ዳግም ድል

 ጣልያን በ1888 ዓ.ም. በጥቋቁሮቹ ኢትዮጵያውያን አናብስት በአድዋ ተራሮች ስር አሳፋሪ ሽንፈት ተከናንባ አንገቷን ለመድፋት ተገደደች። በጀግኖች ኢትዮጵያን የደረሰባትን ቅስም ሰባሪ ሽንፈት ተበቅላ ቀና ለማለት ለ40 ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ ስትዘጋጅ ቆየች። በቅኝ ግዛት በያዘቻቸው ኤርትራ እና ሶማሊያ ግዛት ጦሯን ስታከማች ሰንብታ መሪዋ ዱቼ ሙሶሎኒ ለምስራቅ አፍሪካው የጣልያን ጦር አዛዥ ጀኔራል ደቦኖ ደብዳቤ ጻፈ።

ጳውሎስ ኞኞ “የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት” በሚል መስከረም 1980 ዓ.ም. ባሳተመው መጽሐፉ እንዳሰፈረው ደብዳቤው ‹‹…ጦርነቱ በጥቅምት መጨረሻ ወይም በኅዳር ወር እንዲጀምር ይሁን። …ከሁለቱ ቅኝ ግዛቶቻችን ከተጨመሩት አንድ መቶ ሺ ጥቁር ወታደሮች ጋር አሁን 300‚000 ወታደር አለህ። በተጨማሪ 500 ያህል አይሮፕላኖችና 300 መኪናዎችም አሉህ። በጥቅምት ወር ሶስት ዲቪዚዮን ጦር እንዲጨመርልህ ጠይቀሃል። አስር እልክልሃለሁ። እደግመዋለሁ አስር እልክልሃለሁ። … በጥቂት ሺ ሰዎች እጥረት ምክንያት የአድዋን ድል አጣነው። ያን ስህተት አንደግመውም›› የሚል ነበር።

ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ታሪክ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ 168 ላይ በኢትዮጵያ እና ጣሊያን ሰራዊቶች መካከል የነበረውን አለመመጣጠን ሲገልጹ ‹‹ … ጣልያኖች በሰሜን ሶስት መቶ፣ በደቡብ አንድ መቶ የጦር አውሮፕላን በማሰለፍ መላ ሰማዩን ሲቆጣጠሩ ኢትዮጵያ ማሰለፍ የቻለችው ስምንት አውሮፕላኖች ብቻ ነበር። እነዚህም አብዛኛዎቹ ለጭነት እንጂ ለውጊያ የሚያገለግሉ አልነበሩም። በዚህ ላይ የጣልያኖች የመርዝ ጋዝ ሲጨመርበት ኢትዮጵያውያን መሸነፋቸው ሳይሆን ያን ያህል መዋጋታቸው ነው የሚገርመው። በስንቅና ትጥቅም ረገድ ልዩነቱ እጅግ የሰፋ ነበር። የኢትዮጵያ ሠራዊት ዘመናዊ የስንቅና ትጥቅ ድርጅት ያለው አልነበረም። ቁስለኞች ህክምና ማግኘት የሚችሉትም ጦሩን ለመርዳት ብለው በፈቃዳቸው ከውጭ አገር በመጡ የህክምና ሰዎች አማካኝነት እንጂ የተደራጀ የህክምና ክፍል አልነበረም። የሬዲዮ ግንኙነት ባለመኖሩ ወይም በቅጡ ባለመስራቱ ወታደራዊ እርምጃን ማቀናጀት አስቸጋሪ ነበር›› በማለት ጽፈዋል።

አቶ ተረፈ ወርቁ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታሪክና ቅርስ አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በደቡብ አፍሪካ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ በቤተመዘክርና ቅርስ ጥናት ሰርተዋል። አቶ ተረፈ እንደሚናገሩት የሁለተኛው የጣልያን ወረራ ዋነኛ ምክንያት ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት ባገኘችው ድል በአፍሪካ፣ በጥቁሩ ዓለም እንዲሁም በአጠቃላይ በሰው ልጆች ታሪክ የነጻነት ተምሳሌትና አርማ ሆና መታየቷ ነው። ኢትዮጵያ በአድዋ ላይ የነጮችን የበላይነትና ኩራት በድል መትታ የሰበረች አገር ናት። በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለመበገርና የእንቢተኝነት መንፈስ እንዲነቃቃ ለጥቁር ሕዝቦች ደግሞ ከፍተኛ ወኔ እንዲኖራቸው ያደረገች በመሆኗ ኢትዮጵያን በመቅጣት በነጮች ላይ የደረሰውን ቅሌት እንደገና በክብር ለመመለስ የፋሽስት ጣልያን መንግሥት ወራሪ ጦሩን በከፍተኛ ሁኔታ አደራጅቶ መጥቷል።

