“ከታጠቡ አይቀር ከክንድ …”

ደስታ ተክለወልድ ያማርኛ መዝገበ ቃላት (1962፣ 249) ግጭትን መግጨት፣ መገጨት፣ ድንገተኛ ጥል፣ ዕለተ ጠብ፣ ያልታሰበ አደጋ፣ የጊዜ ጦርነት ሲል ይገልጸዋል። የዘርፉ ምሁራን ደግሞ ግጭት የማኅበራዊ ኑሮ ተጋሪ በሆኑ ቡድኖችና ሕዝቦች መካከል በሚኖር ተቃራኒ ፍላጐቶች፣ ዕሴቶች እና ግቦች ምክንያት በሚከሰቱ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ ወይም ቁሳዊ መበላለጦች አማካይነት የሚከሰት ትግል እንደሆነ ይገልጻሉ።

ስለግጭት አይነቶች የተለያዩ አተያዮች ቢኖሩም በአብዛኛው በኢኮኖሚ፣ በዕሴት እና በስልጣን ፍላጎቶች የሚነዱ ሦስት አይነት ግጭቶች መኖራቸው ላይ ስምምነት አለ። የኢኮኖሚ ግጭት የሚባለው የላቀ ጠቀሜታ ያለውን ወይም ውስን የሆነ የጥሬ ሀብት ክምችትን ያለ ተጋሪ በግል ባለቤትነት ለመቆጣጠር ባለ ፍላጎት የሚከሰት ፍጥጫን የሚያመለክት ነው። የዕሴት ግጭት በኃይማኖት፣ በርዕዮተ-ዓለም፣ በአስተሳሰብና በባህል ልዩነት ወዘተ ሳቢያ በሚፈጠር አለመግባባት የሚከሰት ልዩነት ወይም ግጭት ነው። የሥልጣን ግጭት ደግሞ በግለሰቦችና በቡድኖች መካከል በሚኖር ፖለቲካዊና ማህበራዊ አወቃቀር ውስጥ መንበረ ሥልጣንን ለማቆየት ወይም ከፍ ለማድረግ በሚኖር ፍላጎት ምክንያት የሚቀሰቀስ ነው።

ግጭቶች በአግባቡ ሳይፈቱ ቀርተው አንድ ጊዜ ከእጅ ካመለጡ አላስፈላጊ ወደ ሆነና አደጋ ሊያስከትሉ ወደሚችሉበት አስከፊ ደረጃ ሊሸጋገሩ ይችላሉ። በአንጻሩ ግጭቶች በከፍተኛ ጥንቃቄና ብልሃት ከተፈቱ ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ ውጤት ማስመዝገብ የሚቻልበትን አጋጣሚ መፍጠር ይቻላል። ስለዚህም ግጭትን በከፍተኛ ጥንቃቄና ብልሃት ለመፍታት የሚያስችል ዕውቀት መገብየትና ልምድ ማካበት የአብሮ መኖር ሂደትን ውጤታማ፣ የጋራ ሥራን ስኬታማ በማድረግ ረገድ ትርጉም ያለው አስተዋጽዖ ያበረክታል።

ቀደምት ኢትዮጵያውያን የአገር ህልውና ላይ አደጋ የሚጥሉ አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት አገር ያሻገሩባቸው አጋጣሚዎች አሉ። ልዩነቶችን ማቻቻልና መፍታት ባለመቻል ደም አፋሳሽ ግጭት ውስጥ ገብተው ከፍተኛ ኪሳራ ያስተናገዱበት አጋጣሚም የታሪካቸው አካል ነው። ዛሬም ይህ ኡደት እንደቀጠለ ነው። በዛሬ ትውልዶች ምርጫና ውሳኔ አቅጣጫ የሚይዝ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ነገም ከሁለቱ በአንዱ ቅኝት ውስጥ መውደቁ እንደማያጠያይቅ ግልጽ ነው። በዚህ ጽሑፍ አለመግባባትን በንግግር መፍታት ትናንት ምን መልክ እንደነበረው፤ ዛሬ ምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እና ነገ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ምን መሠራት እንዳለበት ተመላክቷል።

ትናንት

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ኤምሬትስ ፕሮፌሰሩ ሹመት ሲሻኝ ከእኛ በፊት የነበሩት አባቶቻችን ከግጭት ይልቅ መግባባት የተሻለ ዕድል እንደሚፈጥር ስለተገነዘቡ ፈጥረዋቸው የነበሩ የመግባቢያ ሀሳቦች እና ዘዴዎች እንደ ነበሯቸው ይገልጻሉ። ይሄ ባይሆን ኖሮ እንደ ማኅበረሰብ መቀጠልም አይቻልም ነበር የሚሉት ፕሮፌሰሩ ታሪክን ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት ብዙ ሰዎች በሥልጣን ጉዳይ ይፎካከራሉ እስከ መዋጋት ይደርሳሉ። በአካባቢ ልዩነቶችም ምክንያት ግጭቶች ይፈጠራሉ። ተሰሚነት ያላቸው ማኅበራዊ ልሂቃን ነገሮች ጎጂ ወደ ሆነ መጠፋፋት እንደሚያመራ ሲያዩ የተለያዩ ዘዴዎችን በመፍጠር አደጋውን ለማስቀረት ይጥራሉ። ሥልጣን ላይ ባሉ ኃይሎች መካከል የነበሩ አለመተማመኖች እንዲወገዱና የተሻለ ኅብረት እንዲፈጠር በነገሥታቱ፣ በራሶቹ እና በጎሳ መሪዎቹ መካከል የሚደረጉ ውይይቶች ነበሩ። የበለጠ ሁኔታው የጸና እንዲሆን በጋብቻ እና በመሳሰሉት ዝምድናዎች የከረረው ጉዳይ ላልቶ የተሻለ ሰላምና ማኅበራዊ መረጋጋት እንዲፈጠር ይደረግ ነበር ሲሊ(ጥቃቅን) አለመግባባቶች ወደ ግጭት እንዳያመሩ የሚሰሩ ሥራዎች እንደነበሩ ይገልጻሉ።

