ትኩረት የሚሻው የጮቄ ተራራ ሰንሰለት

መግቢያ

ይህ መጠጣጥፍ፣ ከተለያዩ ጽሑፎች፣ አውደ ጥናቶች፣ ምርምሮች እንዲሁም ጮቄን ከተለያዩ አቅጣጫዎች በመኪና እና በእግር በመጓዝ በተገኙ መረጃዎች ላይ የተመሠረተ ነው። የጮቄ ተራራ ሰንሰለት ከ30 ሚሊዮን ዓመታት በፊት በተከሰተ የእሳተ-ገሞራ ፍንዳታ መንስዔ የተፈጠረ የምድር ገጽታ ሲሆን፣ የሚገኘውም በአማራ ክልል በምዕራብ እና በምስራቅ ጎጃም ዞኖች ውስጥ ነው። ጮቄ የአባይ ወንዝ ተፋሰስ ከሆኑ አካባቢዎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ የተራራው ሰንሰለት የአባይ የውሀ ጋንና የብዝሃ-ህይወት መገኛ አምባ ነው። የጮቄ ተራራ ሰንሰለት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ቢኖረውም፣ በአሁኑ ወቅት ግን ያላግባብ በሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች በመጎሳቆል ላይ ይገኛል። የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ፣ ሳይንስን ከማኸዘብ በተጨማሪ፣ የጮቄ ተራራ ሰንሰለትን እንደምሳሌነት ወስደን በአካባቢው እየደረሰ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት መጎሳቆል ለማመላከትና ችግሩን ለመታደግ የሚያስችሉ ተግባራትን ለመጠቆም ነው። እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብትን መንከባከብ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የተወሰነ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው።

የአካባቢው ቅንጭብ የታሪክ እይታ

የጮቄ ተራራ ሰንሰለት አካባቢ ከዓመታት በፊት በእፅዋት የተሸፈነ፣ ብሎም የሽፍታ(የቀማኛ) መሸሸጊያ፣ እንዲሁም የአርበኞች መጠጊያ እንደነበረ በርካታ መረጃዎች ይመሰክራሉ። አለቃ ተክለየሱስ ዋቅጅራ (ሐተታ በሥርግው ገላው)፣ ካሳ ኃይሉ (በኋላ አፄ ቴዎድሮስ) ሰኔ 23 ቀን 1844 ዓ.ም የጎጃምን ጦር ድል ነስቶ በጮቄ ተራራ ሰንሰለት በኩል ወደ ደብረታቦር ሲመለስ፣ የደጋ ዳሞት ገበሬ (የጮቄ ሰንሰለት አካል ነው) በጦርነት የደከመውን የካሳ ኃይሉን ወታደር ለመዝረፍ አስቦ ተንቀሳቅሶ እንደነበር በሚከተለው መንገድ ገልጸውታል፤”… የደጋ ዳሞት ገበሬ እርሻውንና ቁፋሮውን እየተወ፣ በማቅ (ባና) ትርትር የሚሽቱ (ሚስቱ) ወስፌ በአምጃ (የደጋ ዛፍ) ሽመል አስሮ ፈረስና በቅሎ እየፈለገ ሊማርክ ተደከመ ተቆሰለ ሠራዊት ገንዘብ ሊቀማ እየፋነነ ወጣ። በለሰለሰው ከአሰታውና ከጅብራው (የደጋ ዛፎች) ውስጥ ብቅ እያለ የጎሹን ደመኛ የዓሊን ወደረኛ ትሰደዋለህ አለ። የደጃች ካሳን ሠራዊት አላሳልፍ ብሎ ብዙ ሰው ገደለ። የዚህን ጊዜ ደጃች ካሳ ሰገዶ ከሚባል አገር ላይ ሰፈር አድርጎ ወገኑን (የጋማ ከብት) ለቀቀለት። በፈረስና በበቅሎ እርስ በርስ ሲጣላ ዙሪያውን ነፍጠኛ አስከብቦ ፈጀው። ከዚያም በኋላ ባልዋ ፋኖ ሄዶ የሞተባት የደጋ ዳሞት ሴት ስታለቅስ፣ አመጣለሁ ብሎ የካሳን ፈረስ፣ ሳያርመው ሞተ የዘራውን ገብስ።” ማለትዋን አስቀምጠዋል።

የጮቄ የተራራ ሰንሰለት አካባቢ በጠላት ወረራ ዘመን የብዙ አርበኞች ምሽግ፣ አምባ ነበር። በሰከላ እነ ዘለቀ ደስታ (ደጃዝማች)፣ በፈርስ ቤት እነ ኃይለየሱስ ፍላቴ (ደጃዝማች) የተራራውን ሰንሰለት ተገን አድርገው ከወራሪው ጠላት ጋር የተፋለሙበት አካባቢ ነበር።

የጮቄ ተራራ ሰንሰለት ከተፈጥሮ ሃብትነት አንፃር

ጮቄ የአባይ የውሀ ጋን አምባ ነው፣ አብዛኛዎቹ የጐጃም ወንዞች የሚፈልቁት ከጮቄ ተራራ ሰንሰለት አካባቢ ነው።ከጮቄ ተራራ ሰንሰለት በአጠቃላይ 59 ወንዞችና 273 ምንጮች ሲፈልቁ፣ ከአካባቢው ወደ አባይ የሚገባው የውሃ አመታዊ ፍሰት መጠን 9.4 ሚሊዮን ሜ/ኩብ ነው።ይህም ከአጠቃላይ የአባይ ውሀ ፍሰት መጠን አሥር በመቶ (10%) ገደማ ይሆናል።

