የአንተነህ “ምልጃ”

 

ገጣሚ አንተነህ አክሊሉ ታህሳስ 26 ቀን 2014 ዓ.ም፣ 4 ኪሎ በሚገኘው ዋሊያ መጻሕፍት መደብር በርእሳችን የጠቀስንለትን የሥነግጥም መድበሉን አስመርቆ ነበር። በእውነቱ ደስ የሚል፤ በአብዛኛውም በወጣት የጥበብ ቤተሰቦች የታጀበና የደመቀ ሆኖ ነበር ያለፈው።

አንተነህ ወጣት ነው፤ ወደ ጉልምስናው እየሄደ መሆኑ ገብቶት ነው መሰል ከእድሜ ጋር ግብ ግብ ገጥሞ በእሱ መሪነት ሁለቱ አብረው እየተጓዙ ነው። ለዚህ መሪነቱ ደግሞ ዋቢው ዳራውን ታሪካዊና ማህበረ-ባህላዊ እሴት ላይ ያደረገው “ምልጃ” ነውና ከእሱው ጋር እንቆይ።

ለመሆኑ “ምልጃ” ምንድን ነው? የሚለውን እንደ መነሻ ወስደን፣ በፎክሎር (በተለይም አማላጅ ከመላክ/አለመላክ … ጋር በተያያዘ፤ ክዋኔና ከዋኙን አካትቶ …) ፣ ባህል፣ ሥነመለኮት ወዘተ ጥናት መስኮች ቢተነተን የበለጠ የሚያዋጣ መሆኑን ጠቆም አድርገን፣ ስለ እሱ አንዳንድ ነጥቦችን እናንሳ።

“ምልጃ” ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ቱባ ማህበረ-ባህላዊ እሴታችን ነው። እሴትነቱም ከኃይማኖታዊነቱ (መንፈሳዊ ትርጉሙና ፋይዳው)፣ ትውፊታዊነቱና ታሪካዊነቱ ይቀዳል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሰረት አማላጅነት ሦስት ነገሮችን (አካላትን) የሚይዝ ሲሆን፤ እነሱም:-

ሀ) ተማላጅ (የሚለመን)፡- ተማላጅ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር አምላክ ነው። “ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ማን ይችላል?” (ሉቃ 5፡21)

ለ) አማላጅ (የሚለምን)፡- አማላጅነት የፍጡር ሥራ ነው። አማላጆች ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ ሐዋርያት፣ ቅዱሳን ናቸው። ቅዱሳን በጸሎታቸው፣ በቃል ኪዳናቸው ከእግዚአብሔር ስለ በደለው ሰው ምሕረትን የሚያሰጡ ናቸው። (1ኛ ዜና 21፡07፣ ዘፍ 08፡23)

ሐ) የሚማለድለት (የሚለመንለት)፡ – ኃጥኣን የቅዱሳን ምልጃና ቃል ኪዳን የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ናቸው። (ኤር 7፡06- 09፣ ዘኊ 21፡6-9)። (1ኛ ጢሞ 2፡1-2ም እራሱን ችሎ ሊጠቀስ ይችላል።)

ከግጥሞቹ በአንዱ፣ በ”የምልጃ ትሩፋት” ውስጥ የሚንፀባረቀው “ምልጃ” ታሪካዊ መሰረቱም ይሁን ማህበረ-ባህላዊ ዳራው (ለምሳሌ፣ “ማህሌት” ወይም አቋቋም) የሚለውን ስንመረምር፣ ከቅኔ መስራቹ ቅዱስ ያሬድ ባለፈ የዜማ መሳሪያዎቹ (ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውሉቱ ማለትም ከበሮ፣ ጽናጽል፣ መቋሚያ … ፈጥነው ወደ አእምሯችን ጓዳ እንደሚመጡት ሁሉ) ጥልቅ ነው። ከጥበብ አኳያ ስንምለከተው “ምልጃ” ተስተዋይ ነውና አስተዋይን ይጠይቃል። ለስሜትና ግንዛቤ (ከነሽፋን ምስሉ) ቅርብ ነውና ምልጃ ከውስጥ፣ ካ’ንጀት … ነው እንጂ “የጸሎት ገደል ማሚቶ” አይደለም፤ ልባምን የሚፈልግ ባህላዊ፣ መንፈሳዊ፣ ስነልቦናዊ ተግባር ነው። በመሆኑም ከቃል ፍቺነቱ በዘለለ በእስብ (ኮንሴፕት) ደረጃ ቢፈታ ኪናዊ ፋይዳው ተፈንቅሎ ይወጣልና ነገሩ እንዲያ ነው።

