አልገፋ ያለው ዳገት

አብሮ አደግ ወዳጄ ተክዞ አገኘሁትና ‹‹ምን ሆነህ ነው? ›› ብዬ ጠየኩት። ‹‹ሁለት ወይም ሶስት ሆነው ባሉበት የኑሮ ውድነት ወሬ በሰፊው ይነሳል ሲባል ሰምተህ ታውቃለህ ወይ? ›› በማለት ጥያቄውን በጥያቄ መለሰልኝ። ‹‹ሰምቼ አላውቅም›› አልኩት። ‹‹አንተ እሱን ሳትሰማ፣ የኑሮ ውድነቱ አንድን ሰው ብቻውን እንዲናገር ማድረግ ደረጃ ደርሷል! ›› አለኝ።

ወዳጄ እውነት አለው። የኑሮ ውድነቱ ያልነካው የህብረተሰብ ክፍል የለም ማለት ይቻላል። በተለይ ዕለት በዕለት በምንጠቀምባቸው ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት የትየለሌ ነው። ለምሳሌ የሾላ ወተትን እንመልከት ግማሽ ሊትሩ አስር ብር ሲሸጥ ቆይቶ አስራ ሁለት ብር ገባ። ከዚያ 15፣ 18፣ 20 እያለ አሁን 25 እና ከዚያ በላይ እየተሸጠ ይገኛል (ይሄ ጽሑፍ ታትሞ እስኪወጣ ድረስ ዋጋው ከ40 በላይ እንዳይሆን ምን የሚያግደው ነገር ይኖራል?)። ሌሎቹማ ወተቶች ዋጋቸው የሚደመጥ እንጂ የሚሸመት አልሆነም። ድፍን ምስር አንድ ኪሎ 120 ብር ሲሸጥ ቆይቶ 130፣140፣150፣160 እያለ አሁን ዋጋው ነጋዴው በወሰነው ሆኗል። ጠዋት 160 ተገዝቶ ማታ እዚያው ቦታ ለመግዛት ሲኬድ 170 ይባላል። አቅሙ ካለ መግዛት፤ ከሌለ ትቶ መሄድ እንጂ አቤት ቢባል ጉዳዩን በጥልቀት አይቶ መፍትሔ የሚሰጥ አካል የለም።

ይሄም ስለሆነ ነጋዴው በዋጋው ላይ እንደፈለገው ያዛል። እንዲሁም የሚሸጠውን ሸቀጥ በማከማቸት ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ እንዲንር ያደርጋል። ከዚህ አንጻር ዘይት ላይ የተሠራውን ስንመለከት አምስት ሊትር ፈሳሽ ዘይት ሶስት መቶ ብር ይሸጥ ነበር። ነጋዴዎች ከገበያ ለዐይን እንኳን እንዲጠፋ አድርገው በኋላ ላይ አንድ ሺህ ብር እና ከዚያም በላይ በሆነ ዋጋ ሸጠዋል።

ዘይት ላይ የተደረገውን ብቻ ሳይሆን በሌሎች ምርቶች ላይ ያለውንም መጥቀስ ይቻላል። የሲሚንቶ ዋጋ መሸጥ ከሚገባው ከሶስት እጥፍ በላይ መሸጡ የአደባባይ ምስጢር ነው። አንድ ቤት የሚሠራ ሰው መደበኛውን ሂደት በመከተል ሲሚንቶ ማግኘት ፈተና ቢሆንበት አማራጭ ባገኝ ብሎ ደላላ ጋር ሲደውል “አሁን መግዛት ትችላለህ መኪና ላይ ሲሚንቶው ተጭኖ ገዢ እየጠበቀ ነው” ብሎ ቀለል አድርጎ በነገረው መሰረት ተደራድሮ የሚችለውን ያህል መጠን በመውሰድ ችግሩን አቃሏል። በመደበኛ አካሄድ ማግኘት እንዳይቻል ችግር የሚፈጥረው ማን ነው? ችግሩስ እንዴት ይፈታል? በሚል ትኩረት ሰጥቶ ከልብ የሚሠራ አካል ባለመኖሩ ችግሩን የሚፈጥሩት አካላት በድርጊታቸው ገፍተውበታል።