ፕሮፌሰር ሹመት እንደሚናገሩት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ቀደም ሲል ጀምሮ በተለይም የጦር መሳሪያውና ፉክክሩ ባየለበት 19ኛው ክፍለ ዘመን አለመግባባቶችን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ይደረጉ የነበሩ ጥረቶች በስፋት ታይተዋል። በተለያዩ አካባቢዎች ሠላምን ለማስፈን የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ዘዴዎች ነበሩ። ግጭቱ ሙሉ ለሙሉ ላይወገድ ይችላል ነገር ግን በተለያዩ ዘዴዎች አገሪቱን ስጋት ውስጥ ወደማይጥልበት ደረጃ ያወርዱት ነበር። በዚያ ዘመን አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች ምን ያህል ርቀት እንደሚጓዙ በንጉሠ ነገሥት አጼ ዮሐንስ እና በንጉስ ምንሊክ መካከል የነበረውን አለመግባባት መፍታት የተቻለበት መንገድ ጥሩ ማሳያ ነው።

ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሥ ሆነው ይገዙ ከነበሩበት ጊዜ በኋላ አጼ ዮሐንስ እና አጼምንሊክ የተባሉት ሁለቱም የአካባቢ ገዢዎች ብቻ ነበሩ። አጼ ዮሐንስ ትግራይ፣ ምንሊክ ደግሞ ሸዋን ያስተዳድሩ ነበር። በተለይ ምንሊክ ወደ ወሎ አካባቢ ወዳለው ክፍል እየሰፉ አጼ ዮሐንስ እንደሞቱ ብርቱ ኃይል መስርተው ነበር። አጼ ዮሐንስ ደግሞ እንግሊዞች ከመቅደላ ሲመለሱ ብዙ መሳሪያ ጥለውላቸው ሄደው ኃይለኛ ተፎካካሪ ሆነዋል። የዳግማዊ ቴዎድሮስን ሞት ተከትሎ ዘውዱን የበለጠ ጉልበት ያለው እንደሚወስደው የታወቀ ነበር።

ተክለጊዮርጊስ ከላስታ ተነስተው ‹‹ከሁሉም የበለጥኩኝ ነኝ›› ብለው ንጉሠ ነገሥትነቱን ወስደው ነበር። ነገር ግን ያን ንጉሠ ነገሥትነት(ንግስና) የሚያጸና ኃይል በእጃቸው ስላልነበረ ራስ ካሳ በቀላሉ ወስደውባቸዋል። አጼ ዮሐንስ ንጉሠ ነገሥት ብለው ራሳቸውን ሲሰይሙ ምንሊክን ማሸነፍ የሚችሉበት ኃይል አልነበራቸውም። ምንሊክም ዮሐንስን አሸንፈው ንጉሠ ነገሥት የሚሆኑበት ዕድል ጠባብ ነበር። በሁለቱ መካከል ከፍተኛ የሆነ ፉክክር ስለነበር እጅግ በጣም ደም አፋሳሽ የሆነ ግጭት ለመድረስ ተቃርቦ ነበር።

ይህን ችግር በጥበብና በዘዴ የፈቱት በነገስታቱ ዙሪያ የነበሩ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎችና ሽማግሌዎች ናቸው። በዚህ የሥልጣን ፉክክርና ግዛት መቀራመት ተጎጂው ሕዝቡ ስለሆነ የአንዳቸውን ሥልጣን ለማረጋገጥ ሲባል አገር መጥፋት የለበትም ተብሎ የሁለቱ ጥቅም የሚከበርበት ስምምነት ላይ መድረስ ተችሏል። ስምምነቱ እንዲጸና እና በመካከላቸው የጠነከረ መተማመን እንዲፈጠር የአጼ ዮሐንስ ልጅ አርአያ ስላሴ የንጉሥ ምንሊክን ልጅ ዘውዲቱን እንዲያገባ ተደረገ። ይህ ዘዴ ያስፈለገው የአባቶቻቸው ጸብ ዛሬን ብቻ መሰረት ያደረገ ባለመሆኑ ነው። ንግስናውን የማን ልጅ ነው የሚወርሰው የሚለውም ትልቅ ጉዳይ ነበር።

