የዳሎል ስምጥ ሸለቆ ሳይንሳዊ ይዘት፣ አስደናቂ ውበት እና እምቅየተፈጥሮ ሃብት

የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ሳይንስን ማኸዘብ (የሳይንስን ዘዴ እና ዕውቀት ለሕዝብ እንዲዳረስ ማድረግ) ሲሆን፣ የተዘጋጀው በዳሎል ስምጥ ሸለቆ ሳይንሳዊ ይዘት፣ አስደናቂ ውበት እና እምቅ የተፈጥሮ ሃብት እንዲሁም ትዝታ ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ስለ ዳሎል በረሃ ዝርዝር ሁኔታ ከማቅረባችን በፊት፣ ትንሽ ደረቅ ያለ ሳይንስን ማውሳቱ አይቀሬ እና አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል።ጽሑፉ የአካባቢውን ሥነ ምድራዊ (ጂኦሎጃዊ) አመሠራረት፣ አካባቢው በከርሱ ያመቀውን እምቅ ሃብት፣ እንዲሁም ከላይ የሚታየውን ልዩ ውበት ይዳስሳል።

ዳሎልን አንዳችን (ሽብሩ ተድላ) የጎበኘው በአካባቢ ጥናት መንስዔ ሲሆን፣ ሌላችን (ገዛኸኝ ይርጉ) በተደጋጋሚ በሳይንሳዊ ምርምር መንስዔ አካባቢውን ጎብኝቷል፣ እየጎበኘም ነው።እዚህ ላይ በብዛት የሚወሳው በአካባቢ ጥናት ጉብኝቱ ተመሥርቶ የተገኘ ግንዛቤ እና እይታ ነው፡፡

የዳሎል ስምጥ ሸለቆ (Dalol Depression) ሳይንሳዊ ሁኔታ

የአፋር ስምጥ ሸለቆ ቅርፅ እንደ “ትራያንግል” (triangle) መሰል ሲሆን፣ የሸለቆው አጠቃላይ ስፋቱ 50 ሺ ኪሎ ሜትር ካሬ ገደማ ነው።የስምጥ ሸለቆው አመሠራረት የጀመረው ከ25 ሚሊዮን ዓመት ገደማ በፊት እንደነበረ ይገመታል።የምድር ጠንካራውና ውጫዊው ክበብ (lithosphere) አካል የሆኑ ሁለት “ስፍሃን “ (Plates)፣ ማለት ግዙፉ የአፍሪካ “ስፍሃን “ እና መጠነ ውስኑ (አንፃራዊ) የዓረቢያ “ስፍሃን” የሚገናኙበት አካባቢ ሆኖ፣ በሁለቱ “ስፍሃን “ ዝግመታዊ የመራራቅ እንቅስቃሴ መንስዔ የተከሰተ ሸለቆ ነው።ይህም የቀይ ባህር ስምጥ ሸለቆ፣ የኤደን ባህረ ሰላጤ ስምጥ ሸለቆ እና የምሥራቅ አፍሪቃ ስምጥ ሸለቆ (East African Rift Valley) መገናኛ አካባቢ መሆኑ ነው።

የአፋር ስምጥ ሸለቆ የአፍሪካ ክፍለ ዓለም (ስፍሃን) ለሁለት የሚከፈልበት የመጀመሪያው ምዕራፍ የመጀመሪያው ጫፍ ሲሆን፣ ከሚሊዮኖች ዓመታት በኋላ ምሥራቅ አፍሪካን ለሁለት የሚከፍለው (የሚሰነጥቀው) እና የሚለያየው ግዙፍ እንቅስቃሴ እውን የሆነበት አካባቢ ነው።የመሬት አካል መሰነጣጠቅ የዚህ ስምጥ ሸለቆ አንዱ ባህርይ ነው።የዚህ መሬት መሰንጠቅ ክፍተት በየዓመቱ ከሰባት ( 7mm) እስከ ሃያ ሚሊሜትር (20mm) ገደማ እየጨመረ ነው፡፡

የሰሜን አፋር (ደንከል) ስምጥ ሸለቆ፣ በሰሜን የዳሎል ረባዳ የጨው ሜዳ አካባቢ ሲሆን፣ በደቡብ ኤርታ አሌ (Ert’ale) እሳተገሞራዎች ሰንሰለት ይገኛሉ።የዳሎል የጨው ሜዳ አራት ሺ ኪሎ ሜትር ካሬ ይሸፍናል።በዚህ አካባቢ በሰሜን አቅጣጫ ከዘይላ ወደብ በስተደቡብ ዝቅ ብለው የተዳፈኑ እሳተገሞራ ኮረብታዎች ይታያሉ።ከነሱም ውስጥ የጃልዋ (Jalua) እና የአሊድ (Alid) እሳተገሞራ ኮረብታዎች፣ አካባቢው በቀይ ባሕር ውሃ እንዳይጥለቀለቅ ይገታሉ፡፡

እሳተገሞራ

በመሠረቱ ምድር አሎሎ መሳይ ቅርፅ ይዛ፣ ከላይ በስሱ እንደ ቅርፊት ከሚሸፍናት አካል በቀር፣ ውስጧ እሳት (እጅግ የጋለና አልፎ አልፎም የቀለጠ ድንጋይ እና የብዙ ንጥረ ነገሮች ቅልቅል) ነው።ሽፋኑ (ጠጣር አካሉ) በጣም ውስን ሲሆን፣ ከአጠቃላይ ይዘቱ አንድ ከመቶ (1%) በታች ነው፣ ሳይንሳዊ ስያሜውም “ሊቶስፊር” (lithosphere) ይባላል፡፡

