ተስፋ የተጣለበት የመስኖ ስንዴ የት ደርሷል?

ግብርና የሀገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው። ግብርና፣ 27 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ወይም 34 ነጥብ አንድ በመቶ የጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ድርሻን የሚይዝ፣ 79 በመቶ ለሚሆኑ ዜጎች መተዳደሪያ ነው። በተመሳሳይ መጠን 79 በመቶ የሚሆነውን የውጭ ንግድ ገቢ የሚሸፍን እና ለአገር ውስጥ ኢንቨስትመንትና ገበያም ቀዳሚ የጥሬ እቃ ምንጭ መሆኑን “የግብርና እና የገጠር ልማት ትራንስፎርሜሽን በኢትዮጵያ ተግዳሮቶቹ፣ አበረታች ሁኔታዎች እና አስፈላጊ የማሻሻያ እርምጃዎች” በሚል በ2012 በዶክተር ጌታቸው ድሪባ የተዘጋጀው ጽሑፍ፣ የግብርና ሚኒስቴርን ጠቅሶ አስፍሯል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ በምርት መጠኑ ከጤፍ፣ በቆሎና ማሽላ ቀጥሎ በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የስንዴ ሰብል ምርታማነትን በ2011 ከነበረው ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በ2015 ወደ አራት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ለማሳደግ ዕቅድ ይዟል። እንዲሁም፣ በ2011 ወደ ሀገር ውስጥ የገባውን አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በ2015 ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት ማቀዱን ይፋ አድርጎ፣ ለእቅዱ ስኬት እየሠራ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የመስኖ ስንዴ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ዳንኤል ሙለታ በሰጡን ማብራሪያ መሠረት፣ ስንዴ በኢትዮጵያ በዝናብ ወቅት ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን እስከ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር ላይ የሚመረት የሰብል አይነት ነው። ምንም እንኳ ይህን ያህል መሬት በየዓመቱ እየታረሰ ምርት ቢሰጥም የሀገራችንን የስንዴ ፍላጎት ግን ማሟላት አልቻልንም። 25 ከመቶ የሚሆነውን የስንዴ ፍላጎታችንን እያሟላን ያለነው ከውጭ በማስገባት ነው።

ይህ ደግሞ በዓመት ከ400 እስከ 700 ሚሊዮን ዶላር እያስወጣን ይገኛል። ይህን ያህል ወጪ እያወጣን፣ ሀገራችን ቡና፣ ጥራጥሬና የቅባት እህሎችን ወደ ውጭ በመላክ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ መልሰን ስንዴን ከውጭ ለማስገባት የምንጠቀመው ከሆነ ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም ያሉት ዶክተር ዳንኤል፣ የስንዴ ፍላጎታችንን በራሳችን ማሟላት ብንችል ግን ከውጭ ለማስገባት የምንጠቀመውን የውጭ ምንዛሪ ለቴክኖሎጂዎች ማስፋፊያና ለተለያዩ የልማት ሥራዎች የማዋል እድል እንደሚሰጠን ይገልጻሉ።

ለስንዴ የምናወጣው ወጪ ከፍተኛ እንደሆነና በቅርቡም በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት፣ ወደ 700 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደተደረገ ያስታወሱት የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርሄ ተስፋ በአጼ ኃይለ ሥላሴ የስልጣን ዘመን አርሲና ባሌን የስንዴ አካባቢ ያደረገ ፕሮጀክት እንደነበር ያወሳሉ። እርሳቸው እንዳሉት፣ በጊዜው እንዲህ ዓይነት ፕሮጀክቶች መስፋፋት አለባቸው በሚል እሳቤ ወደ ወላይታም ተስፋፍቶ ነበር። እንዲህ ዓይነት ፕሮጀክቶች ሀገራችንን ከምርት እጥረት ስጋት ነጻ የሚያወጡ በመሆናቸው በስፋት ሊሠራባቸው የሚገቡም ናቸው። በተለይ፣ በከፍተኛ ስንዴ አምራችነታቸው የሚታወቁት ሩስያና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ በገቡበትና የስንዴ ዋጋ የዓለም ገበያ ላይ እየጨመረ ባለበት በዚህ ጊዜ በሀገራችን እየተሠራ ያለው የመስኖ ስንዴ ልማት ፕሮጀክትም ለኛ የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ያስገነዝባሉ።

የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈቶ ኢሴሞ፣ በበኩላቸው ከውጭ ከምናስገባቸው ሰብሎች መካከል ስንዴ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ጠቅሰው፣ ባለፉት 10 ዓመታት የሀገራችን ሕዝብ በስንዴ ምርት ላይ የተመሰረቱ ምግቦችን የመጠቀም ልማዱ በመጨመሩ የስንዴ ፍላጎትም በተመሳሳይ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ይናገራሉ። በኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ቦታ ያለውን የስንዴ ፍላጎት ለማሟላት በሀገር ውስጥ የሚመረተውን የስንዴ ምርት መጠን ማሳደግ አለብን በሚል ወደ ሥራ እንደተገባም ይገልጻሉ።

የመስኖ ስንዴ ልማት ፕሮጀክት ሲጀመር፣ የቆላ ስንዴ ይባል እንደነበር ያወሱት ዶክተር ፈቶ፣ ከሌሎች ሀገራት ልምድና ከምርምር ውጤቶቻችን በመነሳት ስንዴን በአዋሽ ተፋሰስ፣ በኦሞ ተፋሰስ፣ በሸበሌ ተፋሰስ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በአፋር ክልል፣ በሱማሌ ክልል በተለይ ጎዴ አካባቢ እና በኦሮሚያ ክልል የቆላ ስንዴ ውጤታማ ሆኖ መገኘቱ ለተጨማሪ ሥራ እንዳነሳሳ ያብራራሉ። በመቀጠልም በቆላ የተጀመረው የስንዴ ልማት ሥራ ለምን በደጋማ ቦታዎችስ በመስኖ አንሞክረውም በሚል መነሻ ሀሳብ የኦሮሚያ ክልል ኃላፊነት ወስዶ በተሠራው ሥራ ውጤታማ እንደሆነ ያስታውሳሉ። በዚህም የቆላ ስንዴ የሚለው ስያሜ ቀርቶ ፕሮጀክቱ የመስኖ ስንዴ እንደተባለና ከቆላማው አካባቢ ይልቅ የመስኖ ሥራው የበለጠ በሀገር ደረጃ ምርታማ እንዳደረገንም ነግረውናል።

ዶክተር ዳንኤልም፣ ከውጭ የምናስገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት እንሸፍናለን ብሎ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጥናት ሲያካሂድ እንደቆየ አስታውሰው፣ በምን መልኩ ብንሠራ ከውጭ የምናስገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት መተካት እንችላለን? ለስኬቱስ ምን ዓይነት አቅጣጫዎችን ብንከተል ያዋጣናል? የሚለውም በጥናቱ መመላከቱን አንስተዋል።

በስንዴ ራሳችንን እንችላለን ብለን ስንነሳ አራት መሠረታዊ ምሰሶዎች ይዘን ወይም አቅጣጫዎችን ለይተን ነበር ያሉት ዶክተር ፈቶ፤ የመጀመሪያው፣ በፊት እንጠቀመው በነበረ መሬት ላይ አስፈላጊ ግብአቶችን በመጠቀም ምርታማነትን መጨመር፤ ሁለተኛው፣ ለመስኖ የሚሆኑና በበጋ የሚፈሱ ወንዞች አካባቢ ያሉ ሰፋፊ መሬቶችን በመጠቀም በበጋ ጊዜ ማምረት፤ ሶስተኛው ውሃ የሚያዝሉ የኮትቻ(ጥቁር አፈር) ያለባቸውን መሬቶች ማንጣፈፍ፤ አራተኛው ደግሞ፣ አሲዳማ አፈርን በማከም የደከመውን መሬት ወደ ምርታማነት መመለስ ናቸው። ከእነዚህ መካከል በስፋት የተሠራው የመስኖ ስንዴ ሲሆን፣ እነዚህን አማራጮች በሙሉ አቅም መጠቀም ብንችል የምርት መጠንን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ይቻላልም ብለዋል።

