የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ሀብት እና አጠባበቅ

መግቢያ

ኢትዮጵያ ብዙ የተለያዩ ሥርዓተ ምህዳሮች አሏት፣ ይኸም ሁኔታ ከፍተኛ የብዝሃ ሕይወት ባለ ሀብት ለመሆን አብቅቷታል። ለተለያዩ ሥርዓተ ምህዳሮች መገኘት ምክንያት ከሆኑት አንዱ፣ ኢትዮጵያ የምድር ገፅታ ከምድር መቀነት(equa­tor) በሰሜን አቅጣጫ ከሦስት ዲግሪ “ኪክሮስ” እስከ አሥራ አምስት ዲግሪ “ኪክሮስ”(lati­tude) የተለጠጠ መሆኑ ነው። በተጨማሪ ምድረ-ገፅታዋ፣ በጣም ሙቀት ከሆነው ከባህር ወለል በታች 115 ሜትር(ዳሎል) ጀምሮ፣ በጣም ቀዝቃዛ እስከሆነው አካባቢ ከባህር ወለል በላይ እስከ 4,620 ሜትር(ራስ ደጀን) መዝለቁ ነው። የገፀ ምድሩም አቀማመጥ ወጣ ገብ ነው፣ ሸለቆ፣ ኮረብታ፣ ተራራ፣ ወዘተ. ይኸም ለተለያዩ ሥርዓተ ምህዳሮች መገኘት መንስዔ ሆኗል።

የተለያዩ ሥርዓተ ምህዳሮችም በበኩላቸው ለተለያዩ እፅዋት፣ እንስሳት፣ ዘረ እንጉዳይ(fun­gus) እና ደቂቀ ሕዋሳት(ሚክሮብ/microbes) መኖሪያነት ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ፤ ብርድ፣ ሙቀት፤ ደረቅ፣ እርጥብ፤ ሸለቆ፣ ተራራ፣ ሜዳ፤ በረሃ፤ ጫካ፣ ወዘተ. ስለሆነም ለተለያዩ ሕያው አካላት ምቹ የሆኑ አካባቢዎች ይፈጠሩላቸዋል። በእነዚህም ምክንያቶች ኢትዮጵያ ለመጠነ ሰፊ የብዝሃ ሕይወት ስብጥር መከሰት፣ ብሎም ኢትዮጵያ በዓለማችን ውስጥ ከሚገኙ በብዝሃ ሕይወት ሀብት ከታደሉት ጥቂት አገሮች አንዷ ለመሆን በቅታለች። በተጨማሪም ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች፣ በሌላ አካባቢዎች የማይገኙ ግን በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ፣ የኢትዮጵያ “አገሬ” ዝርያዎች(endemic spe­cies) ባለቤት እንድትሆን አድርገዋታል።

ብዝሃ ሕይወት ምንድን ነው?

ብዝሃ ሕይወት ማለት ሕይወት ባላቸው አካላት ሁሉ(እፅዋት፤እንስሳት እና ደቂቅ ዘአካላት) መካከል ያለ ተለያይነት(variation) ማለት ሲሆን፣ ይህም በይዘት በሦስት የእርከን ደረጃዎች ይመደባል። አንደኛው በአንድ የብቸኛ ዝርያ(species) ስብስብ(population) ውስጥ ባሉ ነጠላ ሕያው አካላት(individuals within a species) ውስጥ ያለው የበራሂዎች ክምችት ተለያይነት ሲሆን፣ “ጄኔቲክ ተለያይነት”(Genet­ic diversity) በመባል ይታወቃል። ሁለተኛው በተለያዩ የብቸኛ ዝርያዎች(species) መካከል የሚገኘው የበራሂዎች ክምችት ተለያይነት ሲሆን፣ ይኸም የብቸኛ ዝርያዎች ብዝሃ ሕይወት በመባል የሚታወቀው ነው፣ ብሎም በአንድ አካባቢ የሚገኙ የብቸኛ ዝርያዎች ቁጥርና ክምችት የሚገለፅ ይሆናል። ሦስተኛው ቀደም ካሉት በዘለለ ሁኔታ፣ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሕያው አካላት፣ በዚያን መሰል ሥርዓተ ምህዳር(ecosys­tem) ለመኖር የሚያበቃቸው የበራሂ መሰናዶዎች አሏቸው፣ ስለሆነም በአካባቢው ከሚገኙ ሌሎች ሕያው አካላት ጋር አካባቢውን ተጋርተው ይኖራሉ። በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ሕያው ብዝሃ ሕይወት የከባቢውን ሁኔታ ሚዛን ጠብቆ ለመኖር አለኝታ ነው። በአንድ ሥርዓተ ምህዳር ለመኖር የሚያስችሉ፣ በተለያዩ ሕያው አካላት የታቀፉ የበራሂዎች ጥርቅም፣ የበራሂዎች ክምችት የሥርዓተ ምህዳር ብዝሃ ሕይወት በመባል ይታወቃል። ሥርዓተ ምህዳር ውስን ወይም ሰፊ ሊሆን ይችላል፣ ዋናው መለያው ግን ሚዛን ጠብቆ በአካባቢው የሚኖሩ ሕያው አካላትን አስተናጋጅ መሆኑ ነው።

የመጀመሪያው በነጠላ አካል ውስጥ ያለው በራሂ ክምችት፣ ሁለተኛው በብቸኛ ዝርያ ስብስብ ውስጥ ያለው የበራሂ ክምችት፣ በሦስተኛ ደረጃ በአንድ ሥርዓት ምህዳር ውስጥ ያለውን የበራሂ ክምችት ገላጮች ናቸው። በዘመናችን የሚገኘው(አሁን ያለው) የብዝሃ ሕይወት ሀብት በዝግምተ ለውጥ(evolution) እየተገራ፣ በቢሊዮን ዓመታት የተገኘ የተፈጥሮ ሀብት ነው።

ከላይ እንደተጠቀሰው ብዝሃ ሕይወት በመሠረቱ የበራሂዎች ክምችት ነው። የሕያው ቅርጽ፣ ባህርይ እና ተግባራት የሚወሰነው፣ ከወላጆቻቸው በሚወርሷቸው በራሂዎች(genes) ነው። በራሂዎች በማርዳ(የልጆች የአንገት ጌጥ) መሰል፣ ሃብለ በራሂ(chromosomes) በመባል በሚታወቅ አወቃቀር፣ ተገንብተው፣ በሕያው አካላት የሚፈበረኩ የፕሮቲኖችን ዓይነት እና ይዘት ይወስናሉ። ለምሳሌ የአንድ ቤት ፕላን፣ የሚገነባው ቤት ምን ዓይነት እንደሚሆን፣ ስንት ክፍሎች፣ በሮች፣ መስኮቶች፣ ወለሎች፣ ወዘተ. እንደሚኖሩት ይወስናል። የሚገነባው ቤት አካል የሚሆኑ ክፍልች ሁሉ በእቅዱ መሠረት ነው የሚገነቡት፣ እቅዱ ይዘታቸውንም ሆነ ቅርጻቸውን ይወስናል። በዚሁ አምሳያ በራሂዎች ለሕልውና ወሳኝ የሆኑ ተግባራት የሚያስተናግዱ የኬሚካላዊ ውሁድ፣ ሕልውና፣ እቅድ ወሳኝ መዋቅሮች ናቸው።

