ሶስተኛው ሙሌት

የዓለማችን ረዥሙ አባይ ወንዝ አስራ አንድ ሀገራትን በማካለል 6‚700 ኪ.ሜ ተጉዞ ሜዲትራኒያን ባህርን ይቀላቀላል። 84 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ከሚደርሰው ዓመታዊ የወንዙ ፍሰት 84 በመቶ ያህሉ የሚገኘው ከኢትዮጵያ ምድር ነው። ኢትዮጵያ ለዘመናት ይህን ታላቅ የተፈጥሮ ስጦታዋን በአርምሞ በመመልከት ተወስና ኖራለች። ይህ ታሪክ ግን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የተቀየረው መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የታላቁን የህዳሴ ግድብ መሰረት ድንጋይ ጥላ የዘመናት ቁጭቷን ለመቋጨት ጉዞዋን አንድ ብላ ስትጀምር ነው።

ከ 11 ዓመታት በፊት እውን የሆነው የታለቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀከት በኢትዮጵያውን ርብርብ ብዙ ውስብስብ ደረጃዎችን አልፏል። አሁን ላይ ደግሞ ሶስተኛውን ሙሌት ለማከናወን ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ያሉበት ወቅት ላይ ደርሷል። አገራችን ደግሞ በሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት ከፍተኛ ጫና ውስጥ ትገኛለች። ከዚህ አንጻር በዚህ ጽሁፍ ሶስተኛውን ሙሌት ለማከናወን ዝግጅቶችን ማጠናቀቋ ያለውን ትርጉም፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አንድምታ እንዲሁም ሙሌቱን ተከትሎ ከግብጽ እና ሱዳን በኩል ሊመጡ የሚችሉ ጫናዎችን እና አገራችን ማከናወን የሚገባትን ቅድመ ዝግጅቶች ዳስሰናል። መልካም ቆይታ።

በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ትንታኔዎችን በመስጠት የሚታወቁት የታሪክ ተመራማሪው እና ፀሐፊው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ሶስተኛውን ሙሌት ከመጀመሪያውና ሁለተኛው ሙሌት ነጥሎ መመልከት እንደማይቻል፣ ሁለቱ ሙሌቶች ሲከናወኑ በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ አንጻር ምን ነበር የተከሰተው እንዲሁም ችግሩን እዴት ሰብረን ማለፍ ቻልን የሚለውን አብሮ መመልከት እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ።

ሁለቱ የታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት በተለይም ግብጾች ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውን ያላቸው መረዳት ችግር እንዳለበት የሚገልጹት ፕሮፌሰር አደም፣ እኛ ይህን ግድበ ለመግንባት ያሰብነው ከአገራችን ርሃብን እና ድህነትን ለመቅረፍ እንጂ በማንም ላይ ተጽዕኖ ለማድረስ አለመሆኑን ያስረዳሉ። ተጽዕኖ ለማድረስ ብንፈልግ ኖሮ ግድቡን ከመስራት ይልቅ ስድስቱን የአባይ ገባሪ ወንዞች አቅጣጫ እንዲቀይሩ በማድረግ ግብጾችንም ሆነ ሱዳኖችን ውሃ ማሳጣት ይቻል ነበር። ከጥንት ጀምሮ ግን እኛ ወደዚህ አይነት ተግባር አልገባንም፤ በእነሱ ላይም ተንኮል አስበን አናውቅም። እነሱ ግን እኛን ከጥንት ጀምሮ የሚያዩን የዋህ አድርገው ነው። ሌላው ቀርቶ አገራችን በ1966 እና 1977 ዓ.ም ለርሃብ ስትጋለጥ እና ተፈጥሯዊ ችግሩን ስትጋፈጥ ግብጾችና ሱዳኖች አንዳችም እርዳታ ለማደረግ ጥረት አላደረጉላትም። ከዚያም አልፎ መጽሔቶቻቸው እና ጋዜጦቻቸው በሙሉ በእኛ ላይ ይሳለቁብን እንደነበር ያወሳሉ።

