የተመጣጠነ ምግብ እና የአዕምሮ እድገት

“ማንኛውም የሚበላና በውስጡ ለሰውነት እድገትና ጤና አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ-ነገሮችን ያየዘ፤ በማኅበረሰቡ ባህልና እምነት ተቀባይነት ያለው ነገር” የሚለው ሃሳብ ብዙዎችን የሚያስማማ ለ “ምግብ” የተሰጠ ብያኔ ነው። ብያኔው፣ ምግብ ወደ ሆድ ውስጥ የሚገባ ነገር በመሆኑ ብቻ ሳይሆን በይዘቱም ጭምር እንደሚለካ ያሳያል፤ ምግብ ከይዘቱም ባሻገር ንጽህናውና ደህንነቱ የተጠበቀ ሊሆንም ይገባዋል። ከልጅነቱ ጀምሮ በአስፈላጊ ንጥረ-ነገሮች የበለፀጉና ደህንነታቸው የተጠበቁ ምግቦችን እየተመገበ ያደገ ሰው ለበሽታ የመጋለጥ እድሉ ያነሰ፣ ተክለ ሰውነቱ የተስተካከለና አዕምሮውም ብሩህ ይሆናል። ከዚህ በተቃራኒ የተመጣጠነ-ምግብ ሳያገኝ ያደገ ሰው፣ ሰውነቱ የቀጨጨ፣ በቀላሉ በበሽታ የሚጠቃ ይሆናል፤ በአስተሳሰብ ችሎታውም ያንሳል። በሀገራችን “ሰው የሚመገበውን ይመስላል” የሚል ብሂል አለ፤ ፈረንጆቹም “You are What you eat” ይላሉ። አባባሎቹ ለሰው ልጅ ውስጣዊና ውጫዊ ገጽታ ምግብ ያለውን ከፍ ያለ ሚና ያሳያሉ።

ሥርዓተ-ምግብ

ለሰው ልጅ ህልውና፣ ዕድገትና ጤና ወሳኝ የሆነው “ምግብ” ራሱን ችሎ ሥርዓተ-ምግብ (Nutrition) በሚል ይጠናል። ሥርዓተ- ምግብ በምግብ ውስጥ ስላሉ ንጥረ-ነገሮች፣ ንጥረ- ነገሮቹ በሰውነት ውስጥ ስለሚኖራቸው ተግባር፤ በአጠቃላይ በምግብ እና በሰው አካላዊና አእምሯዊ ዕድገትና ጤና መካከል ያለውን ዝምድና የሚያጠና ሳይንስ ነው።

በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የምግብ ሳይንስና ሥነ-ምግብ ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ካሳዬ ቶሎሳ፣ “ሥርዓተ-ምግብ” በንጥረ ነገር የበለፀገ፣ ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ መመገብን የሚገልጽ ጽንሰ-ሃሳብ መሆኑን ገልጸው፣ አንድ ሰው በቀን ውስጥ የሚመገባቸው ምግቦች ካርቦሀይድሬት፣ ፕሮቲንና እንደ አይረን፣ ዚንክና ካልሺየም ያሉ ማዕድናትን፣ ቫይታሚኖችና ስብ ነክ ያላቸውን ምግቦች የያዘ መሆን እንዳለበት ያስረዳሉ።

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፣ አንድ ሰው ቁርስ፣ ምሳና እራቱን ተመሳሳይ የምግብ አይነትን ደጋግሞ የሚበላ ከሆነ ሆዱን ሞላ እንጂ፣ ሰውነቱ አስፈላጊ ንጥረ-ነገሮችን አላገኘም። ሰውነታችን አስፈላጊ ንጥረ-ነገሮችን አለማግኘቱ ከአካላዊ እድገት ችግር ባሻገር አስተሳሰባችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖን ያሳድራል፣ ለተለያዩ በሽታዎችም በተደጋጋሚ ለተጋላጭነት ይዳርጋል።