የበራሂዎች ኬሚካላዊ መዋቅሮች በተለያዩ ምክንያቶች ሊቀየሩ ይችላሉ። ለምሳሌ በፀሐይ ጨረር፣ በኑክሊየር ጨረር፣ በመርዛማ ኬሚካላዊ ውሁዶች፣ ወዘተ. ። ስለሆነም በነኝህ መንስዔዎች የተቀየሩ በራሂዎች በተከታይ ትውልድ ስለሚወረሱ፣ በሂደት የልጅ፣ ልጅ፣ — ልጆች ባህርይ እና ቅርጽ ከምንጅላቶቻቸው የተለየ ሊሆን ይችላል። ሁኔታው አመቺ ሆኖ ሲገኝ፣ በሂደት አዲስ ብቸኛ ዝርያ(species) ሆነው ሊከሰቱ ይችላሉ። በዚህ ሂደት ነው አዳዲስ የእንስሳትም ሆኑ የእፅዋት፣ የዘረ እንጉዳይም ሆነ የሚክሮብ ብቸኛ ዝርያ ዓይነቶች የሚገኙት/የሚከሰቱት።

ከላይ እንደተጠቀሰው፣ የሕያው አካላት ይዘት፣ ቅርፅ፣ ባህርይ ተግባር የሚወስኑትበራሂዎች ናቸው። የሰው ልጅ ከ35 እስከ 45 ሺ የሚገመቱ በራሂዎች፣ በሃብለ በራሂ(chro­mosome) ይዘት ተያይዘው፣ ተሰድረው ይገኛሉ። የያንዳንዱ ግለሰብ በራሂዎች ከሌሎች ግለሰቦች በራሂዎች ጥቃቅን ልዩነቶች አሏቸው። ለዚህም ነው በዓለማችን ሁለት ምንም ልዩነቶች የሌሏቸው፣ በሁሉም ሁኔታ አንድ ዓይነት የሆኑ ግለሰቦችን ማግኘት የማይቻለው። እያንዳንዱ ግለሰብ ልዩ ነው፣ ልዩነቱም በበራሂዎች ልዩነቶች ላይ የተመሠረተ ነው። የሰው ልጆች የጣት አሻራ በበራሂ አማኻኝነት የተመሠረተ ስለሆነ ነው ለያንዳንዱ ግለሰብ እንደ ልዩ መለያ ሆኖ የሚወሰደው/ የሚያገለግለው። ምንም ጥቃቅን ልዩነቶች ቢኖሩ፣ የሰው ልጆች ካለምንም ችግር ለመራባት/ለመዋለድ ስለሚችሉ፣ የአንድ ብቸኛ ዝርያ አባላት ናቸው። የሰው ዘር ብቸኛ ዝርያ “ሆሞ ሳፕያንስ”(Homo sapiens) በመባል ይታወቃል፣ ከላይ እንደተወሳው በዓለም ላይ ያሉት ሕዝቦች፣ ምንም ጥቃቅን ልዩነቶች ቢኖሯቸው፣ በአንድ ብቸኛ ዝርያ ነው የታቀፉት።

ሕያው አካላት በተፈጥሮ የተጎናፀፉት እምቅ የብዝሃ ሕይወት ሀብት አላቸው። እንዲሁም የተለያዩ ሕያው አካላት፣ የተለያዩ በራሂዎች ውጤቶች ናቸው። አንድ አካባቢም በውስጡ ምን ዓይነት እፅዋት፣ እንስሳት፣ ዘረ እንጉዳይ ወይም ማይክሮብ ሊያንሰራሩ እንደሚችሉ ይወስናል። ስለሆነም አካባቢም የራሱ የሆነ የብዝሃ ሕይወት ባለቤት ነው። በነኝህ ምክንያቶች ነው፣ ብዝሃ ሕይወት እንክብከቤ ሲደረግ፣ የእንስሳትም ሆኑ የእፅዋት ክምችቶች፣ በያሉበት አካባቢ(in situ)፣ ለምሳሌ ቆላ፣ ደጋ፣ ረግረጋማ ቦታ፣ ጫካ፣ ወዘተ. እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው።

የብዝሃ ሕይወት ጥቅማ ጥቅሞች

ከላይ በተገለጸው መሠረት፣ ብዝሃ ሕይወትን በሥነ ፍጥረት ይዘቱ ብቻ መገንዘብ ግንዛቤውን ጎደሎ ያደርገዋል። ብዝሃ ሕይወት ለሰው ልጆች ብዙ ጥቅማ ጥቅሞችን ያበረክታል። ይኸውም በምግብ፣ በማገዶ፣ በመጠለያ ግንባታ፣ በቁሳቁስ መሰናዶ፣ ወዘተ. ይተረጎማል። የሰው ልጆች ምግብ ፍጆታቸው መሠረቱ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ(ሳር፣ ቅጠላቅጠል ተመግበው ያደጉ እንስሳት አማኻኝነት) እፅዋት ናቸው። ከምግብ ዋስትና በተጨማሪ፣ ብዝሃ ሕይወት ለሰው ልጆች ከሚያስገኘው ዘርፈ ብዙ ጥቅማ ጥቅም አንጻር ግንዛቤ ማዳበር ይገባል። የመድኃኒት፣ ንፁህ አየር እና መጠለያ፣ በአጠቃላይ ለጤና ተስማሚ የሆነ አካባቢ መገኘትም ብዝሃ ሕይወት ዓይነተኛ ምክንያት ነው።

የብዝሃ ሕይወት ጥቅማ ጥቅም ጎልቶ የሚታየው ከእፅዋት አንፃር ነው። በዓለማችን ሰባት ሺ ገደማ እፅዋት ለሰው ልጆች ምግብነት ያገለግላሉ፤ ሆኖም የሰው ልጅች በብዛት ለምግብነት የሚጠቀሙባቸው(የሚበሉት)፣ ዘጠና በመቶ(90%) የምግብ ፍጆታን የሚያሟሉት ሰላሳ ገደማ ብቸኛ ዝርያዎች ናቸው። በብዛት የምግብ ፍጆታዎችን የሚያሟሉት የተላመዱ(domesticated races) የእፅዋት ብቸኛ ዝርያዎች ሲሆኑ፣ ለነኝህ ለተላመዱት፣የቅርብ ወገኖች የሆኑ፣ ያልተላማዱ(wild races) አቻዎች አሏቸው። ከተላመዱት ብቸኛ ዝርያዎች ይልቅ ባልተላመዱት ብቸኛ ዝርያዎች ውስጥ የበራሂዎች ስብጥር ልዩነቶች አለ፤ ስለሆነም ያልተላመዱት፣ ከተላመዱት ጋር ሲነፃፀሩ፣ የላቀ የበራሂዎች ተለያይነት ሀብታሞች ናቸው። በአንፃሩ የተላመዱት ደግሞ የበራሂዎች ተለያይነት ክምችት ድሆች ናቸው።

