“የጋራ መግባባት” የሚለውን ጽንሰ-ሃሳብ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በቀላሉና ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ምንነቱን የተገነዘበው አይመስልም። ቃሉ ለጆሯችን እንግዳ አይደለም፣ የተለመደና ሁል ጊዜ የምንሰማው ጉዳይ ነው። ሁላችንም ተመሳሳይ በሆነ ደረጃ ማን፣ ከማን ጋር እና በምን ጉዳይ ይግባባል? የሚለውን ግን በውል አልተረዳነውም፤ ወይም ደግሞ ተረድተነው ተግባራዊ ማድረግ አቅቶናል። ለዚህም ነው ዛሬ ላይ በማህበረሰቡ መካከል የሃሳብ ልዩነቶች እየተፈጠሩ እዚህም እዚያም በተለያየ ደረጃ ግጭቶች ሲከሰቱ የምናስተውለው።
ይሁን እንጂ “የጋራ መግባባት” ማለት እንደዜጋ ሁላችንን በሚመለከቱን አገራዊ አጀንዳዎች፣ ጉዳታቸውም ሆነ ጥቅማቸው እንደ ማህበረሰብ ወይም እንደ ህዝብ በሚመለከቱን የጋራ ጉዳዮቻችን ዙሪያ፣ ትናንሽ ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን በመተው የጋራ ስምምነት በመፍጠር፣ ለአገር ዕድገትና ልማት ስኬት አንድነታችንን በማጠናከር በጋራ መቆም ማለት መሆኑን አብዛኛው ሰው ይስማማበታል። በመሆኑም የጋራ መግባባት ስንል በማህበረሰቡ መካከል የሚፈጠር የሃሳብ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በጋራ ጉዳዮቻችን ላይ እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ መሰረተ-ልማት፣ ሠላም፣ የአገር ሉአላዊነት፣ ወዘተ የመሳሰሉ የሁላችንን በጎ ተሳትፎና ድጋፍ የሚጠይቁ መሰረታዊ አጀንዳዎቻችን ላይ የግል ልዩነታችንን አጥብበን ለውጤታማነታቸው መተባበር መቻል ማለት ነው። በጋራ ራዕይ፣ ግብ፣ መርህ እና በአጠቃላይም አገርን በማስቀጠል አጀንዳ ላይ የጋራ አመለካከት መያዝ ነው።
የጋራ መግባባት በመፍጠር ሂደት የትኩረት አቅጣጫን አስፍቶ ማየት ተገቢ መሆኑን በሚመለከት ኮሎኔል አስጨናቂ ገ/ጻድቅ በሆርን ኦፍ አፍሪካ ድረ-ገጽ ኖቬምበር 24/2017 ባሰፈሩት ጽሑፍ “እኔ መግባባት እያልኩ ያለሁት ፖለቲከኞች ስለሚያወሩት መግባባት ሳይሆን እንደ ተራ ዜጋ የእርስ በርስ መደማመጥንና መስማማት አለመቻላችንን ለመግለጽ ፈልጌ ነው… አነሳሴም ቢያንስ አሁን በምንገኝበት አደገኛ ሁኔታ ምክንያት ትንሽ ደንገጥ ብለን ለአገራችን ስንል ተቀራርበን በመነጋገር መስማማት እንኳ ባንችል ቢያንስ ከነልዩነታችንም ቢሆን በሰላም የምንኖርበትን መንገድ እንድንፈልግ ለማሳሰብ ነው“ በማለት የጋራ መግባባትን ከከፍተኛ የማህበረሰቡ መዋቅር ወይም ከፖለቲካ ፓርቲዎች በዘለለ በቤተሰብ፣ በሰፈርና በአካባቢም ተግባራዊ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል። በዚህ ርዕሰ- ጉዳይ ዙሪያ በተለይም በጋራ መግባባት ምንነት፣ በጉዳዩ ማን፣ ምን ማከናወን እንደሚገባው በዘርፉ የተሰማሩ ምሁራኖችን ሃሳብ ለመዳሰስ ጥረት አድርገናል።