ለትምህርት ውጤታማነት ትምህርትን የሚመራው ተቋምና የመሪዎች ጥንካሬ፣ የትምህርት ሥርዓቱ፣ ትምህርት ቤቶች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጆችና ጠቅላላው ማኅበረሰብ የየራሳቸው ድርሻ አላቸው። የመምህራን ሚና ደግሞ ከሁሉ ይልቃል። “መምህርነት” በሥነ-ምግባሩ የታነፀ፣ በእውቀት የደረጀ፣ ሀገርን የመረከብ ዝግጁነትና አቅም ያለው በሳል ትውልድን የማፍራት ኃላፊነት የተጣለበት ሙያ ነው። ታዲያ ይህ ከባድ ኃላፊነት የተጣለበት መምህር ትምህርቱን ከማስተማር ባለፈ፣ በሁለንተናው ለተማሪዎቹ ምሳሌ መሆን የሚችል፣ ዕውቀትና መልካም ሥነ-ምግባርን የተላበሰ ሊሆን ይገባዋል።
ትምህርት በተቋም ደረጃ ሥርዓት ተበጅቶለት መሰጠት ከመጀመሩ ብዙ ዓመታት በፊት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለብዙዎች ተምሳሌት መሆን የቻሉ፣ በተማሪዎቻቸው ሕይወት ላይ የማይጠፋ በጎ አሻራን ያሳረፉና እያሳረፉ ያሉ የሀገር ባለውለታ መምህራን በርካቶች ናቸው። እነዚህ መምህራን በተለያየ የሙያ መስክ ተሰማርተው ስኬታማ የሆኑ፣ ከራሳቸው አልፈው የሀገር መከታ ባለሙያዎችን/ ምሁራንን አፍርተዋል። ከእነዚህ ምስጉን መምህራን በተቃራኒ፣ በተለይም በዚህ ዘመን፣ መምህርነት የሚጠይቀውን እውቀትና ሰብዕና ያላሟሉ፤ ትውልድ የመቅረጽ አቅም የሌላቸው፣ ለሙያቸው ተገቢውን ክብር ያልሰጡ መምህራን መኖራቸው ይሰማል።
የአራት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ሰጠኝ ኃ/ ገብርዔል፣ ልጆቻቸው አሁን እስከደረሱበት የትምህርት ደረጃ ድረስ በተለያዩ ትምህርት ቤቶችና መምህራን መማራቸውን ጠቅሰው፤ ከልጆቻቸው ጋር የጠበቀ ተግባቦት ስላላቸው ስለ ውሏቸውም ሆነ መምህራኖቻቸው በግልጽ እንደሚያወሩ ይገልጻሉ። ለተማሪዎቻቸው እውቀትን ለማካፈል፤ በሥነ-ምግባርም ለማነጽ የሚጥሩ በርካታ ትጉህ መምህራን እንዳሉ ሆነው፤ በመማሪያ ክፍሎቻቸው ቁጭ ብለው ከእነርሱ ለመማር ዝግጁ ሆነው ለሚጠብቁ ተማሪዎቻቸው የሚመጥን ዝግጅት የማያደርጉ፣ የተሻሉ ሆነው መገኘት የሚያቅታቸው፣ ከአለባበስና ከንግግር አንጻርም በበሳል ተማሪዎች ትዝብት ውስጥ የሚወድቁ፣ አልፎ አልፎም ከሴት ተማሪዎቻቸው ጋር አላስፈላጊ ተግባቦት የሚፈጥሩ መምህራን ጥቂት አለመሆናቸውን አቶ ሰጠኝ ይናገራሉ፤ አያይዘውም “ተማሪ የመምህሩ ውጤት ነውና የአቅምና የሥነ-ምግባር ጥያቄ የሚነሳበት መምህር በእውቀትና በሥነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ሊያፈራ አይችልም” የሚል አስተያየት ይሰጣሉ።
የ23 ዓመታት የማስተማር ልምድ ያላቸውና በአሁኑ ሰዓት በሰበታ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የማኔጅመንት ኮርስ እየሰጡ የሚገኙት መምህር ኮስትር ጉዱ በበኩላቸው፣ የሀገራችን የትምህርት ጥራት ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ መግባቱን አንስተው መምህራን ደግሞ ለትምህርት ጥራት ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን የተለያዩ የጥናት ውጤቶች እንደሚያመላክቱ ይጠቅሳሉ። ከጥናቶቹ በመነሳትም፣ የትኛውም ቴክኖሎጂና፤ የትምህርት መሠረተ ልማት ባልተሟላበት ሁኔታ አንድ አስተማሪ በሚያስተምረው መስክ በሚገባ ተዘጋጅቶ ተማሪዎቹን ማስተማር ከቻለ ተማሪዎቹን 75 ከመቶ ውጤታማ ማድረግ እንደሚችል ይጠቁማሉ። ከዚህ በመነሳት መምህር ምን ያህል ተማሪዎቹን ውጤታማ የማድረግ እድል እንዳለው መረዳት እንችላለን ያሉት መምህር ኮስትር፣ ከሥነ- ምግባር አኳያም መምህር በቅድሚያ ሙያውን የሚወድ፤ ለሙያው ክብር የሚሰጥ መሆን አለበት ብለዋል። እንደ እርሳቸው ሐሳብ መምህር ከሁሉ አስቀድሞ ለሙያው ዋጋ የሚሰጥ ከሆነ ራሱን ለማብቃት ጥሩ ችሎታና ሥነ-ምግባር ያለው ለተማሪዎቹ ዓርዓያ የሆነ መምህር መሆን ይችላል።
አቶ ሰጠኝ፣ ልጆች ትምህርት ቤት የሚሄዱት የቀለም እውቀት ብቻ ይዘው ለመምጣት ብቻ አይደለም፤ በሕይወታቸው፤ በቤተሰብም ሆነ በማኅበረሰብ ውስጥ ሲኖሩ መረዳት ያለባቸውን ተረድተው፣ ማኅበራዊ ኃላፊነት ያለባቸው መሆናቸውን እንዲያውቁ የሚያደርጋቸውን እውቀትም ጭምር ለመቅሰም በመሆኑ መምህራን ይህንን እውቀት ሊሰጡ የሚችሉት ኖረው በማሳየትም ጭምር ሊሆን ይገባል ይላሉ፡ መምህር ኮስትርም ይህንን ሐሳብ ሲያጠናክሩ ማስተማር ማለት መናገር ብቻ አይደለም፤ መምህሩ በሚያስተምረው የትምህርት መስክ ጥልቅ እውቀት ያለው፤ እውቀቱን ለተማሪዎቹ በሚገባቸው አካሄድ ማስረዳት የሚችል ሊሆን እንደሚገባው ሁሉ ከተማሪዎች ጋር ባለው ግንኙነትም ሆነ በቤተሰባዊና ማኅበራዊ ሕይወቱ ምሳሌ የመሆን አቅም ያለው ሊሆን ይገባል በማለት ይናገራሉ።
የተማሪ የመጀመሪያ ዓርዓያ መምህሩ ነው ያሉን፣ መምህር ኮስትር፣ እንዲያውም ብዙ ልጆች በለጋነት እድሜያቸው ምን መሆን ትፈልጋላችሁ ለሚለው ጥያቄ መልሳቸው መምህር መሆኑን ያነሳሉ፤ እሳቸው እንዳሉት፣ በተለይ ቀደም ባለው ጊዜና አሁንም በገጠር አካባቢዎች “መምህር” በስሙ የማይጠራ በተማሪዎቹና በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚወደድና የሚከበር ነው። ስለሆነም መምህሩ ትውልድ የሚሠራበትን ክቡር ሙያ ማክበር፣ በንባብ አዕምሯዊ አቅሙን ማሳደግ፣ በአካላዊ እንቅስቃሴ አካላዊና ሥነ-ልቡናዊ አቋሙን ማጎልበት፣ ሙያዊ ግዴታውን በታማኝነት መወጣት ይጠበቅበታል የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
አቶ ሰጠኝም፣ እኔ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ተማሪዎች መምህራኖቻቸውን የሚያከብሩ መምህራኑም በንግግር፣ በአለባበስና ባላቸው እውቀት ለተማሪዎቻቸው ዓርዓያ የሆኑ ተወዳጆች ነበሩ በማለት አሁንም በርካታ እንዲህ ያሉ መምህራን መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ ቢሆንም፣ ልጆቻቸው “እገሌ እኮ አይችልም” ብለው ስማቸውን የሚያነሷቸው መምህራን እንዳሉ በመጥቀስ የሚመለከተው አካል የመምህራን አቅም ላይ በሚገባ በመስራት ትውልድን ከውድቀት እንዲታደግ ጠይቀዋል።
