የነባር ተቋማት እሴት፣ የዲማ ጊዮርጊስ ገዳም ተምሳሌትነት

መግቢያ

የዚህች ጽሑፍ ዋና ዓላማ የዘመናችን ዐቢይ ጉዳዮችን በአግባቡ ለማስተናገድ እንዲቻል ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ የነባር ተግባራትን ተሞክሮ ለአንባቢያን ማቅረብ ነው። እንደምሳሌነት የተወሰደው ደግሞ የዲማ ጊዮርጊስ ገዳም አስተዳደር እና በገዳሙ የነበረው የትምህርት ይዘት ነው። የዲማ ጊዮርጊስ አንዱ ስያሜ ደብረ ድማሕ ነው። ስለሆነም ገዳሙ ዲማ ጊዮርጊስ ወይም ደብረ ድማሕ በመባል ይታወቃል። ተመሳሳይ ሁኔታዎች በሌሎች አከባቢዎች እንደነበሩ/ እንዳሉ እገምታለሁ። ነገር ግን በቂ መረጃ ማግኘት የቻልኩት ስለ ዲማ ጊዮርጊስ ብቻ ነው። መረጃዎችንም ያበረከቱልኝ የዲማ ካህናት ተወላጆች ናቸው። በተለይም ሰፋ ያለ የጽሑፍ መረጃ የተገኘው ከቄስ ዋለልኝ ትዕዛዙ መሆኑን መግለጽ እፈልጋለሁ።

የዲማ ጊዮርጊስ ታሪክ

በታሪክ (አፈ ታሪክ እና በጽሑፍ) እንደሚወሳው በአፄ አምደ ጺዮን ዘመነ መንግሥት (1297-1327 ዓም)፣ ስመ መንግሥቱ ገብረ መስቀል፣ የደብረ ድማሕ ቤተ ክርስቲያን አሁን ባለበት ቦታ ተመሠረተ። በአፄ ዳዊት (ቀዳማዊ ዳዊት) ዘመነ መንግሥት (1382-1411 ዓ.ም) ቤተ ክርስቲያኑ በሥርዓተ ገዳም ተቋቋመ። ከአፄ ይስሐቅ ዘመነ መንግሥት (1414-1429) ጀምሮ እስከ ፯ኛው መምህር እስከ አቡነ ተክለ አልፋ ድረስ መነኵሳቱ በአንድነት (ከህዝብ ተነጥለው/ ርቀው) በገዳም ሥርዓት፣ የአካባቢው ሕዝብም እንዲሁ በአንድ ወገን (ከመነኵሳቱ ተለይቶ) ይኖሩ ነበር። አቡነ ተክለ አልፋ የዲማ አካባቢ ሃይማኖታዊ መሪ የነበሩት በአህመድ ኢብን ኢብራሂም (በተለምዶ ግራኝ ተብሎ በሚጠራው) መሪ ዘመን (በ16ኛው ክፍለ ዘመን) ነበር። በዚያን ዘመን በሊቃውንት ብዛት እና ጥራት በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት መንበርነት እንዲሁም በእውነተኛ መነኵሳት መኖሪያነት በዓይነቱ ስመጥር ሆኖ ነበር።

በአህመድ ኢብን ኢብራሂም የጦርነት ዘመን፣ አቡነ ተክለ አልፋ ታቦቱንና መነኵሳቱን ይዘው ተሰደዱ። የጦርነቱ ዘመን አልፎ ከስደት ሲመለሱ፣ መነኵሳቱ በፈቃዳቸው ስደት አማቶናልና (አንገላቶናልና) ከሕዝብ ተነጥሎ የብቻ (መነኮሳቱ ብቻ በአንድነት) ሰብሰብ ብሎ መኖር ይቅር ብለው አቡኑን ለመኗቸው። አቡነ ተክለ አልፋም የመነኮሳቱን ልመና ተቀብለው፣ የመነኮሳቱን ከሕዝብ ተነጥሎ መኖር አስቀርተው፣ከዓለማውያን ጋር በአንድ አካባቢ እንዲኖሩ ፈቀዱ።

አቡነ ተክለ አልፋ የአካባቢውን መሬት፣ ለማኅበር ቤት የተወሰነ ርስት አስቀርተው፣ ለመነኮሳቱና በስደት ጊዜ ጥገኝነት ሰጥተዋቸው ለነበሩ መሳፍንት (እነ ራስ ወይናጎን፣ እነ ራስ እንደበሉን እና ሌሎችንም) በርሥተኝነት መደቡ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ “ማኅበር” የሚባሉት ቡድን መሰል ስብስቦች፣ በተከሥተ ብርሃን ዘመን ከነበሩት ባለርስቶች እና በተክለ አልፋ ዘመን ከተሠሩት አባቶች የተወለዱት ናቸው።

አቡነ ተክለ አልፋ የመነኮሳትን ከሕዝብ ተነጥሎ መኖርን ቢያስቀሩም፣ ማህበረሰቡ ቀደም ሲል ይተዳደርበት የነበረው ደንብ ቀጥሎ ነበር። በአሰፋፈርም ቢሆን፣ ምንም ብዙ መነኮሳት ደልዳላ ቦታ ላይ ከሚገኘው ቤተ ክርስቲያኑ አካባቢ ቢኖሩም፣ ጥቂት መነኮሳት ገድ ገደል ውስጥ ከማኅበረሰቡ ተለይተው ነበር የሚኖሩት።

