይስ ከሌሎች አካላት የምታገኙት እገዛ አለ ?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- መንግሥት አዋጅ አስቀምጧል። እኔ ጣልቃ አልገባባችሁም ሥራችሁን የምትሠሩበት ሕንጻ ሰጥቼያችኋለሁ፤ የሚያስፈልገውን ነገር አቀርባለሁ፤ የምትጠይቁትን በጀት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርባችሁ ማስፈቀድ ትችላላችሁ ባለው መሠረት እንዲሁም እኛ በቀጥታ ተጠሪነታችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለሆነ የሚያስፈልገንን በጀት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበን አጸድቀናል። አብዛኛው ሥራ 2015 ላይ የሚከናወን ነው ብለን ስላሰብን ወደ ሦስት ቢሊዮን ብር ገደማ ነበር የጠየቅነው። ይህን ገንዘብ እንደ ድህነታችን እንደጊዜው ሁኔታ በጥንቃቄ የተወሰነ ገንዘብ ከገንዘብ ሚኒስቴር እየወሰደን በመጠቀም ላይ ነን።
ሥራችንን እንደጀመርን ብዙ የውጭ ድርጅቶች ገንዘብ እንርዳችሁና ኤክስፐርት እንስጣችሁ አይነት ጥያቄዎች አቅርበውልን ነበር፣ አይሆንም ነው ያልነው። ይሄ ኢትዮጵያዊ ፕሮግራም ስለሆነ ከሀገራችን በምናገኘው በጀት መወሰን መቻል አለብን። ገንዘብም ከፈለግን ከሀገራችን ውስጥ ማግኘት አለብን። እናንተ ገንዘብ የምትሰጡንም ከሆነ ቋት ገንዘብ ሚኒስቴርውስጥ አስቀምጠንላችኋል እዚያ ክተቱ በገንዘብ ሚኒስቴር ሕግና ደምብ መሠረት ከዚያ እያወጣን እንጠቀምበታለን እንጂ ገንዘብ ወደ እኛ ቤት መምጣት አይገባውም ብለን ነው ለፈረንጆቹ የነገርናቸው። ምክንያቱም ፈረንጆቹ እጆቻቸው በጣም የረዘሙ ናቸው። የረዘሙ እጆቻቸው ምን እንደሚሠሩ አስተውለናል።
በተለየ ሁኔታ ግን የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ላለፈው ዓመት ወደ 80 ሚሊዮን ብር ገደማ መድቦልን ለሥራችን የሚያስፈልጉንን መኪኖች፣ ኮምፒዩተሮችና የመሳሰሉትን ነገሮች ገዝተን የእኛን የገንዘብ ሚኒስቴርን በጀት ሳንጠቀም እዚህ ደርሰናል። ወደፊትም እናግዛችሁ የሚሉን ዓለም አቀፍ ተቋማት ካሉ በዚህ መሠረት ብቻ ነው የምንቀበለው። ይሄ ሁሉ ጥንቃቄ የእኛን ተዓማኒነት እና ገለልተኝነት መጠበቅ ስላለብን ነው።
ዘመን፡- ኮሚሽኑ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ምን አይነት ትምህርት ወስዷል ?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- ባነበብናቸውና ባደረግናቸው ጥናቶች ብዙ ሀገሮች ውስጥ ውይይቶች ተካሂደዋል። የእኛ ግን ለየት ይላል። ለየት የሚልበት ምክንያት በተለያዩ ሀገራት የተደረጉት ውይይቶች በዓላማ የተደረጉ ናቸው። ዓላማ ምን ማለት ነው ለምሳሌ ኬንያ ውስጥ ምርጫ ተካሄደና በምርጫው ውጤት ባለመስማማት ብዙ ሕዝብ አለቀ። ስለዚህ ምን እናድርግ በሚል አጀንዳ ከላይ ወረደና በዚያ ላይ ተወያዩ። አጀንዳው ከላይ ከመውረዱ በተጨማሪ አወያያቸው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስር ይሠሩ የነበሩት ኮፊ አናን ስለነበሩ ውይይቱ የተመራው በጉልበተኛ ነው። እንደዚህ ዓይነት ውይይት የውጭ ተጽዕኖ ያለበት ነው። የውጭ ተጽእኖ ያለው ውይይት ደግሞ ዕድሜ አይኖረውም።
የሀገር ውስጥ ጉልበተኛ ተፅዕኖ ያለበት ውይይትም ወደ አሸናፊነት ብቻ የሚሄድ በመሆኑ ዕድሜ አይኖረውም። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በሱዳን ውስጥ የተካሄደው ውይይት ነው። አጀንዳዎች ተቀረጹ ሕዝቦች ተሰባሰቡ ውይይቶች ተጀመሩና በመሐሉ በወቅቱ የነበሩት ፕሬዚዳንት እጃቸው ረዝሞ ስለገቡበት ውይይቱ ከሸፈ። የመን ብዙ ዓመት ጦርነት ላይ ከቆየች በኋላ ውይይት እናድርግ ብለው ሴቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎችም የተሳትፉበት በጣም ጥሩ የሚባል አካሄድ ተከትለው ነበር። የገልፍ ሀገሮች እጃቸውን አስረዝመው ውይይቱ ውስጥ በመግባት እኛ እንምራና ባልናችሁ መንገድ ሂዱ ማለት በመጀመራቸው ውይይቱ ከሸፈ። አሁን እንደሚታየው ዛሬም የመን ጦርነት ውስጥ ነው ያለችው። ሱዳንም እየተገራገጨች እዚህ ደርሳለች። ስለዚህ የብዙ ሀገሮች ውይይቶችን ስናይ አጀንዳ ከላይ ወደታች ይወርዳል ወይም የሀገሩ መንግሥት ጉልበተኛ ሆኖ ጣልቃ ይገባል አለበለዚያ ደግሞ የውጭ ሀገራት እጃቸው ረዝሞ ውይይቱ ውስጥ ገብተው እኛ ካልመራነው በማለታቸው ምክንያት ይፈርሳል። ከእነዚህ አካሄዶች እኛ ብዙ እየተማርን ነው። በዚህ ምክንያት ለውይይቱ ሂደት ጥበቃ እናደርጋለን። የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖርም በጥብቅ እንጠብቀዋለን።
የእኛ ውይይት የሚይዛቸው ሥራዎች በጣም ሰፊ ናቸው። ሌላ ሀገር እንደዚህ ተሄዶበታል ? በንባባችን አላገኘንም። ብዙ ጊዜ በቶሎ የሚያልቁ ትናንሽ አጀንዳዎች ናቸው የሚሆኑት። የተሳካላቸውን ሀገሮችን እንኳን ብንመለከት ቱኒዚያ ምስቅልቅል ብላ በነበረችብት በአንድ ወቅት የሆነው ምንድን ነው፣ ተሰባሰቡና የሠራተኛ ማኅበሩና ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው በሙሉ አብረው ተወያይተው መንግሥት መሠረቱ። ያ መንግሥት በአሁኑ ሰዓት ቢያንስ በሥርዓት እየሄደ ነው ያለው። ቱኒዚያ ትንሽ ሀገር ነች እንደ እኛ ከ80 በላይ ቋንቋ እና ከ200 በላይ ከእነዚህ ቋንቋዎች የወጡ ዘዬዎች የሚነገርባት ሀገር አይደለችም። የሕዝቦቿ ቁጥር አነስተኛ መሆን ጠቅሟታል።
ዘመን፡- በእስካሁኑ ጉዟችሁ ያጋጠሟችሁ ችግሮች እና የወሰዳችኋቸው የመፍትሔ እርምጃዎች አሉ ?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- የእኛ ኮሚሽን የሥራ ዕድሜ ሦስት ዓመት ነው። ከሦስት ዓመቱ ላይ ዘጠኝ ወሩን እያነሳንለት ነው። ይሄ ዘጠኝ ወር ዝም ብሎ አይደለም ያለፈው። ከላይ እንደገለጽኩልህ እጅግ በጣም በርካታ መሠረታዊ ሥራዎች ሲሠሩበት ነው የከረመው። ብዙ ጊዜ ወገኖቻችን ከስሜት የተነሳ ለምን ዝም አሉ ወይም ድምጻቸው አይሰማም ወይም ደግሞ ቀን ቆጥረው ሦስት ዓመት ሲሞላቸው እንደቀደሙት ኮሚሽኖች ሊከስሙ ይችላሉ የሚል ፍራቻ አላቸው። በተለይ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረው ጦርነት እና በየቦታው ያለው ግጭት ሕዝባችንን ስላሰለቸው፣ ብዙዎቹ እኛ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ሁሉ እንመስላቸዋለን። እርቅ የምናመጣ የምናደራድር ሁሉ ይመስላቸዋል። እርቅ የሚቀጥለው ውጤት ነው የሚሆነው። ወይም ደግሞ እርቀ ሰላም አይደለም ሥራችን። እርቀሰላም የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የእናቶች ሥራ ነው። የእኛ ሥራ መጨረሻ ላይ ወደ ሀገራዊ እርቅ ማምጣት ነው። ቀደም ብሎ ከመጣም እሰየው፤ ይረዳናል። ምክንያቱም ሁለት በአካባቢ ጉዳይ የተጣሉ ወገኖች ቢታረቁ የታረቁበት ሁኔታ ዘላቂ ይሁን ከተባለ ውይይት ያስፈልጋቸዋል። አለበለዚያ በየአካባቢው ይጋጫሉ በሬ ያርዳሉ ይታረቃሉ በሚቀጥለው ቀን ደግሞ በግጦሽ መሬት መገዳደል ይጀምራሉ። የእኛ ሥራ መገዳደል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲበቃ ተወያይተን አንድ መፍትሔ ላይ እንድረስ ማስቻል ነው።
እንደምታውቀው ተፎካካሪዎቹን እና ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ በሀገራችን የተመዘገቡ 53 የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ። በተፎካካሪ ፓርቲዎች ዘንድ በመጀመሪያዎቹ ቀናት ጭምር የአዋጁን ሂደት አለመቀበል፤ እኛ የተመረጥንበትን ሂደት አለመቀበል አልፎ ተርፎም እኛን ይሄ ሰውዬ ወይም ያቺ ሴትዮ ከዚያ ነች ወይም ከዚህ ነች በማለት የነበሩ ጥርጣሬዎች ነበሩ። እነዚህን ሁሉ ነገሮች በየደረጃው ማጥራት ነበረብን። ከፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር ጥምረታቸው ጋር መገናኘት ነበረብን። በሂደት ባደረግነው ክትትልና ሥራ ከ 53ቱ ውስጥ ከ40 በላይ የሚሆኑት ከእኛ ጋር አብረው ለመሥራት ተስማምተዋል። በቅርብ ጊዜ ውስጥ የስምምነት ማዕቀፍ እንፈራረማለን። ከተቀሩት ጋርም አብረን እንሠራለን ብዬ ነው የማስበው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አካላትም የተለያዩ ብዥታዎች እና ስሜቶች ነበሯቸው። አንዳንዶቹ አምባሳደሮች ለምሳሌ ሰሜን ውስጥ ሰላም ሳይሰፍን ወይም ጦርነት ሳይቆም ውይይት ማካሄድ ትችላላችሁ ወይ ይሉን ነበር። እኛ ደግሞ ሁለት ነገር ነበር የምንነግራቸው። አንደኛ እኛ ሕዝብ ጠቁሞን በአዋጅ ነው የተቋቋምነው። ተወዳድረን እዚህ ቦታ ካልገባን ብለን የመጣን ኮሚሽነሮች አይደለንም። እንዲህ ያለ ኃላፊነት ሲሰጠን ለሀገራችን የተወሰነች እንኳን ድርሻችንን እንወጣ ብለን ነው የመጣነው። እዚህ በመግባታችን ኃላፊነትን ከመሸከም ውጭ የምናገኘው ጥቅም የለም። አንዳንድ ኮሚሽነሮቻችን እንደውም ትልልቅ ሥራዎቻቸውንና የሚያገኟቸውን ከፍተኛ ክፍያዎች ትተው ነው ወደዚህ የመጡት፣ ብለን ያለውን ነገር በትክክል በማስረዳት አካሄዱ ሁለት ነገር ሊሆን እንደሚችል እንነግራቸዋለን።
አንዱ መንገድ በየቦታው ያለው የሰላም መደፈረስ እስኪቆም እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥና መረጋጋት ሲኖር ሥራችንን መጀመር ነው። ሌላው ግን እየተዘጋጀን እና ሌሎች የሰላም ሂደቱን የሚጠርጉት እያመቻቹልን እኛምሁኔታዎችን እያመቻቸን ሰላም ባለበት ቦታ የውይይቱን ወይም የምክክሩን ሂደት እያጠናከርን ሌሎች ደግሞ ወደ ሰላም ሲመጡ ያንኑ አጠናክረን መሄድ ነው። ሁለተኛው አማራጭ የተሻለና ተገቢ መሆኑን መጀመሪያ በመላ ሀገሪቱ ሰላም መስፈን የለበትም ወይ ለሚሉን የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አካላት እያስረዳን ቆይተናል። እንደ ዕድል ሆኖ የእግዚአብሔርም ፈቃድ ሆኖ ልክ እኛ እንዳልነውና እንደተመኘነው በአሁኑ ሰዓት ቢያንስ የሰሜኑ የሰላም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል።
ዘመን፡- አሁንም ድረስ ውይይቱ መፍትሔ አያመጣም የሚል አቋም በመያዝ ራሳቸውን ከሀገራዊ ምክክሩ ሊያገሉ እንደሚችሉ እየገለጹ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች አሉ። እነዚህን ወገኖች ለማግባባት እያደረጋችሁ ያላችሁት ጥረት አለ ?
ፕሮፌሰር መስፍን፡– ከእኛ ጋር ለመሥራት ፍላጎት ካላሳዩት 10 እና ከዚያ በላይ ከሆኑት ፓርቲዎች ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እየተገናኘን እኛ ማን እንደሆን እንዲሁም ሥራችን የት ድረስ እንደሚሄድና የሥራ ኃላፊነታችን ምን ምን እንደሆነ በማስረዳት ላይ እንገኛለን። እኛ የውይይትን ሥራ የምናመቻችና የምናሳልጥ እንጂ ወሳኞች ስላልሆንን ይህንን እያሳወቅናቸው ነው።
ብዙ ሕዝብ ተቀብሎናል ያልሰሙንና ያልፈለጉን ጥቂት የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው ብለን እነሱን ወደ ኋላ መተው የለብንም። ምክንያቱም ለእነሱም ኢትዮጵያ ሀገራቸው ነች። ልዩነታችን እነሱ ሀገራችን ልትጓዝበት ይገባል ብለው የሚያምኑት ሌላ መንገድ በመሆኑ ነው ብዬ ነው የማስበው፤ ያ ደግሞ መብታቸው ነው። ነገር ግን እነሱም የመጨረሻ ግባቸው ሀገራቸው ኢትዮጵያ እስከሆነች ድረስ፣ እኛም የመጨረሻ ግባችን ሀገራችን ኢትዮጵያ እስከሆነች ድረስ እና የእኛ ሥራ የእነሱንም አጀንዳ ጭምር አካቶ ወደ ውይይት ማምጣት ስለሆነ ለእነሱም ጭምር ነው እየሠራን ያለነው። እነዚህ ያልተቀበሉን ወይም የተቃወሙን የፖለቲካ ፓርቲዎች ነገ ጠዋት ሁኔታዎች ከተመቻቹ ሀገር የሚመሩና የሚያስተዳድሩ ስለሆኑ ሕዝብ የተዋደደበትንና የተፋቀረበትን ጠንካራ ሀገርን መምራት ለፖለቲካ ፓርቲዎችም ትልቅ ዕድልና ጸጋ ይመስለኛል።