በመስኖ ስንዴ ማምረት በተመለከተ የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ በሦስት ሺህ 500 ሄክታር ላይ፣ በቀጣዩ ዓመት በ20 ሺህ ሄክታር ላይ ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል። ይህንኑ ተሞክሮ በማስፋት ባለፈው ዓመት በ187 ሺህ ሄክታር ላይ አመርቂ ውጤት ማግኘት መቻሉን ዶክተር ዳንኤል ይናገራሉ። እርሳቸው እንዳሉት፣ ዘንድሮ ደግሞ በመጀመሪያ ዙር በአጠቃላይ በ404ሺህ 900 ሄክታር ላይ ሲተገበር፣ ከዚህ ውስጥ 311 ሺህ 106 ሄክታር ወይም 88 ከመቶ የሚሆነው የተሸፈነው በኦሮሚያ ክልል ነው፤ በአማራ ክልል 40 ሺህ በሚሆን ሄክታር፣ በአፋር በ7500 ሄክታር፣ በደቡብ ክልል በአምስት ሺህ ሄክታር እና ሲዳማ ክልል አዲስ የተቋቋመ በመሆኑ ለማሳያ ያህል በ157 ሄክታር ላይ ተግባራዊ ሆኗል። ለወደፊቱም በክልሉ የተሻለ ለማምረት አቅም እንዳለ ግንዛቤ እንደተያዘ ይገልጻሉ።

በሁለተኛው ዙር ከመስኖ በተጨማሪ የበልግ ዝናብንም በመጠቀም በኦሮሚያ በ257 ሺህ 800 ሄክታር፣ በአማራ ክልል በ28 ሺህ ሄክታር ላይ ለመዝራት የታቀደና በሥራ ላይም ያለ ሲሆን፣ በዓመቱ መጨረሻ በአጠቃላይ ወደ 693 ሺህ 350 ሄክታር አካባቢ መሬት በስንዴ ይለማል። ይህንን በትንሹ በሄክታር 35 ኩንታል ብናገኝ ብለን ብናሰላው በአጠቃላይ ወደ 25 ሚሊዮን ኩንታል ማግኘት ያስችለናል የሚሉት ዶ/ር ዳንኤል፣ በተለይ የሩስያና ዩክሬን ጦርነት ያስከተለውን የኢኮኖሚ ቀውስ ተከትሎ፣ የዓለም ሀገራት ምርታቸውን ወደ ውጭ ማስወጣት ማቆማቸውን ይናገራሉ። የስንዴ ዋጋም በዓለም ገበያ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን በማንሳት፣ ምርታችንን በዚህ ልክ ማሳደግ መቻላችን ትልቅ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው አጽንዖት ይሰጣሉ።