አንዳንድ ጊዜ “ችግሩን ለማቅለል ይሄን የመሰለ የመፍትሔ አካሄድ ተከትለናል” ተብሎ በተነገረ በጥቂት ቀናት ውስጥ ያው ችግር መልኩን ቀይሮ በሌላ መንገድ ይገለጻል። ይሄን በሲሚንቶ ንግድ ላይ በስፋት ለማስተዋል ተችሏል። ስለኑሮ ውድነቱ አስከፊነት ማሳያ ለማቅረብ የቱ ተነስቶ፣ የትኛው ይቀራል በሚል ለመምረጥ ይቸግራል። በዚህ የኑሮ ውድነት የተነሳ ከአምስት ዓመት በፊት ትዳር ይዘው ከቤተሰባቸው የወጡ ወጣቶች ትዳሩን ማስቀጠል ስላቃታቸው አሁን ሁለት ልጆቻቸውን እንደ ዕቃ ተካፍለው ወደ ቤተሰቦቻቸው ቤት መመለሳቸውን አውቃለሁ። መጀመሪያ ተፋተው መስሎኝ ነበር፤ በኋላ ባልየው ሲያስረዳኝ ተፋተው ሳይሆን ቢያንስ የቤት ኪራይ ወጪ ለማዳን ያደረጉት ዘዴ እንደሆነ ነገረኝ።

የዋጋ ግሽበትና የማኅበረሰቡ የመግዛት አቅም ማነስ የፈጠረው የኑሮ ውድነት ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ዕድገቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቶ አሁን እንደሚታየው ለመቆጣጠር በሚያስቸግር ደረጃ ደርሷል። ስለሆነም አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልገዋል። የኑሮ ውድነቱን የሚመጥን መፍትሔ ለመስጠት በዋናነት መንግሥት የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ አለበት። መንግሥት ኃላፊነቱን በመወጣት መቅደም አለበት እንጂ ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደድርሻቸው ኃላፊነት ወስደው መሥራት ይገባቸዋል።

መንግስት የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ የተለያዩ ጥረቶች አድርጓል። ነገር ግን የውስጥ እና የውጭ ተጽዕኖዎች በፈጠሩት ጫና ዘላቂ መፍትሔ ባለማምጣቱ ሕዝቡ ሊቋቋመው ከሚችለው በላይ ሆኖበታል። በተለይ መንግሥት የነዳጅ ድጎማውን ማንሳት ከጀመረ በኋላ ያለው ደግሞ የተለየ ነው። ወደፊት ያለው ከዚህ የባሰ እንዳይሆን ምን ቢደረግ ይሻል ይሆን? ለዚህ ብቁ የሆነ ምላሽ መስጠትና መፍትሔ የሚሆን የውሳኔ ሀሳብ ማቅረብ የሚችሉት ለመንግሥት ቅርብ የሆኑ ባለሙያዎች ናቸው። ነገር ግን አንድ ወዳጄ እንደሚለው እነሱ የኑሮ ጫናው እንደሕዝቡ አይሰማቸውም። ይህ ወዳጄ ስለእነዚህ ሰዎች ሲያስረዳ ‹‹እነሱ የነዳጅ ተብሎ የሚሰጣቸው ብር በሊትር ተተምኖ ነው የሚያገኙት፤ የአርባ ሊትር ነዳጅ በብር ተሰልቶ የሚሰጣቸው ከሆነ ዋጋ ጨመረ፣ ቀነሰ ለእነሱ ምንድን ነው? ዋጋ ሲጨምር ገንዘቡ ተጨምሮ ይሰጣቸዋል፤ እንዴት ተብሎ መፍትሔ ይምጣ! ›› በማለት በምሬት ይናገራል።

መቼም የኑሮ ውድነቱ ሁሉም እኩል እንዲሰማው ባይጠበቅም፣ አብዛኛውን ሕዝብ ዕለት በዕለት እያመሰው ይገኛልና ተመጣጣኝ መፍትሔ መስጠቱ ግድ ይላል። አስከፊ የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስና መረጋጋት ለመፍጠር መፍትሔ ይሆናል ብዬ ከምለው ነገር አንዱ የሥራ ግብርን ምጣኔን ማሻሻል ነው። በፌዴራል ገቢ ግብር አዋጅ 983/2008 እንደተደነገገው፣ ማንኛውም ተቀጣሪ የሚያገኘው ጠቅላላ የወር ገቢ ከ601 ብር በላይ ሲሆን፣ ከአሥር በመቶ አንስቶ፣ እስከ 35 በመቶ የሚደርስ የግብር ምጣኔ ይጣልበታል። ይህን የሥራ ግብር ምጣኔን ማሻሻል መንግሥት ሊያገኝ የነበረውን ገንዘብ ሊያሳጣው እንደሚችል ይታወቃል። ነገር ግን የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ሌሎች ሀገሮችም የሚጠቀሙበት ስልት ስለሆነ መንግሥት እየመረረውም ቢሆን ለዜጎቹ ሲል ሊጠቀምበት ይገባል። ይህን ስልት በመጠቀሙ የሚያጣውን ገንዘብ ጥናት ተደርጎ ወደ ተግባር ያልገባውን የንብረት ታክስን ወደ ተግባር በማስገባት ሊያካክሰው ይችላል።