ጣሊያኖች ወራሪ ጦራቸውን ከማደራጀት ባለፈ አድዋ ላይ የገጠማቸው ሽንፈት በኢትዮጵያውያን አንድነትና ህብረት መሆኑን ተረድተው በሕዝቡ ዘንድ ያለውን አንድነት ለማላላት በሀይማኖት፣ በጎሳ፣ በዘር፣ በስነ-ልቦና እና በጥቅም ህዝቡን ለመለያየት አስቀድመው መሥራታቸውን አቶ ተረፈ ይጠቅሳሉ። ጣልያኖች ለበቀል እስከ ምን ድረስ እንደተዘጋጁ ሲያስረዱ የምስራቅ አፍሪካ ገዢ የነበረው ግራዚያኒ ለዱቼ ሙሶሎኒ በአንድ ወቅት በጻፈው ደብዳቤ ኢትዮጵያን ከተቻለ ከሕዝቦቿ ጋር ካልተቻለ ግን ሕዝቦቿን በጦርነት በመጨረስ ገፀ-በረከት አድርጎ እንደሚያቀርብ መግለጹን ይጠቅሳሉ።

የፋሽስት ጣልያን መንግሥት ከፍተኛ ዝግጅት አድርጎ ወደ ጦርነቱ ሲገባ ኢትዮጵያውያን በአድዋ ጦርነት ድል ተመቻችተው ብዙ ዝግጅት አለማድረጋቸውን አቶ ተረፈ በቁጭት አውስተው በተለይ ከአይሮፕላን ላይ የሚለቀቀው የመርዝ ጋዝ (ጭስ) ከፍተኛ የሆነ ሽብርና እልቂት እንደፈጠረ ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት አብዛኛው የገበሬ ጦር ስለነበረ የመርዝ ጋዙን ከእግዚአብሔር የተላከ መቅሰፍት አድርገው የቆጠሩ እንደነበሩ ያነሳሉ።

ጳውሎስ ኞኞ እንደሚተርከው ጣልያኖች 40 ዓመት ሙሉ መዘጋጀት የሚገባቸውን ያህል ተዘጋጅተው በ1927 ዓ.ም. የጦርነቱ ሰበብ ወልወል ላይ እንዲጀመር አደረጉ።

ወልወል በቀድሞ አጠራር በሐረርጌ ክፍለ አገር በኦጋዴን ውስጥ የሚገኝ ከወሰን 96 ኪሎ ሜትር የሚርቅ የኢትዮጵያ መሬት ነው። ሙሶሎኒ ለኢጣሊያ ሶማሊያ ቅኝ ግዛት ገዢ ለነበረው ራቫ ወሰን አልፈው ገፍተው እንዲሄዱ ባስተላለፈው ትዕዛዝ መሰረት ወታደሮች ወልወል ላይ ሰፈሩ። ኅዳር 14 ቀን 1927 ዓ.ም. የኢትዮጵያና የእንግሊዝ የወሰን ኮሚሽን ሹማምንት ድንበር የማካለል ሥራ ለመሥራት ወልወል ሲደርሱ 250 የኢጣሊያ ወታደሮች ለጦርነት በሙሉ ትጥቅ ተሰልፈው ወሰን ተካላዮችን አቆሟቸው። የተከሉትን የጣልያን ባንዲራም አልፈው እንዳይሄዱ አስጠነቀቋቸው።

ወሰን ተካላዮችን አጅበው የመጡት ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ግን ከጣልያኖች ጋር ተፋጠጡ።

ወሰን ተካላይ ሹማምንቶቹ ጠብ እንዳይነሳ በማለት በትዕዛዝ ብቻ ሊመለሱላቸው ስላልቻሉ፤ በልመናም ጭምር የኢትዮጵያን ወታደሮች ንዴት አበረዱት። በቅርብ ርቀት ሆነው ተፋጠው ዋሉ፤ተፋጠው አነጉ።

