የቀንዱ ቀንደኛ ሀገር ተጋድሎ

ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን እና ጂቡቲን የያዘው የአፍሪካ አህጉር ምሥራቃዊ ጫፍ (በቅርጻዊ አጠራሩ የአፍሪካ ቀንድ) በምስራቅ በህንድ ውቅያኖስ እና በሰሜን በኤደን ባህረ ሰላጤ መካከል ይገኛል። የአፍሪካ ቀንድ በመቶዎች በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ወደ አረብ ባህር ይዘልቃል። ከ 772,200 ስኩዌር ማይል በላይ የሚሸፍን ሲሆን አብዛኛው ከፊል ደረቃማ እና ደረቃማ የአየር ጠባይ ያለው ነው። አካባቢው ለባህር ንግድ፣ ለነዳጅ ታንከሮች እና ለጭነት አገልግሎት ከፍተኛ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ የዓለም ኃያላን ሀገራት አይን ማረፊያ ነው።

ኢትዮጵያ በቀጠናው በሚገኙ ሀገሮች ሰላም፣ ፀጥታና መረጋጋት ላይ ቁልፍ ሚና የምትጫወት ሀገር ነች። ከሦስት አስርት አመታት በፊት በሩዋንዳ የተፈጸመውን የዘር ፍጅት ተከትሎ ሀገሪቱን ለማረጋጋት ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን ከላኩ ሀገራት መካከል ግንባር ቀደም ናት። አሜሪካኖች ተዋርደው ወደ ወጡባት ሶማሊያ ወታደሮቿን በመላክ መንግሥት አልባነትንና አክራሪነትን ታግላ መንግስት እንዲመሰረት ጉልህ ሚና ተጫውታለች። በሱዳን-ዳርፉር ግዛት የእርስ በርስ ግጭት እንዳይስፋፋ የበኩሏን አስተዋጽኦ አበርክታለች። ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በይገባኛል በሚወዛገቡበት የአብዬ ግዛት ከሁለቱም ወገን እምነት የተጣለባት ብቸኛ ሀገር ሆና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ስር ሰላም አስከባሪ ኃይል በማሰማራት በጎ ሚናዋን አጠናክራ ቀጥላለች።

ይህ ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ የምትጫወተው ቁልፍ ሚና በታሪካዊ ጠላቶቿ እና በአካባቢው ጥቅማቸውን ለማስከበር በሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት ዘንድ በበጎ አይታይም። ስለዚህም ምቹ ጊዜ አገኘን ብለው ባመኑ ቁጥር ይህችን ታላቅ ሀገር ወደ ደርዘን ትናንሽ ሀገርነት ለመቀየርና ህዝቦቿን ለመበተን የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። ይህን ማድረግ የማይቻል ሆኖ ሲገኝ ደግሞ የተረጋጋችና ሰላማዊ ሀገር እንዳትሆን የጦርነት አውድማ ሊያደርጓት ላይ ታች ይላሉ። ኢትዮጵያ በቀጣናው ካሉ ሀገራት ጋር ያላትን የመሰረተ ልማት ትስስር በአይነትና በመጠን እያሰፋች መምጣቷ እንቅልፍ ነስቷቸዋል።

ፀሐይ በምስራቅ እንደምትወጣ የአፍሪካ የነጻነት ፀሐይ ኢትዮጵያም በምስራቁ የአህጉሪቱ ክፍል መገኘቷ ግጥምጥሞሽ ብቻ አይመስልም። እንደ ትናንቱ አድዋ ሁሉ ለወቅታዊው የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ እምቢኝ አሻፈረኝ በማለት የሞት ሽረት ተጋድሎ አድርጋ ዛሬም ለአፍሪካውያን የነጻነት አርማ ሆና መቀጠሏን በተግባር አስመስክራለች። በዚህ ጽሑፍ ኢትዮጵያ የገጠማትን ውስጣዊ ችግር ለመሻገር ባደረገችው ተጋድሎ የተቀናጀችውን ድል እና አጋጣሚውን ተጠቅመው ከካርታ ላይ ሊፍቋት የተነሱ ጠላቶቿን ርብርብ ከምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ጋር አያይዘን እንመለከታለን፤ መልካም ቆይታ።

አሞራ በሰማይ …

“አሞራ በሰማይ ሲያይሽ ዋለ” ተብሎ የተዘፈነው ለአፍሪካ ቀንድ ሳይሆን አይቀርም። ምድሯ ላይ ላለው ስጋ የሚፋለሙት የሰማይ አሞራዎች ቁጥር የትየለሌ ነው። መሬት ላይ ያለው ሀቅ እና ቀጠናውን ለመቀራመት የሚቋምጡ ሀገራት የሚያስተጋቡት ትርክት የማይገናኝ ነው። “ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ግጅራ ነሽ ይሏታል” ነው ነገሩ። አፍሪካን አይዞሽ ባዮቹ አመዛኝ “ወዳጆቿ” ማጽናኛቸው “No matter how bad you are, you’re not useless. You can still be used as a bad example.” የሚል ነው። አጃኢብ! እውነታው ግን ሌላ ነው። የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ህዝቦች በባህል፣ በታሪክ፣ በቋንቋ ፣ በአብሮ መኖር፣ በጋብቻ በመተሳሰር እና አንዱ የሌላኛውን ሀገር እንደ ሁለተኛ መኖሪያው በመቁጠር ጥብቅ ግንኙነት የመሰረቱ እና ዘመናትን በዘለቀ ትስስር የተጋመዱ ናቸው።

