ፓርላማ – ከየት ወዴት?

የአንድ ሀገር ሕዝብ ይወክለኛል የሚለውን ተወዳዳሪ በነጻነት ከመረጠ በኋላ፣ ራሱን በራሱ ከሚያስተዳድርበት የዲሞክራሲ ሥርዓት መገለጫ አንዱ ፓርላማ ነው። በየጊዜው የተካሄዱት የኢትዮጵያ የፓርላማ ምርጫና ውክልናቸው እንደየሥርዓቶቹ የተለያዩ ቢሆኑም ታሪካቸው የሚጀምረው ግን ከዘውዳዊው ሥርዓት መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ምርጫና ፓርላማ በዘውዳዊ ሥርዓት /1911-1967 ዓ.ም./

በኢትዮጵያ ምርጫ የተጀመረው በንጉሣዊው (በዘውዳዊው) ሥርዓት በአጼ ኃይለሥላሴ የአስተዳደር ዘመን በ1911ዓ.ም. መሆኑን የተለያዩ የጽሑፍ መረጃዎች ይገልጻሉ። ምርጫው ግን ሕዝቡ በነጻነት የሚያከናውነው አልነበረም። ከደጃዝማቾችና ከመኳንንቶቹ መካከል ንጉሡ የፈለጓቸውን በአማካሪነት ይረዱኛል ብለው የሚያስቧቸውን ነበር የሚመርጧቸው። እነዚህም የንጉሡ አማካሪዎች “የዘውድ አማካሪዎች” ተብለው ሲታወቁ ምክር ቤቱም “የዘውድ ምክር ቤት” በመባል ይጠራ ነበር።

በ1923 ዓ.ም. ደግሞ የመጀመሪያው የተጻፈ ሕገ- መንግሥት ተረቆ የንጉሠ ነገሥቱ ሥልጣን፣ የዘውድ አወራረስ እና የፓርላማ ማቋቋሚያ አዋጅ ወጥቶ የመጀመሪያው ፓርላማ እንዲቋቋም ተደርጓል። የተዘጋጀው ሕገ- መንግሥት ግን ሕዝቡ ራሱ መምረጥ እስኪችል ድረስ የምክር ቤቶቹ አባላት በንጉሡና መኳንንቱ ይመረጣሉ የሚል ሕዝብን አግላይ ይዘት ነበረው። የተቋቋመው ፓርላማ እኩል የአባላት ቁጥር ያለው የሕግ መወሰኛ እና የሕግ መምሪያ የሚባሉ ሁለት ምክር ቤቶች ነበሩት።

ከነጻነት በኋላ በ1935 ዓ.ም. የተቋቋመው ፓርላማም እንደፊተኛው ሁሉ የሕግ መወሰኛ እና የሕግ መምሪያ ምክር ቤቶችን የያዘ ነበር። የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት በንጉሠ ነገሥቱ የሚመረጡ ነበሩ። የሕግ መምሪያ አባላት ግን የሀገር ሽማግሌዎች በየወረዳቸው ተሰብስበው የሚመርጧቸው ባላባቶች እንዲሆኑ ተደርጓል። ከ1948 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ሕዝቡ ራሱ በቀጥታ እንደራሴዎቹን እንዲመርጥ ዕድል ተፈጥሮለት ነበር። ከዚያም እስከ 1967 ዓ.ም. ድረስ በየአራት ዓመቱ አምስት ተከታታይ ምርጫዎች ተካሂደዋል። የምርጫ ቦርድ ተቋቁሞ ከሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጋር በመተባበር ምርጫዎቹ እንዲካሄዱ ተደርገዋል።

ምርጫና ፓርላማ በደርግ ዘመነ መንግሥት/1967-1983 ዓ.ም./

ደርግ ከ40 ዓመታት በላይ ሀገሪቱን ሲያስተዳድር የቆየውን ዘውዳዊ ሥርዓት በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን አስወግዶ በጥቂት ወታደራዊ መኮንኖች የተወከለ “ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ” በሚል ስም ሥልጣኑን ጨበጠ። በ1967 ዓ.ም. በጥቅምት ወር ከልዩ ልዩ ወታደራዊ ክፍሎችና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ 60 አባላት ያለው የመማክርት ጉባኤ እንዲመሰረትም አድርጓል። ይህ የመማክርት ጉባኤ እስከ 1968 ዓ.ም. ድረስ የፓርላማን ሥራ ሲሠራ ከቆየ በኋላ እንዲበተን ሆኗል። በ1979 ዓ.ም. ደግሞ የሥራ ዘመናቸው አምስት ዓመት የሆኑ 835 አባላት ያሉት ባለ አንድ ሸንጎ ምክር ቤት በምርጫ ተሰይሞ ነበር። ይሁን እንጂ ተወዳዳሪዎቹም ሆኑ ተመራጮቹ በሙሉ የኢሠፓ (የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ) አባል የሆኑ ብቻ ነበሩ። ሥርዓቱም ቢሆን የመድብለ ፓርቲን ሥርዓት የሚቃወምና የማያስተናግድ፣ የሶሻሊስት ርዕዮትን የሚያቀነቅን ነበር።

