አዲስ ሥርዓተ-ትምህርት ለምን ?

ሥርዓተ ትምህርት በትምህርት ተቋማት አማካይነት እንዲመጣ የሚፈለገው ለውጥ የሚመራበት ሳይንስ ነው። ለውጡ ደግሞ በተማሪዎች በኩል መታየት አለበት። የባህርይ፣ የአመለካከት፣ የክህሎት መዳበር፣ዕውቀት የመፍጠር አቅም ለውጦች የሚመሩበት ሥርዓት፤ የትምህርት ተቋማት አስፈላጊውን አመለካከት እንዲያመጡ፣ተማሪዎች ዕውቀት እንዲፈጥሩ እና የክህሎት መዳበር እንዲኖራቸው ለማድረግ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ታቅዶ ትምህርት ቤቶች የሚመሩበትና ተግባራዊ የሚደረግበት መንገድ ነው ሥርዓተ ትምህርት።

በሥርዓተ ትምህርቱ እንዲመጣ የሚፈለገው ለውጥ ማዕከል የሚያደርገው በአንደኛ፣ በሁለተኛ እና በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ከሚገኙ ተማሪዎች የአካል፣ የመንፈስና የአዕምሮ ዕድገት ጋር የሚያያዝ መሆን እንዳለበት የዘርፉ ምሑራን ይገልፃሉ። ተማሪዎችን በባህላቸው እንዲቀረጹ እና እንዲያድጉ የሚያግዝ፣ልጆች ሲያድጉ በአካል፣ በአዕምሮና በስሜት፣በሀገራቸው ባህል፣ ወግና ሥርዓት ስር እንዲሰዱ ለማድረግ ሥርዓተ ትምህርቱ ማኅበረሰቡንም ከግምት ማስገባት ይኖርበታል። ሥርዓተ ትምህርት ከሀገሪቱ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ፍልስፍና ጋርም መያያዝ መቻል አለበት። ሥርዓተ ትምህርት የአንድ ሀገር ማኅበረሰብ የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ፣ ትውልዱ የሚገኝበትን የሥነ ምግባርና የግንዛቤ፣ እንዲሁም የማኅበረሰቡን ሁለንተናዊ የአኗኗር ደረጃ ታሳቢ አድርጎ ይቀረጻል። በወቅቱ የሚገኘውን የማኅበረሰቡን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የዕድገት ደረጃ ከግምት ውስጥ ያስገባ፣በተለይም ሥርዓተ ትምህርት የነገውን ማኅበረሰብ የዕድገት ደረጃ የሚደግፍና የሚያፋጥን የትምህርት ሥርዓትን ታሳቢ ያደርጋል።

የትምህርት ዓላማም ለዕድገት፣ ለብልጽግና፣ ለለውጥ እና ለሽግግር ማብቃት ስለሆነ፣ትምህርት ከተማሪዎች እድገት፣ከወቅቱ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለውጥ እና ከማኅበረሰቡ እሴት ጋር ተያይዞና ተጣጥሞ የሚሰጥ መሆን አለበት። በመዋዕለ ሕጻናት፣ በአንደኛ፣ በሁለተኛ እና በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሚሰጥ ሥርዓተ ትምህርትም በመሠረታዊነት ከተማሪዎች የተለያዩ የዕድገት ደረጃዎች ጋር አብሮ የሚሄድ መሆን እንዳለበት ግልፅ ነው።

ከዚህ አንፃር የቆየው ሥርዓተ ትምህርት በርካታ ችግሮች እንደነበሩበት በጥናት ተረጋግጧል። በተካሄደው ጥናት የተገኘው ውጤት በዋናነት አራት መሠረታዊ ችግሮች የነበሩበት መሆኑን በአራዳ ክፍለ ከተማ የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ይመር ይገልጻሉ። የትምህርት ሥርዓቱ የሕግ ማዕቀፍ የሌለው መሆኑ፣ ሥርዓተ ትምህርቱ በራሱ ክለሳ የሚያስፈልገው መሆኑ፣ የትምህርት አደረጃጀቱ በተለይም መዋቅሩ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር መከለስ ማስፈለጉ እና የትምህርት ፖሊሲም ለውጥ ማስፈለጉ ባለፉት ዓመታት ይተገበር የነበረው ሥርዓተ ትምህርትን ለመቀየር ምክንያት ሆነዋል።