ይህ በእንዲህ እያለ በሹማምንቶች መካከል ንግግር እየተደረገ ባለበት ወቅት ኅዳር 26 ቀን ረቡዕ ልክ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ሲሆን በድንገት ጣልያኖች በኢትዮጵያውያን ወታደሮች ላይ አደጋ ጣሉ። ወዲያውም በሰማይ አይሮፕላኖች በምድር ታንኮች ደርሰው በመድፍና በቦንብ መሬቲቱ ተርገበገበች። ኢትዮጵያውያኑም ያሉበትን ስፍራ ሳይለቁ ባላቸው አሮጌ መሳሪያ እስከ ሌሊቱ አምስት ሰዓት በጀግንነት ተዋጉ። በዚህም ጦርነት 94 ኢትዮጵያውያን በጀግንነት ሲወድቁ 45 ቆሰሉ። ከጣሊያኖች ደግሞ 127 ወታደሮች ሞተዋል። ከብዙ የጀግንነት ተጋድሎ በኋላ በጦር መሪዎች ትዕዛዝ ሠራዊቱ ወደ አዶ አፈገፈገ። የእንግሊዝ መቶ አለቃ ክሊንግውድ የወልወልን ጦርነት እና የኢጣሊያን የግፍ አሠራር በፊልም ቀርጾት ስለነበረ ለንደን እንደገባ በእንግሊዝ ሕዝብ ዘንድ በአድናቆትና በሐዘን ታይቷል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ይህን የጣልያን የግፍ አድራጎት በመቃወም አዲስ አበባ ከተማ ላለው የጣልያን መንግስት ጉዳይ ፈጻሚ ለሲኞር ሞምቢሌ በደብዳቤ ገለጹ። ጉዳይ ፈጻሚውም ጥፋቱ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሆነ፣ ለተገደሉባቸው የጣልያን ወታደሮች ካሳ እንዲከፈላቸው እንዲሁም ይቅርታ እንዲጠየቁ በማሳሰብ የካሳውን እና የይቅርታ ስነ-ስርዓቱን ዝርዝር በማከል መልስ ሰጠ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከጣልያን መንግሥት የቀረበውን የካሳና የይቅርታ ሀሳብ ሳይቀበል ጉዳዩ በሊግ ኦፍ ኔሽን (የባለ ቃል ኪዳን አገር) እንዲታይ ክስ አቀረበ። በየጊዜው የተሰበሰበው ጉባዔና ለዚሁ ጉዳይ የተመረጡ ዳኞችም አንዳችም እርዳታና ደጋፊ ውሳኔ ለኢትዮጵያ ሳይሰጧት ጉዳዩን በማድበስበስ ቆዩ።

ጉዳዩ ተድበስብሶ ተይዞ እያለ ከወልወል በተጨማሪ ከፋሽስት ጣልያን ወታደር ጋር ቆራሄ ላይ ከፍተኛ ጦርነት ተካሂዶ ብዙ ጀግኖች ተሰውተዋል። በዚህ ጦርነት ከፍተኛ ተጋድሎ ካደረጉት መካከል አንዱ ደጃዝማች አፈወርቅ ወልደ ሰማዕት ናቸው። ያን ጊዜ አፈወርቅ የነበራቸው ማዕረግ ግራዝማችነት ነው፤ ደጃዝማች የተባሉት ከሞቱ በኋላ ነው።

ደጃዝማች አፈወርቅ ቆራሄ ላይ ምርጥ ምሽግ አሠርተው ነበር። ጣልያን ምሽጉን ለመያዝ ዘወትር በአይሮፕላን በቦምብ ይደበደባል። ምሽጉ ግን እንደ አለት ጠጥሮ ምንም አላስነካም። ደጃዝማች አፈወርቅ ብቸኛውን ፀረ አይሮፕላን መሳሪያ ይተኩሳሉ። ኢትዮጵያውያን ወታደሮች አይሮፕላን ለመምታት በየምሽጋቸው ሆነው በጠመንጃ ይተኩሳሉ። ደጃዝማች አፈወርቅ በወታደሩ መሀል እየተገኙ ያነቃቃሉ። በሬዲዮ መገናኛ ዕርዳታ እንዲደርሳቸውና ጦራቸው እንዲጠናከር ይጠይቃሉ። ለጥያቄያቸው ሁሉ ግን መልስ አላገኙም።

አስቸጋሪ ሆኖ የቆየውን የቆራሄ ምሽግ ጣልያኖች በተጠናከረ ኃይል ለመስበርና ለመያዝ ተነሱ። ስድስት ክፍለ ጦር ወታደሮች፣ 150 ካሚዮኖች፣ አራት ታላላቅ መድፎች፣ ዘጠኝ ታንኮች እና 30 ብረት ለበስ መኪናዎች በአንድነት ሆነው ተሰለፉ። ስንቅና ትጥቁ የተሟላለት የጣልያን ጦር ወደቆራሄ በሚያመራበት ጊዜ ቆራሄ ያለው የኢትዮጵያ ወታደር የነበረው ጭብጥ በሶና የመጨረሻዋ ኩባያ የማትሞላ ውሃ ብቻ ነበረች። ደጃዝማች አፈወርቅ የተዳከመ ጦራቸውን እየተዟዟሩ ‹‹አፈወርቅ እጁን ለጠላት አይሰጥም፤ አንተም የአፈወርቅ ነህና የተቀደሰ እጅህን ላልተቀደሰ ጠላት አትሰጥም›› እያሉ ያበረታቱ ነበር።

ከሌሎቹ ቀናት በተለየ ሃያ አውሮፕላኖች የቆራሄን ምሽግ እየተመላለሱ ቦምብ በመጣል ደበደቡት። ደጃዝማች አፈወርቅ ብቸኛ ፀረ አውሮፕላን መሳሪያቸውን ከየአቅጣጫው በሚመጣው አውሮፕላን ላይ እየተዘዋወሩ ተኮሱ። በመሃል ከአይሮፕላን ላይ በተጣለ ቦምብ እግራቸውን ተመቱ፤ ክፉኛም ቆሰሉ። ክፉኛ የቀሰለ እግራቸውን እየጎተቱ ወደ አይሮፕላኖቹ መተኮሳቸውን ቀጠሉ። በሚቀጥሉት ሁለት ቀናትም አይሮፕላኖቹ በቦምብ ይደበድባሉ፤ጀግናዎቹ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የቆራሄን ምሽግ ላለማስያዝ ይታገላሉ፤ይሰዋሉ።