በቅርቡም የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የመምህራን አቅምን በተመለከተ ከፍተኛ ችግር መኖሩን አንስተው በሚያስተምሩበት የትምህርት ዓይነት ፈተና ተሰጥቷቸው ከግማሽ በላይ ያገኙ መምህራን 30 ከመቶ ያህሉ ብቻ መሆናቸውንና ተቋሙ ለመምህራን አቅም ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ መግለጻቸው ይታወሳል።
የመምህራን አቅም ከትምህርት ጥራት ጋር የተቆራኘ መሆኑን የሚናገሩት በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራን ትምህርት አመራር ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ሞረዳ፣ ከትምህርት ተደራሽነትና ፍትሃዊነት አኳያ ባለፉት ጊዜያት የተመዘገቡ ውጤቶች አመርቂ መሆናቸውንና በአሁኑ ወቅትም በየገጠር ቀበሌው ቢያንስ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት እንደሚገኝ፣ በወንድና ሴት ተማሪዎች መካከል ይታይ የነበረው የተሳትፎ ምጣኔ ልዩነትም ላለፉት 30 ዓመታት በእጅጉ እየጠበበ መምጣቱን ይጠቅሳሉ፤ ከዚሁ ጎን ለጎን የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያግዙ ተግባራትም ታቅደው ሲተገበሩ መቆየታቸውንም አንስተዋል። ለየትምህርት ደረጃው ተመጣጣኝ የትምህርት ዝግጅትና ብቃት ያላቸው መምህራንን ለማፍራት የቅድመ ሥራና የሥራ ላይ ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ሥልጠና መርሀ ግብሮች ተቀርጸው ተግባራዊ ቢሆኑም፣ እየተሰጡ ያሉ የቅድመ ሥራና የሥራ ላይ የሥልጠና መርሃ ግብሮች በመምህራኑ የሙያ ብቃትና ሥነ-ምግባር ላይ እያመጡት ያለው ለውጥ የተፈለገውን ያህል አለመሆኑን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር ያስጠናቸው ጥናቶች እንዳመላከቱ አቶ ብርሃኑ ይናገራሉ። በጥናት ግኝቶቹ መሠረት በቅድመ ሥራም ሆነ በሥራ ላይ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና መርሀ ግብሮች ዙሪያ መስተካከል ያለባቸው ክፍተቶች ሰፊ ናቸው።
ከመምህራን የቅድመ ስራ ስልጠና ጋር ተያያዞ ለመጀመሪያና ሁለተኛና ደረጃ መምህርነት የሚመለመሉ ብዙዎቹ እጩዎች በአካዳሚክ ብቃትና ባላቸው የማስተማር ሙያ ፍላጎት መሠረት አለመሆኑ ወይም እጩዎቹ ሥራ ለመያዝ በሚል ብቻ የሚቀጠሩ መሆናቸው፤ በማሰልጠኛ ተቋማት የሚሰጠው ትምህርት በፅንሰ ሐሳብ የታጨቀ መሆንና በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ የሚሰጡ ትምህርቶች በትምህርት ቤት ደረጃ በመማር ማስተማር ሂደት ከሚከናወኑ ተግባራት ጋር አለመተሳሰር፤ የመምህራን ማሰልጠኛ ሥርዓተ ትምህርትና የአጠቃላይ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት የተናበቡ ሆነው አለመዘጋጀት፣ የመምህራን ማሰልጠኛ ሥርዓተ ትምህርት ይዘቶች በኮርሱ አጠቃላይ እውቀት ላይ ያተኮሩ መሆን፤ የአሰልጣኝ ተቋማቶቻችን የሥልጠና ሥነ ዘዴዎችና አቀራረቦች ሰልጣኝ ተኮር ባለመሆናቸው ምክንያት፣ እጩ መምህራኑ በቂ፣ ውጤታማና ተጨባጭ የማስተማር ሥነ ዘዴ ክህሎትን ጨብጠው መውጣት አለመቻላቸው፤ ከሁሉም በላይ በሥራ ላይ የነበረው የመምህራን ሥልጠና ሥርዓተ ትምህርት ይዘቶች የ21ኛው ክፍለ ዘመን የመምህርነት ሙያ ስልጠና የሚፈልጋቸውን ብቃቶች፣ ማለትም፡- በጥልቀት ማሰብን ወይም መመራመርን (critical thinking)፣ የራስን እውቀት ማዳበር (self-knowledge)፣ ሰዎችን የመምራት እና የማስተዳደር ክህሎትን (people management skills) እና የተግባቦትና የጽብረቃ ክህሎትን (communication and reflective skills) ያሟላ አለመሆን በጥናቶቹ ከተጠቀሱት ክፍተቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
አቶ ብርሃኑ፣ መምህራኑ በሥራ ላይ እያሉ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው የተከታታይ የሙያ ማሻሻያ /ተሙማ/ መርሀ ግብርን በተመለከተም የነበሩ ክፍተቶች በጥናት መለየታቸውን አንስተዋል፤ ቀደም ሲል ተዘጋጅተው ሥራ ላይ እንዲውሉ የተደረጉት የተሙማ ማዕቀፍ እና ቱልኪት አቀራረብ ውስብስብ መሆን፤ መምህራን “መርሀ ግብሩ ይጠቅመናል፣ ብቃታችንን ያጎለብትልናል” ብለው ከመውሰድ ይልቅ፣ በእነርሱ ላይ ጫና ለመፍጠርና ጊዜያቸውን ለመሻማት ታስቦ የተዘጋጀ አድርጎ የመውሰድ፤ የመምህራን የሙያ ብቃት ማጎልበቻ ሥራዎችን / ሥልጠናዎችን/ በቀጥታ ከጥቅማ ጥቅም ጋር ማያያዝ ወይም ጥቅም ካላስገኘልኝ ለምን ጊዜዬን አባክናለሁ ብሎ ማሰብ፤ በመምህራን የሙያ ማሻሻያ ሥልጠናዎች በሙያ ብቃት ምዘና ውጤት እና በደረጃ እድገት መካከል ትስስር እንዲኖር አለመደረግ፤ የመምህራን በግል ተከታታይ የሙያ ማሻሸያ የቅድሚያ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ለይቶ ለማውጣት መቸገር፣ በዚህም የተነሳ በየዓመቱ ተደጋጋሚነት ያላቸውን የተሙማ እቅድ አዘጋጅቶ ለመተግበር መሞከር፤ የመርሀ ግብሩን አተገባበር በባለቤትነት የሚከታተል፣ የሚደግፍና ወቅታዊ ግብረ መልስ የሚሰጥ አስተባባሪ አካል በየመዋቅር ደረጃው አለመኖር መርሃ ግብሩን ለመተግበር በተካሄዱ ጥናቶች የተለዩ ክፍተቶች መሆናቸውን ዘርዝረዋል።
የተካሄዱ ጥናቶች ከዚህ በፊት የነበሩብንን ችግሮች ፍንትው አድርገው ያሳዩ ነበሩ ያሉን፣ በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት አመራር ልማትና አስተዳደር ዳይሬክተር ወ/ሮ አሰገደች መሬሳ ሲሆኑ፣ እንደ እርሳቸው ሐሳብ፣ ለትምህርት ተደራሽነትና ፍትሃዊነት ሲደረግ የነበረው ጥረት ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረከተ ነው። ይሁን እንጂ፣ አጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ሥርዓታችን በተለይ በጥራቱ በኩል ከፍተኛ ጉድለት የታየበት መሆኑ ተገምግሞ በጥናትም ተረጋግጦ የትምህርት ሥርዓቱ አሁን ሙሉ በሙሉ ለውጥ ውስጥ ነው ከጥናት ውጤቶቹ በመነሳት በመምህራን፣ በወላጆች፣ በተማሪዎችና በማኅበረሰቡ ሲነሱ የነበሩ የትምህርት ጥራት ችግሮች በቀጥታ ከመምህራን ትምህርት ስልጠና ጋር ቁርኝት ያላቸው መሆኑ እንደታመነበት ገልጸዋል።