ፕሮፌሰር ሹመት ችግሮቻችን ሁሉ ይፈቱ የነበረው በውይይት እና በንግግር ብቻ አልነበረም በማለት በንግግር ሳይፈቱ ቀርተው ወደ ግጭት ያመሩ አለመግባባቶች እንደ ነበሩ ይጠቅሳሉ። ምንም እንኳን ግጭቶች ውስጥ የተገባባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም ቀደምቶቻችን በውይይትና ድርድር አለመግባባቶችን የመፍታት ባህላቸውን ጨርሰው አልጣሉትም። ይህ ባይሆን ኖሮ ኢትዮጵያ እንደ አገር አትቀጥልም ነበር። በግጭት ብቻ የሚያምን የልሂቅ ገዢ መደብ ያለባቸው አገሮች ቀጣይነት የላቸውም። በታሪክ ዕድሜያቸው ሊረዝም የቻሉ ሀገረ-መንግስቶች በአብዛኛው ውይይትን የግጭቶች መፍቻ አድርገው የተጠቀሙ ናቸው። ይህንን ባህል ያላዳበሩ አገራት ሁሉ ወድቀዋል ፈርሰዋል። ኢትዮጵያ ሳትፈርስ የቆየችው ይህ መሳሪያ በእጇ ስለነበረ እና ስለዳበረ ነው በማለት ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ልማድ ያላቸው ስልጡን ሕዝቦች እንደነበሩ ይገልጻሉ።

የተለያዩ ቋንቋዎችና ባህሎች ባሏቸው የተለያዩ አካባቢዎች ከማኅበረሰቡ ውስጥ የወጡ ያደጉና የገነኑ የሀሳብ መሪዎች እንደነበሩ የሚገልጹት ፕሮፌሰሩ፣ የመንግስት ሥልጣን በሌሎች እጅ ይሁን እንጂ እነዚህ አካላት በብልሃታቸው፣ በእውቃታቸው፣ በሽምግልናቸው እና በሃይማኖት መሪነታቸው ምክንያት በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነት እንደ ነበራቸው ያወሳሉ። አያይዘውም “እንዲህ ያሉ ሰዎች ሲናገሩ ሕዝብ ያደምጣቸዋል። እንዳለመታደል ሆኖ ደርግ ሲመጣ በመጀመሪያ ደረጃ የመታብን ለሕዝቡ ቅርብ በመሆናቸው ሕዝቡ ያዳምጣቸው የነበሩ አገርን የሚያረጋጉና ሕዝብን ከአደጋ ይጠብቁ የነበሩ አዋቂዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን እና ሽማግሌዎችን ነው። ደርግ እነዚህን ተደማጭነት ያላቸውን ሰዎች ‹አደሀሪያን› ብሎ ከመድረክ አወረዳቸው። በእነሱ ምትክ የተተኩት ለፍላፊ ካድሬዎች ነበሩ። ካድሬዎቹ ይሄ ነው የሚባል ከሕዝቡ የላቀ እይታ ስላልነበራቸውና ከሕዝቡ ጋር አብረው ያልበቀሉ ሀሳብንም የማያስተናግዱ በመሆናቸው ምክንያት ሕዝቡ ያለ አካባቢ መሪ እና የሀሳብ ሰዎች ብቻውን ቀረ” ሲሉ በቁጭት ይናገራሉ።

በመቀጠልም ደርግን የተካው ሕወሓት ይመራው የነበረው መንግስት ሆነ ብሎ የአገር ዕሴቶችን አውድሟል። በየብሔረሰቡ እና ኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉት ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ዕሴቶች እንዲዳከሙ አድርጎ አሁን የምናየው የጥላቻ፣ የክፍፍል እና ያለመተዛዘን ኢ-ሞራላዊ ስሜት እንዲኖር አድርጓል። ሙስና እና የአገልግሎት አሰጣጥ ብሉሽነትም ከእነዚህ አገራዊ ዕሴቶች መሸርሸር ጋር የሚገናኝ ነው የሚሉት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የሲቪልማኅበራት ጉዳዮች ኃላፊው ዶክተር አለሙ ስሜ ናቸው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር የወንጀል ሕግ፣ የሕዝብ ፖሊሲ እና የሕግ ፍልስፍና ተመራማሪው ዶክተር ስሜነህ ኪሮስ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ታሪክ የአገርን ህልውና የሚፈትኑ ከባድ ችግሮች ሲያጋጥሙ ተጻራሪ ኃይሎች ወደ ውይይትና ድርድር የሚገቡት ‹እኔ ወይ አንተ ማሸነፍ አለብን› ብለው እንዳልነበር ይገልጻሉ። ንግግራቸውን በምሳሌ ሲያስረዱ “አለመግባባቱ በንጉሠ ነገሥት እና በአካባቢ ንጉስ መካከል ከሆነ የሚመጡት ከየራሳቸው አካባቢ ስለሆነ አንተም የራስህን ያዝ እኔም የራሴን ልያዝ ነገር ግን አንተ እግዚአብሔር የቀባህ ንጉሥ ነህና እኔ ላንተ እገብራለሁ ተባብለው ተግባብተው፣ ተስማምተው ሠላም ያወርዳሉ። ይሄ ጥበባቸው ነው። ዳግማዊ ምንሊክ ድል ካደረጉ በኋላ ምህረት ያደርጉና የተዋጋቸውን ሰው መልሰው ይሾሙ ነበር” ይላሉ።

በመካከላቸው ምንም አይነት ልዩነት ቢኖር እንኳን የውጭ ወራሪ ሲመጣባቸው ተግባብተው አንድ ላይ ይሰሩ እንደ ነበር የሚገልጹት ዶክተር ስሜነ በእርግጥ በዚህ ረገድ በኩራት የምንገልጸው ታሪክ ብቻ አይደለም ያለን፣ ይላሉ። አጼ ቴዎድሮስን አሳልፈው የሰጡት አጼ ዮሐንስ መሆናቸውን፤ አጼ ዮሐንስም ምንሊክን በጠሩ ጊዜ ምንሊክ ሆነ ብለው ዘግይተው ከሽንፈት በኋላ መድረሳቸውን ይጠቅሳሉ። ነገር ግን ሌላ ሸምጋይ ሳይኖር እርስ በእርሳቸው ተነጋግረው ቤተክርስቲያን ጣልቃ እየገባች፤ ቀሳውስቱ እየረዱ ችግሮች ይፈቱ ነበር። በዚያ ዘመን እንዲህ ባለ መንገድ ችግሮች ይፈቱ የነበረው ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ አደረጃጀቶች በመኖራቸው እና መንግስት ሁልጊዜም ደካማ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ይገደድ ስለነበር መሆኑን ይጋልጻሉ።