ከምግብነት በተጨማሪ እፅዋት የሰው ልጆች መድኃኒት ፍላጎቶችን ያሟላሉ፣ 70 ሺ ገደማ እፅዋት ለመድኃኒትነት ያገለግላሉ። በገጠር የሚኖሩ ማህበረሰቦች የመድኃኒት መደብሮቻቸው እፅዋት ናቸው። ለምሳሌ የሰማኒያ በመቶ(80%) አፍሪካውያን መድኃኒት መደብሮቻቸው እፅዋት ናቸው፣ አገራችንም ከዚህ የተለየች አይደለችም። በአገራችን እነ ቀብርቾን፣ መተሬን አንደ ምሳሌነት ማውሳት ይቻላል። በአደጉ አገሮችም ቢሆን፣ ለምሳሌ ሰሜን አሜሪካ፣ በሐኪሞች ከሚታዘዙት መድኃኒቶች ግማሹ(50%) መሠረታቸው የእፅዋት ዝርያዎች ናቸው፣ ለምሳሌ “ፔኒሲሊን”(penicil­lin)፣ “አስፕሪን”(aspirin)፣ የወባ ኪኒን(qui­nine)፣ ወዘተ. ።

ብዝሃ ሕይወት ከሥርዓተ ምህዳር አንፃር ሲታይ፣ አንደ አካባቢ ሚዛን አስተናጋጅ ሊወሰድ ይችላል። አካባቢ በካይ የሆነውን “ካርቦን ዳይኦክሳይድን”(CO2) እፅዋት ምገው፣ በፀሐይ ኃይል ታግዘው፣ “ካርቦን ዳይኦክሳይድን” ለእድገታቸው ግብዓት ካደረጉ በኋላ፣ ለሕያው ሕልውና አስፈላጊ የሆነውን የአየር ዓይነት፣ “ኦክሲጅንን”(O2) ያበረክታሉ። ስለሆነም የአካባቢውን ብክለት ቀንሰው፣ ጠቃሚ አየር አፍልቀው፣ የሕያውን ሕልውና አረጋግጠው፣ ሁኔታውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ያስተናግዳሉ።

እፅዋት ለአካባቢ ውበትም አለኝታዎች ናቸው። ለአረንጓዴ ቅጠላቅጠል እንዲሁም በአበባ ሕብረ ቀለማት ያሸበረቀ አካባቢ አበርካቾች ከመሆናቸው በተጨማሪ በእንደዚህ ያሉ አካባቢዎችም ወፎች ሲከንፉ፣ ቢራቢሮዎች ብር ትር ሲሉ ማየት ይቻላል። ይህም ለሰው ልጆች መንፈሳዊ እርካታን ያበረክታል።

በኢትዮጵያ ብዝሃ- ሕይወት” (biodiversity) ጥቅማ ጥቅሞች ምሳሌዎች

ብዝሃ-ሕይወት በጥቅሉ ሲታይ ሰበነክያልሆነ፣ በተፈጥሮ የሚገኝ የተትረፈረፈ ሀብት ነው። ከላይ እንደተገለጸው የብዝሃ-ሕይወት ጥቅም ፈርጀ-ብዙ ነው። ቀደም ሲል፣ በሌላ ጽሑፍ በአንዳችን (ሽብሩ ተድላ) እንደተወሳው፣ ከኢትዮጵያ የተገኘች አንድ የገብስ ዘር፣ የካሊፎርንያን(USA) የቢራ ግብዓት የሆነን የገብስ ዘር ከመጥፋት ታድጋለች። ታሪኩ እንዲህ ነው፤ ከዓመታት በፊት ከሰሜን ሸዋ የተገኘች አንድ የገብስ ዝርያ፣ በካሊፎርንያ የቢራ ግብዓት የሆነን የገብስ ዘር ሊያጠፋ የደረሰውን የበሽታ መንስዔ “ቫይረስ”(Virus) ለመቋቋም የሚያስችል “በራሂ”(gene) እንዳላት በምርምር ተደረሰበት።

ስለሆነም ይህች የገብሱን በሽታ ለመቋቋም የምታስችለዋ “በራሂ”፣ ኢትዮጵያ ከተገኘው የገብስ ዘር ተፈልቅቃ ወጥታ፣ በበሽታ ሲጠቃ የነበረው የካሊፎርንያ ገብስ “ሃብለ በራሂ” ሰንሰለት አካል እንድትሆን ተደርጋ (ከነባሩ ተቆርጣ አዲሱ በበሽታ ከሚጠቃው ላይ ተቀጥላ)፣ ሊጠፋ የነበረውን የካሊፎርንያ የገብስ ዘር በሽታውን ለመቋቋም በቃች፣ ሂደቱም “የዘረመል” ምህንድስና ነው። ስለሆነም፣ ሊጠፋ የደረሰው የካሊፎርንያ የገብስ ዝርያ “በቫይረሱ” ምክንያት ሲጠቃ ከኖረበት በሽታ ነፃ ሆኖ፣ በካሊፎርኒያ የቢራ መፈብረኩ(ማምረቱ) ሥራ ቀጠለ። ይህች በኢትዮጵያ ገብስ ውስጥ ያለች “በራሂ”፣ ማለትም የኢትዮጵያ “የብዝሃ-ሕይወት” አካልና ሀብት፣ ውቅያኖስ አቋርጣ ምንም ዋጋ ሳይከፈልባት(ጥቅም ሳናገኝባት)፣ ለሌላ አገር ሰዎች ጥቅም አበርካች ለመሆን በቃች-ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል እንዲሉ።

በተጨማሪ በ1970ዎች የቡና በሽታ(Coffee rust) የብራዚልን፣ የመካከለኛውን አሜሪካ እና እንዲሁም የሲሪላንካን የቡና ተክል ባጠቃበት ወቅት፣ በሽታውን ለመከላከል በሚችል፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በተገኘ የቡና ዘር ነው በሽታውን ለመቋቋም የተቻለው።

በመሠረቱ ታዳጊ አገሮች የብዝሃ ሕይወት ሀብት ባለፀጎች ሲሆኑ፣ ያደጉ አገሮች ደግሞ የቴክኖሎጂ ልህቅና አላቸው። የብዝሃ ሕይወት ጥቅማ ጥቅም አንዱ መግለጫ፣ ባዮቴክኖሎጂ ሲሆን፣ የባዮቴክኖሎጂ ዋናው ግብዓት(በራሂዎች) የሚገኘው በብዝሃ ሕይወት ዋና ቋት ውስጥ ነው። በራሂዎች ናቸው ከአንድ ሕያው አካል ሃብለበራሂ ተቆርጠው፣ ሌላ ሕያው አካል ሃብለ በራሂ አካል ተደርገው፣ የሚፈለገውን ተግባር የሚያስተናግዱ። ለምሳሌ በሽታን ወይም ቅዝቃዜን፣ ወዘተ. መቋቋም የመቻል አቅምን የሚያጎናጽፉ። ስለሆነም ታዳጊ አገሮች የብዝሃ ሕይወት ሀብታቸውን አቅርበው፣ ያደጉ አገሮች ደግሞ በቴክኖሎጂ ተጠቅመው፣ በጋራ ብዙ ጠቀሜታ ያሏቸው ተግባራትን ማከናወን ይቻላል። ወደፊት ታዳጊ አገሮችም የቴክኖሎጂ ዕውቀትን እና ክህሎትን ይጎናፀፋሉ፣ ብሎም የብዝሃ ሕይወት ሀብታቸውን ካለ እገዛ ሊጠቀሙበት ይችላሉ።