ምርጫና ፓርላማ በኢህአዴግ ዘመን /1983-2013 ዓ.ም./

ኢህአዴግ በትጥቅ ትግል መላ ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ከግንቦት 24- 28 ቀን 1983 ዓ.ም. በተካሄደ የልዩ ልዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ስብሰባ የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት አድርጓል። በዚህ የሽግግር ወቅት እንደ ሕገ-መንግሥት የሚያገለግል ቻርተርም አጽድቋል። በቻርተሩ መሠረት ደግሞ 86 አባላት ያሉት የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የተሳተፉበት የሽግግር መንግሥት ምክር ቤት መስርቷል።

በሽግግር ወቅቱ ምክር ቤት የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 11/1984 ዓ.ም. ተዘጋጅቷል። በየካቲት ወር 1984 ዓ.ም. ደግሞ የወረዳና የቀበሌ ጊዜያዊ አስተዳደር አካላት መርጫ ተከናውኗል። በዚሁ ዓመት በግንቦት ወርም የብሔራዊ፣ ክልላዊ፣ የዞን እና የወረዳ ምክር ቤቶችን አባላት ምርጫ አካሂዷል። ምርጫ ኮሚሽን ሥራውን እንደጨረሰም በምትኩ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በአዋጅ ቁጥር 64/1985 ዓ.ም. እንዲቋቋም ተደርጓል። ቦርዱ ከተቋቋመበት ህዳር ወር 1986 ዓ.ም. ጀምሮ የምርጫ አዋጁ አምስት ጊዜ የመሻሻል ዕድል አጋጥሞታል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮም አምስት ሀገር አቀፍ ምርጫዎችን የማካሄድ ሥራ አከናውኗል።

በሀገራችን በየጊዜው የተካሄዱት ስር ነቀል ሊባሉ የሚችሉ የፖለቲካ ለውጦች አጀማመራቸው በሀገሪቱ ሠፍነው ለነበሩት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቅሬታዎች ምላሽ ለመስጠት ነበር። በዚህም ዕኩልነትን፣ ዕድገትንና ማኅበራዊ ፍትህን ለማስፈን ያለሙ ነበሩ። ይሁን እንጂ ሁሉም ትልሞች አንግበው የተነሱበትን ዓላማቸውን ሙሉ በሙሉ ያሳኩ ነበሩ ለማለት ግን አያስደፍርም።

ከሁሉም ለውጦች በተሻለ ሁኔታ በኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት በሀገሪቱ ውስጥ በጎ ሊባሉ የሚችሉ ለውጦችን ማሳየቱን የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በኢኮኖሚ ረገድ በሀገሪቱ ፈጣን ሊባል የሚችል የኢኮኖሚ ዕድገት እና አመርቂ የመሠረተ- ልማት ውጤቶች ስለመመዝገባቸው በጣም ብዙ የተለያዩ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። የተገኘው የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የመሠረተ-ልማትና የማኅበራዊ አገልግሎቶች መስፋፋት ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ማርካት ካለመቻላቸው በላይ የተወሰኑ ቡድኖችን ተጠቃሚ ያደረጉ ነበሩ። በመሆኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የህብረተሰቡ ሁለንተናዊ የልማት ፍላጎት ሕዝባዊ ተቃውሞ አስነስቶ በሀገሪቱ ከፍተኛ ቀውስ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። የሕዝባዊ ተቃውሞው ውጤትም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን በፈቃደኝነት ለቀው ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በቦታቸው እንዲተኩ አድርጓቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ደግሞ የተለያዩ የለውጥ እርምጃዎችን መውሰዳቸው ይታወቃል። ከእነዚህ ለውጦች መካከል የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት ያሏቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው እንዲንቀሳቀሱ መደረጋቸው ይጠቀሳል።