በደብረ ማርቆስ የኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ ዶክተር አያናው ማሞ በኢትዮጵያ የሩቅ እና የቅርብ ጊዜ ታሪክ አለመግባባቶችን በሰከነ መንገድ በውይይት የመፍታት ባህል እንደነበረ ያወሳሉ። ተፈሪ መኮንን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከመባላቸው በፊት ከልጅ እያሱ ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው ነበር የሚሉት የታሪክ መምህሩ “አንቱ በተባሉ ሽማግሌዎች ጠመንጃቸውን መሬት ላይ አጋድመው እንዲራመዱ ተደርጎ ታርቀዋል። አለመግባባቶችን በንግግር በመፍታት የሚገኘው ድል በጦርነት ከሚገኘው በላይ ብዙ ትርፍ የሚያስገኝ ነው። በዚያ ዘመን የሚደረጉ ውይይቶች፣ ድርድሮችና እርቆች እውነተኛ ነበሩ” በማለት “ከታጠቡ አይቀር ከክንድ ከታረቁ አይቀር ከሆድ” ይባል የነበረበት ዘመን እንደነበር ይናገራሉ።

አያይዘውም የብሔራዊ እርቅ ጥያቄ በተበጣጠሰ መልኩም ቢሆን ድሮም ቢሆን የነበረ ነው። የኢትዮጵያ የእውቀት አደባባይ በዝምታ ተውጦ እጅግ ብዙዎቹ ምሁራን ከሕዝብ ተዋጽኦ ሲያፈገፍጉ ጥቂት የማይባሉት ደግሞ ከስርዓቱ ጋር በጥቅመኝነት የተቆራኙ እንደነበሩ አይካድም። ነገር ግን የቅርብ ጊዜውን እንኳን ብንመለከት ይቅርታ እና እርቅን በተመለከተ አጀንዳውን ይዘው አደባባይ የወጡ ብዙ ሰዎች ነበሩ። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማሪያም፣ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ፕሮፌሰር ላጲሶ ዴሌቦ፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ አቶ እንድሪስ ሙሀመድ፣ ልጅ ዳንኤል ጆቴ፣ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፣ አምባሳደር ዘውዴ ረታ፣ ወይዘሮ ማዕዛ አሻናፊ እና ሌሎችም ብዙ ለፍተዋል በማለት ኢትዮጵያውያን የቀደምቶቻቸውን ባህል እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይዘው ቆይተዋል ሲሉ ይሞግታሉ።

ዛሬ

የብልጽግና ፓርቲ አመራሩ ዶክተር አለሙ ባለፉት አራት አመታት በተጨባጭ በተግባር የታየው በየክልሉ ያሉ ጥሩ ጥሩ ዕሴቶች እንዲጎለብቱ፣ እንዲከበሩ፣ ወደ አደባባይ እንዲወጡ እና ዜጎችም በዚያ እንዲቀረጹ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ያብራራሉ። የሃይማኖት ተቋማትም ራሳቸውን እንዲያጠናክሩ፤ ገለልተኛ ሆነው የሃይማኖታቸው መርህ በሚያዛቸው መሰረት የውስጥ ችግራቸውን በራሳቸው እንዲፈቱ የለውጡ መንግስት ብዙ ሥራዎችን ሲሠራ እንደነበረ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚገባ እንደሚያውቀውም ዶክተር አለሙ ያወሳሉ። መጀመሪያ ራሱ በሁለት እግሩ የቆመ የእምነት ተቋም ሲኖር ነው ሃይማታዊ ዕሴቶች ወደ ምዕመናን ሊተላለፉ የሚችሉት በሚል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት መካከል የነበረውን ክፍፍል ፈትተን ወደ አንድ ለማምጣት ብዙ ርቀት ተጉዘናል፤ በእስልምና እና በሌሎች የሃይማኖት ተቋማትም መሰል ጥረቶች ተደርገዋል ይላሉ።

ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያ ብልጽግና የሚረጋገጠው ያሉንን መልካም ነገሮች እንደ እርሾ ተጠቅመን የሚቀሩንን ስንሠራ ነው ብሎ ያምናል። የሚመራበት የመደመር እሳቤም ለእነኚህ አገራዊ ዕሴቶች ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ነው። ኢትዮጵያ ወደፊት የምትራምደው በራሷ አቅም ባሏት ዕሴቶች ተመርኩዛ እንጂ ከውጪ በሚመጣ አስተሳሰብ አይደለም። ሕወሓት ‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ› ብሎ ተነስቶ አገራዊ ዕሴቶች እዲሸረሸሩ አድርጓል። ብልጽግና ግን ኢትዮጵያን የሚያበለጽገው በአገር በቀል እውቀትና ዕሴት ላይ ተመርኩዞ ነው። የፓርቲው መነሻና አቋም ይሄ በመሆኑ የሃይማኖት እና የባህል ተቋማት መጠናከር አለባቸው ብሎ እንደሚያምን ይገልጻሉ።