የግብጽ እናቶች ልጆች ወልደው ጡት ከማጥባት ባልተናነሰ መልኩ ስለ አባይ ማንነት እና ምንነት ነው ልጆቻችንን የምንመግበው ብለው እደሚናገሩ ፕሮፌሰር አደም ይገልጻሉ። የግብጽ ኢታማዦር ሹም የነበሩ አንድ ጀኔራልም ወጣቶቻቸውን 18 ዓመት ሞልቷቸው ግዳጃቸውን እንዲወጡ ወደ ወታደራዊ ካምፕ አስገብተው ቃለ – መሃላ እንዲፈጽሙ የሚያስደርጉት ለሀገሬ ግብጽ እሞታለሁ ብለው ሳይሆን አባይን በተመለከተ ህይወቴን እሰዋለሁ ብለው መሆኑን መናገራቸውን ያስታውሳሉ። ሔርቶራላማል የምትባል የጥናትና ምርምር ማዕከል ባለሙያ የሆነች ግብጻዊት ደግሞ፣ እኛ እና ኢትዮጵያ የአምስት ሺህ ዓመት ጥላቻ ወይም ጸብ ያለን ነን፤ ምን ጊዜም ቢሆን ኢትዮጵያን በበጎ መልክ አንመለከታትም ስትል አቋሟን ገልጻ ነበር። በመሆኑም አንዲት የግብጽ ምሁር እንዲህ አይነት አስተሳሰብ ያላት ከሆነ ተራውን ህዝብ እንዴት ልታሳስት እና ከመንገድ ልታስወጣ እንደምትችል መገመት አይከብድም። ስለሆነም የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ ይህን የመሰለ የተዛባ አመለካከት የያዘ የግብጽም ሆነ የሱዳን ህዝብ በቅንነት ይቀበሉታል ብለን መጠበቅ የለብንም ባይ ናቸው – ፕሮፌሰር አደም።

ግብጾች በአረብኛ ቋንቋ አፍሪካን በተመለከተ 2‚222 መጽሀፍት አሳትመዋል። ከዚህ ውስጥ ግን 220 ያህሉ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ናቸው። በህትመቶቹም ኢትዮጵያ ማን ናት፣ ምንድ ናት በሚል የህዝቧ እና የተፈጥሮዋ ጉዳይ በዝርዝር ተጠንቶ ተዘጋጅቷል። ህትመቶቹም አረብኛ ለሚናገር ህዝብ ሁሉ ተዳርሶ ግንዛቤ እንዲያዝ ተደርጓል የሚሉት ተመራማሪው፣ ከመጀመሪያውም ኢትዮጵያ የግድቡን መሰረት መጣሏን ግብጾች በቅንነት እንዳልተመለከቱት ይግልጻሉ።

እንደ ፕሮፌሰር አደም ገለጻ፣ ከጥንት ጀምሮ የግብጽ መንግሥታት ለኢትዮጵያ ቀና አመለካከት ኖሯቸው አያውቅም። ቀደም ብለው የነበሩ የግብጽ መንግሥታት እ.ኤ.አ በ1885 እና በ1886 ሁለት ጊዜ ኢትዮጵያን በኃይል ለመውረር ዘመቻዎች አድርገው ከሽፎባቸዋል። ከዚያ ቀጥሎ የመጡት የግብጽ መሪ ጀማል አብድል ናስር ነበሩ። እሳቸው ብልህ ስለነበሩ ከአፍሪካውያን ጋር መጣላት አልፈለጉም። በተለይም ወቅቱ አጼ ኃይለሥላሴ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመስረት እየተንቀሳቀሱ የነበረበት ስለነበር በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ከማካሂድ ይለቅ ግድቤን ሰርቼ ውሃዬን ባከማች ይሻላል በሚል የአስዋን ግድብ ገንብተዋል። በመቀጠል አንዋር ሳዳት ወደ ሥልጣን ሲመጡ ዛቻ ነበር ያስተላለፉት። በአንድ ወቅት ወታደራዊ ካምፕን ሲያስመርቁ ለወታደሮቻቸው ያስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ግድብ ለመገንባት ዓላማና ዕቅድ ያላት በመሆኑ ይሄን ጉዳይ በጸጋ የምንቀበለው ነገር ባለመሆኑ ለሀገራችሁና ለህዝባችሁ ለመዋጋትና ለመሞት ተዘጋጁ ነበር ያሉት።

ከሳዳት ዘመን በኋላ ወደ ሥልጣን የመጡት ሁስኒ ሙባረክም የግድቡን ግንባታ ለመጀመር በዋዜማው ላይ ባለንበት ወቅት የደህንነት ተጠሪያቸውን እና ልዩ መልዕክተኛቸውን ወደ ሱዳን ልከዋል። ለሱዳን የላኩት መልዕክትም ኢትዮጵያ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አካባቢ ግድብ ልትገነባ ስለሆነ ኢትዮጵያን ለመምታት በቀጥታ ከግብጽ ከምንነሳ እንዲመቸን የጦር ካምፕ የምንመሰርትበት ቦታ ስጡን የሚል ነበር። አልበሽር ከደቡብ ሱዳን ጋር ችግር ውስጥ ስለነበሩ ሌላ ፋይል መክፈት ባለመፈለጋቸው አሁን ጊዜው አይመችም በሚል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ስለገለጹላቸው የጦርነት ሙከራው ከሽፏል።