በተለይ በሶስተኛው ቀን ጀግናው አፈወርቅ ክፉኛ የቆሰለ እግራቸውን እየጎተቱ በመተኮስ ላይ እያሉ ደከሙ፤ መሳሪያው ላይም ድፍት ብለው እጆቻቸው መሬት ላይ ወደቁ። ይህን በመሰለ ሁኔታ የአገሬ ዳር ድንበር ሲደፈር ቆሜ አላይም በማለት ተሰው። ጦሩም ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ ተደረገ።

በወልወል አካባቢ የነበረው ተጋድሎ በጥቂቱ ይህን የሚመስል ሲሆን በሰሜን በኩል የመረብን ወንዝ ተሻግሮ ጦርነት የገጠመው የጣልያን ፋሽስት ጦር እጅግ ከፍተኛ ውጊያ የገጠመው ማይጨው ላይ ነው። ከማይጨው ጦርነት በፊት፣ በርካታ ውጊያዎች ተደርገው በየአውደ ውጊያው ሠራዊትና አዛዦች ሞተዋል። የጎጃምና የጎንደር ጦር በምዕራብ ትግራይ ተዋግቶ፣ እያሸነፈም፣ እየተሸነፈም በመጨረሻ በአይሮፕላን መርዝ ተጠቅቶ ተበትኗል።

በጦር ሚኒስትሩ የሚመራው ከ50 ሺ በላይ ይሆናል ተብሎ የተገመተው ጦርና ከወለጋ የተንቀሳቀሰው ጦር በአምባ አራዶምና በሌሎች ቦታዎች ተዋግቶ ጊዚያዊ ድል ያገኘ ቢሆንም በአይሮፕላን መርዝና በጣልያን ዘመናዊና ከባድ መሣሪያ ጉዳት ስለደረሰበት አዛዦችም ጭምር በጦር ሜዳ ተሰው። በተምቤን በኩል የዘመተው የሰላሌ፣ የደቡብ ጎንደር፣ የከምባታና የላስታ ጦርም ከታዘዘበት ቦታ ሳይደርስ ጣልያኖች እየቆረጡ አጠቁት። ለሰባት ወራት፣ ኢትዮጵያኖች ሲፋለሙ ቆይተው፣ ከሞት የተረፉት አዛዦችና ወታደሮች ንጉሠ ነገሥቱ በሚመሩት ጦርነት ለመዋጋት ማይጨው ላይ ተሰበሰቡ።

ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር አብሮ የዘመተው ተዋጊም ከፋሽስት ጣልያን ጋር ጦርነት ለማድረግ በማይጨው ተዘጋጀ። መጋቢት 22 ቀን 1928 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሚመራው የኢትዮጵያ ጦር በሶስት ግንባር ተሰለፈ። በጄኔራል ባዶሊዩ የሚመራው የጣልያን ሠራዊትም በዘመናዊ መድፎችና ከ70 በላይ በሚደርሱ የጦር አይሮፕላን እየታገዘ ተሰለፈ። ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት ላይ ጦርነቱ ተጀመረ።

ውጊያው እንደተጀመረ ኢትዮጵያኖች ጣልያኖች ካምፕ ድረስ ዘልቀው በሚያስደንቅ ጀግንነት ተዋጉ። ጀነራል ባዶሊዩ ገና በጠዋቱ፣ የጦር አይሮፕላኖቹ በሙሉ ኃይላቸው በቦምብና በመርዝ ጋዝ ኢትየጵያኖቹን እንዲደበድቡ አዘዘ። ከፍተኛ እልቂትም ሆነ። ጀነራል ባዶሊዮ ራሱ ሲመሰክር ‹‹ የኢጣሊያ አይሮፕላኖች ዘመናዊና ባለሙሉ ትጥቅ ባይሆኑ ኖሮ ኢትዮጵያውያን የአድዋን ድል እንደገና ይደግሙ ነበር። በፓይለቶቻችን ታላቅ ተግባር ጣልያኖች ድል ለማድረግ በቃን›› ብሏል።