በስነቃል ተመራማሪዎች በሚገባ ሊረጋገጥ እንደሚችለው “ምልጃ” ክዋኔ (በምልጃው ወቅት የሚደረግ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ) ነው (ከላይ “ሀ”፣ “ለ” እና “ሐ”ንም ይመለከቷል)። አድራጊና የሚደረግ ተግባር አለው። “ምልጃ” በሂደቱም ሆነ ውጤቱ ሥነልቦናዊ ነው። በተግባር አእምሯዊ ሲሆን ነባር ማህበረ- ባህላዊ (ሀገረሰባዊ) ቅርስ/እሴት ነው። በእምነት ደረጃም ሃይሞኖታዊነቱ ያይላል። አስቀድመን እንዳልነው፣ እሴትነቱም ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ትውፊታዊ … መሰረት ያለው ነው። ለዚህ ደግሞ፤ ሎሬት ፀጋዬ “ምነው እመብርሃን ኢትዮጵያን ጨከንሽባት / ቀኝ እጅሽን …” እንዳለው (አንተነህም “ማርያም ማርያም …” እንዳለው)፣ ወይም በ”’ባክሽ” እንደተማለደው፤ በተለይ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ማርያምን በአማላጅነት የማየቱ ጉዳይ ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው። በመሆኑም አጠቃላይ “ምልጃ” በጠቅላይ ርእስነት መምጣቱ ሥነጽሑፍ “በሙሉ” በሚባል ደረጃ ከበርካታ ዲሲፕሊኖች ጋር ትስስር እንዳለው ያመለክታልና ገጣሚው ይህን በማድረጉ የአገር ባህልና እሴቱ እንዲቀጥል ለትውልድ በማስተላለፉ በኩል ተሳክቶለታል።

“ምልጃ” ተፈፃሚ ነውና በትጉህ ፈፃሚ የሚከወን ተማፅኖ ነው፤ ልመና ነው፤ ለታመነ ከጭንቅ መውጫ ቀዳዳ፤ የይቅርታ መግቢያ በር፤ የበዳይ/ተበዳይ ቂም-በቀል መቅረፊያ ሥነልቦናዊ መሳሪያ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ላይ ባለው እውነት እናጠቃልለው፤ ምልጃ በቤተ ክርስቲያን ከሚደረጉ የጸሎት ክፍሎች አንዱ ነው። ቤተ ክርስቲያን የምስጋና ጸሎት፣ የልመና ጸሎት፣ የምልጃ ጸሎት አላት፤ እነዚህንም በንባብ፣ በቃልና በዜማ ታደርሳቸዋለች። ‹‹ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ዂሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ›› እንዲል (ፊልጵ. 4፥6) ምዕራፉ።

በአንድ መቶ ሃምሳ ብር ለአንባቢ የቀረበው “ምልጃ” በ118 ገጽ ላይ ያረፈ ባለ 86 ግጥሞች (ግራና ቀኝ ያሉትን ታሪክ አከል ታሪኮች ሳናካትት፤ (በእነፀጋዬ፣ መንግሥቱ … በኩል በከፈተው ቀዳዳ እራሱ ሾልኮ በመግባት፣ የጎሞራውን “በረከተ መርገም” በሚያስታውሰን መልኩ (ገጽ 116)፣ የራሱን ትውልድ የሸነቆጠበትን ስላቅ ያስቧል) መድበል ሲሆን፤ የገጣሚ አንተነህ (በተማሪነት ሕይወት ዘመኑ ለትምህርት ተግባር ያከናወናቸውና በመምህራኑ ይሁንታን አግኝተው ቤተ- መጻሕፍት እንዲቀመጡ የተደረጉ ስራዎቹ ካልተቆጠሩ በስተቀር) የበኩር ስራ ነው።

ስለሆነ ብቻ “የበኩር …” እንበለው እንጂ ምድቡ ከሥነሰብአዊ ዘውግ የሆነው “ምልጃ” በአንድ ጊዜ ተስፈንጥሮ ከአንጋፋዎቹ ተርታ መሰለፍ የቻለ፤ “የዘመኑ ግጥም Fast food ነው። ማታ ተመርቶ ጠዋት …፤ አንዴ ተነቦ … በቃ …” በሚል ከተፈረጁት ዘመነኞቹ ጎራ ላለመቀላቀል ያፈነገጠ፤ አፈንግጦም ዘመኑን ሳይቀር ያስፈነገጠ ዘመን አፈራሽ የጥበብ ስራ ነው – ከበኩርነት የዘለለ፤ ከጀማሪነት የጠነነ። (በመሆኑም ነው መምህራኑ “ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ …” ይባልለት ዘንድ የሚጠይቁት) እንዲሁም፣ አንተነህ የሚያነሳቸው ፍሬ ሀሳቦች ምጥቀት (ኢንቴሌክቹዋል ኤሚነንስ)፣ የአቀራረብ ኃይሉ ምክንያት በዘውጉ በተደረጉ በውይይቶች እንዳስመሰገኑት ሁሉ፤ በሚደረጉ ውይይቶችም ለአድናቆት እንደሚያበቁት ከወዲሁ መናገር ይቻላል።