ይህ ስስ የምድር ሽፋን፣ በአማካኝ ከ100 ኪሜ ጥልቀት ሲኖረው፣ ደረቁ የላይኛው ቅርፊት (crust) ከ35 እስከ 50 ኪሜ ይዘልቃል፣ በጣም ከፍተኛ ቦታዎች የሚገኙባቸው አካባቢዎች ከላይ ያለው ደረቅ ቅርፊት ከዚህ ወፈር ይላል።ከምድር ገፅ ወደ ከርሰ ምድር በተዘለቀ መጠን፣ ሙቀቱ አብሮ ይጨምራል፣ በእያንዳንዱ ኪሎሜትር የጥልቀት ጭማሪ፣ ሙቀቱ በሰላሳ ዲግሪ ሴልሲየስ(30°C) ይጨምራል።በዚህም ምክንያት ወደ ውስጥ በተዘለቀ መጠን ውስጣዊው የምድር ክፍል ጠጣርነቱ እየላላ እየላላ ሄዶ፣ ምድር አስኳል (outer core) ሲደርስ ሙሉ በሙሉ የቀለጠ ድንጋይ/ ብረታ ብረት ፈሳሽ ይሆናል፡፡

አንዱ የእሳተ ገሞራ መንስዔ የምድር “ስፍሃኖች” (Plates) ሲፋተጉ/ሲጋጩ በሚፈጠረው ከፍተኛ ሙቀት አለት ሲቀልጥ ነው።ሌላውና ዋናው መንስዔ ግን ከስፍሃን በታች ያለው እጅግ የጋለውና የላላው አካል ወደ ላይ ሲነሳና: ቀድሞ የተጫነው ከፍተኛ ግፊት በፍጥነት ሲቀንስ (decompression) ያለምንም ተጨማሪ ሙቀት ጠጣርነቱ ተቀይሮ ፈሳሽ ይሆናል (ይቀልጣል)፣ የቀለጠው አለት በስንጥቅ ውስጥ ፍጭጭ ብሎ ወደላይ ሰረጎ መሬት ገፅ ላይ በፍንዳታ መልክ ይፈሳል፣ ይህ ነው እሳተገሞራ የሚባለው፡፡

በዓለማችን ሰባት ግዙፍ “ስፍሃን “ አሉ፣ አንዳንድ ተመራማሪዎች እነዚህን በሰባት ፋንታ ስምንት ናቸው ይላሉ።ሰባቱ “ስፍሃን” የአፍሪካ፣ የአንታርክቲካ፣ የዩሮእስያ፣ የሰሜን አሜሪካ፣ የደቡብ አሜሪካ፣ የሰላማዊ ውቅያኖስ እና የኢንዶአውስትራሊያ ናቸው።ስምንት ናቸው የሚሉት ደግሞ የመጨረሻውን፣ ኢንዶአውስትራሊያዊውን ለሁለት በመክፈል እና ኢንዶያዊ እና አውስትራሊያ ብለው በመሰየም ነው።ከነዚህ ከግዙፍ “ስፍሃን” በተጨማሪ ትናንሽ (አንፃራዊ)”ስፍሃን” አሉ፣ ለምሳሌ የዓረቢያ፣ የካሬቢያን፣ የፊሊፒንስ፡፡

እነኝህ “ስፍሃን” ብለን የሰየምናቸው ግዙፍና ጠጣር የድንጋይ ሰፌድ/ምጣድ መሰል አካላት፣ ሽፋኖች፣ ከበታቻቸው ከሚገኘው ከጋለውና ከላላው የምድር ከርስ ላይ ተንሳፈው፣ ተጠጋግተው ነው የሚገኙት።እነሱም በዓመት እስከ አሥር ሴንቲ ሜትር (10 cm) ገደማ ይንቀሳቀሳሉ (ነባር ቦታቸውን ይለቃሉ)።ጎን ለጎን ያሉ “ስፍሃን” በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ከሚገናኙበት ወሰን እየተራራቁ ሊሄዱ ወይም ሊቀራረቡ ብሎም ሊጋጩ ይችላሉ።በሚጋጩበት ጊዜ አንዱ ግዙፍ ሰፌድ/ምጣድ ጠርዝ ሌላኛው ላይ ሊያርፍና ሊደረብ ይችላል።አንዱ ወፍራምና ቀላል፣ ሌላኛው ስስና ከባድ (አንፃራዊ) የሆኑ ሲገናኙ፣ ወፍራሙና ቀላሉ ከላይ ሲሆን፣ ስሱ ደግሞ በክብደቱ ወደ ታች ይጠልቃል።ይህ ሲከሰት በታች የሚገኘው ስፍሃን ቀስ በቀስ እየተንሸራተተ ዝቅ ይላል (ወደ ውስጥ ይሰምጣል)፣ በተቃራኒው ላይኛው ደግሞ ከነበረበት ከፍ ይላል።

አብዛኛው እሳተ ገሞራ የሚፈነዳው (60% ገደማ) እነኚህ ግዙፍ ምጣዶች ከሚገናኙባቸው (ወሰኖች) አካባቢዎች ነው።በተቃራኒው ላይኛው ክብደተ-ቀላሉ ስፍሃን ደግሞ፣ በመደራረብና በመተጣጠፍ ከነበረበት በጣም ከፍ ይላል፣ይህም ለተራራ ሰንሰለት መከሰት መንስዔ ይሆናል።ለምሳሌ በእስያ አህጉር የሚገኘው “የሂማላያ ተራራ ሰንሰለት” (Himalaya) በዚህዓይነት “ስፍሃ” ግጭት መንስዔ የተገኘ የተራራ ሰንሰለት ነው፡፡