አገራችን የታላቁ ህዳሴ ግድብን መሰረተ ድንጋይ ባስቀመጠችበት ወቅት ወደ ሥልጣን የመጡት ሙርሰም አዲስ ነበሩ። በመሆኑም ኢታማዦር ሹሙ፣ የጦር አዛዦቹ፣ የሃይማኖት መሪዎች እና አፈ-ጉባዔ ሳይቀር ካቢኔው በሙሉ የሚገኙበት አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት በጉዳዩ ዙሪያ ምን ማድረግ አለብን የሚል ሃሳብን አጀንዳ አድርገው አቀረቡት። በውይይቱም ኢትዮጵያን በተመለከተ በአምስት ነጥቦች ላይ ተስማምተው መግለጫ ሰጡ። አንደኛው በወቅቱ ከኤርትራ ጋር አገራችን ሰላም ስለልነበረች ኤርትራውያንን አስታጥቀን በኢትዮጵያ ላይ ውጊያ ማስከፈት፣ ሁለተኛው ጂቡቲ የአረብ ሊግ አባል አገር ስለሆነች ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የወደብ አገልግሎት እንድታቆም በሊጉ አማካኝነት ተጽዕኖ መፍጠር፤ ሶስተኛው ሼህ መሃመድ አላሙዲን ትውልዱ ኢትዮጵያዊ ቢሆንም የሳውዲ ዜግነት ስላለው ከሳውዲ መንግሥት ጋር ተነጋግረን ሁሉን ነገር ይዞ ወደ ሳውዲ እንዲመለስ ማስገደድ፤ አራተኛው የኡጋዴ ነጻ አውጪዎችን አስታጥቀን ኢትዮጵያ ላይ በምስራቁ ክፍል ጦርነት እንዲከፍቱ ማድረግ እና አምስተኛው ደግሞ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በሥርዓቱ ላይ ኩርፊያ እንዲኖራቸው ጥረት ማድረግ የሚል ነበር።

አስቸኳይ ስብሰሰባው ከተካሄደ ከሁለት ወር በኋላ ሙርሲ ወደ ወህኒ ቤት ወርደው በምትካቸው አል ሲ ሲ ወደ ሥልጣን መጡ። አል ሲ ሲ እ.አ.አ. በ2015 ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም እና ከሱዳኑ አልበሽር ጋር በመሆን በግድቡ ዙሪያ ሁሉን አቀፍ ሊባል የሚችል ስምምነት ለመፈራረም በቅተዋል። ይሁን እንጂ በወቅቱ የግብጽ ተቃዋሚ ኃይሎች አል ሲ ሲ ያደረጉት ስምምነት ሕገወጥ ነው በሚል ተቃውሞ አንስተውባቸው ነበር። ምክንያቱም የግብጽ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 11 ማንኛውም ስምምነት ከመፈረሙ በፊት የግዴታ የህዝብ ድጋፍ ማግኘትና በፓርላማ መጽደቅ አለበት የሚል ስለነበር ነው።

ከ 80 ሺ በላይ የሚሆኑ የግብጽ ምሁራኖችም በመላው ዓለም ተበትነው ተጽዕኖ ማሳደር የሚችሉባቸውን እንደ የተባበሩት መንግሥታት፣ የዓለም ባንክ እና የመሳሰሉ ቦታዎችን ይዘው ይገኛሉ። በዚህም አል ሲ ሲ ኢትዮጵያ በአላት አነስተኛ ኢኮኖሚ እና ዲፕሎማሲዊ አቅም የተነሳ ይሄን ግድብ መስራት አትችልም የሚል እምነት ላይ ደርሰው ነበር።

የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ከአነስተኛ ነዋሪው ከጫማ ጠራጊው እስከ መንግሥት ሰራተኛው እና ነጋዴው ድረስ ከኪሱ ገንዘብ አዋጥቶ ግንባታውን መካሄድ ጀመረ። ግንባታው ቀጥሎ 40 በመቶ ደረጃ ላይ ሲደርስ ግብጾችን ጉዳዩ አሳሰባቸው። ኢትዮጵያውያኖች ግድብን መስራት ይችላሉ የሚል ድምዳሜ ላይ ሲደርሱ ደግሞ የተለያየ ኮሚቴ አዋቀሩ። በአል ሲ ሲ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሚ ሽኩሪ የሚመራው ቡድን የዲፕሎማሲውን ስራ እና ፕሮፖጋንዳውን እንዲይዝ ተደረገ። በቴክኒኩ ረገድ አሉ የሚባሉ መሃንዲሶች ግድቡን በተመለከተ የሀሰት መረጃዎችን በማካተት ጭምር ጥናት እንዲያካሂዱ አቅጣጫ ተቀመጠ። በዚህም ግንባታው የሚካሄድበት መሬት ግድቡን መሸከም ስለማይችል የመሬት መንቀጥቀጥ ሊነሳ ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ ለግብጽ ብቻ ሳይሆን ለቀይ ባህር አገራት በሙሉ አደጋ ነው በሚል የቀጠናውን አገራት ድጋፍ ለማግኘት መንቀሳቀስ ጀመሩ።