ኤምሬትስ ፕሮፌሰር ሹመት ደርግ ተደማጭነት ያላቸውን ሰዎች ካስወገደ በኋላ ባለው ዘመን የመጡት ሲጨንቀን የምንጠራቸው ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት መሪዎች ሕዝባዊ መሰረትና ስር ያላቸው አይደሉም ይላሉ። ቀደም ሲል ከነበረው ትርክት በመነሳት ልንጠቀምባቸው የምንጥር ነገር ግን አንዳንዶቹ የእህል ውሃ አበል እየተከፈላቸው ሌሎች ደግሞ መኪና እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች እየተሰጧቸው ቅብ ሆነው ያሉ ናቸው ሲሉም ይተቻሉ።

ፕሮፌሰሩ ዛሬ አለመግባባቶችን በውይይት የመፍታት ተግባር እጅግ በጣም አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን ይገልጻሉ። በአንድነት ከመሰባሰብ ይልቅ መበተኑ እየቀናን ሄዷል። መድረኩን የጨበጡት ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ኃይሎችምቢሆኑ አብዛኛውን ጊዜያቸውን እና ጥረታቸውን የሚያውሉት በሚከፋፍለን እና በሚለያዩን ጉዳዮች ላይ እንጂ አንድ ከሚያደርጉን ላይ አይደለም። ብዙ ማኅበረሰቡን የሚያደናግር ሀሳብ ተበትኗል። በዚህም ምክንያት ብዙ ኃይሎች የተለያዩ ጥቅሞችን እያገኙ ነው። ይሄ ጥቅም ደግሞ በአብዛኛው ከሌሎቹ ጋር ተጋርቼ አስፈጽመዋለሁ ሳይሆን ተፎካክሬ የተሻለ አገኛለው በሚል ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ባለፉት ሃምሳ እና ስልሳ አመታት ራሱን እያባዛ ሄዷል። ከፋፋዩ ክፍል የበለጠ ኃይል እያገኘ መሃሉን እየናደ በመምጣቱ በአብዛኛው የቆምንበት መሬትም እንዳይጸና ያደረግንበት ሁኔታ ተፈጥሯል በማለት በዚህ ምክንያት ብዙ ጊዜ መባከኑን እና ያመለጡ እድሎችም መኖራቸውን ይገልጻሉ።

እንደ እርሳቸው ገለጻ የተከተልነው የፖለቲካ አቅጣጫ የተሻለ ዕድል የሰጣቸው ቡድኖች አሉ። በሌላ መንገድ መታወቅና መከበር የማይችሉ ሰዎች ሕዝብን ወደ ጠብ የሚነዱ ሀሳቦችን ማጠንጠን የተሻለ ዕድል እየሰጣቸው ነው። ስሜታዊ የሆኑ፣ ሕዝቡን ወደ አንድነት ሳይሆን ወደ ጠብ የሚነዱ ሀሳቦችን በማጠንጠን እንጀራቸውን እያገኙ ነው። አንድ ጉዳይ ደግሞ እንጀራ ከሆነ ይገፋበታል እያደር እየበረታ ይሄዳል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በዚህ ሰዓት ቆም ብሎ መገንዘብ ያለበት በዚህ አቅጣጫ ምን ያህል ልንቀጥል እንችላለን? ይሄ ለሁሉም ስጋት አይደለም ወይ? ይህንን አይነት ውድድርና ግብግብ በአሸናፊነት ሊወጣ የሚችል የለም። ይሄ ከስግብግብነት፣ ግለኝነትና የዋህነት የሚመነጭ ነው እንጂ በጉዞ መጨረሻ ላይ ሁሉም ወደ ገደል ነው የሚደርሰው። መለስ ብሎ ሁኔታውን በመገምገም ወደ መሃል ወደሚመጣ ሀሳብ መሰባሰብ ያስፈልጋል።

የሕግ ምሁሩ ዶክተር ስሜነህ አሁን ባለንበት ዘመን ባህላዊ አደረጃጀቶቹ በመፍረሳቸው ችግሮችንን በውይይት ለመፍታት ተቸግረናል ይላሉ። ሰሞኑን ትንሽ እያቆጠቆጡ ካልመጡ በቀር ቀደም ሲል አገሪቱን ያስተዳድር በነበረው ትህነግ ታዋቂ ሰዎች እየታገቱ ከየትኛውም አካባቢ ለሽምግልና የሚጠራ ሰው እንዳይኖር ተደርጓል ሲሉም ይከሳሉ። “ሃይማኖታዊ ስርዓቶች በነጻነት እንዳይኖሩ በውስጣቸው የተሰራባቸውን ነገር ሁሉም ሰው ያውቀዋል። እነዚህ ሁለቱ ተቋማት ሲዳከሙ ሕዝብ የሚተማመንበት ሦስተኛው እና የመጨረሻው ተቋም መንግስት ነው። የመንግስት ተቋም ደግሞ ብሔርተኛ ሆነ። የሚያስረው የሚፈታው፣ የሚዳኘው ወይም በጀት የሚመድበው ሰው ወደ ራሱ ብሔር ማዘምበል ያዘ። ደረጃ በደረጃ ዕሴቶቻችን እየተናዱ መጥተው መተማመን የማንችልበት ደረጃ ደርሰናል” ይላሉ።