እሳተገሞራ ከምድር ውስጥ ፈንድቶ የሚወጣ የድንጋይ (በብናኝ ቅላጭ ወይም በአለት መልክ) ቃጠሎ ነው።ምድር ውስጥ እያለ በወፍራም ሊጥ መልክ የሚገኝ “ቅላጭ ድንጋይ” (“ማግማ” / magma) ነው።ከ”ቅላጭ ድንጋይ” (“ማግማ”) በተጨማሪ እሳተ ገሞራ ጋዝ ብናኝ ቅላጭ እና ጠጣር አለትም ያስወጣል።እሳተ ገሞራ የሚተፋው “ገሞራ ትፍ” (lava) ሙቀቱ በአማካኝ ከሰባት መቶ እስከ ሺ ሁለት መቶ ዲግሪ ሴልሲየስ (ከ700 እስከ 1,200 °C ) ይሆናል።ዝልግልግነቱም በውሕዱ ዓይነት ይወሰናል (ቀጭን ከሆነ እንደ ቀለጠ ማር፣ በብዛት “ሲሊካ” (Silica) ካለበት እንደ ዳቦ ሊጥ በጣም ወፍራም ሆኖ፣ ዝግ ብሎ፣ የሚፈስ ይሆናል)።

የመሬት መንቀጥቀጥ መንስዔም የ”ስፍሃን” መሰንጠቅና መለያየት እንዲሁም ግጭት ነው፡፡ አንድ ስፍሃን ሲወጠርና፣ ውጥረቱ ስብራት ፈጥሮ ሲለቅ ወይም ሁለት “ስፍሃን “ ሲፋተጉ፣ ከፍተኛ ኃይል ስለሚገኝ፣ ይህ ኃይል ነው ለመሬት መራድ/ መንቀጥቀጥ (earthquake) መንስዔ የሚሆነው፡፡

ጨዋማ አካባቢዎች

ጨው የሁለት ንጥረ-ነገሮች፣ “ሶዲየም” [Sodium (Na)] እና “ክሎሪን” [Chlorine (Cl)] ኬሚካዊ ውሁድ ሲሆን፣ ሳይንሳዊ ስያሜውም ጨው [“ሶዲየም ክሎራይድ”/ Sodium Chloride (NaCl)] ነው።“ሶዲየም” የሚባለው ንጥረ-ነገር በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የፈሳሽ ይዘት መጠን ይቆጣጠራል፣ ሚዛኑን ጠብቆ በሠራ አካላታችን በጠቅላላ እንዲሰራጭ ያደርጋል። ይህም በአካል ውስጥ የሚገኙ ፍሳሾች ይዘት ሚዛኑን/መጠኑን እንዲጠብቅ ያደርጋል፣ ተግባሩ እና ሂደቱ እንደ ንዑስ የሕዋስ ፖመፕ ይመሰላል፡፡

የዳሎል በረሃ ረባዳ መሬት የጨው ሜዳ፣ በጨዋማ የባሕር ውሃ ትነት የተገኘ ሲሆን፣ የትነቱ ቅሪት ከጨው በተጨማሪ ሌሎች ኬሚካላዊ ውሑዶች ይገኙበታል፣ ለምሳሌ “ፖታሽ”፣ የድኝ ውሑዶች ወዘተ።በዳሎል ረባዳ ሜዳ ይህ በትነት የተገኘ የጨው አለት ጥልቀቱ እስከ 970 ሜትር እንደሆነ ይገመታል።ይህን የጨው አለት በአካባቢው ለመከማቸት ከአንድ መቶ ሺ ዓመት በላይ እንደፈጀ ይገመታል።በዚሁ አካባቢ ወደ ደቡብ አቅጣጫ “የአሳሌ” ጨዋማ ሐይቅ ይገኛል፡፡

የጨው ባሕር ውሃ ከቀይ ባሕር ወደ ዳሎል ረባዳ መሬት ሰርጎ የገባ ሁለት መቶ ሰላሳ ሺ ዓመት ጀምሮ እስከ ሃያ አራት ሺ ዓመት በፊት ገደማ፣ ማለት 206 ሺ ዓመት ገደማ የፈጀ ፍሰት ነው።አካባቢው በተደጋጋሚ በባሕር ጨዋማ ውሃ ተጥለቅልቆ እንደነበረ ሳይንሳዊ መረጃ አለ።ቅሪት ጨውማ ውሃ ከቀይ ባሕር ሰርጎ ዛሬም “አሳሌ” የጨው ሐይቅ ይገኛል ።

አንዳንዴ ከደጋው አካባቢ ከርሰ ምድር የሚመጣ ውሃ፣ ከአካባቢው በከርሰ ምድር የሚገኝ ከፍተኛ ሙቀት ካለው አለት ጋር እየተገናኘ፣ በፍልውሃ (የፈላ ውሃ) መልክ ወደ ላይ ይዘልቃል።በዚህ መንገድ የሚፈላው ውሃ ሙቀት ከርሰ ምድር ውስጥ እንዳለ እስከ 280- 370 0C ድረስ ይዘልቃል፣ ሆኖም መሬት ላይ ሲደርስ የውሃው ሙቀት አንድ መቶ ሴልሲየስ (100 0C) አካባቢ ነው።ፍልውሃው ሙሉ በሙሉ የአሲድ ባህርይ አለው (አሲዳማ ነው)።ዳሎል በብዙ አካባቢዎች የተንጠባጠቡ ጨዋማ ኩሬዎች/ ሐይቆች የሚገኙበት ቦታ ነው፡፡

የአፍዴራ ጨዋማ ሐይቅ የሚገኘው ከባሕር ወለል በታች 112 ሜትር ገደማ ላይ ሲሆን፣ በአማካኝ ጥልቀቱ 20.9 ሜትር ገደማ ነው፣ ስለሆነም አጠቃላይ የጨዋማው ውሃ መጠን 2.4 ኩብ ኪሎ ሜትር፣ ወይም 2.4,000,000,000 ሜትር ኩብ ነው (አንድ ሜትር ኩብ አንድ ሺ ሊትር ነው)።ሐይቁ ከሁለት መቶ ሺ ዓመት በፊት አሁን ከሚገኝበት ከፍታ በ50 ሜትር ገደማ ከፍ ብሎ ነበር (ማለት ከባሕር ጠለል በታች ያለው ጥልቀቱ ቀንሶ)።ሆኖም በሳይንስ ጥናት እንደተደረሰበት፣ ሐይቁ ላለፉት አሥር ሺ ዓመታት ገደማ ይህ ነው የሚባል ለውጥ አላሳየም።ላለፉት አምሳ ዓመታት ገደማ የሐይቁ ከፍታ እንዳልተለወጠ ይታወቃል።