እንደ ዶክተር ፈቶ ማብራሪያ፣ በኢትዮጵያ የአንድ ሰው አማካይ የስንዴ ፍጆታ 0.7 ሲሆን፣ ይህንን ባለን የሕዝብ ቁጥር ስናባዛው ወደ 77 ሚሊዮን ኩንታል ይደርሳል፤ አሁን እያመረትን ያለነው ደግሞ፣ በዓመት 50 እና 55 ሚሊዮን ገደማ ኩንታል ነው። 20 ሚሊዮን ኩንታል ያህሉን ስንዴ ለማሟላት ከውጭ እናስገባለን። በቂ መሬት፣ ለም አፈር፣ ምቹ የሆነ የአየር ፀባይ፣ ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች እያሉ ራሳችን ማምረት የምንችለውን “ለምን ከውጭ እናስገባለን?” በሚል ቁጭት በተጀመረው ፕሮጀክት የ20 ሚሊዮን ኩንታል ጉድለታችንን ለመሙላት ጥቂት ብቻ እንደሚቀረው ይናገራሉ። ዶ/ሩ ፕሮጀክቱ ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን መቅረፍ ቢቻል፤ በመስኖ፣ በበልግ እና በክረምት በሚመረተው የስንዴ ምርት ከራሳችን አልፈን ወደ ውጭ የመላክ እድላችን የሰፋ ነው በማለት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ራስን ችሎ ስንዴን ወደ ውጭ ለመላክ ለሚደረገው ጥረት ስኬት በቀጣይ ዓመት በስንዴ ምርት የሚሸፈን መሬትን አንድ ሚሊዮን ሄክታር ለማድረስ መታቀዱን የተናገሩት ዶክተር ዳንኤል፣ ቀደም ሲል የነበሩ ተግዳሮቶችን መቅረፍ ከተቻለ እቅዱን ማሳካት እንደሚቻል ጠቁመዋል። ከዚሁ ጋር አያይዘው ፕሮጀክቱ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ያለ ቢሆንም፣ በኮሚቴ የሚሠራ መሆኑ ሥራው ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ይናገራሉ። ሥራው በሚፈለገው ልክ ስኬታማ እንዲሆን፣ በብሔራዊ ደረጃ ራሱን የቻለና የራሱ በጀት ያለው የሥራ ክፍል ሆኖ ከመሰረቱ ሁሉንም ነገሮች እያቀደ የሚሠራ ቢሆን የተሻለ ውጤት ይገኝበታል ብለዋል። መንግሥት ባለው አቅም የተቻለውን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት ዶክተር ዳንኤል፣ “በጀቱ ከፍ ቢልና ቀድሞ ገበሬዎችን ለማሰልጠንና ቦታዎችን ለመምረጥ በጀቱ በጊዜ ተለቆ ፈጥኖ ወደ ሥራ ቢገባ ሥራውን ለማሳለጥ ትልቅ እገዛ ያደርጋል። ቆይቶ መዘራቱም ምርታማነቱን ስለሚቀንሰው ቶሎ አቅዶ በጊዜ ሊዘራና በታቀደው መሠረት ሊጠናቀቅም ይገባል” ብለዋል።

በጊዜ ከመዝራት በተጨማሪ አሁን እየተጠቀምን ያለነው ባህላዊ የመስኖ ውሃ አጠጣጥ ዘዴ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቢሆን፣ ውሃን በራሳቸው ወስደው አየር ላይ የሚበትኑ መሳሪያዎች በሰፊው ቢገቡ መልካም ነው ያሉት ዶክተር ዳንኤል፣ እዚህ ላይ መንግሥትም የግል ባለሀብቱም ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አድርገዋል።

ከስንዴ ውጪ ዘይትም እየተቸገርንበት ያለ ግብዓት መሆኑን አንስተው የዘይት ጥራጥሬዎችን ለማምረት የመሬትም ሆነ የአየር ችግር የለብንም ያሉት ዶክተር ዳንኤል፣ ትኩረት ሰጥተን ባለመሥራታችን ብቻ አቅማችንን መጠቀም አልቻልንም በማለት በቁጭት ይናገራሉ። የትኛውም ባለሀብት ተነሳሽነት ኖሮት በሀገር ልማት ላይ ለማኅበረሰቡና ለሚኖርበት አካባቢ አስተዋጽዖ ለማድረግ ወስኖ በቁርጠኝነት ቢሠራና የመንግሥትም ድጋፍ ቢጠናከር ጥሩ ነው ብለዋል። የብድር አገልግሎት ማግኘት ለግብርናው ማነቆ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተሩ ባለሀብቶች ግብርና ላይ ሲሠማሩ ለማሽነሪ የሚሆን ብድር ስለሚያስፈልጋቸው፣ አበዳሪ ተቋማት ግብርናን በፋይናንስ እንዲያግዙ መንግሥት አቅጣጫ መስጠት እንዳለበት ጥቆማ ሰጥተዋል። ከዚሁ ጋር አያይዘው፣ የግል ባለሀብቶች እናለማለን ብለው የወሰዱትን ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሚገባ ኢንቨስት አድርገውበት ዘመናዊ የመስኖ ስርዓት ተክለውበት ቢሠሩ፣ በእርግጠኝነት አሁን የምናስበውን ነገር ማሳካት እንችላለን ይላሉ። በመንግሥት በኩል ደግሞ ባለሀብቱ የወሰደውን መሬት በአግባቡ እየሠራበት መሆኑን ክትትል የሚያደርግበትን ሁኔታ በድጋሚ ሊመለከት እንደሚገባ አሳስበዋል።