ጤናማ ሥርዓተ-ምግብ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ የምግብ እጥረት (Undernu­trition)፣ ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ-ነገሮች እጥረት (Micronutrient deficiencies)፣ ቀዳሚ የህብረተሰብ ጤና ችግሮች ሆነው ከ 50 በመቶ በላይ ለሚሆኑ ህፃናት የሞት ምክንያት እንደሆኑ ቀጥለዋል። እ.ኤ.አ በ2019 የተካሄደ የሥነ- ህዝብና ጤና ዳሰሳ ጥናት፣ ከአምስት አመት በታች በሆኑ ህፃናት ላይ 37 በመቶ የመቀንጨር፣ 21 በመቶ ከክብደት በታች፣ ሰባት በመቶ ደግሞ የመክሳት ችግር መኖሩን አመላክቷል። በሌላ መልኩ፣ ከልክ ያለፈ ውፍረት (Obesity) እና ከፍተኛ ክብደት (Overweight) እንዲሁም፣ እንደ ደም ግፊት፣ ስኳር፣ የልብ ህመም እና ካንሰር የመሳሰሉት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በፍጥነት እየጨመሩ በመምጣታቸው ያለእድሜ ለሚከሰት ሞትና የአካል ጉዳት መንስዔ ሆነዋል። በአብዛኞቹ ከሰሃራ በታች በሚገኙ ሃገራት፣ በንጥረ-ምግብ የበለፀጉ ጤናማ ምግቦች አወሳሰድ አስፈላጊ ከሆኑ መስፈርቶች አንፃር ሲታይ በጣም ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በእነዚህ ሀገራት ከሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል መካከል አንድ ሶስተኛ የሚሆነው ምግብ የማግኘት ችግር አለበት። ከ 70 በመቶ በላይ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ በአብዛኛው ተመሳሳይ የምግብ ዓይነት በተለይም ጥራጥሬ (cereals) እና የእህል ዘሮችን (starchy staples) ይመገባል።

የግብርናውን መስክ ስናይ፣ የግብርና ክፍለ- ኢኮኖሚ ዋነኛ ዓላማ የተሰባጠሩ እና በንጥረ- ምግብ የበለፀጉ ምግቦችን በሁሉም የእድሜ ክልል ላሉ ዜጎች በየትኛውም ጊዜ ከገበያና ከእርሻ ቦታዎች አምጥቶ ማቅረብና መዳረሱን ማረጋገጥ ሲሆን፣ ከዚህ አንጻር መሻሻሎች ቢኖሩም የሚፈለገው ደረጃ ላይ ለመድረስ ግን ብዙ ርቀት ይቀረዋል።

ለአብነት ያህል፣ በኢትዮጰያ የአንድ አዋቂ ሰው የነፍስ ወከፍ ዓመታዊ የወተት ፍጆታ 16 ነጥብ ስድስት ኪ.ግ ሲሆን፣ የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መስፈርት መሠረት፣ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ የወተት ፍጆታ 225 ኪ.ግ ነው። በተመሳሳይ የስጋ የነፍስ ወከፍ ዓመታዊ ፍጆታ ሰባት ነጥብ ሰባት ኪ.ግ ሲሆን፣ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው መስፈርት 20 ነጥብ አራት ኪ.ግ ነው። የአትክልት አመጋገብን ስናይ በአማካይ አንድ ሰው 50 ነጥብ ሁለት ኪ.ግ ሲጠቀም፣ የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መስፈርት መሠረት አንድ ሰው በአማካይ በአመት መመገብ ያለበት የአትክልት መጠን ግን 146 ኪ.ግ ነው።

በ2019 የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ጥናት መሰረት 54 በመቶ የሚሆኑ ቤተሰቦች ከሰባቱ የምግብ መደቦች ውስጥ አራትና ከዚያ በታች ይመገባሉ። ከዚህ ውስጥ ህፃናትና ሴቶች አነስተኛውን የምግብ ስብጥር ይጠቀማሉ። በ 2016 የስነ-ህዝብና ጤና ዳሰሳ ጥናት መሰረት ደግሞ፣ ከስድስት እስከ 23 ወር መካከል ያሉ ህፃናት፣ ሰባት በመቶዎቹ ብቻ ዓለም አቀፉን ዝቅተኛ የአመጋገብ መስፈርት ያሟላሉ።