ይህ ጸሐፊ ገጣሚው “አንድ የሥነጽሑፍ ሰው፣ በተለይም ገጣሚ ከሥነጽሑፍና ፍልስፍናው በተጨማሪ በፊልም፣ ሥዕል፣ አርክቴክቸር፣ ትያትር … ጋር ሕይወት ሰጪ በሆነ መልኩ ትውውቅ ሊኖረው ይገባል።” የሚለውን ሙያዊ አስተያየት ስለ ማሟላት አለማሟላቱ ድምዳሜ ላይ ባይደርስም “አያሟላም” የሚለው ግን ይመጥነዋል ማለት እንደማይችል መናገር ይቻላል በሚለው የሚያምን ሲሆን መነሻውም እየተነጋገርንባቸው ያሉት እስቦችና በገጣሚው የተሰጣቸው ኪናዊ ስፍራ ነው። በተለይም መድብሉ በራሱ ከዘመን አመጣሹ የከተሜ ጭብጦች (town themes) ማለትም ከተካረረና ቅጥ ያጣ ፖለቲካ፣ ሥርአተ-ፆታዊ ጦርነት፣ መሸተኝነት የተላቀቀ መሆኑም እንደዚሁ።

ሌላውና “አዎን፤ ነበረ። በዚያን ቅጽበት በሆነው የጽሁፍ ዘመን ዮፍታሔ፤ የኢትዮጵያን የሥነጽሁፍ ኅዋ በቅኔ፤ በግጥም፤ በመዝሙርና በተውኔት የብርሃን ጎርፍ ሰንጥቆ አጥለቅልቆት ጠፍቷል። ዛሬ የሚያሳዝነው የዚህ ተወርዋሪ ኮከብ ተጽእኖ በዘመናችን መጥፋቱ ነው።” በማለት ለዮፍታሔ ንጉሤ የተሰጠን አስተያየት፤ ፍቃደ አዘዘ በ”ጩኸት” (ያዲሳባ ጉዶች) (እና ሌሎች በርካቶችም) ትውልዱን የሸነቆጠበትን (linguistic acrobatics የሰራበትን) ሁኔታ የሚያስታውሰን (ከላይ የጠቀስነውን ገጽ ልብ ይሏል) የመኖሩ ጉዳይ ነው።

(ከላይ ከጠቀስነው “Fast food …” ጋር በተያያዘ፤ ከአሁኑ ዘመን ሥነጽሑፍ፣ በተናጠልም የአማርኛ ሥነግጥምን ይዞታ (ስታተስ) በተመለከተ ይህ ጸሐፊ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ (ማክሰኞ ነሐሴ 18/1/2013 ዓ.ም) በፍልስፍና አምድ ላይ “የሥነግጥማችን አሁናዊ ይዞታ” በሚል ርእስ ያወጣውን፤ በ”ባለ ውለታዎቻችን” አምድ ላይ (እሳቷ “ታዛ” መጽሔት ያለ ምንም አይነት ምንጭ ጠቀሳ ላፍ ያደረገችውን)ና “የዘመናዊ አማርኛ ሥነግጥም መስራች” (ብርሀኑ ገበየሁ፣ የአማርኛ ሥነግጥም) የሆኑትን የተመለከተውን፤ “የከበደ ሚካኤል ዐስርቱ ትእዛዛት”ን፤ እንዲሁም ሌሎች የዚህ ጸሐፊ ስራዎች መመልከት ይቻላል።)

እዚህ ላይ አንተነህ በፌስቡክ ገጹ ላይ ካኽሊል ጅብራንን ጠቅሶ ‘እኔኮ ትንሽ እሳተ ገሞራ፤ አፍላ ማዕበል ነበርኩ።’ እንዳለው፣ የገጣሚው እሳተ ጎመራ ፈንድቶ፣ በ”ምልጃ” በኩል አድርጎ ዛሬ የሕዝብ ሀብት ሆኗልና “የእጅህን አሻራ በትን / ይዘኸው …” (እዚህ ጋ ደቤ ትዝ ካላችሁ ልክ ናችሁ) እንጂ ሌላ ምን ይሏል እንዲሉ፤ ወደ ቴክኒካዊ ጉዳዮች እንግባ፤ ከቋንቋውም እንጀምር።