አያይዘውም ከውጭ የምናስገባው ስንዴ ብቻ አለመሆኑን ያነሱት ዶክተር ፈቶ፣ ለግብርናው ትኩረት ተሰጥቶ በሚፈለገው ልክ ኢንቨስት ቢደረግ፣ መሬታችን የማያበቅለው ነገር የለምና እንደ የምግብ ዘይት፣ ስኳርና ሌሎችም የግብርና ውጤቶችን በራሳችን አቅምና መሬት በማምረት ለእነዚህ የምናወጣውን የውጭ ምንዛሪ ማስቀረት እንደምንችል ይናገራሉ።

ዶክተር ቆስጠንጢኖስም “ሀገራችን ከ70 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ሰፊ መሬት ቢኖራትም የምናርሰው ግን ያለንን 20 ከመቶ አይሞላም፤ እስካሁን ያልታረሱ ብዙ ማዳበሪያ የማይፈልጉ መሬቶችም አሉን፣ ወንዞቻችንም በየዓመቱ በአማካይ 122 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሊትር ያህል ውሃ ይዘው ይወጣሉ። ኢትዮጵያ በሰሜንና በምስራቅ አፍሪካ የውሃ ቁንጮ በመባልም ትታወቃለች።

 ሰሜንና ምስራቅ አፍሪካን ጭምር መመገብ የሚችል አቅም እያለን ግን፣ ከስንዴ በተጨማሪ በራሳችን ማምረት የምንችላቸውንና በብዛት ተፈላጊነት ያላቸውን የቢራ ገብስና ሽንኩርት ጭምር ከውጭ እናስመጣለን። ከዚህም አልፈን ተርበን እርዳታ እንጠይቃለን። ከዚህ ለመውጣት መሥራት የሚገባንን የቤት ሥራ ሠርተን የሚያስፈልገንን ምርት በብዛት ወደማምረት መሸጋገር ይጠበቅብናል” ብለዋል።

በስንዴ ላይ እየተሠራ ያለውን ሥራ ውጤታማ ለማድረግና በአጠቃላይ ሀገራችን ካላት የግብርና ሀብት ተጠቃሚ እንድትሆን ለግብርናው ተጠሪ የሆኑ ተቋማትን በተለይም፣ የቴክኖሎጂ ምንጭ ለሆነው የግብርና ምርምር ላይ በሚፈለገው ልክ ኢንቨስት ማድረግ አለብን ያሉን ዶክተር ፈቶ፣ ለዘርፉ በቂ በጀት መድቦ በመሥራት ለውጭ የምናወጣውን ወጪ እዚሁ ሀገር ውስጥ አስቀርተን ሀገራችንን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሳደግ እንደምንችል ይናገራሉ።

ዶክተር ፈቶ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በሥሩ 20 የሚሆኑ ማዕከላት ያሉት ተቋም ሆኖ በሰው ኃይልም በሶስት እጥፍ ከሚበልጠው ከአንድ ሆስፒታል ጋር ተመሳሳይ በጀት የተመደበለት መሆኑን ያነሳሉ። ሆስፒታሉ በቂ በጀት የሚያስፈልገው መሆኑ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ባይሆንም፣ ለግብርና ምርምር የሚመደበው በጀት ከሥራውና ከሰው ኃይሉ አኳያ በቂ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ። የጤና ስትራቴጂያችን ቀድሞ ከመከላከል ይልቅ ሰው ከታመመ በኋላ ማዳን ላይ ማተኮራችንን ያሳያልና ለግብርናው ተገቢው ትኩረት ይሰጠው ይላሉ።