የሥራ ግብር ምጣኔ ሲሻሻል የኑሮ ውድነቱ በከፍተኛ ሁኔታ ያጠቃቸውን ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ የሚያገኙትን የሚያግዝ ሊሆን ይገባዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊታይ የሚገባው ሌላ ጉዳይ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ነው። የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) የሠራተኛውን የኑሮ ጫና ታሳቢ በማድረግ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን በሚመለከት ለመንግሥት ጥያቄ አቅርቦ በረቂቅ ደንቡ ላይ ውይይት ተደርጓል። ረቂቁም በቀድሞው የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡ የሚታወቅ ነው። እስካሁን ግን ረቂቁ ታይቶ ወደ ተግባር አልተገባም። በሚኒስትሮች ምክር ቤት አማካይነት ደንቡ እንዲወጣ ቢደረግ ከድህነት ወለል በታች ለሚኖሩ ዜጎች መፍትሔ ይሆናል። በተለይ በዚህ ወቅት ያልወጣ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ክፍያ መቼ ሊወጣ ነው? ለአብነት ኬንያ የዓለም አቀፍ የላብ አደሮች ቀን ሲከበር ከዚህ ቀደም በሥራ ላይ የነበረውን ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የኑሮ ውድነትን ከግምት ውስጥ በመክተት፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አደባባይ ተገኝተው ዝቅተኛ የደመወዝ ወለሉን በአዋጅ በስድስት በመቶ እንዲጨምር አስደርገዋል። ኢትዮጵያ ከመነሻውም ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የሌላት ሀገር በመሆኗ መንግሥት በጉዳዩ ላይ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል።

አሁን እየተደረገ ያለው የሸማቾች ማኅበራት ከተለያዩ የጅምላ አከፋፋዮች ጋር ትስስር በመፍጠር በመረከብ ኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ለሽያጭ ማቅረባቸው የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ተጠቃሽ የሚሆን ነው። በተለይ የእሁድ ገበያ ተብሎ በተለያዩ ቦታዎች በማኅበራቱ የሚሸጡ መሰረታዊ የሆኑ ምርቶች በብልጣብልጥ ነጋዴዎች ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች በውድ ዋጋ ለሚገዛ ሰው መፍትሔ ሆነዋል። የዋጋ ውጣ ውረድ ስለሌለው በትክክለኛው ወቅታዊ ዋጋ ለመግዛትም አስችለዋል። ይህ ተግባር ያለበትን ውስንነት በማሻሻል ባልተቆራረጠና ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ቢፈጸም ለኑሮ ውድነቱ መረጋጋት ያለው ድርሻ ከፍተኛ እንደሚሆን እስካሁን ካሳየው ስኬት መመልከት ይቻላል።

ጽሑፌን የማጠቃልለው ማሳሰቢያ በመስጠት ነው። ‹‹የኑሮ ውድነቱ መናር ያለበትን ያህል ንሯል፤ ከዚህ በኋላ መፍትሔው ጫንቃዬን አደንድኜ የሚመጣውን ችግር መጠበቅ ነው›› የሚለው የኅብረተሰብ ክፍል ቁጥሩ አይሎ፣ ነገን በፍርሃትና በሰቀቀን የሚጠብቅ ከሆነ አደጋው ለሀገር ይተርፋል። ስለሆነም ለመፍትሔው የአንበሳውን ድርሻ የሚውስደው መንግሥት፣ ማኅበራዊ ቀውስ ከመምጣቱ በፊት የኑሮ ውድነቱን የሚመጥን መፍትሔ ይስጥ።

ስሜነህ ደስታ

Recommended For You