አንዳንድ ኃያላን ሀገራት እንዲሁም አህጉር እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በሌሎች መሰል ቀጣናዎች ባልተለመደ ሁኔታ ለአፍሪካ ቀንድ ብቻ ልዩ መልዕክተኛ መሾማቸው ለብዙዎች እንግዳ ነገር ነው። አሜሪካ፣ ቻይና፣ ብሪታንያ፣ የአውሮፓ ህብረት ተመድ እና የአፍሪካ ህብረት በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ (ልኡክ) ሾመዋል። እነዚህ ሀገራት እና ተቋማት በአፍሪካ አህጉር ካሉ ክፍሎች ውስጥ ልዩ አምባሳደር የሾሙት ለአፍሪካ ቀንድ ብቻ ነው።

አሜሪካ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ ቀድሞ ያልነበረ አዲስ መዋቅር በመፍጠር የአፍሪካ ቀንድን ሁኔታ “ለመከታተል” በሚል ልዩ መልዕክተኛ ከመደበች ገና ሁለተኛ አመቷን መያዟ ነው። መጀመሪያ ጄፍሪ ፌልትማንን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አድርጋ ሾማ የነበረ ሲሆንውጤት እንዳጣ የእግር ኳስ ቡድን አንዱን አባራ ሌላኛውን እየተካች በሁለት አመት ውስጥ አራት ልዩ መልዕክተኞችን አፈራርቃለች። ሴናተር ክሪስ ኩንስ፣ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ፣ አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ እና አሁን በኃላፊነት ላይ ያሉት አምባሳደር ማይክ ሐመር ለዲፕሎማቲኩ መንደር እንግዳ በሆነ መንገድ ተፈራርቀው የአፍሪካን ቀንድ “ሾፍረዋል”

ፎሬይን ፖሊሲ የተባለው መጽሔት አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ ከኃላፊነት መነሳታቸውን ሲሰማ እርምጃውን “ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የጅምላ ግድያና የረሃብ ስጋት ባለበት ቀጣና ትልቅ የሆነ የዲፕሎማሲ ክፍተት የሚፈጥር” ሲል ዘግቦት ነበር። መሰል ዓለም አቀፍ የዜና ተቋማት የአፍሪካን ቀንድ ሲኦል አድርገው በማቅረብ ራሳቸውን የቀጣናውን ህዝብ ለመታደግ እሳት ውስጥ የተገኘ “መልአክ” አድርገው ማቅረብ መደበኛ ስራቸው ነው። በጎ ነገርን ላለማየት ሆነ ብሎ አይንን የጨፈነን ሰው እውነታውን እንዲመለከት መለማመጥ ጉንጭ ማልፋት ቢሆንም በቀጣናው ያሉ ኢትዮጵያን የመሰሉ ሀገራት ግን ሳይታክቱ እውነታውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስረዳት ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ከማድረግ አልተቆጠቡም። ጽናት!

አሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ከሾመች ከ 270 ቀናት በኋላ ቻይናም በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛዬን እወቁልኝ ብላለች። ቻይና አምባሳደር ሹ ቢንግን በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አድርጋ መሾሟን ይፋ ስታደርግ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ በኩል በሰጠችው መግለጫ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ልማት እንዲጎለብት ለማበረታታት እንደምትሰራ ገልጻለች። በቀጣናው ያሉ ሀገራት የሚያጋጥሟቸውን የፀጥታ እና ደህንነት ስጋቶችን ለመቀልበስ የሚያደርጉትን ጥረት እደግፋለሁ ስትልም በአካባቢው የሚገኙ ሀገራትን አለውላችሁ ብላለች። በዚህ እርምጃዋ ያልረካቸው የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ ሁሉም ሀገራት በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ላይ ያተኮረ ጉባዔ እንዲያደርጉ ሃሳብ እስከመገፋፋት ደርሰዋል።

የብሪታኒያ መንግስት ለአፍሪካ ቀንድ እና ለቀይ ባሕር አካባቢ አዲስ ልዩ መልዕክተኛ መሾሙን ያሳወቀው ከአምስት ወራ በፊት ነበር። በወቅቱ በብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ በአፍሪካ ቀንድ ካለው የሰብዓዊ ቀውስ እስከ ገልፍ ባለው ቀጣና ብሪታኒያ ከቀይ ባህር ጋር ያላት ግንኙነት ጠንካራ ሰው እንደሚፈልግ ገልጸው ነበር። ከሹመት ዜናው ጋር በቀይ ባህር እና በአፍሪካ ቀንድ ባሉ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የብሪታኒያን ምላሽ የልዩ መልዕክተኛዋ ስራ መሆኑ ተገልጿል። ለአፍሪካ ቀንድ እና ለቀይ ባሕር አካባቢ የተሾሙት ልዩ መልዕክተኛ ሳራህ ሞንትጎሜሪ ናቸው። አዲሷ ልዩ መልዕተኛ የአፍሪካ ቀንድ በግጭት፣ባለመረጋጋትና በአየር ጸባይ ለውጥ ምክንያት የሰብዓዊ መቅሰፍት ላይ እንደሆነ በመግለጽ ስለቀጣናው ያላቸውን የተንሸዋረረ ግንዛቤ ተንፍሰው ትልቅ ስራ ይጠብቀኛል ሲሉ ለመኩራት ዳድቷቸው ነበር።

ልዩ መልዕክተኛ ከመሾም በበለጠ በአፍሪካ ቀንድ የጦር ሰፈር ለመገንባት የሚደረገው እሽቅድምድም ሀገራትን ፍጥጫ ውስጥ እየከተተ ይገኛል። ፈረንሳይ፣ ቱርክ ፣አሜሪካ፣ ቻይና እና ጃፓን በቀጠናው የጦር ሰፈር ገንብተዋል። ጂቡቲ የስምንት ሀገራትን የጦር ሰፈሮች በመያዝ በቀዳሚነት ተቀምጣለች። ሀገራቱ አሜሪካ፣ ጃፓን ፣ ጣሊያን፣ ቻይና፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ፈረንሳይ ፣ ጀርመን እና ስፔን ናቸው። በኤርትራ ደግሞ የሩሲያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የጦር ሰፈራቸውን ገንብተዋል። በሶማሊያ የቱርክ የጦር ሰፈር የተገነባ ሲሆን በሶማሊላንድ የተባባሩት አረብ ኤምሬትስ የቀጣናው ሁለተኛ ሰፈር ይገኛል። ሩሲያ ሁለተኛ የጦር ሰፈሯን በሱዳን ለመገንባት የአሜሪካ ተጽዕኖ ያረፈበት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናት። ሌሎች ሀገራትም በአካባቢ ባሉ ሀገራት ውስጥ የጦር ሰፈር ለመገንባት መንገድ ላይ ናቸው።