ከ40 በላይ ከሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋርም አብረን ለመሥራት ስምምነት ላይ እስክንደርስ ድረስ የራሳቸው ጥርጣሬ ነበራቸው። አንዳንዶቹ በአዋጁ አቀራረጽ ሂደት ላይ ነው ችግራችን ያሉን አሉ። ሌሎች በኮሚሽኑ ስም ላይ ጥያቄ አንስተው የውይይትና የእርቀ ሰላም ኮሚሽን መሆን አለበት ያሉን አሉ። እናንተስ ምን ያህል ተዓማኒ ናችሁ? ከመንግሥት ጋር ወይም ከዚኛው ጋር ከዚያኛው ጋር ትወግናላችሁ ያሉን ነበሩ። እኛ የሰጠናቸው መልስ አዋጅ ጸድቆ እኛ እንዴት እንደተጠቆምን ባላወቅንበት ሁኔታ ለዚህ ሥራ ተሰይመናል። አብራችሁን በመሥራት እዩን፣ እንደምትሉት ሳይሆን ገለልተኝነታችንና ተዓማኒነታችን የሚታይ ነው የሚሆነው። ተዓማኒነታችን ብዙም የሚያስደነግጥ አይደለም፣ ምክንያቱም ሕዝብን ነው የምናወያየው፤ የሚወስነውም ሕዝብ ነው። ራሱ ተወያዩ እንጂ እኛ ሀገር እንዲህ ትሁን ብለን አቅጣጫ አንሰጥም ስለዚህ አብረን እንሥራ የሚል ነው።
የእኛ ትልቁ ኃላፊነት ሂደቱን በሥርዓት መርተን ውጤቱን በትክክል ጠምረን ተከታትለን እስከ መጨረሻው ድረስ ሄደን መሠራትና አለመሠራቱን ማረጋገጥ ነው። ተስፋ እማደርገው ቅቡልነቱ እየሰፋ እንደሚሄድ ነው፤ እየሆነም ያለው እንደዛ ነው።
ዘመን፡- ከመንግሥት የምትፈልጉት ድጋፍ እያገኛችሁ ነው ?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- መንግሥት ሀገራዊ ምክክሩ ትልቅ ፕሮግራም መሆኑን አምኖበት አዋጅም እንዲወጣ አመቻችቶ እዚህ አድርሶናል። የሚሰጠን ገንዘብ ሁልጊዜም እንደምለው የሕዝብ ገንዘብ ነው። እኔም አንተም ታክስ የምንከፍለውን ገንዘብ ነው መልሶ የሚያደላድለን። በየክልሎች ስንሄድም የክልል መንግሥታት ሁኔታዎችን አመቻችተውልናል፣ በሚችሉት እረድተውናል አግዘውናል።
ከጥቂት ጊዜያት በኋላ በየክልሉ ጽሕፈት ቤቶችን እንከፍታለን። የምንከፍታቸው ጽሕፈት ቤቶች በፌዴራል ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲሆኑ ነው የወሰንነው። ስለዚህ ከፌዴራል ዩኒቨርሲቲዎች ስብስብ ጋር የስምምነት ማዕቀፍ ተፈራርመናል። በፌዴራል ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲሆን የፈለግነው ኢትዮጵያን የሚወክሉ በመሆናቸው ነው። ጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ያሉ ተማሪዎች ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሄዱ የሁላችንም ልጆች ናቸው። ወጣቶች የሀገራቸው ጉዳይ ስለሚመለከታቸው በዚህ በእኛ ሥራ ሂደት ውስጥ መሳተፍ አለባቸው። አወያይ ሊሆኑ ይችላሉ። አስተማሪዎቻቸው ይሳተፉበታል በመጨረሻም ሁሉንም ባይሆን እንኳን የተወሰነውን ሥራችንን ሠርተን እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ ደርሰን ቢያንስ ለዴሞክራሲ መሠረት ጥለን ስንወጣ በየዩኒቨርስቲው ያሉት ልጆቻችን የጀመርነውን ነገር ያስቀጥሉታል።
ቢያንስ ቢያንስ የሚኖረንን ነገር እዚያው ትተንላቸው ስለምንወጣ ተቋማቱ የሰላም ግንባታ እና የምርምር ማዕከላት ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ተስፋ ነው ያለኝ። ምክንያቱም የጸብ መነሻም ሆነ የሰላም ግንባታ ቦታ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው። ዩኒቨርሲቲዎች ሳይንስ ላይ ብቻ አይደለም ማተኮር ያለባቸው አብሮ መኖር ላይ እና አብሮ መሥራት ላይም ማተኮር አለባቸው። ያንን እያዳበሩ ሲሄዱ ነው ትልቅ ሀገር ሊገነቡ የሚችሉት።