የሃይማኖት ተቋማቱ እንዲዳከሙ መደረጉን የሚገልጹት ዶክተር ስሜነህ ‹‹አሁን እንደምናየው በየአካባቢው ወንበር እና ጠረጴዛ መወራወር ተጀምሯል። መንግስት ለእነዚህ የሃይማኖት ተቋማት ይህንን ዕድል እና ዕውቅና አልሰጠም። እንደውም እጁን እያስገባ እየረበሻቸው ነው ያለው። መንግስት በቀጥታ የሃይማኖት ተቋማቱን እየተጋፋ ነው ያለው።” ሲሉ ይወቅሳሉ። አክለውም እነዚህ ተቋማት ከሌሉ በቀጥታ ችግራችንን ሊፈታ የሚችለው መንግስት ነው የሚሆነው። የሕዝባችን ቁጥር በመጨመሩና ከተሜነት እየተስፋፋ በመምጣቱ በሃይማኖት፣ በቋንቋ እና በዘር የማንግባባ ብዙ ሰዎች አለን። ስለዚህ መሀል ላይ መንግስት ብርቱ ኃላፊነት አለበት ማለት ነው። ነገር ግን መንግስት ለዚያ በሚበቃ አቋም ላይ አይደለም ያለው አሁን። ሁሉ ነገር በጎሳና በብሔር በሚሰራበት ሁኔታ መንግስት የትኛው ቦታ ላይ ችግር ሊፈታ እንደሚችል እኔ አላውቅም በማለት ማናቸውንም ጉዳዮች በገለልተኝነት አይቶ ሊወስን ይችላል ብሎ ለማመን መቸገራቸውን ይገልጻሉ።

ዶክተር ስሜነህ እንደሚናገሩት መንግስት እነዚህን ተቋማት በሚገባ መጠቀም ይችል ነበር። በየአካባቢው ያሉ ሽማግሌዎች የአካባቢውን ወጣቶች መምከር፣ መገሰጽ እና ስርዓት ማስያዝ ይችላሉ። እነዚያን ሽማግሌዎች ሰብስቦ አንዱን ጎሳ ከሌላው ጎሳ ማስታረቅ ይቻላል። ከፍ ብሎ ደግሞ አንዱን ብሔር ከሌላው ብሔር ማነጋገር ይችላል። ነገር ግን እነዚህን ተቋማት አላጠናከርናቸውም ዛሬም እንደፈረሱ ነው ያሉት።

የታሪክ መምህሩ ዶክተር አያኖ ሁለቱ ተቋማት መዳከማቸው ላይ ቢስማሙ ጨርሶ ፈርሰዋል ብለው አያምኑም፤ ዛሬም እርሾ አለ ባይ ናቸው። “ዛሬም የአገር ሽማግሌዎች ብዙ ነገር ሲሰሩ እያየን ነው። በቅርብ ጊዜ የጋሞ አባቶች የቡራዩ ክስተትን ተከትሎ በቁጣ የተነሱ ወጣቶችን እርጥብ ሳር ይዘው ተንበርክከው ከግጭት እንደመለሱት ትልቅ ተቀባይነት ያላቸው ጥበበኞች ናቸው። በጌዴኦ እና ጉጂ ኦሮሞ መካከል ጦርነት ከመካሄዱ በፊት እናቶች ራቁታቸውን የቆዳ ልብስ ለብሰው ወንዶችም እንዲሁ ባህላዊ ልብስ ለብሰው ከሁለቱም ወገን ተወጣጥተው ያደረጉት ጥረት አለ” በማለት ተዳከሙ እንጂ ሙሉ ለሙሉ ከጨዋታ ውጭ አልሆኑም ብለው ይከራከራሉ።

ብሔራዊ መግባባቱ እንዲሳካ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ ከሚችሉ ተቋማት መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሱት የሃይማኖት ተቋማት እንደሆኑ የሚናገሩት ዶክተሩ ተቋማቱ አሁን ባላቸው ቁመና በሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ስም ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሥራ መሳካት በቀጥታ ከሚያደርጉት አስተዋጽኦ በተጨማሪ ሂደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ በቤተ ክርስቲያናት ምህላ በመስጅዶች ደግሞ ቆነት ወይም ልዩ ጸሎቶች እንዲካሄዱ ቢያደርግ ጥሩ ውጤት እንዲገኝ ያግዛሉ ብለው እንደሚያምኑ ይገልጻሉ።

ነገ

በብዙ አካባቢዎች ሠላም ለማስፈን እና እርቅ ለማውረድ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የሚደናቀፉት በእውነተኛ ተዋንያን ስለማይመሩ እንደሆነ የሚናገሩት ፕሮፌሰር ሹመት፣ እውነተኛ የሆኑ የሃይማኖት አባቶችና ሽማግሌዎችን ከፈጠርን አለመግባባቶችን እና ግጭቶችን ቀደም ሲል በነበረን ባህል መሰረት እየፈታን ነጋችንን ብሩህ ማድረግ እንችላለን ይላሉ።

እርሳቸው እንደሚገልጹት ሕዝቡ ብሔራዊ ምክክሩን ቁምነገር ብሎ እንዲይዘው የአደጋውን መጠን መገንዘብ አለበት። በተያያዝነው መንገድ ከቀጠልን አንድ ወይም ሁለት ክፍል ሳይሆን የሚጎዳው ሁሉም ጠፊ ነው። ሰዎች ስለሆንን ማሰብ እንችላለን እና ይህንን ስህተታችንን እና ሞኝነታችንን ቆም ብለን እንደገና ተመልክተን የአቅጣጫ ለውጥ ልናደርግ ይገባል። የሰው አእምሮ ካለፈው ተምሮ የተሻለ ወደፊትን ማምጣት ስለሚችል አገራዊ ምክክሩ በቁምነገር ከተወሰደ ወደዚያ አቅጣጫ ሊመራን ይችላል። ነገር ግን ይህን ለማድረግ የአብዛኛው ሰው መንቃትና በሂደቱ መሳተፍ ያስፈልጋል።

