ተስፋ ፈሩ
ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ የፖለቲካ ለውጥ እና የሥርዓተ መንግሥት ማሻሻያ እንድታደርግ ዕድል የሰጡ ሦስት ዐበይት ሕዝባዊ አመጾችን አስተናግዳለች። በ1966 እና 1983 ዓ.ም. የገጠሟት ሁለቱ ዕድሎች በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት ቀጥፈው፤ አካል አጉድለው እና ንብረት አውድመው ሳትጠቀምባቸው አምልጠዋታል። ከተቆራረጠ እና ዘለግ ካለ የትግል ምዕራፍ በኋላ ከአራት ዓመታት በፊት እውን የሆነው ሦስተኛው ዕድል እየወደቀ እና እየተነሳ በሂደት ላይ ይገኛል።
አንዳንዶች ኢትዮጵያ ያለችበትን አሁናዊ ሁኔታ በተሳካ ሀገራዊ ውይይት ሥርዓተ መንግሥቷን የምታጸናበት አልያም የምትበተንበት ይሆናል ሲሉ በሁለት አማራጮች መካከል ያስቀምጡታል። ኢትዮጵያውያን ሀገራዊ ምክክሩን በጥንቃቄ እና በብስለት መምራት ከቻልን እንደ አድዋ ድል ሁሉ በልጅ ልጆቻችን የምንዘከርበት፣ ራሳችንን ታግለን ያሸነፍንበት አንጸባራቂ ድል ሆኖ በደማቅ የወርቅ ቀለም የሚጻፍ የዚህ ትውልድ አኩሪ ታሪክ እንደሚሆን ብዙዎች ይስማሙበታል።
ይህ ጽሑፍ ትኩረቱን የዛሬ ኢትዮጵያውያን የምንደምቅበትን አሊያም የምንደበዝዝበትን እጣችንን ይወስናል በተባለለት ሀገራዊ ምክክር ላይ ያደርጋል። ለዘመናት ከተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች አንደበት ተደጋግሞ የሚደመጠው “ሀገራዊ ምክክር” የተሰኘ ሐረግ የተሸከመው ጽንሰ ሀሳብ፣ ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎቹ እና ኢትዮጵያ በሀዲዱ ላይ የምታደርገው ጉዞ ተዳሰውበታል።
ሀገራዊ (ብሔራዊ) ምክክር ምንድነው ?
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባሉ አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን የሀገራዊ ምክክርን ምንነት ሲያስረዱ በሥርዓተ መንግሥቱና በሀገራዊ ተቋማት መካከል የሚኖረውን ግንኙነት እንደገና መገንቢያ መንገድ፤ በሥርዓተ መንግሥቱና በግጭት የተለያዩ ማኅበረሰቦችን እንደገና ማሰባሰቢያ አጀንዳ፤ አዲስ ማህበራዊ ውል ማሠሪያ ገመድ፤ ሀገራት ውስጣዊ መሰንጠቅና የመበተን አደጋ ሲጋረጥባቸው የሚሻገሩበት ድልድይ፤ አለመረጋጋትና የግጭት አዙሪት ለሚንጣቸው ሀገራት ከውድቀት መውጫ ምርኩዝ እንዲሁም ሥርዓተ መንግሥት መገንባት ላልቻሉ ሀገራት ሕዝባቸውን በጋራ የታሪክ መሠረት፣ በዛሬ እኩልነትና በነገ ተስፋ ማሰባሰቢያ ነጋሪታቸው ነው ሲሉ ይገልጹታል።
ሀገራዊ ምክክር በዓለማችንም ሆነ በአህጉራችን አፍሪካ የቅርብ ክስተት ሳይሆን ዘመናትን የተሻገረ የግጭት ማርገቢያ እና ልዩነቶችን መፍቻ ዘዴ በመሆን ሲያገለግል ኖሯል የሚሉት አርክቴክት ዮሐንስ፣ በዓለማችን የተለያዩ ክፍላተ አህጉራት የፖለቲካ ሽግግሮችን ለማሳካት በተደረጉ ጥረቶች የምክክር ባህሉ እየተለመደ መምጣቱን ይገልጻሉ።
ታሪካዊ ዳራውን በዝርዝር ሲዳስሱም የሶሻሊዝምን ውድቀት ተከትሎ በመካከለኛው እና በምሥራቅ አውሮፓ የተከሰተውን የፖለቲካ ምስቅልቅል ለማስከን በፖላንድ፣ በሀንጋሪ፣ በቼኮዝላቫኪያ፣ በምሥራቅ ጀርመን እና በቡልጋሪያ ሀገራዊ ምክክሮች ተካሂደዋል። በ1990ዎቹ የፈረንሳይ ቅኝ ተገዢ በነበሩ የአፍሪካ ሀገሮች የፈረንሳይ አብዮትን ሁለት መቶኛ ዓመት መታሰቢያን ተከትሎ አፍሪካውያን እያደገ የመጣውን የሕዝቦች ግንዛቤ፣ በመሪዎቻቸው መካከል እየሠፋ የመጣውን ቅሬታ ለመፍታት ብሔራዊ ጉባዔያት ተደርገዋል። በ1990ዎቹ ቦሊቪያን እና ኮሎምቢያን በመሰሉ የላቲን አሜሪካ ሀገራት ሕዝብን አሳታፊ ሥርዓተ መንግሥትን እና ልማትን ለማምጣት መግባባት ላይ የተመሰረቱ(consensus based) ሕገመንግሥት የመገንባት ሂደቶች ተከናውነዋል። የአረብ የጸደይ አብዮቶችን ተከትሎም በሞሮኮ፣ ሊቢያ፣ ቱኒዚያ፣ ግብጽ፣ ሱዳን፣ ሊባኖስ፣ ዮርዳኖስ፣ ባህሬን እና የመን የተለያዩ ሀገራዊ ምክክሮች ተደርገዋል ይላሉ።