የገጣሚውን (Repertoire) የቋንቋ ባለፀጋነት (አንባቢን መገዳደሩ እንዳለ ሆኖ)፣ የቃላት ምርጫና (የሁለንተናዊ-ሰብአዊነት አቀንቃኝነቱን ጭምር የሚያንሾካሽኩ) በዛም ውስጥ የሚያራምደውን ርእዮት፣ የሚከተለውን ፍልስፍና (እነ “ህልውና”፣ “ህላዌ”፣ “ህያው”፣ “አድማስ”፣ “ከአድማስ ባሻገር”፣ እና የመሳሰሉትን ያስቧል) አይን ከሰበከት እያገላበጠ ያሳየ (“ህልውና” እና “ህላዌ”ን በጎሞራው “በረከተ መርገም” ስንኝ ሁለት ላይ ለምን ፋይዳ እንደገቡ እናስታውስ)፤ የዘመነኞቹን አቅም በመፈታተን ባልተጠበቀ ፍጥነት ወደ አንጋፋዎቹ እየተምዘገዘገ ያለ የአሁኑ ዘመን ቁንጮ ስራ ነው። (እዚህ ላይ የቋንቋ ነገር ሲነሳ በቀላሉ ሊታይ እንደማይገባ ልብ እንለው ዘንድ የሚያሳስበን አንድ ታላቅ ስብእና ያለው ሰው – ሼክስፒር – አለም አቀፍ እውቅናንና ስራዎቹ ዘመን ተሻጋሪ ይሆኑ ዘንድ በሁለት እግሮቹ ያቆሙት ሁለት አበይት ጉዳዮች ብቻ ሲሆኑ አንዱ የቋንቋ ችሎታውና ያንንም ችሎታ መጠቀም መቻሉ (“eyeball”, “puppy dog”, “anchovy” እና የመሳሰሉትን ጨምሮ 2000 ፍጥር ቃላትንና ሐረጋትን ለእንግሊዝኛ አበርክቷል።

ዛሬ ፖለቲከኞች በቁጥጥር ስር ያዋሉት “መልካም አስተዳደር” (Good Governance) ወላጁ ቀሲሱ ሼክስፒር መሆኑን ስንቶቻችን እናውቃለን? ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ዓለም አቀፋዊነቱ (ሰበነክ (ሂዩማኒቲ) እንጂ ዘር፣ ቀለም፣ ኃይማኖት፣ ፆታ እና የመሳሰሉት ሰፈር አለመገኘቱ ነው። የነፃ ስንኝ አባት፤ የአሜሪካ ዲሞክራሲ መስራች ወዘተ የሚባለው እውቁ ባለ ቅኔ፣ ወግ ጸሐፊና ጋዜጠኛ ዊትማን (Walter Whitman; May 31, 1819 – March 26, 1892) ሰው ተኮርነቱ ነው ለዚህ ሁሉ ያበቃው (የእኛው ሰለሞን ደሬሳም በዚሁ፣ በነፃ ስንኝ አጻጻፍ ስልት ጎልቶ የወጣ ገጣሚ ነው)። በመሆኑም ሌላው እንኳን የግል ምርጫና ዝንባሌ ቢሆንም የቋንቋ ጉዳይ ግን ቸል ሊባል እንደማይገባው የካድሬው ማስታወሻ “ሊሰመርበት ይገባል” እንዳለው፣ እኛም እንደግመዋለን።

ገጣሚው ዘይቤ ላይም ወገቡን አስሮ ነው የተጋበት። ከማነጻጸሪያው “እንደ ….” (ገጽ 81)፣ ከድግግሞሽ “ግዴለም” (3 ጊዜ፣ ገጽ 62)፣ “በሰቀቀን” (78)፤ ደጋሚ ቀለም “የየየ…”፣ “ከከከ…” (ገፅ 71) በየስንኞች መጀመሪያ፣ ገጽ10)፤ ደጋሚ ቃል …. በምልጃ “ጠቃሽ”ም እንደ አንድ የገጣሚው ግጥማዊ ብልኃት ያገለገለ ሲሆን፤ (ታሪክ ጠቃሽ የ”ግሪክ አምላክ”፣ “ሲሲፈስ”፤ ከሥነፅሁፍ ጠቃሽ ዘይቤ አኳያም ገጽ 116 (እነ ፀጋዬ …) ጥቂቶቹ ናቸው። ጊዜ እና ስፍራንም በ”ለየቅል” (ይህ አንዱ ምሳሌ ብቻ ነው) አማካኝነት “እዚህ” እና “እዚያ” ሆኖ እናገኘዋለን።

እዚህ ላይ ስለ ደጋሚም ሆነ ደጊመ ቃል ስናነሳ የኢትዮጵያ የስነግጥም ሊቃውንት ከበፊት ጀምሮም አሳምረው ያውቁት፤ አውቀውም ይጠቀሙበት የነበረ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ማሳያው ዮፍታሔ ሲሆን፤

ድንግል ሀገሩ ሆይ ጥንተ ተደንግሎ

ጥንተ ተደንግሎ ጥንተ ተደንግሎ

ህፃናቱ ታርደው ያንቺም ልብ ቆስሎ

ልጅሽ ተሰደደ አንቺን ተከትሎ

የህፃናቱ ደም አዘክሪ ኩሎ።

አዝማች፤ አስጨነቀኝ ስደትሽ

እመቤቴ ተመለሺ እመቤቴ ተመለሺ

በማለት (በተለይ የመጀመሪያና ተከታዩን ስንኞች ይመልከቱ) መቀኘቱን መጥቀሱ ብቻ ይበቃልና አንተነህም ጋ ይህ የአገጣጠም ብልሀት ይታያል። ገጣሚው እንደ ነቢይ መኮንን “ስውር ስፌት” በስውር የሰፋው ካለም መገላለጡ የእኛው ሂሳዊ ተግባር ነውና ያኔ ዛሬ ከዮፍታሔ ጋር እንዳስተያየነው ሁሉ፤ ከነቢዩ ጋር እናጋጥመውና እንፈትሸው ዘንድ እንገደዳለን ማለት ነው።