የተመጣጠነ-ምግብ ለመመገብ የምግብ ዋጋ መሠረታዊ ጉዳይ ሲሆን፣ በቅርቡ በኢትዮጵያ በተካሄደው የምግብ ዋጋ ጥናት መሠረት ከአራት ሰዎች ሶስቱ ዝቅተኛውን የንጥረ-ነገር መስፈርት ያሟላ የበለፀገ ምግብ ለመመገብ እንኳ አቅሙ የላቸውም።

ኢትዮጵያ በአለም ላይ ከፍተኛ የሥርዓተ- ምግብ ችግር ካለባቸው ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ያነሱት፣ በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምግብ ሳይንስና ሥነ-ምግብ ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ማስረሻ ተሰማ፣ በዚህ አመት ብቻ ከ35 ከመቶ በላይ ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህጻናት የቀነጨሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። ጤናማ አመጋገብ ከተስተካከለ አቋምና ከጤናማ አካል ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ከተስተካከለ አዕምሮና ከጤናማ አስተሳሰብ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው ያሉት ዶ/ር ማስረሻ፣ ከዚህ የተነሳ የሥርዓተ-ምግብ ችግራችን አጠቃላይ በሀገራችን ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ሕይወታችን ላይ ያመጣው ተጽዕኖ እንዳለም ይናገራሉ። ለዚህም የሥርዓተ-ምግብ ችግር በከፋባቸው ሀገራት ያለው ኢኮኖሚና ሀገራዊ ሠላም፣ ሥርዓተ-ምግብ የማኅበረሰብ ችግር ባልሆነባቸው ሀገራት ካለው የኢኮኖሚ እድገትና ሀገራዊ ሠላም ጋር ያለውን ልዩነት በማሳያነት አንስተዋል።

ሥርዓተ-ምግብና የህጻናት እድገት

በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምግብ ሳይንስና የሥነ-ምግብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ማስረሻ፣ ለህጻናት እድገት ጤናማ ሥርዓተ- ምግብ መሠረታዊና ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው ይናገራሉ። እርሳቸው እንዳሉት ቤት ሲገነባ መሠረቱ ጥሩ ካልሆነ ጥራት እንደሚጎድለውና የቤቱም እድሜ እንደሚያጥረው ሁሉ፣ ነገ ሀገርን የሚረከቡ ህጻናትም ጤናማ አካላዊና አዕምሯዊ እድገት እንዲኖራቸው ጤናማ አመጋገገብ ያስፈልገጋል በተለይም በእናታቸው ሆድ ከተጸነሱበት ጊዜ ጀምሮ ሁለት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ያለው ጊዜ ለእድገታቸው መሠረት የሚጣልበት ነው፤ አንድ ጨቅላ ህጻን በእነዚህ የመጀመሪያዎቹ 1000 ቀናት ውስጥ ከእናቱ ጡት ወተት ጀምሮ ለአካላዊና አዕምሯዊ እድገቱ አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ-ነገሮችን ማግኘት ይኖርበታል።

በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሥርዓተ- ምግብ ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ካሳዬ ቶሎሳም በበኩላቸው፣ ለጤናማ የልጅ አስተዳደግ እናት ገና ነብሰ-ጡር ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ ህጻኑ ተወልዶ ሁለት አመት እስኪሞላው ድረስ ያሉት የመጀመሪያዎቹ 1000 ቀናት ወሳኝ መሆናቸውን ጠቁመው፣ አንድ ልጅ የሚያስፈልገውን ንጥረ-ነገር ሳያገኝ ሁለት አመት ካለፈውና ከተጎዳ በኋላ የተመጣጠነ- ምግብ ሰጥተን ከጉዳቱ እንመልሰዋለው ቢባል የማይቻል መሆኑን ያስረዳሉ። ዶ/ር ካሳዬ አያይዘውም፣ የተመጣጠነ- ምግብ አለማግኘት ወይም ጤናማ ሥርዓተ-ምግብን አለመከተል