ከኤርትራ መንግስት ጋር ሠላም መፍጠር መቻሉም ሌላው የለውጡ አካል ነው። እንደ ምርጫ ቦርድና ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመሳሰሉ ተቋሞች ላይ ተቋማዊ ማሻሻያዎች ተካሂደዋል። መብት ገዳቢ በነበሩ አንዳንድ ሕጎች ላይም ማሻሻያ መደረጋቸው የለውጡ ዐቢይ ዕርምጃዎች ተደርገው ይነሳሉ።

ምርጫና ፓርላማ በብልጽግና /ከሰኔ 2013 ዓ.ም. ወዲህ/

የአራት ክልላዊ ፓርቲዎች ጥምረት የነበረው ኢህአዴግ፣ ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን በብቸኝነት አስተዳድሯል። በኋላ የገጠመውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ፣ ከውስጡ በወጡ መሪዎች አማካኝነት ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን በማድረግ “ብልጽግና” በሚል ስያሜ ራሱን በአዲስ መልክ አዋቅሯል። ብልጽግና ከቀደምት አባል ፓርቲዎች መካከል ህወሃትን የቀነሰ ቢሆንም፣ በርካታ ክልላዊ ፓርቲዎችን በማካተት ፖለቲካዊ መሠረቱን አስፍቷል። በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫም ከትግራይ ክልል ውጪ አዲስ አበባን ጨምሮ በተደረጉ ምርጫዎች በአብላጫነት በማሸነፍ ሀገሪቱን ለአምስት ዓመታት የማስተዳደር መንበሩን ተረክቧል። በመሆኑም “ብልጽግና” አንድ ወጥ ፓርቲ ከሆነ በኋላ ከኢህአዴግ ጋር ሲነጻጸር በፓርላማ እንቅስቃሴ ምን የተሻሉ ጎኖች እንዳሉት መረጃዎችን መነሻ በማድረግ ለመዳሰስ ጥረት አድርገናል።

የተከበሩ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ በ6ኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ በአማራ ክልል ብልጽግናን ወክለው በመመረጥ የፓርላማ አባል እና የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው። እንደ አንድ የፓርላማ አባል በፓርላማው የታዘቡትን ሲናገሩ፣ የፓርላማው አንዱ ጥንካሬ ብለው ያነሱት የፓርላማ አባላት በቀጥታ ወደ ሥራ እንዲገቡ አለመደረጉን ነው። ምክንያቱም አባላቱ የመጡት ከተለያየ የሥራ አካባቢ በመሆኑ የፓርላማን ሕግና ሥነ-ሥርዓት አያውቁትም። ስለሆነም ሕግና ሥርዓቱን ማወቅ አለባቸው በሚል የፓርላማ አባላቱ የትውውቅ ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል። ስልጠናው የፓርላማውን ተግባርና ኃላፊነት ምንነት አሳውቋቸዋል። ደንቦችን እና አሠራሮችን የማስገንዘብ ሥራም ሠርቷል። በተለይ ደንብ ቁጥር 6/2008ን የአባላት አሠራርና ሥነ-ሥርዓት ደንብን አባላቱ በአግባቡ እንዲገነዘቡት አድረጓቸዋል። ይህንንም በጠንካራ ጎን አንስተውታል።

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ተወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበር ያገኙት እና የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ ደግሞ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ሐሙስ ሚያዚያ 27 ቀን 2014.ዓ.ም. ዕትም ጋር በነበራቸው ቆይታ የ“ብልጽግና” ፓርላማን፤ “የአሁኑ ምክር ቤት በአንጻራዊነት የተማሩ ሰዎች ማለትም ከምክር ቤት ውጪ ኑሯቸውን ለመምራት አቅምም ብቃትም ያላቸው ሁሉም ባይሆን እንኳ የተወሰኑት የምክር ቤት አባላት ከፖለቲካ ዝንባሌያቸው ባለፈ በምሁርነታቸው በአደባባይ የተመሰከረላቸው እና እንደግለሰብ ለኢትዮጵያ እና ለልጆቿ ባላቸው ቀናኢ ሀሳብ የሚደነቁ ናቸው። ይህ ሲታይ የ6ኛው ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት ሲሆን እስካሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ሊጠቅሙ የሚችሉ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ረገድ በአንጻራዊነት የተሻለ ተሳትፎ ያላቸው ናቸው ለማለት ያስደፍራል” በማለት ገልጸውታል።

