በሀገር ደረጃ ሙስና ወይም ሌብነት ዝርፊያ ያስከተለውን ኪሳራ ከፍ ተደርጎ ሲነገር ችግሩ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ያመጣውን ተፅዕኖና ውጤት ቶሎብለን ላናስበው እንችላለን።በተለያየ የሕዝብም ሆነ የግል መገልገያ ሀብትና ንብረት ላይ ሌብነት እያደረሰ ያለው ኪሳራ ከእያንዳንዳችን ኪስ ውስጥ የተዘረፈ ስለመሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል።አገልግሎት ለማግኘት በምንሄድባቸው ተቋማት ተገቢው ምላሽ አለማግኘት፣አላግባብ ተጨማሪ ክፍያ እንድንከፍል መገደድ በዚህ መሐል ያጠፋነው ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት ከኑሯችን ላይ እየቀማ ያለው ብዙ ነገር አለ፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች በአገልግሎት አሰጣጥ ከመሬት ጋር የተያያዙ አሠራሮች፣ በፋይናንስ ዘርፍ፣ በሽያጭና ግዥ ዘርፍ፣ በፍትሕ አገልግሎት የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት መስጫውን ሁሉ ሕዝብ እየተንገላታ እየተማረረ እየተመለከትን ነው።ባለጉዳይ የሚያስፈልገውን ሁሉ አሟልቶ ቢቀርብም ጉዳዩን ለመፈፀም ገንዘብ ይጠየቃል።እርግጥ ነው በተለያዩ ጊዜያት ሙስናን ለመከላከል ያስችላሉ የተባሉ እርምጃዎች ተወስደዋል።በሙስና በመሳተፍ የተጠረጠሩትም ተጠያቂ ከማድረግ ጎን ለጎን በአንዳንድ ዘርፎች ላይም አሠራርን በቴክኖሎጂ በመደገፍና ከእጅ ንክኪ ነፃ በማድረግ ሙስናን ለመከላከል የሚያስችል ሥርዓት ለመዘርጋት ጥረት ተደርጓል ወይም መልካም ጅምሮች አሉ።ነገር ግን ሙስና አሁንም ስር እየሰደደ ነው የመጣው።
ይህንን በአግባቡ የተረዱት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ይፋ አድርገዋል።መንግሥት ሙስናን ለመቆጣጠር እና ሙሰኞችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ በዚህ ደረጃ ቁርጠኝነቱን ማሳየቱ ትልቅ እርምጃ ነው፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባወጡት መግለጫ ሙስና ሀገርን የሚበላ ነቀዝ፣ የሀገርን አንጡራ ሃብት እየቦረቦረ ጥሪቷን ባዶ ለማስቀረት ሌት ተቀን የሚማስን ተባይ ነው በማለት ገልፀውታል።ሙስና የሀገር ደህንነት ስጋት ሆኗልም ሲሉ የችግሩን ስፋት ልክ አስቀምጠዋል።
ከሕግ እና ከአሠራር ማሻሻያዎች በተጨማሪ የሙስና ተዋናዮች ሁሉ ሙስናን እርም እንዲሉ የሚያደርግ እርምጃ ያስፈልጋል።ሙስና ተቀባዩም፣ሙስና ሰጪውም፣ እድል አመቻቹም ያለው ማኅበረሰብ ውስጥ ነው።አሠራሮችን በማወሳሰብ ሰው እንዲማረር በማድረግ ሙስናን አማራጭ እንዲያደርግ የሚገፋፉ አሠራሮችን፣ አመራሮችንና ግለሰቦችን በመጠቆም ለሕግ አሳልፎ በመስጠት መተባበር ያስፈልጋል።መንግሥት ጥርት ባለ አሠራር ተጠርጣሪዎችን በሕግ ተጠያቂ በማድረግ በየጊዜው የተወሰዱ እርምጃዎችንና የተገኙ ውጤቶችን በመግለፅ፤ ለሙስና ጠቋሚዎች ከለላ በመስጠት ይህ ጅምር እንዲሳካ በትጋት መሥራት አለበት።መገናኛ ብዙኃን ሙስናን በማጋለጥ፣ የሲቪል ማኅበራትና ሌሎች ሕዝቡ ሌብነትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ግንዛቤ እንዲኖረው የማስተማር ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡
ከተጠያቂነት ጎንለጎን ሌብነትን የሚፀየፍ ዜጋ ለመፍጠር መጠነ ሰፊ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።በቤተሰብ፣ በትምህርት ቤት፣ በየአካባቢያችን ትውልድ የምንቀርፅበትን መንገድ መለስ ብለን ማየትና ማስተካከል፣ ለእውነትና ለሕግ የሚቆም ዜጋ ለማፍራት የሚያስችል ሥራ መሥራት ከሁላችን ይጠበቃል።