ሌላው የ”ምልጃ” መለያ ደግሞ “ሌጋሲ” የማስቀጠሉ ተግባር ነው። ከዚህ አንፃር በአዳም ረታ ሲዘወተር የምናገኘው “ግራጫ” በ”ምልጃ” ውስጥ ለሥነግጥም አድባር (በርካታ ስፍራዎች) አድሮ ሲገብር መገኘቱን መመልከት ይቻላል። ለምን? አማረ ማሞ “ቋንቋ ምንድን ነው?” ብሎ ከጠየቀ በኋላ “ያወያያል፣ ያነጋግራል፣ ያመራምራል …” እንዳለው ነውና ለጊዜው እንዝለለው። (ይህ “ሌጋሲ” (አሻራ) ን የማስቀጠል ተግባር ለሥነግጥም አዲስ አይደለም። ይህንን ስንል አፄ ቴዎድሮስ “አገሬ ገነት ናት” ያሉትን በገብረ ክርስቶስ ደስታ “ሀገሬ” ውስጥ እናገኘዋለንና ነው።) ይህ አይነቱ ተስተላለፎ ሥነጽሑፍ ከአገር፣ አገረ መንግስትና ትውልድ ግንባታ አኳያ ያለውን ሚና ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ በመሆኑ ቢዘወተር ፋይዳው ብዙ ነው።

“ጠቃሽ”ነቱንም ከዚሁ ከገጣሚው የዳበረ የንባብ ልምዱ ጋር አያይዞ ማንሳት የሚቻል ሲሆን፣ ይህም ከእነ ሎሬት ፀጋዬ፣ መንግስቱ ለማ፣ ደበበ ሰይፉ፣ ሰለሞን ደሬሳ፣ ወዘተ ጋር የቅርብ ወዳጅነትን እንዲመሰርት፤ መስርቶም አንዳች ነገር እንዲል ማድረግ ብቻም ሳይሆን ወደ ምስራቁ አለም ቻይና ሁሉ እንዲዘልቅና ያንግን ያነሳ፤ ወደ አረቡ አለምም ጎራ ብሎ ከካኽሊል ጅብራን ጋር ወዳጅነት ይመሰርት ዘንድ አስችሎታልና የ”ምልጃ”ው ባላባት የዋዛ አይደለም። ከባዱ ጥያቄ “ለምን አይነት ኪናዊ ፋይዳ ሲል ተጠቀመ(ባቸው)?” የሚለው ሲሆን፤ የዚህ ጸሐፊ የአሁን ተግባር ጉዳዩን ለሃያሲያን ትቶ ማለፍ ነውና ታልፏል።

ምናልባት ከዚሁ ጋር አሰናስለን ማንሳት የሚያስፈልገን ከሆነ ልናነሳው የሚገባው፣ የአገራችን የፍልስፍና ምሁርና ሊቅ ዶክተር እጓለ ገብረዮሃንስ (የጎሞራው ወንድም) በአገራችን ብቸኛ በሆነው “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” ስራቸው “አሃዝ/ተርም” ስለሚሉት የቃላት (በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ) ጉዳይ ከሆነ፤ የገጣሚው ሰብአዊ የሆነ የቃላት ምርጫ (እራሱ ሰብአዊ፣ ስነልቦናዊውን “ምልጃ” ጨምሮ፣ “ህልውና”ን አካቶ፣ “ህላዌ”ን አስከትሎ፣ “ሰብዕና”ን አንተርሶ … እና የመሳሰሉትን ለተመለከተ ማለት ነው) እንደ ገጣሚው ርእዮተ አለም (እምነት፣ አተያይ፣ ፍላጎት ….) ምርጫና መገለጫ ሆኖ ያገለግላል (አገልግሏል)? ወይስ ሌላ? ገጣሚው የራሱን የገጣሚነት ቀለም፣ አሻራ ወዘተ ከማኖር (ግለ-ወጥነት (ኦሪጂናሊቲ) ብንለው ትክክል የምንሆነው ማለት ነው) አኳያስ? በፕሮፌሰር መስፍን “መሰላል ለመውጣት” (መውጣት/ መውረድ) ስራ ላይ የዋለው “ዳይኮቶሚ”ስ በ”ምልጃ” ውስጥ ተስተናግዷል ወይስ የለም? የተጠየቅስ ጉዳይ? የሚሉትን ነውና ይህን ከዚህ ጽሑፍ ውስንነት አኳያ ስናልፈው በጥያቄ ምልክት ስር አድርገነው ቢሆንም፤ ታታሪ ሃያሲ ቢዘልቅበት ደግሞ የበለጠ አዋጭ እንደሚሆን በማሳሰብ ነው።