ለዲማ ጊዮርጊስ ገዳም የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ቦታዎች (ክፈፎች) በአካባቢው የነበሩ መሳፍንት ከግዛቶቻቸውእየቆረሱ ለገዳሙ ገፀ በረከት ያበረክቱ ነበር።ስለሆነም በዲማ ገዳም ስር የሚተዳደሩት ክፈፎች፣ ከገዳሙ አካባቢ ከሚገኙት በቀር፣ ሌሎች ኩታ ገጠሞች አይደሉም። ለምሳሌ ደብረ ማርቆስ አከባቢ፣ ከገዳሙ ከስድሳ ኪሎሜትር ርቀት በላይ የሚገኙ፣ በገዳሙ የሚተዳደሩ ክፈፎች አሉት። በገዳሙ አስተዳደር ስር ያሉ ክፈፎች የሚተዳደሩትም ዲማ ገዳም በሚሰይምላቸው ጭቃ ሹሞች ነበር።

የኢትዮጵያ ነገሥታት ደግሞ ለገዳሙ ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ያበረክቱ ነበር። ቀደም ሲል የነበሩትን እንተዋቸውና በቅርብ ዘመን አፄ ቴዎድሮስ የወርቅ መቋሚያ እና የወርቅና የብር መስቀሎች፤ አፄ ዮሐንስ ደግሞ የወርቅ የራሥ ቁር እና የወርቅ ጫም ለዲማ ገዳም አበርክተዋል (ስጦታው/ በረከቱ ንስሃ መሰል ገፅታ የተላበሰ ነበር)።

የዲማ ማኅበረሰብ ይተዳደርበት የነበረው ሥርዓት

የዲማ አካባቢ ማኅበረሰብ (ማኅበሩ) በአራት ክፍል የተመደበ ነበር። አንደኛ “የሹም ሽር ቤት”፡ ሁለተኛ “የቄስ ቤት”፣ ሦስተኛ “የመሪ ቤት” እና አራተኛ “የጨዋ ቤት” የተባሉት ነበሩ።ራሳቸው ከመሾም እንዲሁም ሹሞችን ከመምረጥ፣ በጠቅላላው በሀገር አስተዳደር የማይሳተፉ፣ በጸሎት፣ በፍታት፣ በተስካር በአትርሱኝ ብቻ የሚኖሩ፣ “የሰዓታት ቤት”፣ “የገዳማት ቤት” የሚባሉ ሁለት ክፍል ማኅበሮችም ነበሩ። የዚህ ስብስብ አበላት ከላይ እንደተጠቀሰው፣ አይመርጡምም፣ አይመረጡምም። የማኅበረሰቡ ቤት ብሎ የመደባቸው ስብስቦች ከላይ ከተጠቀሱት ርስት የተሰጣቸው ባለውለታዎች ተወላጆች እና ነባር ባለ ርስቶች ተወላጆች ብቻ ነበሩ።

በዘመኑ የነበረው የትምህርት ይዘት

በዚያን ዘመን ዲማ የተወለደ ወንድ ልጅ ሁሉ ለትምህርት ሲደርስ (በአራት ዓመቱ) ተማሪ ቤት እንዲገባ ይደረግ ነበር። ትምህርት ዕድላቸው የሆኑት ሕፃናት ከንባብ ቤት ገብተው ዳዊት ደግመው የንባብ ትምርትን ሲያጠናቅቁ፣ የንባብ መምህሩ ወስዶ ለዜማው መምህር ያስረክባቸዋል። በዚህ ጊዜ “ሰላም ለኪ” ብለው የዜማን ትምህርት ከጀመሩበት ቀን ጀምሮ እንደ ቅድምያ እንደ ቅድምያቸው (በቅደም ተከተል) የቤተክርስቲያን አቋቋምና የተዝካር አቀማመጥ ደረጃ ይይዛሉ።

የዜማ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ የዜማው መምህር ለቅኔው መምህር ያስረክባቸዋል። ከዚያም ቅኔ ዜማ እየተማሩ ከቤተ መቅደስ በዲቁና፣ ከቅኔ ማኅሌት ስብሐተ ነግህ ማኅሌትም እየቆሙ፣ ከበሮ በመምታት፣ መቋሚያ ጸናጽል በማቀበል ሲያገለግሉ ያድጋሉ። አካለ መጠን ሲደርሱ ምንኵስናን የመረጡ መንኵሰው በቤተ መቅደስ ያገለግላሉ። ከላይ በተጠቀሰው ሂደት አድገው ከዚያው ተምረው ከሚመነኩሱት በቀር፣ ተወላጅ ያልሆነ ከውጭ የመጣ ቄስም፣ ዲያቆንም ቢሆን፣ ከቤተመቅደስ እንዳይገባ ሥርዓቱ አጥብቆ ይከለክል ነበር። “የቄስ ቤት” የሚባለው የማኅበረ ሰቡ አካል የነኝህ መነኵሳት ስብስብ (ክፍል) ነው።

ሁለተኛው ክፍል፣ ምንኵስናን አንፈቅድም ብለው፣ ሚስት አግብተው ቤት ሠርተው በቅኔ ማኅሌት እያገለገሉ፣ በሀገር ጉዳይ ሲወጡ ሲወርዱ የሚኖሩ መዘምራን “መሪዎች” ይባላሉ። የእነዚህ የደብተሮች አንድነት (ስብስብ) ነው “የመሪ ቤት” የሚባለው።