በሀገራችን ኢትዮጵያ በዓፄ ዘርዓያዕቆብ(ከ1434 እስከ 1468 እ.ኤ.አ) እና በዓፄ ፋሲል(ከ1632 እስከ 1667 እ.ኤ.አ) ዘመነ መንግሥታት ሀይማታዊ ልዩነቶችን ለመፍታት የተደረጉ ጉባኤዎች የብሔራዊ መግባባት ይዘት እንደነበራቸው የሚጠቅሱ ምሁራን መኖራቸውንም ይጠቅሳሉ።
በብሔራዊ ምክክር ዙሪያ የሚሠራው የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ምክትል አስተባባሪ አቶ መስፍን ጌታቸው በበኩላቸው በዘርፉ የተሰማሩ ምሁራን ለብሔራዊ ምክክር በተለያዩ አገላለፆች ትርጉም ለመስጠት መሞከራቸውን ያወሳሉ። ከእነዚህም መካከል በፖለቲካ ሽግግር ሂደቶች ወቅት አሳታፊነትን ከገዢ ሊሂቃን በተጨማሪ ወደ ልዩ ልዩ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና ማህበራዊ ቡድኖች ለማስፋት የተቀረፀ የድርድር ሂደት አድርገው የሚያቀርቡት አሉ። ሌሎች ትርጓሜዎች ደግሞ ልሂቃን ተኮር ከሆኑ እና የተጋጩትን አካላት ብቻ ከሚያሳትፉ ድርድሮች እና በሶስተኛ አካል አደራዳሪነት ከሚደረጉ የሽምግልና ሂደቶች በተለየ ብሔራዊ ምክክር በአንድ ሀገር ውስጥ ባሉ ባለድርሻ አካላት ሰፊ ተሳታፊነት እና ባለቤትነት የሚካሄድ የግጭት መፍቻ ሂደት እንደሆነ ይገልጻሉ። አንዳንዶች ደግሞ ሁለቱን አጣምረው ሁሉ አቀፍ፣ ሰፊ እና አሳታፊ የሆነ ሀገራትን ከቀውስ ወደ ፖለቲካ ሽግግር የሚወስድ የድርድር ማዕቀፍ አድርገው ያቀርቡታል።
ጠቅለል ባለ አገላለጽ ብሔራዊ ምክክር በአንድ ሀገር ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት በፖለቲካ ቀውሶች ጊዜ ቀውሶቹ ወደ ለየለት ብጥብጥ እና የእርስ በእርስ ጦርነት እንዳያመሩ፤ በጥልቅ የፖለቲካ ሽግግር ጊዜ አዲስ ማህበራዊ ውል ወይንም ሕገ መንግሥት ቀረፃ ለማካሄድ፤ እንዲሁም ከርስ በእርስ ጦርነቶች በኋላ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በሀገሬው ባለቤትነት የሚካሄድ የግጭት መፍቻ ሂደት ነው ብሎ መግለጽ ይቻላል ይላሉ።
አቶ መስፍን እንደሚናገሩት አብዛኞቹ ብሔራዊ ምክክሮች የሚያልፉባቸው አራት ደረጃዎች አሉ። እነዚህም የጥንሰሳ፣ የዝግጅት፣ የምክክር እና የትግበራ ደረጃዎች ናቸው። የጥንሰሳ ደረጃ ዋነኛ ዓላማ ለብሔራዊ ምክክሩ ፖለቲካዊ ቅቡልነት ማስገኘት ነው። የዝግጅት ደረጃ የምክክሩ አጀንዳዎች ተሳታፊዎች፣ ሰብሳቢዎች፣ የአቅርቦት እና የድጋፍ ሥራ ተቋማት ዝግጅቶች የሚደረግበት ነው። ለዝግጅት በቂ ጊዜ መውሰድ እና ምክክሩን እስከ ትግበራው ድረስ ማቀድ ለምክክሩ ስኬታማነት መሰረት እንደሆነ ጥናቶች ማመላከታቸውንም ይጠቅሳሉ።
የምክክር ደረጃ ደግሞ የምክክሩ ተሳታፊዎች የሚሰበሰቡበትና ሰብሳቢዎች የሚሰየሙበት ነው። እጩ አጀንዳዎች ቀርበው የውይይቱ ዋነኛ አጀንዳዎች የሚለዩበት እና ቅደም ተከተል የሚይዙበት (በዝግጅት ጊዜ ተመርጠው ከሆነም የተለዩት የሚቀርቡበት) ጊዜ ነው። በዚህ ደረጃ የምክክሩ አሠራር ቅርፅ፣ ውሳኔ አሰጣጥ መንገዶች እና መመሪያዎች ውሳኔ ያገኛሉ፤ አስቀድመው ከተወሰኑም ይገለጻሉ። በዚህ ጊዜ ግልፅ፣ የተወሰኑ እና እንደ ሀገር የግጭቶች ቁልፍ መንስኤ የሆኑትን አጀንዳዎች ለይቶ በቅደም ተከተል መመካከር ለስኬታማነቱ መሰረት ነው።