ሎግማን ኦስማን በተመድ የአፍሪካ ቢሮ የደህንነት አማካሪ ሲሆኑ የአፍሪካ ቀንድ የጸጥታ እና ደህንነት ጉዳዮችን በመተንተን ይታወቃሉ። ሎግማን ኦስማን ለአንላይን የዜና ድረ ገጽ እንደተናገሩት፤ ባለጸጋ ሀገራትን ጨምሮ መላው የዓለማችን ሀገራት ሁሉ የተፈጥሮ ሀብት፣ ሰፊ የገበያ አቅም ያለው ህዝብ ብዛት መኖር እና አካባቢው ከሌሎች አህጉራት ጋር ያለው ቅርበት ሀገራቱን ለአፍሪካ ትኩረት እንዲያደርጉ አድርጓል ብለዋል። እነዚህ ሀያላን ሀገራት ወደ አፍሪካ ቀንድ መምጣታቸው በራሱ ችግር ባይኖረውም የፍላጎት መወሳሰብ እና በሉዓላዊ ሀገራት የውስጥ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ መግባትን ሊያስከትል እንደሚችል ስጋታቸውን አክለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ የአፍሪካ እና ኢስያ ጉዳዮች መምህር ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ በበኩላቸው አፍሪካ ቀንድ በዓለም ላይ ካሉ ተፈላጊ ቦታዎች መካከል አንዱ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ሽብርተኝነት፣ የባህር ላይ ዝርፊያ እና ሌሎች ጉዳዮች በአካባቢው ያሏቸውን ጥቅሞቻቸውን እንዳያሳጧቸው በመስጋት የአፍሪካ ቀንድ በኃያላኑ ሀገራት ትኩረት የሚደረግበት ቦታ በመሆኑ፣ ወታደራዊ የጦር ሰፈርን ከመገንባት ጀምሮ ልዩ ልዑክ እስከመሾም የደረሰ እንቅስቃሴዎች እንደሚደረጉበት ይናገራሉ። እነዚህ የዓለማችን ሀገራት ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ የአጋር ሀገራት መሪዎች በስልጣን ላይ እንዲቆዩ ድጋፍ ማድረግን ጨምሮ ለጥቅማቸው ስጋት የሆነ ሀገር ስርዓትን እንዳይረጋጋ በሚል ቡድኖችን እና አማጺዎችን እስከመርዳት ሊደርሱ እንደሚችሉም ዶክተር ሳሙኤል ይገልጻሉ። ከዚህ በፊት አፍሪካ ቀንድ ላይ ትኩረት የሚያደርጉት ዋና ዋና የዓለማችን ሀያላን ሀገራት እንደነበሩ በማውሳት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ቱርክ፣ ኢራን ፣ግብጽ እና መሰል ሀገራትም ለቀንዱ ልዩ ትኩረት በመስጠት ላይ ናቸው። እነዚህ ኃያላን ሀገራት ጥቅማቸውን ሊያስጠብቁላቸው የሚችሉ ታዛዥ ሀገራትን መያዝ ዋነኛ ትኩረታቸው በመሆኑ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትከጥገኝነት ሊያወጧቸው የሚችሉ ስራዎችን ከወዲሁ ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ።

በቀጣናው ተስፋን የሚሰጡ መልካም ዜናዎችም እየተሰሙ ነው። የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ የሀገራቸውን ቀጣይ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ስትራቴጂ በተመለከተ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ “ቅድሚያ ሰጥተን ከምንሰራባቸው የውጭ ጉዳይ ቁልፍ ስራዎች መካከል ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያለንን ሁሉን አቀፍ አጋርነት ማጠናከር አንዱ ነው” ማለታቸው ቻይና ለቀጠናው ከሰጠችው ትኩረት ጋር ተደምሮ አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት በአፍሪካ አህጉር ብሎም በአፍሪካ ቀንድ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ልጓም ሊበጅለት ጊዜው መቃረቡን አመላካች ተደርጎ እየተወሰደ ነው። እ.አ.አ በ2019 ስትራቴጂካዊ በሆነ ውሳኔ በሶቺ የተጀመረው የሩስያ አፍሪካ ጉባኤ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችል ሁነኛ ሀዲድ በመሆን እያገለገለ ነው። ቻይና እና ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር ያላቸው ግንኙት የሚመራበት መርህ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥን እና ወንድማማችነትን በማጠናከርና ሉዓላዊነትን ማክበር ላይ ያተኮረ በመሆኑ የእጅ ጠምዛዦቹ እና አዛዥ ናዛዦቹ ጀንበር መጥለቅ አይቀሬ መሆኑን ነጋሪ ሆኗል። የቀጣናው ትልቅ ሀገር ኢትዮጵያ የዚህ ስበት ማዕከል መሆኗ ሳይታለም የተፈታ ነውና አሁናዊ ተጋድሎዋ ከቀንዱ አውድ ተለይቶ ሊታሰብ አይችልም።

