ቡናችን

የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና፣

የገቢ ምንጫችን ቡና ቡና፣

የእድገታችን ገንቢ ቡና ቡና፣

ዋልታ ነው ቡናችን ቡና ቡና፣. . .

“ጅማ ከተማ፣ ቦሳ ቀበሌ 04 ኪነት ቡድን”

በኢትዮጵያ አብዛኛውን አካባቢ አንድ ጊዜ የተወቀጠ ቡና ተመጥኖ ጀበና ውስጥ ከገባ በኋላ ከአቦል እስከ በረካ ይጠጣል። ጀበናው በተጣደ ቁጥር አተላው ተደፍቶ የተወቀጠ ቡና እንደአዲስ እየተጨመረ የሚጠጣ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን በሚላከው መጠን ወደ ውጭ ገበያ አይላክም ነበር። ስለሆነም የቡና አፈላል ስርዓታችንን ጠብቀን ማቆየታችን ለቱሪዝም ከሚያበረክተው አስተዋጽዖ በተጨማሪ የውጭ ንግድ አቅርቦት መጠንን ከፍ ለማድረግ የተጫወተው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም። ለማሳያነት በ1994 ዓ.ም. 126‚188 ቶን የቡና ምርት ሲመረት፣ ለውጭ ገበያ የቀረበው 110‚347 ቶን ነበር፤ ከ10 ዓመታት በኋላ በ2014 ዓ.ም. ደግሞ 652‚208 ቶን ቡና የተመረተ ሲሆን፣ ለውጭ ገበያ የቀረበው ደግሞ 300‚000 ቶን ነበር። ይህም፣ ከተመረተው ከግማሽ በላይ የሆነው ምርት ለውጭ ገበያ አለመቅረቡን ያሳያል። ለውጭ ገበያ ያልቀረበው ቡና በሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ተጠጥቷል ባይባልም፣ በከፍተኛ ሁኔታ እንደተጠጣ ግን መገመት ይቻላል (በኮንትሮባንድ ከሀገር የሚወጣውን ታሳቢ በማድረግ)።

ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ሀገር ነች። የቡና መገኛ

ሀገር እንደመሆኗ ቡናን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ሲገባት በዛ ልክ ተጠቃሚ አልሆነችም። ቡና ከነዳጅ ቀጥሎ በከፍተኛ ደረጃ ኢኮኖሚውን የሚዘውር እና የሚያነቃቃ ሰብል እንደሆነ በስፋት ይነገርለታል።

“የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና . . .” እንደምንለው ያህል ከማሳው ጀምሮ እስከ ውጭ ገበያው ባለመሥራታችን ብራዚል፣ ቬትናም፣ ኮሎምቢያ እና ኢንዶኔዥያ ሀገሮች ቡናን በብዛትም በጥራትም በማምረት የዓለም ገበያን በስፋት ተቆጣጥረውት ይገኛሉ። እነዚህ ሀገራት ለዚህ የበቁት የአሰራር ሥርዓታቸውን ትኩረት ከገበሬው ጀምሮ እስከ ውጭ ገበያው ድረስ በማድረጋቸው ነው።

ኢትዮጵያ ቡና ወደ ውጭ መላክ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በ2014 ዓ.ም የላከችውን ያህል ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ልካና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ አግኝታ አታውቅም፤ በ300 ሺህ ቶን ቡና አንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ዶላር አግኝታለች። በዚሁ ዓመት ለሶስተኛ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ በተደረገ የባለልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር (ካፍ ኦፍ ኤክሰለንስ) ላይ 480 ኪሎ ግራም ቡና ለፍጻሜ ውድድር ያቀረበው ከሲዳሞ ክልል፣ አርቤጎና ወረዳ፣ ቡርሳ ቀበሌ የመጣው አቶ ለገሠ በጦሳ በውድድሩ አንደኛ በመውጣት አንድ ኪሎ ቡና በ884 ነጥብ 10 ዶላር (ከ47 ሺህ ብር በላይ) ሸጧል። ይህ ገቢ በኢትዮጵያ የቡና ሽያጭ ታሪክ በከፍተኛ ዋጋ ሆኖ ተመዝግቧል።

በ2014 ዓ.ም. ለተገኘው ውጤት በአንድ በኩል በቡና ምርት ላይ የተለያዩ ጉልህ ሥራዎች መሠራታቸው በምክንያትነት ሲጠቀስ በሌላ መልኩ ደግሞ የብራዚል ቡና ምርት በድርቅና በውርጭ በመመታቱ የተገኘ ልዩ አጋጣሚ ያመጣው ዕድል ነው በሚል ሲገለጽም ይሰማል። ይህንና ሌሎች ቡናን የተመለከቱ ጉዳዮች በማንሳት ከቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይይሬክር አቶ ሻፊ ዑመር፣ ከኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር (በአዲሱ ስያሜ “የኢትዮጵያ ቡና ማህበር”) ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ እና ከኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ ተስፋ ጋር ቆይታ በማድረግ የሚከተለውን አቅርበናል።

በዓለም ውስጥ የተለያዩ ሀገራት፣ የተለያየ ጣዕምና መጠን ያላቸውን የቡና ምርቶችን ያቀርባሉ። በተለይ “አረቢካ” የሚባለው ቡና በአሜሪካ በጣም ተወዳጅና ሰባ አምስት ከመቶ ያህሉን የቡና ገበያ የሚሸፍን ነው የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ ኢትዮጵያ አረቢካ ቡናን ለዓለም ገበያ የምታቀርብ ቢሆንም፣ ብራዚል ግን ከፍተኛውን ድርሻ እንደምትይዝ ይጠቅሳሉ። በ2014 ዓ.ም. የብራዚል ቡና በውርጭ በመመታቱ፣ ቡና አቅራቢ የሆኑ ሀገራት በዚህ አጋጣሚ ተጠቃሚ እንደሆኑና ኢትዮጵያም የዚህ ዕድል ተቋዳሽ እንደሆነች ይገልጻሉ። ከዚህ በፊትም የብራዚል ቡና ውርጭ ሲመታው የኢትዮጵያ ቡና በከፍተኛ ሁኔታ የውጭ ገበያ አግኝቶ ገቢ ማስገኘቱን ያስታውሳሉ።

ከአሜሪካ ሀገር ገበያ በተጨማሪ ቻይናን ጨምሮ ሌሎችም ሀገራት በሰፊው ገበያ ውስጥ መግባታቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፣ በውርጭና በኮቪድ ምክንያት አንዳንድ ሀገራት የቡና ምርታቸው ሲቀንስ፣ በሀገራችን ያለው የቡና ግብይት ሥርዓት ግን የተወሰነ መሻሻል ማሳየቱን ይገልፃሉ፡፡ በሀገራችን የተመዘገበው የቡና ምርት ውጤት እንዴት እንደመጣ ከአጠቃላይ እይታ አንጻር መልስ ለመስጠት ያህል ነው እንጂ፣ ሀገር ውስጥ ባደረግነው ጥረት ነው? ወይስ ዓለም ውስጥ ባለው የአቅርቦት ሰንሰለት መበላሸት ነው? የሚለውን ለመለየት ሰፋ ያለ ምርምር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቡና ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ ደግሞ፣ ከፍተኛ ገቢ የተገኘበትንሁኔታ ሲያስረዱ፣ በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በኩል ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ቡናን በተመለከተ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በምክንያትነት ያነሳሉ። ግብይቱ ላይ ያለው ችግር ሙሉ ለሙሉ የተፈታ ባይሆንም ለማስተካከል የሚደረገውን ጥረት በበጎ ጎኑ የሚታይ መሆኑን ገልጸው፣ የብራዚል ቡና በድርቅና በውርጭ በመመታቱ በዓለም የቡና ገበያ አቅርቦት ላይ ክፍተት መምጣቱንና በዚህ ሳቢያም የዓለም ቡና ገበያ ዋጋ ቀደም ሲል ከነበረው ጭማሪ በማሳየቱ፣ በ2014 ዓ.ም. ከተላከው ቡና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሊገኝ ችሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር፣ በ2014 ዓ.ም የብራዚል ቡና በድርቅ በመመታቱ ምክንያት ገበያ ላይ የተወሰነ ክፍተት መፈጠሩን ቢያምኑበትም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለመገኘቱ ይሔ ምክንያት ነው የሚለውን እይታ ግን አይቀበሉም፤ ለዚህ ደግሞ ብራዚል ዓመቱን በሙሉ ገበያ ውስጥ መቆየቷን ለማሳያነት ያነሳሉ። ብራዚል እና ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ቡና አቅራቢ ሀገራት በመኖራቸው ተወዳዳሪ መሆንን እንደሚጠይቅ ጠቅሰው ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ መገኘት ከፍተኛውን ደረጃ የሚይዘው ባለፉት አራት ዓመታት ቡናን በተመለከተ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ችግሮችን በመለየት የቡና መጠን አቅርቦትና ጥራት ላይ የተሠራ ሥራ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው ይናገራሉ።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም. ብቻ ሳይሆን ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ከሁለት መቶ ሺህ ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ ማቅረቧን በማስታወስ፣ ለተከታታይ አምስት ዓመታት በመጠን ብቻ ሳይሆን በጥራትም ማምረት መቻሏንም ይገልጻሉ። በእነዚህ ዓመታት ውስጥም ብራዚል በሙሉ አቅሟ ገበያ ውስጥ እንደነበረችም በመጥቀስ ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ። እርሳቸው እንዳሉት፣ ለዚህ ውጤት መገኘት አስተዋጽኦ ካደረጉ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው፣ ቡና ላይ ያሉ ችግሮችን በመለየት በሪፎርም ለመፍታት ጥረት መደረጉ ሲሆን፣ ሪፎርሙን ሊያግዙ የሚችሉ አዋጆች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች ተዘጋጅተው ወደ ሥራ መገባቱ፣ በተለይ “Vertical Integration” በሚል የተደረገው ለውጥ በላኪና ተቀባይ መካከል ያለው ግንኙነት በአግባቡ እንዲፈፀም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። በዚህም የግብይት ሰንሰለቱ አጥሮ እንዲሳለጥ ሆኗል፤ የቡና መጠንና ጥራት በመጨመሩም የውጭ ምንዛሬ መጠንን ከፍ ማድረግ ችሏል።

ባለፉት ዓመታት ቡና ላይ የተሰሩ ውጤታማ ሥራዎችን መሰረት በማድረግ በ2015 ዓ.ም. 360 ሺ ቶን ቡና በመላክ አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ዕቅድ መያዙን ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ ያለፉት ሶስት ወራት 430 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 426 ሚሊዮን ዶላር በማግኘት የዕቅዱን 98 በመቶ መፈጸም እንደተቻለ ገልጸዋል።

የቡና የውጭ ንግድ ሰንሰለቱ የተሳለጠ መሆን ለከፍተኛ ገቢ መገኘት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ይኖራል። የግዥ ሰንሰለቱ ከገበሬ ጀምሮ እስከ ውጭ ንግዱ የተራዘመ ከመሆኑ በተጨማሪ በመሃል ደላሎችም አሉበት። አቶ ግዛት ምርቱ የት የት አካባቢ እንዳለ፣ከገበሬ የሚገዛበትን ዋጋ፣ በሳምንት ውስጥ ምን ያህል ቡና እንደተሸጠ፣ ያልተሸጠበት አካባቢ የት እንደሆነ፣ ወዘተ. መረጃ የሚሰጥ የተደራጀ ማዕከላዊ አካል የግልም ሆነ የመንግሥት ቢኖር ደላላ የሚመራበትንና የሚያዝበትን ሁኔታ ማስቀረት እንደሚቻል በአጽንኦት ይናገራሉ።

በዚህ ረገድ ያለውን ሁኔታ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ሲናገሩ፣ የቡና የውጭ ንግድ ሰንሰለቱ ብዙ ፈተና ነው ያለው። ደላላ በዚህ ዋጋ ነው የሚሸጠው በሚለው እንዲሸጥ ያደርጋል። ላኪዎች መረጃ እንዲያገኙ በሚል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት ቢቋቋምም መሥራት የሚገባውን ያህል አልሠራም ይላሉ። ብዙ ጊዜ ደላላ የበላይነት የሚያገኘው መንግሥት ሊሠራ የሚገባውን ሥራ በአግባቡ ሳይሠራ ሲቀር እና የቁጥጥር ኃላፊነቱን ሲያስተጓጉል ነው። ስለሆነም ደላላን ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ቡና የሚያመርተውንም ሆነ ቡና የሚያቀርበውን ገበሬ ምን ማድረግ እንደሚገባው ተገቢ የሆኑ መረጃዎችን እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይገባል በማለት ይመክራሉ።