ታሪክ ጥቅም አለው ከተባለ ከእኛ በፊት የተፈጸሙ ነገሮችን አስተውለን ከዚያ ተምረን ስህተቶች እንዳይደገሙ፤ ውጤት ያስገኙ መንገዶች ካሉ ደግሞ የሂደታችን አካል በማድረግ አባቶቻችን አደጋዎችን ቀድመው እንዳስወገዱት ሁሉ እኛም መከራው ሳይደርስብን ቀደም ብለን በማወቅ የቀሰምነውን ዘዴ በመጠቀም ከአደጋዎች እንድናመልጥ ለማድረግ ነው። ፕሮፌሰሩ “ከፍተኛውን ትምህርት የምንወስደው በሀሳብ በተለያየንባቸው ዘመኖች ምን ያህል ጥፋት ደረሰ እንዲሁም ስንተባበር ደግሞ ምን ያህል ስኬት አስመዘገብን ከሚለው ነው። ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ በቆሙባቸው ወቅቶች ሁሉ በጋራ የሚኮሩባቸውን ስኬቶች አስመዝግበዋል።ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ በተሰለፉ ጊዜ አንዣቦባቸው የነበረውን ጥፋት ማስወገድ ችለዋል። በተከፋፈሉበት ጊዜ ደግሞ ለከፍተኛ እልቂት ተዳርገዋል። ይህም እጅግ በጣም ወደ ኋላ መልሷቸዋል፤ በብዙ ዜጎቻቸው ላይ ከፍተኛ ሰቆቃ ደርሷል” ይላሉ። ከትናንት በመማር ዛሬ ላይ የማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድ ነገን ከተመሳሳይ አዙሪት መታደግ እንደሚገባ ያሳስባሉ።

ፕሮፌሰር ሹመት እንደሚናገሩት ወደ ኋላ መለስ ብለን ብንመለከት አብዛኛው የአውሮፓ አገራት ኢትዮጵያ ከነበረችበት የተለየ ሁኔታ ውስጥ አልነበሩም። ኅብረቱ ሙሉ ለሙሉ የሰመረም የሠለጠነም አልነበረም። ያሠለጠኑትና ያዘመኑት ሥራዬ ብለው በ19ኛው ክፈለ ዘመን በሠሯቸው የፓለቲካ ሥራዎች ነው። በተለይ ተሳካላቸው የሚባሉ የአውሮፓ ነገሥታት ከዘመናቸው በፊት የነበሩትን ድክመቶች በማረም ሕዝቡ ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲመለከት ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ፕሮጀክት ቀይሰው ያንን ተፈጻሚ በማድረግ ብዙ ቋንቋ ተናጋሪ እና ብዙ ሃሳብ አቀንቃኝ የነበረውን ማኅበረሰብ እንደ ወንድም እና እንደ አንድ ዜጋ እንዲተያይ ነው ያደረጉት። በዓለም ላይ ተሰርቶአልቆ ቁልጭ ብሎ የተፈጠረ መንግስት የለም። በአንዲት ትንሽ ቦታ በጥቂት ሊኂቃን የተመሰረተ ሀሳብ እየሰፋና ይዘቱ እየተለወጠ ነው አገረ- መንግስት የሚገነባው። ከጥቂት ቦታ በመነሳት እየሰፋ ሄዶ አገር መፈጠሩ ዓለም አቀፍ እውነታ ነው። የትም የነበረ ሂደት ነው። ከትልቅ ሊጀምር አይችልም አልቆ ተሰርቶ ሊከሰት አይችልም። ትንሽ ከሆነ ጠባብ ቦታ ተነስቶ እየሰፋ ሄዶ ነው አገር የሚሆነው።

ኢትዮጵያውያን በተለይ በዘመናዊው ጊዜ ሕዝቡን ወደ አንድ ወደ መሃል በማምጣት የሰነፍንባቸው ጊዜያት እንደነበሩ የሚስታውሱት ፕሮፌሰር ሹመት “ሕዝቡ እርካታ እንዲያገኝ አስፈላጊ የሆኑ የፖለቲካ ተሃድሶዎችን በወቅቱ አለማድረግ እንዲሁም አንድ እይታ እንዲኖረውና ባለፈው ታሪኩ እየተናቆረ ከሚኖር ይልቅ ወደፊት እየተመለከተ አንድ የሚያደርጉት እና የወደፊት እጣ ፈንታውን የሚወስኑለት ሀሳቦች እንዲጋራ ማድረግ ላይ ትልቅ ሥራ መሠራት አለበት። ይህንን አለማድረጋችን አሁን ለምናያቸው መናቆሮች አንደኛው ምክንያት ነው። ይሄንን ሥራ ጎን ለጎን ማካሄድ ብሔራዊ ምክክሩ አመርቂ ውጤት እንዲያስመዘግብ ይረዳል” ሲሉ ይመክራሉ።