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የጆርናሊዝምና ኮሙዩኒኬሽን መምህር እና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል አስተባባሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ዓለማየሁ እንደሚናገሩት፣ አገራዊ የጋራ መግባባትን አስመልክቶ ልዩነት ተፈጥሯዊ ባህርይ እንዳለውና የሰው ልጅም የተለያየ አፈጣጠር ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አስተሳሰቡም ሆነ አመለካከቱ የተለያየ ሊሆን እንደሚችል በአግባቡ መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። ይህን ተፈጥራዊ ልዩነት ደግሞ ከመረዳትም አልፎ በበጎ መንገድ መመልከት እና ማክበር አብሮ በመኖር ሂደት የግድ ነው ይላሉ። እንደ አቶ ተስፋየ አገላለጽ፣ እነዚህ ልዩነቶች ግን በማህበረሰቡ ውስጥ በሚያከናውነው መስተጋብር ከርረው በአብሮነቱ ላይ ችግር እንዳያመጡበት መጠንቀቅ ይገባዋል። በተለይም ማህበረሰቡ የቆየ ሠላማዊ አንድነቱን ጠብቆ ለማቆየትና ለጋራ የአገር ሠላም መስፈን ሲል ልዩነቱን ማስወገድ አለበት። ካልሆነ ደግሞ ሰው በመሆኑ በሚጋራው እና የጋራ በሚያደርጉት በሰላም፣ በጤናና በፍቅር የመኖር፣ ከፍ ሲልም በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮቹ ዙሪያ ትኩረት ሊሰጥ የግድ ነው። የተረጋጋች አገርን በማሰብ፣ የግል ልዩነቱን ወደ ጎን በማድረግና በተቻለ መጠን አጥብቦ ለውጤታማነቱ አንድ ላይ ከቆመ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ይቻላል።
ዶክተር ተሻገር ሽፈራው ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ አገራዊ መግባባት ማለት መሰረታዊ በሆኑ የልዩነት ነጥቦች ላይ በመነጋገር የራስን መረዳት ከሌላው ጋር በማነጻጸር የጋራ ሃሳብ ላይ መድረስ ማለት እንደሆነ ይገልጻሉ። በመግባባት ሂደት ግን አንድ አይነት ሃሳብ ይኖራል ማለት ሳይሆን የሌሎችን የልዩነት ሃሳብ ተቀብሎ በሚያስማማ ጉዳይ ላይ በጋራ መቆም ማለት መሆኑን ይገልጻሉ።
የጋራ መግባባትን በምሳሌ ሲያስረዱ፣ ሁለት ሰዎች አንደኛው ከገደሉ ጫፍ ላይ ቆሞ፣ ሌላኛው ደግሞ ከገደሉ ስር ሆኖ፣ መንገዱን አንዱ ቁልቁለት ነው ሲል ሌላው መንገዱ አቀበት ነው ቢል፣ መንገዱን የተመለከቱትና የገለጹት ከየራሳቸው እይታ አንጻር በመሆኑ ነገሩ እውነት ቢሆንም ልዩነቱ የመጣው ግን ሁሉም የየግላቸውን ሃሳብ በማራመድ አንዱ በሌላው ቦታ ላይ ቆሞ ሁኔታውን ለመረዳት ባለመሞከሩ ነው ይላሉ።
በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ስትኖር እና ሀገረ- መንግስት ስታስብ በውስጡ መንግስት፣ ህዝብ፣ ድንበር እና ወሰን ከዚያም ሉኣላዊነት የመሳሰሉ ጉዳዮችን ማሰብ የግድ ይላል። በዚህች ሉኣላዊ በሆነች አገር ውስጥ ደግሞ ሰፊ ህዝብ በጋራ ይኖራል። በጋራ አገር ውስጥ ሲኖርም እንደ ግለሰብና ቤተሰብ በየሁሉም ቤት ግላዊ የአኗኗር ዘዴና የሀብት አጠቃቀም መኖሩ የግድ ይሆናል። ለተለያዩ ነገሮችም የአስተሳሳብ እና አመለካከት ልዩነት ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል። በዚህ በተለያየ ማህበረሰብ ውስጥም በፖለቲካ፣ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በባህል፣ በወግ፣ በመሳሰሉት ጉዳዮች በጣም የተለያዩ ማንነቶች ይስተናገዳሉ። እንደ ጋራ አገር ሲቆምና የጋራ መግባባት ሲታሰብ ግን የአንድን አገር የጋራ ጥቅሞች የሚወስኑ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ሊኖር የሚችለው አተያይ ተቀራራቢ እና ተመሳሳይ ሊሆን ይገባል። ሁሉንም የሚያግባቡ ገዥ ሃሳቦች እንዲኖሩ የሚደረግበት ሂደትም የጋራ መግባባት ነው የሚሉት በወሎ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ክፍል መምህር የሆኑት አቶ እንግዳወርቅ ታደሠ ናቸው።