ጨው ለብዙ ኬሚካላዊ ውሑዶች ለመፈብረክ ለኢንዱስትሪ ግብዓት በመሆን በምግብ ማጣፈጫነት፣ ብዙ የምግብ ዓይነቶች እንዳይበላሹ (መበስበስ፣ ወዘተ) አነባሪ (Preservative) ሆኖ ማገልገል፣ ሳሙና ለመፈብረክ፣ በክረምት በረዶ በሚጥልባቸው አካባቢዎች በመንገዶች ላይ የሚከመረውን በረዶ ለማሟላት ያገለግላል፡፡

የጨው ታሪካዊ ይዘት በኢትዮጵያ

ጨው እንደገንዘብ ሆኖ በብዙ የዓለም አካባቢዎች፣ ለምሳሌ በቻይና፣ በሮማን ግዛት፣ በቅርብ ምሥራቅ እንዲሁም በሀገራችን ለዘመናት አገልግሏል።እንዲያውም በላቲን “ሳል” (“sal”) ጨው ማለት ሲሆን ፡ ይህም “ ሳላሪየም” “salarium” ለሚባል ቃል መነሻ ሆኖ፣ ብሎም ደመወዝ /Salary/ ለሚለው ቃል መሠረቱ እንደሆነ ይታወቃል።“አሞሌ ጨው” እስከ ቅርብ ዘመን በኢትዮጵያ መገበያያ ገንዘብ ነበር።ለመንግሥት ከፍተኛ የገቢ ምንጭ በመሆን አገልግሏል፡፡

የአክሱም ዘመነ መንግሥት ከተዳከመ በኋላ፣ ከብር እንዲሁም ከወርቁ የተሠሩ መሐለቅ ሲጠፉ፣ ዓይነት በዓይነት ከመለዋወጥ (barter system/trading) በተጨማሪ፣ ለዘመናት ጨው (አሞሌ ጨው) መገበያያው ሆኖ ነበር።መገበያያነቱም በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ አንሰራርቶ እንደነበረ ታሪክ ያወሳል።ከትግራይ እስከ ባሌ፣ ከወለጋ እሰከ አርጎባ፣ ተስፋፍቶ ሳለ፣ የጨው ነጋዴዎች በትናንሽ መንደሮች ሁሉ ይገኙ ነ በ ር ። የ መ ን ግ ሥ ት ግብርም ይከፈል የነበረው በአሞሌ ጨው ነበር፡፡

በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥትም ከጨው ንግድ በቀረጥ መልክ አርባ ሺ ጠገራ ብር ይሰበሰብ እንደነበረ ተመዝግቧል፣ የቀረጥ ግምት ይሰላ የነበረው፣ በአንድ የግመል ጭነት (አምስት መቶ አሞሌ ገደማ የምትሽከም) ወይም በሁለት በቅሎ/አህያ ጭነት (ከ200-250 አሞሌ የምትሸከም) አንድ አሞሌ እንዲከፈል ነበር።በሃያኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ጠገራ ብር፣ ያም የአገሪቱ በመቶ ሃያ ሰባተኛ (27%) የቀረጥ ገቢ፣ ከጨው ይገኝ ነበር።

ለዘመናት በትግራይ አካባቢ በግመል (500 አሞሌ በጭነት)፣ በበቅሎ (250 አሞሌ በጭነት)፣ በአህያ (200 አሞሌ በጭነት)፣ እንዲሁም በሰው ሸክም (50 አሞሌ በሸክም)፣ ከበረሃው (ዳሎል እና ሌሎች አካባቢዎች) ሰላሳ ሚሊዮን ገደማ አሞሌ ጨው፣ ግምቱም አንድ ተኩል ሚሊዮን ጠገራ ብር የነበረ ይጋዝ እንደነበረ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡

የዳሎል ስምጥ ሸለቆ ጉብኝት

በዚህ ጽሑፍ በብዛት የሚወሳው የዳሎል ጉብኝት በአካባቢ ጥናት ላይ የተመሠረተ ነው።ጉዞው የአካባቢ የመስክ ጥናት ሲሆን (Natural and Social Impact Assessment)፣ የጥናት ቡድን የተሠማራ “ቢ ኤች ፒ” (BHP Billiton World Exploration Inc–Ethiopia፡ Danakil Potash Explora­tion Project) የሚባል ኩባንያ፣ በዳሎል አካባቢ በፖታሽ ማዕድን ሥራ ላይ ሊሠማራ አስቦ፣ የፖታሽ ማዕድን ማምረት በአካባቢ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ ለማጥናት በዳሎል በረሃ በሥራ፣ ለአሥር ቀናት ያህል አንዳችን (ሽብሩ ተድላ) ተሰማርተን ነበር።የአካባቢ ጥናቱ የተካሄደ በጥቅምት 2003 ዓም ነበር፡፡

የጥናቱ ቡድን “ኽልተ አውላሎ” ከፍተኛ ቦታ (2400 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ) ወደ ዳሎል በረሃ (115 ሜትር ከባሕር ጠለል በታች/ በድምሩ 2515 ሜትር) ወርዶ፣ በረሃሌ ለመድረስ ሁለት ቀናት ፈጅቶበታል።ጥልቀቱ እንደወረደ ሲሰላ፣ ከጎሐ ጽዮን እስከ አባይ ድልድይ ድረስ ያለውን ጥልቀት እጥፍ ይሆናል፡፡

ደቂቀ እስጢፋኖስ (ደቂቀ እስጠፋ)