አቶ ወንድሙ በዋናነት የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ ያስፈለገበትን መሠረታዊ ጉዳዮች ሲያብራሩም፣ አንደኛው ሥርዓተ ትምህርቱ በመጽሐፍ ዝግጅቶቹ የይዘት መጨናነቅ ይበዛበታል። ሁለተኛው ጉዳይ የሥርዓተ ትምህርቱ ይዘት ትኩረቱ ከተማሪዎች እና ከኅብረተሰቡ ሕይወት ጋር መቆራኘት አለመቻሉ ነው። ይህ ማለት ደግሞ የትምህርቱ ትኩረት በተማሪዎች ዕውቀት ላይ ብቻ እንጂ ተማሪዎቹን ወደ ተግባር የሚመራ አልነበረም። ሌላው ችግር ለሀገር በቀል ዕውቀት የሰጠው ቦታ ዝቅተኛ በሚባልበት ደረጃ ላይ መገኘቱ ነው። የሥነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርትም ትኩረት የሚያደርገው መብት እና ግዴታዎች ላይ በመሆኑም ለግብረገብ ትምህርት የሚፈለገውን ቦታ እና ትኩረት የሰጠ አልነበረም። ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች፣ በተለይም ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውን ተማሪዎች ሥርዓተ ትምህርቱ አላካተታቸውም የሚሉ ይገኙበታል።

አቶ አገኘሁ መለሠ ደግሞ በዳግማዊ ምኒልክ አጸደ ሕጻናትና የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት የመማር ማስተማር ምክትል ርዕሰ መምህር ናቸው። እንደሳቸው አስተያየት፣ የቆየው ሥርዓተ ትምህርት ከሥነ ምግባሩ ላይ ትኩረት አድርጎ ባለመሥራቱ ምክንያት ሀገራችን የሰለጠነ የሰው ኃይል ሳታጣ፣ ሥነ ምግባር የጎደለው ምሑር እየተፈጠረ ሀገሪቱን ለከፍተኛ ብጥብጥ ዳርጓታል ይላሉ። አቶ አገኘሁ አያይዘውም፣ አንዳንድ የትምህርት ዓይነቶች የተማሪዎችን አቅም የማያገናዝቡ፣ የትምህርት አሰጣጣቸውም ከከባዱ ወደ ቀላሉ የመሄድሂደት ስለነበረው በችግርነት የሚነሱ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

የቆየው ሥርዓተ ትምህርት በአብዛኛው፣ በተለይም በአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች የማንበብ፣ የማስላት እና የመጻፍ ችግር የነበረበት መሆኑን የሚገልጹት ደግሞ በአጼ ናኦድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ አሳየ የኋላሸት ናቸው። የመጽሐፍቶቹ አዘገጃጀትም ተማሪ ተኮር ከመሆን ይልቅ አስተማሪ ተኮር የነበሩ መሆኑን በተካሄደው ጥናት መረጋገጡን ያብራራሉ።

ዶ/ር በቀለ ወርቄ ደግሞ በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ መምህር፣ ተመራማሪ፣የትምህርትና ስነ ባህርይ ጥናት ኮሌጅ ዲን ናቸው። እንደ ዶ/ር በቀለ አስተያየት ደግሞ የቆየው ሥርዓተ ትምህርት የሚከተሉት ችግሮች ነበሩበት፣ የመጀመሪያው ችግር ከእውነታዎች፣ ከመርሆዎች፣ ከንድፈ ሃሳቦች ጋር በተያያዘ፣ተግባርን ያገለለ የይዘት መታጨቅ ነው። ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ማነብነብ፣መግለጽ እና ችግርን መተንተን ቢችሉም ችግርን የመፍታት ብቃት ግን የላቸውም። ምክንያቱም ችግር እንዲፈቱ ሆነው አልተለማመዱም፣ንድፈ ሃሳቡን ወደ ትግበራ እንዲቀይሩት አልተማሩም። ስለዚህ ተማሪው ችግር ያወራል እንጂ ችግር ግን አይፈታም። በዋናነት ደግሞ ሥርዓተ ትምህርቱ የምዕራቡ ዓለም ተጽዕኖ ያጠቃው ስለነበር የማኅበረሰቡን ችግር በመፍታት እና የግለሰብን ሕይወት በማሻሻል ላይ ትኩረት አላደረገም።