አቶ ሻፊ ዑመር፣ በቡና የውጭ ገበያ ላይ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል አንዱ ደላሎች በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ እየገቡ ማወካቸው መሆኑን በጥናት ከተገኙ ውጤቶች ውስጥ እንደሚጠቀስ ያስቀምጣሉ። እንደእርሳቸው ገለጻ፣ ደላላ በሚበዛበት ጊዜ አርሶ አደሩ ተጠቃሚነቱ ይቀንሳል። የደላላን ሚና ለመቀነስና መፍትሄ ለማበጀት ደግሞ ሪፎርም ተሠርቷል። በሪፎርሙም ለአርሶ አደሩ የተለያዩ አማራጮች ቀርበውለታል። አርሶ አደሩ ራሱ ወደ ውጭ መላክ አይችልም ነበር፣ አሁን ግን ተፈቅዶለታል፤ በሀገር ውስጥም ለህብረት ሥራ ማህበራት መሸጥ ይችላል። አማራጩ ሰፊ ስለሆነለት አርሶ አደሩ ከደላላ ጋር የሚያገናኘው መስመር ተቋርጦ ጥራት ያለው ቡና በማቅረብ በተሻለ ዋጋ መሸጥ ችሏል። በገበያ ሂደቱ ቀደም ሲል አቅራቢ ራሱ ሰብስቦ ወደ ውጭ መላክ አይችልም ነበር። አሁን አቅራቢ ከፈለገ ፈቃድ አውጥቶ ወደ ውጭ መላክ እንዲችል ስለተፈቀደ ሌላው አማራጭ ሆኖ ቀርቧል። በእነዚህ አሠራሮች ደላላ ሙሉ ለሙሉ ተወግዷል ባይባልም ሚናውና ጫናው እንዲቀንስ ተደርጓል። አሠራሩን በማዘመንና በማጠናከር ከዚህ በበለጠ ሲሠራ ደግሞ የደላላን ሚና የበለጠ ማሳነስ ይቻላል።

በቡናና ሻይ ባለስልጣን በኩል የገበያ ሂደቱ እንዲያጥርና እንዲሳለጥ የተለያዩ አዋጆችና እነሱን ለማስፈጸም የሚረዱ መመሪያዎችና አሠራሮች እየወጡ ይገኛሉ። አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ካደረጉ አሠራሮች መካከል የቀጥታ የገበያ ትስስር አንዱ ነው። በተለይ በቀጥታ የገበያ ትስስር አሠራር ላይ መጀመሪያ እንዳሳዩት አይነት ጥራት ያለው ቡና አለማቅረብ እንዲሁም በተዋዋሉበት ዋጋለመገበያየት የቁጥጥር ዘዴ አለመኖር በባለድርሻ አካላት የሚነሱ ችግሮች ናቸው። የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በሚሠራቸው ሥራዎች ላይ የተለያዩ ደረጃዎች ይኖራቸው ይሆናል እንጂ ችግሮች ይኖራሉ በማለት የሚጀምሩት የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ፣ የቀጥታ ገበያ ትስስር አሰራር ብዙ አርሶ አደሮችን እንደጠቀመ ይገልጻሉ። አሠራሩ ያልገባቸው አንዳንድ ተጠቃሚዎች አሠራሩን በትክክል ካለመተግበራቸው የተነሳ አዲሱ አሰራር ችግር እንዳመጣ ሊያነሱ ይችላሉ ያሉት ዳይሬክተሩ ይህ እንዳይፈጠር፣ በባለስልጣኑ በኩል ተገቢ የሆነ ስልጠና መስጠቱን ጠቁመዋል፡፡ በተለይም ቀደም ሲል አላግባብ ተጠቃሚ የነበሩ ደላሎች የገበያ ሰንሰለቱ ስላጠረ ብዙ ሊሉ እንደሚችሉ ያነሱት አቶ ሻፊ አሰራሩ በአቅራቢና በላኪ መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በተገቢ ሁኔታ መፍታት የሚያስችልና ቅሬታ ያለው አካል ቅሬታውን አቅርቦ ማስፈታት የሚችልበት አሰራር ነው ብለዋል።

ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ መገኘት አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች አንዱ የባለልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር (ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ) በሀገራችን ውስጥ መከናወኑ እንደሆነ ይጠቀሳል። ቀደም ሲል ይካሄድ የነበረው አሜሪካ ነበር። አሁን ግን እንደ ኬኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ እና ኢትዮጵያ የመሳሰሉ በሀገራቸው ውስጥ የጥራት ውድድሩን ያካሄዳሉ። የቡና ጥራቱ ከ85 በመቶ በላይ ሲሆን፣ ከፍተኛ ጣዕም አለው ይባላል፤ ዋጋውም በከፍተኛ መጠን ይጨምራል፤ ከዚህ አኳያ ውድድሩ በኢትዮጵያ ውስጥ መደረጉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘቱ በተጨማሪ አምራች ገበሬዎች የሌሎቹን ውጤት በማየት በቀጣይ ጥራት ላይ ተበረታተው እንዲሠሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ቀደም ሲል አንድ ኪሎ ኮሜርሻል ቡና በአለም ገበያ ከሁለት ዶላር በታች የነበረ ሲሆን አሁን ከሁለት ዶላር በላይ ሆኗል። የቡናን ጥራት በማሻሻል ወደ ስፔሻሊቲ ቡና ግብይት ቢገባ እንዲሁም ቆልቶና ፈጭቶ መሸጥ ቢቻል በከፍተኛ ዋጋ መሸጥ ይቻላል በሚለው ዶክተር ቆስጠንጢኖስና አቶ ግዛት ይስማማሉ።

ቡና ቆልቶና ፈጭቶ መላክ በዕውቀት ስለሚሠራ ከደላላ ተጽዕኖ ያላቅቃል የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ አሜሪካ በሥራ በነበሩበት ወቅት ስታርባክስ የተባለ ድርጅት ከኢትዮጵያ ግማሽ ኪሎ ጥሬ ቡና አንድ ዶላር ባልሞላ ዋጋ ገዝቶ፣ ቆልቶና ፈጭቶ 24 ዶላር ይሸጥ እንደነበረ ያስታውሳሉ። በተለይ ስፔሻሊቲ ቡና በ ጥሬው ከ መላክ ቆ ልቶና ፈ ጭቶ ገ ዥ ዎች በሚፈልጉት ልክ በአንድም ሆነ በሁለት ኪሎ በማሸግ መላክ ለላኪውም ሆነ ለሀገር ከፍተኛ ገቢ እንደሚያስገኝ ያስገነዝባሉ።

አቶ ግዛት የባለልዩ ጣዕም ቡና ጥራት ውድድር ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ዕድገት አስተዋዖ እንዳለው አንስተው በሀገራችን በተለይ ገበሬው ጥራትን የማሻሻል ጥቅምን እንዲረዳ በማድረግ በኩል አስተዋጽዖ እንዳደገ ተናግረዋል። አክለውም፣ ውድድሩ ተጠናክሮ ከቀጠለ ከፍተኛ የምርት ጥራት ብሎም የውጭ ምንዛሪ እንደሚያመጣ ያላቸውን ተስፋም ገልጸዋል።

ዋና ሥራ አስኪያጁ ግብይቱን ከኮሜርሻል ወደ ስፔሻሊቲ ቡና ማስገባት በዓብይ ጉዳይ ሊታይ እንሚገባውና ከማሳው ጀምሮ እስከ ግብይቱ ጥራት ማሻሻል ድረስ ጠንካራ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ይመክራሉ። ከጥራት ጎን ለጎን በሔክታር ከ7 እስከ 8 ኩንታል የሚገኝበትንና በመጠንም ለማሳደግ የሚያስችል አሰራርን ማጠናከር ያስፈልጋልም ብለዋል።

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ እንደሚሉት ደግሞ፣ ስፔሻሊቲ ቡና ማለት የተለየ ትኩረት ሰጥቶ በዕውቀት ላይ በመመስረት መልቀም፣ ማድረቅ እና ማከማቸት እና ማሸግን የሚያካትት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ቡና ስፔሻሊቲ በማድረግ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት መንግሥት አበባን ለሚልኩ አምራቾች የሚያደርገውን ማበረታቻና ድጋፍ ለቡና አምራቾች እና ላኪዎችም ቢያደርግ ሰፊ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። አንዳንድ ሙከራዎች ቢኖሩም በስፋት ሥራዬ ብሎ ምን መሥራት እንደሚገባ፣ መንግሥት ከአምራቹና ከላኪው ጋር በመወያየት ወደ ስፔሻሊቲ ቡና ሽያጭ መግባት እንደሚያስፈግ አጽንኦት ሰጥተው ያስገነዝባሉ።