በሀገራችን የፖለቲካ ሂደት እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ሴቶች ለፖለቲካ የተገቡ እስከማይመስል የደረሰ የአመለካከት ችግር ነበር። በዚህ ምክንያት የነበራቸው የፖለቲካ ተሳትፎ በእጅጉ አናሳ ሆኖ እድል ተነፍጓቸው ቆይቷል ማለት ይቻላል። አሁን ላይ ግን ሴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ፖለቲካው እንዲገቡ የሚያበረታቱ እንቅስቃሴዎች በገዢውም ሆነ በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ መሻሻሎች እየታዩ መምጣታቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

አቶ ናምሲ አልቃ ይባላሉ። በደቡብ ክልል ስር በሚገኘው የደቡብ ኦሞ ዞን የአሪ ብሔረሰብን ወክለው ከ1987 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. ማለትም ከ1ኛው እስከ 3ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በመመረጥ ለተከታታይ 15 ዓመታት የፓርላማ አባል ነበሩ። አሁን ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽ/ ቤት የፓርላማ መረጃ አገልግሎት ቡድን መሪ ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ። አቶ ናምሲ በፓርላማ የረጅም ጊዜ ቆይታቸው እንደታዘቡት ከሆነ፣ አሁን ላይ ብዙ ነገሮች እየተሻሻሉ መምጣታቸውን ይናገራሉ። በፓርላማ የሴቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። በመጀመሪያው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሴት የፓርላማ አባላት በቁጥር 13/2.38%/ ብቻ ነበሩ። በ5ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ደግሞ 212/38.8%/ ደርሰዋል። በ6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይም ገና ምርጫ ያልተካሄደባቸው ብዙ አካባቢዎች በመኖራቸው አሁን ላይ በፓርላማ የሚገኙት በቁጥር 195 በመሆናቸው ቁጥሩ ያነሰ ቢመስልም ምርጫው ሲጠናቀቅ የተሻለ ቁጥር ሊመዘገብ እንደሚችል ገልጸዋል።

የተከበሩ አቶ ደሳለኝም የአቶ ናምሲን ሀሳብ በመደገፍ፣ ፓርላማው ለውጥ አመጣ ተብሎ ከሚነሳባቸው ተግባራት መካከል በዋናነት የጾታ ስብጥሩን ከፍ ማድረግ መቻሉ መሆኑን ይናገራሉ። እንደ የተከበሩ አቶ ደሳለኝ አገላለጽ፣ የፓርላማ የጾታ ስብጥሩ በሂደት የሚያድግ ቢሆንም እስከ አርባ በመቶ ድረስ የሴቶች ድርሻ አለው። ዋናው በጠንካራ ጎን የሚነሳው የሴቶችን ቁጥር ማሳደግ መቻሉ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ተሳትፎ ሴቶች የሚገኙበት መሆኑ ነው። በምደባ ሲታይ ከአፈ-ጉባኤዎቹ መካከል አንዷ እና ከመንግሥት ተጠሪዎች ውስጥ ደግሞ አንዷ ሴቶች ናቸው። ከአስራ አንዱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ውስጥ ደግሞ ሁለቱን የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላት በሰብሳቢነት ይዘውታል። ከቀሪዎቹ ዘጠኝ ቋሚ ኮሚቴዎች መካከል ስድስቱ ሴቶች በሰብሳቢነት የሚመሯቸው ናቸው። የሴቶች ተሳትፎ ደግሞ በቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢነት ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በቋሚ ኮሚቴው ውስጥ የአባልነት ስብጥሩም በዚያው ልክ ሰፊ ነው። የሴት የፓርላማ አባላት ጎልተው የሚታዩት በቁጥር እና በተሳትፎ ብቻ ሳይሆን ሚናቸውም ከፍተኛ መሆኑ ጭምር ነው። ሴት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ሥራቸውን ሲሠሩ፣ የሠሩትን ሥራ ሪፖርት ሲያደርጉ፣ ኮሚቴያቸውን ሲያስተባብሩ፣ ተቋማትን ሲከታተሉና ግብረ መልስ ሲሰጡ ብዙዎቹ ከወንዶቹ የተሻሉ ናቸው።