 አካላዊ ብቻ ሳይሆን የአእምሮ እድገት ላይም ተጽዕኖን እንደሚያስከትል፣ ወላጆች ግን ብዙውን ጊዜ የሚጨነቁት ለልጃቸው አካላዊ ገጽታ እንደሆነ ይገልጻሉ። በተጨማሪም ለእድገቱ የሚያስፈልገውን የተመጣጠነ-ምግብ ያላገኘና አዕምሮው በተገቢው ልክ ያላደገ ህጻን ወደፊት ሰርቶ ማግኘት ያለበትን ለማግኘት አቅም ያንሰዋል፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ ከራሱ አልፎ የሀገርን ምርታማነት ይጎዳልም ብለዋል።

አዕምሮው የቀነጨረ ልጅና ትክክለኛ እድገት ያለው ልጅ ኒውራል ሴል (የአዕምሮ የማሰብ ችሎታን የሚወስነው ሴል) በአልትራ ሳውንድ ሲታይ እድገቱ ከፍተኛ ልዩነት አለው ያሉት ዶ/ር ማስረሻ፣ ጤናማ አመጋገብ ያለው ልጅ አዕምሮው የተሻለ የመፍጠር አቅም ያለው መሆኑን፣ ጤናማ ሥርዓተ-ምግብን አግኝቶ ያላደገ ህጻን ደግሞ የአዕምሮው እድገት ውስን፣ የመፍጠር አቅሙ ያነሰ፣ በተደጋጋሚ ለበሽታ የሚጋለጥ እንደሆነ ይገልጻሉ። አያይዘውም፣ ችግሩ ህጻኑ ካደገ በኋላ በሕይወት ዘመኑ መገኘት ባለበት ቦታ እንዳይገኝ፣ በትምህርትም ሆነ በሥራው ውጤታማ እንዳይሆን፣ ጤናማ ተግባቦትና ማኅበራዊ ሕይወት እንዳይኖረው ያደርገዋል ያሉት ዶ/ር ማስረሻ፣ ይህ ችግር በአንድ ግለሰብ ብቻ ሳይወሰን የሀገር ኢኮኖሚና ሠላም ላይም አሉታዊ ጫናን እንደሚያሳርፍ፣ በአፍሪካ እየታየ ያለው የኢኮኖሚና የፖለቲካ አለመረጋጋትም ጤናማ ሥርዓተ-ምግብ ካለመኖር ጋር የተያያዘ መሆኑን ይናገራሉ።

ሥርዓተ – ምግብና ትምህርት

ሥርዓተ-ምግብና ትምህርት ከፍተኛ ቁርኝት እንዳላቸው የሚናገሩት፣ በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደሊል ከድር፣ የሥርዓተ- ትምህርቱን ዓላማ ከግብ ለማድረስ በተለይም ህጻናት ጤናማ ሥርዓተ-ምግብ እንዲኖራቸው ማድረግ ወሳኝ ነው ይላሉ። ዳይሬክተሩ እንዳሉት፣ በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህጻናት በምግብ እጥረት ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው። ይህ ደግሞ በትምህርት አቀባበላቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አለው። አንድ ልጅ ባዶ ሆዱን ትምህርት ቤት ሄዶ ለመማር ቢሞክር የሚያዳምጠው ትምህርቱን ሳይሆን ሆዱን ነው፤ የተመጣጠነ-ምግብም ሆነ የምግብ እጥረት አዕምሯዊና አካላዊ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው። በትምህርት ሚኒስቴር ጥናት መሠረት በተደጋጋሚ በትምህርት ገበታ ላይ ላለመገኘት አንዱ ምክንያት የህጻናት በአግባቡ አለመመገብ ሲሆን፣ ከትምህርት ገበታ መቅረት ደግሞ የክፍል መድገምን ያስከትላል። ይህም ከተማሪው አልፎ በትምህርት ጥራትና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖን ያስከትላል።