ዘመን፡- በአንድ ወቅት ከአንድ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ መንግሥት ጣልቃ የሚገባ ከሆነ ሥራዎን እንደሚለቁ ገልጸው ነበር። እስካሁን ከመንግሥት በኩል የገጠማችሁ ጣልቃ ገብነት አለ ?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- ምንም ነገር የለም። አንደኛ እኔ ቀጥታ ሪፖርት የማደርገው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ነው። አፈ ጉባኤው ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ ከቃለ መሐላችን ስንወጣ ያሉን ነገር ቢኖር እናንተ በተቻለ መጠን ገለልተኛና ተዓማኒ ሆናችሁ መሥራት ነው ያለባችሁ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በጭራሽ ወደ እናንተ ውስጥ አይመጣም ነው ያሉት። ያንን ጥያቄ እንደዛ የመለስኩት ለምንድን ነው ጥያቄው በእንደዛ አይነት መልኩ ተቃኝቶ ስለመጣ ነው። መንግሥት መጀመሪያውኑ እንዳይቋቋም ማድረግ ሲችል ለምን ጣልቃ ይገባል? በነገራችን ላይ ልክ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሊጠቀሙ እንደሚችሉት ሁሉ መንግሥትም ተጠቃሚ ነው የሚሆነው። አሁን አስተውለህ ከሆነ ብዙ ሥራዎች ወደ ሀገራዊ ምክክር እየመጡ ነው። ምክንያቱ ምንድን ነው፣ የመጨረሻው ወሳኝ ሕዝብ ስለሚሆን መንግሥትም ታጋዥ ነው የሚሆነው። ይሄ ሥራ የተሳካለት ቢሆን ተምሳሌታዊ ሥራ ሠራ የሚባለው ወገናችን፣ ሕዝባችንና ሀገራችን ስለሆነ ተጠቃሚ ነው የሚሆነው።
ዘመን፡- ሁለተኛው ምዕራፍ ተገባዶ ምክክሩ ሊጀመር ጥቂት ጊዜ ነው የቀረው። ትግራይ ክልል በነበረው ሁኔታ ምክንያት እንደሌሎች አካባቢዎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች አልተሠሩም። በቀረው አጭር ጊዜ ክልሉን በውይይቱ ለማሳተፍ ምን ታስቧል?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- በአጋጣሚ እኔ አልነበርኩበትም እንጂ በቅርቡ ኮሚሽነሮቻችን ወደ ትግራይ ሄደው ነበር። እኔ በኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች ካውንስል ውስጥ ሰብሳቢ ሆኜ ሰላምን በሚመለከት በተደጋጋሚ ወደ ትግራይም ወደ አማራም ወደ ብዙ ክልሎች ሄጄ ነበር። እንደ ዕድል ሆኖ ጦርነቱ ከመከሰቱ በፊት ሁሉ በመጨረሻ ሰዓት መቀሌ ሄጃለሁ። በኋላም ላይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተጀመረበትም ጊዜ ጭምር ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር የመሄድ ዕድል ነበረኝ። ይሄ ብቻ ሳይሆን ወጣት ሐኪም ሆኜ ትግራይ ስለሠራሁ ለሕዝቡ በጣም ከፍተኛ ፍቅር አለኝ። ችግር ውስጥ በነበረበት በቀይ ኮከብ ዘመቻ ጊዜ ነው ያንን ሕዝብ የማውቀው። ምን አይነት ኢትዮጵያዊ ሕዝብና ወገን ወዳድ እንደሆነ አውቃለሁ። ዋናው ነገር አሁን ሰላሙ እየመጣና እየተጠናከረ ከሄደ በሌሎች ክልሎች በሚገኙ የፌዴራል ዩኒቨርሲቲዎች እንደምናደርገው ሁሉ በትግራይ ክልልም ጽሕፈት ቤታችንን በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንከፍታለን ብዬ ነው ተስፋ የማደርገው። ያ ማለት በክልሉ ውስጥ ባሉት ዞኖች ሁሉ በሌሎች ቦታዎች ስንሠራቸው የነበሩትን ሥራዎች እንቀጥላለን።
ለዚህ ውይይት የዚያ አካባቢ ሕዝብ የበለጠ የሚዘጋጅበት ይሆናል ብዬ ነው የማምነው። ምክንያቱም ጦርነትን የአካባቢው ሕዝብ ላለፉት 50 ዓመታት በሚገባ ያውቀዋል። በታሪክ ወደኋላ ከሄድን ምናልባት ብዙ መቶ ዓመታትም ወደ ኋላ ሊወስድ ይችላል። አካባቢው የሀገር በር በመሆኑ ብዙዎቹ ጦርነቶች በዚያ ስለሚያልፉ የአካባቢው ሕዝብ ለብዙ መቶ ዓመታት ለችግርና ለጦርነት ተጋላጭ ነው። ያለፉት 50 ዓመታት ደግሞ ከተመለከትን ብዙ የተፈተነ ሕዝብ ስለሆነ በእርግጠኝነት ከነፍጥ ይለቅ ቁጭ ብሎ መወያየት እንደሚቻል ከማንኛውም አካባቢ ባላነሰ ግንዛቤ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ።