ማንኛውንም ማስተካከያ ለማድረግ ሊረፍድ አይችልም የሚሉት ደግሞ የሕግ ምሁሩ ዶክተር ስሜነህ ናቸው። በአገር እና በሕዝብ ተስፋ አይቆረጥም። ነገር ግን ከፈጠርነው ችግር አንጻር በብርቱ ትጋት መሥራት ይኖርብናል። በመጀመሪያ ደረጃ መንግስት ገለልተኛ መሆኑን ማሳየት አለበት። ከሁሉቱ ተቋማት እጁን ማውጣት አለበት። እነዚህ ተቋማት ነጻ ከሆኑ ራሳቸውን ችለው በሁለት እግራቸው መቆም ይችላሉ ብዬ አምናለሁ ይላሉ።

አያይዘውም “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሁለት እግሯ ለመቆም የመንግስት ድጋፍ አያስፈልጋትም። መንግስት እጁን ከሰበሰበ ቤተክርስቲያኗ ሠላም ትሆናለች። በቤተ ክርስቲያኗ ሥር ያለው ሕዝብ በሙሉ በያለበት አካባቢ ሠላም ይሆናል። የእስልምና ሃይማኖትም ጣልቃ ገብነቱ ከቀረለት በሁለት እግሩ ይቆማል። መስጊድ ባለበት ሁሉ ሠላም ይሆናል። ምክንያቱም ሕዝባችን አማኝ ነው። ቤተ ክርስቲያን ሳይሄድ መስጊድ ሳይሰግድ የሚኖር ሰው የለም። አንድ ጊዜ ሄዶ መልካም ነገር ሰምቶ ይመጣል። የሚሰማው ነገርም መንግስት ላይ የሚደርስ ተቃውሞ እና መንግስት መራሽ ሸፍጥ አይሆንም። ከእነዚህ ተቋማት መንግስት እጁን ከሰበሰበ ራሳቸውን ችለው ቆመው ኃላፊነታቸውን መወጣት ይችላሉ። ተቋማቱ የሠላም ተቋማት በመሆናቸው በየአካባቢያቸው ሠላም ማስፈን ይችላሉ” በማለት የችግሩ ፈጣሪም ሆነ መፍትሔው መንግስት መሆኑን ይገልጻሉ።

የሕግ ምሁሩ ዶክተር ስሜነህ የሰነዘሩትን ወቀሳ የሚቃወሙት ዶክተር አለሙ “አሁን የሚቀርቡ ክሶች በማስረጃ የሚረጋገጡ አይደሉም። ከዚህ ቀደም የነበረው አሰራር ይታወቃል። በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በማን ትዕዛዝ አጀንዳ እንደሚቀረጽ እና ውሳኔዎች አስቀድመው ይተላለፉ እንደነበር ይታወቃል። ከአራት አመታ በፊት በሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ ቀጥተኛ የፓርቲ እና የመንግስት ተሳትፎ ነበር። ይሄ አሁን ሙሉ ለሙሉ የለም። ተቋማቱን መደገፍ በሚያስፈልግበት ቦታ ለመደገፍ ከመጣር ውጭ ማንኛውም ሃይማኖት ተቋም ውስጥ የመንግስትም ሆነ የፓርቲያችን እጅ የለበትም።” በማለት በፓርቲያቸውና በመንግስት ላይ የሚቀርበው ክስ መሰረተ ቢስ መሆኑን ያስረዳሉ።

አካታች አገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያውያን ሁሉ አጀንዳ መሆኑን የሚገልጹት ዶክተር አለሙ፣ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲናፍቁት፣ ሲመኙት እና ሲፈልጉት የነበረ ጉዳይ ነው። መንግስት ሁኔታዎችን ያመቻቻል እንጂ አጀንዳው ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የመንግስት ሰራተኛው፣ አርሶ አደሩ፣ ነጋዴው ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት እና ሌሎች ሲቪክ ማህበራት ሁሉ ይመለከታቸዋል። በእኛ በኩል እንደ ፓርቲ በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እንዲሁም እንደ መንግስት እንቅፋቶችን በማስወገድ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የሚጠበቅብንን እንወጣለን። በማለት እያንዳንዱ አካል የሀገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል ብሎ የሚጠበቅበትብ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ ያቀርባሉ።

ዶክተር አያኖ በበኩላቸው ባለፈ ታሪክ እየተነታረክን ለባሰ ችግር መዳረግ የለብንም። ያለፈ ታሪክ ሊያባላን አይገባም። ያደረ ቂም የነገውን ትውልድ ችግር ውስጥ ሊከተው አይገባም። በዘመን ተሻጋሪው ይቅር የመባባል ዕሴታችን ልንፈታው ይገባል። አሁን ያለንበት ዘመን ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በተለየ ተቀራርበን ተናጋግረን አብረን የምንቆምበት ነው። ጸብ ውስጥ ከርመን ለጠላቶቻችን ምቹ ሁኔታ መፍጠር የለብንም። ችግር አለ የሚሉ አካላት ሁሉ ጉዳያቸውን ወደ ጠረጴዛ አምጥተው በንግግር ለመፍታት መዘጋጀት አለባቸው። በብሔራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ አካላት በቀናነት ወደ መድረኩ መምጣት ይጠበቅባቸዋል። እርቅ እርሳው ልርሳው ተወው ልተወው በሚል አይጸናም በውስጡ ፍትህ ሊኖር ይገባል ሲሉ ይመክራሉ።

ተስፋ ፈሩ

ዘመን መጽሔት ሐምሌ 2014 ዓ.ም

Recommended For You