ብዝሃ ሕይወት ሕያውን ከማላመድ(Domestication) አንፃር

የብዝሃ ሕይወት ይዘት ቀለል ባለ መልክ ልንገነዘብ የምንችል በርቢ/በማዋለድ ሂደት ነው የሚል እይታ አለን። ለምሳሌነት እንዲያገለግሉ ከእፅዋት እንዲሁም ከእንስሳት ምሳሌዎች አናወሳለን። ጽጌ ረዳ የእፅ ዝርያ ነው፣ ሁሉም የጽጌረዳ ዓይነቶች መሠረታቸው ሰብነክ ያልሆነ፣ ማለት ያልተላመደ(wild) የጽጌረዳ ዝርያ ነው። የሰው ልጅ በማዳቀል ተግባር የተለያዩ ቀለማት ያሏቸው የጽጌረዳ ዓይነቶችን ለማምረት በቅቷል። ስለሆነም በመሠረቱ ሰብ ነክ ያልሆነው ዘር፣ የተለያዩ ቀለማትን ለማግኘት የሚያስችል በራሂዎች አሉት ማለት ነው፤ ይህም እንደ ብዝሃ ሕይወት ባለሀብትነት፣ አቅም፣ ይወሰዳል። በማዳቀል/ማዋለድ ሂደት የተፈለገውን ቀለም ለማግኘት (ቢጫ፣ ቀይ፣ ወይን ጠጅ፣ ወዘተ.) የሚያስችሉ በራሂዎቸን መርጦ፣ የተፈለገውን ዓይነት ጽጌረዳን ማምረት ይቻላል።

እንዲሁም ለዓለም ገበያ የሚውል አበባ ሲመረት፣ ከተፈላጊው የአበባ ቀለም ዓይነት በተጨማሪ፣ በቶሎ የማይጠወልግ እንዲሆን ይፈለጋል። በዚህ ሂደት የአበባውን መዓዛ ልናጣ እንችላለን። ሽታ አልባ ወይም መዓዛው ውስን የሆነ አበባ ነው ለማምረት የምንገደደው። ምክንያቱም በትነት የአበባ መዓዛ አመንጪ የሆኑ የተፈጥሮ ዘይቶች፣ ከአበባው በቶሎ ከመጠውለግ ጋር የተዛመዱ ስለሆኑ፣ በምርጫ ተግባር የአበባ ዘይቶች፣ በመትነን የአበባን ሽታ የሚያበረክቱት መጠን በጣም እንዲቀንስ ይደረጋል፣ ብሎም የአበባ የሚያውድ ሽታ ይደበዝዛል።

በአገራችን ለምግብነት ከምንጠቀምባቸው የእፅዋት ዝርያዎች አተርን እንወስድ። ምርጥ የአተር ዘር ብለን የምናውቀው አተር ቀደም ሲል ከነበረ የአተር ዘር በማዋለድ የተገኘ ነው። ግኝቱንም የወሰኑት የበራሂ ዓይነቶች ናቸው፣ ስለሆነም በራሂዎች ናቸው የተመረጡት ማለት ነው። የተመረጠው አተር ምንም መጠኑ ካልተመረጠ የአተር ዘር ጋር ሲነፃፀር የላቀ ቢሆንም፣ በመምረጥ ሂደት ከነባር ባህርዮች የምናጣቸው ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ በአገራችን ያለው የአተር ምርጥ ዘርን ተመጋቢዎች የለመዱት ጣእም የለውም፣ ነባሩም ቀለም በመጠኑ ይቀየራል። ስለሆነም ጣፋጭነትን የሚወስኑ ባህርያትንም ሊያጣ ይችላል። ይህ እጦት ለምርት መጠን ብዛት የሚከፈል እዳ ነው፤ ያም ነፃ የሚባል ምግብ የለም፣ ይከፈልበታል፣ እንደ ማለት ሊታይ ይችላል።

ከእንስሳት ዓይነት ምሳሌ ብንወስድ፣ ውሻን ማዳቀል አንዱ ሊሆን ይችላል። ውሻ እና ተኩላ አንድ ብቸኛ ዝርያ(species) ናቸው፣ ማለትም ተኩላ እንዳልተላመደ ውሻ ይቆጠራል። ከነባሩ የውሻ ዝርያ(wild)፣ ማለት ገና ሰበ ነክ ካልነበረው የውሻ ዘር ሃበለ በራሂ ቋት በማዋለድ ሂደት፣ የተፈለገውን ዓይነት ውሻ፣ የተለያዩ ተክለአቋም እና መጠን ያሏቸው የውሻ ዓይነቶች ለማግኘት ተችሏል። እነሱም ድመት አከል፣ ድመት መሰል ድንክዬ፣ ወይም አንበሳ መሰል ግዙፍ አውሬ መሰል ሊሆኑ ይችላሉ። ስለሆነም ብዝሃ ሕይወት ለተለያዩ ሕያው ገላጭ ለሆኑ ተግባራት እንደ ግዙፍ ቋት ሊመሰል ይችላል። በርቢ ጊዜ የሚፈለገውን ባህርይ ለማግኘት፣ ወሳኝ የሆኑት በራሂዎች ናቸው የሚመረጡት። ሰበ ነክ ካልነበረ ውሻ ውስጥ የነበረው ብዝሃ ሕይወት፣ በርቢ ከተመረጡት የውሻ ዓይነቶች የበራሂ ቅልቅል በጣም የላቀ ነው። በሰበነክ ምርጫ ብዙ በራሂዎች ይታጣሉ።

በራሂዎችን በሸማኔ ባለቀለም ክሮች ብንመስላቸው የሚፈለገውን ጥለት ለማግኘት፣ ተፈላጊ የሆኑ ቀለማት ያሏቸውን ክሮች መምረጥ ይገባናል። በተመረጡ የክር ቀለሞችም የተለያዩ ዓይነት የልብስ ጥለቶችን ለመሸመን እንችላለን። በበራሂዎች ምርጫም የተፈለገው ባህርይ ያሏቸውን ሕያው አካላት ማግኘት ይቻላል።

ብዝሃ ሕይወት ለብቸኛ ዝርያውም ጥቅም አለው፣ ይህን ገላጭ የሆነ አንድ ምሳሌ እንውሰድ። በእንግሊዝ አገር ቅድመ-ኢንዱስትሪ አብዮት አንድ የእሳትራት ዝርያ ነበረች። የዝርያዋ አባላትም ብዙዎቹ ክንፎቻቸው ወደ ነጭ ያደላ ቀለም ያለው ነበር፣ ያም እሳትራቶች የሚያርፉበትን የዛፍ ቅርፊት ቀለም መሰል ነበር። ስለሆነም የሳትራት-በል ወፎች፣ ዛፎች ቅርፊት ላይ ያረፉትን የሳትራቶች በቀላሉ ለማየት ይሳናቸው ነበር። ጥቂት ቢሆኑም አንዳንድ ጠቆር ያለ ቀለም ክንፍ ያሏቸው በማኻላቸው ይገኙባቸው ነበር። ስለሆነም የብቸኛ ዝርያው ብዝሃ ሕይወት ጥቁርም ነጭ ቀለም ክንፍ ያሏቸው አባላት ነበሩት። አእዋፍ ጠቆር ያለ ቀለም ያላቸውን በቀላሉ ለማደን ይችላሉ፤ ይህም የሆነበት ምክንያት በነጭ ቅርፊት ላይ ያረፈን ጥቁር ክንፍ ያለው የሳትራት በቀላሉ ለማየት ስለሚቻል ነበር።