ሥርዓተ ትምህርቱ የሥነ ምግባር ትምህርት ይዘትን በአግባቡ ባለማካተቱ ተማሪዎች ከባህል ያፈነገጡ፣ትውልዱን ደግሞ ከኢትዮጵያዊነት እንዲርቅ አድርጎታል። ችግሩ ደግሞ በየቦታው የሚስተዋል እና በወላጆች፣በመምህራን፣ እንዲሁም በማኅበረሰቡ የሚታይ ነበር። ይህ ደግሞ ሕጋዊነትን፣በተለይም አብሮ መኖርና መ ብ ላ ት ፣ መ ተ ባ በ ር ፣ መ ከ ባ በ ር ፣ መ ደ ጋ ገ ፍ የሚባለውን ኢትዮጵያዊነትን አጥፍቶታል። በአብሮነት ውስጥም ልዩነት መኖሩን መገንዘብ እንዳይችሉ ሆነዋል።

የሕይወት ዘመን ክህሎትን በተገቢ ደረጃ ትኩረት ባለመስጠቱ፣ተማሪዎች ከሰው ጋር መግባባትና ሃሳባቸውን የመግለጽ ችግርም ታይቶባቸዋል። የኢትዮጵያን ሕዝብ ለዘመናት በሰላም አብሮ ላኖረው ለባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት፣ለሀገር በቀል ዕውቀት ቦታ አለመስጠቱም ሌላው የሚነሳ ችግር ነው። ተከታታይ የትምህርት ምዘናን በተመለከተም በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ይገለጽ እንጂ በተግባር እየተሰጠ አልነበረም። ተማሪዎቹን ዘላቂነት ባለው መልኩ በመፈተን ምን ውጤት አገኙ፣ምን ደካማ ጎን ነበረባቸው፣ምን መሻሻል አለበት፣ተማሪዎቹ እንዴት ይደገፉ የሚለው ነገር በአግባቡ አልተዳሰሰም።

በመሆኑም ይህን የትምህርት ጥራት ችግር ለማሻሻልና ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ለመስጠት፣ ትምህርት ሚኒስቴር አዲስ ሥርዓተ ትምህርት አዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ተገብቷል። በያዝነው 2015 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው አዲሱ ሥርዓተ ትምህርትም ተገቢውን ዕውቀትና ክህሎት ከሥነ ምግባር ትምህርት ጋር አጣምሮ ለመስጠት የሚያስችል ነው። በትምህርት ዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረውም በትምህርት ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ዴስክ ኃላፊ፣ ወ/ሮ ዛፉ አብርሃ መስከረም 6 ቀን 2015 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አብራርተዋል።

እንደ ወ/ሮ ዛፉ አብርሃ ማብራሪያ፣ አምስት ዓመታትን በፈጀውና ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በርካታ ነባር ችግሮችን ይፈታል ተብሎ ይታሰባል። በዚህም በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ግብረገብ፣ ሀገር በቀል ዕውቀት፣ ሙያና የቀለም ትምህርት፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርትና ተግባር፣ ጥናትና ምርምር ትኩረት አግኝተዋል። ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ላሉ የክፍል ደረጃዎች ትምህርት በአፍ መፍቻ ቋንቋ ይሰጣል። ከሰባተኛ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል ያሉት ተማሪዎች በእንግሊዘኛ ቋንቋ ይማራሉ። ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ተማሪዎች የእንግሊዘኛ ቋንቋን እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ይወስዳሉ።

በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ሦስተኛ ክፍል ላይ በክልሎቹ ውስጥ በስፋት የሚነገረውን ተጨማሪ ቋንቋ በመምረጥ ተማሪዎቹ እንደ አንድ የትምህርት አይነት እንዲወስዱ ይደረጋል። 10ኛ ክፍል ይሰጥ የነበረው ሀገራዊ የመልቀቂያ ፈተና ቀርቶ፣ በክልል ደረጃ ስድስተኛ ክፍል፣ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ስምንተኛ እና 12ኛ ክፍል ላይ ይሰጣል። ሦስት ዓመት የነበረው የተማሪዎች የዩኒቨርስቲ ቆይታ፣ዝቅተኛው የቆይታ ጊዜ አራት ዓመት ይሆናል። ለሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በመጀመሪያ ዓመት ከሚሠጡ የትምህርት ዓይነቶች ውስጥ እንደ ጂኦግራፊ፣ አንትሮፖሎጂ፣ ሶሺዮሎጂና ሥነ-ምግባር የመሳሰሉት ይካተታሉ። ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል የግብረገብ፤ የማኅበራዊና የተፈጥሮ ሳይንስ ውሑድ ትምህርትም ይሰጣል።

ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል በተናጠል ይሰጡ የነበሩት ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪና ባዮሎጂ አጠቃላይ ትምህርት ተብለው፣ እንዲሁም ጂኦግራፊና ሂስትሪም ተቀናጅተው ይሰጣሉ። የእርሻ ትምህርት፣ አካውንቲንግ፣ ቢዝነስና ጄኔራል የሆነው የሥራና ክህሎት ትምህርት በሙያ ትምህርትነት ይካተትላቸዋል። 11ኛ እና 12ኛ ክፍሎች ላይ የጤና፣ የግብርና፣ የእርሻ፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ቢዝነስ፣ አካውንቲንግ የመሳሰሉት የሙያ ትምህርቶችን እንዲማሩ ይደረጋል።

የዘጠነኛና የአስረኛ ክፍልን፣ እንዲሁም ከአንድ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያሉ የተመረጡ አምስት የትምህርት አይነቶችን የመጽሐፍት ዝግጅት ትምህርት ሚኒስቴር ሲያከናውን፣ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውን የትምህርት መጽሐፍት ክልሎች በራሳቸው ባህልና አካባቢያዊ ሁኔታ ቃኝተው ያዘጋጃሉ።

ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ አገኘሁም፣ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ከቆየው በተለየ መንገድ፣በተማሪዎች ሥነ ምግባር ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ፣ከንድፈ ሃሳብ በዘለለ ተግባር ላይ ያዘነበለ፣ በተለይም ተማሪዎች ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍል ላይ ሲደርሱ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የሚያግዝ መሆኑን ያስረዳሉ። ከዚያም አልፎ የአንድ ሀገር ትምህርት የአገሪቷን ነባራዊሁኔታ፣ወግ፣ባህል፣እሴት፣ አኗኗር፣ወዘተ መሠረት አድርጎ መቀረጽ ስለሚኖርበት ሀገር በቀል ቋንቋዎች እንዲካተቱበት የተደረገበት ሁኔታ በጠንካራ ጎኑ ሊታይ እንደሚገባው ይናገራሉ።

በተመሳሳይ መንገድ ርዕሰ መምህር አቶ አሳየም፣ በተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናና በተካሄደው ውይይት አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ተማሪዎች የሚማሩትን ትምህርት ከገሃዱ ዓለም ጋራ አገናዝበው እንዲማሩ በማድረግ ለፈጠራ ሥራ ትኩረት የሰጠ መሆኑን ተረድተዋል። የመጽሐፍቶቹ አዘገጃጀትም ተማሪዎች የተማሩትን የንድፈ ሃሳብ ትምህርት ወደ ተግባር እንዲቀይሩ የሚጋብዙ ሆነው አግኝተዋቸዋል። እንደማሳያ የሚያቀርቡትም የቴክኒክና ሙያ ትምህርት በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ መካተቱ እና የአይ ሲ ቲ ትምህርት በመካከለኛ የትምህርት ደረጃ እንዲሰጥ መደረጉን ነው።

አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በዕቅድ ደረጃ ሲታይ ጥሩ መሆኑን የሚገልጹት ደግሞ ዶ/ር በቀለ ናቸው። እንደ ዶ/ር በቀለ ሃሳብ፣ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በዋናነት ለመዋዕለ ሕጻናት ትምህርት ትኩረት ሰጥቷል። ይህ የትምህርት ደረጃ ደግሞ የልጆች የመማር ፍላጎት የሚቀሰቀስበት፣እንዲማሩ የሚዘጋጁበት እና አካባቢያቸውን እንዲያውቁ የሚታገዙበት ስለሆነ በጣም ወሳኝ ነገር ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርትም መዋዕለ ሕጻናት 2 ዓመት ከተማሩ እና በአግባቡ ከተዘጋጁ በኋላ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል እንዲማሩ ተደርጓል። ይህ ደግሞ ትምህርት ለሁሉም የሚለውን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን አድርጎታል። 10ኛ ክፍል ላይ ይሰጥ የነበረው የሁለተኛ ደረጃ ትምርት ማጠናቀቂያ 12ኛ ክፍል መሰጠቱ ተማሪዎችን ሁለት ዓመት በአካልና በአዕምሮ እንዲጎለብቱ ስለሚያደርጋቸው በትምህርት ውጤታቸው ላይ ለውጥ ያመጣሉ። በአጠቃላይም አዲሱ የትምህርት መዋቅር ከ70 በመቶ በላይ ከሚሆኑ አገሮች የትምህርት መዋቅር ጋር ስለሚመሳሰል እንደባለሙያ ሳየው የሚደገፍ ነው ይላሉ።