ጮቄ የብዝሃ-ህይወት አምባ ነው፣ የተራራ ጉራንጉር አካባቢዎች ከሰው ልጅ የቀን ተቀን ንክኪ ትንሽ ራቅ ያሉ ስለሆኑ፣ የእፅዋት መሸሸጊያ አካባቢዎች መሆናቸው ይታወቃል። በሌሎች አካባቢዎች የጠፉ እፅዋትም በዚያ አካባቢ ይገኛሉ። እፅዋቶቹ ለመድሐኒትነትና ለምግብ ማጣፈጫነት (ቅመማ ቅመም) በመሆን ያገለግላሉ። በአካባቢው 24 አጥቢ እንስሳት፣ 52 የወፍና 85 የእፅዋት ዝርያዎች ይገኛሉ። ስለሆነም የብዝሃ-ህይወት ሃብት ጥቅሙ በአግባቡ ሳይታወቅ ሊወድም ስለሚችል፣ ቅድሚያ ሰጥቶ ሀብቱን ከውድመት መታደግ ጠቀሜታው የጎላ ነው። የብዝሃ -ህይወት ሃብት ደግሞ የዓለም አቀፍ ሃብትም ጭምር ነው።

ጮቄ የአየር ንብረት ዑደት ተቆጣጣሪ የተራራ ሰንሰለት ነው፣ በመሠረቱ የከፍተኛ ቦታዎች የዝናብ መጠን ከፍ ያለ ነው። በእፅዋት የተሸፈኑ የተራራ አካባቢዎች የነፋስንም ሆነ የደመናዎችን እንቅስቃሴ በከፊልም ቢሆን ይቆጣጠራሉ። ውሃ አዘል ነፋስ ተራራ ዘንድ ሲደርስ፣ ከተራራው በላይ ለመክነፍ ከፍ ስለሚል ውሃ የተሸከመው አየር ይቀዘቅዛል። ቀዝቃዛ አየር ደግሞ ብዙ ርጥበት ማቀፍ ስለማይችል የአየሩ እርጥበት በዝናብ መልክ ወደ መሬት ይወርዳል። ለምሳሌ በአካባቢያችን የሌሊት አየር ቀዝቃዛ ስለሆነ፣ በውስጡ የነበረን ርጥበት ማቀፍ ስለማይችል ወደ መሬት ይለቀዋል። ጠዋት ጠዋት ላይ በጤዛ መልክ የምናየው ውሃ የዚያ ውጤት ነው።

ተራሮች አየር የተሸከመን ደመና (የተሸከመውን እርጥበት) እንዲያራግፍ እና ውሃ በዝናብ መልክ ለአካባቢው እንዲያበረክት ያደርጉታል። የጮቄ የተራራ ሰንሰለትም የምዕራብና የምስራቅ የዝናብ ስርጭትንና መጠንን የመወሰን ሚናው ከፍተኛ ነው። የዝናብ ውሃንም ወደ ከርሰ-ምድር የማስገባት ባህሪ አለው። የዝናቡ ውሃም መሬት ውስጥ ሰርጐ በመግባት የከርሰ ምድር የውሃ ጋኖችን ይሞላል። ከዚያም የከርሰ ምድር ውሃ ከየተራራው ጐን በምንጭ፣ በጅረት እና በወንዝ መልክ ይፈልቃል።

ይህም ሁኔታ የወንዞችን ጥርቅም ፍሰት፣ ማለትም የአባይ ወንዝን ፍሰት አዛብቶታል፣ በበጋ ፍሰቱ በጣም ውስን ሲሆን፣ በክረምት ደግሞ በጣም ከፍተኛ ነው።በመሆኑም ለታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች የጎርፍ ችግርን ያስከስታል። የዓባይ ወንዝ ውሃም በከርሰ ምድር የተጣራ ሳይሆን፣ ከላይ ጋላቢ ጎርፍ፣ አፈር አዘል፣ ደለል መሰል ፍሰት እንዲኖረው ያደርገዋል። ይህም በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነቡ ግድቦች ሁሉ እድሜያቸውን የሚያሳጥር ይሆናል።

ጮቄ ለቱሪዝም ልማት ምቹ ነው፣ በጮቄ ተራራ ሰንሰለትና በአካባቢው የሚገኙ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቦታዎች ለቱሪዝም መስህብነት አመቺ ናቸው። የተራራ ላይ ጉዞ /Mountain Trekking)፣ ፎቶግራፍ / Photography)፣ ተፈጥሮ አድናቂ/ Nature Tour)፣ ወዘተ ሊተገብሩ ይችላሉ። ሰከላ ግልገል አባይ የሚመነጭበት አካባቢ ሲሆን፣ የአባይ ምንጭ (ግሸ አባይ)፣ ከአሁኑ የተሻለ ጥበቃና እንክብካቤ ተደርጎለት፣ ለቱሪስት መስህብ ከሚያገለግሉ አካባቢዎች መካከል አንዱ ሊሆን ይገባል። በተራራው ሰንሰለት አካባቢ፣ በሰሜን ደረት ዝነኛው የዋሸራ ቅኔ ትምህርት ቤት፣ በደቡብ ደረት የጎንደር ነገሥታት የቤተ-መንግሥት ፍርስራሾች ስለሚገኙ፣ እነኝህ ቦታዎች ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻ መሆን ይችላሉ። ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት በመሠረተ- ልማት አለመኖር ምክንያት አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ያስቸግራል።