በኢንዱስትሪ አብዮት መንስዔ፣ የእንግሊዝ ገጠር አካባቢ በኢንዱስትሪ ጢስ ሲበከል፣ የአካባቢ ዛፎች ቅርፊት በጥላሸት መሸፈን ጀመረ። በዚህን ጊዜ የሳትራት አዳኝ አእዋፍ ነጭ ክንፎች የነበሯቸውን የሳት ራቶች በቀላሉ ለማየት፣ ብሎም ለማደን በቁ። በአንፃሩ ጥቁር ክንፎች የነበሯቸው አባላት፣ ከአእዋፍ እይታ ተሰወሩ፣ ብሎም ከመታደን ተረፉ። በሂደት በአካባቢው በብዛት የሚታዩት ባለ ጥቁር ክንፍ የሳትራቶች ሆኑ። በዚህ ሂደት የሳትራት ዘር እንዳይወድም የብዝሃ ሕይወት ሀብት ስብጥር ታደገው ማለት ነው።

የቁልፍ ብቸኛ ዝርያዎች (Keystone Species) ጉዳይ

በአንዳንድ አካባቢዎች ብዙ ውስብስብ ተግባራትን የሚያከናውኑ ሕያው አካላት አሉ። እነኝህ ዓይነቶች ሕያው አካላት ቁልፍ ብቸኛ ዝርያዎች ይባላሉ። እንደ አካባቢውም ሕያው መዋቅር ዋልታ ተደርገው ይወሰዳሉ፤ እንዲሁም እንደ የማዕዘን ድንጋይ ይመሰላሉ። እንደ ዋልታ የሚመሰለው፣ ብቸኛ ዝርያ የሚያከናውናቸውን ተግባራት፣ እሱን ተክቶ ለማከናወን የሚችል ሌላ ዝርያ በአካባቢው አለመገኘቱ፣ ተኪ አልባ መሆኑነው። በማዕዘን ድንጋይ የሚመሰለውም፣ የማዕዘን ድንጋይ ሾልኮ ከወጣ፣ ሕንፃው(ቤቱ) ስለሚናድ ነው። ቁልፍ ብቸኛ ዝርያዎች ሲጠፉ የአካባቢው ሚዛናዊ ሁኔታ ይናዳል፣ ትስስሩ ይበጠሳል።

ለምሳሌ ንቦች ለጥቂት የእፅዋት ዝርያዎች፣ ርቢ ሂደት ወሳኝ ሚና አላቸው። ንቦች ከአካባቢ ቢጠፉ፣ የብዙ እፅዋት ዝርያዎች ርቢ/ስነ ተዋልዶ ሥርዓት ይቃወሳል። ምክንያቱም ንቦች ናቸው የአበባ ወለላ(nectar) በመቅሰም ላይ ሲሰማሩ፣ ከአንድ የባለ አበባ እፅ፣ ፅጌ ብናኝ(pollen) ወሰደው፣ ለሌላ ባለ አበባ እፅ የሚያበረክቱት፣ ሂደቱም ርክበ ብናኝ(pollination) በመባል ይታወቃል። የወንድ አባለ ዘር የሚገኘው በፅጌ ብናኝ ይዘት ውስጥ ነው። ንቦች በአካባቢው ከሌሉ ይህ የመዋለድ ተግባር ይስተጓጎላል። በዚህ መንስዔ አንዳንድ የእፅዋት ዝርያዎች ለውድመት ይዳረጋሉ።

እንደዋልታ የሚመሰሉት ሕያው አካላት፣ በተለያዩ ተግባራት የተሠማሩ ሊሆኑ ይችላሉ። አዳኝ ሥጋ በል፣ ለምሳሌ ድመት፣ የአይጥ ዝርያዎች ተራብተው ቁጥራቸው ከመጠን በላይ እንዳይንር ይቆጣጠራል። አይጥ ካለ ገደብ መራባት ለብዙ የአካባቢ ሚዛን መዛባት (የበሽታ ስርጭት፣ የሀብት መውደም፣ ወዘተ.) ምክንያት ሊሆን ይችላል።

በዘመናችን ብዝሃ ሕይወት ሀብት መመናመን

ለብዝሃ ሕይወት መጎሳቆል፣ መመናመን ብዙ ምክንያቶች አሉ። ይህም የተፈጥሮ አንዱ ሂደት እንደሆነ ይታወቃል። በራሂዎች ይከስማሉ፣ ብሎም በአዳዲስ በራሂዎች ይተካሉ፤ ይህ ተግባር የዝግመተ ለውጥ(evolution) መሠረት ነው። እንደውድመት የሚቆጠረው ግን ሰበ ነክ የሆነው ነው። ብዝግመተ ለውጥ የሚከሰተው በራሂዎች መክሰም፣ ሰበ ነክ ከሆነው ጋር ሲነፃፀር በጣም ኢምንት ነው። ሰበ ነክ የሆነው የበራሂዎች ውድመት፣ በተፈጥሮ ከሚከሰተው በመቶ እጥፍ ከፍ ያለ ነው።

የሰው ልጅ በገፀ ምድር ከተከሰተ ጀምሮ የብዝሃ ሕይውት ሀብት ተፈጥሮ ካሰናዳለት ፈር ወጣ እያለ መሄድ ጀምሯል። ለምሳሌ በእንስሳት ርቢ የሚፈለገውን ባህርይ የሚያበረክቱ (ፈጣን ፈረስ፣ በዛ ያለ ወተት የሚታለብ ላም፣ ወዘተ.) ለማግኘት እንስሳትን ማርባት፣ ብሎም ማዳቀል፣ እዕዋትን ማላመድ፣ እንዲሁም በእፅዋት ውጤቶች አጠቃቀም (ማገዶ፣ ቤት መሥራት፣ ቁሳ ቁስ ከእንጨት ውጤቶች ማበጀት፣ መፈብረክ፣ ወዘተ.)፣ የከባቢን አየር መበከል፣ እና መሰል ተግባራት በብዝሃ ሕይወት ሀብት አሉታዊ ተፅዕኖ አድርሷል። ጥቂት እንስሳትን ወይም እፅዋትን ለይቶ ለሰው ልጅ ምግብ ፍጆታ ማሟያ ማድረግም፣ እፅዋቱን ወይም እንሳሰቱን ለውድመት ይዳርጋል።