መምህራን ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውም ባለሙያ በተሰማራበት የስራ ዘርፍ ያለውን ሙያ ማሻሻል እንደሚጠበቅበት ያነሱት ወ/ሮ አሰገደች፣ መምህራን ደግሞ የማስተማር ሙያ ላይ ያሉ እንደመሆናቸው በየጊዜው አቅማቸውን ማሳደግና ከወቅቱ ጋር ማስኬድ እንዳለባቸው ይናገራሉ፤ አያዘውም ከዚህ በፊት ስንጠቀምበት የነበረው የተከታታይ ሙያ ማሻሻያ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ችግሮች የነበሩበት ነበር በማለት የአቶ ብርሃኑን ሐሳብ ያጠናክራሉ። መርሃ ግብሩ መምህራን ስሩ ስለተባሉ የሚሰሩት ሳይሆን ወደውና ፈልገውት፤ “ተለውጬ ተማሪዎቼን ለመለወጥ ይጠቅመኛል” ብለው የሚሰሩት እንዲሆንና በየሙያ ዘርፉ በሀገር አቀፍ ደረጃም አሰልጣኞች እንዲኖሩ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት (ከ2008-2011ዓ.ም) ለመጀመሪያ እና ለሁለተኛ ደረጃ መምህራን እና የትምህርት አመራሮች የሙያ ብቃት ምዘና ሲሰጥ መቆየቱን ያወሱት አቶ ብርሃኑ፣ የምዘናው ውጤት ትንተና ሪፖርት እንደሚያሳየው የብቃት ምዘናውን ከወሰዱ መምህራንና የትምህርት አመራሮች መካከል ከፊሎቹ ከተቀመጠው ስታንዳርድ በታች ውጤት ማስመዝገባቸውን ይናገራሉ፣ ለአብነት፡ በ2010 ዓ.ም ለነባር /ሥራ ላይ ላሉ/ መምህራን በተሰጠው የብቃት ምዘና አዲስ አበባ፣ ደሬዳዋ፣ ሀረሪ እና አማራ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ሲሆን፣ የቀሪዎቹ ክልሎች ውጤት በአማካይ ከ50% በታች መሆኑ በምዘና ውጤት ትንተና ሪፖርት ላይ ተመላክቷል። በተለይም የጋምቤላና ሱማሌ ክልሎች የብቃት ምዘና ውጤት ዝቅተኛነት ሁኔታው ልዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑ መመላከቱን ገልጸዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ የተሰጠው የብቃት ምዘና ውጤቱ በትምህርት እርከን ሲታይ የ2ኛ ደረጃ መምህራን ውጤት ከመጀመሪያ ደረጃ መምህራን የተሻለ ሲሆን፣ በ2011ዓ.ም በተሰጠው የብቃት ምዘና የሁለተኛ ደረጃ መምህራን አማካይ የማለፍ ምጣኔ 42 ከመቶ፣ የመጀመሪያ ደረጃ መምህራን የማለፍ ምጣኔ ደግሞ 28 ከመቶ የነበረ መሆኑን ከብቃት ምዘናው የውጤት ትንተና ሪፖርት መገንዘብ ተችሏል።
እንደአጠቃላይ ከ2008 እስከ 2011ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ብዛታቸው 319ሺ 540 የአንደኛ ደረጃ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች እንዲሁም 98ሺ 877 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች፣ በድምሩ 418ሺ 417 መምህራንና የት/ቤት አመራሮች የሙያ ብቃት ምዘና የወሰዱ ሲሆን፣ ከእነዚህ