ዘመን፡- ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም አካታች ከሆነ በተለያየ የሀገሪቱ ክፍል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች ወደ መድረኩ ሊጋበዙ ይገባል የሚሉ ወገኖች አሉ። በዚህ ላይ የኮሚሽኑ አቋም ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- ወደ ውይይት ሲመጣ መጀመሪያ መቀመጥ ያለበት መሣሪያ ነው። መጀመሪያ እኔና አንተ ወደ ውይይት የምንመጣው አንተም ፈልገህ እኔም ፈልጌ ነው። አንተ ሳትፈልግ እኔ በግድ ባመጣህ የጉልበት ክርክርና ጭቅጭቅ እንጂ ውይይት አይሆንም። ውይይት ሁለታችንም የምናሸንፍበት እስከሆነ ድረስ ሁለታችንም መሣሪያችንን አስቀምጠን ሰላምን አንግበን ነው የምንመጣው። ለሰላም ፍላጎቱ እስካለና ጥያቄው ከዛ እስከመጣ ድረስ እኛ ሽብርተኝነትን እስከማስነሳትና ለዚህ ውይይት የሚመጡትን ደህንነት እስከማስጠበቅ ድረስ እንሄዳለን። ለምሳሌ ሽብርተኛ ተብሎ በውይይት ላይ መቀመጥ አይችልም። ስለዚህ እኛ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ይሄ አካል ለውይይት ስለመጣ የሽብርተኝነት ስያሜው ይነሳለት ብለን የመጠየቅ መብት አለን። በእርግጥ የሀገሩ ሕግና አካሄድ ምን እንደሚልና ምን ሊል እንደሚችል ባላውቅም ያንን እስከመጠየቅ ድረስ መብት እንዳለን ግን ከጅምሩ ጀምሮ አፈጉባኤው አረጋግጠውልናል።
ስለሰላም እስከተመጣ ድረስ ለሰላም የማይከፈል አቋም የለም። ለሰላም በሚከፈል መስዋዕትነት ውስጥ ደግሞ ሕይወት አይጠፋም። ለምን ? ጠብመንጃ ቁጭ ብሏል። ይሄንን ነው እኔ ሁልጊዜ የምናገረው። ይሄ የግል አቋሜ ነው በእርግጠኝነት ሌሎቹም ባልደረቦቼ ኮሚሽነሮች ከዚህ ብዙ የወጣ አቋም ይኖራቸዋል ብዬ አላስብም።
ዘመን፡- በምዕራብ ኢትዮጵያ በሚንቀሳቀሱት ኃይሎች በኩል በሀገራዊ ውይይቱ ለመሳተፍ ፍላጎት የሚኖር ከሆነ ኮሚሽኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ያቀርባል ?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- ግዴታችንም ነው እንጂ። ምዕራብ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሕዝባችን ከየትኛውም አካባቢ በላይ ሰላም የጠማው ነው። ምክንያቱም የደረሰውን ችግር እናውቃለን። እዛ ያሉ ኃይሎች የለም በቃ ያተረፍነውን ነገር አየነው፣ እኛ በሀሳብ ለማሸነፍ ወደ ውይይቱ እንመጣለን ካሉ እነኚህ አካላት በአጀንዳ ቀረጻው ሂደት ውስጥ ለመወያየት ዝግጁ ናቸው ብለን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ እናቀርባለን። ሄደን እናንተን አያገባችሁም የሚል መልስ የሚሰጠን ከሆነ ደግሞ ያንንም ለሕዝባችን እንነግራለን። እኛን እዚህ አስቀምጦናል ብለን የምናምነውሕዝባችንን ነው፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቃለ መሐላ የፈጸምነው ለዛ ነው። ስለዚህ የጠየቅነው ነገር ሲፈጸምም ሆነ ሳይፈጸም ሲቀር ለሕዝባችን እንነግራለን።
ዘመን፡- ኮሚሽኑ ለእነዚህ ኃይሎች በቀጥታ ጥያቄ ያቀርባል ወይስ በራሳቸው ወደ መድረኩ ለመምጣት ፍላጎት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- እኛ እንግዲህ በቀጥታ መንገዱ የለንም። ለምሳሌ ባለፉት ሁለት ዓመታት ፍላጎቱ ቢኖረንም ትግራይ አልሄድንም። መንገዱ መመቻቸትና ፈቃዱ ከዚሀም ከዚያም መገኘት መቻል አለበት። ከምታነሳቸው ኃይሎች በኩል ጥያቄው ከመጣ ግን ያንን ጥያቄ የማስተናገድ ኃላፊነት አለብን። አሁን የት ሄዳችሁ ከማን ጋር ነው የምትነጋገሩት ብትለኝ የት ጋርና ማን ምን እንደሆነ በማላውቅበት ይሄ ነው ልልህ የምችለው ሁኔታ ግን የለም።