ሰበ ነክ ለሆኑ ውድመቶች ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም ዋና ዋናዎቹ ደን መጨፍጨፍ፣ ረግረግ ቦታዎችን አጠንፍፎ ለግብርና ወይም ለሌላ ተግባር ማዋል (ረግረግ ቦታ እንደ ጉበት ይመሰላል፣ ያን ዓይነት አካባቢ ከፍተኛ የባክቴሪያ/የሚክሮብ ዝርያዎች የሚገኙበት ሲሆን፣ እነኝህ ሚክሮቦችም ጎጂ ኬሚካላዊ ውህዶችን የማስወገድ/ የማውድም ባህርይ አሏቸው)፣ የዱር እንስሳት እና የእፅዋት የሆነውን ክልል ጥሶ በመግባት እና አካባቢውን በመመንጠር፣ ሰፋፊ እና የተንጣለሉ የመኖሪያ ሰፈሮችን በመመሥረት ምክንያት የነባር ሕያው አለኝታን ማጎሳቆል እና አካባቢውን ሚዛን ማዛባት ናቸው።

በአካባቢው ነባር ያልሆኑ እፅዋትን ሆነ እንስሳትን ወደ አዲስ አካባቢ በማስገባት፣ ነባር ባለቤቶችን ለውድመት ይዳርጋል። ይህም በአውስትራሊያ ክፍለ ዓለም በገሃድ ታይቷል። ያም የሚከሰተው መጤዎችን የሚያጠቁ ሌላ ሕያው አካል በአዲሱ አካባቢ አለመኖራቸው ነው (የበሸታ መንስዔም ሆነ፣ መጤዎች ለምግብነት የሚጠቀም፣ ወዘተ.)።

ኬሚካላዊ ብክለትም ለብዝሃ ሕይወት ውድመት አንዱ ምክንያት ነው። ለምሳሌ የወባ ትንኝን ለመከላከል የሚረጨው “ዲዲቲ”(D­DT) ለአካባቢ ኬሚካላዊ ብክለት አንድ ዋና መንስዔ ሆኖ ስለተገኘ፣ በብዙ አካባቢዎች በዚህ ኬሚካላዊ ውሁድ መጠቀም የተወገዘ ነው። ከኢንዱስትሪ የሚመነጩ ኬሚካላዊ ውሁዶች ለአካባቢ ብክለት፣ ብሎም ለብዝሃ ሕይወት ውድመት መንስዔዎች ናቸው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአየር ቅጥ/ንብረት ለውጥ(climate change) ለብዙ ሕያው ውድመት መንስዔ እየሆነ መጥቷል። የአየር ቅጥ ለውጥ የሚያስከትለው ዋናው ችግር ድርቅ ሲሆን፣ በድርቅ መንስዔ ብዙ ብቸኛ ዝርያዎች(እፅዋት እና እንስሳት፣ ወዘተ.) ለመመናመን፣ ከዚያም ባለፈ ለውድመት ይዳረጋሉ። በአየር ቅጥ ለውጥ መንስዔ የአካባቢ ሙቀት ሲጨመር፣ አንዳንድ አካባቢዎች ለወረራ ይጋለጣሉ፣ ለምሳሌ የወባ ትንኝ ወደ ደጋ አካባቢዎች መዛመት።

በኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ሀብት ችግሮች መከሰት ምክንያቶች

የብዝሃ ሕይወት መጎሳቆል ዋናው መንስዔ የሰው ልጅ የሚያከናውናቸው ተግባራት ናቸው፣ ማለት ችግሩ ሰበነክ ነው። ሰው በበዛ መጠን ለእርሻ የሚውለው መሬት ስፋት ይጨምራል። በኢትዮጵያ ለከብት መዋያ ያገለግል የነበረው፣ መታረስ የማይገባው ተዳፋት መሬት ተመንጥሮ ወደ ሰብል ማምረቻነት ተቀይሯል። እንዲሁም ወንዝ አጠገብ ያለው ውሃ-አዘል መሬት ሁሉ ወደ ማሳነት/ወደ እርሻ መሬትነት ተቀይሯል። ከብት የሚሰማራበት ቦታም እየጠበበ ሄዷል። ባለንበት ወቅት፣ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ወይናደጋ እና ደጋማ ቦታዎች የሚገኙ የከብት ማሰማሪያ ቦታዎች በብዙ እጅ ቀንሰዋል። ስለሆነም፣ የቤት እንስሳት በቂ መኖ አያገኙም፤ በቂ ምግብ ካላገኙ ምርታማነታቸውም ሆነ ጉልበታቸው ይቀንሳል። በሂደት እፅዋት አየተጨፈጨፉ ነው።

ሃሩር ቢፈጃቸው፤

የሳቶችን እናት፣ ፀሐይቱን ሸሽተው፤

እንስሳት በሙሉ፣ ከዛፍ ስር አረፉ፤

ምሳር ሲያሳድደው፣ የት ይሸሸግ ዛፉ።

(ስብስብ ግጥሞች-በውቀቱ ስዩም ስንኝ በግርድፉ የተዘረፈ..)

የሕዝብ ብዛት ብቻውን የአካባቢ ቀውስን አያስከትልም። ነገር ግን ሕዝቡ የድህነት ሰለባ ከሆነ በአካባቢ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ያደርጋል። ሕዝብ ሲበዛ፣ ተጨማሪ ማሳ፣ ተጨማሪ ጎጆ፣ ተጨማሪ ምግብ ማብሰያ ማገዶ ያስፈልጋል። ይህም ሂደት በአካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ያመናምነዋል፣ ሥርዓተ ምህዳሩንም ያቃውሳል። የድህነት ሰለባ የሆነው ማህበረሰብ ኑሮውን በቀጥታ ከመሬት በሚገኝ የተፈጥሮ ሀብት ላይ እንዲመሠረት ይገደዳል። የሕዝቡ ብዛት በጨመረ መጠን በየቤቱ የሚሰማው ሮሮ፣ ምግብ ሳያልፍበት የሚውለው/ የሚያድረው ጉሮሮ ይበረክታል። ያም ለተጨማሪ የአካባቢ መጎሳቆል መንስዔ ይሆናል፣ ሂደቱ አዟሪት መሰል ነው።

ከላይ የተደረደሩት ችግሮች ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በመጠኑም ቢሆን ቀንሰዋል። ይህ ማለት ከችግሩ ተላቀናል ማለት እንዳልሆነ መገንዘብ ያሻል። ከችግር የመላቀቅ ጥረቱ ኅብረተሰቡን በጠቅላላ ባሳተፈ መልኩ ነገ ዛሬ ሳይባል መቀጠል ይኖርበታል።

የኢትዮጵያ የብዝሃ ሕይወት ሀብት እና እንክብካቤ /ጥበቃ/

በእፅዋት ይዘት ያለው የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ሀብት መጠነ ሰፊ ነው። በኢትዮጵያ ከስድስት ሺ እስከ ሰባት ሺ የሚገመቱ የእፅዋት ብቸኛ ዝርያዎች አሉ። ከነኝህ በመቶ አሥሩ(10%) ኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ “አገሬ”(indigenous species) ዝርያዎች ናቸው። እንዲሁም 284 አጥቢ የዱር እንስሳት፣ 861 የአእዋፍ ብቸኛ ዝርያዎች፣ 201 የገበሎ አስተኔ ብቸኛ ዝርያዎች፣ 200 ገደማ የዓሣ ብቸኛ ዝርያዎች፣ 63 የእንቁራሪት አስተኔ ብቸኛ ዝርያዎች አሉ። ከነዚህ 29 አጥቢ ብቸኛ ዝርያዎች፣ 18 የአእዋፍ ብቸኛ ዝርያዎች፣ 10 የገበሎ አስተኔ ብቸኛ ዝርያዎች፣ 40 የዓሣ ብቸኛ ዝርያዎች እና 25 የእንቁራሪት ብቸኛ ዝርያዎች በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ “አገሬ” ዝርያዎች ናቸው። ስለ ሦስት አፅቄዎች(insects) ብዙ መረጃ ባይኖርም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙ ብዙ እንዳሉ ይገመታል።