ለሀገር እድገት መሠረት የሆነው ትምህርት ተጎዳ ማለት የሀገር ኢኮኖሚና ህልውና አደጋ ውስጥ ገብቷል ማለት ነው የሚሉት አቶ ደሊል፣ ከዚህ አንጻር ልጆችን የተመጣጠነ ምግብ በመመገብ የትምህርት አቀባበላቸው ላይ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ሀገርን የመረከብ አቅም ያለው ትውልድን የማፍራት ተግባር ነው ይላሉ።

አቶ ደሊል እንዳሉት፣ የመቀንጨር ችግር ተማሪዎች ክፍል እንዲደግሙና የትምህርት ውጤታቸው ዝቅተኛ እንዲሆን ከሚያድርጉት ምክንያቶች አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል። ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃም እንደሚያመለክተው “መቀንጨር” 16 በመቶ ለሚሆኑት የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ትምህርት መድገም አንዱ ምክንያት ሲሆን፣ ይህ የክፍል መድገም አገራችንን በዓመት 400 ሚሊዮን ብር ለሚሆን ወጪ ይዳርጋታል። የህጻናት መቀንጨርን ለመቅረፍ ደግሞ በአመት 55 ሚሊዮን ዶላር ታወጣለች።

የሥርዓተ-ምግብ ተግዳሮቶች

ዶ/ር ማስረሻ፣ ኢትዮጵያ ጤናማ ሥርዓተ- ምግብን ከመከተል አንጻር ካለፉ ጊዜያት ይልቅ መሻሻሎች እንዳሏት አንስተው፣ ነገር ግን አሁንም ቢሆን በጣም ብዙ መሠራት ያለባቸው የቤት ሥራዎች መኖራቸውን ያስረዳሉ። ከሀገራችን ህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ካለፉ አመታት ይልቅ ጤናማ ሥርዓተ-ምግብን የማይከተሉ ቤተሰብና ህጻናት ቁጥር እየጨመረ መጥቷል ያሉት ዶ/ር ማስረሻ፣ እየጨመረ ካለው የህዝብ ቁጥርና የተመጣጠነ-ምግብ ማግኘት ካልቻሉ ህጻናት ቁጥር አንጻር ሲታይ መሻሻሉ በጣም ውስን መሆኑንና ብዙ መሥራት እንደሚያሻም ይናገራሉ። ቀዳሚው ሥራ በሥርዓተ-ምግብ እና የልጆች አስተዳደግ ላይ የማኅበረሰብን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በተለይም በገጠር አካባቢ ያለው ማኅበረሰባችን ስለ ስርዓተ-ምግብ በቂ ግንዛቤ የለውም የሚሉት ዶ/ር ካሳዬ፣ ከዚህ የተነሳ አንዲት እናት እንቁላል ሸጣ ለልጇ ብስኩት ልትገዛ ትችላለች ይላሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ሀገርም የሥርዓተ-ምግብ ችግሮችን ለመቅረፍ የምግብና የሥርዓተ-ምግብ ፖሊሲና ስትራቴጂ ወጥቶ ህብረተሰቡ የሚጠቀምበት መመሪያም መዘጋጀቱን ያነሱት ዶ/ር ካሳዬ፣ የጓሮ አትክልት ማምረት የሚችለው በገጠርም ሆነ በከተማ ያለው ማኅበረሰብ ራሱን እንዴት መጥቀም እንዳለበትና ያመረተውን ሁሉ ከመሸጥ ይልቅ ለራሱም የተሰባጠረ አመጋገብ እንዲኖረው ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ-ነገሮችን የያዙ ምግቦች ችላ እንደሚባሉ የተናገሩት ዶ/ር ካሳዬ፣ ለዚህም ከሚበሉ ምግቦች መካከል ‘ዱባ’ን በማሳያነት ይጠቅሳሉ። እርሳቸው እንዳሉት፣ ‘ዱባ’ በቫይታሚንና በቤታ ካሮቲን የበለጸገ፣ በተለይም በደም ማነስ ለሚጠቁ ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ህጻናትና እናቶች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም ብዙ ተጠቃሚ የሌለው፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ተንቆ የሚጣል