ዘመን፡- ሥራችሁ እጅግ በጣም ሰፊ ነው። ኮሚሽኑ የተጣለበትን ኃላፊነት በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ይወጣል ብለው ያምናሉ ?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- አላምንም። የተሰጠን ኃላፊነት በጣም ብዙ ነው። ነገር ግን መሠረታዊ ሥራዎችን እንሠራለን ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም የኢትዮጵያ እጅግ መሠረታዊ ችግሮች ጥቂት ልሂቃን እንደምናምነው አንድ ሁለት ሦስት ብቻ ናቸው ብዬ አላስብም። የሀገራችንን ችግር በሚገባ እንመልከተውና እንሂድበት ሙሉ ለሙሉ ወደ መግባባት እንምጣ ከተባለ በጣም በርካታ ይሆናሉ ብዬ አምናለሁ። ያ ሁሉ በዚህች በቀረችው ሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ያልቃል የሚል የዋህ አመለካከት የለኝም። እኔ የማምነው ግን በተወሰኑ እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መወያየት ምን እንደሚመስል በማሳየት ለሕዝባችን አካሄዱን በሚገባ አስቀምጠን እናስተላልፋለን ብዬ ነው። ይህ ትልቅ ነገር ነው። ለዴሞክራሲም መደላድል በር ይከፍታል።
ብዙ ጊዜ እዚህ ሀገር ሲነገር የምሰማው ውይይት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አዲስ አይደለም የሚባል ነገር አለ። አላውቅም፣ እሱን ለመሞገት ፈልጋለሁ። ለምን እኛ የተዋረድ ማኅበረሰብ ነን። በአንድ ቤት ውስጥ አባትና እናት አሉ። አባት ወይም እናት የበላይ ነን የሚሉበት ልጆች ደግሞ ከታች የሆኑበት ኅብረተሰብ ነው ያለን። በእኛ ኅብረተሰብ ውስጥ ሥልጣኑ ትልቁ የሀገር ሽማግሌ ወይም ትልቁ የሃይማኖት አባት ዘንድ ነው የሚሆነው። በዚህ መልኩ የተዋረድ ኅብረተሰብ መሆናችን ጥሩ ነገር ነው፤ እሱም ነው ለብዙ ሺህ ዓመታት የጠበቀን ብዬ አምናለሁ። አሁን ግን ስለውይይት በምንነጋገርበት ጊዜ የ 18 አመት ወጣትም ሆነ የ80 አመት አረጋዊ ወይም እናት ቁጭ ብለው እነኚህ ናቸው አጀንዳዎቻችን ብለው ይወያያሉ።
አዋጁ ለሦስት ዓመታት ነው ይሄን ኮሚሽን ያቋቋመው እንደአስፈላጊነቱ ይራዘማል ይላል። እንደአስፈላጊነቱ ሲራዘም አንዳንዶቻችን በጡረታ ዕድሜ እያገለገልን ስላለን ሊረዝምብን ይችላል። ስለዚህ በዚህ የሥራ ሂደት ውስጥ በትክክል መተካካት ሊኖር ይገባል ብዬ አምናለሁ። ከላይ እንደጠቀስኩልህ ሁሉ ነገር ላይ የግድ መግባባት ላይ እንደርሳለን ማለት አይደለም። ባለመግባባትም ተግባብቶ መቀጠል ቀላል ነገር አይደለም። ስለዚህ ያልጨረስናቸውን አጀንዳዎች ሕዝብ እስካመነበት ድረስ በቀጣይ ይሄው ተቋም ተረክቦ ሊያስኬዳቸው ይችላል።
ዘመን፡- ከተለያዩ አካላት ጋር በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነቶችን ተፈራርማችኋል። ስምምነቶቹ ምን እያስገኙ ነው ?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- የሁለትዮሽ ስምምነቶች ከሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት ጋር ተፈራርመናል። እነዚህ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት የሚሠሩልን በተለይ ግንዛቤ ማስጨበጡ ሂደት ላይ ታች ድረስ ሄደው ስለሆነ የሚሠሩት ብዙ እገዛዎችን ያደርጉልናል ብዬ አምናለሁ። ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ስንፈራረም ዋናው ዓላማ ፓርቲዎቹ ተከታዮቻቸው በትክክል በውይይቱ ሂደት ላይ እንዲሳተፉ እንዲያስችሉ ነው። ስለዚህ ከአካል ጉዳተኞችም ማኅበር ሆነ ከሌሎች ማኅበራትም ጋር የምንፈራረማቸው ስምምነቶች ዓላማቸው የራሳቸውን ተከታዮች እንዲያነቁልን ማስቻል ነው። ያ ማለት የእኛ ሥራ ወደ ኅብረተሰቡ በቀላሉ እንዲሰርጽ ያሰችላል። ምክንያቱም ኅብረተሰቡ ጋር ያሉት እነሱ እንጂ እኛ እዚህ ማዕከል ያለነው አይደለንም። በነገራችን ላይ ይሄ ሚዲያና ተግባቦት ማዕከላትንም ይመለከታል። ለምሳሌ በቅርቡ ከሶሻል ሚዲያው ማኅበረሰብ ጋር አንድ ስብሰባ አካሂደናል፤ ወደፊትም የሚቀጥል ይሆናል።
ዘመን፡- በቅርቡ ፍትሕ ሚኒስቴር የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮችን አርቅቆ ለባለድርሻ አካላት ለውይይት አቅርቧል። እርስዎ የሚመሩት ኮሚሽን ሥራ ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የሽግግር ፖሊሲው የሚኖረውን ሚና እንዴት ይገልጹታል ?