ራሱን የቻለ መዋቅር ተዘርግቶለት አራት ሺህ የግብጽ ሚዲያዎችን የያዘው ዘርፍ ደግሞ ኢትዮጵያ ጦርነት አወጀችብን በሚል ፕሮፖጋንዳ በመስራት አደጋውን እንዲያሳይ ማድረጉን ተያያዙት። በተጨማሪም ራሳቸውን የቻሉ የሃይማኖት ደርጅት እና የሚሊተሪ ኮሚቴዎች እንዲቋቋሙ ተደርገዋል። ይህ ሁሉ አደረጃጀትና ኮሚቴ ሲዋቀር የእኛ የመከታተል አቅማችን ደካማ ቢሆንም ግንባታውን መቀጠላችንን ግን አላቋረጥንም። ቁጥር አንድ ሙሌቱ ሲቃረብ ደግሞ ጩኸቱ በረከተ። በወቅቱ የግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ለጩኸት ወደ አረብ ሊግ አባል አገራት፣ቀጥሎም ወደ አሜሪካ ተጓዙ። በመሃሉ ባልተጠበቀ ሁኔታ ግድቡ ተሞልቶ አደረ። ግብጾች አፍሪካዊነታቸውን ክደው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ትኩረቱን ያደረገው በምዕራቡ ዓለምና አሜሪካ ላይ ነበር። ፕሬዚደንት ትራምፕም ግድቡ መመታት እንዳለበት በተናገሩ ማግስት በምርጫ ተሸንፎ ነጩን ቤተመንግሥት ለቀው ወጡ።

ሁለተኛው ሙሌት ሲቃረብ ግብጽና ሱዳን በጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል አገር የነበረችውን ቱኒዚያን በመጠቀም ግድቡ በመድረኩ አጀንዳ እንዲሆን አደረጉ። ይህን ያደረጉት ግድቡን ምቱ የሚል ይሁንታ ለማግኘት ነበር። ግድቡን ለመምታትም ግብጾች ራፋል የሚባል ከፈረንሳይ የገዙትን ሶስት ሺህ ኪ.ሜ ነዳጅ ሳይጨምር የሚጓዝ አውሮፕላን አዘጋጅተው ነበር። ይሁን እንጂ እንደታሰበው ሃሳባቸው ድጋፍ ሳያገኝ ቀርቷል። ቀጥሎ የሱዳኗ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ራሺያ ነበር ያመራችው። የግብጹ ድግሞ ወደ አውሮፓ ህብረት ሄዶ ነበር። ነገር ግን ሁሉም የነገሯቸው ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ህብረት እንዲመልሱት ነው። ብዙም ሳይቆይ ቁጥር ሁለት ሙሌቱ ጊዜውን ጠብቆ በስኬት ተጠናቀቀ። የግድቡን ሙሌት ተከትሎም በዓለም ዙሪያ በአንድ ሰዓት ውስጥ ብቻ የኢትዮጵያ ስም 25 ሺህ ጊዜ በሚዲያ መተላለፍ ችሏል።

ፕሮፌሰር አደም ከሶስተኛው ሙሌት በፊት የነበሩ ሁነቶችን የዳሰሱበትን ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፣ ግብጾች በስጋት ተውጠው ከመጀመሪያ ጀምሮ ያደረጉት ትግል ግድቡ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ ሳይደርስ ለመምታ ነበር። ከዚህ በኋላ ግን 8 ሺ 400 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ስለሚይዝ አንድ ጥይት ቢተኮስበት አቀማመጡ ኢትዮጵያ 500 ሜትር፣ ሱዳን 320 ሜትር እንዲሁም ግብጽ 220 ሜትር ከባህር ወለል በላይ ስለሆኑ ውሃው ጥሶ ቢሄድ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ ሃያ ሚሊየን ህዝብ ጠራርጎ ወደ አስዋን ግድብ ስለሚከት የተጠመደ ፈንጅ ሆኗል ይላሉ።