ከኮሜርሻል ወደ ስፔሻሊቲ ለመግባት ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ሻፊ ዑመር፣ በቡናና ሻይ ባለስልጣን በኩል ከዚህ በፊት ከተሰጠው በተጨማሪ በቅርቡ ጅማ፣ ሚዛን እና ሀዋሳ ላይ ስልጠና ተሰጥቷል። በዚህም ቡናን በጥራት በማምረት ወደስፔሻሊቲ ለማስገባት እስከታች ወረዳ ድረስ ስልጠናው ዘልቋል ይላሉ። እርሳቸው እንዳሉት፣ ስልጠናውን ተግባራዊ በማድረግ በርካታ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል፤ በዚያው ልክ ሀገሪቷም የውጭ ምንዛሪ አግኝታለች። ጥራት ያለው ቡና ከተለያዩ አካባቢዎች ስለሚመጡ ከዚህ በፊት ያልታዩ የቡና ዝርያዎችን ለማወቅም ዕድሉ ተገኝቷል። በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት ስፔሻሊቲ ቡና ለመላክ በተሠራው ሥራ የሚላከውን ቡና መጠን ከ36 በመቶ ወደ 40 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል። ይህ ተግባር ወደፊት በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል።

ስለኢትዮጵያ ቡና ሲነሳ መነሳት የሚገባው አንዱ የጫካ ቡና ነው ያሉት አቶ ግዛት፣ የጫካ ቡና ማንም ሰው ሳይንከባከበው አድጎ ይመለከተኛል የሚል አካል ለመልቀም ብቻ በመሄድ የሚሰበስበው እንደሆነ ያስረዳሉ። እርሳቸው እንዳሉት፣ የጫካ ቡና እንክብካቤ ስለማይደረግለት ጥራቱ እንክብካቤ እንደሚደረግለት ባይሆንም፣ ለማስታወቂያ አገልግሎት የሚሰጠው ጥቅም ግን ከፍተኛ ነው። “የኢትዮጵያ ጫካ ቡና በተፈጥሮ የበቀለና ከንክኪ በፀዳ ሁኔታ የሚያድግ ነው” በሚል መሸጡ ከሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ በበለጠ የኢትዮጵያ ቡናን ያሻሽጣል። ስለሆነም ማስተዋወቁ ላይ ተግቶ መሥራት ይገባል።

የጫካ ቡና ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ እንደማይገኝና ኢንዶኔዥያ እያቀረበች በከፍተኛ ዋጋ እንደምትሸጥ የሚገልጹት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ አሁን ገበሬዎችና ባለሀብቶች ሰፋ አድርገው ማምረት በመጀመራቸው መሻሻል አምጥቷል እንጂ፣ ቀደም ሲል በነበረመረጃ 98 በመቶ የኢትዮጵያ ቡና ወፍ ዘራሽ (የጫካ ቡና) እንደነበረ ያስታውሳሉ። አያይዘውም፣ የኢትዮጵያ ጫካ ቡና፣ የቡና መነሻ ተብሎ ዩኔስኮ መመዝገቡን ጠቅሰው፣ ይህን በማስተዋወቅ ገበያውን ማሳደግና ማስፋፋት እንደሚገባ ይናገራሉ። “በመረጃና በማስረጃ ራሳቸውን መግለጽ የሚችሉ የቡና ነጋዴዎችና አስተዋዋቂዎች መኖር አለባቸው። ቬትናሞች የቡና ገበያው ላይ ራሳቸውን ማስተዋወቅ ስለቻሉ ከዓለም ሁለተኛ ቡና ላኪ ሀገር ሆነዋል። ኮሎምቢያም ቡናን በማስተዋወቅ በኩል ከፍተኛ ሥራ በመሥራቷ ሶስተኛ ላኪ ሀገር ሆናለች። የማስተዋወቅ ሥራ ካልተሠራ በስተቀር በየጊዜው ተከታታይነት ያለው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አይቻልም። ጎረቤታችን ኤርትራ እንኳን የቡና አፈላል ባህልን በተለያዩ መንገዶች በከፍተኛ ሁኔታ ታስተዋውቃለች፤ ለቱሪዝም መስህብነትም ትጠቀምበታለች” በማለት የማስተዋወቅን ጥቅም ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ጫካ ቡና ተፈጥሯዊና በጣም ጣፋጭ ቡና ስለሆነ በተለይ አውሮፓዎች የሚፈልጉት እንደሆነ የሚጠቅሱት አቶ ሻፊ ናቸው። በተለይ በኤግዚቢሽኖች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሠራ እንዲሁም የጫካ ቡና ተብሎ ብራንድ እንደተለየላቸው ይናገራሉ። በተሠራው ሥራ ገበያ ከመገኘቱ በተጨማሪ ጎብኝዎችም መጥተው እየተመለከቱት ስለሆነ ለቱሪዝም የሚሰጠው አገልግሎት ከፍተኛ ነው ይላሉ።