ለመስኖ ልማቱ ውጤት መገኘት ትልቅ አስተዋጽዖ ያደረገው ክልሎች ሥራውን በባለቤትነት ወስደው ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸው ነው ያሉት ዶክተር ዳንኤል፣ የኦሮሚያ ክልል ከፕሬዚዳንቱ ጀምሮ ትልቅ አስተዋጽዖ እያደረጉ መሆናቸውን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። አያይዘውም፣ ለቀጣይም ለፕሮጀክቱ ስኬት የሁሉም ክልሎች ተሳትፎና ድጋፍ አስፈላጊ ከመሆኑ በተጨማሪ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል። በመንግሥት ደረጃም ለሥራው የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ እንደሆነም አንስተው ይሄ የመንግሥት ድጋፍም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የገበያ ትስስርን በተመለከተ ጥያቄ ያቀረብንላቸው ዶክተር ዳንኤል፣ መጀመሪያ ትኩረት አድርገን ስንሠራ የነበረው ፍላጎትን ለማሟላት ምርትን መጨመር ላይ ስለነበረና የገበያ ትስስር ላይ ትኩረት ስላላደረግን፤ እንዲያውም በብዙዎች ዘንድ አልተሠራም የሚል እሳቤ ነበር ይላሉ። ይህ እሳቤ የተፈጠረው የገበያ ትስስር በበቂ ደረጃ ባለመሠራቱ ነው ብለን ዘንድሮ የህብረት ሥራ ማኅበራት፣ የእህል ንግድ ድርጅት እና የአደጋ ስጋትና መከላከል እህሉን እንዲገዙና እንዲይዙ አድርገናል ብለዋል። በተጨማሪም የገበያ ትስስሩ በሰፊው እንዲፈጠር፣ ከኦሮሚያ ግብርና ቢሮ እና የስንዴ ምርትን ግብዓት አድርገው የሚሠሩ ፋብሪካ ካላቸው ባለሀብቶች ጋር በመነጋገር ትስስር እንዲፈጠር ማድረጋቸውንም ነግረውናል።

ዶክተር ፈቶም፣ መጀመሪያ የስንዴ ልማት ሥራው ሲጀመር በሙከራ መልክ ስለነበር የገበያ ትስስሩ እንዳልታሰበበትና በዚህ ሳቢያም የተመረተው በበቂ ደረጃ ወደ ገበያ አልወጣም የሚሉ ወቀሳዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል። ከማሳ እስከ ሹካ የሚለው የምርት ሰንሰለት በሰነድ ደረጃ ቀድሞውንም በዝርዝር የሰፈረ ስለነበር በዚህ ዓመት የገበያ ትስስሩን ለማጠናከር የፋብሪካ ባለቤቶች ምርቱ ማሳ ላይ እያለ አይተው ራሳቸውን ለግዢ እንዲያዘጋጁ የማድረግ፣ ህብረት ሥራዎችም ያልቻሉ ምርቱ ከተሰበሰበ በኋላ እንዲገዙ፣ የቻሉት ደግሞ በቀጥታ ከማሳው የሚሰበስቡበትን ሥርዓት መዘርጋት መቻሉን ገልጸውልናል።

ኢትዮጵያ ካለችበት ጆኦግራፊያዊ አቀማመጥ አንጻር ጎረቤቶቻችን ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኤርትራ እምብዛም ስንዴ አምራች ሀገራት ካለመሆናቸውና ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የስንዴ አቅርቦት እየቀነሰ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ህገ ወጥ የስንዴ ንግድ ስጋት መሆኑን ዶክተር ዳንኤል ተናግረዋል። በተጨባጭም ለምሳሌ በኮንስትራክሽን ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ህገ ወጥ የስንዴ ንግድ ውስጥ የገቡ እንዳሉ መረጃ እንደደረሳቸውና ባለሀብቶቹ ስንዴውን በህገ ወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት ሀገር ካስወጡና ከሸጡ በኋላ የሚያገኙትን ዶላር ለኮንስትራክሽን ሥራቸው የሚሆን ግብዓትን ከውጭ ለማስገባት እንደሚጠቀሙበት አንስተዋል። ይህንን ጉዳይ ወደ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እንደተወሰደና እነርሱም መረጃው እንዳላቸው ተናግረዋል። ምንም ያህል ስንዴ ቢመረት ድንበራችን በሚገባ ካልተጠበቀና ለዝርፊያ እንዳንጋለጥ ካልተደረገ ለሕዝባችን ደርሰን፣ ለውጭ ሀገራትም ልከን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የምናደርገው ጥረት ሁሉ ከንቱ ይሆናል ያሉት ዶክተሩ፣ ሕዝቡም መረጃው ኖሮት ይህንን ህገ ወጥ ንግድ ሲመለከት ለተገቢው የመንግሥት አካል እንዲያሳውቅም ጥሪ አቅርበዋል።