ምኞት አይከለከልም

ኢትዮጵያ ያላት የመልማት እምቅ አቅም እንዲሁም እየጨመረ የመጣው በምስራቅ አፍሪካ ያላት ተሰሚነት ስጋት ውስጥ እየከተታቸው፤ በሌሎች ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት በምታራምደው የገለልተኝነት አቋም እና በዓለም አቀፍ ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ አውንታዊ ሚና በመጫወት የምታበረክተውን አስተዋጽኦ ተመልክተው “ይህች ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም” በሚል ጥርሳቸውን የነከሱባት አንዳንድ ኃያላን ሀገራት አሉ። የዛሬ አያያዟን አይተው የነገ ተስፋዋ እያስፈራቸው፤ እንደ እምቢኝ አልገዛም ባይነቷ ሁሉ በራስ እግር መቆምንም በተግባር ለቀረው አፍሪካ አሳይታ ታላቢ ላሞቻችንን ከጉያችን ትነጥቅብናለች የሚል ስጋት ገብቷቸው ከጉዞዋ ሊያሰናክሏት ጠዋት ማታ የሚዶሉቱባትና በተደራጀ መንገድ ባለ በሌለ ኃይላችው የሚዘምቱባት በዝተዋል። እነዚህ አካላት በብዙዎች ዘንድ የአፍሪካ የነጻነት ጸሐይ የወጣባት ምድር ተደርጋ የምትቆጠረው ይህች የአፍሪካ ቀንድ ቀንደኛ ታላቅ ሀገር ችግር ውስጥ ገብታለች ብለው ባሰቡ ቁጥር ከታሪካዊ ጠላቶቿ ጋር በማበር ሊበታትኗት ይመኛሉ፤ ምኞት አይከለከልም።

አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት እና ድርጅቶች በተቀናጀ መንገድ ተደጋጋሚ ጫናዎች ሲያደርሱባት ቆይተዋል። አሜሪካዊው የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት የተወሰኑ ምዕራባውያን አፍሪካን በቁጥጥራቸው ስር አድርገው እንደፈለጉ የማዘዝ ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው። በአህጉሪቱ ጠንካራ መንግስትና ሀገር እንዳይኖር እየሰሩ ስለመሆኑ ጠቁመው በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት በማባባስ ደካማ ሀገር የመፍጠር እቅድ ይዘው እየሰሩ መሆኑን ተናግረው ነበር።

መንግስት የሀገር ሉዓላዊነትን ለማጽናት በትግራይ ክልል ቁልፍ ከተሞችን እየተቆጣጠረ በመጣ ወቅትም አንዳንድ ምዕራባውያን በመንግስት ኃላፊዎቻቸው፣ በተቋማትና በሚዲያዎቻቸው የተናበበ ጫና ሲፈጥሩ ቆይተዋል። በእነዚሁ አካላት በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው ጫና ለእነሱ የሚላላክ መንግስት ለመፍጠር ካላቸው የረጅም ጊዜ እቅድ የሚቀዳ ስለመሆኑም ተንታኙ ይገልጻሉ፤ ምኞት አይከለከልም።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የኤክስፐርቶች ቡድን ከሁለት ዓመታት በፊት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በሁሉም ወገኖች የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን የሚያሳይ ማስረጃ ማግኘቱን ጠቅሶ ሪፖርቱ በማውጣት ኢትዮጵያ ላይ ፖለቲካዊ ተልዕኮ ያነገበ ጫና ለመፍጠር ተንቀሳቅሷል። በሪፖርቱ “የኢትዮጵያ ሰራዊት በትግራይ ክልል በነበረባቸው ጊዜያቶች ሰላማዊ ዜጎች ላይ ግድያዎች መፈጸሙን መረጃ አግኝቻለው” ያለው ተቋሙ፤ በተጨማሪም “ረሃብን አና መድሃኒቶችን መከልከል እንደ ጦር መሳሪያነት ጥቅም ላይ እየዋለ ስለመሆኑ የሚያሳዩ መረጃዎችም አሉ” በማለት የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ በመፈለግ ግፊት አድርጎ ነበር። መቼስ ምኞት አይከለከል። ነገር ግን ዕድሜ ለእንቁ ዲፕሎማቶቿ እና ወዳጅ ሀገራት የጸጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ አንዳች አቋም ለመያዝ ተቸግሮ ያለስምምነት ተበትኗል።

እጇን ጠምዝዘን ለፍላጎታችን እናንበረክካታለን በሚል ከማዕቀብ መጣል እስከ ብድር ክልከላ እና የእዳ መክፈያ ጊዜን ላለማራዘም ዳተኛ እስከመሆን የደረሱ ደባዎች ኢትዮጵያ ላይ ተፈጽመዋል። የጸጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያን ሁኔታ አጀንዳ አድርጎ እንዲነጋገርበት ተደጋጋሚ ጥረቶች ተደርገዋል። ማስፈራሪያና ዛቻዎች ሲዥጎደደጎዱ ቆይተዋል። ከፍተኛ በጀት ተመድቦ ትልቅ ስም ባላቸው ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የኢትዮጵያን ስም የሚያጠለሹ ዘገባዎች በዘመቻ መልክ እንዲስተጋቡ ተደርጓል። የአውሮፓ ህብረት የአንድን ሀገር ሉዋላዊነት የሚጋፉ አቋሞችን አራምዷል፤ ተራ ስም የማጥፋት ተግባር እንኳን አልቀረም። በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት ጽሕፈት ቤት ከሳምንታት በፊት በፌስቡክ ገጹ ላይ የኢትዮጵያና ኤርትራ መንግሥታት በትግራይ የዘር ማጥፋት ጦርነት እያፋፋሙ ቀጥለዋል የሚል ይዘት ያለውን የአንድ ግለሰብ የፌስቡክ መልዕክት አጋርቶ ምኞቱን ተንፍሷል። በኋላም ከአንድ አህጉር አቀፍ ድርጅት ንዑስ ጽህፈት ቤት የማይጠበቅ ተራ ፕሮፖጋንዳ መስተጋባቱን ተከትሎ በተነሳ የተቃውሞ ማእበል ከግማሽ ሰዓት ላነሰ ጊዜ የቆየውን ልጥፍ በማንሳት ይቅርታ ለመጠየቅ ተገዷል። በፌስቡክ ገጹ የተጋራው የአንድ ግለሰብ የፌስቡክ መልዕክት የኅብረቱ እውቅና የሌለው መሆኑን ገልጦ አስተባብሏል። አይኑን በጨውአጥቦም “የግለሰቡ መልዕክት የተጋራው የፌስቡክ ገጼ ተጠልፎ ስለነበር ነው”ብሏል።