አቶ ግዛት፣ ለቡና ምርት መጠንና ጥራት መሻሻል በፌዴራል ደረጃ የሚወጡ መመሪያዎች እስከታችኛው እርከን ድረስ ግንዛቤ አግኝተው የተናበበ ሥራ መሥራትን እንደሚጠይቅ ያነሳሉ። አፈጻጸሙ ሲታይ ግን ቡና ላይ እንዲተገበሩ የሚወጡ መመሪያዎች በክልሎችና በወረዳ ደረጃ ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑንም ይጠቅሳሉ፤ አቶ ግዛት እንደሚሉት ፌዴራሉ ያወጣውን ቡናን በሚመለከቱ የሚሰራጩትን መረጃዎ በክልሎች በኩል ተቀባይነት አግኝተው እስከታችኛው እርከን ድረስ በመውረድ ተግባር ላይ እንዲውል ማህበራቸው ከሁሉም አካላት ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት የበኩሉን ጥረት እያደረገ ይገኛል። ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ ቡና የምታቀርበው ኮሎምቢያ እና ብራዚልን ከመሳሰሉ ቡናን በብዛትና በጥራት ከሚያቀርቡ ሀገራት ጋር ተወዳድራ ነው። በመሆኑም፣ ሀገር ውስጥ ያለውን የቡና ማምረትና መላክ ሰንሰለት የተሳለጠና ውጤታማ ማድረግ ላይ ተነጋግሮ መግባባት እንደሚያስፈልግ ይጠቅሳሉ። ይሄ በጊዜ ሂደት ይሻሻላል የሚል ተስፋ አላቸው። አያይዘውም አሁን የሚታዩት በክልሎችና በወረዳ ደረጃ መመሪያዎች ተግባር ላይ ያለመዋል ችግር ሀገሪቱ ውስጥ የሚታየው ያለመረጋጋት ሁኔታ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ያነሳሉ።

ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ትስስር በመፍጠር በቅንጅት እንደሚሠራ የገልጹት ደግሞ አቶ ሻፊ ናቸው። አቶ ሻፊ እንደሚሉት የባለስልጣኑ ትልቁ የሥራ ድርሻ የክልሎችን አቅም መገንባት፣ መመሪያዎችንና አሠራሮችን ማውጣት ነው። ከዚህ አልፎ ግን አምራቹን፣ አቅራቢውን፣ ላኪውን እና ማህበራትን እየደገፈና እያበረታታ ይገኛል። አዋጅ፣ደንብና መመሪያ ሲያዘጋጅ ደግሞ ባለድርሻ አካላትን ያወያያል። ከክልሎችና ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ጋርም የቡናን ግብይት በተመለከተ በጋራ የሚወያይበት፣ የሚያቅድበት እና ሥራዎቹን የሚገመግምበት በሳምንት አንድ ጊዜ የግንኙነት ጊዜ አለው።

ቡና ወደ ውጭ ተልኮ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንዳያስገኝ ማነቆ ከሚሆኑበት ነገሮች አንዱ የኮንትሮባንድ ንግድ ነው። ቡና ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገለት የሚንቀሳቀስ አረንጓዴ ወርቅ ነው። ቁጥጥሩ ቢኖርም በኮንትሮባንድ የሚንቀሳቀስ ቡና መኖሩ በየጊዜው ይነገራል። እንደ አቶ ግዛት ገለጻ፣ ኮንትሮባንድን ለመቀነስ ቁጥጥሩ ላይ ያለውን አሠራር ፈትሾ ከማስተካከልና ከማጠናከር በተጨማሪ አሁን አምራች በሆኑ አካባቢዎች ያለውን የምርት መጠን መጨመር እንዲሁም፣ ለቡና ተስማሚ የሆኑ አዳዲስ መሬቶችን በቡና መሸፈን ያስፈልጋል።