ስለ አስተዋይ (ተራኪው)ና ተስተዋይ (ድርጊቱ) ልብ እንል ዘንድ እድል የሰጠን፤ በተስተዋይ ላይ የአስተዋዩን ልብ አድራጊነት (ኮንሽየስነስ) እናደንቅ፤ እንሆን ዘንድ ያስፏጨን፤ ስለ ጉዳዩም ተጠየቃዊነት (Symbolic logic ወይም Symbolic representation) እንቆዝም ዘንድ ከማስቻልም ባለፈ ልብ ያስባለን የአንተነህ “ምልጃ” የግጥም ባህርያትን (እነዚህ ባህርያት በበድሉ ዋቅጅራ “አጭር ልቦለድሽ” ግጥም ውስጥ እንዴት እንደገቡ፣ ለምን እንደገቡ ….. ማስተዋልና ከምንነታቸው እስከ አስፈላጊነታቸው ድረስ ያለውን ኪናዊ ፋይዳ መረዳት ይቻላል።) አሟልቶ መገኘቱ፤ ወይም የቃላት (በተለይ ከገጣሚያን የሚጠበቀውን ፍካሬያዊ) ምርጫና አገላብጦ የመጠቀም ብቃቱ ይደነቃል።

እስኪ “የዳመና አለላ …” ምን እንደሚመስል የሚናገር ካለ? ፍካሬያዊ የቃላት ምርጫውን በተመለከተስ? ለምሳሌ በ”የመንታ እናት!!” ውስጥ የ”እናት” አጠቃቀሙስ (“እማሬ” ለፈጠራ ሰው የማይመከር፤ ከእሱ(ሷ)ም የማይጠበቅ መሆኑ ይታወቃል።)? እንደው ለመጠቆም ያህል ብቻ። ገጣሚውም ሆነ ሌሎች አዲስ መጥ ወጣቶቻችን በዚህ ከቀጠሉ ወደ ፊት በአለም በቁንጮነታቸው እስከ ዛሬ እንደዘለቁት እንደ’ነ “Because I could not stop for Death –” (ኤሚሊ ዲከንስ)፣ “Harlem” (ላንግስተን ሁፍስ)፣ “Daddy” (ሲልቪያ ፕላዝ) እና ሌሎች ሁሉ መሰል ገጣሚያንና ስራዎችን አገራችን ይኖራታል ብሎ ተስፋ ማድረግ ይቻላልና በአግባቡ በርቱ ማለቱ የሌሎቻችን ድርሻ ይሆናል። አሁንም ቢሆን፣ ስለግብርናና ገበሬ አሻራውን አሳርፏል ከሚባለው ከ“The Red Wheelbarrow” (ዊሊያም ካርሎስ ዊሊያም) ጀምሮ እንደ “The Waste Land” (ቲ. ኤስ. ኤሊየት)፣ “The Road Not Taken” (ሮበርት ፍሮስት)፣ “We Real Cool” (ጔዉንዶሊን ብሩክስ)፣ “One Art” (ኤልዛቤት ቢሾፕ) … ሁሉ የአንተነህ “ምልጃ”ም የራሱን ርቀት ያህል ሄዷልና ይበልም ቢያሰኝና ይህንን ጽሑፍ ቢያጭር አይገርምም።

እዚህ ላይ ጠቅሰን ልናልፈው የሚገባንን የቋንቋ ጉዳይ ካነሳን የ”ስታየል”ንም ጣጣ ማየት ተገቢ ሲሆን፤ አንዱም ሂ’ወት፣ ሒ’ወት፣ ህ’ወት፤ ኣብርሆት፣ ኣብርኈት፤ ጸጋሽ፣ ፀጋሽ ወዘተ በተመለከተ ወጥነት አለመኖሩና ትክክለኛውን መለየት አለመቻሉ ነውና በ2ኛው ዕትም የሚለቀሙ ስለመሆናቸው ከወዲሁ መተማመን ይቻላል።

እንዲሁም ሌሎች በርካቶች የገጣሚውን ትዕምርትን የመጠቀም ብቃት፣ ተምሳሌታዊነት፣ አፈንጋጭነት፣ የ(Socio-Cultural) ማህበረ- ባህላዊ እውቀት ዳራ (ከ”ስሜት ሰጩ አሃድ” (የብርሀኑ ገበየሁን “የአማርኛ ሥነግጥም” ይመለከቷል) ርእሱ ጀምሮ) ወዘተ መመልከት በቂ ሲሆን፤ ሌሎችም ብዙ አሉ።