ሦስተኛው “የሹም ሽር ቤት” የሚባለው በደብተርነት ማዕረግ፣ በቅኔ ማኅሌት እያገለገሉ ቆይተው፣ “በዘጠኝ ባለወግ” ተመርጠው፣ “ገበዝ”፣ “መጋቢ”፣ “እራቅማሰራ”፣ “መሪጌታ” ተብለው የተሾሙ እና የሹመት ጊዜያቸውን ጨርሰው ሹም መሆናቸው ያከተመ መዘምራን አንድነት (ስብስብ) ነው።

አራተኛው “የጨዋ ቤት” የተባለው በአራት ዓመቱ ከተማሪ ቤት ከገባ በኋላ፣ ትምህርት ዕድሉ ሳይሆን ቀርቶ፣ በእርሻና በንግድ የሚተዳደር ሲሆን፣ የጨዋ ልጅ ተብሎ ርስቱን ይዞ ቤተ ክርስቲያንን በጉልበት፣ በገንዘብ፣ እየደገፈ ይኖራል። የገዳሙን ሹሞች የመሾም የመሻር ሥልጣን ያላቸው “ዘጠኙ ባለወጎች” የሚመረጡት ከእነዚህ በአራት ክፍል ከተመደቡት ባለ ርስቶች (ተወላጆች) ነው።

የ«ዘጠኙ ባለወጎች» አመራረጥ

የ”ዘጠኙ ባለወጎች” ስብስብ ማኅበረሰቡ በውክልና የገዳሙን አስተዳዳሪዎች የመሻር/ የመሾም ሥልጣን የተሰጣቸው የማኅበረሰቡ አባላት (ስብስብ) ናቸው። ሹም ሽር በሚደረግበት ጊዜ በቧኝ ተለፍፎ (በስማ በለው)፣ እነዚህ በአራት ክፍል የተመደቡት ባላባቶች ተሰብስበው፣ በአንድነት ይመክራሉ። ከዚያ በኋላ ሹመት ይገባናል የሚሉ መዘምራን ከሹም ሽር ቤትና ከመሪ ቤት እየተነሡ፣ አገልግሎታቸውን እያስረዱ፣ ለአባቶቻችን ማዕረግ አብቁን እያሉ ልመናቸውን ያቀርባሉ።

ከዚያም የአራቱ ክፍል ማኅበር (ስብስብ)፣ ለየራሳቸው ተለይተው ይመክራሉ። “የሹም ሽር” ቤት ብቻውን መክሮ የታመኑ ሦስት፣ “የቄስ ቤትም” እንደዚሁ በበኩሉ ታማኝነት ያላቸው ሁለት፣ “የመሪ ቤትም” እንዲሁ የሹመት ፈቃድ የሌለባቸውን (ለመሾም የማይፈልጉ) ሁለት፣ “የጨዋ ቤትም” ደግሞ ሁለት ሽማግሎችን መርጠው ያቀርባሉ። በጠቅላላው ዘጠኝ ምርጦች ይገኛሉ፣ እነኝህ ግልሰቦች ናቸው “ዘጠኙ ባለወጎች” የሚባሉት። የተለያዩ ክፍሎች መራጮቹን የመወከል ስልጣን ይለያያል። “የሹም ሽር” ቤት ሦስት ተወካዮች ሲመርጥ፣ የተቀሩት ሌሎች ክፍሎች ሁለት፣ ሁለት ወኪሎች ብቻ ነው የሚመርጡ። ይህም ቀደም ሲል ሹሞች የነበሩ ስለ ገዳሙ አስተዳደር የበለጠ ግንዛቤ ይኖራቸዋል ከሚል እይታ የመነጨ ይመስላል። “ዘጠኙ ባለወጎች” እንደተሰየሙ፣ ወዲያው ሥዕል መስቀል ቀርቦ፣ ለወዳጅ ለዘመድ ብለን አናዳላም። ለሀገር የሚጠቅመውን በእውነት እንመርጣለን እያሉ ይምላሉ። የሚመረጡት ሹሞች አንደኛ የገዳሙ መምህር (ከሁሉም ሹሞች በላይ ሆኖ የሚሰየመው)፣ ሌሎች ገበዝ፣ መጋቢ እና እራቅማሰራ ናቸው።

የገዳሙ ሹሞች አመራረጥ

መምህሩ በመላ ማኅበር ፈቃድ በትምህርቱ፣ በትሩፋቱና በግብረ ገብነቱ ተመርጦ ይሾማል። ማኅበሩ ባልተስማሙበት ጊዜ በድምፅ ብልጫ ይሾማሉ እንጅ እንደ ሌሎች ሹማምንት በምረጡኝ ሂደት አይሾሙም። የተሾመው መምህር ጉባኤ ሠርቶ ለማስተማር የሚችል ከሆነ፣ በሱባዔ ተወስኖ፣ በማስተማር ጸንቶ ይኖራል። ጉባኤ ሠርቶ ለማስተማር የማይችል ከሆነ፣ እግሩ ከመቆም፣ አንደበቱ በጸሎት ከመደመም ሳይለይ፣ በመዓልትም በሌሊትም ቤተ እግዚአብሔር በማገልገል ይኖራል። ስለሀገር አስተዳደር ገበዙንና መጋቢውን እራቅማሰራውን ተከትሎ የሚሠራ፣ “ተቋጣሪ” (ወኪል) የወደደውን ከመዘምራኑ መርጦ መምህሩ ይሾማል። በማናቸውም ጉዳይ መምህሩ አይወጣም፣አይወርድም። መምህሩ ነውር ቢገኝበት፣ ከማኅበር አልስማማም ቢል በደንቡ መሠረት በማኅበር ተመክሮ ይሻራል። ከተሻረም በኋላ በማናቸውም ምክንያት ችግርና ውርደት እንዳያገኘው፣ የማኅበር ቤት ከሚባሉት አገሮች (ክፈፎች) አንዱ፣ በማኅበር ተመክሮና ተመርጦ በሕይወት እስካለ ድረስ መተዳደሪያ ይሰጠዋል።