የተራራው ሰንሰለት ከአካባቢ ጥቅም እይታ

የአባይ ወንዝ የበጋውንና የክረምቱን የፍሰት ሚዛኑን ጠብቆ፣ መጠኑ ሳይዛባ እንዲፈስ በማድረግ በጎርፍ የሚጠቁ የተፋሰሱ አገሮችን መታደግ ይቻላል። በርሃማነትን የመታደግ ሚናም ይኖረዋል። አንዱ ዘዴ ተራራውን በእፅዋት መሸፈን ነው። በተራራው ሰንሰለት እፅዋት እንዲያንሰራሩ ማድረግ፣ ውሃ ወደ ከርሰ ምድር እንዲገባ ማድረግና በህዋ ውስጥ ያለውን “የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን” ለመቆጣጠር ያገለግላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየአካባቢው ዛፍ መትከል፣ መንከባከብ፣ እንደ አቢይ ተግባር መወሰዱም አበረታች ነው። ይህም ኢትዮጵያ ለአካባቢ እንክብካቤ በተለያዩ ጊዜያት የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መተግበራቸውን ያረጋግጣል። እንክብካቤውን እንዲቀጥል ማስቻል ደግሞ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ድጋፍ የማግኘት እድል እንዲኖራት ያደርጋል።

የአካባቢውን ሥነ-ምህዳርና የአየር ጠባይ በማገናዘብ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊነት ያሏቸውን ልዩ ልዩ ፍራፍሬዎችንም ሆነ ለኢንዱስትሪ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ እፅዋትን በቴክኖሎጂ በተደገፉ ዘዴዎች በማምረት አካባቢውን መታደግ ይቻላል።

በጮቄ ተራራ ሰንሰለት የተከሰቱ ችግሮች

ካለፈው ምዕተ-ዓመት አጋማሽ ወዲህ የጮቄ ተራራ ሰንሰለት ከፍተኛ መጎሳቆል ደርሶበታል። መጎሳቆሉን በተመለከተም ከብዙ አካባቢዎች መረጃዎች ተሰብስበዋል። በግል ከተገኘ መረጃ መካከል አንደኛው፣ መስከረም 1949 ዓ.ም ከጽሁፉ አቅራቢዎች መካከል አንደኛው (ሽብሩ ተድላ)፣ ከሰሜን ከፈለገ ብርሃን ወደ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ጮቄን በእግር አቋርጦ ነበር። እንዲሁም ከአምሳ ዓመት ገደማ በኋላ (በመጋቢት 2001 ዓ.ም) በዚያው መንገድ፣ ከደቡብ አቅጣጫ (ቁይ ከሚባል ከተማ) ወደ ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ ወደ ፈለገ ብርሃን በእግር ተጉዞም ነበር። በእነዚህ ጉዞዎች በአምሳ ዓመት የዕድሜ ልዩነት ውስጥ የተከሰተውን የአካባቢውን መጎሳቆል መረዳት ተችሏል።

ከአምሳ ዓመታት ገደማ በፊት የነበሩት የአስታና የአምጃ ጫካዎች ጨርሰው ወድመዋል። ከአምሳ ዓመት በፊት በሳር/በዛፍ ያልተሸፈነ መሬት በአካባቢው አልነበረም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አካባቢው ገጣባ ሆኖ፣ ምድረ-በዳ መሰል ገጽታም ተላብሷል። ስለሆነም የአካባቢው የእፅዋት ሃብት ጭራሽ ዘሩ ጠፍቷል ማለት ይቻላል።

የጮቄን የተራራ ሰንሰለት በሌሎች አቅጣጫዎች በመኪና በመጓዝ ለማየት እና መረጃ ለመሰብሰብም ጥረት ተደርጓል። ከደብረ ማርቆስ በረቡዕ ገበያ አልፎ ወደ ቢቡኝ ወረዳ ወደ ድጎ ጽዮን፣ እንዲሁም በደምበጫ በኩል አድርጎ ወደ ፈረሰ ቤት ከተማ፣ በሰንሰለቱ አናት ወደ ከሰላ በመጓዝ ሁኔታውን ለመገንዘብ ተችሏል። ከሰሜን አቅጣጫ ተነስቶ በዋሸራ ገዳም በኩል፣ ወደ ደቡብ፣ ወደ ቲሊሊም ጉዞ ተደርጎ ነበር።

በተገኘው መረጃ መሠረት የአካባቢው ማህበረሰብ ኑሮ ከተፈጥሮ ሃብት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላለው (የምግብ ማብሰያ ማገዶ፣ የከብት መኖ፣ የግንባታ ቁሳቁስ፣ የባህል መድሐኒት፣ ወዘተ) በአካባቢው የነበረ የተፈጥሮ ሃብት (ብዝሃ-ሕይወትን ይጨምራል) በመመናመኑ ምክንያት ለከፍተኛ ችግር ተጋልጧል።

የአካባቢው ዋና ዋና ተግዳሮቶች የመሬት መጎሳቆል፣ የህዝብ እና የቤት እንስሳት ቁጥር መብዛት፣ መታረስ የሌለባቸው ተራራማ ቦታዎችን ለእርሻ ተግባር ማዋል፣ አግባብ ያልሆነ የእርሻ ዘዴ መጠቀም፣ የብዝሃ-ሕይወት መመናመን ብሎም መጥፋት እና የአፈር ለምነት መቀነስ ናቸው። እነዚህ ችግሮች ተደራርበው ለአካባቢው ህዝብ የኑሮ አለኝታ መቃወስ ምክንያቶች ሆነዋል። ከተራራው የሚፈልቁ የምንጮች እና የወንዞች ፍሰትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል። ወንዞቹ በክረምት መጠነ ሰፊ የሆነ ደለል ተሸክመው ከአባይ ጋር ይቀላቀላሉ። በበጋ ደግሞ አንዳንዶቹ ወንዞች ፈጽሞ ይደርቃሉ።