አገራዊ የጋራ መግባባትን አስመልክቶ በአገራችን በተለይም ከ1983 ዓ.ም ለውጥ ወዲህ ፖለቲካው እንደ ብሄር አስተዳደርም፣ እንደ ፖለቲካ አወቃቀርም ተደርጎ ሲኖርበት የቆየ በመሆኑ፣ በዚህ ሂደት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በውዴታም ሆነ በግዴታ ካለፈውም ሆነ ከነበረው ስርዓት ጋር ማህበረሰቡ ጠላትነትንና ወዳጅነትን እንዲፈጥር አድርጎት ቆይቷል የሚሉት አቶ ተስፋዬ፣ ይህ አስተሳሰብ ደግሞ ቀስ በቀስ ከፖለቲከኞች መንደር ወርዶ በማህበረሰቡ ውስጥም የእርስ በእርስ የመገፋፋት፣ የመጠላላት እና የግጭት ፖለቲካን ፈጥሮበት ቆይቷል። የፖለቲካ ጥላቻው ደግሞ የህብረተሰቡን የኖረ ሰላማዊ አብሮነት ረብሾታል። ይባስ ብሎ በወቅቱ በነበሩ የለውጥ ፖለቲካ አራማጆች አማካኝነት ኢፍትሃዊ አስተዳደርና አደረጃጀት እየተስፋፋ ከመምጣቱ በተጨማሪ በተለያየ ሁኔታ የሚነሱ የህዝብ ፖለቲካዊም ሆኑ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች በበቂ ሁኔታ ሊመለሱ አልቻሉም። ስለሆነም ችግሮቹ መስመር እየለቀቁ በመምጣታቸው ምክንያት ህብረተሰቡ ለከፍተኛ ችግር መጋለጡን ያስረዳሉ።
በጋራ መግባባት ተግባራት ዙሪያ የሚስተዋለው ችግር የጉዳዩን አስፈላጊነትና ጥቅሙን ህብረተሰቡ በአግባቡ ሊገነዘበው አለመቻሉ ነው። በዚህም ምክንያት በጉዳዩ ዙሪያ በማህበረሰቡ መካከል የተለያዩ ክርክሮችና ንትርኮች እየተስተዋሉ መጥተዋል። በተለይም አንዳንዱ የአገራችን ፖለቲካ ከቋንቋ እና ከባህል ጋር ተያይዞ የብሄር ተጽዕኖ የሚስተዋልበት በመሆኑ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል። በመሆኑም ዜጋው ከዚህ ችግር ነጻ ሆኖ በሰላም የሚኖርባት አገር ልትሆን ይገባል በማለት ሰላማዊ ትግሉን በአማራጭነት የተቀላቀለ የፖለቲካ ፓርቲ አለ። በዚህ ሰላማዊ ትግልም አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ሊፈጠር ይችላል ብሎ ያምናል። ስለሆነም በጋራ መግባባቱ ሂደት አገራዊ ችግሩ በሰላም ይፈታል ብለው የሚያስቡ አካላት መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ እንግዳወርቅ፣ ይሁን እንጂ የጋራ መግባባት ሂደቱ በህግ መጠየቅ የሚኖርበት አካል በእርቅ ምክንያት እንዳይጠየቅ በማድረግ ፍትህና ህግ ሊጣስ፣ መርሆዎቹም ላይከበሩ፣ ወንጀለኛንም ተጠያቂ ላያደርገው ይችላል የሚል ሥጋት ያላቸው እንደሚገኙበት ያብራራሉ።
በተቃራኒው ደግሞ ስልጣን የያዘው አካል የምክክር መድረኩን ለስልጣኑ መታደጊያ/ ማስጠበቂያ ለማድረግ የፈጠረው ድራማ እንደሆነና ውይይቱ የሁሉንም ፍላጎት የሚያስተናግድ አይደለም። በሰላማዊ ትግል ሰበብም ስልጣን የያዘው አካል ሰላማዊ ታጋዮችን በተለያዩ መንገዶች ስለሚያዳክማቸው ከውይይቱ በኋላ በአቋማቸው ጸንተው እና ተጽዕኖውን ተቋቁመው ለማህበረሰቡ የሚጠቅም ስራ አይሰሩም። ከዚያም አልፎ ለተለያየ ዓላማ ተቋቁመው የግላቸውን አስተሳሰብና አቋም እያራመዱ ህብረተሰቡን ከመረበሽ አልፎ የጋራ መግባባቱን በበጎ ጎን የማይመለከቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም እንደማይጠፉ ያስረዳሉ።