በፓርላማ የተፎካካሪ ድርጅቶችን ተሳትፎ በተመለከተም ቀደም ባሉት ምርጫዎች ተመርጠው ሲሳተፉ ቢቆዩም በ5ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ግን ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጠፍተዋል። በዚህ ምክንያት ኢህአዴግ ከአጋር ድርጅቶቹ ጋር ብቻውን ፓርላማውን ተቆጣጥሮት መቆየቱን የሚናገሩት አቶ ናምሲ፣ በ6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ግን አብንን እና ኢዜማን ጨምሮ አራት የሚሆኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳታፊ መሆን በመቻላቸው በፓርላማ የፓርቲ ተሳትፎ ወደ ኋላ የመመለስ ጉዞው መገታቱን ይገልጻሉ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ የተከበሩ አቶ ታገሠ ጫፎ “ፓርላማ” መጽሔት፣ መስከረም 2014 ዓ.ም፣ ቅጽ 26 ላይ፤ የምክር ቤቱን አባላት የሀሳብ ተሳትፎ በተመለከተ ከዝግጅት ክፍሉ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ የምክር ቤቱ አባላት ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝቡ እና ለህሊናቸው ታማኝ መሆን እንዳለባቸው በሕገ-መንግሥቱ ተደንግጎ ይገኛል። ካለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል ወዲህ ሀገራዊ ለውጡ ከተጀመረ በኋላም የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ውሳኔዎች በፓርላማው በሚተላለፉበት ወቅት በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጠውን ድንጋጌ ባከበረ መልኩ የመሰላቸውን ሀሳብ በነጻነት እየመከሩ እና እየተከራከሩ ይገኛሉ። ባልመሰላቸው ጉዳዮች ላይ ደግሞ በተቃውሞ ይወጣሉ። ወይም ድምጸ-ተአቅቦ እንዲያደርጉ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩንና የሚታዩ ጅምሮችም በጠንካራ ጎን የሚታዩ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የፓርላማ አባላት በምክር ቤት የሀሳብ ተሳትፎ በሚመለከት የሚያሳየውን ጠንካራ ጎኑን የተከበሩ አቶ ደሳለኝ ሲያብራሩ፣ የቆየው የፓርላማ አባላት በአብዛኛው ከተማ ገብተው ራሳቸውን ለማሳደግ ፍላጎት የነበራቸው ነበሩ። በተለይም ትምህርታቸውን አሻሽለው ወደ ከፍተኛ አመራር ለማደግ የሚፈልጉ ናቸው። በዚህም ምክንያት በድርጅት እሳቤ እና ዲሲፕሊን ላይ ብቻ የተገደቡና የታጠሩ ስለነበሩ፣ ከድርጅት አስተሳሰብ ወጥተው ለመናገር ብዙም የሚደፍሩ አልነበሩም። ከለውጡ በኋላ ከተመረጡ የፓርላማ አባላት መካከል ግን በብዛት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ማዕረግ የነበራቸው፣ በዞንና በክልል ደረጃ ደግሞ በከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ላይ የነበሩ ይገኙበታል። ይሁን እንጂ አባላቱ ለሕዝብ የምችለውን አስተዋጽኦ ላበርክት በሚል የተቆርቋሪነት ስሜት ከከፍተኛ ክፍያ፣ ደመወዝ፣ ጥቅማጥቅም እና ገቢ በጣም ዝቅ ብለው የመጡ ናቸው። በመሆኑም በምክር ቤቱ ሀሳባ ለመስጠት የሚሰጉበት፣ የሚሸማቀቁበት እና ይህን ብንል ይህን እናጣለን ብለው የሚፈሩት ነገር የላቸውም። የማስመሰልና የድብብቆሽ ሥራንም ቢሆን አያውቁትም፤ አይወዱትም። ስለሆነም የሚመስላቸውንና ይጠቅማል የሚሉትን ነገር በነጻነት በመናገር ለአንድ ዓላማ እና ለአንድ ሀገር እየታገሉ ይገኛሉ። የሚያደናቅፍ እና ትክክል ያልሆነ ነገር በፓርላማ ሲፈጠር ደግሞ ልክ አይደለም በማለት ሀሳቡን የማስተካከል አቅሙ እንዳላቸው ይናገራሉ።

የተከበሩ አቶ ደሳለኝ ሀሳባቸውን በምሳሌ ሲያስረዱ፣ ከምርጫ ማግስት የፓርላማ አባላት በየተመረጡበት አካባቢ እየኖሩ በተመላላሽነት የፓርላማ ሥራቸውን ያከናውኑ የሚል ጥናት ቀርቦ ነበር። ይሁን እንጂ የፓርላማ አባላቱ ጥናቱ ልክአለመሆኑን በሀሳብ ተሟግተውታል። በዚህም አዲስ አበባ ሆነን በተረጋጋ መንገድ የመንግሥትን ጥንካሬም ሆነ ድክመት እየተከታትልንና እየተቆጣጠርን እናግዛለን በሚል ጥናቱን እስከማስቀየር የደረሰ ጠንካራ ፓርላማ መሆኑን አንስተዋል።

