‹‹ሆድ ሲያውቅ – ዶሮ ማታ››

ለአንድ ተግባር አሠራር ይቀመጥለታል። ምን መከናወን እንዳለበት፣ አፈጻጸሙ እንዴት እንደሆነ፣ ወይም ደግሞ የትኛው ተግባር መከናወን እንደሌለበት በግልጽ የሚያመላክት አሠራር ይኖራል። ይህን መንደርደሪያ ሀሳብ ማንሳቴ ስለ አሠራር ዕውቀት ኖሮኝ ላስተምር፣ አልያም በዘርፉ ልመራመር ፈልጌ አይደለም። ሁሉም እንደሚገነዘበው ግን ለሥራ ውጤታማነት ሲባል ዝርዝር አሠራር መቀመጡ ተገቢም፣ አስፈላጊም ነው ባይ ነኝ። በጉዳዩ ዙሪያ ዳር ዳር ማለቴ ግን አንዲት በቅርቡ ያስተዋልኳትን አነስተኛ ”የአሠራር ድብብቆሽ” ትዝብቴን ለማጋራት ፈልጌ ነው። ትዝብቴ ለሌላው አብሮት ለቆየው ሰው አዲስ ላይሆንበት ይችል ይሆናል። ምንም ይሁን ምን ግን የተሰማኝን ለአንባቢ ማድረስ ወደድኩ።

አዲስ አበባን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ቀደም ብየ አውቃታለሁ። በተለይም በተማሪነት ሕይወቴ በተሻለ ሁኔታ አውቃታለሁ ብዬ አስባለሁ። ከብዙ ዓመት መለየት በኋላ ደግሞ በቅርቡ ብቅ ብየባታለሁ። በመሆኑም ከአካባቢው ጋር ራሴን ለማለማመድ ደፋ ቀና ማለቱን ተያይዤዋለሁ። አዲስ አበባን ለመልመድ የማደርገው ጥረት ሁሉ አስቸጋሪ ነው። ለመልመድ ከፍተኛ ጥረት ከማደርግባቸው ተግባራት መካከል ደግሞ ግንባር ቀደሙ የታክሲ ወረፋና ግፊቱ ነው። ረጅሙን ሰልፍ ተሰልፎ ተረኛ ታክሲ እስኪመጣ ድረስ በከፍተኛ ትዕግስት ጠብቆ መሳፈር የዘወትር ተግባሬ መሆኑን ተገንዝቤዋለሁ። አዲስ አበባን ለመልመድ በማደርገው ጥረት፣ ሁሉም ከባድ ቢሆንም የከፋው ግን የታክሲ ወረፋ መጠበቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ትዝብቴን አንድ ብዬ ልጀምር፣ የታክሲ ወረፋ ደርሶህ ስትሳፈር ጋቢና ውስጥ የመግባት ዕድል ያጋጥምሃል። ጋቢና ገብተህ ወንበር ላይ እንደተቀመጥክ ቅድሚያ ማከናወን የሚጠበቅብህ ተግባር አለ። አንተ ባትረሳውም እንኳ ሾፌሩም፣ረዳቱም፣ተሳፋሪውም ሁሉም በአንድነት ያስታውሱሃል። ትንሽ ከዘገየህ ቀድመው ይነግሩሃል። አንተም ቢሆን የደህንነት ቀበቶውን ትክሻህ ላይ ጣል ማድረጉን በፍጹም አትዘነጋውም። አሁን ላይ የዘወትር ተግባር ስለሆነ ሁሉም ቀበቶውን የታሰረ ለማስመሰል እንደነገሩ ትከሻው ላይ ጣል ማድረግን ለምዶታል። የደህንነት ቀበቶ ማሰር ደግሞ ተሳፋሪን ከጉዳት ለመከላከል፣ ሕይወትን ለማትረፍ መሆኑን ማንም አይስተውም። ስለሆነም ቀበቶውን ተሳፋሪ እንዲያስር ያላደረገ ሹፌር እንደሚቀጣ አሠራር ተቀምጦለት ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑ እሰየው የሚያስብል ነው። ጠቀሜታው ለተሳፋሪ እስከ ሆነ ድረስም በትክክል መጠቀም ከተሳፋሪ ይጠበቃል። በዚህ ጉዳይ መደራደር ተገቢ ነው ብየ አላምንም።