ዶክተር ተሻገር ደግሞ፣ በጋራ መግባባት ሂደት ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል አንዱ በሌላው ቦታ ሆኖ ሁኔታውን ለመገንዘብም ሆነ ለመረዳት አለመሞከሩ ነው። ተበደልን የሚሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ቢኖሩም እንኳ፣ ችግሩ በዳዩ አካል የሚነሱ ቅሬታዎችን በአግባቡ መረዳት አለመቻሉ ነው። ስለሆነም ይህን የተራራቀ የህብረተሰብ ግንኙነት ወደ ጋራ መግባባት ለማድረስ ከተፈለገ ሁሉም ለውይይት ተቀምጠው መወያየትና እውነታውን መገንዘብ የግድ ይላቸዋል። በውይይት ለመግባባት ደግሞ በቅድሚያ በማህበረሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተው የተሟላ ምቹ ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል። በኃይል እና በጉልበት የራስን ፍላጎት ብቻ ለመጫን ከመሞከር ይልቅ ለውይይት የሚቀርበው አካል የሌላውን ሃሳብ በቀናነት በመመልከት ለመግባባት ራሱን አዘጋጅቶ መቅረብ ይገባዋል። በተለይም አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ የተግባቦት ተግዳሮቶች መካከል አለመተማመንን፣ ለጥቃት እጋለጣለሁ ብሎ መስጋትን፣ ይህንን ዕድል ካጣሁ መልሼ የማላገኘው አማራጭ ሃይል ነው የሚሉትንና መሰል ችግሮችን ተገንዝቦ ማስወገድ ተገቢ መሆኑን ይናገራሉ።
ይህን ሃሳብ አቶ ተስፋዬ ሲያጠናክሩት፣ አገራዊ የጋራ መግባባት የሚያስፈልገው በተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት በማህበረሰቡ መካከል ልዩነትና አለመስማማት በመኖሩ ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ። አሁን ላይ የህብረተሰቡ መሰረታዊ ችግር ደግሞ ፍርሃት፣ ስጋት፣ አለመተማመን፣ እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊ ችግሮች መሆናቸውን ያነሳሉ። ይህን የአገራችን ከአቅሙ በላይ የተረበሸ የፖለቲካ ቀውስ ወደ ባሰ ሁኔታ እንዳይሄድ ለማርገብና ለማስተካከልም ሁሉን ባካተተ መንገድ የጋራ ስምምነት ፈጥሮ ዘላቂ አገራዊ ሠላምን በማስፈን ሁሉም የተስማማበት የሽግግር ሂደትን መፍጠር ወሳኝ ነው ይላሉ።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፣ እኛ ኢትዮያውያን የአንድ አገር ህዝብ በመሆናችን ለአገራችን ዘላቂ መረጋጋትና እድገት የተሻለ መስራት ከእያንዳንዳችን ይጠበቅብናል የሚል የጋራ አቋም መያዝ ያስፈለጋል። በአንድ አካባቢ የሚኖር ማህበረሰብ እርስ በእርሱ ሊግባባና ሊረዳዳ፣ አንዱ ለአንዱ በችግሩም ሆነ በደስታው ሊደርስለት ይገባል። ሁሉም የጎረቤቱን፣ የአካባቢውንና የአገሩን ሰላም ማክበርና መጠበቅ አለበት። አንድ አካባቢ የሚፈጠር ችግር ደግሞ ይዘገይና ደረጃው ይለያይ እንደሆነ እንጂ ሌላው ላይ ሊደርስ እንደሚችል መረዳት ጥሩ ነው። ስለሆነም ሁሉም ዜጋ በአገሩ ጉዳይ እንደሚመለከተው ተረድቶ ሠላምን በማስፈን የተረጋጋ ህይወትን ለመምራት የሚጠበቅበትን ግዴታ ማበርከት ይገባዋል። በተጓዳኝም መንግስት በህብረተሰቡ መካከል ያለው የሃሳብና የተግባር ልዩነት እንዲሁም አለመግባባት ወደ ከፋና ወደ ስርዓተ-አልበኝነት እንዳይሄድ በየጊዜው ለሚነሱና ፍትህ ለሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች ቅድሚያ ሰጥቶ ማስተናገድና መፍትሄ በመስጠት እምነት እንዲጣልበት ማድረግ ይኖርበታል።