“ገበዙ” የሚመረጠው ከዚያ በፊት፣ ቀደም ሲል በመጋቢነት ወይም እራቅማስራነት ተሹመው ከነበሩ፣ ከሹም ሽር ቤት ነው። መጋቢውና እራቅማሰራው ግን ከቤተ እግዚአብሔር በማገልገል ስለሀገር ጉዳይ በመላክ፣ ሲወጡ ሲወርዱ ከቆዩት፣ “ከመሪ ቤት” ይመረጣሉ። ሹም ሽር የሚደረገው በየሦስት ዓመቱ ነው። ሆኖም ግን ቀደም ሲል ከተመረጡት መካከል ለሀገር ጠቃሚነታቸው ከታመነበት ከሦስት ዓመት በላይ የሹመት ዘመን የሚጨመርለት ሹም ቢኖር ደምቡ አይከለክልም።

የ«ዘጠኙ ባለወጎች» የውክልና ተግባር

መምህሩ የሚመረጠው በዘጠኙ ባለወጎች ሳይሆን በአጠቃላይ በማኅበረሰቡ ነው። ዘጠኙ ባለወጎች ወዲያው እንደተሰየሙ፣ሳይውል ሳያድር ሕዝቡ ተቀምጦ ስለሚጠብቃቸው የሦስቱን የገዳም ሹሞች ምርጫ ያካሂዳሉ። የዘጠኙ ባለወጎች ስብስብ “ገበዝ”፣ “መጋቢ” እና “እራቅማሰራ” ይመርጣል። የአመራረጡ ሥነ ሥርዓትም መስፈርት አለው። መስፈርቶቹ በአራት ምድብ የተከፈሉ ናቸው፡- አንደኛው፣ ተምሯል፣ በጉባኤ ውሏል፣ ምሥጢር አደላድሏል፣ ወልድ ዋህድ የምትል ሃይማኖታችንን ይጠብቅልናል፣ ብንጠይቀው ይመልስልናል (ያስረዳናል)፤ ሁለተኛው፣ አንደበት አለው (አንደበተ ርትኡ ነው)፣ ከአደባባይ ይውላል፣ ነገር ያውቃል፣ ከቡታ (ከሃብታም)ና ከመስለኔ ተከራክሮ ቅፈፋችንን/ የአስተዳደር ግዛታችንን) ይጠብቅልናል፣ ደብራችንን ያስከብርልናል፤ ሦስተኛው፣ ሃብት አለው፣ እንጀራ አለው፣ እንግዳ ቢመጣ ይቀበላል፤ አራተኛው፣ ስለሀገር ጉዳይ በመላላክ፣ ወጥቶ ወርዶ ሀገሩን አገልግሏል የሚሉ ታሳቢዎችን ከግምት ውስጥ የሚያስገቡ ናቸው። በዚህም በስም፣ በቦታ ይክበር ብለው ፈርደው፣ ቢስማሙ በአንድ ድምፅ፣ ባይስማሙ በድምፅ ብልጫ ግብዝናውን ለእገሌ፣ መጋቢነቱን እና እራቅማሰራቱን ለእገሌ ሰጥተናል ብለው ይወስናሉ። ከዚያም በስምምነት የደረሱበትን ውሳኔለተሰበሰበው ሕዝብ ያሳውቃሉ።

ህዝቡም ቅሬታ ሳይሰማው የተመረጡትን ሹሞች በደስታ ይቀበላል። ከዚያም ማኅበረሰቡ የተመረጡትን ለሹመታቸው እውቅና ሰጥቶ፣ እንደየማዕረጋቸው ያከብራቸዋል፣ ይታዘዛቸዋልም። ሹሞች ከተሰየሙ በኋላ፣ በዚያኑ ሰሞን የማኅበረሰቡ አባላት (የአካባቢው ሕዝብ) በሙሉ አንድ በአንድ በመሶብ እንጀራ በገንቦ ጠላ እጅ መንሻ ለሹሞች ያገባል።

የ«መሪጌታው» ሹመት

መሪጌታነቱን የሚሾመው አመልጥኖ መርቶ፣ አመርግዶ ጸፍቶ፣ ቅኒ ቢጎድል ሞልቶ፣ መውጣት የሚቻለው ባለሙያ ካህን ተመርጦ ነው። ተመራጮቹም ሆኑ መራጮቹ “የመሪ ቤት” በሚባለው ማኅበር (ከአራቱ አንዱ ክፍል ብቻ) የሚገኙት መዘምራን ናቸው። እነሱም መሪጌታውን መርጠው፣ ሹመው፣ አልብሰው አስጠምጥመው፣ ወስደው፣ ከመምህሩ ጀምረው በሹመት ለከበሩት ሹሞች ለሚባሉት እጅ ያስነሳሉ። ሹሞቹም ደግሰው ይቀበሏቸዋል።