ገጣሚ አንተነህ አክሊሉ ለዘመናት የገጣሚና ፈላስፎች ጥያቄ መልስ ያገኘ ሁሉ የሚያስመስለው መሳጭ፣ ተወዳጅ … ግጥምንም ይዞ የመጣ ሲሆን፤ የፈላስፋ ዲዮጋን ሲኖፕስኪ በፋኖስ ሰው ፈልጎ የማጣት (በእውቀቱ “ውሻው …” ሲል እንዳላገጠው ሳይሆን)፣ ተወርዋሪ ኮከብ መሆኑ የተመሰከረለት ዮፍታሄ ንጉሤ (ስለ’ዚህ ሰው እና አጠቃላይ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ለማወቅ ዮሐንስ አድማሱ ያዘጋጀውንና ዮናስ አድማሱ ያሰናኘውን፤ ተጀምሮ ለሕትመት እስኪበቃ ከአራት አስርት አመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረውን “ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፤ አጭር የሕይወቱና የጽሑፉ ታሪክ” ተመልከት። (በነገራችን ላይ የእነዚህን የሶስት በታሪክ የተያያዙ ሰዎች የስማቸው መነሻ የሆነውን “ዮ” የሚያጠናና “እነሆ በረከት” የሚለን እንዴት ጠፋ?)) “ዓይኔን ሰው ራበው …” በማለት ምርርርርር … (በቴዲ አፍሮ ዜማ “እርርርርር …”) ያለበትና ሎሬቱ በ”የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ”ን ግጥም “ሰው እንዳጣ ምድር በዳ”ን የጀመረበትን ስንኝ እናስብ ዘንድ በሚቀሰቅስ መልኩ ምድር በሰው ምድረ በዳ የተመታችበትን፤ እንዲሁም ሌሎች በርካቶች የቆዘሙ-የተከዙበትን፤ የአቤ ጉበኛን “መልካሙ ሰው”፤ እንዲሁም ዳግላስ ጴጥሮስ “የሰው ያለህ!” (“ብሌን” መጽሔት) የሚያስታውሰን አንተነህ ግን በ”አዲሱ ሰው!!” አማካኝነት ጥያቄያቸው ምላሽ አግኝቶ ይሆን? የሚል ጥያቄ እናነሳ ዘንድ ያሳስባልና እልል በቅምጤ እንዳሉት ሴትዮ … “እሰየው” ነው። (ቴዲ አፍሮ “ሰው አለ ወይ….?” ለሚለው ጥያቄ አብነት አዎ “ሰው አለ…” ሲል እንደ”መለሰው” ማለታችን ነው።)

«አደፍርስ» በተሰኘ ልብ ወለድ ድርሰቱ ባነሳቸው ጭብጦች እና የተራቀቀ የአጻጻፍ ስልቱ የአማርኛን ዘመናዊ ልብ ወለድ ወደ ድንቅ ከፍ ካለ እርከን ያወጣ፤ “እምቧ በሉ ሰዎች” በሚለው የግጥም መድብሉ ውስጥ በተካተቱ ግጥሞቹ ስለሀገሩ ልማትና ዕድገት ተቆርቋሪነቱን የገለጠ ዕውቅ የሥነጽሑፍ ምሁር፤ ሃያሲና ተርጓሚ መሆኑ የፀደቀለት ከሁሉም በቀደመ ተውኔት ድርሰቱ «ሰው አለ ብዬ» ያለውንም እዚህ መጥቀሱ በበርካታ ምክንያቶች ምክንያት ተገቢ ሲሆን፤ የአንተነህ “አዲሱ ሰው!!” ምናልባት መልሶለት ከሆነ የሚነግረን ጥናት ያስፈልገናል።

በዚህ፣ ምናልባትም ከ2ኛ እትሙ ጀምሮ “ሙዳዬ ቃላት” ያስፈልገዋል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ደርዝ ባለው የሽፋን ሥዕል የታጀበው “ምልጃ” የሥነግጥም መድብል ገጣሚው የገጣሚ ነፍሱ ለይዘት ብቻ ሳይሆን ለቅርጽም ስለመጠበብ-መቸገሯ፤ አብዝታም ስለመጠቀሟ በርካታ ማሳያዎች አሉ። ለምሳሌ አንተነህ “አንጓ”ን ከቅርጽ ባለፈም ለሀሳብ አደረጃጀትና ፍሰት ይሁነኝ ብሎ ስራ ላይ አውሏል። (ምሳሌ ካስፈለገም ባለ ሶስት አንጓውን፣ “ኮከብ ዕጣ”ን መመልከት ይቻላል።) “ጥያቄያዊ አቀራረብ”ን (“?” ምልክት) ከእኔ ባይ ተናጋሪው የእውነትን ፍለጋ ፍላጎት ባሻገር የአንባቢን ቀልብ ለመሳብ፣ ስቦም ከ’ራሱ ጋር ለማቆየት፣ አቆይቶም የድርጊቱ ተካፋይ፣ የስሜቱ ተጋሪ ወዘተ ለማድረግ አስቦበት አድርጎታል። (ለተጨማሪ “ምነው!?”ን ተመልከት።)