በተመሳሳይ ሁኔታ አቶ እንግዳወርቅም፣ በጋራ መግባባት ሂደት ዋነኛው ተዋናይ ከኃላፊነት እና ከብዙ የተለያዩ ታሳቢዎች አንጻር፣ የፕሮጀክቱ አንቀሳቃሽ ወይም ጉዳዩን ማቀንቀን የሚኖርበት መንግስት ይሁን እንጂ፣ ባለቤቱ ግን ማህበረሰቡ ሆኖ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸውን ይናገራሉ። በተለይም በተሳትፏቸው አገረን አገር የሚያሰኙት ሁሉም አካላት ጉዳዩ እንደሚመለከታቸው ሊገነዘቡት፣ በማህበረሰቡ የሚንጸባረቀው በጋራ መግባባት ጉዳይ የሚመለከተው አንድን የተወሰነ ክፍል አድርጎ የመቁጠር አዝማሚያ መወገድ ይኖርበታል ይላሉ። ለምሳሌ ያህል፡ – ጉዳዩን የመንግስት፣የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በየዘርፉ ያሉ የሃይማኖትም ሆኑ የፖለቲካ ሊህቃን፣ወዘተ ብቻ አድርጎ የማየት ሁኔታም ትክክል አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ድምጽ የሌላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ድምጻቸው ሊሰማ የሚችለው በእነዚህ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ወይም በተለያዩ ሊህቃን ቡድኖች ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ቢኖርም፣ እነዚህ አካላት በጋራ መግባባት ጉዳዩ ላይ ስምምነት ከሌላቸው ግን ጉዳቱ ተመልሶ የሚያርፈው በማህበረሰቡ ላይ መሆኑን ያስረዳሉ።
የጋራ መግባባት የሚመለከተው ጠቅላላ ህዝቡን ስለሆነ፣ ሁሉም ያገሩን ጉዳይ ራሱ እንዲበይን እድል ማግኘት አለበት እንጂ እነገሌ ናቸው ማወያየትም ሆነ መወያየት ያለባቸው የሚለው አስተሳሰብ አግባብነት የለውም የሚሉት ዶክተር ተሻገር፣ አሁን ላይ ቅራኔ እየተፈጠረ ያለው አንድን ጉዳይ አንደኛው ጥቁር፣ ሌላኛው ነጭ፣ ሌላው ደግሞ ግራጫ፣ ወዘተ በማለት ነገሮችን ከግል ፍላጎትና አመለካከት በመነሳት የመበየን ልዩነት ነው በማለት ይገልጻሉ። በአገር ጉዳይ ግን የጋራ መግባባት ለመፍጠር መወያየት ያለበት ያለልዩነት ሁሉም ዜጋ ነው። በብሄራው መግባባት ሂደት ደግሞ ዴሞክራሲ በጣም ወሳኝ እና አስፈላጊ ነገር በመሆኑ ውይይቱ የተወሰኑ ወገኖች ተገልለው ወይም ወደ ዳር ተገፍተው ወይም ደግሞ ከውይይቱ ተነጥለው የሚካሄድ ከሆነ የሚጠበቀው ውጤት ይመጣል ብሎ ማሰብ የዋህነት መሆኑን ያሰምሩበታል።
ዶክተር ተሻገር ሃሳባቸውን በመቀጠል ሲያስረዱ፣ መረሳት የማይገባው ነገር አገራዊ መግባባት የሚባለው ነገር አንድ ጊዜ ተካሂዶ የሚቆም የአንድ ወቅት ተግባር አለመሆኑ ነው። በአንድ አገር ውስጥ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እስካሉ ድረስ በራሱ በህብረተሰቡም ሆነ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ሁል ጊዜ የሃሳብ ልዩነት፣ አለመግባባት እና አንዳንድ ጊዜም ቅራኔ ስለሚኖር ሂደቱ ቀጣይ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። የጋራ መግባባትን ለመፍጠርም በማህበረሰቡ ውስጥ የሚነሱ ልዩ ልዩ አጀንዳዎችን ከግምት ማስገባት ተገቢ ነው። ለምሳሌ፡- ቋንቋን ብንወስድ በምስራቅ አፍሪካ የስዋህሊኛ ቋንቋን አራትና አምስት አገሮች የብሄራዊና የስራ ቋንቋ አድርገው እየተገለገሉበት እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ። ወደ 150 ሚሊዮን የሚጠጋ የህብረተሰብ ክፍልም በቋንቋው እንደሚጠቀምበት ይገመታል። በመሆኑም ኢትዮጵያ ከአፍሪካውያን ጋር የምትግባባበት የዚህ ቋንቋ ተጠቃሚ መሆን አለባት የሚል ጥያቄ ቢነሳ፣ የሚጠቅመው በሰከነ መንፈስ ጥቅምና ጉዳቱን ተወያይቶ በመመዘን መግባባት ላይ መድረስና መስማማት እንጂ መጨቃጨቅና መጋጨቱ አይደለም። ሌላው ምሳሌ፡- የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ የአንድ ወቅት የማህበረሰቡ ከፍተኛ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል። ጥያቄውም በህዝብ ድምጽ እንዲወሰን ተደርጓል። ይህ ማለት ግን ሲዳማ በደቡብ ክልል ስር እንዲቆይ የሚፈልግ የማህበረሰቡ አካል አልነበረም ማለት አይደለም። ጉዳዩ እልባት ያገኘው በህግና ዴሞክራሲያዊ በሆነ በሰላማዊ መንገድ መግባባት ላይ በመደረሱ ምክንያት ነው። ስለሆነም በሚያለያዩ ጉዳዮች ላይ አግባብነት ባለው መንገድ ውይይት እየተካሄደ የልዩነት ሃሳቦች ተቀባይነት እያገኙ እና መግባባት ላይ እየተደረሰ ይሄዳል ማለት ነው ይላሉ።
የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ሌላው በተደጋጋሚ የተለያዩ ሃሳቦች የሚነሱበት አንዱ ከፍተኛ የመወዛገቢያ ጉዳይ መሆኑን ዶክተር ተሻገር ሲያብራሩ፣ አንደኛው ወገን ጉዳዩን ከአገሪቱ አኩሪ ታሪክ ጋር ያያይዘዋል። ሌላኛው ሰንደቅ ዓላማው የጭቆና፣ የሰቆቃ እና የብሶት ታሪካችንን ያስታውሰናል ይላል። ሌላው ደግሞ ሌላ ሊል ይችላል። ስለሆነም ይህን የመጨቃጨቂያና የመነታረኪያ አጀንዳ በውይይት የሃሳብ ልዩነቶቹን አስታርቆ ስምምነት ላይ መድረስ የግድ ነው። አንዳንድ ጊዜ የጋራ መግባባት ጉዳይ የማህበረሰብ ስነ-ልቦና ጉዳይ ይሆናል። በመሆኑም መደማመጥና መደራደር፤ ድርድሩ ነጻ፣ተአማኒ፣ የአንዱን ስሜትና ማህበራዊ ስነ- ልቦና መረዳትን ይጠይቃል። ይህንን በከፍተኛ ደረጃ የሚያናቁር የልዩነት ሃሳብ ከነ ምላሹ በብዙሃን መገናኝ በማስተላለፍ በቂ ግንዛቤ መፍጠር የሚቻል ከሆነ ችግሩ ቀስ በቀስ በሂደት የመፈታት ዕድል ይኖረዋል። ነገር ግን የሃሳብ ልዩነቶች ወደ ረብሻ፣ ወደ ነውጥ እና ወደ ሁከት አምርተው ዜጎች የሚሰጉበት፣ የሚፈሩበት፣ የሚታሰሩበት፣ የሚቆስሉበት፣ የሚፈናቀሉበት እና የሚሞቱበት ከሆነ የጋራ መግባባት የሚባል ነገር እንደማይታሰብ ያስረዳሉ።
እንደ አቶ ተስፋዬ ማብራሪያ ደግሞ፣ የአገራዊ የጋራ መግባባት አጀንዳው አገራዊ ጉዳይ ነውና እያንዳንዱ ዜጋ፣ የህብረተሰብ ክፍል፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ የሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በሙሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ያገባቸዋል። መንግስት ከተጣለበት ኃላፊነት አኳያ የበለጠ ስለሚመለከተው የጋራ መግባባት ስራ ላይ ከፍተኛውን ድርሻ ሊወስድና ዳር ሊያደርሰው እንደሚገባም ያምናሉ። በተግባሩ ዙሪያ ደግሞ ኃላፊነት ወስደው ችግሩን ለማቃለል የሚሰሩ አካላትን በመከታተል፣ በመደገፍና በመቆጣጠር በኩል የበለጠ ማጠናከር ከመንግስትእንደሚጠበቅ ይናገራሉ።