አራተኛውና የመጨረሻው የትግበራ ደረጃ ነው። ምክክሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ተጨባጭ ውጤቶቹን በተግባር ላይ ለማዋል አዲስ ወይም የነበሩ አስፈፃሚ ተቋማት የሚለዩበት እና ውጤቱን በተግባር የማዋል ሥራ የሚጀመርበት ደረጃ ነው። የውጤቶቹን አተገባበር ለመገምገም የተዘረጋው ሥርአት የሚተገበርበት ቀጣይ የምክክር መድረኮች ካስፈለጉ የሚካሄድበት ጊዜ ነው።
ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች
አቶ መስፍን ብሔራዊ ምክክር የሚባለው አሠራር ወይም ሂደት አዲስ ክስተት አለመሆኑን ይገልጻሉ። በዘመናዊው ዓለም ብሔራዊ ምክክር ብለን ከምንጠራቸው ሂደቶች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ አሠራሮች ከ200 ዓመታት በፊት ጀምሮ ይከወኑ ነበር። እ.ኤ.አ 1787 በአሜሪካ የተካሄደው የሕገ መንግሥት ጉባኤ እንዲሁም እ.ኤ.አ 1789 በፈረንሳይ የተካሄው እና ለፈረንሳይ አብዮት መነሳት አንዱ ምክንያት የሆነው ቀሳውስቱን፣ መኳንንቱን እና ተራውን የፈረንሳይ ሕዝብ ያቀፈው “ኢስቴትስ ጀነራል” የተሰኘው ጉባኤ ለሀገራዊ ምክክር አሠራር ቀዳሚ ምሳሌዎች
የሚሉት አቶ መስፍን፣ በቀጥተኛ ተሳታፊዎቻቸው ብዛት እ.ኤ.አ በ2008 በኬኒያ ከተካሂደው ስምንት ቀጥተኛ ተሳታፊዎች ከነበሩት ብሔራዊ ምክክር አንስቶ እ.ኤ.አ(2002-2004) እስከተካሄደው 3000 ቀጥተኛ ተሳታፊዎች ከነበሩት የሶማሊያ ብሔራዊ ምክክር ድረስ ልዩ ልዩ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
አያይዘውም በአጀንዳቸው ይዘትም ግልፅ እና ውስን አጀንዳዎችን ይዘው ካሳኩት ከኬንያ እና ቱኒዚያ ምክክሮች አንስቶ ሁሉንም የሀገሪቱን አጀንዳዎች ለመፍታት እስከ ሞከሩት የሱዳን እና የየመን ምክክሮች ድረስ የተለያዩ እንደነበሩ ያስረዳሉ። በወሰዱትም ጊዜ ከአንድ ሳምንት በታች ወስዶ ያለ ስምምነት ከተጠናቀቀው የግብፁ ምክክር እና ዓመታትን እስከወሰዱት የሶማሊያ ፣ ኔፓል እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምክክሮች ድረስ በአይነታቸው እንደሚለያዩ ይጠቅሳሉ።
እንደ አቶ መስፍን ገለጻ የመን እና ቱኒዚያ የተከተሉት ሂደት እና ያገኙት ውጤት ብሔራዊ ምክክር ለማካሄድ ለሚነሱ ሌሎች አገራት ትልቅ ትምህርት ሰጪ ነው። በየመን የገልፍ ሀገራት ካውንስል ኢኒሺዪቲቭ የጠነሰሰው ብሔራዊ ምክክር ያተኮረባቸው አጀንዳዎች ከመብዛታቸው የተነሳ በምክክሩ መጨረሻ ከ5000 በላይ ምክረ ሀሳቦች አቅርቦ ነበር። እነዚህን ምክረ-ሀሳቦች ለመተግበርም እስከ 30 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚጠይቅ ተገምቶ ነበር:: በመጨረሻም ምክክሩ ላለመሳካቱ የአጀንዳዎቹ መብዛት ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ ይጠቀሳል።