አንተነህ አንባቢን ከተለመደው የሥነግጥም አነባበብ ይትባህል ያላቀቀና የባለ ቅኔና የሥነጽሑፍ መምህሩ ሰይፈ መታፈሪያ ፍሬውን “የሥነግጥም ንባብ ሙዝ ላጥ ዋጥ አይደለም”ን ዳግም ያፀደቀ መሆኑም እራሱ አንድ ለሥነጽሑፍ (ለፈጠራ ሁሉ) እድገት የተደረገ አስተዋፅኦ ነውና እዚህ ሊጠቀስ ይገባዋል። (እዚህ ጋ እያወራን ያለነው በስራዎቹ ውስጥ አንባቢን የሚገዳደር፣ የደራሲውን መልእክት እንዳያገኝ የሚጋርድ ነገር – Opaqueness (the opaqueness of a poem makes it hard to figure out the poem’s meaning የሚለው ለ”ምልጃ” ይሰራል/አይሰራም? እና የመሳሰሉት አሉ/የሉም? ከሆነ ልክ ነን ማለት ነው።) ምን ምን መልኮችን (ማህበራዊ፣ ስነልቦናዊ ….) ያሳያል? የሚለውን አሳስቦን ከሆነም፤ ገጣሚው በየትኛው ፎከረ፣ በየቱስ አቅራራ፣ በየትኛውስ ዘመረ፣ በየትኛውስ ግጥሙ አዚሞ በየትኛው ዘየረ …? ለምን? የሚለውንም ወደ’ዚህ ጽሑፍ አንባቢ አእምሮ ከች አድርገን ከሆነም ለአንባቢያን ተገቢ መተከዣ አቀብለናልና አበጅተናል።)

አንተነህ ወቅቱንም ሰንዷል። “ምልጃ” የህትመት ብርሀን ያየችበት ወቅት ለእኛ ጥሩ ወቅት አልነበረም። የነበረው እርስ በእርስ እየተጨራረስን፤ “የህልውና ዘመቻ”፤ “የሕግ የበላይነትን የማስከበር ዘመቻ” እያደረግን፤ በየቀኑ የንፁሀንን ሕይወት እየገበርን የነበረበት ወቅት ነው። አንተነህ ይህንን የታሪክ መጥፎ ጠባሳ ዝም ብሎት አላለፈም። ከእራሱ “የመንታ እናት!!” ባለፈ ከካህሊል ጅብራን ጠልፎ ባመጣው ዘለግ ያለ “ሰሎሜ!” ግጥሙ አማካኝነትም ለታሪክ አኑሮት አልፏል።

ይህ ጽሑፍ ሂስ አይደለም። ተንታኝ ጽሑፍም አይደለም። አስተዋዋቂ (ፖፑላራይዘር)ም አይደለም። … አይደለም። ጽሑፉ የገለጥ ገለጥ፣ ገልበጥ ገልበጥና ገረፍ ገረፍ ንባብ፤ እንዲሁም የገጣሚውን እምቅ አቅምና ብቃት መገንዘብ ያመጣው ድማሜ ውጤት ነው። ይህ የተደረገበት ዋናው ምክንያት ደግሞ በሳል ሃያሲያንን የሚጠብቀው “ምልጃ”ን ያለ በቂ ፍተሻ ላለመደንቆል በማሰብ ነው።

በአጠቃላይ፣ ጋሽ ፀጋዬ ገብረመድህን “ሥነግጥም የፈጠራ ሁሉ፤ የሥነጽሑፍ ሁሉ የደም ጠብታ ነው።” ያለው ገዥ ድምዳሜ እንደ ማንኛውም ለሥነጽሑፍ የቀረበ ሰው በዚህ ጸሐፊ ልብና አእምሮ ውስጥም ተገቢውን ስፍራ የያዘ ነው። በመሆኑም “ምልጃ”ና የመሳሰሉ ጠንካራ ስራዎች ሲገኙ ፈጣሪዎቻቸውን ከፍ አድርጎ ማየትን ግድ ይላልና አንተነህ ተሳክቶለታል፤ ወደ ፊት ደግሞ የበለጠ ይሳካለታል፤ መምህራን፣ ጋዜጠኞች፣ የጥናትና ምርምር ሰዎች፣ ፖለቲከኞች (ካደረጉት)፣ የሥነግጥም (በተራዛሚው የሥነጽሑፍ) አድናቂዎች ወዘተ ለእለት ተእለት እንቅስቃሴና ተግባራቸው ግብአት፤ ለአእምሯቸው ጂምናስቲክ ማሰሪያ አግኝተዋልና ደስ ይላል ስንል ከ1300 እስከ 1400 የነበረው የግእዝ ሥነፅሁፍ ወርቃማ ዘመን፤ የ1960 እና 1970ዎቹ የአማርኛ ሥነፅሁፍ ወርቃማ ዘመን ተመልሶ ይመጣ ዘንድ በመመኘት፤ ደራሲዎቻችን፣ በተለይም ወጣት ደራሲዎቻችንም ከዚሁ አኳያ እንዲሰሩ በማሳሰብ ነው።

ግርማ መንግሥቴ

ዘመን መጽሔት ግንቦት 2014 ዓ.ም  

Recommended For You