 በንጥረ-ነገር የበለጸገ የምግብ ዓይነት ነው። ይህን አመለካከት መቀየር፣ በጓሮዎቻችን ማምረት የምንችላቸውን የተለያዩ አትክልቶችን ማምረት ብንችል እና በቀላሉ የምናገኛቸውን ምርቶች መጠቀም ብንችል፣ ካለብን የተመጣጠነ-ምግብ የመመገብ ችግር መላቀቅ እንደምንችል ይናገራሉ።

በከተማ አካባቢ የተመጣጠነ-ምግብ ለመመገብ በተለይም የፍራፍሬዎችና የእንስሳት ተዋጽዖዎች ዋጋ ከፍተኛ መሆኑንም ዶ/ር ካሳዬ አንስተዋል፣በተለይም እንደ ብርትኳን፣ ሙዝ፣ አፕል የመሳሰሉ ፍራፍሬዎች እና እንደ ስጋ፣ አሳና ዶሮ ያሉ የእንስሳት ተዋጽዖዎች ዋጋ ከብዙኃኑ ማኅበረሰብ የኢኮኖሚ አቅም አኳያ ውድ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ይህ በሆነበት ሁኔታ ማኅበረሰባችን ግንዛቤው ቢኖረው እንኳ፣ የተመጣጠነ-ምግብ መመገብ እንደማያስችለው ተናግረዋል። ስለሆነም፣ እነዚህን በንጥረ-ነገር የበለጸጉ ምግቦች በብዛት እንዲመረቱ ማድረግ፣ ዋጋቸውን የማኅበረሰቡን ኪስ የማይፈትኑበትን ሁኔታ መፍጠር፣ ቶሎ የማይበላሹበትንም ዘዴ መጠቀምና ከብክነት መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የሥርዓተ-ምግብ ችግርን ለመቅረፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት

የምግብና የሥነ-ምግብ ችግሮች በአንድ መሥሪያ ቤት ብቻ የሚፈቱ አይደሉም ያሉን ዶ/ር ማስረሻ፣ ለተግባራዊነቱ ጠንካራ ትስስር፣ ትኩረትና በጀት እንደሚጠይቅ፣ እና ውጤት ማምጣት የሚቻለው የተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተውና ተናበው ሲሰሩ እንደሆነ አጽንዖት ሰጥተው ይናገራሉ። በቅርቡ በጤና፣ በትምርትና በግብርና ዘርፍ ያሉ ተቋማት የተሳተፉበት የሥርዓተ-ምግብ መመሪያ መዘጋጀቱን አንስተው፣ መመሪያው ጤናማና ረጅም እድሜ የሚኖር ህብረተሰብን መፍጠር ዓላማው ያደረገ፣ ለሁሉም የህብረተሰብ አካባቢዎች የሚሆንና በግለሰብና በቤተሰብ ደረጃ አገልግሎት ላይ የሚውል መመሪያ እንደሆነ ገልጸዋል። የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም በህብረተሰብ ጤና ላይ እንደሚሠራ ተቋም በሥርዓተ-ምግብ ላይ በርካታ የምርምርና የማኅበረሰብ ግንዛቤን የሚጨምሩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ተማሪዎችን በትምህርት ቤት የመመገብ ጥረት በሀገራችን በ1987 እንደተጀመረ ያወሱት አቶ ደሊል፣ በአሁኑ ጊዜ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል አገልግሎቱ በተደራጀ ሁኔታ እየተሰጠ እንደሚገኝ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የትምህርት ቤት ምገባ ኤጀንሲን እንዳቋቋመ ጠቅሰዋል። እሳቸው እንዳሉት በዚህ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ሰባት ሚሊዮን ህጻናት ተጠቃሚ ናቸው። ይህ ቁጥር በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የተወሰነ ሲሆን፣ በቀጣይም የምገባ ፕሮግራምን በክልሎችም ተግባራዊ ለማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቅድመ ሁኔታዎችን እያመቻቸና ግንዛቤ ከመፍጠር አንጻርም በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ አቶ ደሊል አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትም በሥርዓተ-ምግብ ዘርፍ በርካታ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑን እንደነገሩን እንደ ዶ/ር ካሳዬ ገለጻ፣ በኢንስቲትዩቱ ስር የተቋቋመው የምግብ ሳይንስና ሥነ-ምግብ ዳይሬክቶሬት በዋናነት የግብርና ምርቶችን የንጥረ-ነገር ይዘት የማጥናት እና ለታለመላቸው ዓላማ ለማዋል የሚያስችል ጥራት እንዳላቸው የማረጋገጥ ሥራ ይሠራል፤ የምግብ ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎችን ይፈጥራል፤ በሥነ-ምግብ የበለጸጉ ምግቦችን እሴት በመጨመርና በድህረ-ምርት ብክነት መቀነስ ላይም ትኩረት ያደርጋል፣ በዚህ ላይ የተመሰረቱ ቴክኖሎጂዎችንም ያወጣል። እንዲሁም በሀገራችን በባህላዊ መንገድ የሚዘጋጁ ምግቦች ንጥረ- ነገራቸው ሳይባክን እና ሳይጠፋ አዘገጃጀታቸውን የማሻሻል፣ በሰብል ምርምር ዘርፍ የሰብሎችን ምርታማነት የሚጨምሩና ከበሽታ የሚከላከሉ አዳዲስ ዝርያዎችን አብሮ የማሻሻል ሥራም ያከናውናል።