በጦር ሜዳው ተሰልፎ ሲዋጋ የነበረ የጣልያን ቁስለኛ መኮንን ሎዊጂ ባርዚኒን በበኩሉ ምስክርነቱን ሲሰጥ ‹‹ ወደ ኢትዮጵያውያኖቹ የመትረየስ ጥይት እንዘራለን። ኢትዮጵያውያኖቹ ግን መትረየሳችንን ዝም ለማሰኘት እየተወረወሩ ከላዩ ላይ ይወድቁበታል። – – – አደገኛ ተዋጊዎች ናቸው። አንድ ጊዜ እንዳየሁት 15 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያኖች መሃል ቦምብ ተጣለና አስሩን ገደላቸው። የተረፉት አምስቱ በመሸሽ ፈንታ የደረሰውን አደጋ ጉዳት ሳይሉት እየሮጡ መጥተው ከጦራችን ጋር ተደባለቁ›› ብሏል።

በማይጨው ጦርነት ከተሰለፉ 70 አውሮፕላኖች መካከል 36 አይሮፕላኖች ተመትተው መውደቃቸውን ጣልያኖቹ አምነዋል። ተመትተው ከወደቁትም መሀል አንዱ የሙሶሎኒ ልጅ ቪቶሪዮ ሙሶሎኒ የሚያበረው ነበር። በጦርነቱ በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ 34 ቶን የሚመዝን ቦምብና የመርዝ ጋዝ ተጥሏል። 61‚200 የመትረየስ ጥይትም ተተኩሷል።

ከማይጨው ጦርነት የተረፈው የኢትዮጵያን ሠራዊት የጣልያን አይሮፕላኖች እየተከታተሉ በቦምብና በመርዝ ጋዝ እየደበደቡት መጋቢት 26 ቀን አሸንጌ ደረሰ። ይህ የደከመና የተንገላታ ሠራዊት አሸንጌ ሲደርስ 73 ቶን የሚመዝን ቦምብና የመርዝ ጋዝ ተጣለበት። መትረየስ ተኳሽ አይሮፕላኖችም አስር ሜትር ድረስ ዝቅ እያሉ በመትረየስ ፈጁት። አንዳንድ በየጥጋጥጉ እየተደበቀ የቀረ ሠራዊት እንዳለ በማለትም የመርዝ ጋዙ በየጫካው ተረጨበት፤ ሠራዊቱ እንደ ቅጠል ረገፈ። ኢትዮጵያኖችም ከሰማይ ከሚተኩስባቸው ጠላት ጋር በሚያስደንቅ ጀግንነት ተዋጉ።

በሰውነታቸው ላይ የተረጨባቸውን የመርዝ ጋዝ እንዲያቀዘቅዝላቸው ለመታጠብ እና የውሃ ጥማቸውን ለማስታገስ አሸንጌ ሀይቅ ሲገቡ በመርዝ ጋዝ ተበክሎ ስለጠበቃቸው ብዙዎቹ ስቃያቸው በርትቶ ሞቱ። ያን የደከመ ሠራዊት ለመጨረስ 150 አይሮፕላኖች እየተመላለሱ እንዲደበድቡት ታዘው ነበር። ከእነዚህ መሃል ኢትዮጵያውያኖቹ 28 አይሮፕላኖች መጣላቸውን ጣልያኖቹ አምነዋል።

ከማይጨው ሽንፈት በኋላ ንጉሡና ጥቂት የቅርብ ረዳቶቻቸው በስደት አገር ጥለው ወጡ። ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም. የማርሻል ባዲሊዮ ጦር አዲስ አበባ ገባ። ግንቦት 1 ቀን 1928 ዓ.ም. ሙሶሎኒ ‹‹ – – የኢጣሊያ መንግሥት ኢትዮጵያን ድል አድርጎ ይዟል። ከዛሬ ጀምሮ ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ቄሳር ግዛት መሆንዋን ለዓለም እንሳውቃለን›› በማለት አወጀ።

የኢትዮጵያ አርበኞች ግን አዲስ አበባ ከተማ ብትያዝም ሽንፈትን አንቀበልም እንዲሁም ለጠላት አስተዳደር አንገዛም በማለት በተለያዩ ቦታዎች በቡድን ተደራጅተው ጥቃት ይፈጽሙ ጀመር። የጣልያን አየር ኃይል አዛዥ ማርሻል ማሊዮኮ በሶስት አይሮፕላን ከተከታዮቹ ጋር ሆኖ ወደ ወለጋ ተጓዘ። ሰኔ 20 ቀን 1928 ዓ.ም. ለቀምት ከተማ አይሮፕላኖቹ እንዳረፉ ከጦርነቱ

 በፊት በሆለታ ጦር ትምህርት ቤት ሲማሩ በነበሩ ወጣቶች ተኩስ ተከፍቶ በተደረገ ውጊያ ማርሻል ሚሊዮኮ እና 11 የጣልያን መኮንኖች ተገደሉ። ይህም በጣልያን አገር እንደተሰማ “ኢትዮጵያን ድል አድርገን ይዘናል” የሚለው ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ሆኗል።