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በአዝርእት ብዝሃ ሕይወት የከበረች ናት። ስለሆነም በዓለም ደረጃ “የብዝሃ ሕይወት ማዕከል” ተብላ ተመድባለች። በዓለማችን ካሉ ሀብታም የአዝርእት ብዝሃ ሕይወት አካባቢዎች ተብለው ከተመደቡት ከአሥራ ሁለቱ “የቫቪሎቭ ማዕከሎች” አንዷ ኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያ “የአረቢካ ቡና”(Cof­fee arabica) ዋና የብዝሃ-ሕይወት ማዕከል ናት። በተለያዩ ደረጃዎችም ቢሆን (የብዝሃ-ሕይወት ክምችት መግለጫ ደረጃዎች አሉ)፤ የጤፍ፣ የእንሰት፣ የአንጮቴ፣ የሰናፍጭ፣ የማሽላ፣ የአጃ፣ የአተር፣ የኑግ እና የሰሊጥ ዋና ዋና ማዕከሎች ከሚባሉት አንዷ ናት።

የብዘሃ ሕይወት ሀብት እንዳይመናመን፣ ማለት በያንዳንዱ ብቸኛ ዝርያ በራሂ ይዘት እንዳይመናመን፣ እንዳይቀንስ፣ እንዳይጠፋ ለማድረግ እየተሞከረ ነው፡፡ እንዲሁም ለአካባቢ ተገቢውን ክብካቤ ለማድረግ በሥርዓት ምህዳር የታመቀው የብዝሃ ሕይወት ሀብት እንዳይመናመን ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የብዝሃ ሕይወት ሀብት እንክብካቤ ሁለት ዋና ዋና ስልቶች ያሉ ሲሆን፣ አንዱ ሀብቱን በነባር አካባቢው፣ በሚገኝበት አካባቢ ተገቢው ክብካቤ የማድረግ ዘዴ ነው(in situ conservation)፡፡ ለዚህም ምሳሌ የሚሆኑት በብዙ አካባቢ የተመሠረቱት የዱር እንስሳት ጥብቅ አካባቢዎች(wildlife parks/zoological parks/sanctuaries) እና ጥብቅ ደኖች ናቸው፡ ፡ ሁለተኛው ዘዴ ደግሞ ከነባር መኖሪያ አካባቢ አውጥቶ ለዚሁ ተግባር በተዘጋጀ ሥርዓት ብዝሃ ሕይወትን ከውድመት መታደግ ነው(ex situ conservation)፣ ለዚህም ተምሳሌቶች የበራሂ ባንኮች(gene banks) እና የእፅዋት ማዕከሎች(botanical gardens) ናቸው፡፡ ለዚህ ተግባር አካባቢው እንግዳ አይደለም፣ ምክንያቱም ለተግባሩ ቀዳሚ ተዋናይ የነበሩ ብዙ የእምነት ማዕከላት በኢትዮጵያ ስለሚገኙ ነው፤ እነሱም አንደ እፅዋት ማዕከላት ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡

ኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወትን ለመታደግ ተቋማትን መሥርታለች፣ ፖሊሲዎች፣ ሕግጋት አና ደንቦችን አውጥታለች፡፡ ከነዚህም ዋና ዋናዎቹ፣ የብዝሃ ሕይወት ተቋም(Institute of Biodiversity) መመሥረት፣ የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ስትራቴጂ መንደፍ፣ የተግባር እቅድ ማውጣት(National Biodiversity Strate­gy and Action Plan)፣ የዱር እንስሳት ጥብቅ አካባቢዎች(Protected areas) መመሥረት ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ገፀ ምድር አሥራ አራት በመቶው(14%) በተለያዩ ደረጃዎች የእንስሳት ጥበቃ አካባቢዎች ተመሥርተዋል፡፡ እንዲሁም ከአገሪቱ ገፀ ምድር አሥራ አምስት ተኩል በመቶ(15.5%) በተለያዩ ደረጃዎች የእፅዋት ጥበቃ አካባቢዎች ተመሥርተዋል፡፡

በበራሂ ባንኮች(Gene banks) ወደ 494 የእፅዋት ብቸኛ ዝርያዎች በነባር አካባቢዎቻቸው ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው። ከነዚህም 297 የዛፍ ዝርያዎች እና 13 የቤት እንስሳት ዝርያዎች ናቸው። ብዙ የሰብል ዝርያዎች በዚሁ መንገድ ክብካቤ እየተደረገላቸው ነው። እንዲሁም 275 የእፅዋት ዝርያዎች ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉ በበራሂ ባንኮች ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው። በተጨማሪ 460 ብቸኛ እፅዋት ዝርያዎች ለዚሁተግባር በተዘጋጀ ቀዝቃዛ አካባቢ በበራሂ ባንኮች ይዘት እየተጠበቁ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትምህርት እና ምርምር መዋቅሮችም ለብዝሃ ሕይወት ክብካቤ ትኩረት እየተሰጠ ነው። በተለይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ ለዚህ ተግባር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። በጉለሌ የሚገኘው “የእፅዋት ማዕከልም” የዚህ ተግባር አካል ነው። እንዲሁም ስለ ብዝሃ ሕይወት ክብካቤ ብሎም ጥቅማ ጥቅም ማህበረሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ጥረት እየተደረገ ነው።

ዓለም አቀፍ የሆኑ የተለያዩ ስምምነቶች፣ በብዙ አገሮች(መንግሥታት) ተቀባይነት አግኝተው የብዙ አገሮች የሕግ አካላት ተደርገው ተወስደዋል። ስምምነቶቹም ለብዝሃ ሕይወት ክብካቤ እና ጥበቃ ልዩ ትኩረት ሰጥተው በፈረሙት መንግሥታት እየተተገበሩ ይገኛሉ። ብዝሃ ሕይወትን ለመንከባከብ ትኩረት የሰጡ ተቋማትም ተመሥርተዋል።

በተቋም ደረጃ እንደ የዩኔሰኮ “የሰው ልጅ እና ሕያው አካባቢውን”፣ “የዓለም የተፈጥሮ ሀብት ተቋም”፣ “የእፅዋት ብዝሃ ሕይወት ቦርድ” እና መሰሎች የሚጠቀሱ ናቸው። በስምምነት ደረጃ የአእዋፍ ጥበቃ፣ ለውድመት የተቃረቡ ብቸኛ ዝርያ ንግድ፣ የሕያው ክብካቤ፣ “የራመሳር ረግረግ አካባቢዎች ጥበቃ”፣ “የአፍሪካ የሕያው እና ተጓዳኝ ሀብት ጥበቃ”፣ “የካርታጀና ሕያው ነክ አጠቃቀም ጥንቃቄ ዙሪያ”፣ “የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ስምምነት” እና መሰሎቹ ይገኙባቸዋል። ለብዝሃ ሕይወት ክብካቤም ተግባር የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችል ሥርዓት ተዘርግቷል። ጠቅለል ተደርገው ሲታዩ፣ ስምምነቶችም ሆኑ ተቋማቱ ትኩረት የሰጡት ለብዝሃ ሕይወት ጥበቃ እና ክብካቤ ነው።