ከይዘት አኳያም ሥርዓተ ትምህርቱን ዶ/ር በቀለ ሲዳስሱት፣የሥነ ምግባር ትምህርት ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል መሰጠቱ ውጤቱን ዘላቂ የማድረግ ዕድሉ ሰፊ ነው ይላሉ። የቴክኒክና የሙያ ትምህርትን 7ኛ እና 8ኛ ክፍል ላይ እንዲሰጥ መደረጉም ተማሪዎች 8ኛ ክፍል ላይ ባይሳካላቸው በአገኙት የቴክኒክ ዕውቀት በመታገዝ የሆነ ዳቦ፣የሆነ እንጀራ መቁረስ እንዲችሉ ያደርጋቸዋል። በአጠቃላይ የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ጠንካራ ጎኖች የሚመነጩት ከቆየው ሥርዓተ ትምህርት ችግሮች በመሆኑ ጠንካራ ጎኖቹን ያጎላቸዋል በማለት ያብራሩታል።

የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ቅድመ ዝግጅትና አተገባበርን በተመለከተ ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ አገኘሁ ሲያብራሩ፣ በ2014 በጀት ዓመት የሙከራ ጊዜ ስለነበረ በመማር ማስተማሩ ሂደት የተወሰነ ልምድ እና ተሞክሮ አግኝተዋል። በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ምንነትና አተገባበር ዙሪያም ለትምህርት አመራሩ ስልጠና ተሰጥቶ ውይይት ተካሂዷል። ለተማሪዎችም በተመሳሳይ መልኩ የትውውቅ ፕሮግራም ተዘጋጅቶላቸዋል። መምህራን ደግሞ በሁለት ዙር ስልጠና ወስደዋል። በአፋን ኦሮሞ እና በአማርኛ በሁለቱም ቋንቋዎች መጽሐፍቶች ተዘጋጅተው በሶፍት ኮፒ በየትምህርት ቤቶች ተደራሽ ሆነዋል።

ርዕሰ መምህር አቶ አሳየም የምክትል ርዕሰ መምህር አቶ አገኘሁን አስተያየት በመደገፍ፣ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ መስጫ ስልጠናዎች መስጠታቸውን ይናገራሉ። በተካሄዱ የግንዛቤ ፈጠራ መድረኮችም አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ከቅርጽም ሆነ ከይዘት አኳያ ምን እንዳካተተ፣ የማስተማሪያ መጽሐፍት ምን እንደሚመስሉ፣ መምህራን ለሰን ፕላን እንዴት ማዘጋጀት እንደሚኖርባቸውና ማስተማር እንዳለባቸው፣ ተማሪዎችን እንዴት በደረጃቸው ከፍለው ማስተማርና መደገፍ እንደሚገባቸው በመድረኮቹ መነሳታቸውን ያስረዳሉ።

ለተማሪዎችም ምን ዓይነት ትምህርት፣ በምን ዓይነት የትምህርት ፕሮግራም እንደሚማሩ የማሳወቅ ተግባር መከናወኑን ርዕሰ መምህር አቶ አሳየ ይገልጻሉ። በት/ቤት ደረጃም አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት አስመልክቶ ከመምህራን ጋር ውይይት ተደርጓል። በተካሄደው ውይይትም ማን ምን ቢያስተምር የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት አተገባበር ውጤታማ ሊሆን ይችላል የሚለው ጉዳይ ዋና የመወያያ ርዕስ እንደነበር ይናገራሉ። በተለይም በሙያው የተመረቁ መምህራን የሌሉባቸው የትምህርት ዓይነቶችን ማን የትኛውን ቢይዝ ውጤታማ መሆን ይቻላል በሚለው ጉዳይ ላይበመወያየት በፍላጎት ላይ የተመሠረተ የመምህራን ምደባ ማድረግ ተችሏል።

በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት አተገባበር ላይ ድጋፍና ክትትል ማድረግን በተመለከተ ርዕሰ መምህር አቶ አሳየም፣ የየትምህርት ዓይነቱ ኃላፊዎች በየሳምንቱ በትግበራው ወቅት ሲያስተምሩ ያጋጠማቸውን ችግር ለመለየት በቃለ ጉባኤ የተደገፈ ውይይት እንደሚያካሂዱ ይናገራሉ። እንደ አስተዳደር ደግሞ በየ15ቀኑ የዲፓርትመንት ኃላፊዎችን በመያዝ በሚካሄድ የውይይት መድረክ ያጋጠሙ ችግሮችንና የተፈቱበትን መንገድ፣ የተገኙ ስህተቶች ካሉም በምን መልኩ መስተካከል እንደሚኖርባቸው የሚያመላክቱ ሃሳቦችን በቃለ ጉባኤ እንደሚወያዩ ይገልጻሉ። አሁን ላይ ወደ ትግበራ ሲገቡ፣ በተለይም ከሥርዓተ ትምህርቱ ቅበላና ቅድመ ዝግጅት ጋር በተያያዘ በከተማ አስተዳደር፣በክ/ከተማና በወረዳ ደረጃ ድጋፍና ክትትል ተደርጎላቸዋል፤ ግብረ መልስም ተሰጥቷቸዋል። በተሰጠው ግብረ መልስ ግን በጎላ መልኩ የታየ ክፍተት ባለመኖሩ የትግበራ ሂደታቸው ደህና መሆኑን ተገንዝበዋል።

እንደ አራዳ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽ/ ቤት የሙከራ ትግበራ ውስጥ ሲገባ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናል የሚል እምነት እንደሌለው አቶ ወንድሙ ያብራራሉ። ስለሆነም የሥርዓተ ትምህርት ትግበራውን በሁሉም የመንግሥትም ሆነ የግል ትምህርት ቤቶች በተጠናከረ ድጋፍና ክትትል መመራት እንዳለበት በዕቅዳቸው ላይ በግልጽ ማስቀመጣቸውን ያስረዳሉ። በክፍለ ከተማ ደረጃ የሱፐር ቪዥን ቡድኖች ስላሉ በእነሱ አማካይነት አተገባበሩ እየተፈተሸ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ አሠራር ተቀምጧል።

እንደ አቶ ወንድሙ ማብራሪያ፣ በክትትልና ድጋፍ ተግባር መምህራን የሚያስተምሩትን መጽሐፍ ከይዘት እና ከሌሎች ጉዳዮች አንጻር የሚገመግሙበት መስፈርት ተዘጋጅቶ እንዲወርድላቸው ተደርጎ ግምገማ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ከሰዓት፣ ከይዘት፣ከያዘው ጭብጥ አንጻር ማነቆ የሚሆኑ ነገሮች ካጋጠሙ እየተከታተሉ ለማስተካከል እንዲቻል የመጽሐፍ ግምገማ ተግባርን እንዱ የትኩረታቸው አካል አድርገውታል። በየዕለቱና በየሳምንቱ ታቅደው ለሚከናወኑ ተግባራትም በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ እየተከናወኑ ስለመሆኑ ቅጽ አዘጋጅተው በማውረድ የሚከታተሉበት እና ክፍተቶች የሚስተካከሉበት አሠራርም ተፈጥሯል።

የመማሪያ መጽሐፍት ሙሉ በሙሉ ቀደም ብለው ባለመድረሳቸው ምክንያት ዓመታዊ ዕቅዳቸውን አቅደው ወደ ሥራ ለመግባት መቸገራቸውን ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ አገኘሁ ይናገራሉ። ወደየትምህርት ቤቶች የደረሱት የእያንዳንዱ የትምህርት ዓይነት ሁለትና ሦስት ቻፕተሮች ብቻ ለዚያውም በሶፍት ኮፒ ነው። በእርግጥ አሁን ላይ ስርጭት በመጀመር ላይ እንደሚገኝ የሚገልጹት አቶ አገኘሁ፣ ስርጭቱም ቢሆን በግዴለሽነትና በተለያዩ ምክንያቶች የመዘግየትና ያለመድረስ ሁኔታ ስለሚኖር በሥርዓተ ትምህርቱ አተገባበር ላይ እንደ ስጋት ያነሱታል። የተማሪዎች ቴክስትም በእጃቸው አለመድረሱ አሁንም በችግርነት የሚያዩት ጉዳይ ነው። በመሆኑም የመጽሐፍት ዝግጅትም ሆነ ስርጭት ቶሎ አለመከናወኑ በትምህርት አሰጣጡ ላይ ራሱን የቻለ አሉታዊ ተጽዕኖ ስለሚኖረው በየደረጃው የሚገኙ አካላት ሊያስቡበት እንደሚገባ ያሳስባሉ።