ከ”ኽልተ አውላሎ” ላይ ሆኖ ወደ በረሃው ሲወረድ፣ ደጋው ላይ በግራ በኩል ከሩቅ የደቂቀ እስጢፋኖስ (ደቂቀ እስጢፋ) ገዳም የነበረ ይታያል።ደቂቀ እስጢፋኖስ በኢትዮጵያ ክርስትና እምነትን የሞገቱ፣ አንዳንድ እምነት ቀመስ ድርጊቶችን የተቃወሙ፣ የቀን ተቀን ድርጊቶችን የማይቀበሉ፣የእምነት ምሰሶ የነቀነቁ፣ ቤተ ክህነት የማትቀበላቸው፣ እንዲያውም በኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማንያን የተወገዙ፣ በአሥራ አምስተኛው ምዕተ ዓመት ያበቡ፣ የተሐድሶ እንቅስቃሴ መሪዎች ነበሩ፡፡

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እንደዘገበው፣ የወሰዱት አቋም መለያዎች፣ ዋናዎቹ ተሐድሶ መስተጋበር ለአብ፣ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር ለሥዕል፣ ለመስቀል ለንጉሥ አንሰግድም (እራስን በሚያስጎነብስ እጅ አንነሳም)።ደቂቀ እስጢፋ የተነሱት በአፄ ይስሐቅ (1406-1421) ዘመን ሲሆን፣ “ማርቲን ሉተር” ጀርመን ላይ ተመሳሳይ ሐሳብ ይዞ ከመነሳቱ ከሠላሳ ዓመት ገደማ በፊት ነበር።እንዲያውም ከደቂቀ እስጢፋ ከመቶ አምሳ ዓመት በፊትም ተመሳሳይ እምነት የነበራቸው ታላላቅ ሰዎች በትግራይ ተነስተው ነበር፣ እነሱም ለሥዕል አንሰግድም ምክንያቱም ሥዕል ሰሌዳ ነው፣ ለመስቀል አንሰግድም፣ ምክንያቱም መስቀል የጐሎጎታ እንጨት ነው ብለው ነበር።ይህንን ታሪካዊ አካባቢ ቡድኑ እያየ ነበር ዘበጣዘበጡን (escarp­ment) መውረድ የጀመረው።ከሁለት ሺ አራት መቶ ሜትር ከባሕር ጠለል በላይ ከፍታ ጀምሮ፣ በተጠማዘዘ ጥርጊያ መንገድ ወደ በረሃው ወርዶ መሐል ላይ ሲደርስ ነበር ለማመን የሚቸግር የመሬት ገፅታን ማየት የተቻለው፡፡

የአፋር ስምጥ ሸለቆ እይታ

አፋር ስምጥ ሸለቆ ታች ደልዳላው ቦታ ቡድኑ ከመድረሱ በፊት፣ በግራ በኩል የሚታየው፣ ግዙፍ ጅብ ከመሬት የሆድ እቃ የቦጨቀው፣የተቦደሰ ገደላ ገደል ነበር።በዚህ ግዙፍ ጥረሶች በቦጨቁት፣ ግዙፍ ጣቶች ባጎሰቋቆሉት የመሬት ገፅታ በድኑ ካለፈ በኋላ፣ ደልዳላው መሬት ላይ ከመደረሱ በፊት፣ በመጀመሪያ ጎጆ ቤቶች የሚያክሉ ቋጥኝ፣ ከዚያም መለስተኛ ይዘት ያሏቸው የድንጋይ ቋጥኞች በየቦታው ተፈነጋግለው መታየት ጀመሩ።ወደ በረሃው በተዘለቀ መጠን የሚታዩት የድንጋዮች መጠን እየቀነሰ ሄዶ፣ በመጨረሻ ኮረት መሰል፣ ጠጠር፣ ከዚያም አሸዋ ላይ ይደረሳል።ግዙፍ ቋጥኞች ተቦጭቀውበት የነበረው አካባቢ የተለያየ ቀለማት ያሉት፣ በብዛት ሰማያዊና ደብዛዛ ሮዝ መሰል፣ በገደሉ ደረት ላይ ይታዩ ነበር።

ታች ደልዳለው መሬት በአሸዋ የተሸፈነ ሲሆን፣ አሸዋው በንፋስ ኃይል ተገፍቶ፣ አንዳንድ ቦታ የተወቃ “ዳቦ ጤፍ” (ጥቁር ጤፍ|) የመሰለ ተከምሮ፣ አልፎ አልፎ ጉብ ብሎ ይታይ ነበር።እንዲሁም በአሸዋ መሬት ላይ አልፎ አልፎ የበቀሉ ንዑስ የእፅዋት ዝርያዎች ይታዩ ነበር።ከደጋ ዝናብ ሲዘንብ፣ ጎርፍ የሚወርድባቸው አካባቢዎች፣ በጣም ጥቂት ቢሆኑም በአካባቢው ነበሩ።

ከባሕር ጠለል በታች ያለው አብዛኛው አካባቢ፣ እፅዋት አልባ የሆነ፣ በደቃቅ አሸዋ የተላበሰ አካባቢ ነው።ቡድኑ ጉዞ በጀመረ በሁለተኛው ቀን ሲመሽ “ሃማዴላ” ከምትባል መናኸሪያ ደረሰ።ዋናው የአካባቢ ጥናቱ ትኩረት እዚች ቦታ አካባቢ ነበር።ሃማዴላ” በ2000 ዓ.ም መባቻ አካባቢ ሁለት ግለሰቦች (ባል እና ሚስት) ከአካባቢው ተጠልፈው፣ ታፍነው፣ ተወስደው ከብዙ ሳምንታት በኋላ ነበር በነፃ የተለቀቁ።እኛም እነሱ ተጠልፈው ከተወሰዱበት መጠለያ (ሆቴል) ነበር ያረፍነው፡፡