አያይዘውም አሁንም ቢሆን ቁጥር ሶስት ሙሌት የሚከናወንብት ጊዜ እየቀረበ በመምጣቱ ስለማይተኙልን መልሰው አጀንዳውን ማንሳታቸው አይቀርም። ስለሆነም በእኛ በኩል መሰራት የሚገባቸውን ስራዎች ማከናወን እንደሚገባን ይገልጻሉ። አንደኛ የዲፕሎማሲ የቤት ስራዎቻችንን በሚገባ በመስራት አፍሪካውያንን ከጎናችን ማሰለፍ መቻል አለብን። ሁለተኛ ነብዩ ሙሀመድ የሀበሻ ምድር የሆነችውን ኢትዮጵያን አትንኩ ማለታቸውን መሰረት በማድረግ የሙስሊም አገራትን ድጋፍ በማግኘት የግብጾችን እንቅስቃሴ ማክሸፍ ይገባል። ሶስተኛ ከዚህ በኋላ ግድቡን ለማጥቃት ባያስቡም፣ ትኩረታቸውን ኢትዮጵያ ሰላም እዳታገኝ እና አንድነቷ እንዳይጠበቅ ማድረግ ላይ ማድረጋቸው ስለማይቀር ይህን በቅጡ መረዳትና መስራት ያስፈልጋል። በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት እና የኢትዮጵያውያኖች በገፍ ከሳውዲ መባረር ዝም ብሎ ከሜዳ የመጣ አለመሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።

ግብጾች ይሄን ሁሉ ችግር በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጥሩት እውነት የውሃ እጥረት አጋጥሟቸው ነው ወይ የሚለውን ነገር ጠለቅ ብልን ማጤን ያስፈልገናል። ግብጽ ውስጥ 30 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት የሚያደርጉ ሰባት ሺ የሳውዲ ኩባንያዎች አሉ። የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ባለሀብቶችም እዚህ ውስጥ ይገኛሉ። በግብጽ የሚመረተው አትክልትና ፍራፍሬ ነው ስድስቱን የገልፍ አገሮች የሚመግበው። የግብጽ ስጋት ግን ኢትዮጵያ ግድቡን ሰርታ ከጨረሰች ሁሉም ኢንቨስተሮች ኮብልለው ወደ ኢትዮጵያ ስለሚገቡ እኛ ባዷችንን እንቀራለን የሚል ነው።

በመሆኑም በዚህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ዝግጅት ምን መምሰል እንዳለበት ሲገልጹም፣ የግብጾች የዲፕሎማሲ እንቅስቀቃሴ ወደ አፍሪካም ሊመጣ ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ በኛ በኩል ምን መደረግ አለበት በሚል ቀድሞ መዘጋጀት ይገባል። በቅድሚያ በግብጽ እና በሱዳን በኩል ያሉ ደካማ ጎኖችን መለየት ነው። ግብጾች በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የተነሳ የምግብ ዋስትና ችገር አጋጥሟቸዋል። ለምሳሌ ሳውዲ አረቢያ ለስንዴ መግዣ አምስት ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጋላቸው ነበር። ዩክሬን ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ስንዴ አልሸጠም ብላ አቋም ወስዳለች። አሁን ያላቸው የግብጾች የመጠባበቂያ ክምችታቸው ቢበዛ ከሶስት እስከ ስድስት ወር የሚያደርስ ብቻ ነው። ስለዚህ አል ሲ ሲ የግድቡን ጉዳይ የውስጥ ፖለቲካ ማረጋጊያ አጀንዳ እያደረገው መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ሁለተኛ ሊቢያ ውጥንቅጧ እየወጣች ያለች የግብጽ ጎረቤት አገር ነች። ሱዳን ውስጥም ያልተረጋገ ሁኔታ አለ። የዳርፉር ጉዳይ እና የህዝቡ አመጽም እንዳለ ነው። ስለዚህ በአገራችን ላይ ችግር እንዳያደርሱ ደካማ ጎናቸውን አውቆ መስራት እንደሚገባ ይመክራሉ።

የውጭ ጉዳይ ሚንቴስትር የዲፕሎማሲ ጥረት እና ጥንካሬ ወሳኝ ነው የሚሉት ፕሮፌሰር አደም፣ አረብኛ ቋንቋን አቀላጥፈው የሚናገሩ በቂ ዲፕሎማቶችን በአረቡ ዓለም በመመደብ የኢትዮጵያን አውነት ማስረዳት ይገባል። በተለይም በአሜሪካና በመከካከለኛው ምስራቅ አገራት የሚኖሩ ዜጎቻችን አገራቸውን እና ህዝባቸውን ወክለው የበለጠ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ የእስልምና ጉባኤም ተጠናክሮ መንቀሳቀስ ይኖርበታል። ወደ ተለያዩ አገራት በማቅናትም ሆነ በአገር ውስጥ የሙስሊም ምሁራኖችን እና አምባሳደሮችን ጋብዞ ኮንፍረንሶችን በማካሄድ የኢትዮጵያ ችግር ርሃብ እና ድህነት መሆኑን ማስረዳት አለበት። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ደግሞ የግድቡን አስፈላጊነት ማሳመን ይጠበቅባቸዋል። እነዚህን የቤት ስራዎቻችንን በሚገባ ከተወጣን ግብጽ እና ሱዳን ምንም ሊያደርጉን እንደማይችሉ በእርግጠኝነት ይናገራሉ።

የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ በመሆን ለሰባት ዓመታት ያገለገሉት፤ በአንድ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በፈረሙት የመርህ ስምምነት ላይ የተሳተፉት እና በአሁኑ ወቅት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶክተር ኢንጂነር ወንድሙ ተክሌ ደግሞ፣ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ችግር ቢገጥመንም የኢትዮጵያ ህዝብ በጋራ ጉዳዮቹ ላይ ወደ ኋላ የሚልበት ሁኔታ ስለሌለ ሶስተኛውን የውሃ ሙሌት ማከናወን ይቸግረናል የሚል እምነት የለኝም ይላሉ።

የቆየ ታሪካችን እንደሚነግረን በኢጣሊያ ወረራ በአድዋ ጦርነት እንዲሁም በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመን በነበረው ዳግም ወረራ ወቅትም ወስጣዊ ችግሮች ነበሩብን። በደርግ ዘመን በነበረው የሶማሌ ጦርነት ወቅትም የውስጥ ችግሮች አልጠፉም። የኢትዮጵያ ህዝብ ግን የነበሩበትን ልዩነቶች ወደጎን ብሎ በአንድነት በመቆም የተቃጣበትን ወረራ በድል አሸንፏል። በተለይ ደግሞ ከውጭ ጠላቶች ጋር የሚካሄድ ጦርነትን ዳር ቆሞ ተመልካች የሆነበት ጊዜ የለም። በእርግጥ በአሁኑ ወቅት የውስጥ ጦርነት ቢኖርብንም ሰላም ይመጣል የሚል እምነት አለኝ የሚሉት ዶክትር ኢንጂነር ወንድሙ፣ ግብጽ እና ሱዳን የሚያደርጓቸውን የጸብ አጫሪ እንቅስቃሴዎችን ስንመለከት የዓለም አቀፍ ሁኔታውን ማየት እንዳለብን ይገልጻሉ። አገራችን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አባል እንደመሆኗ መጠን ዓለም አቀፍ የውሃ ስምምነቶች እና የወሰን ተሻጋሪ የውሃ ሀብት አስተዳደር መርሆችን መሰረት በማድረግ የግድቡን ግንባታ መመልከት እንደሚያስፈልግም ያስረዳሉ። በዚህም ሶስት ዋና ዋና ንድፈ ሃሳቦችን ማጤን ይገባል። እነሱም፡ – ፍጹም የግዛት ሉዋላዊነት (absolute territorial sovereignty)፣ ፍጹም የግዛት አንድነት (absolute territorial integrity) እና ውስን የግዛት ሉዋላዊነት (limited territorial sovereignty) የሚባሉት ናቸው።

የመጀመሪያው ፍጹም የግዛት ሉዋላዊነት (absolute territorial sovereignty) የሚለው ንድፈ ሀሳብ ማንኛውም አገር በግዛቱ የሚፈሰውን ውሃ ሌላውን ሀገር የማማከር ግዴታ ሳይኖርበት መጠቀም እንደሚችል የሚገልጽ ነው። በሌሎች አገሮች ላይ ተጽዕኖ አሳደረም፣ አላሳደረ የራሱን ንብረትና ሀብት ከመጠቀም አይከለክልም። በዚህ መሰረት የላይኞቹ ተፋሰስ አገራት የታችኞቹን ተፋሰስ አገራት ሳያማክሩ የሚጠቀሙበት ሁኔታ አለ ማለት ነው። እ.አ.አ በ1895 በሜክሲኮ የተገነባው ሪዮ ግራንዴ ግድብ አንዱ ማሳያ ነው። ይሁን እንጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙም ተቀባይነት ያለው አካሄድ አይደለም። በመሆኑም ይህ ንድፈ-ሃሳብ አይደገፍም ማለት ነው።

በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጠው ፍጹም የግዛት አንድነት (absolute territorial integrity) ድግሞ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ምንጊዜምቢሆን የታችኞቹን ተፋሰስ አገሮች ሳያማክሩ እና ፍቃድ ሳያገኙ ወሰን ተሸጋሪ ወንዞችን መጠቀም የለባቸውም የሚል ነው። በዋናነት እነግብጽ የሚያራምዱት ሃሳብ ይህን መነሻ ይዘው ነው። ይሁን እንጂ እንደመጀመሪያው ንድፈ ሃሳብ ሁሉ ይህኛውም በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙም ተቀባይነት የለውም።