በተመሳሳይ መንገድ አቶ ናምሲ፣ ቀደም ባሉት ፓርላማዎች የተለያዩ ሹመቶች በኢህአዴግ እንዲጸድቁ ጥቆማዎች ሲቀርቡ ያለምንም ተቃውሞ፣ ተቃውሞ ቢኖርም እንኳ የቀረቡ ሹመቶች በሙሉ፣ በድምጽ ብልጫ በሚል እንዲጸድቁ ይደረግ እንደነበር ይናገራሉ። ከለውጡ በኋላ ግን በምክንያት የሚቀርቡ ተቃውሞዎች ተቀባይነት አግኝተዋል። በዚህም በሀሳብ የመደገፍና የመቃወም ጥንካሬ እየጎላ መጥቷል። ለሹመት የሚቀርቡ ተጠቋሚዎችም ምክር ቤቱ ሳያምንባቸው ሲቀር በሌላ ሲተኩ እያስተዋሉ መሆናቸውን በመግለጽ የሚታየው ጅምር የሚያበረታታ መሆኑን አስምረውበታል።

የተከበሩ አቶ ጫላ ለሚ ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሲሆኑ፣ በፓርላማ መጽሔት ላይ “አንድ የምክር ቤት አባል ተገዥነቱ ለህሊናው፣ ለሕዝቡና ለሕገ-መንግሥቱ በመሆኑ በሚናገረው ሀሳብ የሚከሰስበትና የሚገመገምበት ምንም ዓይነት የሕግ መነሻ የለም” በማለት የምክር ቤት አባላት ሀሳብ ለመስጠት ምቹ ሁኔታ የተፈጠረላቸው መሆኑን ያስረዳሉ።

በፓርላማ የሚነሱ የሀሳብ ግጭቶችን አስመልክቶ አቶ ናምሲ ሲገልጹ፣ የሀሳብ ክርክሮች ቀደም ሲል በነበሩ ፓርላማዎችም ነበሩ። ልዩነቱ ቀደም ባሉት ጊዜያት ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተጠናከረ ሀሳብ እንዳያነሱ ድርጅቶቹ እርስ በእርሳቸው እንዲከፋፈሉ የማድረግ ሥራ ይሠራ ነበር። የሀሳብ መስጫ ሰዓት የሚፈቀደው ደግሞ በመቀመጫ ብዛት ነበር። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን እንዲገልጹ ይሰጣቸው የነበረው ሰዓትም አንድ ደቂቃ ብቻ በመሆኑ፣ ሀሳቡ ሳይጠናቀቅ የሚያስቆም አሠራር ስለነበር ሰዓቱ ገዳቢ ነበር። ለኢህአዴግ አባላት ግን ረዘም ያለ ጊዜ እስከ አንድ ሰዓት ሀሳባቸውን እንዲገልጹ አሠራሩ ይፈቅድላቸዋል። አሁን ላይ ግን ተግባራዊ በመደረግ ላይ የሚገኘው ወጥነት ባለው መንገድ ሁሉም ፓርቲ ሀሳቡን በነጻነት የሚሰጥበት ሁኔታ ተፈጥሯል ይላሉ።

ፓርላማ ላይ በሚደረግ ውይይት የሚመስላቸውን ሀሳብ ያለምንም መሸማቀቅ እና ስጋት ለሕዝብ ይጠቅማል የሚሉትን ሀሳብ ቀድመው የሚሰጡት በአብዛኛው ሴቶች ናቸው ማለት ይቻላል። ሕዝብን ይጎዳል ብለው ያሰቡትን ሀሳብ ደግሞ በድፍረት ይቃወማሉ። ስለሆነም በዚህ ለውጥ በሴቶች ላይ የታየው ጥሩ ነገር ቁጥራቸውን ከፍ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ሚናቸውን ማጉላት መቻሉ ነው። የተደበቀ አቅማቸውን አውጥተው ፓርላማው የተስተካከለ ቁመና ላይ እንዲገኝና ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲይዝ በማድረግ ረገድ የሴቶች ተሳትፎ ትልቅ ድርሻ ያለው መሆኑን የሚገልጹት የተከበሩ አቶ ደሳለኝ ናቸው።