ቡድኑ በበነጋው ጠዋት ነበር የተነሳው፣ በበረሃ እስከ ረፋድ መተኛት ያዳግታል።ከዚያም በፊት ለፊት ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ተንጣሎ ይታይ ነበረው ገፅታ ነበር ከሁሉም በላይ ለቡድኑ እንግዳ የሆነው።ዳር ላይ ሸክላ መሰል ጭቃ፣ ከዚያም በአጭር ርቀት፣ መስተዋት መሰል፣ ወደ ነጭነት ያደላ፣ በስስ ደመና የተሸፈነ የሚመስል የመሬት ገፅታ ነበር የሚታይ።ከሩቅ ሰማይና መሬት የተገናኙበትን አካባቢ ለይቶ ለማየት በጣም አዳጋች ነበር፣ ከሩቅ ያለ ነጭ መጋረጃ መስሎ ነበር አካባቢው የሚታየው።ራቅ ብለው ሲያስተውሉት በሸክላማ ጥለት የተሸመነ ሰፊ፣ ጠንፍ አልባ ጋቢ መስሎ ነበር የሚታይ፡፡

“ከሃማዴላ” ወደ ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ “አሳሌ ሃይቅ” ይታያል፣ ቀጥታውን ወደ ምሥራቅ እና ሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ የጨው አለት የሸፈነው አካባቢ ሲሆን፣ ይህን አካባቢ ከቅርብ መመልከት ቅዠት ውስጥ እንደመግባት ይመሰላል፣ በሆድ ሽብር ይለቃል፣ እይታን ያቃውሳል፣ የአንድን አካል ጥላ መሰል ገጽታ ዙሪያውን ማየት ይጀመራል።ከሁሉም አካባቢ ያለው የጨው ውሃ እንደመስተዋት ሆኖ፣ ለአንድ አካል ዙሪያውን ጥላ መሰል እይታ ያበረክታል።ይህ የጨው ሐይቅ፣ በከፊል ከታች፣ ወደ ፈሳሽነት ያደላ፤ ከላይ ጠጣር የሆነ አካባቢ ሲሆን፣ በዚህ የጨው አለት ላይ መኪና መንዳት ይቻላል፡፡፣

በጨው ላይ የሚሽከረከሩ መኪናዎች ከሩቅ ሲታዩ፣ ለአካባቢው ነፀብራቅ መንስዔ፣ በነጭ ጋቢ ላይ የሚሄዱ ሸረሪቶች ነበር የሚመስሉት።አንዳንድ በጨው ሐይቅ የቆሙ የቡድን አባላትም ትናንሽ ችካሎች መስለው ነበር የሚታዩት፣ በዚያ አካባቢ የአካልን ገፅታ ለይቶ ለማስተዋል ያዳግታል።በችካል መሰሉ አካል እና በአካባቢው ያለው የጨው ሐይቅ ድንበር በቅጡ መለየት አይቻልም።የፀሐይ ጨረርም እንዲሁም ወደ አምሳ ሴንቲግሬድ (50 0C) የሚጠጋ ሙቀት፣ ሁኔታውን ያባብሰዋል፡፡

በጨው አለት በተላበሰው አካባቢ አልፍ፣ አልፎ፣ ጉብ ጉብ ያሉ፣ ትናንሽ የቋጥኝ ድንጋይ ኮረብታዎች ይታያሉ።እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች በሕብረ ቀለም ያሸበረቁ፣ አብዛኛው ቢጫ ቀመስ የድኝ ውሑድ ሲሆኑ፣ አልፎ አልፎ ሌሎች ቀለማት ያሏቸው፣ ለምሳሌ ሰማያዊ ቀመስ (የመዳብ ውሑድ መሰል ይዘት ያላቸው)፣ ሌሎች ደግሞ ደማቅ ቀይ (የብረት ውሑድ መሰል ቀለም የተጎናፀፉ)፣ እና ሌሎች ቀለማት የተላበሱ ብዙ አካባቢዎች ይታያሉ።ያንን ዓይነት የአካባቢ ይዘት በሌሎች የቱሪስት መስህብ በሆኑ የአገራችን አካባቢዎች አይታይም።

ከሰዓት በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ፣ ከሩቅ ሲታዩ ጉንዳን መሰል አካላት ወደ ሰሜን አቅጣጫ ድንበር ሲመጡ ቡድኑ ተመለከተ፣ እየተጠጉ ሲመጡ ተከታትለው በሰልፍ በመጓዝ ላይ ያሉ ሲሆን፣ሰልፉ እየተጠጋ ሲመጣ፣ ሰልፉን የሚመሩት ወጣት ጠምዛዛ የበረሃ ጀግኖች፣ ተመሪዎች ጨው የተጫኑ ግመሎች መሆናቸውን ለመረዳት ተቻለ።ከሩቅ እነሱን (መሪዎችን) ከግመሎች ነጥሎ ለማየት ያዳጋታል።በአካባቢው የሚታይ ሌላ አካል ስለሌለ፣ ግመሎች ብቻ ናቸው በነፀብራቅ ጥላ መልክ ከሩቅ ሲያዘግሙ የሚታዩት።ያም በጨረቃ ላይ እንደሚሄድ ሰው ሰራሽ አካል ሊመሰል ይችላል፡፡

የሰልፉ ፍጥነት ሳይቀንስ፣ ሳይጨምር፣ ከአካላቱ ውጭ ባለ ኃይል የሚገፋ (በለሰስተኛ ነፋስ) ሰልፍ ነበር የሚመስለው።በጣም እየቀረቡ ሲመጡ ግመሎች፣የጨው አእማድን የተሸከሙ ግመሎች (የበረሃ ታንኮች) መሆናቸውን ቡድኑ በእርግጥ ለመረዳት ቻለ።እያንዳንዱ ግመል ከሁለት መቶ ኪሎ ግራም በላይ የወፍጮ መጅ መሰል የጨው ዓምድ ይሸከማል።ከቅርብ እርቀት ጉዞውን ለሚመለከት፣ ጉዞው፣ በእልከኛ፣ ግን የተዳከመ መሪ፣ ጉዞ የሰለቻቸውን ግመሎች የሚመራ ይመስላል።ያለማቋረጥ ተራ በተራ እግር ይነሳል፣ ከዚያም ወደፊት ይጣላል፣ ብሎምጉዞው ይቀጥላል፡፡