የብዝሃ ሕይወት እንክብካቤ አሁን ላለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን፣ ገና ወደፊት ለሚመጣው ተከታታይ ትውልድ ፋይዳ ያለው ተግባር ነው፤ ስለሆነም ነው የብዝሃ ሕይወት እንክብካቤ አስፈላጊ የሆነው። እንዲሁም ብዝሃ ሕይወት ሲወድም ጥቅማ ጥቅሙ ሳይታወቅ ሊወድም የሚችል የተፈጥሮ ሀብት አለ።

መደምደሚያ

በኢትዮጵያ የብዝሃ ሕይወት ሀብት አካባቢ ያሉ ተግዳሮቶች እየተገመገሙ፣ ችግሮችን ለመታደግ የሚበጁ ፖሊሲዎች፣ ሕጎች እና ደምቦች እያዘጋጁ ወደ ተግባር መቀየር ይገባል። ከዚያም ባለፈ “ሳይንሳዊ አስተሳሰብን በማስገዘብ(ሕዝባዊ በማድረግ)”፣ እንዲሁም ሳይንሳዊ አስተሳሰብን የባህላችን አካል በማድረግ፣ ችግሩን በማህበራዊ ደረጃ ልንገታው እንችላለን። “ሳይንሳዊ አስተሳሰብ” ማለት በሳይንሳዊ አስተሳሰብ ዘዴዎች መጠቀምን እንጂ የዕውቀት ዘርፍን አያመላክትም።

የሳይንሳዊ አስተሳሰብ አንዱ ዋና ዓላማ፣ አንድን ጉዳይ፣ ተግባር፣ ወዘተ. ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለማየት ማስቻሉ ነው። ስለሆነም ሳይንሳዊ አስተሳሰብ የሚያበረክትልን እይታ አድማሱም ሆነ ጥራቱ፣ ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ካላዳበረ አስተያየት ጋር ሲነፃፀር፣ በጣም የላቀ ነው። የማንኛውም የዕውቀት ዘርፍ የመረጃ አሰባሰብም ሆነ በመረጃ ላይ ተመርኩዞ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የሚጠቀምበት ዘዴ ሆነ ሂደቱ የሚስተናገደው በ “ሳይንሳዊ አስተሳሰብ” ነው።

የአገራችን ዓበይት ችግርች ናቸው ተብለው ከሚወሰኑት ጉዳዮች መኻከል፣ አገሪቱ ያላት የተፈጥሮ ሀብት ብሎም ብዝሃ ሕይወት በከፍተኛ የውድመት ሂደት ያለ መሆኑ ነው። የዚህ ውድመት መከሰቻው የለም አፈር መታጠብ፣ የመሬት የእፅዋት አልባሳት መመናመን፣ በአንዳንድ ቦታዎች የምድር አልባስ ጨርሶ መጥፋቱ፣ ምንጮች ብሎም ወንዞች መድረቃቸው፣ ወዘተ. ናቸው። ችግሮቹ ውስብስብ እና ተመጋጋቢ ስለሆኑ፣ የርስ በርስ ግንኙነቶችም አሏቸው። እነዚህ እና እነዚህን የመሰሉ ችግሮች ተደራርበው ከፍተኛ የሰው ምግብ እና የከብት መኖ እጥረት(እጦት)፣ የ መ ጠ ጥ ( ው ሃ ) መጥፋት፣ የማገዶ ችግር እና ተመሳሳይ ሌሎች ችግሮች በኢትዮጵያ እንዲከሰቱ አድርገዋል።

የተፈጥሮ ሀብት መመናመኑ እንዳይቀጥል መደረግ እንዳለበት በማመን፣ በብዙ አካባቢዎች የእርከን ግንባታ እና በተለይ በቅርብ ጊዜ የእፅዋት ተከላ ቢከናወንም፣ የተደረጉት ጥረቶች ተገቢውን (የሚጠበቀውን) ውጤት ገና አላመጡም። የሂደቱ አንዱ እንቅፋት፣ ጥረቱ/ ሙከራው በባህል/ ልማድ ላይ የተመሠረተ አለመሆኑ ነው። ችግሩን ለመፍታት ግን መጀመሪያ በተፈጥሮ ሀብት ክብካቤ ዙሪያ ባህላዊ ለውጥን ማምጣት ያሻል። መጥፎ ልማድን ለማስጣል እና በምትኩ ጥሩ ልማድን ለመተካት፣ የለውጥ መሠረታዊ ግብዓቶች(አንቀሳቃሾች/ ሞተሮች) ትምህርት ብሎም ዕውቀት/ ክህሎት ናቸው። ጉዞውም ረጅም ነው፣ አርቆ ማየት ያሻል።

ስለሆነም የባህልን ለውጥ ለማምጣት ከሚያገለግሉ መድረኮች ዋነኛው ትምህርት ቤት ነው። በትምህርት ቤት ውስጥ፣ ከትምህርት ጋር አቀናጅቶ ጥሩ ጥሩ ልማዶችን/ ባህሎችን መመሥረት ብሎም ማዳበር ይቻላል። በብዙ አገሮች የተፈጥሮ ክብካቤ ባህል የሚዳብረው በክለቦች አማካኝነት ነው። ስለሆነም፣ በየትምህርት ቤቱ አንዳንድ የተፈጥሮ ክብካቤ ክለቦች፣ በብቸኝነትም ሆነ፣ ከሳይንስ ክለቦች ጋር ተቀናጅተው በጣምራ እንዲመሰረቱ ጥረት ማድረግ ያሻል። የተመሠረቱም ካሉ እንዲጎለብቱ ማድረጉ ይበጃል። ተግባሮችም እንደየአካባቢው፣ ከአካባቢው ባህል፣ ማህበራዊ ኑሮ ጋር እየተዛመዱ፣ አመቺነታቸው እየተቃኘ፣ ተስማሚነታቸው እየተመረመረ፣ እየጠለለ ሥራ ላይ ሊውሉ(ሊተገበሩ) ይገባል።

እነኝህን እና እነኝህን መሰል ተግባሮች ዛሬ ነገ ሳይባል በማከናወን፣ ከከፍተኛ የሕልውና ሥጋት መላቀቅ ይቻላል።

የባህልን ለውጥ ለማምጣት ከሚያገለግሉ መድረኮች ዋነኛው ትምህርት ቤት ነው። በትምህርት ቤት ውስጥ፣ ከትምህርት ጋር አቀናጅቶ ጥሩ ጥሩ ልማዶችን/ ባህሎችን መመሥረት ብሎም ማዳበር ይቻላል።

Recommended For You