ተባባሪ ፕሮፌሰር ጋሻው መሐመድ ሞቱማ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ናቸው። በተለይ በማይጨውና በአሸንጌ ሐይቅ የተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት ሲገልጹ በአይሮፕላን የሚጣለው መርዝ ኢትዮጵያዊ ተዋጊዎችን ሕይወታቸውን ማጥፋት ብቻ ሳይሆን አካላቸውን ፍርስርስ ያደርግ ነበር። ተዋጊዎቹ በመርዝ ጋዝና ጭሱ የሚሆኑት ግራ ሲገባቸው አሸንጌ ሐይቅ ውስጥ ገብተው ያለቁ ብዙ ናቸው በማለት በከፍተኛ ሐዘን ያስረዳሉ።

ሀሳባቸውን በመቀጠልም የጣልያን ግፋዊ ወረራ ለመመከት ኢትዮጵያውያን በአራቱም አቅጣጫ ፆታ፣ ዕድሜ፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋና ብሔር ሳይወስናቸው እና ልዩነት ሳይኖር አቅማቸው በፈቀደ መልኩ በተለያዩ አካባቢዎች ራሳቸውን አደራጅተው ከፍተኛ ፍልሚያ አድርገዋል። አንዳንዶቹ አርበኞች የከፈሉት ተጋድሎ፣ አስተዋጽኦና ፍልሚያ እንዳልተዘከረ እንዲሁም እንደተረሳ ይገልጻሉ።

ከእነዚህ መካከል ወሎ ውስጥ ቦረና አውራጃ ከበላይ ዘለቀ ጋር ግንኙነት የነበረው የውስጥ አርበኛ ፈለቀ እንድሮ የሚባል አንጥረኛን ይጠቅሳሉ። መሳሪያ መፍታት፣ መግጠም እንዲሁም የማደስ ከፍተኛ ችሎታ ነበረው። ከጣልያኖች ጋር ቅርበት መስርቶ ወዳጅነት ፈጥሯል። ቀን ቀን ለጣልያኖች የጦር መሳሪያ መግጠምና ማደስ ሥራ ይሠራል። ማታ ማታ ከአርበኞች ጋር ግንኙነት ያደርጋል። በመጨረሻ በተጨባጭ ሁኔታ አጣርተው በመያዝ እመን ሲሉት ክዶ ይከራከራል። ቤቱ ሲፈተሽ ደብቆ ያስቀመጠው የጦር መሳሪያና ማደሻ ይገኛል። ከእነማን ጋር ግንኙነት እንዳለው መረጃ እንዲሰጥ ከፍተኛ ምርመራ ቢደረግበትም አዎንታዊ ምላሽ ሊሰጥ አልቻለም። ምስጢር እንዲያወጣ እሳት ነዶ በወናፍ እየተነፋ ሁለት እግሩ እንዲማገድና እንዲቃጠል ተደርጎ ይቆረጣል። እሱ ግን እጅግ ከፍተኛ የሆነ አሰቃቂ ጉዳት ቢደርስበትም ምስጢር አላወጣም። በመጨረሻም ለመቀጣጫ ሕዝቡ እንዲያየው በአደባባይ ተሰቅሏል።

ተባባሪ ፕሮፌሰር ጋሻው የአርበኝነቱ ተጋድሎ ዜጎች አገር ወዳድ እንዲሆኑ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ሲያስረዱ፤ ‹‹ሰው መቼም በኑሮው ከሁለም በላይ ልጁን አብልጦ ይወዳል። አርበኛው ደጃዝማች በላይ ዘለቀ በወራሪው ጦር ልጁ ተይዛበት ነበር። ልጁን ለማስለቀቅ በነበረው ድርድር ከልጄ አገሬ ትበልጥብኛለች ብሎ ምላሽ ሰጥቷል። ፋሽስት ጣልያን የተለያዩ የመደለያ ጥቅማ ጥቅሞች በማቅረብ ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ ቢያቀርብም ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ግን እስከመጨረሻው ከአቋሙ ፈቀቅ ሳይል በተደጋጋሚ አገሩ እንደምትበልጥበት አሳይቷል። ከዚህ ተግባር ስለአገር ወዳድነት ከፍተኛ ትምህርት መውሰድ ይቻላል›› ይላሉ።

ጣልያኖች የአርበኝነት ትግሉ ሲበረታባቸው የአርበኞች መከማቻ ሆኗል ያሉትን አንኮበር አካባቢን በአይሮፕላን በመታገዝ ከደበደቡ በኋላ ከፍተኛ የእግረኛ ጦር በማምጣት ከተማዋን ግንቦት 21 ቀን 1928 ዓ.ም. ይዘዋል። አርበኞቹ ደግሞ ሐምሌ 14 እና 15 ቀን 1928 ዓ.ም. በተደረገ ውጊያ መልሰው ከተማዋን ተቆጣጥረዋል። ቀደም ሲልም ሐምሌ 2 ቀን ናዝሬት የሠፈረውን የጣልያን ጦር አርበኞች አጥቅተው አንጋፋው የጦር መሪ ጀነራል ሜርካቲን ጨምሮ ብዙ ጣልያኖች ገድለዋል።