በዚያ ውሃ በሌለበት በረሃ፣ መሪም ተመሪም ውሃ ጥም መቋቋም አቅም አላቸው፣ መሪው በተለምዶ፣ ተመሪው በተፈጥሮ የተላበሱት አቅም ነው።ግመል ከማንኛውም አጥቢ እንስሳ በላይ ውሃ ጥም መቋቋም ችሎታ አላት፣ በበረሃው ውሃው ከአካሉ እየተነነ ሲወጣ፣ በአካሉ ውስጥ ያለው የጨው ሙዥረት (ውፍረት) አንፃራዊ ይዘት እየጨመረ ይሄዳል።ውሃ ሲገኝ ግመል ለቀናት የሚያስፈልጋትን ውሃ የመጠጣት አቅም አላት።ያ ሲሆን በአካሉ ውስጥ ያለው የጨው ሙዥረት (ውፍረት) አንፃራዊ ይዘት በጣም ይቀንሳል።ያም ሆኖ በአካል ውስጥ ያለው የፍሰት መጠን ሚዛኑን ጠብቆ፣ የአካላት ተግባር ሳይዛባ፣ ሳይቃወስ፣ ይቀጥላል፡፡

የጨው አለት በአንድ አካባቢ በምሳር (መጥረቢያ) ከተገዘገዘ በኋላ፣ ብዙ የአፋር ወጣቶች ተጋግዘው፣ ከስር አጣና አስገብተው፣ በአጣና ሰርስረው ተጋግዘው ይፈነቅሉታል።የተፈነቀለው ሰፊ የጨው ዓለት በምሳር እየተከረከመ የጨው መጅ መሰል ቅርፅ ይጎናፀፋል።እንዲሁም መጠነ ውስን የሆኑ የጨው አለት ንጣፎችን ዙሪያቸውን በመጥረቢያ ከገዘገዙ በኋላ፣ ተፈንቅለው ወጥተው፣ በመጥረቢያ የሚፈለገውን ቅርፅ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡

የጨው መጅም ሆነ አሞሌ ጨው የማምረት ተግባር ሂደት ለዘመናት የተቀየረ አይመስልም።በነጭ ሜዳ መልክ የሚታየው የጨው አለት፣ በምሳር (መጥረቢያ) ከአራት አቅጣጫ ከተቆረጠ በኋላ ተመሳሳይ ቅርጽ እንዲይዝ ይጠረባል።የጨው መጅ በግምት 30 ሳ.ሜ፣ በ15 ሳ.ሜ እና በ 5 ሳ.ሜ ገደማ ስፋት እና ወርድ ይጠረባል።ከዚያም ለዚህ ተግባር በተዘጋጀ ገመድ ብጤ ይጠቀለል እና በመደራረብ በግመል ጀርባ ላይ ይጫናል።ለዚህ የጨው መገነዣ የሚሆነው በአካባቢው በበረሃው ውስጥ የሚበቅል፣ ዘምባባ መሰል ዛፍ ቅጠል ነው የሚሸረበው።እፁ በአፋርኛ “ጎራይቶ” በመባል ሲታወቅ፣ ሳይንሳዊ ስያሜው “ሃይፌኔ ቴባቻ” (Hyphaene thebaica) ነው።የዚህ እፅ ቅጠል ጭረት በጣም ጠንካራ ስለሆነ፣ ቅጠሉ ለብዙ ዓይነት ቁሳቁስ ማበጃነት ያገለግል፣ ለምሳሌ የወተት ማለቢያ፣ የወተት/የቅቤ ማስቀመጫ፣ የውሃ መቅጃ፣ ወዘተ፡፡

ከዚያም ቡድኑ ሁለት ቀናት “ሃማዴላ” ካሳለፈ በኋላ ወደ አፍዴራ አመራ።በመንገድ ላይ ከሩቅ በስተምሥራቅ ኤርታ አሌ (Ert’ale) እሳተገሞራ ይታይ ነበር።በኢትዮጵያ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለዘመናት በተለያዩ ጊዜያት የፈነዱ ብሎም የከሰሙና የተዳፈኑ (የሚያንቀላፉ/ ያሸለቡ) እሳተገሞራዎች ይገኛሉ።አብዛኞቹ ከዘመናት በፊት የከሰሙ ቢሆኑም፣ ከሁለት መቶ ዓመት በፊት ገደማ የፈነዱ እና የተዳፈኑ ጥቂት አሉ፣ ከነሱም ቆኔ፣ ማንዳ-ኢናኪር፣ ቱሉ ሞዬ፣ ይገኙባቸዋል።ባለፈው ምዕተ ዓመት የፈነዱ እና የተዳፈኑ ብዙ ናቸው ለምሳሌ፣ አፍዴራ፣ አሌ ባጉ፣ አሉቶቱ ።በቅርብ ጊዜ ፈንድተው የተዳፈኑ፣ ዳባሁ፣ ዳፊላ እና ዳሎል እንደ ምሳሌነት ሊወሰዱ ይችላሉ።ብዙ ሰው የሚያውቀው አሁንም ሕያው የሆነውን ኤርታ አሌ (Ert’ale) እሳተ ገሞራ ሲሆን፣ ብዙ ጊዜ ስሟ የማይወሳው ዳሎል ረባዳ መሬት የምትገኘው ትንሿ “ካተሪን” (Catherine) እሳተገሞራ በዘመናችን አልፎ አልፎ ትፈነዳለች።የዳሎል ስምጥ ሸለቆ አካባቢ በብዛት በእሳተገሞራ ቅሪቶች የተሸፈነ ነው፡፡