ይህ ሁሉ ጉራማይሌ ማዋከብ ኢትዮጵያን ከተያያዘችው የብልጽግና ጉዞ ጠልፎ ለማስቀረት ካለ ፍላጎት የሚቀዳ ምኞት የወለደው መተራመስ ነው። ኢትዮጵያ ግን ወጀቡን እየቀዘፈች ጉዞዋን ቀጥላለች። ምድሯ ላይ ላለው ስጋ የሚፋለሙት የሰማይ አሞራዎችና ታሪካዊ ጠላቶቿ ደግሞ የማይነጋ ህልም ማለማቸውን ቀጥለዋል።

አንገት ከሚሰበር …

ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በአንድ ሙዚቃው ሆድ ከክብር እና ነጻነት በላይ አለመሆኑን ሲገልጽ “አንገት ከሚሰበር ባይበላስ ቢቀር” ሲል ተቀኝቷል። ኢትዮጵያም ፍርፋሪ ለማግኘት ስትል ክብሯን እንደማትጥልና በነጻነቷ እንደማትደራደር ኢትዮጵያዊ ወኔን በተሞሉ ቃላት በመግለጽ “ባይበላስ ቢቀር” ያለችባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት በማስመልከት ያወጣውን ሪፖርት ቆፍጠን ያለ አቋም በመያዝ ውድቅ አድርጋዋለች። መጀመሪያም ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ቢሮ ምርመራ ግኝት እያለ ሌላ አጣሪ ኮሚሽን መቋቋሙ ፖለቲካዊ ዓላማ ያነገበ ነው ስትል ተቃውሟ ነበር። በጄኔቭ የተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ አምባሳደር ዘንበ ከበደ፤ የተመድ የሰብአዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን ያወጣውን ሪፖርት ፖለቲካዊ አላማን የያዘ ነው ሲሉ አጣጥለውታል። የሰብአዊ መብት አጣሪ ኮሚሽኑ ያወጣው ሪፖርት ድምዳሜዎች እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ እና ወገንተኛነት ያለበት መሆኑን ለኤ.ኤፍ.ፒ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ሰብአዊ እርዳታን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀሙን የሚያሳይ አንድም ማስረጃ በሪፖሩቱ አልቀረብም። ሪፖርቱ ፌዝ እና የማይረባ ስለሆነ ውድቅ ከማድረግ ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለን እወቁት ብለዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬደዋን ሁሴን በበኩላቸው በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ ኢትዮጵያን ዝቅ የማድረግ ፖለቲካዊ ስራ ውጤት ነው ሲሉ የነቀፉትን ሪፖርት የመወንጀል አላማ ያለው፤ እርስ በእርሱ የሚጣረስ እና ተዓማኒነት የሌለው ነው ሲሉ ገልጸውታል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጥቅምት 18 ቀን 2015 ዓ.ም “ኃላፊነት የጎደላቸው አካላት ለአደገኛ የፖለቲካ አጀንዳ ሲባል እየፈጠሯቸው የሚገኙ መሠረተ ቢስ ውንጀላዎችን ኢትዮጵያ ታወግዛለች” በማለት ባወጣው መግለጫ እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ ሲል ጠንካራ መልዕክት አስተላልፏል። መግለጫው በምዕራባውያንና የተለያዩ አካላት አማካኝነት በኢትዮጵያ ላይ የሚነዙ የሐሰት ስም ማጥፋቶችን የኢትዮጵያ መንግሥት ፈጽሞ አይታገሥም። እነዚህ አካላት ኢትዮጵያ ውስጥ የከፉ ወንጀሎች ሊፈጸሙ ይችላሉ በሚል የታሪካዊ ጠላቶቻችን ጊዜ ያለፈበት ፕሮፓጋንዳ እንደ በቀቀን መድገማቸው አሳፋሪ ነው። እነዚህ አካላት የሚከሱት ፍንጮችን ወይም ተጨባጭ ክስተቶችን መሠረት አድርገው አይደለም፤ የመፈጸም ዕድል አለ በሚል ያልተጨበጠ ግምት እንጂ። እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ የተሻለ ስም ያላቸው ተቋማት ሳይቀሩ ይሄንን በኢትዮጵያ ላይ ተቀነባብሮ የሚለቀቅ ፕሮፓጋንዳ ለመቃወም አለመቻላቸው ነው። ጥቂቶቹም ስለ ኢትዮጵያ የተነገረውን ስም ማጥፋት በማመን ሳይሞኙ እንዳልቀሩ ይገመታል። አንዳንዶችም እነዚህን የሐሰት ክሶች ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ሊጠቀሙባቸው ይፈልጋሉ ሲል ወቅሷል።