መካከል 76 ከመቶ የሚሆኑት ከአጥጋቢ በታች ውጤት ያስመዘገቡ መሆናቸው በውጤት ትንተና ሪፖርቱ ተመላክቷል። በሪፖርቱ እንደተመላከተው የ2ኛ ደረጃ መምህራን በአንፃራዊነት ከአንደኛ ደረጃ መምህራን የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ቢሆንም፣ በመምህራን የብቃት ስታንዳርድ ላይ ከተመለከተው መስፈርት አንፃር ሲታይ በሁለቱም የትምህርት ደረጃዎች የሚያስተምሩ መምህራን ያስመዘገቡት ውጤት አጥጋቢ አለመሆኑን አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል።
በመሆኑም፣ መምህራን በተከታታይ የሙያ ማሻሸያ መርሀ ግብሮች ላይ በመሳተፍ ራሳቸውንና የሥራ ባልደረቦቻቸውን የሚያበቁበት የሥራ ላይ የአቅም ማጎልበቻ መርሀ ግብሮችን አጠናክሮ ማስተግበር የትምህርት መዋቅር (ከትምህርት ሚኒስቴር እስከ ትምህርት ቤት) ኃላፊነት መሆኑን አቶ ብርሃኑ ያሰምሩበታል፤ መምህራንም በሙያቸው ሀገራዊና ግላዊ ፋይዳ ያላቸው ውጤቶችን ለማስመዝገብ በየጊዜው የራሳቸውን አቅም ማጎልበት፣ ወቅቱና ያሉበት የትምህርት ደረጃ የሚጠይቀውን ብቃትና የሙያ ሥነ-ምግባር መላበስ ይጠበቅባቸዋል ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ በዚህ ረገድ የተከታታይ ሙያ ማጎልበቻ መርሀ ግብሮችንና ተያያዥ የሥልጠና ማቴሪያሎችን ከመምህራን የሙያ ብቃት ስታንዳርድ እንዲሁም እንደ የደረጃ እድገትና የትምህርት ዕድል ያሉ የመምህራን ጥቅማ ጥቅም ማዕቀፍ ጋር አስተሳስሮ የማዘጋጀትና ወደ ተግባር የመቀየር ሥራ መሠራት እንደሚገባው ገልጸዋል። ከዚህም ባለፈ “የሙያ ግዴታቸውን በብቃትና በኃላፊነት ስሜት የሚወጡ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች የሚወደሱበት እንደ አስፈላጊነቱም የሚሸለሙበት፤ ከዚህ ውጪ የሆኑት ደግሞ የሚኮነኑበትና ወደ መስመር እንዲገቡ የሚደረግበት ሥርዓት ተዘርግቶ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባ እናምናለን፤ በዚህም አግባብ እየሠራን እንገኛለን” ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በትምህርት ሥርዓቱ እየተካሄዱ ያሉ ለውጦችን ማንሳቱ ተገቢነት እንደሚኖረው የጠቀሱት አቶ ብርሃኑ፣ ከአሁን ቀደም በተለያየ አግባብ እንደተገለፀው ላለፉት ዓመታት ሲሰራበት የነበረው የ4+4+2+2 የትምህርት መዋቅር ወደ 6+2+4 መቀየሩንና፤ ይህም ቀደም ሲል በ10ኛ ክፍል ደረጃ ሲጠናቀቅ የነበረው የአጠቃላይ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ወደ 12ኛ ክፍል ከፍ እንዲል መደረጉን አስታውሰዋል። እርሳቸው እንዳሉት፣ ከትምህርት መዋቅር መቀየርና የአጠቃላይ ሥርዓተ ትምህርት በአዲስ መልክ መዘጋጀት ጋር ተያይዞም የየትምህርት ደረጃውን የመምህራን የትምህርት ዝግጅት ማሻሻል አስፈላጊ ሆኗል። በዚህም አግባብ የቅድመ አንደኛ ደረጃ መምህራን ከሠርተፊኬት ወደ ዲፕሎማ (12+2)፣ የአንደኛ ደረጃ መምህራን ከዲፕሎማ ወደ መጀመሪያ ዲግሪ፣ የ2ኛ ደረጃ መምህራን ከመጀመሪያ ዲግሪ ወደ ማስተርስ ዲግሪ የትምህርት ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ አቅጣጫ ተቀምጦ ለተግባራዊነቱ ተገቢ ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛሉ።
