አገራችን አሁን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት በአንድ በኩል በውስጥና በውጭ ኃይሎች ሴራ አገርን የማተራመስና ብሎም የማፍረስ ጥረት ከመቼውም ጊዜ በላይ የታየበት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከድህነትና ኋላ ቀርነት ጋር ከፍተኛ ግብግብ ውስጥ የተገባበት ነው። በዚህ ወቅት አገርን መታደግ የሚቻለው በአንድነት በመቆም ብቻ ነው። አገሪቷን ከወቅታዊ ፈተናዎች መታደግ እና የበለጸገችና ለዜጎቿ ምቹ የሆነች አገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ከአድዋ ድል የምንማረው ሌላኛው ገጽታ ነው።
በትግራይ ክልል የተካሄደውን ሕግ የማስከበር ዘመቻ ተከትሎ አጋጣሚውን በመጠቀም እጅን ለመጠምዘዝ የሚሞክሩ አካላት የመኖራቸውን ያህል ለጥፋት የተሰለፈ ገንዘቡንና ጊዜውን በደንብ አስልቶ ተደራጅቶ የሚሰራ ኃይል ስለመኖሩም የማይካድ እውነታ ነው። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በብዙ ፈተናዎች ተፈትና ያለፈች፣ በአገራቸው ጉዳይ የማይደራደሩ ቆራጥ ልጆች ያላት፣ ያልተገባ ጫናን ጥቃትን መድሎን በዘመናት መካከል የተሻገረች ሀገር በመሆኗ ፈጽሞ እንደማትፈርስ መዘንጋት የለበትም። አበቃላት፣ ወደቀች፣ ተበተነች ስትባል የማትወድቅ ሀገር መሆኗን በተደጋጋሚ አሳይታለችና።
አገሪቷ ላለፉት አራት ዓመታት ያህል በለውጥ ሂደት ውስጥ ነች። ለውጡ ያመጣውን ነፃነት አንዳንዶች ወደ ሥርዓት አልበኝነት ቀይረውት ሠላምና መረጋጋት ሲያሳጡን ቆይተዋል። መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በወሰዳቸው እርምጃዎች ሕግና ሥርዓትን ብቻ ሳይሆን የአገር ህልውናን ማቆየት እንደተቻለም ይታወቃል።
በየጊዜው እዚህም እዚያም በሚለኮሱ ብሔርና ማንነት ላይ ያተኮሩ ጥቃቶች የጋራ አገር የሌለን እስኪመስለን ድረስ ቆሽታችንን አድብነውት ለዜጎቿ የማትመች አገር ባለቤት መሆን ሳይሆን ኢትዮጵያ የምትባል አገር ዜጎች መሆናችንን እንድንጠራጠር አድርጎን ነበር።
አሁን የተጋረጡብን ችግሮች ልንፈታ የምንችለው ስንደማመጥና አንድ ሆነን ስንቆም ብቻ ነው። አለበለዚያ የሚገጥሙን ማናቸውም ፈተናዎች የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ሊያንበረክኩን እንደሚችሉ ግልጽ ነው። “ካልተደራጀ ትልቅ ሀገር የተደራጀች ትንሽ መንደር ትልቅ ስራ ትሰራለች” እንደሚባለው ችግሮቻችንን ለመወጣት በአንድነት አብሮ መቆም ምን ያህል ትርጉም እንዳለው የአድዋ ድል ህያው ማሳያ ነው።
ኢትዮጵያ ዜጎቿ በአንድነት የሰሯት፣ አንድነታቸውን ያስመሰከሩባት፣ በጥረታቸው ነፃነቷን ጠብቀው ለትውልዱ ያቆዩዋት አገር ነች። አድዋ የአባቶችን ታሪክ ተገንዝቦ፤ ያወረሱንን መልካም ገጸ በረከት ማስቀጠልና ለቀጣዩ ማስተላለፍ የሚችል ትውልድ መሆን እንደሚገባን ያስታውሰናል። የአድዋ እና የማይጨው ድል ስኬታማ የሆኑት በመላ ኢትዮጵያውያን የአንድነት መንፈስ በመሆኑ አሁንም ሆነ ወደፊት የአገራችንን እድገትና ብልጽግና የምናረጋግጠው በአንድ ላይ በመቆም ብቻ ነው።