አርበኞቹ በተለያዩ ቦታዎች ከሚያደርጉት ውጊያዎች በተጨማሪ በጋራ ሆነው ቅንጅት ፈጥረውም ውጊያ በማድረግ የጣልያን ጦርን ያሸብሩ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ አዲስ አበባ ከተማን ወረው የጣልያንን ጦር ከከተማው ለማስወጣት በማሰብ አምስት ቀናት የፈጀ ስብሰባ አድርገው እንዴት እንደሚያጠቁ የጦርነት ድልድል ያደረጉበት ተጠቃሽ ነው። ድልድሉ ከተከናወነ በኋላ ደጃዝማች አበራ ካሳ ሐምሌ 21 ቀን 1928 ዓ.ም. በቅድሚያ ወደ አዲስ አበባ በመግባት ተኩስ ከፈቱ። በድልድላቸው መሠረት በህብረት ሆነው በተለያዩ አቅጣጫዎች ተኩስ ከፍተው ለመግፋት ያደረጉት ጥረት ስላልተሳካ ሁሉም ወደ መጡበት ለመመለስ ተገደዱ። የደጃዝማች አበራ ሠራዊትም ሐምሌ 22 ቀን ወደ መጣበት ወደ ሰላሌ ሄደ። ሌሎችም የቻሉትን ያህል ከተዋጉ በኋላ ወደ ኋላቸው አፈገፈጉ። ይህ ተግባር ሙሶሎኒን ጭምር እጅግ በጣም ያበሳጨና ያስጨነቀ ነበር።

አብዛኛውን ጊዜ የወንዶቹ አርበኞች ስምና ተግባር ስለሚጠቀስ እንጂ ሴቶች አርበኞችም ከወንዶቹ ባልተናነሰ አንዳንዴም በበለጠ ሁኔታ ተጋድሎ አድርገዋል። በዶሎ ጦርነት የታየውን የአንዲት ኢትዮጵያዊት የማይታለፍ የጀግንነት ታሪክን ማንሳት ተገቢ ነው።

ስም አይጠቅስም እንጂ ዊሊያም ማኪን የሚባል ፀሐፊ የእኚህን ኢትዮጵያዊት ታሪክ እንደሚከተለው ዘግቦታል ‹‹…በዶሎ አካባቢ አበሾች በየተራራው ላይ መሽገው የኢጣሊያን መምጣት ይጠባበቃሉ። የዚያ ቦታ ጦር መሪ የሆነችው የደጃዝማች ሀብተ ሚካኤል ሚስት ከተራራ ላይ ሆና ስትመለከት የኢጣሊያ ወታደሮች ሲመጡ አየች። የኢጣሊያ ጦር በመምጣት ላይ ነውና ይመታ ብላ ለባልዋ ነገረች። ጥሩ የመከላከያ ቦታ ስለሌለ ከኢጣሊያ ወጥመድ እንዳይገቡ በመስጋት ሄደው መዋጋትን ባላቸው አልደፈሩም። ሚስቲቱ ከባልዋ ተለይታ ፈቃደኛ የሆኑ 150 ሰዎች አዘጋጅታ ከጨረሰች በኋላ ከበቅሎዋ ላይ ወጥታ የጦርነት ጩኸት እየስጮኸች ወደ ኢጣሊያ ጦር ወደ ፊት ገሰገሰች። የአበሻው ጦር አዛዥ የሚስታቸውን ከጠላት ጋር መዋጋት እንደሰሙ ጦራቸውን ይዘው ለእርዳታ ሄዱ። ደጃዝማች ከውጊያው ቦታ ሲደርሱ ውጊያው አልቆ ረዳት ከማያስፈልግበት ደረጃ ላይ ነበር። ብዙ ኢጣሊያኖች ተገድለዋል፤ ብዙዎች ቆስለዋል። ያቺ አገርዋን የምትወድ ተዋጊ ሴት ከጠላትዋ ብዙ ጠመንጃና ጥይት ማርካ ተመለሰች።›› (“የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት”)

አርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ፣ ዘውዲቱ ግዛው፣ ብዙነሽ ከበደ፣ አበበች ጨርቆሴ እና ሌሎችም ሴት አርበኞች ከወንዶች ባልተናነሰ ለእናት አገራቸው ዳር ድንበርና ለባንዲራቸው ክብር በጦር ሜዳ ተፋልመዋል። ከእነዚህ አርበኞች ውስጥ ባንዲራዬንማ ጥዬ አላፈገፍግም ብለው የቆሰሉትንና በጠላት እጅ የወደቁትን የአርበኛ ልክየለሽ በያን ተጋድሎ የታሪክ ምሁሩ አቶ ተፈራ ወርቁ እንደሚከተለው ይተርኩታል።