በሀገሪቱ ከሚገኙ 24 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ 21ዱን ያሳተፈው እና ከእያንዳንዱ ሁለት ተሳታፊ በማቅረብ በድምሩ 42 ቀጥተኛ ተሳታፊዎች የነበሩት የቱኒዚያ ብሔራዊ ምክክር ደግሞ በስኬታማነቱ ተጠቃሽ ነው። ካልተሳኩ ሁለት ሙከራዎች በኋላ በሦስተኛው በፈጠሩት የሲቨል ማኅበራት አራትዮሽ ጥምረት ያቀዷቸውን አዲስ የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋም፣ የምርጫ ሕግ ማውጣት፣ የሕገ መንግሥቱን ቀረፃ ማጠናቀቅ እና አዲስ ካቢኔ ማቋቋም የሚሉ ውስን አጀንዳዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በማሳካታቸው ጎረቤቶቻቸው በአረብ አብዮት ተንጠው እስከ መፍረስ ሲደርሱ ቱኒዛውያን ሀገራቸውን ከፖለቲካ ቀውስ ማሻገር ችለዋል። ይህም በምክክር ደረጃ ግልጽና የተወሰኑ አጀንዳዎች ላይ የማተኮርን አዋጭነት በተጨባጭ የሚያስረዳ ተሞክሮ ነው።
አርክቴክት ዮሐንስም ቀደም ብለው በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ካለፉ ሀገሮች ስኬት እና ውድቀት መማር እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በርካታ የሦስተኛው ዓለም ሀገሮች ያልተቋጩ የሥርዓተ መንግሥት ግንባታዎቻቸውን በሀገራዊ ውይይት ለመሙላት የሞከሩ ሲሆን የአንዳንዶቹ ጥረት በስኬት የተቀሩት ደግሞ በዳግም ውድቀት ደምድመዋል። በየመን፣ ቱኒዚያ፣ ካሜሮን፣ ዚምቧቡዌ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ኬንያ ሀገራዊ ውይይት(National Dialogue) ዙሪያ የተጻፉ የምርምር ወረቀቶችን
መዳሰስ ጠቃሚ ልምዶችን እንድንወስድ ይረዳናል በማለት በርዕሰ ጉዳዩ ዙሪያ ከተዘጋጁ የምርምር ወረቀቶች አንዱ የሆነውን ዳዊት ዮሐንስ (PhD) እና መረሳ ካኽሱ በጋራ “National dialogues in the Horn of Africa፡ Lessons for Ethiopia’s political transition” በሚል ርዕስ ያቀረቡትን የጥናት ወረቀት ይጠቅሳሉ። ጥናቱ በሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ኬንያ የተደረጉት የሀገራዊ ምክክር ፕሮጀክቶች በማሳያነት የቀረቡበት ሲሆን የሁለቱ ሱዳኖች በውድቀት የኬኒያው ደግሞ በስኬት መጠናቀቃቸውን ያወሳል።
የጥናት ወረቀቱ እንደሚያስረዳው ሱዳን ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ የተገደደችው የገጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ በመባባሱ፣ በመንግሥት ውስጥ በሚገኙ ኃይሎች መካከል የሥልጣን ሽኩቻ በመጧጧፉ እና ነፍጥ ያነሱ ኃይሎች ውጊያ በመግጠማቸው ምክንያት ነው። ምክክሩን የጋበዙት የወቅቱ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ኦማር አልበሽር ሲሆኑ አናሳዎቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጥሪውን ተቀብለው በሂደቱ መሳተፍ ጀምረው ነበር። ይሁን እንጂ ውጊያ ላይ የነበሩ ቡድኖችና ዋንኛው ተፎካካሪ ፓርቲ በምክክሩ ሕጋዊነት እና አካታችነት ላይ ጥያቄ በማንሳት ከሀገራዊ ምክክር ተሳትፎ ራሳቸውን በማግለላቸው ሀገራዊ ውይይቱ ውድቀት ገጥሞታል። አልበሽር የመሩት ውይይት 1000 ያህል ውሳኔዎችን ቢያሳልፍም አብዛኞቹ ለትግበራ ሳይበቁ ቀርተዋል።
የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪርም የትጥቅ ትግል እንዲያከትም፣ ሀገራዊ መግባባት እንዲሰፍን፣ የውጪ ጣልቃ ገብነትን ለመከላከል እና ሀገሪቱን ከመበተን ለመታደግ በሚል የሀገራዊ ምክክር ጥሪ አቅርበው ነበር። ውይይቱ ሦስት ደረጃዎች የነበሩት ሲሆን የታችኛውን ኅብረተሰብ እንዲሁም ክልላዊ እና ብሔራዊ ምክክሮችን አካትቷል። የደቡብ ሱዳን ሀገራዊ ምክክር ዋነኛው ውድቀት የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት፣ የአጀንዳዎች ብዛት (996 አጀንዳዎች ነበሯቸው)፣ የአወያዮቹ እምነት ማጣት እና የውይይቱ አካታች አለመሆን ናቸው። ደቡብ ሱዳን በውይይቱ አሳካቸዋለሁ ያለቻቸውን አሥር ዋነኛ መዳረሻዎችን አስቀድማ ያስቀመጠች ቢሆንም ተቺዎች ግን በሂደት ሊደርስባቸው የሚችሉ ዝርዝር ጉዳዮችን ቅደም ተከተል ከማስያዝ ይልቅ በአንድ ጊዜ ሁሉንም አጀንዳ አግተልትላ መዘርገፏን እንደ ችግር ይቆጥሩታል።
በኬንያ የተካሄደው ሀገራዊ ምክክር በሀገሪቱ ምርጫን ተከትሎ የተነሳውን ግጭት መፍታት፣ ዘላቂ ሀገራዊ ሠላምን መገንባት፣ ሀገራዊ መረጋጋትን ማምጣት እና ፍትሕን ማስፈን ዓላማው አድርጎ የተነሳ ነበር። ምክክሩ አስቀድሞም ከግጭት መውጪያ መንገድን ያለመ እና ግልጽ የአካሄድ መርኅ የነበረው ነው። ከሁለቱ ሱዳኖች ይልቅ የኬንያው ሀገራዊ ምክክር የተሰፈሩ እና የተቆጠሩ ግቦቹን እና የስልጣን ወሰኖቹን ከማስቀመጡም በላይ አወያዮቹ(ኮሚሽነሮቹ) በአጭር እና በረጅም ጊዜ ተለይተው የሚፈቱ አጀንዳዎቻቸውን ለይተው ማስቀመጣቸው ለስኬት እንዳበቃቸው ይነገርላቸዋል። ይሁን እንጂ ኬንያውያኑ በተለይ የረጅም ጊዜ አጀንዳዎቻቸውን የማስፈጸሚያ ስልት እና የጊዜ ገደብ አለማስቀመጣቸው ውሎ አድሮ አንዳንድ ውሳኔዎቻቸው ሳይፈጸሙ ዝርው ሆነው እንዲቀሩ አድርጓቸዋል። በአወያይነትም በከፊል የውጪ ሀገር ሰዎችን ጭምር ማካተቱ(ጋናዊው ኮፊ አናን፣ የታንዛኒያው የቀድሞ መሪ ቤንጃሚን ማካፓ እና የኔልሰን ማንዴላ ባለቤትን የመሰሉ) የሀገሪቱን ጉዳይ ሌሎች እንዲፈተፍቱ በር ከፍቷል በሚል በአንዳንድ ተመራማሪዎች ወቀሳ ይቀርብባቸዋል።
ኢትዮጵያ በሀገራዊ ምክክር መድረክ
አርክቴክት ዮሐንስ ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት በብሔረ መንግሥት ግንባታ(Nation Building) ውስጥ ብታልፍም የዳበረ ሥርዓተ መንግሥት(State) ለመገንባት ግን እንዳልታደለች ይገልጻሉ። ብሔረ_መንግሥት(Nation) ስንል በረጅም ዘመናት ጉዞ የጋራ ማንነትን በመገንባት የተለየ የማኅበረሰብ ዕሴት አዳብረው፣ ለዘመናት እንደ ሀገር በጋራ አብሮ መኖር መቻልን ሲያመለክት፤ ሥርዓተ_መንግሥት(State) ስንል ደግሞ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ሀብትና ሥልጣን የሚመጡበት እና የሚወርዱበት የተረጋጋ፤ በሕግ የታወቀ እና የሚከበር መንገድ(ሥርዓት) መፍጠር ማለት ነው ይላሉ።
የተደላደለ ሥርዓተ መንግሥት መገንባት ያልቻሉ የሦስተኛው ዓለም ሀገራት ልዩ መታወቂያቸው የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ከግጭት አዙሪት መውጣት አለመቻላቸው እንደሆነ የሚናገሩት አርክቴክቱ፣ ኢትዮጵያ ከ1950ዎቹ ወዲህ የገጠሟትን የፖለቲካ ለውጥ እና የሥርዓተ መንግሥት ማሻሻያ ለማድረግ በር የሚከፍቱ እድሎች ማባከኗን ይግልጻሉ።