የመሪጌታው መብትና የሥራ ክፍል

የማኅበሩ አባላት በሰላም ለኪ (ጠቅለል ብሎ ሲታይ በዕውቀት) እኔ እበልጣለሁ፣ እኔ እበልጣለሁ በመባባል ቢካሰሱ፣ ዳኛ ሆኖ የሚሰየመው መሪጌታው ነው። ተዝካር ቢደግስ፣ እንደዬ ማዕረጋቸው፣ በሥርዓት አስቀምጦ የሚጋብዝ መሪጌታው ነው። የአትርሱኝ ወይም የፍታት ገንዘብ ቢገኝም፣ የመሪ ቤቶችን ድርሻ ተካፍሎ በደንብ በሥርዓት የሚያካፍል መሪጌታቸው ነው። በቤተክርስቲያን አገልግሎትም በቅኔ ማኅሌት የሚያገለግሉትን “የሹም ሽር” እና “የመሪ ቤቶችን” በየተራቸው የሚያዛቸው መሪጌታው ነው። ትእዛዝ ሲሰጥም የመሪ ቤቱን አባል አዋቂነት፣ የበዓሉን ታላቅነት እያመዛዘነ ያዛል እንጅ፣ በሙያ አነስተኛ የሆነውን ሰው በአበይት በዓላት ጊዜ ለዚህ ተግባር አያሰማራም።

የ«ሊቀ አበው» ሹመት እና ሥልጣን

“ሊቀ አበው” ከመዘምራኑ በገበዙ ተመርጦ ይሾማል። ሊቀ አበውም በውስጡ የሚታዘዙ የሥራ ረዳቶች፣ ሁለት ጓደኞች፣ ከጨዋ ቤት ይሾማል። በሀገር ላይ የሚመጣውን ችግር ለመፍታት የሚያገለግል ማናቸውንም ትእዛዝ ከገበዙ እየተቀበለ (ሁለቱ ጓደኞች እየረዱት) ትዕዛዝ የሚያስፈጽም ሊቀ አበው ነው።

በአራቱ ዋና የገዳሙ ሹሞች (በመምህሩ፣ በገበዙ፣ በመጋቢ እና በእራቅማሰራው) መካከል ቅራኔ ተከስቶ የአንደኛቸው ወይም የሁሉም ሹሞች ስልጣን በሌሎች ተይዞ እንዲቆይ ቢያስፈልግ፣ የሁሉንም ሹሞች ስልጣን ይዞ የሚቆይ (የሚይዝ) “ሊቀ አበው” ነው።

የሹሞች የዳኝነት/ የአስተዳደር ሥርዓት

በማናቸውም ጉዳይ/ችግር ገበዙ፣ መጋቢው እና እራቅማሰራው ችግሩ የተነሣበትን አከባቢ ጭቃ ሹም እንደ ቋሚ ዳኛ አድርገው ይመለከቱታል። ጭቃ ሹሙ ነው በቅርብ ለማኅበረሰቡ ችግር ፈች የሚሆነው። ጉዳዩ ከጭቃ ሹሙ ሥልጣን በላይ ከሆነ (የጭቃ ሹሙ ስልጣን በደምብ የተወሰነ ነው)፣ ሹሞቹ (ገበዙ፣ መጋቢው እና እራቅማሰራው) ጉዳዩን ራሳቸው ከመረመሩት በኋላ፣ መምህሩ የማያስፈልግ ቀለል ያለ ጉዳይ ከሆነ እዚያው ይቋጩታል። ጉዳዩ ከበድ ያለ ከሆነ ግን መምህሩ ባሉበት ለፍርድ ዓርብና ረቡዕ ይቀጠራል።

አራቱም ሹማምንት በሚገኙበት ጉባዔ ጉዳዩ ተመርምሮ ከተጣራ በኋላ፣ ቢስማሙ በአንድ ድምፅ፣ ባይስማሙ በድምፅ ብልጫ ጉዳዩ ይወሰናል። ከዚያ ግራ ቀኙ ተከራካሪዎች ቀርበው፣ የተሰጠው ፍርድ “በጎጃም ነጋሹ” ይነገራቸዋል። የዳኝነቱንም ገንዘብ መምህሩ፣ ገበዙ፣ መጋቢው እና እራቅማሰራው አራቱ እኩል ይካፈሉታል። የገበያውንም ቀረጥ በጭቃ ሹሙ፣ በሊቀ አበውና በጓደኞቹ አስቀርጦ ለአራቱ ሹማምንቶች ገቢ ያደርጋል።

ስለቤተክርስቲያን አቋቋም በቀኝም በግራም ቢሆን ከመምህሩ ቀጥሎ ገበዙ፣ ከገበዙ ቀጥሎ መጋቢው፣ ከመጋቢው ቀጥሎ እራቅማሰራው ይቆማሉ። በመሪ ቤት ያሉ ደብተሮችም በሹማምንት ካልከበሩ በቀር ከመሪጌቶች ቀጥለው በየሰላም ለኪአቸው (በተመደበላቸው ቦታ) ይቆማሉ። ከመሪ ቤት ማኅበር ያልገቡ፣ በተማሪ ቤት ያሉ ወጣቶችም እንዲሁ በየሰላም ለኪአቸው ይቆማሉ። በተዝካርና በምሳ ጊዜም አቀማመጣቸውም እንደዚሁ እንደ አቋቋማቸው ነው።