በተመሳሳይ መንገድ ርዕሰ መምህር አቶ አሳየም፣ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት አተገባበር ዙሪያ ከመጽሐፍት ህትመትና ስርጭት ጋር የተያያዘውን ጉዳይ በችግርነት ያነሱታል። ሌላው እንደ ቴክኒክና ሙያ፣ የዕይታ መስክና ክንውን ጥበብ የመሳሰሉ የትምህርት ዓይነቶች በሙያው የሰለጠኑ መምህራን ያለመኖር የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ሂደት ችግሮች ናቸው ብለው ያቀርቧቸዋል።

በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ከታዩ ክፍተቶች መካከል አንዱ በአሁኑ ወቅት በዓለም ደረጃ ትልቁና አንገብጋቢ ጉዳይ የሆነውን የአካባቢ ጥበቃ ተግባር፣ተማሪዎች ከታችኛው ክፍል ጀምረው ዕውቀት ይዘው ማደግ እንዲችሉ በሥርዓተ ትምህርቱ አለመካተቱ ነው። የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት ደግሞ በሥርዓተ ትምህርቱ አካቱ የሚል እና የወደፊቱም የሰው ልጅ ትልቁ ፈተና በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባ የሚሉት ዶ/ር በቀለ ናቸው። ከሥርዓተ ትምህርቱ አተገባበር ስጋቶች መካከል ደግሞ የመምህራን ፍልሰት መሆኑን ያነሳሉ። በመጀመሪያ ደረጃ መምህራን ሙያውን መርጠውት ሳይሆን ምርጫ ሲያጡ የሚማሩትና በሙያው ላይ የሚቆዩትም ወደ ሌላ ሙያ እስኪሄዱ ድረስ ለመሸጋገሪያነት ነው ይላሉ።

ስለዚህ የመምህራን ችግር፣ በተለይም በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ለተካተቱ አዳዲስ የሙያ ትምህርቶች የሰለጠነ የሰው ኃይል ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ሲታይ ችግሩን የከፋ እንደሚያደርገው ይናገራሉ።

እንደ ዶ/ሩ ገለጻ፣የሰው ሀብት ልማት ለሀገር ዕድገት ቁልፍ ነገር ነው ካልን እና ውጤታማ ለውጥ ማምጣት ከተፈለገ ለትምህርት ዘርፉ ትኩረት በመስጠት የበጀት ጉዳይን መጨመር ያስፈልጋል። በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ዙሪያም ማኅበረሰቡ በቂ ግንዛቤ መያዝ ይኖርበታል። መምህራን ራሳቸው በአግባቡ መገንዘባቸውን ማረጋገጥ ይገባል። የትግበራው አካል የሆኑ ባለድርሻ አካላትም ሥርዓተ ትምህርት ምንድነው፣በሀገር ደረጃ ምን ታስቧል፣ምን ዓላማ አለው፣ልጆች ምን ይማራሉ፣መቼ ይማራሉ፣መቼ ምን ይደረጋል የሚለውን ግንዛቤ ለማስጨበጥ በስፋት መሠራት ይኖርበታል። የግል ትምህርት ቤቶችም የራሳቸው ሥርዓተ ትምህርት ያላቸው በመሆኑ የመንግሥትን ሥርዓተ ትምህርት ለመተግበር ፍላጎት ማጣት ይታይባቸዋል። ስለሆነም በሀገሪቱ ሥርዓተ ትምህርት ለማስተማር ተስማምተው ት/ቤት እስከከፈቱ እና ፈቃድ እስከወሰዱ ድረስ የተዘጋጀውን ሥርዓተ ትምህርት ላለመቀበል ጥረት ማድረጋቸው የሕግ ጥሰት እና ወንጀልም ጭምር በመሆኑ ከአሁኑ መስተካከል አለበት፡