አሁን የገጠማት ምናልባትም የመጨረሻ ሊሆን ይችላል ሲሉ የሚገልጹት ሦስተኛው ዕድል እንዳይባክን በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ስክነት መምራት የወቅቱ አንገብጋቢ(Top Priority) ሀገራዊ አጀንዳችን ሊሆን ይገባል ሲሉም ያሳስባሉ። አያይዘውም 50 ዓመታት ያስቆጠረው እና ሲንከባለል የኖረው የዴሞክራሲያዊ መንግሥት ምሥረታ እውን የሚሆነው ትኩረቱን ያልተቋጨውን የሥርዓተ መንግሥት ግንባታ(State Building) ዳር ማድረስ ላይ አድርጎ በርካታ ሀገራዊ ጥያቄዎችን የሚመልስ በዕውቀት እና በብስለት የሚመራ የሰከነ ሀገራዊ ውይይት ማድረግ ሲቻል ብቻ መሆኑን ይገልጻሉ፡።
እንደ አርክቴክት ዮሐንስ ማብራሪያ የሥርዓተ መንግሥት ግንባታቸውን በቅጡ ላልጨረሱ፣ በግጭት እና በኢኮኖሚ ውድቀት አዙሪት ውስጥ ለሚማቅቁ ኢትዮጵያን ለመሰሉ ሀገሮች ሀገራዊ ውይይት ጥቅሙ ብዙ ነው። ውይይቶቹ የሚመልሷቸው በርካታ ዝርዝር ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆነው ቁልፍ የሚባሉ አራት ርዕሰ ጉዳዮች ግን ሊታለፉ የማይችሉ ናቸው። እነዚህም በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት ማረም፤ የፌዴራሉ መንግሥት አወቃቀር ላይ ስምምነት ላይ መድረስ፤ በሀገሪቱ ታሪክ እና ብሔራዊ ምልክቶች ላይ የጋራ መረዳት መያዝ፤ በታሪክ አጋጣሚ የነበረ ኢፍትሃዊነትን ማረም እና ወደፊት መፈታት የሚገባቸውን አጀንዳዎች ለይቶ በይደር ማቆየት ናቸው።
ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ ለሁሉም የሚሠራ ያለቀለት የሚባል ዓለምአቀፍ ፍኖተ ካርታ ባለመኖሩ ምክክሩ እንደየሀገሮቹ ታሪካዊ ዳራ
እና ነባራዊ ሁኔታ የሚዘጋጅ መሆኑን የሚገልጹት አርክቴክት ዮሐንስ፣ ቀደም ብለው ምክክሩን ካካሄዱ ሀገሮች ትምህርት መውሰድ ግን ሊዘነጋ የማይገባ ተግባር መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህ አንጻር የተለያዩ ሀገራት ያካሄዷቸውን ሀገራዊ ውይይቶች የፈተሹ ተመራማሪዎች ኢትዮጵያ ለምታካሂደው ሀገራዊ ምክክር ይጠቅማታል በሚል ያቀረቧቸው ናቸው ያሏቸውን ሰባት ምክረ ሀሳቦች እንደሚከተለው ይዘረዝራሉ።
1) በፖለቲካ ኃይሎች መካከል መተማመንን መፍጠር፤በሀገራዊ ምክክር ወቅት መተማመንን እንዲፈጠር የሀገራዊ ምክክሩን አጠቃላይ ሂደት ለሕዝብ ግልጽ ማድረግ፤ ሁሉንም ባለድርሻ ኃይሎች አካታች እንዲሆን ማድረግ እና ገለልተኛ እና ነጻ አወያዮችን(ኮሚሽነሮችን) መሰየም እንዲወሰዱ የሚመከሩ እርምጃዎች ናቸው።
2) ሀገራዊ ምክክሩን ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መጠበቅ፤ ሀገራዊ ውይይቶች እጅግ ከፍ ያሉ ሀገራዊ አጀንዳዎች የሚቀርቡባቸው እና የሁሉም ተሳታፊ ወገኖች ሀሳቦች የሚደመጡባቸው መድረኮች እንደመሆናቸው በመንግሥት፣ በገዢው ፓርቲም ሆነ ነፍጥ ባነሱ ኃይሎች ተጽእኖ ሥር መውደቅ የለባቸውም። በምንም ዓይነት የፖለቲካ ቡድን ጠባብ አጀንዳ ማስፈጸሚያ መሆን የለባቸውም። ይህንን መከላከል የሚቻለው የአወያዮቹን ተአማኒነት(integrity) በመጠበቅ እና የምክክሩ ማዕቀፍ(framework) ለሁሉም ግልጽ በማድረግ ነው።
3) ምክክሩን ከተለመዱ ማነቆዎች መጠበቅ፤
በተለያዩ ሀገራት የተካሄዱ ሀገራዊ ውይይቶች የተለመዱ ቅርቃሮች ውስጥ ስለሚዘፈቁ ወይ ይከሽፋሉ አልያም ወደፊት መራመድ ይሳናቸዋል። ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሀገራዊ ምክክር ከተለመዱ ፖለቲካዊ ቅርቃሮች ለመጠበቅ በፓርቲ ውግንና የሚጠረጠሩ አወያዮች እንዳይሰየሙ መጠንቀቅ፤ ቁልፍ ባለድርሻዎች ከምክክሩ እንዳይገለሉ መሥራት እና የውይይቶቹ ውጤት ምንም ይሁን ምን የሚወሰኑ ውሳኔዎችን በሙሉ ልብ ለመተግበር መስማማት ያሰፈልጋል።