የመምህሩ ወኪል (ተቋጣሪ)

የመምህሩ ወኪል (ተቋጣሪ) በመምህሩ ፈቃድ ከመዘምራኑ መካከል ተመርጦ ይሾማል። በተለይ ለመምህሩ መተዳደሪያ የሆኑትን አገሮች፣ ስለመምህሩ ሆኖ ያስተዳድራል። እነዚህ አገሮች ለመምህሩ የሚያስገቡትን ግብር ያስገባል። በሌሎችም ክፈፎች ከገበዙ፣ ከመጋቢው እና ከእራቅማሰራው ጋር ሆኖ ይሠራል። ይሁን እንጂ የሹሞች የበላይነት መብት የለውም።

የ «ጎጃም ነጋሽ» ሹመትና መብት

“ጐጃም ነጋሽ” የሚባለው ጭቃ ሹም ነው። ጭቃ ሹሙ የጨዋ ቤት ከሚባለው ማኅበር ክፍል በጨዋ አንድነት (ስብስብ) ተመርጦ፣ በአራቱ ሹማምንት ፈቃድ ይሾማል። የደብሩንም ሕዝብ እንደ ደንቡ በጭቃነቱ ያስተዳድራል። ከደብሩ የሚገኘውን የገበያ ቀረጥ፣ የዳኝነት ገንዘብ እንደ ዋስ አጋች ሆኖ እየሰበሰበ ለአራቱ ሹማምንት የሚያካፍል እሱ ነው።

ስለ «ቤተ አበዎች»

ዲማ በአቡነ ተክለ አልፋ ጊዜ፣ የአንድነት ገዳምነቱ ቀርቶ ርስቱ ለማኅበር የተወሰነ ተመድቦ ባለርስት ሲመራበት፣ የቀረው መሬት ለዘጠና አበዎች ተከፍሎ ተመድቧል (ዘጠና አበዎች ባለ ርዕስት ሆነውበታል)። እነዚህ ዘጠና አበዎችም በአሥራ ስምንት፣ በአሥራ ስምንት ተከፍለው ለአምስት ዐቢይ ክፍሎች ተመድበዋል። ይህ ምድብ እንዳይፋለስ፣ ድንበር እንዳይጣስ፣ የአበዎች ስም እንዳይደመሰስ፣ የሚጠብቁ የርስት ዳኞች፣ አምስት ቤተ አበዎች ተሾመዋል። እኒህም “ዕቃ ቤት”፣ “ግራ ቤት”፣ “ተርቢኖስ”፣ “ተንሥኤ መድኅን” እና “ቤተ ዮሐኒ” ይባላሉ። ይህን ሹመት እኒህ ሰዎች በጊዜው ተገኝተው ስለተሾሙ በእነርሱ ስም ይጠራል እንጂ፣ በዘር እየወረደ የእነርሱ ዘር ብቻ የሚሾምበት ሥርዓት አይደለም። በአምስት ዐቢይ ክፍሎች ከተከፈሉት፣ በአሥራ ስምንት መደብ ከተመደቡት አበዎች የተወለዱት ሁሉ እንደየክፍላቸው በየቤት፣ በየቤቱ ይሾማሉ።

በደብረ ድማሕ ጊዮርጊስ (በዲማ ጊዮርጊስ ገዳም) የነበረውን የሹሞች አሰያየም እና የተግባር ድርሻ ሲፈተሽ፣ የሹሞች አሰያየም በማህበሩ ምርጫ/ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ፣ ብሎም ጠቅለል ብሎ ሲፈተሸ ዴሞከራሲያዊ እንደነበረ ያመለክታል። የሹሞችም ተግባር መሬት የነካ፣ ችግር ተኮር እና ችግር ፈች እንደነበረ ያሳያል። ምናልባትም ከእንደዚህ ዓይነት የአስተዳደር  ሥርዓት ልንወርሰው የምንችለው አካሄድ ይኖር ይሆን? የሚል ጥያቄ አስነስቶብኛል። ለጥያቄውም አዎንታዊ እይታ አለኝ። ነባር ሥርዓትን ከዘመናዊ ሂደት ጋር ማዛመጃ፣ ማገናኛ ድልድይ ማድረግ ይቻላል በሚል።

ትምህርት በዲማ ጊዮርጊስ/በደብረ ድማሕ/

በደብረ ድማሕ ገዳም፣ በነበረው የትምህርት ሥርዓት፣ እንደ ዘመናችን የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ክፍሎች መታየት የሚችሉ፣ የተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ነበሩ። እነሱም፡- የ“ጸዋተወ ዜማ” (ልዩ ልዩ ዜማዎች እና መዝሙሮች) ትምህርት፣ የ“ግዕዝ ቋንቋና ቅኔ ትምህርት”፤ የ“ሃይማኖት ትምህርት” (የሥነ መለኮት ትምህርት)፣ የ“ብሉያት ትርጓሜ ትምህርት”፤ የ“ሐዲሳን ትርጓሜ ትምህርት”፣ የ”ሊቃውንት መጽሐፍት ትርጓሜ ትምህርት” እና የ“መጻሕፈተ መነኮሳት ትርጓሜ ትምህርት” ነበሩ። በመሆኑም ደብረ ድማሕ ከላይ ለተጠቀሱት የትምህርት ዓይነቶች ማዕከል ሆኖ ለዘመናት ቆይቷል።