አርበኛ ልክየለሽ በያን የአያታቸውን የአቶ ሽብሩ ጤናውን ጠመንጃ ይዘው በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል ተዋግተዋል። አርበኛዋ በወቅቱ የአራት ወር ከአስራ አምስት ቀን አራስ ህፃን ልጃቸውን ለቤተሰብ በመተው የአገራቸውን ነፃነት አስቀድመው የዘመቱ አገር ወዳድ ናቸው። በጦርነቱ ጣልያን የበላይነት ሲያገኝ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ተመልሰው የውስጥ አርበኛ በመሆን አርበኞችን ሲያግዙ ቆዩ። ቀንደኛ የፋሽስት ባንዳ የነበሩትን ቀኝ አዝማች ኩንቢን በ1930 ዓ.ም. በመግደል ናስማሰር ጠመንጃቸውን በመማረክ ጫካ ገቡ። ጫካ ከገቡ በኋላ በድንገት ተኩስ በመክፈት በርካታ የፋሽስት ወታደሮችን ከገደሉና ካቆሰሉ በኋላ በጊዜው አጠራር የውሃ መትረየስ የሚባለውን ማርከዋል። መትረየሱንም በወቅቱ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደርግ ለነበረው ለራስ አበበ አረጋይ አስረክበዋል።

አርበኛዋ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን ሲዋጉ ባለቤታቸው ከጣልያኖች በተተኮሰ ጥይት ተመተው ወደቁ። ጣሊያኖች የባለቤታቸውን አንገት ቆርጠው ለመውሰድ ከፍተኛ ትግል ቢያካሂዱም ጥይት እስኪያልቅባቸው ድረስ ከተዋጉ በኋላ የባለቤታቸውን ሽጉጥ ከሬሳው ወገብ ላይ ፈትተው አራት የጣልያን ወታደሮችን ገድለዋል። የባለቤታቸውን አንገትም ከጠላት ከማስቆረጥ ታድገው በስርዓት እንዲቀበሩ አድርገዋል።

አርበኛ ልክየለሽ በሌላ የጦር ሜዳ ውጊያ ዘወትር የሚይዙት የኢትዮጵያ ባንዲራ ድንገት ሳያዩት በመውደቁ ጥለውት ይሄዳሉ። ትዝ ሲላቸው ‹‹ከሞትሁም ልሙት እንጂ ሰንደቅ ዓላማዬን በፍጹም ለጣልያን አላስረክብም!›› ብለው ወደ ዋሉበት ተመልሰው ዳግም ውጊያ ውስጥ በመግባታቸው ቆሰሉ። አርበኛዋ ቆስለው ከተኙበት ቦታ በጠላት ወታደሮች ተማርከው ከፍተኛ እንግልትና ስቃይ ደርሶባቸዋል።

አርበኞች በኢትዮጵያ በአራቱም አቅጣጫ በተለያዩ ቦታዎች ለአምስት ዓመታት የአርበኝነት ተጋድሎ ካካሄዱ በኋላ መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም. እንግሊዛዊው ሜጀር ጄኔራል ካኒንግሃምና ጦሩ አዲስ አበባን ተቆጣጠረ። ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ደግሞ በራስ አበበ አረጋይ የሚመሩ አስር ሺህ አርበኞች ንጉሠ ነገሥቱን አጅበዋቸው እንዲሁም በሻለቃ ዊንጌት የሚመራው በሱዳን በኩል ከንጉሡ ጋር የመጣው የእንግሊዙ የጌዲዮን ጦርም ተሰልፎ አዲስ አበባ ገባ። መድፍ ተደጋግሞ እየተተኮሰ፣ የኢትዮጵያ የብሔራዊ ሉዓላዊነትና ነፃነት ዓርማ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ አፄ ኃይለ ሥላሴ በክብር ከፍ አድርገው ሰቀሉት። (ዘውዴ ረታ፣ “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት” 2005 ዓ.ም፣ ገጽ 409- 10)

ሚያዝያ 27 የምናከብረው የድል ቀን በኢትዮጵያውያን አርበኞች አኩሪ ተጋድሎ ጣሊያን ለሁለተኛ ጊዜ አንገቷን የደፋችበት የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ዳግም ድል ነው። ኢትዮጵያውያን እጅግ ከፍተኛ የሆነ የቀለብ፣ የመሳሪያ፣ የህክምና መገልገያ እና ሌሎችም እጥረቶች ቢኖሩባቸውም በጽናት በአንድነት በመቆም በዱር በገደሉ ባደረጉት ከፍተኛ ተጋድሎ ዳግም ድልን ተጎናጽፈዋል። የአምስት ዓመቱ የአርበኝነት ተጋድሎና ድል አሁን ላለውም ሆነ ለመጪው ትውልድ ኢትዮጵያዊነት አይበገሬነት መሆኑን የሚያስተምር ቋሚ ሀውልት ነው።

ስሜነህ ደስታ

ዘመን መጽሄት ግንቦት 2014 ዓ.ም

Recommended For You