የጮቄ አካባቢ የሙቀት መጠን እየጨመረ መምጣቱን የሚያመላክቱ ብዙ መረጃዎች አሉ። ለምሳሌ ከሎኔል ብርሃኑ ባይህ እንግዳ ስለ ህይወት ጉዞው በተረከው መፅሐፍ (ማስታወሻ/ረቂቅ) ከደብረ ማርቆስ ወደ ሞጣ በ1936 ዓ.ም ሲጓዝ የአካባቢው ብርድ ከፍተኛ እንደነበረ ይገልጻል። በተለይም በክረምት ወራት ከሞጣ በኩል ጮቄ ከሩቅ ሲታይ በበረዶ የተሸፈነ የተራራ ሰንሰለት የነበረ መሆኑን ያብራራል። በበረዶ በመሸፈኑ ምክንያትም የአውሮፓ ተራራማ አካባቢዎችን ይመስል እንደነበረ ያስረዳል። አሁን ላይ እንደዚያ ዓይነት ሁኔታ በአካባቢው አይታይም።

በጮቄ ተራራ ሰንሰለት ደረት ላይ ያሉ የእርሻ ቦታዎች (ማሳዎች) በተደጋጋሚ እና ያለእረፍት ስለሚታረሱ ለአፈር እጥበት ተዳርገዋል። ከዚያም አልፎ አብዛኛው የተራራው ሰንሰለት አካባቢ ለምድረ-በዳ መሰል ገጽታ ተጋልጧል። የጮቄ አካባቢ ማሳዎች አፈር ታጥቦ፣ የቀረው አፈር አሲዳማ በመሆኑ እህል የማምረት አቅሙ ተመናምኗል። በዚህ ምክንያት የጮቄ ተራራ ሰንሰለት አካባቢ ለሌሎች የሚተርፍ አምራች የነበረ፣ በ20 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ግን የአካባቢው ሕዝብ ራሱን ወደ ማይችልበት ደረጃ ደርሷል። የአካባቢው የሳር ሽፋንም ተመናምኖ የግጦሽ መሬቶች ከጥቅም ውጭ በመሆን ላይ ይገኛሉ።

የሕዝብ ቁጥር በመጨመሩ ምክንያት መታረስ የሌለባቸው አካባቢዎች፣ ለምሳሌ በጣም ተዳፋት የሆኑ አካባቢዎች ስለሚታረሱ፣ አፈሩ በዝናብ ጎርፍ ይከላል። የሚከላው አፈርም ደለል ሆኖ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ፣ እንዲሁም ለሌሎች ወደፊት በአባይ ላይ ለሚገነቡ ግድቦች ተግዳሮት ይሆናል። ይህ ሁኔታ የሚከሰተው በጮቄ ተፋሰስ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉም የአባይ ተፋሰስ አካባቢዎች ከፍተኛ ችግር መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

በተራራው ሰንሰለት የተከሰቱ ችግሮችን ለመታደግ የተወሰዱ እርምጃዎች

የጮቄ ተራራ ሰንሰለት መጎሳቆል ያሳሰባቸው ግለሰቦች እና ተቋማት ተሰባስበው ለመጀመሪያ ጊዜ በምስራቅ ጎጃም ዞን በደብረ ማርቆስ ከተማ በ1999 ዓ.ም አውደ ጥናት አካሂደው ነበር። በአውደ ጥናቱ የተሳተፉ የተወሰኑ የአካባቢው ገበሬ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተጠሪዎች፣ የደብረ ማርቆስና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች፣ የአባይ ምሥራቅ ተፋሰስ ቢሮ (Eastern Nile Technical Regional Office-ENTRO)፣ የኢትዮጵያ ተሰነአዊ ቴክኖሎጂ ማህበር (Ethiopian Society for Appropriate Technology-ESAT) እና የበጎ አድራጎት ድርጅት ዓለም አቀፍ የልማት ተቋም (International Development Enterprise-IDE) ነበሩ።

እነዚህ ጉዳዩ ይመለከተናል ብለው ያመኑ ተቋማትና ግለሰቦች ተሰባስበው ከተወያዩ በኋላ ጉዳዩን የሚከታተል አንድ የባለሙያዎች ኮሚቴ አቋቋሙ። ከዚያ በኋላ የአካባቢውን ችግር በመታደግ ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞችን ለመቅረጽ የተቻለ ሲሆን ሂደቱም ለቀጣይ ፕሮግራሞች መሠረት ለመሆን በቅቷል።

ከጽሁፍ አቅራቢዎች መካከል በአንደኛው (በበላይ ስማኒ) የተመራው የዩኒቨርሲቲዎች ትብብር ብዙ ጠቃሚ ተግባራትን አከናውኗል። የመጀመሪያው ጉዳይ በአውደ ጥናቶች በመሳተፍ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ እቅዶች መነደፋቸው ነው። ዩኒቨርሲቲዎችም (ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ዊስኮንሲን ዩኒቨርሲቲ እና ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ)፣ የተወሰኑ የድህረ-ምረቃ ተማሪዎቻቸው የመመረቂያ ምርምሮቻቸውን በጮቄ ተራራ ሰንሰለት ላይ እንዲመሠረቱ ማድርግ ተችሏል። ከተለያዩ ምርምሮች (ማህበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ተቋማዊና ስነ-ምህዳራዊ፣ ወዘተ) በተገኘ