አንዳንድ ምዕራባውያን ባለሥልጣናት ጭምር ይሄንን የሐሰት ክስ የሚነዙት ኢትዮጵያ ትእዛዛቸውን አልቀበል ስላለቻቸው መሆኑን በይፋ መናገር ጀምረው ነበር። ይህ ጊዜ አመጣሽ የሐሰት ክስ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ጨርሶ አይቀይረውም። እነዚህ ጉምቱ ተቋማትና ወሳኝ ተዋንያን፣ በቂ ግንዛቤ ሳይኖራቸው በዚህ የሃሰት ዘመቻ ተሳትፈዋል። ይሄን የመሰሉ የከፉና ሊወገዙ የሚገባቸው ውንጀላዎች ለፖለቲካ ዓላማ መዋላቸው ኃላፊነት የጎደለውና አሳፋሪ ነው በማለትም ኢትዮጵያ ለምንም አይነት ጫና እንደማትንበረከክ መንግስት ግልፅ አድርጓል።

ብዙዎችን ያስገረመውና የኢትዮጵያን አትንኩኝ ባይነት እና ለነጻነቷ ምንም አይነት ዋጋ ለመክፈል ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው የተባለለት ሌባ ጣትን በማወዛወዝ የተነገረ ያህል በኃይለቃል የተመላው ደግሞ የመግለጫው መቋጫ ክፍል ነው። እንዲህ ይነበባል “ይሄንን ለመሰለው አደገኛ ስም ማጥፋት ምላሽ ሳይሰጡ ታግሦ ማለፍ የሚቻል ባለመሆኑ በከፋ መልኩ በኢትዮጵያ ላይ ያልተረጋገጡና ፖለቲካዊ ዓላማ ያላቸውን ውንጀላዎች ከሚያቀርቡ ከአንዳንድ ሀገሮችና ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት የኢትዮጵያ መንግሥት መልሶ እንዲያጤን ተገድዷል። የኢትዮጵያ መንግሥት ከመነሻውም በግልፅ እንዳሳወቀው በአፍሪካ ኅብረት በኩል እየተደረገ ላለው የሰላም ንግግር ቁርጠኛ ነው። ምክንያቱም ግጭቱን በሰላማዊና ቋሚ በሆነ መንገድ ለመፍታት የጸና አቋም አለውና። በሌላም በኩል በግጭቱ ምክንያት የተከሠቱ የሰብአዊ መብትና የሰብአዊነት ጥሰቶችን ተጠያቂ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ለመግለጥ ይወዳል።”

እንዲህ ያለ የምዕራባውያኑን ደም የሚያንተከትክ ቆምጨጭ ያለ መግለጫ በአፍሪካ ምድር ሊደመጥ የሚችለው ከአፍሪካ ቀንዷ ቀንደኛ ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ነው። ጉልበተኞቹን እንደ ቻይና እና ሩሲያ አሊያም እንደ ኢራን እና ሰሜን ኮሪያ ለመቋቋም የምትደፍር አንድ ለእናቷ አፍሪካዊት ሀገር የአድዋ ድል ወላጅ እናት ብቻ ናት።

ኢትዮጵያዊነት መልኩ ብዙ፣ ሰይፉ ህልቆ መሳፍርት ነው። በመላው ዓለም የሚገኙ 17 የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ጥምረት አባላት በውይይቱ ውጤት ላይ ያልተገባ ጫና ለመፍጠር የሚሞክሩአካላትን ተግባር በገዛ ምድራቸው ላይ ቆመው በመቃወም የሀገራቸውን ድፍረት ደግመውታል። የጥምረቱ አባላት ባወጡት መግለጫ ህጋዊ የሆነው የኢትዮጵያ መንግስት በደቡብ አፍሪካ የተካሄደውን ውይይት ጨምሮ እያከናወናቸው ባሉ ተግባራት ላይ አንዳንድ ሀገራት የሚፈጥሩትን ያልተገባ ጫና እንቃወማለን። በኢትዮጵያም ሆነ በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍን የውይይት ፋይዳ ከፍተኛ ስለሆነ ጸብአጫሪ እጃችሁን ሰብስቡልን ሲሉ ጠይቀዋል። የውይይቱን ውጤት ለመቀየር የሚደረጉ ማናቸውንም አይነት ጫናዎች እንደሚቃወሙ ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ከግጭት ለመውጣት የሚያደርጉትን ጥረት በምንችለው ሁሉ ለመደገፍ ሁልጊዜም ዝግጁ ነን ብለዋል።

ኢትዮጵያ “ባይበላስ ቢቀር” ብላ ጦም ማደርን ብቻ አልመረጠችም። ኢትዮጵያ እስከዛሬ ከውጪ የስንዴ ምርትን ለማስገባት እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ድረስ ስታወጣ የቆየች ሲሆን በዚህ ዓመት ግን በቂ ምርት በማምረትዋ የውጭ ምንዛሬውን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ችላለች። የስንዴ ፍላጎቷን በአገር ውስጥ ምርት ከመሸፈን አልፋ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ሰፊ የመኸር እና የመስኖ ልማት እያካሄደች ትገኛለች። በመኸር እርሻው 13 ነጥብ 37 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም 400 ሚሊዮን ኩንታል የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን ምርጥ ዘሮች ለማግኘት እየተሰራ ነው። በአሁኑ ጊዜ የምርት ስብሰባ ሂደቱ በተለያዩ አካባቢዎች ተጀምሯል። 1ሺህ 500 ኮምባይነሮች ምርት ለመሰብሰብ ተሰማርተዋል። በመኸር እርሻ ወቅት በዘር ከተሸፈነው 13 ነጥብ 37 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታሩ የስንዴ ምርት ነው። ከዚህም 108 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል።