ይህንኑ ስጋት ዶክተር ፈቶም ያነሱ ሲሆን፣ እርሳቸው እንዳሉት፣ ስንዴ በህገ ወጥ መንገድ በድንበር በኩል ይወጣል የሚለውን መረጃ ተከትሎ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ህብረት ሥራ ማኅበራትና ገዢ ባለሀብቶች ማሳ ድረስ ሄደው ከአምራቾች ጋር እንዲነጋገሩና ስንዴው ከሚገኝበት ቦታ በቀጥታ እንዲገዙ የማድረግና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በመነጋገር ስንዴው ከተመረተበት ቦታ ጀምሮ ወደ ገበያ እስኪገባ ድረስ የሚከታተል (ትራክ የሚያደርግ) ሶፍትዌር መዘጋጀቱን ገልጸዋል። በተጨማሪም ስንዴ የተመረተባቸውን አካባቢዎችን በጂፒኤስ የማጠር ሥራ መሠራቱን፤ ሥራው ገና ጅምር ላይ ያለ ቢሆንም ውጤታማነቱ እየታየ ያለና አርኪ ነው ብለዋል።

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ይህንን ፕሮጀክት አሁን ባለበት ሁኔታ መንግሥትና ክልሎች እየሠሩ ለማሳየት ይጠቅም ይሆናል እንጂ በመንግሥት ብቻ መሠራቱ የሚቀጥል ከሆነ ውጤታማነቱ ውስን ይሆናል ይላሉ። ዋናው ነገር ባለሀብቶች ወደ ሥራው እንዲገቡ ማስቻል እንደሆነው ያሰምሩበታል። እንደ ደቡብ አፍሪካ እና ቦትስዋና ያሉ የአፍሪካ ሀገራትን ብናይ የእኛን ያህል መሬትና ውሃ ሳይኖራቸው ነገር ግን፣ የውጭ ኢንቨስተሮች ገብተው በትንሽ መሬት አምርተው ወደ ውጭ እንደሚልኩ በማሳያነት ይጠቅሳሉ። እንደ እርሳቸው ሀሳብ፣ እኛም ይህን ማድረግ የምንችለው የውጭ ኢንቨስተሮችን ስናስገባ፤ እነርሱን መጋበዝ የሚችል የካፒታል አቅምና ሥርዓትን ስንገነባ ነው። እርሻ ሰፊ እውቀትን የሚጠይቅ ነው ያሉን ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በየወረዳው የሚቀመጠው አመራርና ሠራተኛ ሁሉ የሚመጣውን ኢንቨስተር በአግባቡ የማስተናገድ፣ እንዲሁም እየተሠራ ያለውንም በሚገባ መከታተል የሚችል አቅም ያለው መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል። አክለውም ስንዴን ወደ ውጭ ለመላክ በጥራትና በብዛት ማምረት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃን ያሟላ ስንዴን ለማምረት ከፍተኛ አቅም ያላቸው ትላልቅ ኢንቨስተሮችን መጋበዝ የሚሻ መሆኑ ሊታሰብበት ይገባል በማለት አሳስበዋል።

ዘመን መጽሔትም ሀገራችን በግብርናው ዘርፍ በሙሉ አቅሟ ተጠቅማ በምግብ ራሷን ለመቻል ለምታደርገው ጥረት አጋዥ ለሆነው የመስኖ ስንዴ ልማት ፕሮጀክት ስኬት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ይወጣ ትላለች!

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

ዘመን መጽሔት ግንቦት 20 ቀን 2014 ዓ.ም

Recommended For You