 ውጤት መሰረት ስለ ጮቄ ተራራ ሰንሰለት ጠቀሜታ ያላቸው ብዙ መረጃዎች ተገኝተዋል። ከምርምር ስራዎች በተጓዳኝ በተደጋጋሚ ስለ ጮቄ ተራራ ሰንሰለት፤ የአገር ቤት እና የውጭ ዩኒቨርሲቲዎች የተሳተፉባቸው የተለያዩ አውደ-ጥናቶች ተካሂደዋል። በሂደቱም የተማረ የሰው ኃይል ለማጎልበት ጥረት ተደርጓል።

ጮቄን ለመታደግ የተወሰዱ ተግባራት

የጮቄ አካባቢ ሥነ- ምህዳር ጠቀሜታው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለአባይ ተፋሰስ ሀገራትም ጭምር ነው። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የጮቄ ተራራ ቀድሞ ከሚገኝበት ይዞታው በእጅጉ ተጎሳቁሎ ይገኛል። የተራራውን መጐሳቆል ለመታደግ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እና በሌሎች ድጋፍ ሰጪ አካላት ትብብር የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል። የተከናወኑ ተግባራት በሚከተለው መልኩ በአጭሩ ቀርበዋል፡

ጥናት፣ ምርምርና የሰው ኃይል አቅም ግንባታ፡

ስምንት የዶክትሬት እና 12 የማስተርስ ዲግሪ ተማሪዎች የመመረቂያ ምርምሮቻቸውን በጮቄ አካላዊና ስነ-ህይወታዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዳራዎች ላይ እንዲያተኩሩ ተደርጓል። ከመመረቂያ ስራዎቻቸው በተጨማሪ በርካታ ሙያ ተኮር መጽሄቶች (ጆርናሎች)፣ መጽሐፎችና የተለያዩ የስብሰባ ሰነዶች (ፕሮሲዲንጎች) ታትመዋል። ከምርምሩ በተገኘው ውጤት መሠረት የአየር ንብረትን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ በጮቄ ሥነ- ምህዳር ለመገንባት እና የልማት እቅድ (ፕሮፖዛል) ለማዘጋጀት ሀገሪቱ ለምታደርገው የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም እና አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ስርዓት አስተዋፅኦ አድርጓል።

የጮቄ ተራራ ተፋሰስን ባለው ተፈጥሯዊ፣ ማህበረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ሀብቶች መሰረት ለስድስት ስርአተ-ምህዳር በመክፈል ለእያንዳንዱ ስርአተ-ምህዳር የልማትና የእድገት አቅጣጫን ጠቁሟል። ለእያንዳንዱ ስርአተ-ምህዳር ያለውን ሀብትና ችግር በመለየት የወደፊቱን የምርምርና የልማት አቅጣጫ አሳይቷል። ምርምሮች/ጥናቶች በጮቄ ተፋሰስ የሚገኙ የእርሻ ስነ-ምህዳሮችን ለአየር ንብረት መቀየርና መለወጥ ያላቸውን ተጋላጭነት አመላካች የሆኑ ማህበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ተቋማዊና ስነ-ምህዳራዊ ሁኔታዎችን አመላክተዋል። የአየር ንብረት መቀየርና መለወጥ የሚያስከትሏቸውን ተፅእኖዎች እና የወደፊት የልማት አቅጣጫዎችን ጠቁመዋል።

የልማት ሥራዎች፡

ከደ/ማርቆስና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከምስራቅ ጎጃም አካባቢ ጥበቃ፣ የገጠር መሬት አጠቃቀምና አስተዳደር መምሪያ ጋር በመተባበር የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ተከትሎ የአካባቢውን ሕዝብ ኑሮ ለማሻሻል፣ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሃብት ለመጠበቅና በዘላቂነት ለመጠቀም የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ተግባራት ተከናውነዋል። ዓላማዎቻቸውም የሚከተሉትን ማሳካት ነበር፡ –

  • የመሬት ልብስ አልባ መሆንና እነኝህም ክስተቶች ሊያስከትሉ የሚችሉትን ተፅዕኖ መዋጋት ብሎም ማሸነፍ፣
  • የተሞከሩና ጥሩ ውጤት ያመጡ ተለምዷዊ አሠራሮችና ድርጊቶች እንዲስፋፉ ማመቻቸት፣
  • የአካባቢው ሕዝብ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ተላቆ የሚያመርተውን በብዛትም ሆነ በጥራት አሻሽሎ ከሽያጭ ጠቀም ያለ ገቢን እንዲያገኝ አስፈላጊውን ድጋፍ ማበርከት እና
  • ገበሬው ምርቱን ወደ ገበያ በቀላሉ ለማቅረብ የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዲሟሉ፣ አምራችና ገበያ በቅርበት ግንኙነት እንዲመሰርቱ መጣር የሚሉት ናቸው።

በጮቄ የተፋሰስ ልማት በ23 ማህበራት የማህበረሰብ አካባቢ ለዘላቂ ልማት ፕሮጀክቶች ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ ተቀርፀው ተግባራዊ ተደርገዋል። ከ2,300 በላይ ለሆኑ የማህበሩ ተጠቃሚዎች፣ ለፌዴራል፣ ለዞንና ለወረዳ ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጥቷል። ስልጠናውም በስራ አመራር፣ በተፈጥሮ ሃብት አያያዝ፣ በእንስሳት እርባታና መኖ ልማት ላይ ያተኮረ ነበረ። በትምህርት ቤት ለሚገኙ የአካባቢ እንክብካቤ አባላትና ለክበቡ ሃላፊዎች ስለ ብዝሃ- ህይወት አያያዝና አጠቃቀም’፤ የጮቄ ተራራ ሰንሰለት አሁን ስላለበት ደረጃ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል።