በበጋ የመስኖ ልማት ስራ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ እንደሚለማ የግብርና ሚኒስቴር ገልጿል። በበጋው ወራት በዘር ከሚሸፈነው 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 52 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል። ይህ የበጋ የስንዴ ልማት ስራም በዘጠኝ ክልሎች የሚከናወን ነው። መንግስት ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በማስቀረትና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱ ለውጤቱ መገኘት ጉልህ ድርሻ አበርክቷል። ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት እያስመዘገበች ያለችው ውጤት አፍሪካ በምግብ እህል እራሷን ከመቻል አልፋ ለሌሎች መትረፍ እንደምትችል የሚያሳይ ነው። ኢትዮጵያ በስንዴ ላይ ያገኘችውን ውጤት በሌሎች የምግብ ሰብሎች፣ ፍራፍሬዎች እና የእንስሳት ተዋጽኦዎች ላይም መድገም ከቻለች አንገት ሳይሰበር ሆድም ጦም ሳያድር ወደ ነበረችበት ማማ ለመመለስ የጀመረችው ጉዞ ይበልጥ ይፋጠናል።

ማታ ነው ድሌ

አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር በተጠራው 77ኛው የተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ኢትዮጵያ ላይ ለቀረበው የሀሰት ውንጀላ በሰጡት ግሩም መልስ የሀገራቸውን ፈርጣማ አቋም በተዋቡ ቃላት ገልጸዋል። አምባሳደሩ ሴረኞችን ገስጸው ወዳጅ ሀገራትን ባመሰገኑበት ንግግራቸው ኢትዮጵያ እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም ከገጠሟት ችግሮች በላይ እንደምትሆን በማስረገጥ የድሉን ችቦ ቀድመው ለኩሰዋል። አምባሳደር ታዬ በዕለቱ ያደረጉት አጭር ንግግር ተከታዩ ነው።

“እየሰማን ያለነው የሰላም መልእክት ሳይሆን ተከታታይ ማስጠንቀቂያዎችን ነው። ነገር ግን በርካታ የፖለቲካ ምስቅልቅሎችን ማለፍ እንደቻለች ኩሩ አፍሪካዊት ሀገር አባል ሀገራትን አንድ ነገር ማስታወስ እፈልጋለሁ። በርካታ ችግሮቻችንን ተጋፍጠን እንዳለፍናቸው ሁሉ፣ ዛሬም የገጠሙንን ችግሮች በእርግጠኝነት እንሻገራቸዋለን። በአንዳንድ ኃያላን ሀገሮች ዐይን ፊት ልክ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት እንደሆነው ዐቅመ ቢስ መስለን እንታይ ይሆናል። ክቡር ሊቀመንበር፤ አንድ ነገር ግን ላረጋግጥልዎት እወዳለሁ። የውስጣችን መንፈስ ጽኑ ነው። የውስጣዊ መንፈሳችን ጥንካሬ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ለመቆም ብቻ ሳይሆን ሰላማዊ ለመሆን እና ተግዳሮቶቻችንን ለመፍታትም ጭምር ነው። የ120 ሚሊዮን ሕዝባችንን ዕድል ለ200 ኤክስፐርቶች ልንተወው አንችልም። ይህንን ብዬ፤ ሁልጊዜም ቢሆን በጎ ሀሳብ ያላቸውን ተሳታፊዎች በደስታ የምንቀበል ሲሆን ሊያወግዙን እና ለሞት አሳልፈው ሊሰጡን ቀድመው የወሰኑትን ግን “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር ይበላቸው” እላለሁ። ስለዚህ እንደ መንግሥት ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው ሁሉም የሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ የተሳተፉትን ተጠያቂ እናደርጋቸዋለን። ይህንንም የምናደርገው የተወሰኑ ድርጅቶችን ወይም ኤክስፐርቶችን ለማስደሰት ሳይሆን ለራሳችን መርህ ስንል ነው። ዘላቂ ሰላም መስፈን የሚችለው በሁሉም አካባቢዎች ለተሠሩ ወንጀሎች ተጠያቂነት እና ፍትህ ሲሰፍን ብቻ መሆኑን እንረዳለን። ነገር ግን ይህ በሀገሪቱ ባለቤትነት መመራት አለበት።”

የማታ ማታ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ አስረግጠው የተናገሩት ነገር እውን ሆነ። የአድዋዋ ንግስት ተጋድሎዋን በለመደችው ድል ደምድማ የተጋዳሊዎቿን ቅስም ሰባብራ እብሪታቸውን ቀብራለች። ረቡዕ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ፣ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በሕወሓት መሪዎች መካከል ሲካሄድ የነበረው ድርድር ተጠናቅቆ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ተበሰረ። ለአስር ቀናት ያህል ሲካሄድ በቆየው ድርድር ማብቂያ ላይ የተፈረመው ባለ 12 ነጥብ ስምምነት በዘላቂነት ግጭት ማቆም፣ የሕወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት እና የሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ የሚሉ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ተካተዋል። ሕወሓት እና መንግሥት ስምምነቱን ለማብሰር በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በጋራ ሆነው “ግጭቱ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራዎችን አስከትሏል። በዘላቂነት ግጭት ለማቆም መስማማታችንን የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ዓለም ይወቅልን። የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም ከግምት በማስገባት ግጭቱን ምዕራፍ ከኋላችን ትተን በሰላም እና በመቻቻል ለመኖር ተስማምተናል” ሲሉ ተደምጠዋል። ኢትዮጵያታሪካዊ ጠላቶቿ አንገታቸውን የደፉበት ይህ የሰላም ስምምነት አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ አሳይቷል። ስምምነቱ የኢትዮጵያን ሰላም የማይሹ ቡድኖችን ሴራ አክሽፎ ለዘላቂ ሰላም ዕድል ሰጥቷል።