ኢትዮጵያ እያራመደች ያለችው ውስን የግዛት ሉዋላዊነት (limited territorial sovereignty) የተሰኘውን ሶስተኛ አማራጭ ነው። እያንዳንዱ አገር በግዛቱ የሚፈሱትን የጋራ ወንዞች የመጠቀም ነጻነት እንዳለው ያረጋግጣል። የዚህ ጽንሰ ሃሳብ ጥቅም በተመሳሳይ መልክ የታችኛው እና የላይኛው አገራት መብቶች በሁለቱም ወገን ፍላጎቶች ላይ እንዲመሰረቱ ማድረጉ ነው። ይህም ማለት የፍታዊ አጠቃቀም ማዕቀፍ መኖርን ወይም ምክንያታዊ የመጠቀም መብትን ማረጋገጥ ነው። ይህ ንድፈ ሃሳብ ነው በአብዛኛው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እያገኘ የመጣው። በሌለው አገር ላይ ጉልህ ተጽእኖ ሳታሳድር ወይም ጉልህ ጉዳት ሳታደርስ ፍትሃዊ ተጠቃሚ የመሆን ግዴታ ውስጥ የሚከት ነው።

ይህ ማለት ግን የውሃው ድርሻ የግድ እኩል ይሁን ማለት አይደለም። 50 በመቶውን የላይኞቹ፣ 50 በመቶውን ደግሞ የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት እንዲጠቀሙ አያስገድድም። ጉዳት በማያደርስ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ማለት ነው። ይሄ ደግሞ በዓለም አቀፍ ህጎች እና ደንቦች ከፍተኛ ድጋፍ አለው። ለዚህ መነሻው ደግሞ እ.አ.አ በ1966 ሄልሲንኪ ላይ የተፈረመው ስምምነት ነው። እ.አ.አ በ1997 ላይም የተደረጉት የተባበሩት መንግሥታት የውሃ ሀብት ስምምነቶችም ይህን ያካትታሉ። በዚህ መርህ መሰረት ማንኛውም አገር ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በታችኛው አገራት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማያደርስ መልኩ መጠቀም ይችላል። ኢትዮጵያም እየተጓዘች ያለችው በዚህ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባለው መንገድ ነው።

ዶክተር ኢንጂነር ወንድሙ ከሶስተኛው የውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ ሊኖሩ የሚችሉ ጫናዎችን ሲጠቁሙ፣ በግብጾች በኩል ትንኮሳዎች እና አንዳንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ዘመቻዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ተቀባይነት ያላቸው አይደሉም። በእኔ እምነት ምንም አይነት ችግር ይከሰታል የሚል ስጋት የለኝም። ችግር ቢኖር ኖሮ ላለፉት 10 እና 11 ዓመታት እንመለከተው ነበር። ግን ደግሞ መዘናጋት ሳያስፈልግ በሁሉም መንገድ ራሳችንን መከላከል በሚያስችል ቁመና ላይ መገኘት አለብን። በተደጋጋሚ ሲነገር እንደነበረው ኃይድሮ ፓወር ኃይል አመንጭቶ በቀጥታ ወደ ወንዙ ነው የሚገባው። ግድቡ የሚገኘው ከሱዳን ድንበር 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በመሆኑ ያን ያህል ለመስኖ የመዋል ዕድል የለውም ይላሉ።

ሶስተኛው ሙሌት መከናወኑ እና ተጨማሪ ተርባይኖች ኤሌክትሪክ ማመንጨት መጀመራቸው የሚኖራቸውን ኢኮኖሚያዊ አንድምታ ሲያመላክቱም፣ አፍሪካ እ.አ.አ በ2063 አሳካቸዋለሁ ብላ ካቀደቻቸው አጀንዳዎች መካከል ግብ 7፣ 15 እና 17 የመሳሰሉትን ብንመለከት ከአየር ንብረት ጋር ተያይዘው ለሚመጡ ችግሮች ታዳሽ ኃይልን እንጠቀማለን የሚል ነው። በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረት በቅርቡ ያቋቋመው የታዳሽ ኃይል ኢኒሼቲቭ አለ። ስለዚህ ግድቡ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የራሱን አስተዋጽኦ በማድረግ እና አፍሪካን በተለይም የምስራቁን የሀጉሪቱን ክፍል በኃይል ከማስተሳሰር ጋር ተያይዞ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል። ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የኃይል አቅርቦት ችግር አለባት። ከፀሐይ የሚገኘውን ጨምሮ የኤሌክትሪክ ሽፋኗ 44 በመቶ ገደማ ብቻ ነው። የግብጾችን ብንመለከት ግን ወደ መቶ በመቶ የተጠጋ ነው። ከዚህ አንጻር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ ብሎም ለቀጠናው የኃይል አቅርቦት በመሆን ለልማት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉ እንደማያጠያይቅ ያብራራሉ።