የአየር ንብረት ተለዋዋጭነትን የሚቋቋም የተሳለጠ የአረንጓዴ ልማት መንደር (የልቀት ማዕከል) ማቋቋም፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከደ/ማርቆስ ዩኒቨርሲቲና ከምስራቅ ጎጃም አካባቢ ጥበቃ፣ የገጠር መሬት አጠቃቀምና አስተዳደር መምሪያ ጋር በመተባበር 13 የአረንጓዴ ልማት መንደሮችን አቋቁሟ ል። የዚህ ፕሮጀክት ዋና ዓላማ በአነስተኛ የእርሻ ይዞታዎች ላይ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የአርሶ አደሩን ገቢ ከማሳደግ ባሻገር የአየር ንብረት ተለዋዋጭነትን መቋቋምና የካርቦን ልቀትን መቀነስ ነው። ይህን ስራ ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ግብዓቶችን በአግባቡ መጠቀም፣ የአካባቢ ደህንነትን መጠበቅ እና መልካም ተሞክሮዎችን በመቀመር የግብርና ፖሊስዎችን፣ ገበያን ያማከሉ የአመራረት ዘይቤን እንዲሁም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን ካላስፈላጊ ተፅዕኖ የሚያላቅቅ የግብርና ስርዓት መዘርጋት ነው።

ከላይ የተገለፁትን ውጤቶች ለማምጣት የአየር ንብረት ተለዋዋጭነትን የሚቋቋም የሰላ መንደር ሞዴልን መመስረት ያስፈልጋል። ትኩረቱም የማህበረሰቡን የአየር ንብረት መለዋወጥ የመቋቋም ክህሎቶችና ዘይቤዎች ላይ ይሆናል። በተለይ ወቅታዊ የዝናብ መለዋወጥ፣ ደረቃማ ወቅቶችን፣ የሰብልና የእንስሳት በሽታዎችን እና ሌሎች ምርት- አጋች ሁኔታዎችን ከመቋቋም አንፃር የህብረተሰቡን ተለምዷዊ እንቅስቃሴ ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት። የዚህ ቅኝት ግብም የአየር ንብረት ተለዋዋጭነትን መጋፈጥ፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እና የቤተሰብ ገቢን ማሻሻል ላይ ያተኮረ ነበር።

የትኩረት መስኰቹም የተለያዩ ሰብሎችን አማካይ ምርታማነት በ50 በመቶ ማሳደግ፤ ለ50 በመቶ ለሚሆኑ ቤተሰቦች የሰላ ጓሮ እርሻ ስልጠና መስጠት፣ መደገፍና እርሻዎቹ እንዲቋቋሙ ማድረግ፤ ወጣቶችን በመደገፍና በማሰልጠን የተሻሻሉ የባዮጋዝ ምድጃዎችንና የባዮጋዝ ማብላያዎችን እንዲሰሩ ማገዝ፡ የንፁህ ውሃ አቅርቦትንና የፅዳት መሣሪያዎችን በቤተሰብ ደረጃ ማሻሻልና አነስተኛ የገበያ ድርጅቶችን መመስረት ናቸው።

የብዝሃ-ህይወት ማካተቻና ማትጊያ ፕሮጀክት፡

ይህ ፕሮጀክት ከ2008-2011 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ የጮቄን ብዝሃ- ህይወት ሀብት ከተጋረጠበትና ወደፊት ሊገጥሙት ከሚችሉ ተግዳሮቶች እንዲጠበቅ ማድረግ ነበር። ፕሮጀክቱ በየደረጃው ያሉ ፖሊሲ አውጪዎችና ውሳኔ ሰጪ አካላት የብዝሃ-ህይወት ሀብት ለብሔራዊና አካባቢያዊ ኢኮኖሚ ልማት ያለውን ፋይዳ እንዲገነዘቡ ስላደረጋቸው ለብዝሃ-ህይወት ጥበቃ ዘርፍ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርጉ/እንዲጨምሩ አድርጓቸዋል።

ፖሊሲ፡

ጮቄ የአባይ የውሀ ጋንና የብዝሃ-ህይወት አምባ ቢሆንም በአግባቡ ትኩረት ተሰጥቶት እንክብካቤና ተገቢው ጥበቃ እየተደረገለት አይደለም። እየተመናመነ ያለው የጮቄ አናት ጥበቃ እንዲደረግለት የክልሉ መንግሰት ደንብ አውጥቶለታል (ደንብ ቁጥር 184/2011 ዓ.ም፡ በአማራ ክልላዊ መንግስት የጮቄ የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራን ዳር ድንበር አከላለልና አስተዳደር ለመወሰን የወጣ የክልል መስተዳድር ምክር ቤት ደንብ)። በመመሪያ የተደገፈ የሰው ሃብት፣ በጀትና ቁሳቁስ የተሟሉለት ተቋም መስርቶ ተግባራዊ ማድረግ ግን ያስፈልጋል። ስለሆነም የክልሉ መንግሥት ጮቄን የመጠበቅና ከልሎ ብሄራዊ ፓርክ እንዲሆን የማድረግ ጉዳይ በይደር የሚያቆየው ተግባር መሆን የለበትም። የክልልና የዞን አመራሮችም ትኩረት ሰጥተው ጮቄ የሚያበረክተውን የስርዓተ-ምህዳር አገልግሎት በዘላቂነት እንዲቀጥል ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል ተቋማት ጋር በጋራ መስራት ይገባቸዋል።