ከሁሉም በላይ መጠንቀቅ የሚያስፈልገው ነገር በጋራ መግባባት ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ ለህዝብ ቆመናል የሚሉ ከሆነ የህዝብ ሰላም የሚሰፍነውና የሚጠበቀው ችግርን በማራገብ እና በማባባስ አለመሆኑን መገንዘብ አለባቸው። የራሳቸውን የግል ፍላጎት በህዝቡ ላይ በጉልበት የመጫን አዝማሚያቸውንም ማስወገድ ይኖርባቸዋል። ትኩረታቸውንም በአገራዊ ጉዳይ ላይ ብቻ በማድረግ ለአገራቸው፣ ለህዝባቸውና ለህሊናቸው መታመን ይገባቸዋል። የጋራ መግባባት ሲታሰብ ህዝብን ለተሻለ መረጋጋትና መግባባት አድርሶ አገርን በጥሩ መሰረት ላይ ለማቆም የሚያስችል ዕቅድ ሊታቀድ የግድ ይላል። ዕቅዱ መቼ፣ የት፣ በማን ላይ እና ምን መከናወን እንደሚኖርበት በግልጽ የሚያመለክት መሆን አለበት። ታዳሚዎችን በአግባቡ ለይቶና ተገቢ አጀንዳዎችን በመምረጥ በየደረጃው የሚገኘውን የማህበረሰብን ክፍልም ማወያየት ያስፈልጋል በማለት ያሳስባሉ።
አቶ ተስፋዬ አያይዘውም፣ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ ችግር ከተፈጠረ በኋላ እሳቱን ለማጥፋት ላይ ታች ብቻ ማለት የለበትም። ዘላቂነት ያለው ፈጣን፣ ግልጽ፣ ጊዜውን የጠበቀና ተአማኒነት ያለው መረጃ ለህብረተሰቡ ማቀበል ይጠበቅበታል። በሠላምና በጋራ መግባባት ስራ ላይ የተሰማሩ እና ኃላፊነት የተጣለባቸው መንግስታዊም ሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትም ተግባራቸውን በአግባቡ መፈተሽ አለባቸው። ከህብረተሰቡ ጋር በሚያገናኙ ተግባራት በአፈጻጸሙ ግልጽነት ያለው አሰራር የሚከተል የመንግስት ኃላፊ ሊኖር ይገባል። ምክንያቱም መንግስት የሚያከናውናቸውን ተግባራት በህጋዊና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በግልጽነት የሚያከናው ከሆነ በዜጋው ይታመናል። በዜጋው የታመነ መንግስት ደግሞ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር አይቸገርም ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ።
የጋራ መግባባትና ብሄራዊ እርቅ የሚሉት ሃሳቦች ከቃላቶቹ ጀምሮ ጽንሰ-ሃሳባቸው ከመለያየት፣ ከመራራቅ፣ ከመጣላት፣ ከመጋጨት እሳቤ የወጡ፤ ማህበረሰቡን ለትብብር እና ለአንድነት የሚጋብዙ፤ የሚያቀራርቡ፣ የሚያስማሙ፣ የአመጽና የጉልበት ሃሳብ ያልተቀላቀለባቸው ናቸው። ከግንዛቤ እና ከመረዳት ማነስ ችግር ካልሆነ በስተቀር ሰላም ፈላጊ በሆነ ማንኛውም የህብረተሰብ አካል ሁሉ በበጎ ጎን የሚታዩ ለመሆናቸው አስረጅ እንደማያስፈልገው ያነሱት አቶ እንግዳወርቅ፣ ይሁን እንጂ በዲሞክራሲ ሂደት ከተለመደውና ከሚታወቀው አሰራር ለየት ያለ ባህርይን ስለሚያሳይ፣ አንዳንድ ነገሮቹም በባህሪያቸው አመጽን የሚጋብዙ ብዙ ክፍተቶችን ሊፈጥሩ ይችላሉ። ስለሆነም ስለምንነታቸው፣ ስለአስፈላጊነታቸው፣ ስለጠቀሜታቸው፣ ወዘተ በማህበረሰቡ ውስጥ በጎላ መልኩ ግልጽነት እንዲፈጠር በማድረግ ተመሳሳይ ግንዛቤ ማስያዝና ስምምነት መፍጠር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆኑን ያስገነዝባሉ።