እንደ አራዳ ክፍለ ከተማ ጽ/ቤት በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የ2014 ዓ.ም የሙከራ ትግበራ ሁለት በአማርኛና ሁለት በአፋን ኦሮሞ ሥርዓተ ትምህርት የሚሰጥባቸው አራት ት/ ቤቶች እንደነበሩ አቶ ወንድሙ ገልጸዋል። በእነዚህ አራት ት/ቤቶች ከሚገኙ መምህራንንና የትምህርት አመራሩ ጋር በለውጡ ላይ እና የሥርዓተ ትምህርቱን የመጽሐፍት ትውውቅ መደረጉን በጥንካሬ ያነሱታል። በሂደቱም መጽሐፉን ከሽፋን ጀምሮ እስከ ውስጠኛው ይዘት ድረስ ያሉ ችግሮችን አሳይቷቸዋል። ይህም ወደ ዋናው የመጽሐፍ ሕትመት ከመገባቱ በፊት የታዩ ክፍተቶችን ለማወቅ፣ግብረ መልስ ለመስጠትና ለማስተካከል በማገዝ ጥሩ ልምድ ተወስዶበታል ይላሉ።

ይሁን እንጂ በሥርዓተ ትምህርቱ አተገባበር ሂደት ሁለት መሠረታዊ ክፍተቶች መገኘታቸውን አቶ ወንድሙ ይናገራሉ። የመጀመሪያው ለአዳዲስ የትምህርት ዓይነቶች በሙያው የሰለጠኑ የመምህራን እጥረት ማጋጠሙ ነው። ሁለተኛው ችግር ደግሞ መጽሐፍ በበቂ ሁኔታ ለመምህራንም ሆነ ለተማሪዎች በበቂ ሁኔታ ማድረስ አለመቻሉ ነበር። በትግበራ ሂደቱ ያጋጠሙትን ችግሮችን ለማቃለል የተወሰዱ መፍትሔዎችን በተመለከተም አቶ ወንድሙ ሲያብራሩ፣ በመጀመሪያ ደረጃ በእጃችን ላይ ምን አለን የሚለውን በማየት የመጽሐፍት እጥረትን ለማሟላት እየሠሩ ይገኛሉ። በሙያው የሰለጠነ የባለሙያ እጥረትን ለማቃለልም ከመምህራን መካከል በተጓዳኝ በሙያው የሰለጠኑትን በመለየት በምርጫቸው እንዲያስተምሩ የማድረግ ሥራ ሠርተዋል። በተለይም ከአይ ሲ ቲ ሙያ ጋር የተያያዙትን ለመመለስ ጥረት ተደርጓል። የባለሙያ እጥረት ያሉባቸውን የትምህርት ዓይነቶችም በቅጥር ለማሟላት ከተማ አስተዳደሩ ጥረት እያደረገ ይገኛል። ሌላው አማራጭ መፍትሔ ተደርጎ የተወሰደው ደግሞ መምህራንን በአጫጭር ስልጠናዎች በሙያው ብቁ ማድረግን ነው።

ትምህርት ለአንዲት ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና ያለው ጉዳይ መሆኑ አያጠያይቅም። የሀገር ዕድገትም ሆነ ስልጣኔ ያለ ትምህርት አይታሰብም። የታሰበውን ዜጋ ለመፍጠር ደግሞ በአግባቡ የተዘጋጀና ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታውን ከግምት ያስገባ ሥርዓተ ትምህርት ሊኖር የግድ ነው። በዚህ ረገድ ትምህርት ሚኒስቴር በጥናት የተደገፈ የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ አድርጓል። ከዚያም አልፎ ወደ ሙሉ ትግበራ መግባቱም የማያበረታታ ነው። ይሁን እንጂ በትግበራ ሂደቱ የታዩ ጠንካራ ጎኖች እንደተስተዋሉ ሁሉ ችግሮችም አልታጡበትም። በተለይም ከመጽሐፍ ዝግጅትንና ስርጭት፣ እንዲሁም ከመምህራን ጋር የተያያዙ ችግሮች ጊዜ ሊሰጣቸው የሚገባ አይደለም። ስለሆነም በየደረጃው የሚገኘው ጉዳዩ የሚመለከተው ባለድርሻ አካላት ሁሉ፣ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በአግባቡ እንዲተገበር እና የሚጠበቀውን ውጤት ማምጣት ይቻል ዘንድ፣ የሚነሱ ችግሮችን ትኩረት ሰጥቶ መመለስና ክትትልና ድጋፉን ማጠናከር አለበት እንላለን።

ንጉሤ ተስፋዬ

Recommended For You