ፖለቲካዊ አንድምታውም ትልቅ ትርጉም እንደሚሰጠው ሲገልጹ፣ ቻይና ከ40 አመት በፊት እ.አ.አ በ1978 ለውጭ አካላት በሯን ክፍት አድርጋ የመልማት እንቅስቃሴ ከመጀመሯ በፊት ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራራቢ የሚባል ደረጃ ላይ የነበረች አገር ናት። በአርባ ዓመታት በተደረገ አመርቂ እንቅስቃሴ የተመዘገበው አስደናቂ ልማት ግን ቻይና እድትፈራ እና ተደማጭነቷ እንዲጨምር አድርጓታል። ለኢትዮጵያም ኃይል ማመንጨት ብቻውን ግብ አይደለም። ግቡ የልማት ስራዎችን በማካሄድ ማኑፋክቸሪንግን በማስፋፋት የኢንዱስትሪ ልማትን ማሳደግ ነው። የኢንዱስትሪ ልማት ሲያድግም ወታደራዊ አቅምና የተማረ የሰው ኃይል (የሰው ሀብት) በከፍተኛ ደረጃ ያድጋል። የሀብት ክምችት ደግሞ እየጨመረ ይሄዳል። የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በከፍተኛ ደረጃ ይዘምናሉ፣ ይስፋፋሉ። ከ15 ዓመታት በፊት የተገነባው ኢንቮልድ የሚባለው 22 ሺ ሜጋ ባይት የሚያመነጨው የቻይና ግድብ ከፍተኛ የሆነ እድገት እንዲያሳዩ አግዟቸዋል። ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ አቅርቦት በማስገኘትም በቻይና ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ሚና ተጫውቷል። ኢትዮጵያም የአባይን ግድብ አጠናቃ ሙሉ ለሙሉ ኃይል ማመንጨት ስትጀምር ለቤት ውስጥ መብራት ሳይሆን ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ሊያንቀሳቅስ የሚችል ትልቅ አቅም ይፈጠራል። የመልማት የመጨረሻው ጥግ ለመድረስ አቅም ሆኖ ስለሚያግዝ ከፍተኛ ፖለቲካዊ አንድምታም ይኖረዋል ሲሉ እምነታቸውን ይገልጻሉ።

ዶክተር ኢንጂነር ወንድሙ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳየው ዋናው ጉዳይ የልማት ጉዳይ መሆኑን ያነሳሉ። ትልቅ የልማት አቅም ከገነባህ በአፍሪካም ሆነ በሌሎች አገራት የሚኖርህ ተሰሚነት ይጨምራል። አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ አካልት ኢትዮጵያ ላይ እየደረሱ ያሉ ተጽዕኖዎችም ይቀንሳሉ። ሶስተኛውን ሙሌት ተከትሎ በግብጾች በኩል ማስፈራራቶች ሊኖሩ ይችላሉ። በእጅ አዙር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችም አይኖሩም አይባልም። እስካሁንም በተለያየ መንገድ እያየነው ስለሆነ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ግድቡን በተመለከተ በአንድ ወቅት ዶናልድ ትራምፕ ከያዙት አቋም በቀር በአገር ደረጃ ኢትዮጵያን የማውገዝ አቋም ተይዞ የታየበት ጊዜ የለም። የዶናልድ ትራምፕ ሀሳብም ቢሆን ግለሰባዊ እንጂ እንደ አገር ሊወሰድ የሚችል አይደለም። አሜሪካም ሆነች ሌሎች ታላላቅ አገሮች ግድቡ ላይ የተለየ ፍላጎት ቢያሳድሩም እንኳን ከኢትዮጵያ ጎን የማይቆሙበት ምክንያት የለም ይላሉ።

84 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚይዘው የአባይ ወንዝ 50 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ወደ ታችኞቹ ተፋሰስ አገራት እንደሚያደርስ በመጥቀስ፣ የውሃ ሙሌቱን ለማጠናቀቅ ሁለት እና ሶስት ክረምት በቂ ነበር። ኢትዮጵያ ግን በዚህ አቅጣጫ መጓዝን አልመረጠችም። ይሄ ደግሞ በአጋጣሚ እኔም ተሳትፌበት በነበረው እ.አ.አ. በ2015 ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በፈረሙት ስምምነት መሰረት እየተከናወነ ያለ ነገር ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ አንደኛውን እና ሁለተኛውንም ሆነ ወደፊት የሚካሄዱት የውሃ ሙሌቶች ሶስቱ አገራት በፈረሙት የመርህ ስምምነት መሰረት ስለሆነ የሚከናወነው ምንም የተለየ ነገር አይፈጠርም ሲሉ ሀሳባቸውን ያጠቃልላሉ።

ተስፋ ፈሩ

ዘመን መጽሔት ሐምሌ 2014 ዓ. ም

Recommended For You