 መደምደሚያ

በጮቄ ተፋሰስ የሚታዩ ዋና ዋና ችግሮች የመሬት መጎሳቆል፣ የአየር ንብረት ተለዋዋጭነት፣ የህዝብ እና የእንስሳት ቁጥር መጨመር፣ ተራራማ ቦታዎችን ለእርሻ ስራ ማዋልና አግባብ ያልሆነ አስተራረስ፣ የብዝሃ-ህይወት መመናመንና መጥፋት፣ የአፈር ለምነት መቀነስና ድህነት ናቸው። በመሆኑም ችግሮችን በመፍታት፣ የግብርናን ውጤታማነት በመጨመር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሳይንሳዊ የሆኑ አማራጭ መንገዶችን መከተል አስፈላጊ ነው።

የጮቄ ተራራ ቁንጮ በፓርክነት ከተከለለና ህጋዊ እውቅና ካገኘ፣ የውሀ ጋንነቱን ጠብቆ በማቆየት ለአየር ንብረት ለውጥ መጠበቅ እና እንክብካቤ፣ በስነ-ምህዳሩ ያለውን ብዝሃ-ህይወት መጠበቅም ይቻላል። ለተመራማሪዎች እና ለተማሪዎች ምርምር ማካሄጃነትም ምቹ ይሆናል። አካባቢውን ለቱሪዝም ተግባር በማዘጋጀት፣ የቱሪዝም መስህብ ማድረግም ሌላው አማራጭ ነው። መጭው ትውልድም ተስማሚ የአየር ንብረት ያለውና የለማ አካባቢ ይረከባል። ለታላቁ ህዳሴ ግድብም ለተፋሰሶቹ ከጋኑ የሚለግሰው ፀጋ ተጠብቆ ይቆያል። ለዚህም በዞን፣ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ ያሉ አመራሮች ሦስት ዋና ዋና ተግባራትን ማከናወን ይኖርባቸዋል። እነሱም (ሀ) በጮቄ ተራራ የሚታየውን የሰፈራ መስፋፋት መግታት፣ (ለ) የሰንሰለቱን ክብካቤ ተግባር በባለቤትነት እና በኃላፊነት መንፈስ መተግበር እና (ሐ) በአካባቢው ያሉ ወረዳዎች በቅንጅት እንዲሰሩ ማድረግ ናቸው።

የጮቄ ልማት ለኢትዮጵያ፣ ለሱዳን፤ ለግብፅና እንዲሁም ለዓለም ማህበረሰብ ጠቀሜታ ያለው ስለሆነ፣ የአካባቢውን ክብካቤና ልማት በትብብር ማከናወን ያስፈልጋል። ከፓርኩ ውጭ ባሉ ተፋሰሶችም የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን መቋቋምና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ስለሆነም ከአካበቢው ስነ-ምህዳር ጋር በተዛመደ መልኩ የተሳለጠ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የግብርና ሥርዓትን መከተል (ስራ ላይ ማዋል) ዘላቂ ልማትን ያመጣል።

አንዱ እና ዋናው ችግር የሕዝብ ቁጥር መጨመር እና በተወሰነ የእርሻ መሬት (ማሳ) ላይ በየቀኑ የሚጨምር የሕዝብ ፍላጎትን ማርካት አለመቻሉ ነው። ችግሩን ለማቃለል የአካባቢውን ወጣቶች ከመሬት ቀጥተኛ ተጠቃሚነት ማላቀቅ ያስፈልጋል። የኑሮ አለኝታቸውን ግብርና ስራ ላይ ብቻ ሳይወሰን በሌሎች የሰው ኃይል በሚሹ ተግባራት ላይም ማሠማራት ይገባል፣ ለምሳሌ ኢንዱስትሪ። በጣም የተጎዱ አካባቢዎችን ከሰውም ሆነ ከከብት ተፅእኖ በመከለል እንዲያገግሙ ማድረግም ተገቢ ነው። አካባቢን መንከባከብ የአካባቢውን ማህበረሰብ ይታደጋል፣ ብሎም ዘላቂ ጥቅም የማግኘት ሁኔታ ይሻሻላል። ምክንያቱም የአካባቢው ተፈጥሮ ሃብት ተጎሳቁሎ ተፈጥሮ ከችግራቸው ልትታደጋቸው አትችልምና።

በተፋሰሱ የሚኖሩ ወጣቶች አብዛኛዎቹ መሬት አልባ በመሆናቸው ለደን መጨፍጨፍ ዋነኛ ምክንያት ናቸው። ችግሩን ለመቀነስ በአካባቢው የስራ እድል ሊፈጠር ይገባል። አርሶ አደሮች ችግርን የመቋቋም አቅማቸውን ማዳበርና ማጠናከር፣ የመሰረተ-ልማት ግንባታን ማስፋፋትና ማጠናከር፣ የብድርና ቁጠባ አገልግሎት ተደራሽነትም መስፋፋት ይኖርበታል።