ፓርላማው የሚያከናውናቸው አራት ዋና ዋና ተግባራት አሉት። እነሱም፡- ሕግ ማውጣት፣ አስፈጻሚውን መከታተልና መቆጣጠር፣ የሕዝብ ውክልና ሥራን መሥራት እና የፓርላማ የዲፕሎማሲ ሥራ ናቸው። በመሆኑም እነዚህን ተግባራት የሚያከናውንለት ከፓርላማ አባላቱ መካከል ቋሚ ኮሚቴ ያደራጃል። በዚህም በምክር ቤቱ 11 ቋሚ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል። ቋሚ ኮሚቴዎቹ በሕገ- መንግሥቱ በተቀመጠው ድንጋጌ መሠረት አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶችን ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋሉ። እንደ ተከበሩ አቶ ታገሠ አገላለጽ፣ ቋሚ ኮሚቴዎቹ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶችን ክትትልና ቁጥጥር በሚያደርጉበት ወቅት መሰረታዊ ለውጥ በማያመጡ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ጊዜ እንዳይወስዱ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል። እያንዳንዱ ቋሚ ኮሚቴ አንኳር በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ተጨባጭ ውጤት እንዲያስመዘግብ ለማድረግ አቅጣጫ ተቀምጧል። በዚህ መነሻነትም ክትትልና ቁጥጥሩን መለካት የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል። አሠራሩም ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል። በዚያ ልክም በሰነዱ መነሻነት ኮሚቴዎች ሪፖርት ማቅረብ መጀመራቸው የሚበረታታ ጅምር እንደሆነ ያስረዳሉ።

የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዋናነት የመንግሥት በጀትና ንብረት ሕግና ሥርዓት በሚፈቅደው መንገድ ለታለመለት ዓላማ መዋልና አለመዋሉን የማረጋገጥ ሥራን ያከናውናል። በተለይም የፋይናንስና የክዋኔ ኦዲት ላይ በስፋት እየሠራ እንደሚገኝ የገለጹት የተከበሩ አቶ ክርስቲያን፣ የኦዲት ሥራ ቀደም ሲል በተከናወነ ተግባር ላይ የሚያተኩር ነው። በመሆኑም በ2002 እና 2003 በጀት ዓመት አስፈጻሚው ባከናወነው የኦዲት ግኝቶች ላይ ይፋ መድረክ አዘጋጅተዋል። በተዘጋጀው መድረክ ላይም የኦዲት ባለድርሻ አካላት እንዲገኙ ተደርጓል። ኦዲተር ጀኔራሉ ደግሞ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቶባቸዋል። መጨረሻ ላይም ቋሚ ኮሚቴው በሚያስጠይቁ ጉዳዮች ላይ ተቋማት ተጠያቂ እንዲሆኑ ውሳኔ አስተላልፏል። ለአብነት ያህልም፣ በቅርቡ በተካሄደ ክትትልና ቁጥጥር ገንዘብ ሚኒስቴር በ39 አስፈጻሚ ተቋማት ላይ እርምጃ እንዲወስድባቸው ማድረግ ተችሏል። የፍትህ ሚኒስቴር ደግሞ አስተዳደራዊ ውሳኔ በተላለፈባቸው ተቋማት ላይ ምርመራ እንዲያካሂድ ትእዛዝ ሰጥቷል። ጉዳዩ የወንጀል ተጠያቂ የሚያደርጋቸው ከሆነም እንዲወስን ቋሚ ኮሚቴው አቅጣጫ ማስቀመጥ መቻሉን አብራርተዋል።

የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ደሳለኝም በበኩላቸው በቋሚ ኮሚቴያቸው አማካይነት የተከናወኑ ተግባራትን ሲያስረዱ፣ የቋሚ ኮሚቴው አንዱ ተግባር ሕግ ማውጣት ነው። በመሆኑም የመንግሥት ሠራተኞች እና የግል ድርጅት ጡረታ አወጣጥ ሁኔታን የሚደነግጉ ሁለት ሕጎች ተመርተውላቸዋል። ረቂቅ ሕጎቹን አይተው፣ አደራጅተውና አዘጋጅተው የውሳኔ ሀሳብ ጭምር አካተው እንዲጸድቁ ማስደረግ ችለዋል። ሌላው ሥራ ደግሞ ሚኒስቴር መ/ ቤቶችን መከታተልና መቆጣጠር ነው። በዚህ ረገድ መጀመሪያ የቋሚ ኮሚቴውን ዕቅድ አዘጋጅተዋል። የአስፈጻሚዎቹን መ/ቤቶች ዕቅዶችንና የሩብ ዓመት ሪፖርቶቻቸውን በመገምገም ግብረ መልስ ሰጥተዋል። በቋሚ ኮሚቴው ስር የሚገኙ የእያንዳንዱን አስፈጻሚ ሚኒስቴር መ/ቤት የዘጠኝ ወር ሪፖርትም መቀበል ችለዋል። በተለይም ለጠቅላላ የምክር ቤት አባላት የሚቀርቡ የተመረጡ ሚኒስቴር መ/ቤቶች ግብረ መልስ መስጠትን አስመልክቶ የገቢዎች ሚኒስቴርን የ10 ወር ሪፖርት ግብረ መልስ ሰጥተዋል።