ሌላው ደግሞ ጋቢና ውስጥ ሁለት ተሳፋሪ እንዲጭኑ የተፈቀደላቸው ታክሲዎች አሉ። ይሁን እንጂ የደህንነት ቀበቶ እንዲያስር የሚጠበቀው ግን አንደኛው በዳር በኩል የሚቀመጠው ተሳፋሪ ብቻ ነው። በአደጋ ጊዜ የሚይዘውና በአግባቡ የሚደገፈው የሌለው፣እንዲያውም ለከፍተኛ አደጋ ሊጋለጥ የሚችለው መሀል ላይ የሚሳፈረው ተሳፋሪ ሆኖ ሳለ የደህንነት ቀበቶ የለውም። ወንበሩ ሁለት ሰው እንዲይዝ ተደርጎ ቢሠራ ኖሮ የደህንነት ቀበቶውም ሁለት ሆኖ ይዘጋጅ ነበር። እየሆነ ያለው ተሳፋሪው ሁለት፣የደህንነት ቀበቶው ግን አንድ ነው። ስለሆነም የሁለተኛው ተሳፋሪ የደህንነት ጉዳይ የትኛውንም ወገን ያሳሰበው አይመስልም። በእኔ እይታ በእነዚህ ታክሲዎች ጋቢና ውስጥ መጫን የሚፈቀደው የተሳፋሪ ቁጥር አንድ ብቻ እንደሆነ ይሰማኛል። ይህ ባይሆን እንኳ ጋቢና ውስጥ የደህንነት ቀበቶ ሳያስር የሚጓዝ ተሳፋሪ መኖር አልነበረበትም። አሠራሩ እንዴት እንደፈቀደ በራሱ ግራ ያጋባል!

ትዝብቴን አገልግሎት በመስጠት ወደ ሚገኘው የደህንነት ቀበቶ ሳዞር ቀበቶው በአግባቡ ይታሰራል ወይ? ከሚደርስ ጉዳትስ ይከላከላል ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች መልስ ይፈልጋሉ። በእኔ እይታ መልሱ አብዛኛዎቹ የደህንነት ቀበቶዎች በደንብ የሚያስሩ(የሚይዙ) አይደሉም፣ ከጉዳትም አያድኑም ነው። በአብዛኛዎቹ ታክሲዎች ላይ የሚገኙት የደህንነት ቀበቶዎች የተተለተሉና የተንዘላዘሉ ናቸው። የሚገርመው የሾፌሩ ቀበቶ ራሱ የተንዘላዘለው ተርፎ በኋላ በኩል ተንጠልጥሎ ያየሁበት ጊዜ ሁሉ አለ። ጉዳዩን ደግሞ ተሳፋሪው ብቻ ሳይሆን አሠራሩን አስከባሪ የትራፊክ ፖሊሶች ጭምር እንደሚያውቁት እገምታለሁ።