ኢትዮጵያን በመወከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተሰየመው ልዑክ አባል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ስምምነቱን ከፈረሙ ከሰዓታት በኋላ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዕለቱን የገለጹት “የዛሬው ቀን ኢትዮጵያና ሰላም ድል ያደረጉበት ነው” በማለት ነበር። “ለሁሉም ኢትዮጵያውያንና ወዳጆች እንኳን ደስ አላችሁ፤ እኔ ልገልጸው የማልችለው ደስታ ተሰምቶኛል” ሲሉም የሰላም ስምምነቱ በመፈረሙ የተሰማቸውን ልባዊ ደስታ ብዙዎች ላይ አጋብተዋል። አምባሳደሩ እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ወዳጆን ጭምር ነውና ለቃሉ የሚመጥኑት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ ሀገራትና ተቋማት አጸፋውን ለመመለስ ጊዜ አልወሰደባቸውም።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማህማት በአፍሪካ ሕብረት አማካኝነት ሲካሄድ በነበረው የሰላም ውይይት የግጭት ማቆም ስምምነት ለተፈራረሙት ወገኖች አድናቆታቸውን ገልጸው፣ የአፍሪካ ህብረት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። በአዲስ አበባ የሩሲያ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ በፌደራል መንግስትና ሕወሓት መካከል የተፈረመው ስምምነት መላው ኢትዮጵያውያን ሰላምን አረጋጥጠው ብልጽግናን እንዲያገኙና የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም ጠንካራ መሰረት የሚጥል እንደሆነ አመልክቷል። በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ቻይና በፌደራል መንግስትና ሕወሓት መካከል ለተፈረመው የሰላም ስምምነት ያላትን አድናቆት ገልጸው፣ ሀገራቸው በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር የተደረሰውን ስምምነት በበጎ እንደምትቀበለው ጽፈዋል። ሌሎች ወዳጅ ሀገራትና ተቋማትም ደስታቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ዛሬም እንደ ቀድሞ ሁሉ የገጠማትን ችግር ትሻገራለች በማለት የማታ ማታ ኢትዮጵያ አሸናፊ መሆኗ እንደማይቀር ቀድመው የተናገሩት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴም “ሰላም የኢትዮጵውያን የአይበገሬነት ውጤት መሆኑ በድጋሚ ታይቷል” በማለት በኩራት ተናግረዋል።

ፍቅር እንደገና

የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ትናንት ኢትዮጵያን ከግራ ከቀኝ ወጥረው ይዘዋት ከፍተኛ ጫና በማድረግ ሲያስጨንቋት የነበሩ አካላት በሚያስገርም ፍጥነት 360 ዲግሪ ተከርብተው ቀና አሳቢና ተቆርቋሪ ሆነው ተከስተዋል። “አጥበቀን ስንሻው የነበረው” የኢትዮጵያ ሰላምና የግዛት አንድነት በመረጋገጡ ደስ ብሎናል እንኳን ደስ አላችሁ፤ ከጎናችሁ ነን የሚሉ የደስታ መግለጫዎችን አዥጎድጉደዋል።

የአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርለስ ሚሸል ቻርለስ ሚሸል በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ የኢፌዲሪ መንግሥት እና ሕወሓት በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት ባካሄዱት የሰላም ንግግር ስምምነት ላይ በመድረሳቸው መደሰታቸውን ገልጸው፤ የአውሮፓ ሕብረት በቀጣይ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል። የአውሮፓ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ አኔት ዌበር በበኩላቸው በተደረሰው ስምምነት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ ስምምነቱ አበረታች እርምጃ ነው ብለዋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንም ዘግየት ብለው በሰጡት ምላሽ በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ሲካሔድ የቆየው የኢፌዴሪ መንግስትና ሕወሓት የሰላም ውይይት በስኬት በመጠናቀቁ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። የጦር መሳሪያ ድምፆችን በማስቆም የሰብዓዊ እርዳታና መልሶ መቋቋም ስራውን ለማከናወን በሚደረገው ቀጣይ ስራም ከአፍሪካ ህብረት ጎን በመሆን አሜሪካ ድጋፏን እንደምታጠናክር አረጋግጠዋል።

አይኤምኤፍ (IMF) በኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት መደረጉን ተከትሎ ቀጣይ ፈንድ ለመልቀቅ እያሰበ መሆኑን አስታውቋል። ብሉምበርግ እንደዘገበው የድርጅቱ የፈንድ ጉዳይን የሚከታተሉ ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ውይይት እያደረጉ መቆየታቸውን አስታውሷል። ተቋሙ “ቀጣይ እርምጃዎችን እያሰብን ሲሆን ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር እንወያያለን” ብሏል።

መውጫ

ኢትዮጵያ የተፈተነችባቸውና ውስጡም ውጪውም እሳት ያደራባቸው ያለፉት ሁለት አመታት መንግስቷ፣ ዜጎቿ እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያያን ባደረጉት ተጋድሎ ላይ የወዳጅ ሀገራት አስተጽኦ ታክሎበት በድል ተደምድሟል። ድሉ ኢትዮጵያ በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ላይ የተቀዳጅውና ለአፍሪካውያን ዳግም ምሳሌ የሆነችበት ታሪካዊ ድል በመሆኑ የዘመናችን አድዋ ነው። ኢትዮጵያውያን በጋራ ከቆምን የትኛውንም አይነት ተግዳሮት መገዳደር የሚያስችል አቅም እንዳለን የታየበት ነው። ልዩነቶቻችንን በንግግር እየፈታን አንድነታችንን ካፀናን ታሪካዊ ጠላቶቻችን እንኳን ወዳጅ ከመሆን ውጪ ምርጫ አይኖራቸውም። ይህንን አንድነታችንን ሰላምን ለዘለቄታው በማስፈን የጀመርነውን የብልጽግና መንገድ አጠናክረን በመቀጠል ወደነበርንበት የከፍታ ማማ ለመመለስ ልንጠቀምበት ይገባል። ጽሑፌን በአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የሰላም ስምምነቱ በተበሰረበት ቀን ካደረጉት ንግግር በተወሰደ ዓረፍተ ነገር ልቋጭ፤ “ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፣ ትልቅ እንደሆነች መቀጠል ይኖርባታል”።

ተስፋ ፈሩ

Recommended For You