የህዝብ ፍላጎት ቅድሚያ ይሠጠው!

 ከእለታት አንድ ቀን ሶስት ጎረቤታሞች በጣም ጥሩና የሚያምር በሬ ያዩና ይወዱታል፤ ብር ስላልነበራቸው ከገዛን በኋላ እንከፍላለን ይሉና በዱቤ ይገዙና ያርዱታል። በሬው ከታረደ በኋላ ግን፣ ሶስቱም በሬው ይመለስ አንፈልግም ይላሉ። እነዚህ ሰዎች በሬው ከታረደ በኋላ አንፈልግም ያሉበት ምክንያት፡-

አንደኛው በሬውን የፈለገው ቆዳው ለአንድ ሌሎቹ ለማያውቁት ዓላማ ስለነበረና የበሬው ቆዳ ከበሬው ዋጋ ስለሚበልጥ ነበር። ነገር ግን ከታረደ በኋላ ቆዳው ብዙ ቦታ ስለተበሳሳና እንደፈለገው ስላልሆነለት በሬውን አልፈልግም አለ። ሁለተኛው አካባቢው ላይ ያሉ ከብቶች ሆዳቸው ውስጥ ወርቅ ይገኛል የሚል ነገር ስለሰማ ወርቅ አገኛለሁ ብሎ ጠብቆ ነበር። ነገር ግን በሬው ሆድ ውስጥ ምንም ዓይነት ወርቅ ስላልነበረ በሬውን አልፈለገም። ሶስተኛው ደግሞ የበሬው ጉበት ለአንድ ክፉኛ ለታመመ ሰው ፈውስ ይሆናል ብሎ ቋምጦ የነበረ ቢሆንም በሬው ሲታረድ ጉበቱ የተበላሸ ስለነበር በሬውን አልፈለገም።

ሶስቱም ፍላጎታቸው ስላልተሟላ “በሬውን አንፈልግም፤ ይመለስ” አሉ። ነገር ግን በሬው አንዴ ታርዷልና ወደኋላ መመለስ ስለማይችል ከበሬው ሻጭ ጋር ጭቅጭቅ ውስጥ ገቡ። ከሶስቱም ፍላጎት ውጪ የነበረው የበሬው ስጋ ግን ሲታይ እዛ ሀገር ታይቶ የማያውቅ ቆንጆ ስጋ ነበር። ይህንን ቆንጆ ስጋ አካፍለው ሰዎች ስጋውን እንዲበሉ ማድረግ ይችሉ የነበረ ቢሆንም ይህን ማሰብ አልቻሉም። የእነዚህ ሶስት ሰዎች ቤተሰቦች ሲጠየቁ፣ ስለ ቆዳውም፣ በሬው ሆድ ውስጥ ይገኛል ስለተባለው ወርቅም ሆነ ስለጉበቱ ጉዳያቸው አልነበረም። ልክ በሬውን ታርዶ ሲያዩት ፍላታቸው ያረፈው ስጋው ላይ ነበር።

ከዚህ ምሳሌ የምንረዳው አንዳንድ ጊዜ ህዝቡ የሚፈልገው ነገር እኛ የምንፈልገውን ላይሆን ይችላል። የኛ ቆዳ፣ ወርቅና ጉበት ለህዝቡ ሰላም ካላመጣለት ትርጉም የለውምና ከፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል የህዝቡን የልብ ትርታ ማዳመጥ፣ ፍላጎቱን ማወቅና ማክበር፣ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ሀላፊነት አለባቸው። የህዝብ ፍላጎት፣ ሀገሩ የተረጋጋች ሆና፣ ከሀገሩ ሳይሰደድ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተጠብቆ ሠላማዊ ኑሮን መኖር ነው። በመሆኑም ፖለቲከኞች ለሕዝቡ ፍላጎትና ለሠላም ቅድሚያ መስጠት አለባቸው።

የህዝብ ፍላጎትን በመንተራስ ረጋ ብሎ በማሰብ “እንወያይ፤ እንምከር” የሚሉ ግብዣዎችን መጠቀም ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም። ህዝቡ ምን ትፈልጋለህ ቢባል የሚያስቀድመው ሠላሙን ነው። በመሆኑም ፖለቲከኞች የምክክር መድረኩን ለህዝብ ፍላጎት መተግበሪያና ሰላሙን ማስጠበቂያ አንዱ ስልት አድርገው መውሰድ ተገቢ ነው። የምክክር መድረኩም የመጨረሻ ግብ የሕግ የበላይነትን ማስከበርና ለሀገራችን ሠላም ማስገኘት በመሆኑም ምክክሩን በቅንነት በመከወን የህዝብ ፍላጎትን ሊያስቀድሙ ይገባል !

ዘመን መጽሄት ግንቦት  2014 ዓ.ም

Recommended For You