በተጨማሪም፣ የምግብ ጥራትና ደህንነት ላይ በማተኮር የምግብ ተወዳዳሪነትና የሥርዓተ- ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችንም የማውጣት እቅድ ይዞ እየሰራ እንዳለም ዶ/ር ካሳዬ ተናግረዋል። አያይዘውም አንዳንድ ምግቦች በተለይም አትክልትና ፍራፍሬዎች ከምርት ሂደት ጀምሮ ሊበከሉ እንደሚችሉ አንስተዋል፤ እርሳቸው እንዳሉት የብክለቱ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ በርካታ ፋብሪካዎች መኖራቸውና ተረፈ- ምርታቸውን ወደ ወንዝ መጨመራቸው ነው፤ እነዚህን ወንዞች በመጠቀም የሚመረቱ ምርቶች ለጤና ጎጂ የሆኑ አላስፈላጊ ማዕድናትን ይይዛሉ። እነዚህ አላስፈላጊ ማዕድናት በተፈጥሯቸው በውሃ ቢታጠቡም ሆነ ቢቀቀሉ የማይጠፉ በመሆናቸው በዚህ ሁኔታ የተመረቱ ምርቶችን መጠቀም ጤናን ይጎዳል። በምርት ሂደት ጥቅም ላይ የሚውሉ እንደ አረምና ተባይ ማጥፊያ የመሳሰሉ ኬሚካሎችም የምግብን ጥራትና ደህንነት ሊያጓድሉ እንደሚችሉ የጠቀሱት ዶ/ር ካሳዬ፣ ይህን መነሻ በማድረግ ዳይሬክቶሬቱ፣ እየተመረቱ ያሉ ምርቶች ለጤናችን ተስማሚ ናቸው? ወይስ አይደሉም? የሚለውን ጥናት እንደሚያካሂድ፣የጥናቱን ውጤትም ለሚመለከተው የመንግሥት አካል እንደሚያሳውቅና እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ ችግር ካገኘም ጥቆማ እንደሚሰጥ በማሳወቅ ሐሳባቸውን ቋጭተዋል።

እኛም፣ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች አገር ናትና ሀብትን በአግባቡ በመጠቀምና የማኅበረሰባችንንም ግንዛቤ በተገቢው መንገድ በማሳደግ፣ ዜጎች ጤናማ ሥርዓተ- ምግብን እንዲከተሉ በማድረግ ጤንነቱ የተጠበቀ ህብረተሰብ መፍጠር የሁሉም አካል የተቀናጀ ተግባር ነው! እንላለን፡፡

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

ዘመን መጽሔት ግንቦት 2014 ዓ.ም  

Recommended For You