ለችግሮች ዋና እና ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው ግን የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ መቅረፅና ሥራ ላይ ማዋል መሆኑ ይታመናል። በአጭር ጊዜ ሂደት ግን የአካባቢውን መሬት በተሻለ መንገድ ለመጠቀም የሚያስችል ስልት መቅረፅ ያሻል። የተራራው አናት ከሰው አሉታዊ ንኪኪ እንዲላቀቅ ተከልሎ የዝናብ ውሃ ሰርጐ መግቢያነቱ እንዲቀጥል፣ ወንዞች እና ጅረቶች ዓመት እስከ ዓመት እንዲፈሱ ማመቻቸት ያስፈልጋል።

ለዚህም በአካባቢ ልማት ላይ የተሰማሩ መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ዕውቀትና ክህሎት ለአካባቢው ሕዝብ ማበርከት፣የአካባቢው ሕዝብ ደግሞ ምክሩን ተቀብሎ ክህሎቱን አንግቦ አካባቢውን በተሻለ ሁኔታ እንዲንከባከብ ማድረግ ይገባል።መንግሥትም ይህን ለመተግበር የሚያስችል ፖሊሲ ማውጣት እና ማስፈጸሚያ ሕግ መደንገግም ይኖርበታል። የአካባቢው ሕዝብና መንግሥት ተጋግዘውና ተባብረው ያልተቆጠበ ተሳትፎ እንዲያበረክቱ መምከር፣ ማሳመን እና ምክሩን እንዲተገብሩ እገዛ ማድረግንም ይጠይቃል።

የአካባቢው ሥነ-ምህዳር በግርድፉ ሲዳሰስ ከጮቄ ተራራ አናት አንስቶ እስከ አባይ ወንዝ ድረስ ያለውን የሚያጠቃልል ነው። ይህም ከ2,800 ሜትር ከባህር ወለል በላይ ያለው መሬት ለእርሻ አገልግሎት(ቆላው ለጭረት እና ለፍራፍሬ ምርቶች ማምረቻነት) ሊውል ይችላል። ከ2,800-3,000 ሜትር ከባህር ወለል በላይ ያለው መሬት ልዩ ልዩ የደጋ ሰብሎች እና ፍራፍሬዎች ይመረቱበታል። ከ3,000—3,600 ሜትር ከባህር ወለል በላይ ያለው መሬት ለደን ልማት (ለኢንዱስትሪ ግብዓት) እና ለደጋ ፍራፍሬ ማምረቻነት ይውላል። ከ3,600 ሜትር ከባህር ወለል በላይ ያለው መሬት ደግሞ ለብዝሃ-ህይወት መንከባከቢያና ለቱሪስት መስህብነት አገልግሎት ሊውል የሚችል አካባቢ ነው። የዚህ አካባቢ ሥነ- ምህዳር ጠቀሜታው ለኢትዮጵያ ብቻ አይደለም። በአጠቃላይ ለአባይ ተፋሰስ ሀገሮች (ግብፅ እና ሱዳን) ስለሆነ፣ በአሁኑ ወቅት በመጎሳቆል ላይ የሚገኘውን አካባቢ እንዲያገግም የማድረግ ጥረት የሁሉንም የተፋሰሱ አገራት ተሳትፎ ይጠይቃል።

የመሬት አጠቃቀምን በተመለከተ ከላይ በካርታው በግርድፉ በሰፈረው መሰረት ማስተናገድ የሚቻል ቢሆንም፣ አካባቢውን ለመታደግ ግን ፖሊሲ፣ ሕግ እና ደንብ መውጣቱ የግድ ይሆናል። የሚቀረፀው የመሬት አስተዳደር ፖሊሲ ደግሞ የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር በአግባቡ ያገናዘበ መሆን ይገባዋል።

ደን ለአካባቢ ጥበቃ ዋነኛው መሰረት ነው። የደጋ ቀርከሃ፣ አስታ፣ ኮሶ፣ ኮርች ወዘተ ለደንነት ተግባር ያገለግላሉ። የደጋ ፍራፍሬ ዛፎችን ተክሎና ተንከባክቦ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለምግብ ኢንዱስትሪ ግብዓት ማድረግም ይቻላል። የደን (ዛፍ) ውጤትን እንደ ጥሬ እቃነት የሚያውሉ ኢንዱስትሪዎችን (ለምሳሌ፣ ለቤት ወለል እና ጣራ ስራ/ ግንባታ) ታሳቢ ማድረግ ይገባል።

ሂደቱ በቴክኖሎጂ ግብዓትነት መታገዝ እንዳለበት ቢታመንም፣ አዳዲስ የግብርና ምርት ግብዓቶችም ቢሆኑ እንደ ቀላል ተግባር መወሰድ የለባቸውም። ለምሳሌ ፖም ማምረት ብዙ እውቀት የሚጠይቅ እና በጥንቃቄ መያዝ ያለበት ተግባር ነው። ምርቱም ሆነ ጣዕሙ ሳይቀንስ ከዓመት እስከ ዓመት ማምረት ያዳግታል።ስለሆነም አምራቹ ገበሬ ቴክኖሎጂ ነክ መረጃዎችን በተደጋጋሚ እንዲጠቀም ማድረግን ይጠይቃል።

የተጎሳቆለ አካባቢ ሊያገግም የሚችለው የአካባቢው ማህበረሰብ አምኖበት በተግባሩ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን ሲችል ነው። የልማት ተግባርን በትእዛዝ ውጤታማ ማድረግ አይቻልም። ምክንያቱም የተፈጥሮ ሃብት ልማትና አጠቃቀም የአካባቢው ማህበረሰብ በስምምነት ላይ ደንብ እና ሥርዓት ማበጀት የግድ ነው።

ዘመን መጽሄት ግንቦት 2014 ዓ.ም

Recommended For You