መንገድ ላይ አንድ ቀን ካሳለፈ በኋላ በሁለተኛው ቀን አመሻሽ ላይ አፍዴራ ደረሰ።አፍዴራ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ይካሄድባት የነበረችው የበረሃ ጣቢያ ናት።ዋናው የንግድ መሠረት ጨው ማምረት ሲሆን፣ ከዚያም ተጓዳኝ አገልግሎቶች፣ ትራንስፖርት፣ ምግብ ቤትን፣ ወዘተ ያካትታል።ይህች ጣቢያ በቡድኑ በተጎበኘበት ጊዜ በደረቅ ጭነት መኪናዎች የተጣበበች ነበረች፡፡

ጨው የሚመረተው በኢንዱስትሪ መልክ ነበር።ሰፋፊ የእግር ኳስ ሜዳ የሚያክሉ ሁለት ሜትር ገደማ ተቆፍረው፣ የጨው ውሃ ከአፍዴራ ሐይቅ በፖምፓ እየተገፋ ወጥቶ፣ እነኝህን አናሳ ጥልቀት ያላቸው ሰፋፊ ጉድጓዶች እንዲሞላ ይደረጋል።በነገራችን ላይ በአፍዴራ ሐይቅ የሚገኘው ጨዋማ ውሃ፣ የጨው መጠን ባሕር ውስጥ ከሚገኘው መጠን በአምስት እጅ ይበልጣል (አምስት እጥፍ ይሆናል)፣ ምክንያቱም የሐይቁ ውሃ ለበረሃ ፀሐይ ትነት ስለሚዳረግ ነው፡፡

በነኝህ ሰፋፊ ሜዳዎች ገብቶ ለበረሃ ለፀሐይ የተጋለጠው የጨው ውሃ ተኖ እንዳለቀ፣ የጨው ንጣፍ (አለት) ብቻ ይቀራል።ይህ ሰፊ የጨው ሰፌድ አለት፣ በግንባታ መሣሪያዎች እየተከሰከሰ፣ እየተዛቀ ከጉድጓዶች ወጥቶ፣ በአሸቦ መልክ በአካባቢው እንደጠጠር ተከምሮ ይታያል፡፡

የአፍዴራ ሐይቅ ሰፊ መስተዋት መሰል ገፅታን ነው የሚያበረክት፣ በዚህ ሰፊ መስተዋት ውስጥ በስተምሥራቅ ያለውን የአፍዴራ የተዳፈነ እሳተ ገሞራ ተራራ፣ ድንኳን መሰል ቅርጽ ተጎናፅፎ ይታያል፡፡

መደምደሚያ

በአፋር ስምጥ ሸለቆ ገና ያልተጠቀምንበት መጠነ ብዙ የጨው፣ የፖታሽ ማዕድን እና የሌሎች ለኢንዱስትሪ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ኬሚካዊ ውሑዶች ክምችት፣ ብሎም እምቅ ሃብት ያለበት አካባቢ አለ።አካባቢው የብዙ የተፈጥሮ ሃብት ክምችት ስለሚገኝበት፣ በዚህ ሃብት በተገቢ መንገድ ለመጠቀም ይቻላል።ዋናው ሃብት የጨው እና መሬት ማቅለጫነት የሚውሉ ኬሚካላዊ ውሑዶች ናቸው፡፡ውሃ ወደሚገኝበት የምዕራብ እቅጣጫ ለከብት ርቢ በተለይ ለግመል፣ ለበግና ፍየል ርቢ፣ በጣም ምቹ አካባቢዎች አሉ፡፡

እንዲሁም የአካባቢው ለየት ያለ ውበት የቱሪስት መስህብ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፣ አሁንም ቢሆን በመጠኑ እያገለገለ ነው።የስነ ሰብኣት (Anthropology) ምርምር ጥናት በሰፊው ሊካሄደበት የሚችል፣ ብዙ የሕያው ቅሬት አካላት መገኛ አካባቢ ነው፣ “ሉሲም”/ “ድንቅነሽ” ከዚሁ አከባቢ ነው የተገኘችው።ስለሆነም አከባቢው ለሳይንሳዊ ምርምርም፣ እንዲሁም ለሳይንሳዊ ጉብኝት ብዙ ጠቀሜታን ያበረክታል፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው በመጠኑም ቢሆን፣ አከባቢው የቱሪስት መስህብ በመሆን እያገለገለ ነው።ሆኖም የጉብኝቱ አያያዝ መስተናገድ ያለበት ሥርዓት በጥሞና ተጠንቶ ነው ወደ ተግባርነት መለወጥ የሚገባው፣ አሁን ያለው አያያዝ በሥርዓት የተከለለ አይመስልም።እንዲሁም በቱሪስት መልክ የሚደረጉ ጉብኝቶች ሆኑ፣ በተፈጥሮ ሃብት መጠቀም (ለምሳሌ ማዕድን) በተገቢው መንገድ ካልተከናወኑ ያልታሰቡ የአካባቢ ተግዳሮቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡

የበረሃው የወደፊት ዕጣ ፈንታ ባይታወቅም፣ አንዳንድ ግምታዊ አስተያየቶች መቅረብ ይበጃል የሚል እምነት አለን።አካባቢው የተዳፈኑ/ ያንቀላፉ እሳተ ገሞራዎች ያሉበት አካባቢ እንደመሆኑ፣ በአካባቢው ያልታሰበ ከፍተኛ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ከተከሰተ፣ የአካባቢውን ይዘት በጠቅላላ ሊያቃውሰው ይችላል፡፡

ወደፊት የሚከሰተው ባይታወቅም፣ አሁን በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመሥርቶ መሪ እቅድ ተነድፎ፣ በእቅዱ መሠረት አካባቢው ደረጃ በደረጃ ሊለማ የሚችል፣ ብሎም ለሀገር ብዙ ሃብት የሚያበረክት ይሆናል ፡፡

ሽብሩ ተድላ (ፕሮፌሰር ኤሜሪተስ) አና ገዛኸኝ ይርጉ (ፐሮፌሰር)