ዲማ በልብወለድ መልክ ቢሆንም (በፍቅር እስከመቃብር)፣ በሀዲስ ዓለማየሁ በሰፊው እንዲታወቅ ተደርጓል። የደብረ ድማሕ የትምህርት ማዕከልነት፣ ታዋቂነት ከ19ኛው ምእተ ዓመት ጀምሮ እየመነመነ ቢመጣም፣ እርሾው ግን እስከዛሬ ድረስ አልጠፋም።

ዲማ ስለነበረው ትምህርት (በተለይ ቅኔ)፣ ጠቀም ያለ መረጃ ከመጽሐፈ ትዝታ (ዘ አለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ፣ ደማሙ ብዕረኛ መንግሥቱ ለማ እንደጻፈው) ማግኘት ይቻላል። በአሥራ ዘጠነኛው ምዕተ ዓመት አጋማሽ፣ አለቃ ለማ ኃይሉ ዲማ ጊዮርጊስ የቅኔ ተማሪ ነበሩ። እሳቸውም ስለ ዲማ ሊቃውንት በሰፊው በትዝታቸው አስፍረውታል። የአለቃ ለማ ኃይሉ መምህር አለቃ ተጠምቆ በፈንጣጣ ምክንያት በሕጻንነታቸው ማየት የተሳናቸው ነበሩ። የመምህሩ እናት ትውልድ አገር አባ ገሪማ (አድዋ አጠገብ)፣ አባታቸው ደግሞ የሽሬ ተወላጅ ነበሩ። የቅኔ መምህር ሆነው ነበር ካገራቸው ከትግራይ የወጡ። ዕውቀታቸውን ያለጊዜ ገደብ ለማዳበር ግን መጀመሪያ ስሜን (ጐንደር)፣ ከዚያ ወደ ጐጃም ተሻግሩ። ዋሸራ የቅኔ ጉባዔ ዘርግተው ሳለ፣ ወደ ሞጣ ሄደው፣ አገር ባደነቀው ፍጥነት (በሦስት ዓመት) የብሉይ ሊቅ (ጠበብት) ለመሆን በቅተዋል። ከዚያም ወደ ዲማ ዘልቀው የቅኔ መምህር፣ ብሎም የብሉይ መምህር ሆኑ – ጣምራ ፕሮፌሰርነት።

አለቃ ለማ ኃይሉ እንዳሉት፣ አለቃ ተጠምቆ ዲማ የተቀመጡበት ዋና ምክንያት፣ መጽሐፍ እንደልብ ይገኝ ስለነበር (ግለሰብ ሊገዛው የማይችል ብዙ መጽሐፍ ዲማ ተከማችቶ ስለነበር) ነው ይላሉ። ይህም እገረ መንገዱን፣ በዚያን ጊዜ መጽሐፍት ከፍተኛ ዋጋ እንደነበራቸው ያመለክታል። ይህም በቅርብ ጊዜ ለተመሠረተው ስለ “አብርሆት መጻሕፍት ቤት” አስፈላጊነት አንድ ተጨባጭ ምስክር ሊሆን እንደሚችል ልብ ሊባል ይገባል።

በአገር ውስጥ ሁሉ ቅኔ ሲዘራ ይውላል ይባል በነበረበት በዚያን ወቅት፣ የሰቆጣው ተወላጅ አለቃ ሠረገላ ብርሃን ዲማ ነበሩ። መሪጌታ ውብሸት (ስመ ጥሩው የብቸና ተወላጅ የቅኔ ሊቅ)፣ እንዲሁም የአድዋው ተወላጅ አለቃ ትኩ እና የላስታው ተወላጅ ደቂቁ አለቃ ለማም የዲማ ሊቃውንት ስብስብ አካል ነበሩ። ሁሉንም ሊቃውንት ዲማ ላይ ያሰባሰባቸው ድምበር ዘለል የዕውቀት ፍላጐት እንደነበር ይነገራል። ሊቃውንቱ በዘመኑ በተከሰተው ቸነፈር ምክንያት ወደ ሸዋ ለመሰደድ ተገደዋል። በዚህ ሳምንታትን በፈጀ ጉዞ አለቃ ተጠምቆን እየመሩ ደብረ ሊባኖስ ያደረሷቸው ደቂቁ ለማ ነበሩ።

እነዚህን ዘመን አይሽሬ ሊቃውንት ዲማ ጊዮርጊስ ላይ ያገናኛቸው የዕውቀት መሻት እንደነበር አለቃ ለማ ኃይሉ በመጽሐፈ ትዝታ መጽሐፋቸው፤ “በዘመኑ የነበሩትን ሰዎች የአካልና የመንፈስ ጽናት፣ ለዕውቀትም ሆነ ለወጠኑት ዓላማ የነበራቸውን እልህና ትዕግሥት፣ ችግርን መከራን የሚመክቱበት ጥንካሬና ብልሃት፣ እርስ በእርሳቸው የነበራቸውን ሁሉንም ዓይነት ሕይወት ግንኙነትና መስተጋብር ያመለክታል። ማህበረሰቡ እርስ በእርስ ተያይዞ፣ ተቻችሎና ተደጋግፎ ለዘመናት አብሮ እንዲኖር ያደረጉት፣ ከብሔራዊ መንግሥትና ከብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ በላይ የሆኑ እሴቶች እንደነበሩ ይዘከራል” በማለት ገልጸውታል።