4) የሥልጣን ወሰን እና የምክክር አጀንዳዎች ቅደም ተከተል ማስቀመጥ፤ ምክክሩ ከመጀመሩ አስቀድሞ የአወያዮቹም ሆነ የኮሚሽኑ የሥልጣን ወሰናቸው እንዲሁም የሚቀርቡት አጀንዳዎች ለሁሉም ተሳታፊዎች እና ባለድርሻዎች ግልጽ ተደርገው ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል።
5) ሚዛናዊ የሆነ ውክልናን እና ንቁ ተሳትፎን ማረጋገጥ፤ በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ እና የሚወከሉ ቁልፍ ልሂቃንን እና የብዙኀኑን ተወካዮች በጥንቃቄ ማመጣጠን ያሻል። ሚዛናዊ ውክልናን ለማሳካት ግልጽ የማወዳደሪያ መስፈርቶችን ይፋ ማድረግ እና ከባለድርሻዎች ጋር በመስፈርቶቹም ሆነ በአሰያየሙ ላይ ተገቢ ምክክሮችን ማካሄድ ይገ ባል።
6) ሀገራዊ ምክክሩን ከሌሎች ቁልፍ ሀገራዊ የፖለቲካ ሂደቶች ጋር ማሰናሰል፤ ሀገራዊ ምክክሩ በመከናወን ላይ ካሉ ሌሎች ሀገራዊ የፖለቲካ ሂደቶች ጋር ማሰናሰል ካልተቻለ የሚና መደበላለቅ እና የውሳኔዎች መዘባረቅ ይፈጠራል። በኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ አንጻር ሲመዘን ሀገራዊ ምክክሩን ከማንነት እና የወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን ሥራዎች እና ከእርቀ ሰላም ኮሚሽን ሥራዎች ጋር ማሰናሰል ያስፈልጋል። ይህም ማለት አንዱ የሠራውን አንዱ እንዳያፈርሰው፣ አንዱ የዘጋውን አጀንዳ አንዱ እንዳይከፍተው እየተናበቡ እንዲሠሩ ማስቻል ነው።
7) የምክክሩን ውጤት የአፈጻጸም መርኅ እና እቅድ አስቀድሞ ማዘጋጀት፤ የሀገራዊ ምክክሩ ቁልፍ ውሳኔዎች የሀገሪቱ አዋጆች፣ ፖሊሲዎች እና የማስፈጸሚያ ስትራቴጂዎች አካል እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል። ይህንንም ለመከወን እንዲቻል የሀገራዊ ምክክሩን ውሳኔዎች ተከታትሎ ለማስፈጸም ኃላፊነት የሚረከብ ከተጠያቂነት ጋር ሙሉ ሥልጣን የሚሰጠው ተቋምን አስቀድሞ ማሰብ እና ማቋቋም ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ የምታካሂደው ሀገራዊ ውይይት በአዋጁ እንደተገለፀው ከሚወስደው ጊዜ እና አሳታፊነት አንፃር ሰፊ እና የረጅም ጊዜ አላማ ይዞ የሚሄድ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ መስፍን በበኩላቸው ሀገራዊ ውይይቱ የተሳካ እንዲሆን ወይንም እንዲከሽፍ የሚያደርጉ አውዳዊ(contextual) እና የሂደት(process) ጉዳዮች አሉ ይላሉ።
እንደ አቶ መስፍን ገለጻ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች አተኩረው ከሚያነሱዋቸው የብሔራዊ ምክክር የስኬት እና የውድቀት አውዳዊ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የሕዝብ ድጋፍ ቁልፍ ጉዳይ ነው። ምክክሮች በረዘሙ ቁጥር ደግሞ የሕዝብ ድጋፍም እየቀነሰ ተቀባይነትም እያጣ የመሄድ እድሉ ይጨምራል። ስለዚህም የማኅበረሰቡን ድጋፍ መጠበቅ ያስፈልጋል።