መምህራንን ለሚያስተምሩበት ደረጃ የሚመጥኑ እንዲሆኑ ለማድረግም ሰፊ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ወ/ሮ አሰገደች የገለፁ ሲሆን፣ በዚህ መሠረት፣ ከዚህ ቀደም በነበረው የትህርትና ስልጠና ፖሊሲ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን፣ ዲፕሎማ የትምህርት ደረጃ እንዲኖራቸው፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መምህራን ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪ እንዲኖራቸው እንዲሁም የቅድመ አንደኛ ደረጃ መምህራንም በዘርፉ የሚመጥን የትምህርት ደረጃ እንዲኖራቸው፣ የትምህርት ቤት አመራሮችም በዛው ልክ ለደረጃው ብቁ የማድረግ ሥራ በሰፊው ሲሰራ የነበረ ሲሆን፣ በዚህም በትምህርት ደረጃ ማሻሻልና መምህራንን ለደረጃው ብቁ ከማድረግ አኳያ መልካም ውጤቶች ተመዝግበዋል፤ የመጀመሪያ ደረጃን ስናይ ከ91 ከመቶ በላይ ዲፕሎማ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትንም ስናይ በወቅቱ ብቁ የሆኑ ከ85 ከመቶ በላይ ብቁ የሆነ የትምህርት ደረጃ ያላቸው፤ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለደረጃው ብቁ ለማድረግ በተሰራው ሥራ ከ80 ከመቶ ያህሉ አመራር ለደረጃው ብቁ እንዲሆኑ ተደርጓል፤ ሌሎች በርካታ ተያያዥ ስራዎችም ሲሰሩ ቆይተዋል፤
በአጠቃላይ ለመማር ማስተማር ውጤት መሻሻል የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ብቃት ወሳኝ መሆኑ እሙን መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ሂደት ድርሻ ያላቸው ተዋንያኖች ብዙ መሆናቸውን አቶ ብርሃኑ ይገልጻሉ። ሙያቸውን የሚያከብሩና ብቃት ያላቸው መምህራን፣ ጠንካራ የትምህርት ቤት አመራር፣ ምቹ የትምህርት ቤት አካባቢ (ቤተ መጽሐፍት፣ ላቦራቶሪ ወዘተ.) ፣ የ WASh Facilities፣ መልካም የትምህርት ቤትና ወላጅ ግንኙነት፣ የተማሪና መምህራን ሥነ-ምግባር፣ ወዘተ… ለትምህርት ጥራት ማረጋገጥ ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮች ናቸው። ከእነዚህ መካከል የመምህራን ድርሻ የላቀ ሲሆን፣ ከዚህ መሠረታዊ ግንዛቤ በመነሳት በቀጣይ በቅድመ ሥራም ሆነ በተከታታይ የሥራ ላይ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠናዎች የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮችን አቅም