ዲማ ጊዮርጊስ ያፈራቻቸው ሊቃውንት

ደብረ ድማሕ ያስተናግድ በነበረውን ትምህርት ጥራት፣ ልቀት አመልካችና አንፀባራቂ የሆኑ በርካታ ሊቃውንት ተገኝተዋል። ከእነዚህ መካከልም አባ ጲውሊ (የብሉይ እና የሐዲስ መምህር)፣ አባ ዝክረ (የሐዲስ እና መጥሐፈ ሊቃውንት መምህር)፣ እና አባ መዝሙረ ድንግል (የብሉይ መምህር) እንደ ምሳሌነት ሊወሰዱ ይችላሉ።

በቅርብ ዘመንም በጽሑፍ ሥራዎቻቸው በኢትዮጵያ የነበረው ሃይማኖታዊው እና ትውፊታዊው አመራር እንዲቀጥል ትልቅ ስራ የሰሩ በትውልድም ሆነ በትምህርት ዲማ ያፈራቻቸው ምሁራን ነበሩ። ከእነዚህ ምሁራን መካከል አንዱ መልዓከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ናቸው። ሊቁ አድማሱ ጀምበሬ ያበረከቱልን የሃይማኖት መጻህፍት ምክንያታዊ የሆኑ ክርክሮች፣ በተዋህዶ ኦርቶዶክሳውያን እምነት የዕውቀት ምንጮች እንደነበሩ ይታወቃል።

በመልዓከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ የተዘጋጁት መጻሕፍት በጣም ብዙ ናቸው። በተለይም በቃል ይነገሩ/ ይነበነቡ የነበሩ ረቂቅ ቅኔዎችን በሁለት ቅፆች እንዲካተቱ በማድረግ፣ ሊረሱ ይችሉ የነበሩ የአገር ሃብቶቻችንን (ቅኔዎችን) ዘላለማዊ አድርገዋቸዋል። ስለሆነም የቅኔን እይታ እና ይዘት ከፍ ወዳለ ደራጃ አሸጋግረውታል።

እንዲሁም በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ከፍተኛ ስፍራ ያላቸው ሀዲስ አለማየሁ ዲማ ጊዮርጊስ ካፈራቻቸው ሊቃውንት መካከል ይገኙበታል። ዲማን ማዕከል አድርጎ በተጻፈው በዝነኛው ድርሰታቸው፣ በ”ፍቅር እስከ መቃብር” በዘመኑ የነበረው ማህበራዊ ይዘት ምን እንደሚመስል በማሳየት ከፍተኛ የሆነ አይረሴ ትምህርት አበርክተውልናል።

በአንድ ወቅት በምሥራቅ ጎጃም ገድ አፋፍ ላይ የምትገኘዋን ዲማ ጊዮርጊስ ገዳምን ስጐበኝ የተሰማኝን ሃሳብ ከዓመታት በኋላ በአነስተኛ ስንኝ ለመግለጽ እንዲህ ሞክሬያለሁ፣

በዜማ ምሰሶ፣ በትርጉም ተማግራ፣

ገድ አፋፍ ላይ ቆማ፣ ቅኔ እም ታበራ፤

የሊቆች መስፈሪያ፣ እልፍኝ የነበረች፣

«አስኳላ» ገፍትሯት፣ ጋጥ ሆና ከረመች።

መደምደሚያ

ስለ ዲማ ጊዮርጊስ ነባራዊ ይዘት፣ የአስተዳደርም ሆነ የትምህርት ሥርዓት በቂ መረጃ አለኝ። ይህን መረጃ መነሻ አድርጌም በዲማ ጊዮርጊስ የነበረን ባህላዊ አስተዳደርና እና ትምህርት ነክ ይዘት ለመግለጽ ሞክሬያለሁ። የዚህ ጽሑፉ ዋና ዓላማ ደግሞ ቀደም ሲል የነበሩ ይዘቶችንና ሥርዓቶችን በማጥናት፣ በመመርመር፣ ለዘመናችን ሁኔታዎች፣ ችግሮች፣ የመፍትሄ ግብዓቶች ሊሆኑ የሚችሉ ተሞክሮዎችን ለአንባቢያን ማካፈል ነው። በመሆኑም ነባር እውቀትን፣ ተሞክሮን ያገናዘበ እቅድ ላይ ተመርኩዞ፣ የወደፊቱን እንቅስቃሴ፣ እርምጃ መተለም ብሎም መገንባት፣ ለግንባታው ጽናትን ይሰጣል የሚል እምንት ስላለኝ ተሞክሮውን ለማቅረብ ሞክሬያለሁ። በተጨማሪም ስለነበሩ መልካም ሥርዓቶች ማወቁ በራሱ መንፈሳዊ ሃሴት ያጎናጽፋል፣ ባህልንም ያዳብራል የሚል አመለካከት አለኝ።

ዘመን መጽሔት ሐምሌ 2014 ዓ. ም

ሽብሩ ተድላ (ፕሮፌሰር ኤሜሪተስ)

Recommended For You