የህዝብ ችግር ተፈታ ሊባል የሚችለው ሁሉን አካታች የሆነ የተረጋጋና ዘላቂ ሰላም ሲገኝ ነው። ለውጤታማነቱ ደግሞ በሚካሄዱ ውይይቶች ያለልዩነት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል መዳሰስ እና ማሳተፍ ያስፈልጋል። በተለይ ደግሞ ወቅቱ ያለመረጋጋት የሰፈነበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ህዝቡን ወደተሻለ ሁኔታ ለማምጣት እንዲቻል የሚያነሳቸውን የልዩነት ሃሳቦች ሰከን ብሎ ማየትና መረዳት ይገባል። በዚያው ልክ ደግሞ የሚሰነዘሩ ጥያቄዎችን ከስሜታዊነት በራቀና ሚዛናዊነቱን በጠበቀ ሁኔታ ተረድቶ ተገቢ መልሶችን መስጠት ከሚመለከተው እና ኃላፊነት ከሚሰማው አካል ይጠበቃል። በተለይም ደግሞ የማህበረሰብ አንቂዎች በሚያሰራጩት መረጃ በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ በመሆናቸው፣ ለአገርና ለህዝብ ቅድሚያ በመስጠት ለህሊናቸው ተገዥ መሆን እንደሚኖርባቸው አቶ ተስፋዬ ያስረዳሉ።
ዶክተር ተሻገር የፖለቲካ ፓርቲዎች በህጋዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ፣ ደጋፊዎቻቸውን በስነ- ምግባር እንዲመሩ፣ ነውጥን መቀስቀስና ጥላቻን ማቀንቀን ትተው ለጋራ አገር ግንባታ የበኩላቸውን እንዲወጡ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ያሰገነዝባሉ። ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰሩ የማህበረሰብ አንቂዎችም አሁን ላይ መደበኛ ጋዜጠኞችም እየተሳተፉበት ስለሆነ ህብረተሰቡ የሚፈልገውን፣ የሚቀበለውንና ሠላሙን የሚያስጠብቅለትን መረጃ በማውጣት የሙያ ሥነ-ምግባራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ተጽዕኖ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
ህዝብ እንደ ህዝብ እንዲቀጥል ከተፈለገ አገር ሰላም ውላ ሰላም ማደር አለባት። የሃሳብ ልዩነትን ተቀራርቦ ሰላማዊ የሆነ ውይይት በማድረግ ተደማምጦ መፍታት ያስፈልጋል። እርስ በእርስ እየተጠላለፉ አንዱ ሌላውን ለመጣል የሚደረገው ግጭትና ትርምስም ማንንም ተጠቃሚ እንደማያደርግ በውል መገንዘብ ይገባል። የጋራ አጀንዳዎች፣ ከግል ፍላጎትና አስተሳሰብ ተላቀው የጋራ መግባባት ላይ ሊያደርሱ ይገባል። በጋራ መግባባት ሂደት የትኩረት አቅጣጫን ማህበረሰቡ በራሱ በኑሮ ሂደቱ የሚያጋጥሙትን የሃሳብ ልዩነቶች በቆየው የችግር መፍቻ ወግና ባህሉ መሰረት ዛሬም ተደማምጦ አንድ በማድረግ ዘላቂ ሰላሙን እንዲያስጠብቅ ማገዝ ጠቃሚ ነው። የጋራ መግባባትን ስናስብ ህዝብን ለተሻለ መረጋጋትና መግባባት አድርሶ አገርን በጥሩ መሰረት ላይ ለማቆም የሚያስችሉ የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮች በአግባቡ ሊታቀዱ፣ ተግባራዊ ሊደረጉ፣ መጨረሻ ላይም ውጤታማነታቸው ሊገመገም ይገባል። የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፉም ዘላቂነት ያለው ፈጣን፣ ግልጽ፣ ጊዜውን የጠበቀና ተአማኒነት ያለው መረጃ ለህብረተሰቡ ማድረስ አለበት።
ንጉሤ ተስፋዬ
ዘመን መጽሔት ሐምሌ 2014 ዓ.ም