ፕሮፌሰር መስፍን፡– ውይይት መግባባትን ያመጣል። ከመግባባት ቀጥሎ ደግሞ የሚመጡ አሉ። ሀገራዊ እርቅ ወይም የሽግግር ፍትሕ ሊሆን ይችላል። ብዙ በደሎች በሀገራችን ላይ ደርሰዋል። ባለፉት 50፣ 60፣ 100 የፈለገውን መቁጠር እንችላለን፣ በቅርብ ጊዜም የደረሱ አሉ። እነኚህ በደሎች ፍትሕ ይፈልጋሉ። ፍትሕ ማለት የግድ እሰረው ቁረጠው ግደለው ስቀለው ማለት አይደለም። ቢያንስ አንዳችን በአንዳችን ላይ በደል ማድረሳችንን ተማምነን ወደፊት ይሄ እንዳይደገም ተስማምተን፣ በደል ያደረስን ጸጸታችንን ገልጸን ይቅርታችንን ጠይቀን፤ በደል የደረሰባቸው በደል ያደረሱትን ጸጸትና ይቅርታ ተቀብለው ተክሰው ወደፊት መቀጠል መቻል አለብን። ስለዚህ የሽግግር ፍትሕ ብዙ ነገሮችን ነው የሚያካትተው። ቀጥታ ፍርድ ቤት መሄዱ እና እዚያ የሚተላለፈው ቅጣት እንዳለ ሆኖ ሕዝቦች ይቅር ባይ ናቸውና፣ እስካሁንም ድረስ ያስተዋልነው ይሄ ስለሆነ ወደፊት የሚቀጥሉበትን መንገድ የሚያመቻቹት እነሱ ናቸው። ስለዚህ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው በኋላ ላይ የሚደረስበት ውጤት ነው የሚሆነው። ከእኛ ሥራ ጋር ቀጥታ ግንኙነት የለውም ነገር ግን በውይይቱ የሚደረስበት የጋራ መግባባት ወደዚያ ስለሚያመጣን ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር ተነጋግረንበታል።
ዘመን፡- በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር እንዲሳካ ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ ?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ሥራና ኃላፊነቶች አዋጁንም በሚገባ በጥንቃቄ ተረድቶና አውቆ አብሮ በጋራ መሥራት የበለጠ ይጠቅመናል ብዬ አስባለሁ። በብዛትና በኃይል ልዩነቶቻችን ላይ ስለሠራን አሁን የደረስንበት ላይ ደርሰናል። ምናልባት ሀገራዊ ውይይቱ ወደ አንድ ምዕራፍ ያመጣናል ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ እኔ በራሴ የማምነው የጦርነትን አስከፊነት አይተናል። በጦርነት ሰላም አይመጣም። በጦርነት ሰላም የሚመስል ነገር ማምጣት ይቻል ካልሆነ በስተቀር ዘላቂ የሆነ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ሊመጣ የሚችለው ቁጭ ብሎ መሣሪያን አስቀምጦ መወያየት ሲቻል እንደሆነ በየጊዜው እንናገራለን። ይሄ የምንለው ነገር አሁን እየመጣ ነው ያለው። የሰሜኑ ሰላም ለምዕራብ ኢትዮጵያም ሰላም መምጣት በር ይከፍታል የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም በዚህ በጦርነት ያየነው አሳርና መከራ ነው። ወጣቶቻችንን አጣን፤ ብዙ ጉዳት ደረሰ፤ ንብረቶች ወደሙ፤ በድህነታችን ላይ ተጨማሪ ድህነቶችን ነው ስንጭምር የከረምነው። መጠራጠርን ነው ስንጨምር የከረምነው። ለብዙ ሺህ ዓመታት አብረው የኖሩ ወገኖቻችንና ሕዝቦቻችን ላይ ነው ሰቆቃ ስንደርብባቸው የከረምነው።
ኮሚሽናችን የተቋቋመበት አዋጅ የሚለው ምንም እንኳን ብዙ የሚያግባቡ ነገሮች ቢኖሩንም ከጊዜ ወደጊዜ ግን አንዳንድ እጅግ መሠረታዊ የሆኑ የማያግባቡን ነገሮች በመኖራቸውና እነኚያም ለግጭትና አልፎም ለጦርነት ስለዳረጉን ሕዝቦቻችን በማያግባቡን ነገሮች ላይ ተወያይተው ወደፊት ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላማዊ የምትሆንበትን መንገድ ይመቻች ነው። ስለዚህ ውይይት በሚባልበት ጊዜ ተወያዮቹን መግባባት ላይ ማድረስ ነው። መግባባት ላይ እንኳን ባንደርስ ከነአለመግባባታችን ተግባብተን እንድንቀጥል ማስቻል ማለት ነው። ከነአለመግባባታችን ተግባብተን እንቀጥል ማለት አንድ ቀን ያላግባቡን ነገሮች ይፈታሉ ማለት ነው። ስለዚህ ውይይት እንጂ ጦርነት እና መሳሪያ ጥቅም የለውም።
ዘመን፡- ለጥያቄዎቻችን የተብራራ ምላሽ ስለሰጡን እናመሰግናለን።
ፕሮፌሰር መስፍን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ተስፋ ፈሩ