ሁለተኛው የሊሂቃን ድጋፍ ወይም ተቃውሞ ነው። ሊሂቃን በማህበረሰብ ውስጥ ከቀሪው ማህበረሰብ ጋር ሲነፃፀር ተመጣጣኝ ያልሆነ(Disproportionate) ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉልበት እና አቅም ያላቸው ቡድኖችን የሚወክሉ ናቸው። እንደነዚህ አይነት ቡድኖች ሀገራዊ ምክክር ወደ ስምምነት እንዲደርስ እና እንዲፈፀም የማድረግ ወይንም የማደናቀፍ አቅም አላቸው። ይህ ሚናቸውም በሁሉም ምክክሩ ደረጃዎች ሊተገበር የሚችል እንዲሁም ከምክክሩ በኋላ ሳይቀር ውሳኔዎችን የማስቀልበስ አቅም ያለው ነው። ስለዚህም ከእነዚህ ቡድኖች ፍጹም ባይሆንም ቢያንስ ሂደቱን ከመሰናከል በሚጠብቅ ደረጃ ቅቡልነትን ማግኘት ይገባል።
ሶስተኛው የቀጠናዊ እና የዓለማቀፍ ማኅበረሰብ አካላት ናቸው። እነዚህ አካላት በቀጥታም ሆነ በውክልና(በተዘዋዋሪ) በምክክሩ ላይ ተፅዕኖ ሊያደርሱ ይችላሉ። ከቀደሙ አወቃቀሮች እና ግንኙነቶች ጥቅም የሚያገኙ አካላትም ለለውጦች እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ። በተቻለ መጠን የእነዚህንም ትብብር ማግኘት ተገቢ ይሆናል።
አራተኛው የምክክር ባህል መዳበር ወይም አለመዳበር ነው። በምክክር ግጭትን የመፍታት ባህል፣ ምክክርን የማመቻቸት ክህሎት፣ የማደራደርና የማሸማገል ልማዶች ወደ ስምምነት ለማድረስ ከሚያግዙ ወይንም ከሚያደናቅፉ ጉዳዮች ውስጥ ይካተታሉ። የቀደሙ የድርድር እና ምክክር ተሞክሮዎች ደግሞ ካለፉ ስህተቶች ትምህርቶች ተወስደው እንዳይደገሙ ሊረዱ ይችላሉ።
በአምስተኛ ደረጃ የሚጠቀሱት በምክክር ወቅት የሚኖሩ ግጭቶችና ብጥብጦች ናቸው። ግጭቶችና ብጥብጦች ስምምነት ላይ መድረስን እና የትግበራ ሂደትን ሊገድቡ ይችላሉ። ነገርግን አቶ መስፍን በእነዚህም ወቅቶች የተከናወኑ ምክክሮች በርካታ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።
ከምክክሩ የሂደት ጉዳዮች አንፃር ደግሞ በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች መኖራቸውን የሚጠቁሙት አቶ መስፍን፣ የተሳታፊዎች ምርጫ፣ ቁጥር እና ወካይነት ተአማኒ እንዲሁም ተቀባይነትን የሚጨምር መሆን አለመሆኑ፤ የውሳኔ አሰጣጥ መንገዱ አሳታፊ፣ ግልፅ እና ተቀባይነት ያለው መሆንና አለመሆኑ፤ የአመቻቾች እና የሸምጋዮች ምርጫ ገለልተኝነት፣ ቅቡልነት ያለው መሆንና አለመሆኑ፤ የምክክሩ ጊዜ ርዝመት ወይንም እጥረት ስምምነት መድረስ ላይ ተፅዕኖ ባይኖረውም ጥናቶች እንደሚያሳዩት ምክክሮች በረዘሙ ቁጥር ተፈፃሚነታቸው እየቀነሰ ይሄዳል። የድጋፍ መዋቅሮች መኖርና አለመኖራቸው እንዲሁም በምክክሩ ውስጥ የሚፈጠሩ ጥምረቶችም ምክክሩን ሊያሳኩ ወይንም ሊያደናቅፉ የሚችሉበት ዕድል አለ። ስለዚህም እነዚህን አውዳዊ እና የሂደት ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት አገራችን ለጀመረችው ምክክር መሥራት ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ።
የቱኒዚያው ምክክር መቀመጫ ላይ አንድ የምክክሩ ተሳታፊና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ከስምምነት በኋላ አፍጥጦ ስለሚጠብቃቸው የኢኮኖሚ ፈተና ለመናገር “ምክክሩ ቱኒዚያን ከቅዠት(Night mare) አዳናት እንጂ አዲስ ህልም አልሰጣትም̋” ሲሉ መደመጣቸውን የሚያስታውሱት አቶ መስፍን ኢትዮጵያውያንም ምክክሩ ሁሉንም ችግሮቻችንን በአንዴ ይፈታል ብለን ከመጠበቅ ተቆጥበን፣ ለዘመናት ካለንበት የግጭት አዙሪት ሊያወጣን እንደሚችል እንደአንድ ወሳኝ መሳሪያ ልንገነዘበው ይገባል። ምክክር፣ ንግግር፣ ድርድር፣ እና ሽምግልና ብቸኞቹ የግጭት መፍቻ መንገዶቻችን እንዲሆኑ ተባብረን እንትጋ በማለት ሃሳባቸውን ያጠቃልላሉ።
ተስፋ ፈሩ
ዘመን መጽሄት ግንቦት 2014 ዓ.ም