በዚህ ጉዳይ ሀሳቤን የሚያጠናክር አንድ ትዝብቴን ላቅርብ፣ በቅርቡ ሁለት የትራፊክ ፖሊሶች ከመገናኛ ወደ ገርጂ ለመሄድ የደንብ ልብሳቸውን እንደለበሱ ታክሲ ላይ ተሳፈሩ። ሁለቱም ሴቶች ሲሆኑ የተሳፈሩት ደግሞ ጋቢና ውስጥ ነበር። የተሳፈርኩት ከኋላቸው ከቅርብ ነበርና የደህንነት ቀበቶውን ምን ሊያደርጉት ነው ብየ ለማየት ጓጓሁ። ቀበቶውን ከተመለከቱ በኋላ ከሾፌሩ ጋር የሆነ ነገር ይባባላሉ ብየም ጠብቄ ነበር። ፍጹም ባልጠበቁት ሁኔታ የደህንነት ቀበቶውን ለማሰር አልሞከሩም። እንደ ሁል ጊዜው ሁሉ እሰሩ ያላቸው ሾፌር፣ረዳትም ሆነ ተሳፋሪ አልተገኘም። ለነገሩ የሚነግራቸው ይኖራል ብዬ አልጠበኩም። ምክንያቱም ነገሩ “ለቀባሪው አረዱት” ነውና።

የደህንነት ቀበቶ ማሰር አሠራር ከተፈጠረለትና ማሰር የግድ ከሆነ የትራፊክ ፖሊሶች ለምን ተግባራዊ አያደርጉትም? ሁኔታው አሠራር ይበጃል፣ሕግም ይወጣል እንጂ ሕግ አስከባሪው አይተገብረውም የሚለውን ትዝብቴን የበለጠ አጠናክሮታል። የደህንነት ቀበቶውን ለማሰር ያልሞከሩት እንደማይሠራ፣ለይስሙላ ብቻ እንደተቀመጠ ቀድመው ያውቁታል፤ የሚለውን ሌላውን የትዝብቴን ትኩረትም አጉልቶታል። ለጊዜው ምንም ዓይነት የሚያስገድዳቸው አካል ባይኖርም የትራፊክ ፖሊሶቹ ለሕግና ደንቡ መከበር እንዲሁም ከተሳፋሪውም ትዝብት ለመዳን ሲሉ ተግባሩን ማከናወን ነበረባቸው እላለሁ። ምክንያቱም ሕግ አስከባሪው ምሳሌ መሆን ካልቻለ ሌላው አካል ቅጣት ስላለው ካልሆነ በስተቀር እንዴት ሊያከብረው ይችላል?

የታክሲ ወረፋን በተመለከተ ተጨማሪ ትዝብቴን ላንሳ። ተሳፋሪ ወረፋውን ጠብቆ ተረኛ ታክሲ መጥቶ ሊሳፈር ሲል በዚህኛው መንገድ አንሄድም፣አራት ኪሎ ሳይሻገር፣የመጨረሻ ወንበር የሚፈቀደው ለሦስት ሰው ሆኖ እያለ አራተኛ ሰው መጫን፣ወዘተ. የመሳሰሉ ከሕጉና ከተሳፋሪ ፍላጎት ውጪ ለመጫን የሚያስገድድ ሹፌርስ አጋጥመዋችሁ አያውቅም? መደበኛ ባልሆነና ባልተፈቀደ መስመር እየተሽሎከለከ ተሳፋሪን ካልፈለገው ቦታ ማውርድም ተለምዷል።

ትዝብቴን ሳጠቃልለው በአንድ በኩል የደህንነት ቀበቶውን የታሰረ ለማስመሰል የሚፈጠረውን ፍርሃትና ትርምስ ስመለከት፣ በሌላ በኩል ችግሩን አውቀው ሕግ አስከባሪዎች ችላ ማለታቸው ሊገባኝ አልቻለም። በውል የማላውቀውና ያልተገነዘብኩት “የድብብቆሽ ጨዋታ” ስለመኖሩ ግን ደመ-ነብሴ ነግሮኛል። ይህ ትዝብቴ ደግሞ የማውቀውን የቆየ ሀገርኛ አባባል አስታወሰኝ። ይህን መሰል የማይፈጸምና የማይሆን ነገርን እንደሚደረግና እንደሚሆን አስመስሎ መሸንገልን በተመለከተ “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” ብሎ ይገልጸዋል ያገሬ ሰው።

ንጉሤ ተስፋዬ

ዘመን መጽሔት ሐምሌ 2014 ዓ. ም

Recommended For You