ቡና ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገሮች በህገ ወጥ መንገድ እንደሚዘዋወሩ ያነሱት የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ በዓመት ከ1.5 እስከ 3.5 ቢሊዮን ዶላር በህገወጥ ንግድ ታጣለች የሚል ሪፖርት መኖሩን ይጠቅሳሉ። በቅርቡ ህንድ ውስጥ የተያዘ 16 ኪሎ ወርቅ መነሻው ኢትዮጵያ እንደሆነ የተሰማውን ዜና በማሳያነት ያነሳሉ። አያይዘውም፣ ህገወጥ ንግዶች የራሳቸው የሆነ የአቅርቦት ሰንሰለት እንዳላቸው በመግለጽ፣ ህገወጥ ነጋዴዎቹ ከባለስልጣናትና በየድንበሩ ካሉ ተቆጣጣሪዎች ጋር የጥቅም ተካፋዮች ከሆኑ ኮንትሮባንድን መከላከል ከባድ ስለሚሆን ጥብቅ ክትትል ማድረግን እንደሚጠይቅ ያሳስባሉ። ወርቅ፣ ቡና፣ የቁም ከብት፣ እጣንና ሌሎችም በህገወጥ መንገድ ከወጡ በኋላ በዚህ የተገኘው ዶላር ደግሞ ኢኮኖሚውን እንዳሻው ያተራምሳል ያሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው መንግሥት ስለጉዳዩ አያውቅም ማለት አስቸጋሪ ስለሚሆን መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል በማለት ያሳስባሉ። በመጨረሻም አፍሪካ በየዓመቱ በህገወጥ መንገድ ወደ 156 ቢሊዮን ዶላር ታጣለች፤ ይሄ ጉዳይ አፍሪካን በከፍተኛ ሁኔታ ስላደማ በኢትዮጵያም አፈጻጸሙ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው ማሻሻያ እንዲያደርጉበት ይመክራሉ።

የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እንዳሉት፣ በቡናና ሻይ ባለስልጣን በኩል ኮንትሮባንድን ለማስቀረት ሁለት ተግባራት ተከናውነዋል። አንደኛው ቡናን በተመለከተ ብቻ ሀገራዊ የኮንትሮባንድ ኮሚቴን ማቋቋም ሲሆን፤ ኮሚቴው ፌዴራል ፖሊስ፣ ጉምሩክ ኮሚሽን እና ክልሎችን አካቷል። ሁለተኛው ደግሞ፣ በባለስልጣኑ በኩል የቡና ግብይት ሂደትን በተመለከተ ሶፍትዌር በማበልጸግ የቡና ባላንስ እየተሠራ ችግር የሚፈጥሩትን ሰዎች በመለየት እርምጃ እንዲወሰድባቸው የማድረግ ተግባር ነው። እንደሳቸው ገለጻ ቁጥጥሩን በግልጽ ከማድረግ በተጨማሪ በስውርም የማጠናከር ሥራ ተሠርቷል። በዚህም ቡና የሰወሩ አካላት እና ተባባሪዎቻቸው ለሕግ ቀርበው ተጠያቂ እንዲሆኑ ለፌዴራል ፖሊስ መረጃዎች ቀርበዋል። የቡና ኮንትሮባንድ ንግድ ላይ ሰፊ ተግባራዊ ሥራ በመሠራቱ በጉልህ በሚታይ ደረጃ ህገወጥነቱ ቀንሷል። በ2015 ዓ.ም. ደግሞ ቅንጅታዊ አሠራሩን በማጠናከር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ዕቅድ በማውጣት ተፈጻሚ እንዲሆን እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ቡናን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ተከታታይነት ያለው የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ከሌሎች ቡና አቅራቢ ሀገሮች ጋር በመወዳደር ጥራት ያለው ቡና በከፍተኛ መጠን ማቅረብ ይጠበቅባታል። ይህን ተግባር ለመፈጸም ደግሞ በቡና ማምረት፣ ማቅረብ እና መላክ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላትን መንግሥት በክህሎትና በፖሊሲ ሊያግዛቸው ይገባል። በተጨማሪም፣ መንግሥት የቡና የውጭ ንግድ ግብይት ሰንሰለቱ እንዲያጥር አሁን እያደረገ ያለውን ጥረት በማጠናከር መተግበር ይኖርበታል። በዚህም በቡና የውጭ ንግድ ሂደቱ ላይ ሁከት የሚፈጥሩትን የደላላ ጫናንና ሚናን እንዲሁም የኮንትሮባንድ ንግድን በመቀነስ በሂደት ማስቀረት አለበት የሚለው የዝግጅት ክፍላችን መልዕክት ነው።

ስሜነህ ደስታ

Recommended For You