እንደ የተከበሩ አቶ ደሳለኝ አገላለጽ፣ የቋሚ ኮሚቴ አሠራራቸው ከመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር ተያያዥነት ያለው ነው። በመሆኑም ከቋሚ ኮሚቴው የደረሳቸውን የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ግብረ- መልስ በተመለከተ አፈጻጸሙን በመከታተል ላይ ይገኛሉ። በቋሚ ኮሚቴው ከደረሳቸው ሪፖርት መካከል የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ባለስልጣን እና የግዥ፣ የፋይናንስና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ይገኙበታል። የሪፖርቱ ይዘት ደግሞ በየተቋማቱ አላግባብ የሀብትና ንብረት አስተዳደር፣ እንዲሁም የንብረት ክምችት ችግር መኖሩን የሚገልጽ ነው። ስለሆነም ቋሚ ኮሚቴያቸው በየተቋማቱ የታየውን ችግር በአካል በመገኘት ክትትል አድርጓል። ክትትሉም ውጤት እያመጣና ችግሩ እየተፈታ መሆኑን ይናገራሉ።

የሕዝብ ውክልና ሥራን በተመለከተ የምክር ቤት አባላት በዓመት ሁለት ጊዜ (በየካቲት ወርና በክረምት ወቅት) ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር እንዲገናኙ አሠራር ተፈጥሯል። ከወከላቸው ሕዝብ ጋር ውይይት በማድረግ የሚነሱ ችግሮችንም ሪፖርት ያደርጋሉ። በቀረበው ሪፖርት መሰረትም ለሚመለከተው አስፈጻሚ አካል ሰነዱን በመላክ እና ክትትል በማድረግ ችግሩ እንዲፈታ እየተሠራ ይገኛል። ነገር ግን የምክር ቤት አባላት ከሕዝቡ ጋር ጥሩ ግንኙነት ኖሯቸው መሬት ላይ ያለውን እውነት በአግባቡ ተገንዝበው ችግሮች እንዲፈቱ በማድረግ በኩል ውስንነት መኖሩን የተከበሩ አቶ ታገሠ አስ ምረውበታል።

ሕዝብ ይወክለኛል የሚለውን ተወዳዳሪ በነጻነት ይመርጣል። በመረጠው ተወካዩ አማካይነት ደግሞ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት የዲሞክራሲ ሥርዓት አንዱ መገለጫ ፓርላማ መሆኑ ይታወቃል። በሀገራችን በየጊዜው የተካሄዱት የፖለቲካ ለውጦች አጀማመራቸው በሀገሪቱ ሠፍነው ለነበሩት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቅሬታዎች ምላሽ ለመስጠት ያለሙ እንደነበሩ መረጃዎች ያመላክታሉ። ይሁን እንጂ ሁሉም ትልሞች ዓላማቸውን ሙሉ በሙሉ ያሳኩ አልነበሩም። በኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት በአንጻራዊነት በጎ ሊባሉ የሚችሉ ለውጦችን ቢያሳይም የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ማርካት ግን አልቻለም። በመሆኑም በሕዝባዊ ተቃውሞ ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን በማድረግ “ብልጽግና” በሚል ስያሜ ራሱን በአዲስ መልክ አዋቅሯል። ስድስተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ አካሂዶም ፓርላማ መስርቷል። ፓርላማው ደግሞ ከቀደምቶቹ በአሠራር፣ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳትፎ፣ በሴቶች ውክልና፣ በአባላት የሀሳብ ተሳትፎ፣ በመሳሰሉት ጉዳዮች አበረታች ጅምሮችን እያሳየ መሆኑን መረጃዎች አመላክተዋል። እኛም ፓርላማው ይህን የተሻለ ጅምር የበለጠ አጠናክሮ የሕዝብ ውክልናውን በአግባቡ መወጣት ይኖርበታል እንላለን።

ንጉሤ ተስፋዬ

ዘመን መጽሔት ሐምሌ 2014 ዓ. ም

Recommended For You