የማጎልበት ሥራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራ ይሆናል። የተለያዩ የሥልጠና ሞዴሎችን በመጠቀም የመምህራን የትምህርት ደረጃን የማሻሻል፤ የሙያ ብቃት ምዘና የውጤት ትንተና ሪፖርት እና የኢንስፔክሽን ግኝቶችን እንደዚሁም የሥልጠና ፍላጎት የዳሰሳ ጥናት ግኝቶችን መሠረት ያደረጉ የትምህርት ደረጃ ማሻሻያ ሥልጠና እና ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ አጫጭር የሥልጠና መርሃ ግብሮች ተቀርጸው ተግባራዊ የሚደረጉ ይሆናሉ። በተጨማሪም፣ በትምህርት ልማት ዙሪያ በተለይም በመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት ዙሪያ አተኩሮ የሚሰራ ልዩ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ይኖረናል። ይህ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቷ እየተሰጡ ያሉ የቅድመ ሥራና የሥራ ላይ ሥልጠና መርሀ ግብሮችን ውጤታማነት በየጊዜው እየፈተሸ ክፍተቶችን ከመለየት ባሻገር ከሚመለከታቸው የሚኒስቴር መ/ቤቱ የሥራ ክፍሎች ጋር በመሆን ተገቢነትና ጥራት ያላቸው የረጅምና የአጭር ጊዜ የሥልጠና መርሀ ግብሮችን ይቀርፃል፣ በትግበራውም ላይ የሚሳተፍ ይሆናል። በዚህ ልክ ከተሠራ በመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮቻችን ላይ የሚስተዋሉት የብቃትና የሥነ- ምግባር ችግሮች እንደሚቀረፉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
የትምህርት ጥራት ጉዳይ በመምህራን ላይ ብቻ የሚጣል አለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ በተለይ ወላጆች ልጆቻቸውን መምህሩ ላይ ብቻ ከመጣል ይልቅ በቅርበት መከታተል፤ ልጆቻውን ከሚስተምሩበት ትምህርት ቤት ጋር ቅርብ ተግባቦት ሊኖራቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለትምህርት ጥራት መምህሩ ወሳኝ ሚና እንዳለው አጽንዖት የሰጡት ወ/ሮ አሰገደች ደግሞ ለመምህራን፣ “ትውልድን የመቅረጽ ኃላፊነት ተጥሎባችኋልና ራሳችሁን ለማሻሻል ጥረት ማድረግ፣ ተነሳሽነትና ብቃታችሁን ማሳደግ፤ ሙያችሁንም ወዳችሁ ማገልገል ይጠበቅባቸዋል” የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።
ዘመን መጽሔትም፣ “አንድ ፋብሪካ ያመረተው ምርት ቢበላሽ፣ ምርቱን በድጋሚ አስተካልሎ መስራት፤ በተሻለው መተካት ይቻላል፤ አስተማሪ የሚያመርተው ደግሞ ትውልድ ነው፤ ትውልድ ከተበላሸ በሌላ እንተካው ማለት አንችልም፤ የትውልድ ብልሽት የሀገር ብልሽት ነው! ስለሆነም የመምህራን አቅምና ሥነ-ምግባር ትልቅ ትኩረት ሊሰጠውና ሊሠራበት የሚገባ ነውና ከመምህሩ ጀምሮ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት” በሚለው የመምህር ኮስትር መልዕክት ጽሑፏን ቋጨች።
ዮርዳኖስ ፍቅሩ
ዘመን መጽሔት ግንቦት 20 ቀን 2014 ዓ.ም